መቼ ልምጣ እና ልይሽ?
መቼ ልምጣ እና ልይሽ?
***
ከሥርጉተ © ሥላሴ 30.06.2018
(ከኮሽ አይሏ እናት ሲዊዝ።)
„የከበረውን ስሜን የወደዱትን ሰዎችንም በበራ
ብርሃን ከገሃነም አወታቸዋለሁ።“
(መጽሐፈ ሄኖክ ምዕራፍ ፵፪ ቁጥር ፲፫)
መቼ ልምጣ እና ልይሽ ?
ዕንባዬን እንድታብሽ፣
አካሌን እንድትዳስሽ
በእምነቱ እንድትደባብሽ።
ናፍቆኛል እና እጅሽ
የጎረስኩበት ማዕድሽ
የአደኩበት ጓዳሽ
የፏለልኩበት ሜዳሽ
የዘለልኩበት መስክሽ
የሮጥኩበት ዓውድሽ።
መቼ ልምጣ እና ልይሽ?
ዕንባዬን እንድታብሽ
አካሌን እንድትዳስሽ፣
በእምነቱ እንድትደባብሽ።
የሳቅኩበት አድባርሽ
የአሥራ ሦስት ወራት ብርሃንሽ፣
ሀሁ ... ያልኩበት ገበታሽ
የዕውቀት ሸማ ሻሽ-ሽሽ፣
የቤተዘመዱ ውሎሽ
የአንችነትሽን - አዋዋልሽ።
መቼ ልምጣ እና ልይሽ?
ዕንባዬን እንድታብሽ
አካሌን እንድትዳስሽ
በእምነቱ እንድትደባብሽ።
ተፈጠሮዊው ልማድሽ
የፍቅር ጎለጎታሽ፣
የወግ - የትውፊት፣ ህግሽ
አስርቱ ቃላት መንበርሽ
ያልተፃፉትም ቤትሽ
ጠረንሽ ልዩ ማእዛሽ።
መቼ ልምጣ እና ልይሽ?
ዕንባዬን እንድታብሽ፣
አካሌን እንድትዳስሺ
በዕምነቱ እንድትደባብሽ።
ሁለመናሽ ሥርዓት
ተመግቦት ፍቅርሽ፣
ለዛሽ ያማረ ህብርሽ
ሙሉ ወርድ ነው ጌጥሽ
አብሮነት ነው ቀሚስሽ
እጀ ጠባብ ነው ውበትሽ።
መቼ ለምጣ እና ልይሽ?
ዕንባዬን እንድታብሽ
አካሌን እንድትዳስሽ
በእምነቱ እንድትደባብሽ።
ጉርሻው ያማረ ግብርሽ
ዕፁብ ድንቅ ነው ምግባርሽ፣
ትብሽ-ትብሽ፤ ነው መረብሽ
መተሳሰብ፤ መረዳዳት ካባሽ።
መከባበር ... መቅድመ-ጎልትሽ
ሰላም ነበር - የመምሬ አድባርሽ።
መቼ ልምጣ እና ልይሽ?
ዕንብዬን እንድታብሽ
አካሌን እንድትዳስሽ
በእምነቱ እንድትደባብሽ።
ፆም ፀሎት ቢሆን አልተለዬሽ
ቅድስና ግሱ ቤትሽ
ስግደት ቢሆን ሕይወትሽ
ማን እንደ አንቺ ! ወደር የለሽ።
ሱባዬ ነው ምርኩዝሽ
ሰዓታትም ግጥምሽ
ማህሌትም ሰዋሰዋዊ ንጥርሽ።
መቼ ልምጣ እና ልይሽ?
ዕንባዬን እንድታብሽ
አካሌን እንድትዳስሽ
በእምነቱ እንድትደባብሽ።
የዜማ የቅኔ አክሊልሽ
ንባብ የድጓ ብር አንባርሽ።
የሺህ ዘመናት ነዶ-ሽሽ
ከሁሉ ’ሚልቅ ታሪክሽ።
አብነት አለው ሰነድሽ
ልዩ ማውጫ አለው ቀንድነትሽ
የአፍሪካዊነት ሃብልሽ።
መቼ ልምጣ እና ልይሽ?
ዕንባዬን እንዳትብሽ
አካሌን እንድትዳስሽ
በእምነቱ እንድትደባብሽ።
የአዶሊስ እመቤት ውብ ነሽ
የዓለም ድልድይ ዘርሽ።
ሳባ ነበረች አገናኝሽ
የወርቅ ማዕጠንት ሲሳይሽ
የጸጋ ስጦታ ልጅሽ።
ንግስት እሌኒም አረሳችሽ
የታምር ጉዝጓዝ ቋጨችልሽ።
መቼ ልምጣ እና ልይሽ?
ዕንብዬን እንድታብሽ
አካሌን እንድትዳስሽ
በእምነቱ እንድትደባብሽ።
ጃንደረባውም አልረሳሽ
ሰባ ሰገልም አካልሽ …
ለመዳህኒትሽን ሰገደልሽ
ልደትሽን ዓወጀልሽ።
በዓለም ታሪክ የተባ
ንጉስ ክህነትን አበራ!
ያ ... ላሊበላ ቅዱስ …
የእምነት ጋሻ መወድስ።
በኸረ ዛጉኤ ኢዛና
የዕልፍ ዘመናት ገናና!
ፋሲል መሃንዲስ ትጉህ
በፈጠራህ፤ ዛሬም ከበርንልህ።
መቼ ልምጣ እና ልይሽ?
ዕንባዬን እንድታብሽ
አካሌን እንድትዳስሽ
በእምነቱ እንድትደባብሽ።
· ሥጦታ ..
የእናት ሐገራችን ፍቅር እረፍት ላሳጠቸው ወገኖቼ ሁሉ ይሁንልኝ።
ህዳር 26 ቀን 2001 ዓ.ም ዙሪክ አውሮፕላን ማረፊያ ሲዊዘርላንድ፤
· እንደ አወሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2010 ተስፋ መጸሐፌ ላይ ለህትምት የበቃ ነው መደቡ ገጽ 19 - 21 ነው።
ቅኖቹ የኔዎቹ ናፍቆቶቼ እንዲህ ሆነላችሁ ...
· ይህን ጹሑፍ የጻፍኩት ደግሞ ክፉዎች የወያኔ ሃርነት ማንፌስቶ ማህበርተኞች 8 ዓመት የኖርኩበትን ቤቴን አስለቅቀው ለህየውቴ አስጊ ስለነበር ሆቴል እስኪገኝልኝ ድረስ ከጓደኞቼ ቤት ነበርኩኝ። ዙሪክ አውሮፕላን ማረፊያ የ24 ሰዓት አገልግሎት ይሰጥ ስለነበር ተርሚናል ላይ ማስተወሻ ደብተር ገዝዘቼ ምግቤንም መጠጤንም አሰናድቼ እዛው አድሬ ከጻፍኳቸው 38 ግጥሞች ውስጥ አንዱ ነው።
· እጅግ ታሪካዊ ግጥም ነው። ያን ቀን ውስጤ እያለቀስ የጻፍኩት ከመሆኑ በላይ በዛ ህውከት ሰሞን ግን በተረጋጋ መንፈስ ምን ያህል የፈጣሪ መክሊትን ማንም ሊገድበው የማይችል ስለመሆኑ፤ ፈተና እና ወጀብ እዮራዊ ጸጋን ገድቦ የማስቀረት አቅም እንደሌለው ይልቁንም ፈጣሪ በማያለቅ፤ በማይመረመር ሚስጢሩ የውስጥን ሰላም የሚጠብቅበት የሚያጸናበት ረድኤት ያለው ስለመሆኑ የተመሳጠረበት ታላቅ የተጋድሎ ግጥም ነው። እዬት፤ ገምግሙት። በድምጽ የተሠራም አለ። ፋይል ስለሚበዛብኝ አንድ ቀን እለጥፈዋለሁኝ። አንዲትም የፊደል የቃል ማስተካከያ አላድርግበትም። ምክንያቱም መጸሐፍ ላይ ያለ ከመሆኑም በላይ ስዕላዊነቱን ተጽዕኖ ስለሚያሰድርበት።
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።
እልፍ ነን እና እልፍነታችን እልፍ እናድርጋው!
ቅኖቹ ናፍቆቶቼ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ