የቤቴ ውሽክታ ...

 ድገሙኝ
ሰለሱኝ ይል ነበር …
„የእግዚአብሄር ቸርነት ምድርን ሞላች።“
መዝሙር ምዕራፍ ፴፪ ቁጥር ፭
ከሥርጉተ© ሥላሴ
12.09.2018
ከገዳማዊቷ ሲዊዘርላንድ።


  • ·       ውደ ዓመት እና የቤቴ ውሽክታ ….

አቤት ሃሞጭ የመሰለው ጥርስ እንዴት ያምራል? አቤት ዓይን እንዴት ይስባል፤ አቤት ተረከዝ እንዴት ከሩቅ ይጣራል፤ አቤት ሽንጥ እና ዳሌ እንዴት ያስንቃል  የእኔ እንዳይመስላችሁ ውዶቼ የቤቴ ነው …

ትናንት ለመጀመሪያ ጊዜ ኮንፒተር ሳይከፈት ተዋለ ታደረ። ለመጀመሪያ ጊዜም በዘመነ ስደት ቅዱስ ዮሖንስ ዲል ተብሎ በሙሉ መሰናዶ ተከበረ። አይደለም ሥርጉትሻ ቤቴም ሳቀ በሳቅ፤ ሰናይ በሳናይ፤ ፈገግታ በፈገግታ። ተመስገን!

ነፃነት ለካንስ እንዲህ የሳቅ ንጉሥ ነው። ነፃነት ለካንስ እንዲህ ሁለመናን ያፍለቀልቃል። ነፃነት ለካንስ የአቅም መሃንዲስ ነው። ነፃነት ለካንስ ሃይል ነው። ነፃነት ለካንስ እንዲህ ናፍቆትን ይክሳል።

አገር ቤት እያለን ታናሽ እህቴ ጳጉሜን ቤቱን ዝርክርክ ታደርገው ነበር። ቅዱስ ዮሖንስ እንዲደምቅ የምትለው ብሂል ነበራት። አሁን እኔም ከሰሞናቱ እንደዛ ገጥሞኝ ነበር።

ሥራ ብዝት ብሎብኝ ሰነበተ። ግዢውም እንዲሁ። እኔ ለአውድዓመት እንብዛም ነበርኩኝ አገር ቤት። ያው ሥራ ይበዛብኝ ስለነበር። ቤተሰቦቼ ደግሞ ቀን ቆጣሪዎች ናቸው። ይወዳሉ። እንዲያውም ቅዱስ ዮሖንስ እና ፋሲካ አንድ ሳምንት ቢከበር ባዮችም ናቸው።

የሆነ ሆኖ ከአገር ስወጣ ብዙም አልከበደኝም። ነገር ግን ዘንድሮ የተሰማኝ ስሜት የተለዬ ነበር። ደግሞም የዘንድሮው ባዕል መከበር ሲያንሰው ነው። የውስጤ ሊባል የሚገባው ነው። አዬሩ ራሱ እንዴት ደስ ይል ነበር።

የኢትዮ ኤርትራ ዋንጫችን በበለስ ነበር። እዚህ ሲዊዘርላንድ በለስ አገኘሁ እና ገዛሁ። በለስ ጎንደር ቀሃ እዬሱስ አካባቢ አለ። ፈጭፋጭትን ወንዝ ይዞም ነው የሚበቅለው። ድሮ ነበር አሁን አላውቅም። የእኛው ሲበስል ቀለሙ ብርቱካንማ ነው። 

የዚህ አገር ደግሞ ወይናም ቀይ ነው። ጣዕሙ አንድ አይነት ነው። አሁን አውጥ እዚህም አለ። ፍሬው ግን የጫጫ ነው፤ በዛ ላይ ጣዕሙ ይመራል። እነሱ ለዲኮ ነው የሚጠቀሙበት - አውጡን። ምን ስለ ዲኮ ከተነሳ ፍልጥ እንጨትም ለዲኮ፤ ጭድም በቦንዳ ለዲኮ ይካኑበታል …

ብቻ ድፎዬ በኮባ ቅጠል ነበር የተጋገረው። መሰናዶየ ፈጽሞ ከተለመደው ውጪ ነበር። እንግዶቼም ሲያገኙኝ ግርም ነው ያላቸው። ሁለመናዬ ይስቅ ነበር። ለውጥ ይላችሁዋል እንዲህ ነው።

አገር ከገቡት ባለነሰ ነው ኢትዮጵያዊ ውብ ጠረን ባለው አካኋዋን ባዕሉን ያከበርኩት። እኔ ባዕላትን በስደት ቤት ውስጥ እንዲህ ባለ መልኩ በተደራጀ ሁኔታ አቅጄ አስቤው በዚህ መልክ አክብሬ አላውቅም። 

በቤተ እግዚአብሄር ከሆነ የማሳናዳው ያው ለማህበረ ምዕመኑ እንጂ እንዲህ የራሴን ደስታ አጀንዳ አድርጌ ሸር ጉድ ብዬ በውነተኛ ደስታ ሳከብር የመጀመሪያዬ ነው። 

በዬሰዓቱ ተመስገን እያልኩኝ። ሻማዬን አብርቼ። አንድም ነገር ቤት ውስጥ ቀረ የሚባል ነገር አልነበረም። ሁሉም ነገር በተገባው ሁኔታ ነበር የተዘጋጀሁት።

አንዲት ያልተከወነች ነገር አገር ቤት ደውዬ እናቶቼን አላነጋገርኩኝም። እናቴ እንደሚከፋት አውቃለሁኝ። ሌሎችን ስታይ ትቀናላችም ቢያንስ ስልክ። ያሳደጉኝም ጎረቤቶቻችንም እንዲሁ። ምክንያቱም አማራን በሚመለከት በማዕከላዊ መንግሥት ያለው ዕውቅና ቀዝቃዛ ነው። እርግጠኛ የሚያደርግ ነገር የለም። አሁን የ እናቴ ደህንነት ያሳስበኛል። 

ዕውቆቹማ ማን ይናካቸዋል። እንደኛ ታች ሆኖ ለሚፈጋው ቤተሰብ ግን አደጋው ስውር ነው። ጥንቃቄ ያተርፋል እንጂ አያከስርም። ማስተዋል፤ ስክነት፤ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፤ ለሌላው ዘነብ ተብሎ ለእኔ ያካፋል ብሎ መጃጃል አይገባም። ቁጥብነት ጥሩ ነው። ሰብሰብ ክውን ማለት ይገባል። ምን በወጣቸው ወገኖቼ  በእኔ ምክንያት ይሳቀቁብኝ።  

በአጠቃላዩ ኢትዮጵያ ላይ ያለው የለውጥ አዬር ተስፋው ግን መንፈሱ ጥሩ ነው። እጅግም ብዙም ነገሮች ባልተለመደ ሁኔታ ተለውጠዋል። የነፃነት መንፈስ ላቅ ብሎ አይቻለሁኝ።

ውይ እኔን ይርሳኝ በለስ / ቁልቋል 7 ዓመቴ ላይ እያለሁ በልጅነት ጊዜዬ ነበር የበላሁት። ዘንድሮ የገዛሁበት መሰረታዊ ምክንያት የኢትዮ ኤርትራ ቅናዊ፤ ዕውነታዊ፤ ንጹሃዊ፤ እኛዊነታዊ፤ ልባዊ ግንኙነት አስመልክቼ ለዋንጫችን ለማለት ነው። ክብር ለሚሰጣቸው መልካም ነገሮች ክብር ሊሰጣቸው ይገባል።

ትልቁ ዶር አብይ አህመድ ኤርትራ በነበሩበት ጊዜ የተጋበዙት በለስ ነበር።  
እንዲህ የበረንቱ ተራራ፤ የአፋ ቤት ተራራ ሰላም ሲነፍስባቸው ውስጤ ሊባል ይገባዋል። እኔ ኢህአዴግ የወሰደው እርምጃ ደፋርንም ነው ይገባልም ስል እሳቤው ከሴራ - ከጥቅም - የተለዬ ዕውቅና ውዳሴ ለማግኘት፤ የተለዬ ትርፍ ለማጋበስ ሳይሆን ጠረኑ ሰውኛ ስለመሆኑ በሚገባ እመኜበት ነው የባድመ እድምታ በሥርጉተ ዕይታ የጻፍኩት።

እንዳልኩትም የሆነው ሁሉ በትክክል ነው የሆነው። እራሱ እዛ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶችም ስለቀጣይ ተስፋቸው ሁሉ ጽፌ ነበር። የሆነው ያልኩት ነው። ያ ደፋር ውሳኔ ትርፉ ከ - እስከ አይባልም። 

ተቃማዊዎች የመንፈስ መሬታቸውን ነው የተነጠቁት ኢህአዴግ በወሰደው ደፋር ርምጃ። ትርፉ ደግሞ አዬሩን አስተካካለው። ስለዚህ ቁልቋል ቢገዛ ሲያንሰው ነው? ስኬቱ ጥበቡ ዝቀሽ ነውና። የአፈጻጻሙ ቅደም ተከተል በራሱ ልኡቅ ቅቡል ነው። ተመስገን።

የሆነ ሆኖ ይህ በዓል ድገሙኝም ሰልስኙም አስኝቶኛል። ደስታ እንዴት ጥሩ ነገር ነው። ለካንስ የውስጥ ደስታ ብቻ ነው ራስን አጀንዳ እንዲደረግ በመንፈስ የሚያዘጋጅ። ተመስገን።

ትውፊታቸን ያኑረልን ፈጣሪ!

ሰላማችን ያበራክትልን አማኑኤል።  አሜን!
የኔዎቹ ኑሩልኝ።

ማለፊያ ጊዜ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።