እናላችሁ ... ስለ አቶ መላኩ ፈንታ/ ቴ

ሚዛናዊ ሆነ የማዬት ተደሞ።
„የሰው ልብ መንገድን ያዘጋጃል፤ እግዛበሄር ግን አካሄዱን ያቃናለታል።“
ምሳሌ ምዕራፍ ፲፮ ቁጥር ፱
ከሥርጉተ©ሥላሴ
02.10.2018
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።




  • ·       መነሻ።

„አቶ መላኩ ፈንታ የአቶ በረከት ስምኦንን ሚስጢ ዘረገፉት“
  • ·        ቅድመ ተደሞ።

ዛሬ ፏ ብሏል። ፏ ብሏል ስላችሁ ግን ልዕልተይ ተገኝታለች ማለቴ አይደለም። እሷ የለችም። ፊታውራሪ የሰማይ መስኮትም በበቀኝ ዛሬ ቀና ሆኗል። ካፌያ ነገረሩንስ ሳይቀር ተቆጠብ ብሎ ደንግጓል እንደማለት። ኮነሬል ዳመናም እስቲ ይሁናችሁ ብሏል። ስለሆነም አዬሩ የሚመች ብርሃን ያለበት ብራ ሆኗል እላችሁአለሁኝ። ግን እንዴት ናችሁ የኔዎቹ ውዶቹ ነፍሶቹ? ደህና አላችሁልኝ ወይ?

ኢትዮጵያዊነት እኔን መጨመረ አለበት - እናንተንም። እኔን መጨመር ያልቻለ ኢትዮጵያዊነት፤ እናንተንም መጨመር ያልቻለ እትዮጵያዊነት በአፍንጫዬ ይውጣ ትላላች ሥርጉትሻ። ስንቱን ነገር እምቅ አድርጋ ተሸክማ መኖሯን እሷና እና ጥቂት ቅን ወገኖቿ ያውቁታል እና።

እራሱ አካሉን፤ ስደተኛ ወገኑን፤ ጤና ያጠውን ወገኑን ሰርዞ፤ ሲያስድድ የነበረው ሁሉ ተቆጥሮ ነው ኢትዮጵያዊነት የሚበለው። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የወገንን ሰብዕና ምሶ ሲቀብር የኖረው፤ አጋጣሚውን ሲያገኝ ከራሱ ክብር እና ዝና በስተቀር፤ የሌላውን ውስጣዊ፤ ማህበራዊ ሰላም ሲጨምቅ የኖረው ሁሉ ልሙጡን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ስለለበስ ለሥርጉተ የታይታ እንቆቅልሽ ነው - ነገረ ተረብ። 

ኢትዮጵያዊነት አስተዋይነት ነው። ኢትዮጵያዊነትም ሚዛናዊነትም ነው። መጀመሪያ ስደተኛ ወገንህ አክብር አቅርብ አቅርብ ... ይህ ሰብዕዊነትም ነው። ከቅርብህ ያለውን የተከፋን ዕንባ አባሽነት ነው ሰውነት ባለህሊናነት - ለእኔ። ሰላምታ የእግዚሩ ማንም ያጎድላል?! 

ማስተዋል በዜግነት ትርጉም -ተተሆነ እንደ ማለት። ጭብጨባ፤ አጀብ ኢትዮጵያዊነትን አይገልጸውም። ኢትዮጰውያዊነት ውስጥነት በምግባርነት ነው። በመንፈስ እግር ብረት አካልህን አሰረህ/ አሳስረህም፤ አሳደህ፤ ገደብ አስጥለህም ሰንድቅ መልበስ ለእኔ ቧልት ነው። 

ይቅርታውም የእዮር ነው፤ ቢያንስ እዮራዊ ዳኛ አለ ማለት ይገባል። ይቅርታ ልባዊነትን ይጠይቃል እንጂ ዘመንን ደጅ አይጠናም። ስለምትሰማው ነገር ማንዘርዘሪያ፤ ማገናዘቢያ ዐዕምሮ ከነሳህ፤ ከሌለህ፤ ነግ  በእኔ ማለት ካቀትህ አንተ ከህሊናዬ ጋር ኖርኩኝ ለማለት መደፈርህ በውነቱ መተላላፍ ነው ለዛውም የተፈጥሮን ህግን!  „ተናግሮ ካናጋሪ አድነኝ“ ይሉ ጎንደሬዎቹ ሲተርቱ … ተረብ እዬበዛ እዬተባራከት ሲመጣ ኡኡ! የሎሬቱ ያለህ! በህግ አማላክ! እንላለን … 
ለመነሻ ይህን ካልኩኝ ዘንዳ ወደ ጭብጤ … ውዶቼ
  • ·        ሽት እና ሁነት።

ትናንት ምሽት ላይ አንድ ቃለ ምልልስ ተልጥፎ አዬሁኝ። እኩለ ሌሊት ስለሆነ ተዚህ ተሲዊዚና አይፈቀድም። ከምሽቱ አራት ሰዓት ወይንም በአገሬው የሰዓት አቆጣጠር ተ22 ሰዓት በኋዋላ ማዕቀብ አለ። ህግ መተላላፍ ደግሞ ሥርጉትሻ አትሻውም። መቆጠብ ያስከብራል። ያው የጦቢያስ አንባሳደር አይደለሁምን እንደ አቅሚቲ ... ከትክት ... ቁጢጥ አልኩኝ አይደል? "ለራስ ሲቆርሱ" እንዲሉ፤

አልኳችሁ በይደርልኝ ቀጥሬ በጥዋቱ ያው ከተለመደው ከሰንበት ድርሳን ጋራ ተገናኝቼ ሳበቃላችሁ እስቲ ምን እና ምን እዬተባል ነው ብዬ አንኳኳሁኝ፤ የተባረከው የአብርሃሙ ቤት አጤ ጉግል „ቤት  ለእንግዳ፤“ መጣሽልኝ እቴዋዬ አለኝ እና የአቶ መላኩን ፈንታን ቃለ ምልልሱን አዳመጥኩኝ፤ ያው እኔ ጣም ካኝ ድግም አደርጌ ነው የማዳምጣው። ጣሜ ሆነን ተደገመ።

ታዲያንላችሁ ሆ! የሚል ዲሞ ቢጤ ከወደ ጓዳ ብቅ አለ ጫጫታ በረከተ ...  "ያው እንደ ስንቅ ያዳመጥሸውን ቆጣጥሬሪና ጓዳ ጉድጉድ በይ እንጂ" ብሎ አቤቱታ ሲያሰማ ተመንደረ ማጀት እስቲ አንተስ ማን አለህ ካለ እኔ ጠረን አልኩኝ እና ተዛ ተቆያዬን። ያው አኗኗሪዬ ስለሆነ ትኩረት አነስ ስትልበት ዲሞው የተለመደ ነው፤ ደግሞ በሰንበት ዲሞ ግን ይደብራል ….

እናላችሁ አሁን ጣጣዬን ጨራርሼ እንደ ወትሮው ቢሆን ኢትዮ ሚዲያ ላይ ሚዛንን ስለሚያስጠብቅልኝ ስክነት እዛ ነበር። አሁን ወር አለፋቸው ጥፍት ካሉ? ቢኖሩ መልካም ነበር። ስለሆነም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰንበት ትንሽ ፋታ ተገኜ እላችሁለሁኝ። ደንበኛ ሲጣፈ፤ ለነገሩ ሰሞኑን ውዴ ሳተናው ድህረ ገጽም የለም… በደህናው ይሆን? እሱ ሲጠፋ ጭንቅ  ለኛል፤ ለነገሩ አገር ምድሩ ነው ጭር የሚለው የአብርሃሙ ቤት ስለሆነ ... 
  • ·        ናላችሁ …

ውይ! አዬ የእኔ ነገር … „እናላችሁን“ ደግምኩትን „እናላችሁ“ እም! ተሰለሰ እንጂ ብቻ ቃለ ምልልሱን ከልቤ ሆኜ አዳመጥኩኝ። አቶ መላኩ ፈንታ/ ቴ የተፈቱ ሰሞን የኢሳቱ ጋዜጠኛ አቶ ደረጀ ሃብተወልድ ስለምን የጎንደር ህዝብ ሸለማቸው ብሎ አካኪ ዘራፍ ብሎ ነበር። መቼም የቅናቱ መጠን ልክ አጣ። ምን ዶለህ? ቢበላ ምን ሊል እንደሆን አይታወቅም። ቤሲቲ አዋጣ፤ በአቀባባሉ ላይ ተገኝ አልተባለ እሱ … ወይንም ዘግብልኝ ተብሎ ማመልካቻ አልተላከለት … ዛሬ እድሜ ለፌስ ቡክ እቴ ማን ደጅ ይጠናል … ተመስገን እኩል ተኩል ተሆነ ... 

ብቻ ሥጦታ ሰጪውም አክባሪውም ህዝብ ነው። እንዲያውም መቼም የአመል ሆኖባቸው እዛም እዚህም ጥልቅ ማለት ለምዶባቸዋል፤ ካቦታው ሲሆን ጥልቆነት ሲሆን ግን ያጥለቀልቃል። የሆነ ሆነ እኔ ስለ አቶ መላኩ ፈንታ ብዙም እውቀት ስሌለኝ ምንም አላልኩኝም ነበር። እዮባዊነት ታዋጣለች። 

ዶር አብይ አህመድ ወደፊት ሲመጡ አደብን፤ እዮባዊነትን ገንዘብ አድርጉ ስል ሰሚ ጠፋ፤ አሁን ደግሞ የሚታዬው እዬታዬ ነው። ሥርጉትሻ እና ገዳማዊቷ አገር ሲዊዚሻም ሁሉንም በፈርጅ በፈርጁ እዬታዘቡ ይገኛሉ፤ አልፎ አልፎ ከትከት ብለው ይስቃሉ ያው በተደሞ። መቼም ደርዝ ያለው ነገር መልካም ነው። 

ትንሽ ራፊ ነስተህ ያብጠለጠልከውን „ነፍሴ ነህ! ሆዴ ውስጥ አንጀቴ፤ ትንፋሼ፤ የ እኛ ወገኔ ምንትሶ ቅብጥርጥርሶ“ ስትል ሰው ይታዘበኛል ማለት መቼም ያባት ነው። ለነገሩ ልባሙ መንፈስ ይሄው ይቅርታ ምን ማለት እንደሆነ እያሳዬው ነው ለሁሉም። መቼስ ሙያ በልብን ተክህኖበታል ይባልለት።

„እናላችሁ“ እሰዬ ለአራተኛ ጊዜ መጣ ተዛሬው ባላንባራሱ ፡ እናላችሁ" ታምስት ተደረደ የውነት የአቶ መላኩ ፈንታን ትጋት፤ ጥረት፤ ታታሪነት የነበራቸውን ተቀባይነት፤ የነበረባቸውን ፈተና ሳዳምጥ በመመስጥ ነበር የተከታተልኩት። 

ስለምን? ብትሉኝ ጎንደር ተውልዶ ህብረት እና ፋሲለደስ የተማረ ሰው ይህን ያህል ዝም ተብሎ ተለቆ ይህን ሁሉ ደረጃ አልፎ፤ ያን ያህል ውጤት ሲያሰመዘግብ አቶ በረከት ስምዖን የመሰለ ዘንዶ ተቀምጦ፤ ሥርዓቱም ማህረ ደራጎን በራሱ ባለበት የውስጥ ችግር ጋር ሲሰላ የውነት የሰማይ ታምር ነው የመሰለኝ። ያው ጎንደሬዎች ፖለቲካው አይተውነም እኛም ሃራም ብለን ፖለቲካውን አንተዎውም፤ በዛም በዚህ ተብሎ ተዬት ነው ተወዴት ሲባል „ጎንደሬ“ ህም!

ባለፈው ጊዜ የቆሞስ ስመኘው በቀለን ጎንደሬነት ስሰማ እንዴት ይህ ሃላፊነት ተሰጣቸው ብዬ ነበር፤ ከዚህ ቃለ ምልልስ ጋር ሳገናዝበውም ግርም ነው ያለኝ። ቤተሰቦቼም ውጭ ያሉት ግን እንዴት ተዚህ ደረጃ ደረሱ ነው ያሉት። ያውቁታላ በ እህታቸው ያለውን ፈተና .. 

... እኔ ሌላ ምን በድዬ ነው ይህን ያክል በፈተና የታጠርኩት። ያውም የስደቱ ኑሮ ተቀንቶበት። መቼስ ሌላ አገር ቢሆን መማሩም፤ መሥራቱም፤ መፍጠሩም ዕዱሉ ይኖራል ለጠነከረ ሰው ከዚህ እኮ ያው ታሽጎ መባጀት ነው። ብቻ ያው ጎንደሬነት እና አማራነት ፍዳ ነው። ሌላማ ዝንፍ ያለ፤ ቅጥፍ ያለ፤ ምልጭልጭ የሚል አምነባርጭቃነት፤ ዘው ያለ ነገር  የለበትም። በአርምሞ - ቁጥብነት፤ ክውን - ልቅም - ክድን ያለ ሰብዕና ተይዞ ነው እንግዲህ ይህ ሁሉ የመከራ ኩንታል ተሽክሜ የኖርኩት። ኮቴዬን ሲያሳድዱት የኖሩት … ይህው ነው ጎንደሬነት ዕጣ ፈንታው፤

እና እናማ እንዴት እስተዛ ድረስ ይለፍ ተሰጣቸው ነው ጥያቄው ለአቶ መላኩ ፈንታ /ቴ? ይህ ነው በኽረ ጥያቄዬ። አንዳንድ ጊዜ ምን አለ ጎንደርዬ ካንቺ ባልፈጠር፤ እንደገናም ባለውድሽ ውስጤ ባትሆኝ ምን በነበረ ሁሉ እላለሁኝ።

የገሃዱ ሥሜን የቀዬርኩበት መሰረታዊ ምክንያት ፈተናው ቢቀንስ ብዬ እንጂ በጣም ብዙ ሰው የሚያውቀው ከ100 ሥሞች መሃል ተወዳድሮ አሸንፌ የሆነው አበይ እናቴን እብዬን አሸንፎ ያወጣልኝ ተወዳጅ ሥም አለኝ እኮ። ሁለተኛው ሥም ሰፋኒት ነበር። ይህም ወርቅ ነው አይደል። ቤተሰቦቼ ለሥም አወጣጡ ጭንቅ ጥብብ ነው ይሉ የነበሩት ካደኩኝ በኋዋላ ሲነገረኝ። 

ግን ፈተናው ቢታገሥ ብዬ ክርስትና ሥሜን አነግሥኩት። በውነቱ ቤተሰቦቼ ደስተኞች አይደሉም እንጂ ደስተኞች ቢሆኑ ባስቀይረውም በወደድኩኝ በነበረ ሥርጉተ ሥላሴ የብዕር ብቻ ሳይሆን የገሃዱ ዓለም መጠሪዬ በሆነ በነበረ። ምክንያቱም ጎንደር መውለድ አሳር ነው፤ ድንጋይ አለት ወይንም ጭድ ጭንቅላት ካልተሸከሙ ፍዳው ቃላት ሊሸከመው አይቻለውም። የትንፋሽ ቀዳዳ እስከ ጠፋ ድረስ። 

የሚገርመው  … እቴጌነቱን ሆነ ጌትነቱ ያለ በውስጥ ነው ግን በዬተሄደበት ያለው አሳር፤ ያለው ፍዳ፤ ያለው ስቃይ ወቄት የለውም። አሳዛኙ ነገር ያው ራሱ ጎንደሬም የአሳዳጆች ጃንደረባ መሆኑ ነው፤ የሚገርመው የሚደንቀው ነገር። ልብ የላቸውም ጎንደሬዎች። የራሳቸውን ወገን ለማሳደድ፤ ለማስገልል ማን ብሏቸው ... ሌላው ምንም የሌለውን የተራራ ያህል አስከፍሰው አንቱ ሲያሰኙ እነሱ ደግሞ ያለው ሲፈጠፈጥ ማዬት ናፍቆታቸው ነው። ገና የህሊና አብዮት ያስፈልጋቸዋል እነሱው - ጎንደሬዎች፤

ብቻ … አሁን ከዚህ ቃለ ምልልስ ከተረዳሁት ምንም ሰሃ አላግኘሁባቸውም እኔ በግሌ ከአቶ መላኩ ፈንታ/ ቴ። ብቃታቸው፤ ክህሎታቸው፤ ጥረታቸው፤ የፈጠራ አቅማቸው ለአገር የሚበጅ ክህሎት ያላቸው ናቸው። ግን እነ ሳጅን በረከት ስምዖን ልዑል በነበሩበት አገር፤ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ሥርዕዎ መንግሥት አጤ በሆነባት አላዛሯ ኢትዮጵያ የጎንደር ልጅ ለዛውም አማራ ከዚህ በላይ መሄድ አይቻልም ነበር። እንዲያውም አቶ መላኩ ፈንታ እግዚአብሄርን ማመስገን አለባቸው። 

አጥፍተዋቸው ቢሆንስ? ክንፈ መሳልጠኛ ውስጥ ቀብረዋች ቢሆንስ? የቆመስ ስመኘው በቀለ ዕጣ ቢደርስባቸውስ ኖሮ? ወይንም የፕ/ እምሩ ስዩም ዕጣ ገጥሟቸው ቢሆንስ ኖሮ? ወይንም በብክለት አዕምሯቸውን አስተዋቸው ቢሆንስ? የማን ያለህ ሊባል ይችላል?እነሱ መግቢያቸው መቼም አይታወቀም፤ ስልታቸው ረቂቅ ነው ... 

ሌላው የተነሳው የድክመት ሳንክ የፆታዊ ጉዳይ ነው፤ ይህም ለሁሉ አይሠራም፤ ሊያጠቁት የሚፈልጉትን ለዛውም አማራ ላይ ሲኮን ነው ገኖ የመደመጠው። ስንት የበከተ፤ ስንት የከረፋ፤ ስንት የጨቀዬ ሰብዕና የተሸከሙ ሰዎች ናቸው አሁንስ ሥልጣን ላይ ሆነው ከማህል አልመለስ፤ ከዳር አልታረስ ብለው እዬአመሱት ያሉት አዲሱን መንገድ እና ተስፋ? ገማናው እኮ ጉግል እዬጎለጎለው ነው …

ይህ ማለት ግን ጾታዊ ቅጥፈትን ጸያፊነቱ፤ ታማኝነትን ከመግደል ጋር ስለሆነ፤ ጸያፊነት ራስን መግዛት ከመሳን ጋር ስለሆነ፤ በብዙ ሁኔታ ይቅርታ ቢኖረኝም እኔ በዚህ ዘርፍ ይቅርታ የማላደርግበት መስመር ነው። እኔ ታማኝነትን በተማለው ሳይሆን ፍጹም ታማኝ መሆን ለዬትኛውም የሃላፊነት ቦታ ፤ ለጉርብትና ሳይቀር መስፈርቴ ነው። ሰውን የምለካበት ሁለት ነገር ነው፤ አንዱ ፍጹም ታማኝነት ሁለተኛው ደግሞ የአስተሳስብ ድህነት ያላዛገው ህሊና ወይንም ሰብዕና።
  • ·        ብአዴን እና የፊት ለፊት ግዴታው።


የሆነ ሆኖ ወደ ቀደመው ነገር ምልስት ሲሆን ብአዴን እኒህን የአገር ሃብት ይቅርታ ጠይቆ ወደ ሃላፊነታቸው የመመለስ ግዴታ አለበት። እናቷአለሟ ጎንደርዬም የሰጠቻቸው ክብር እና ልዕልናም የተገባ መሆኑን አሁን አረጋግጫለሁኝ። አሁን ዶር አብይ አህመድ፤ ዶር አንባቸው መኮንን ዶር ለማ መገርሳ ዶር ገዱ አንዳርጋቸው አቶ ደመቀ መኮነንስ ያው ኢህአዴግ አይደሉንም? እንዲህ ሐዋርያ፤ ቅኔዎቻችን፤ ቅዱሶቻችን እያልን ስናዘምርላቸው ውለን የምናድረው። ምንጫቸው ኢህአዴግ ነው፤ አሁን የሚሠሩት፤ የሚታታሩት ለግንባራቸው ነው። ስለዚህ የእኒህ ሰው ጉዳይም ከዚህ አንጻር በተደሞ እና በአንክሮ ሊታይ ይጋባዋል። ግን ዶር/ ለማ መገረሳ የት ናቸው? ድጣቸው እራቀ እኮ? የጤና ነውን? 

የሆነ ሆኖ አሁንም የኢህዴግ መርህ፤ የኢህአዴግ ህገ መንግሥስት፤ የኢህአዴግ መዝሙር፤ የኢህአዴግ ሥርዓት ነው ያለው። ይህን የተቀበለ መንፈስ ስለምን አቶ መላኩን ፈንታን አይቀበልም? እኔ እንደማስበው የሳጅን በረከት ስምዖን ኮንፕሌክስ የፈጠረው ችግር ነው ለዚህ መከራ የዳረጋቸው። ግን መታሠራቸው የጎደላቸውን ነገር እንዲያስተካክሉ ይረዳቸዋል ብዬ አስባለሁኝ።

መታሠረም ለእኔ ጥሩ ነው ባይ ነኝ። ታሥሬ ስለ ነበር ፍጹም ደስታ ነኝ። ከህይወቱ ዘርፍ እንደ ትውልዱ ታዳሚነቴ ክብሬ ነው መታሰሬ። ያለዬሁትን ማዬት መቻሌ መኖርን የበለጠ እንዳከበረው አድርጎኛል።
እርግጥ ነው ፈተናውም ለእዬስረኛው የተለያዬ ነው። ለቤተሰም ፍዳ መሆኑን ስቼው አይደለም። ቤተሰብም ቢሆን በፈተና ነጥሮ መፈተን ይኖርበታል መኖር እንዲህ ሲሆነው መኖርን የሚተረጉመው፤

ለአንዳንዱ በቀላሉ፤ ሌላው ደግሞ የመላ ህይወቱን መከራ ያሸከማል፤ ያም የሚሆነው በሰዎች ፈቃድ ሳይሆን የፈጣሪም ያዘጋጀው የሱባኤ ጊዜ ስለሆነ ለእኔ መልካም የተምክሮ ማሳ ነው - ለተማረበት። ግን በጭካኔው፤ በፍዳው፤ በስቃዩ ድርቅ ያለ፤ ርር ያለ መንፈስን ስንቅ ማድረግ አይገባም ባይ ነኝ - በግሌ። ስለምን? ያ እንዲሆን ግድ ስለሆነ፤ ቅዱሳን ሐዋርያት፤ የወንጌል አርበኞች እኮ ታሠረዋል፤ ተወግራዋል  በአደባባይ እንኳንስ ለእኛ ለገሃዱ ዓለምተኞች ቀርቶ …

ቀጣዩ የመስከረሙ የብአዴን ጉባኤ ሌላው የሚለከበት አንዱ የፈተና ግንባር ይሆናል አቶ መላኩ ፈንታን በነበራቸው ክብር ልክ የመቀበል ጉዳይ። ይህን ተላልፎ „አንድ ዓይን ቢኖራት እሱንም በዘነዘና“ ከሆነ ግን ብአዴንም የሚበልጡትን፤ ብልሆችን፤ አቅም ክህሎት ያላቸውን፤ ተምክሯቸው ዝቀሽ የሆኑትን፤ ለዛውም የጎንደር ህዝብ ያከበራቸውን ልክ እንደ አባ ቆስቁስ አቶ በረከት ስምዖን አቅምን፤ ችሎታን፤ ዕውቀትን ይፈራል ማለት ይሆናል። 

የበታችነት ስሜት የሚንጣቸው ናቸው ውጪ አገርም // አገር ውስጥም ሰብዕናን የማመስ፤ ሰውን የማስገለል፤ የማጠልሽት ጃንደረባዎች እና በንጹሃን ላይ ክፋትን ፈጥረው ብርቱ ዘመቻ የሚያደርጉት። አቅም ያለውማ ደፋር ነው። አለዋ!መኖርን ተጠውሮ ሳሆን በዲታ መንፈሱ ልክ ስለሚያበጀው። 

የሆነ ሆኖ ዶር ደብረጽዮን ገ/ ሚኬኤልን የተቀበለች አላዛሯ ኢትዮጵያ ዜግነትን እንዴት እንደምታስተናግደው ይታያል መጪው መስከረም አጋማሽ የብአዴን የማስተዋል አቅም እና ችሎታ። በሌላ በኩል የአብይ ካቢኔም ወርቅ በእሳት እንደሚፈተነው የሚታይበት አንዱ ዓውድ ይሆናል … 


አንዲት ይቅርታ።

አንዳንድ ቦታ ላይ አቶ መላኩ ፈንታ ይላል። ሌላ ቦታ ላይ ግን አቶ መላኩ ፈንቴ ይላል። "ፈንቴ" የተለመደ ሥም ነው ለጎንደር፤ በሚዛን ሲታይ "ፈንታ፤ ፈንታሁንም፤ ፈንታዬም" እንዲሁ። የሆነ ሆኖ ማዕከላዊ የሆነውም "ፈንታ  የሚለውን አብዝቼ  በመጠቀሜ ዝበት ካለበት ባለቤቱን አቶ መላኩ ፈንታን ይቅርታ እጠይቃለሁኝ። 

ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!

የሰውን ነገር ሰምቶ ሰብዕናን ከማክስል ራስን ፈተና አስቅምጦ መለካት ይቅደም!

የኔዎቹ ክብረቶች ኑሩልኝ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።