ዘቢቤ የነባቢቴ ቃናዬ!
ዘቢቤ
***
„የወርቅ እንኮይ በብር ፃህል ላይ የጊዜው ቃል እንዲሁ“
(ምሳሌ መጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ ፳፭ ቁጥር ፲፩)
ከሥርጉተ ሥላሴ
14.07.2018
(ከገዳማዊቷ ሲዊዘርላንድ።)
ሽው አልሽኝ ... ሽው፣ ከአፈሬ ጋር
ትዝ አልሽኝ ... ትዝ፣ ከመዝሙሬ ጋር።
አንች ወ/ሮ እሜቴ
የብሩህ ራዕይ ጉልላቴ
የወልዮሽ ማዕዶቴ።
የእኔ ወዳጄ፣
እንዳት-ወጭብኝ ከእጄ
ልማጸንሽ ይሆን ጀግንነትን ሰድጄ?!
ዘ ተስፋዬ ነሽ ፍጹም ገዴ
ቢ የመልካም ዜማ ነዶዬ
ቤ ተፈጥሮዬ ነሽ ልዩ ዘወዴ።
መሸብያዬ የዓምዴ
የምህረት ዝናር ዬዓውዴ
የህልውናዬ ቀና መንገዴ።
ሽው አልሽኝ ... ሽው፣ ከመንደሬ ጋር
ትዝ አልሽኝ ... ትዝ፣ ከመዝሙሬ ጋር።
የምንጊዜም ልዕልቴ
የጫጉላ ጊዜ ስስቴ
የዕድሜ ልክ ክታብ ህብስቴ
ፍቅረ ዕድምታ መስታውቴ።
ዘ
ቢ የአዝምራ ማሳ ማዕዶቴ
ቤ ሙቀተ-ማህጸን የዕትብቴ
ወላንሳዬ የእኔነቴ
ተቋሜ።
የብርታት ምንጭ ፅናቴ፣
ፍቱነ-ዕሴት አበረንታቴ
የቃና ቅኝት መቀነቴ።
ሽው አልሽኝ ... ሽው፣ ከሉዓላዊነቴ ጋር
ትዝ አልሽኝ ... ትዝ፣ ከመዝሙሬ ጋር።
የታሪክ አድባር መንፈሰ-ስንቄ
የውስጥነት ማውጫ መዝገቤ
የልቤ ክናድ ደሜ።
የናፍቆት አንጀት ዘቤ
የትውፊት መለኪያ ሚዛኔ
የተክሊል ቁርባን ዘቢቤ።
ማህደሬ!!
የጀግንነት አርማዬ ...
የልምላሜ ዋዜማዬ፤
የደፋርነት ዓውድማዬ ...
ዘ የአሻፈረኝ ዜማዬ፤
ቢ የአልገዛም ባይነት ዋናዬ።*
ቤ
ዓላማሽ መጠነ ሰፊ፣ ጥልቅ
የሰማንያ ህብረ - ብሄር ብርቅ።
መቻቻልን አፍልቅ!
የፓን አፍሪካ ቀደምት!
ቅኝ ግዛትን ሰልቅ!
ባርነትን ዘቅዝቅ!
ሽው አልሽኝ ... ሽው፣ ከድንበሬ ጋር
ትዝ አልሽኝ ... ትዝ፣ ከመዝሙሬ ጋር።
የበቃኝ ቋት ሰንደቅ
የነፃነት ጎህ ስንቅ
የአርነት ደወል ብርቅ።
ከቶ አይደለሽም ጨርቅ
ሉዐላዊነትን አልቅ!
የሺህ ዘመናት ዕንቁ ወርቅ።
ዘ የኩሩ ህዝብ መረቅ
ቢ ጎጠኝነትን አወላልቅ
ቤ ኢትዮጵያዊነትን አዝልቅ!
ዝናሽ ! ከተመ እስከ እዮር
ባለ ሦስት አግድም ሚስጢራዊ ቀመር።
የውል፣ የኪዳን ... ቀለበት
የቆራጥነት ህብስት
የተባሽ የአህድዮሽ ወተት
የማትነጥፊ ሙሉ ጋት
የእናት መቀነት ሊቅ ኣናት።
ሽው አልሽኝ ... ሽው፣ ከአፈሬ ጋር
ትዝ አልሽኝ ... ትዝ፣ ከመዝሙሬ ጋር።
አበባዬ ነሽ ጌጤ፣ የእኔ ውዳሴ
መንፈሰ - አራሽ፣ ዜና ፈውሴ
ህሊናዊ - ጥርኝ፣ ልብሴ
ነሽ ነፍሴ ...
ዕንባ አብሴ።
ነሽ ነፍሴ ...
ሆደ - ባሻነትን ገርስሴ
ነሽ ነፍሴ ...
ሐገራዊነትን፤ ብሄራዊነትን አጉርሴ።
አንች ...
አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ኽብር
የመተሳሰብ ገብያ ግብር።
የጥቁርነት አድባር ፈር፤
ፍሬሽ ያማረ ምርጥ ዘር
የአንበሳ ግርማ ሥር፤
ምግባረ መልካም ገር።
ድል አብሳሪ፣ አድሪ
የመለያችን ዓዋጅ፣ ነጋሪ
የቀደምቶቹ አደራን አብሪ!
የአንድነታችን በር
ዬትውፊታችን ጽኑ ድር፤
ሚሥጥረ-ሰብን፣ በአንድምታ አንጥር።
ሽው አልሽኝ ... ሽው፣ ከሐገሬ ጋር
ትዝ አልሽኝ ... ትዝ፣ ከመዝሙሬ ጋር።
ሥወር አይደለሽ ነሽ ግልጽ
የብዙሀኑነ-መዋለ፤ - ጥበብ ድምፅ፣
ታማኝነትን አንፅ!
የውስጣችን-ውስጥ ማዕረገ - ዘብ
የንቦች ቤተ - ህገ - ግንብ።
...እንደ ወትሮሽ ... በይ እሙ እንደወትሯችን-እንደወትሮሽ
በአንችነታችን አሰባስቢን
የጨው ዘር እንዳንሆን ሠራዊቶችሽ።
በእጅሽ እኮ ነው መንሹ ...
አባክሽን - እባክሽን - እባክሽን...
ክብራችነን አፍነሽንሽው።
ስደትን በክርኒ ለውሽው።
ከወንበሩ አውርጅ እና ከስክሸው።
ግርማዬ ነሽ ክብሬ ...
የእኔ ባንዴራዬ ...
የሀሴት ሲናዬ ....
የነባቢቴ ቃናዬ!
· መታሰቢያነቱ፣ ለሐገር ለሉዐላዊነት ሲዋደቁ ለተሰዉ ጀግኖች በሙሉ ይሁንልኝ።
· ሄርሽን ሆቴል ሲዊዘርላንድ ታህሳስ 12 ቀን 2001 ዓ.ም
· ተስፋ መጸሐፌ ላይ ለህትምት የበቃ።
የማከብራችሁ ቅኖቹ ... እጅግ በጣም የምወደው ግጥም ነው በጸጋዬ ራዲዮ እጅግ ለበዛ ጊዜ አዬር ላይ አቅርቤዋለሁኝ። እጅግ በከፋኝ ቀን ግን ፍጹም የሆነ ጽናትን ያጎናጸፈኝ ግጥም ነው።
ነገረ የፍቅራዊነት ጉብኝቱን የኤርትራን ሉዑክ በሰላም አስጀምሮ
በሰላም አስጨርሶ ለባዕታቸው ያብቃልን። አሜን። አኔ ፈሪ ነኝ።
ኑሩልኝ የኔዎቹ።
መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ