እናት የክት እና የዘወትር ልጅ የላትም ...
ሾጣጣ።
„ልጄ ሆይ ቃሌን ጠብቅ፤ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽግ።“
መጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ ፯ ቁጥር ፩
ከሥርጉተ©ሥላሴ 02.10.2018
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።
ሾጤ - ሞጤ - ሽምጤ - ሾጣጤ - ሞጣጤ - ሞጥሟጤ። ሁሎችም ቃሎች ናቸው። ሁሎችም እኩል መብት እና ግዴታ አለባቸው። ሁሎችም የአማርኛ ቋንቋ አባልተኞች ሽሙንሙኖች፤ ሸባላዎች፤ ሸንቃጣዎች ናቸው።
ሁሎችም የስዋሰው ቤተኞች ናቸው። ሁሎችም መነሻቸው ከአማርኛ ፊደላት ነው። ሁሎችም ባለድምጽ፤ ባለ ቃና፤ ባለ ደንብ፤ ባለ ጌጥ፤ ባለ ዘለበታዊ ምት፤ ባላ ዜማ ናቸው። እኩል ናቸው ማለት ነው። እኩልነት እንዲህ ሲገልጥ የልብ ያደርሳል።
ኢትዮጵያዊነት እንዲህ ቢሆን ምኞቴ ነው።
በመኖር እና በመኗኗር መሃከል ግን መኖር ለሁሉ ተፈጠረ፤ ግን ለሁሉ ለመሆን አቅመ ቢስ ነው። ስለሆነም መኖር ወይ እረኛ ነው ወይ ደግሞ የታገተ ነው። ወይ ደግሞ ዲዳ ነው ወይ ደግሞ ሰውር ብቻ።
„አይዋ መኖር“ ተብሎ ሲጠራ „አለሁ ለሁሉም“ ሲል ይደመጣል፤ አንዱን ሲያንጠለጥል አንዱን ሲያፈርጥ አንዱን ሲካለ ሌለውን ሲከውን፤ አንዱን ሲያቆምስ ሌላውን ሲያሰምጥ ብቻ አለሁኝ፤ አኗኗርኩኝ፤ ተኖርኛ ጋር ሆንኩኝ ይለናል ወገኛ በሉት /// አሁም ማን ይሙት አይዋ መኖር አለሁኝ ለሁሉ፤ ሁለማንም ሆንኩኝ ሊል ነውን? አብሶ ለእጣ የለሾች ባለሾጣጣ ዕጣ ፈንታዎች አዳብለኳቸው ቢል ይመረጣል።
አይዋ መኖር ግድዬለሽ ነው። አንዱን ሲያገዝፍ ወይንም ሲያስገዝፍ ሌላውን ደግሞ አጫጭቶ ሲያከስም ወይንም ሲያስተንን፤ አንዱን ባለዝናር ሲያደርግ እና አኮፍሶ ሲያስጀግን ሌላውን ትጥቅ አልቦሽ አድርጎ በዳዴ አንበርክኮ ሲያስኬደው አኗናርኩት፤ ከእኔ ወዲያ እኩልነት እና ነፃነት አዳይ ላስር ብሎ ደግሞ ጃሎ በል ባዩ ደግሞ እሱው ነው አይዋ መኖር አባትሌው በተከዘነ የችግር ባላዬን ሲነዳን የኖረው።
መኖር ለቀናው፤ መኖር ወፍ ላወጣው ተነበረከከም - ተጎነበሰም - ዳህም -ታቱም አለም፤ አንደ ኩሬ ውሃ ባለህበት ረገጠም፤ በቃ ቀን ቀጥ ብሎ ችምችም ያሉት የጥድ ዛፎች ሳይቀሩ በመደዳ ተሰልፈው ኮልት በሉት ምንሽራቸውን አሳምረው በዙር ታጥቀው፤ እንደ አባት አደሩ እግራቸውን ለሰልፍ ምት አስኮልኩለው፤ አፍሯቸውን ከምክምከው፤ በረድ ቢሉት፤ ጠራራ ቢሉት፤ ዳመና ብቻ ምን አልፋችሁ ቅልቋንቁራቸውን ተሸከመው መደለቅ ነው ለባለጊዜው ቀን ሰጥ።
ይህን የሚያደርገው ጄኒራል ዘመን ነው። እሱ ነው የሚያስጨፍራቸው ጽዶችን፤ ወንዱ ዘመን እንዲህ ነው አሰደግድጎ በሉ ሆ! ያሰኛቸዋል … ይልቅ የእጽዋቱ ዳንስ እና እልልታ ይምጣብኝ። ታንጎ፤ ባልስ በጃንቦ ያስኬዱታል ... ወቼ ጉድ ...
ብቻ ሾጣጣውም ሸርም፤ ሞጣጣው ተንኮልም፤ ሞጥሟጣው ሴራም፤ ሽርክቱ አሜትም ዘመን ተሰጠ ምን አለ እንደ መልካምነት ለጥ ሰጥ ብሎ ማደግደግ ነው። ተዬት ወደዬት የለም በግርድፉም በሾፊፎም ምታ ነው /// ተካሄድ ነው ...
ዘመን ሲቀዳም፤ ዘመን ሲያንቆረቁርም፤ ዘመን ሲያንዳልጥም፤ ዘመን ሲኮፍስም ብቻ እድሜ ለዘመን ማለት የአባት ነው። አሉ ደግሞ ታክተውም፤ ለፍተውም፤ ደክመውም፤ ወጥተው ወርደውም አቋጠሪ አጥተው እንደ ጠወለገ አርግሬሳ በቃ ብን .. ትን ብለው የሚቀሩ … ምስኪን … እኔን አፈር ይብላኝ፤ ኧረ! ህ! …
ሾጣጣ ዕጣ ፈንታ ሁልጊዜ ቋያ ነው የሚያነገረግብ፤ ሁልጊዜም የጋመ ነው የሚያንገበግብ፤ ሁልጊዜም ረመጥ ነው የሚያርመጠምጥ፤ ሁልጊዜም አቋጣሪ የሌለው ቁመቀር ነው ባለሾጣጣው ዕጣ ፈንታ፤ ቀደምቶች የ40 ቀን ዕድል ይሉታል እንዲያ ነው ነገርዬው ….
ተሰሞኑ ተዚህች ከደጓ አገር ተሲዊዝዬ ሆኜ እንዲያው መንትዮሽ ግን ፈንጠር ፈንጠር ብለው የተቀመጡ ዕጣ ፈንታዎችን አዬሁኝ በብሌኗ። አንዱ አጤ ሌላው ደግሞ አንጋች ሆነው።
አንዱ ተዳብሎ እስቲ ልመሰል ወይንም ልለሰን ሲል፤ ሌላው ደግሞ አንደበት ልሳን መተንፈሻ ተደርጎ ሲኮፈስ ወይ ፈጣሪ አንተ እንኳን ለባለሾጣጤው ባለ እጣ ብትራራለትስ ስል አቤት! አልኩኝ ለእዬርኛው … እንደ ለመደብኝ። ትንሽ ቢጤ ነገር ብታደርግለተስ ምንአለ ብዬ አሰብኩኝ፤ ይገባል አይደል?
የሚገረመው ሚዲያው ነው። ምን አለ አንዲት ጊዜ እንኳ ሥሙን ለጠፍ ቢያድርግለት ለዛኛው ለባለቤት አልቦሽ ባተሌስ፤ እንዲያው በድምጸትም ባይሆን ባይናገረው ከታች እንዲያው እንደነገሩ አድርጎ … አይዋ እከሌም ተስደት ወደ አገሩ በዚህን ያህል ዓመት ዛሬ ገባ ብሎ ቢጥፈው። ያው እናት እኮ አለች። ሁሉን ትመዝናለች ... እም!
አዬ የአላዛሯ ኢትዮጵያ እናት ተባደጉ ጊዜም እንዲህ ከውትሮው ሳይሻል እንባሽን ሚዛን ላይ ማስቀመጥ ሲሳነው ምን ይባል? እኔም እኩል ዘመን ይምጣልሽ ብዬ ነበር የጮኽኩትስ ግንስ ሆነ መድፊያው?
ሁሉም በዬወገን በዬወገኑ፤ በሁሉም በዬዞግ ሲሆን ሲሆን ከፍ ከፍ ሲደረግ ያ ባለሾጣጣው ነፍስ ግን እንዲያው ሥሙን ያያችሁ ወደዬት ናችሁ እስተማለት አስደረሰ። ግን አይገርምም እስቲ ግርም ይበላችሁ። መቼም የዚህች ሞድሟዳ ዓለም ተብዬ ወጣገባ፤ ተዛነፍ ፍርደ - ገምድልነት … ነፃነቱ ተገኜ ሲባልም እንዲህ ተሆነ። ባለቅርብ ሲቀርብ፤ ሌላው ደግሞ ባይታወርነት እስከበቃህ ድረስ ተጋተው … ይገርም ነው እስተወዲኛው። ሴሮች የትም አሉ …
እኔ ሥርጉትሻ ብሆንላችሁ ማንም ሳልጠጋ፤ ሹልክ ወይንም ሾከክ ብዬ ወደ ባዕቴ እግሬን አውጪኝ ነው። እትብቴ ወደ ተቀበረችባት ጎንደርዬ፤ እንዲያውም አንድ ነገር ሰሞኑን ሰማሁኝ ከወደ አሜሪካ የተነሳች አንዲት ሸባላ አዲስ አባባ ሳታድር እዛው በትራንስፍር ነው አሉ ተለዋጭ አውሮፕላን አግኝታ ወደ ቀሃ እና አንገርብዬን አቀናች ሲባል ያዳመጥኩት። እና ላጥ ጀግኒት ብላ ግብት … ኮሽ ሳታደርግ። እኔም እማደርጋት ያችን ነበር።
ስለምን ብዬ ልለጠፍ፤ ስለምንስ ብዬስ መጣፊያ ልሁን? እህ! ይህ ልባምነት አይደለም። የ የአንዱ ማዕረግ እኮ ለዛ ሰው ነው። ሁሉ ሰው አበጅቷል። የኔው ቢጤ ደግሞ እንደባተል ፍትልትል።
ሰው ራሱን ሆኖ መኖር ነው ያለበት። የአንዱ ክብር ለዛው እንከብርሃለን ለተባለው ብቻ፤ የአንዷም ክብር ያው እናከብርሻለች ለተባለችው ብቻ። እና እኔ ምን ባይ ነኝ መናጆ እምሆነው? በዚህ የነጻነት ተጋድሎ ሁሉም ፍዳውን ከፍሏል። በጥበብም ዘርፍ ቢሆን ሁሉም ኑሮውን ሰቅሎ ረስቶ ባዝኗል።
ሰው ራሱን ሆኖ መኖር ነው ያለበት። የአንዱ ክብር ለዛው እንከብርሃለን ለተባለው ብቻ፤ የአንዷም ክብር ያው እናከብርሻለች ለተባለችው ብቻ። እና እኔ ምን ባይ ነኝ መናጆ እምሆነው? በዚህ የነጻነት ተጋድሎ ሁሉም ፍዳውን ከፍሏል። በጥበብም ዘርፍ ቢሆን ሁሉም ኑሮውን ሰቅሎ ረስቶ ባዝኗል።
እናት አገር፤ እናት ምድር የክት እና የዘወትር እንዲህ ከኖራት ምኔ ሞኝ እኔ መጓጓዣ እምሆነው፤ ለፎቶ፤ ለምስል? አይታሰብም። ያችው ከገመና ከተቿ እትብት መንደሬ፤ ከተገፋችው፤ ሁሉም ካገለላት፤ ለመቆስቆሻ ብቻ ሁልጊዜም ከምትፈለገው እትብቴ ከተቀበረባት ቦታዬ ሳላስነግር፤ ሳለሰውራ፤ በጋዜጣ ይጣፍልኝ ሳልል፤ ነጋሪት ሳላስጎስም፤ ሰውር ብዬ ሄጄ ያው ጉዳዬ ናፍቆት ነው ኖፍቆቴን አጣጥሜ በባለክንፋሙ ምልሰት ወደ ዲል ወደ አለው ከተማ ነዋ። በቃ።
"የሰው ወርቅ አያደምቅም።" ምንግዜም የራሴ የሚሉት ግን ኮሳሳም ይሁን፤ ሸንጣራም ይሁን፤ ሾጣጣም ይሁን፤ ሞጣጣም ይሁን በራስ ስብዕና ላይ በተገነባ ማንነት ላይ ቀጥ ብሎ በሙሉ አቅም አንገት ቀና አድርጎ መሄድ።
ጉዞንም ራስን ችሎ ራስን ሆኖ መሄድ። ዓዋጅ አያስፈልገው፤ የጠገራብር ደልቅልኝ አያሰኝም። አቅሙ ያለው ከህሊና ነው ያለው። በተለጣፊነት ከሆነ ያ የህሊና ጉዳይ ክብካቤውን ሲያጣ ሊያመጣ የሚችለውን የሥነ- ልቦና ድቀት ማሰብ ያስፈልጋል።
አንድ ጨዋታ ተዚህ ላይ ትዝ አለኝ። „ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋል“ ይላሉ ጎንዴሬዎቹ።
እትዬ አልጋነሽ የምትባል ጎረቤታችን ነበረች። በልጅነቷ በጣም ታስብ ነበር። እና የጨነቃቸው „ኤርትራዊ አባት ስለምን ነው ልጄ እንዲህ ሃሳብ የምታበዢ አሏት።“ እሷ ታዲያ „አይ አቦይ እኔ ነኝ እሱ ነው“ እንጂ አለች።
ውዶቼ --- የውነት ታሪክ ነው የምነግራችሁ ኤርትራውያን ወደ አገራቸው እንዲገቡ ከተወሰነባቸው ዜጎች እንዷ ነበረች ሃሳብ አጥማጇ። ጎረቤታችን ብቻ ሳይሆን የውስጣችን ናት እትዬ አልጋዬ … ባለቤቷ በድንገተኛ ሁኔታ ከዚህ ዓለም ሲያልፉም እናቴ እዛ ድርስ ሄዳ ነው የቀበረቻቸው። ይህ ብቻ አይደለም ኢትዮጵያም ሲለቁ የተገባውን በጎ ነገር ሁሉ ፈጽማለች። ክብር ለእምዬ … እናቴ የቀን ሰው አይደለችምና።
የውነት ነው የምላችሁ ሁሉም በዚህ የነፃነት ትግል አፈር ድሜ ግጧል። የደረጃ ልዩነት የለውም። ቤተሰብም ያውቃል። ገንዘቡን፤ ጊዜውን፤ ትዳሩን ሳይቀር የበተነው ብዙ ነው። ሳያገባ የሚኖረውም የዚያኑ ያህል ነው። ያው ይህ መድረክ የሚባለው ነገር ሰዎች ለተወሰነ ዓላማ የሚፈልጓቸው ይኖራሉ፤ በዛ ካልሆነ በስተቀር መድረክ ላይ ጮራ መሆኑ፤ ብዙ ሊገለጽ፤ ሊነገር፤ ሊተነተን የማይችል መስዋዕትነት የከፈሉ ብርቱ እንቁ ወገኖቻችን አሉን። በሁሉም ዘርፍ። አቅማቸው መክሊታቸው እንፈቀደላቸው ...
ስደት ላይ የነፃነት ተጋድሎ መጀመር ራስን ማጣት ነው። እዬሞቱ መኖር።፡ አብሶ ታች ከሆኑ ደግሞ ጭቃ መሆን ነው፤ በርብርብ ድቅቅ ነው የሚደረገው፤ መረጋጋጫ። እና ይህ ሁሉ ታልፎ ዛሬ አንዱ የክት ሌላው የዘወትር፤ አንዱ ቤተኛ ሌላው ባይታዋር፤ አንዱ ከፍ ሌላው አስተዋሽ ሲያጣ ሳዬው ዓለም ጉርምድድ ብላ ተሸራርፋ ትታዬኛለች። የውነት ከምር ነው የምላችሁ። „አፍ ያለው ያግባሽ ነው የሆነው።“
ብዙ ታታሪዎችን በተለያዬ ሁኔታ አውቃለሁኝ እኔ። ከልጅነት እስከ እውቅት አጋጠሚዎች ሁሉንም ነገር አዬ ዘንድ፤ ሁሉንም ነገር እፈትሽ ዘንድ ሰጥቶኛል። ነገር ግን ተዛነፉ፤ ዝበቱ፤ ተባደጉ ነገር ግርም ይለኛል። እና የህግ ፋክልቲ ራሱ ፍትህ የሚለው፤ አውነት የሚለው፤ ፋክት የሚለው፤ የቱን ስለመሆኑ ግራ ይገባኛል … አስመርቆ የሚያወጣውም ...
መንታ ጣትህ እኩል የተሳተፈ፤ እኩልም ያገለገለ፤ ከእኩል ባዕትም የተፈጠረ አንዱ ባለቅርብ ስላለው ሌላው ብረት መዝጊያ ስሌለው ብቻ በተመሳሳይ ወቅት እና በተመሳሳይ ዕድል ማበላለጥ በአገር ደረጃ ሲሆን ይጎረብጣል።
ለዚህ የመከራ ዘመን ዬስደት ቆይታ አንዱ ንጉሥ ሌላው የሎሌ ያህል አቋጣሪ አጥቶ ፤ ለማሟያነትም አልበቃ ብሎ ስመለከት ውስጥን ይፈትናል። እኔ ደግሞ ሚዛን ሲያጋድል ያመኛል። ምክንያቱም በዚህ ማህል እናት አለች። ልጇ ሲባትል/ ወይንም ስትባትል ታውቃለች ያቺ የአላዛሯ ድምጽ አልባዋ እናት፤ ሚስትም አለች። ለሷም እውቅናውን የመንፈግ ያህል ስለሚሰማኝ ነው የሚያመኝ። ሴቶች በ አያያዝ ጉደለት ከእንግዲህ አንገታቸውን ደፍተው ማዬትን አልሻም።
ሁሉም ለዚህ የነፃነት ትግል ማስኗል፤ ለመልካም ዘመን ኳትኗል፤ 24ሰዓት ቀን እና ሌሊት ሠርቷል። ስለሆነም ዘመን ሳይንሿጠጥ፤ ወይንም ዘመን ሳያሽሟጥጥ፤ ወይንም ዘመን ሳይሽበለበል ሁሉንም እንደ ጸጋው፤ እንደ መክሊቱ፤ እንደ ሰው መሆን መቻሉ ቢያሰተናግደው ምኞቴ ነበር፤ ግን የማዬው፤ የማደምጥው ነገር ተባደግ ነው።
ሚዛን የለም! ግን ፍትህ ማለት ምን ማለት ነው? ለመሆኑ ፍትህ ምንድን ነው? ግን ፍትህ ተርጓሚ ተበጅቶለታልን?
ክወና።
የኔዎቹ ኑሩልኝ! ከውስጣቸሁ ሆናችሁ እኔስ ብሆን ብላችሁ ሁሉንም ነገር መርምሩት፤ ለባተሌዎች እናት አገር እኩል ማስተናገድ ይኖርበታል ባይ ነኝ - እኔው። የጥብብ ሰው ከተሆነም እኩል መስተናገድ አለበት። የፖለቲካ ሰው ከሆነም እንዲሁ። ታታሪ ከሆነም እንዲሁ፤ ሊሂቅ ከሆንም እንዲሁ። ምክንያቱም እናት የክት እና የዘወትር ልጅ የላትምእና።
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!
ማለፊያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ