ፉከራ ገደለን።

ፉከራ ገደለን።
„እግዚአብሄር በአንድ መንገድ
በሌላም ይናገራል። ሰው ግን
አያስተውለውም።“
(መጸሐፈ እዮብ ምዕራፍ ፴፫ ቁጥር ፲፬)
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
31.12.2018


·       ቅድም።

ምን ጠላሽ ብባል ፉከራ። ምን ገለማሽ ብባል ፉከራ። ምን አንገሸገሸሽ ብባል ቀረርቶ። ምን ፈራሽም ብባል የጦርነት ዓዋጅስንት ዘመን ነው እኛ እኛን እዬጨረሰን // እያጫረስን የምንዘልቀው። ወጊዎችም ተወጊዎችም እራሳችን ነን።

እስከ ዛሬ መሪ ሙሴ ሁነኛ በማጣት ነበር። አሁን የጠበቀንው አይደለም ከለመነው እጥፍ ድርብ አድርጎ ልዑል እግዚአብሄር አሟልቶ የተሟሉ፤ የሰከኑ፤ የረጉ፤ የአወቁ፤ ያስተዋሉ መሪዎች ፈጣሪ በቃችሁ ሲለን ሰጥቶናል። እኛ እንዴት አንታገሰም? ምን ይሆን አዚሙ?
ከውጭ ወደ አገር ሲገባ ፉከራ ነው „ጉሮ ወሸባዬ ታጋይ ድል አድርጎ“ ሲገባ፤ ከጫካ ወደ ከተማ ሲገባም ያው ፉከራ ነው። ፉከራውን ምን አለ ህዝብን ወደ ሰላም፤ ወደ ማረጋጋት፤ ወደ ማጽናነት ቢኬድ።

ህዝቡ እኮ ደቋል። ህዝብ በድህነት መንምኗል። ህዝብ በስጋት ተወቅቷል። ህዝብ ተስፋ በማጣት አሳሩን በልቷል። ሁለመናው አለቋል። ሁለመናው ወላልቋል። አሁን እኮ ይህን መሰል የመተንፈሻ ዘመን እግዚአብሄር ስለሰጠን እምናመሰግንበት ጊዜ ነበር እንጂ ህውከት እምናጭሰበት ወቅት አይደለም

አሁን አርበኛ መስፍን ተስፉ እና ጓዶቻቸው ከሽምቅ ውጊያ ወደ አገር ገብተዋል። ይህ መልካም ነገር ነው። በዛ በጭንቅ ጊዜ አለንላችሁ ብሎ ኑሮዬን - ትዳሬን - ህይወቴን ሳይሉ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ በመሆን በዱር በገደሉ ክልትምትም ማለቱ፤ የሚችሉትን ለማድረግ በህይወት መወሰኑ የተገባ ነው። ጀግንነትም ነው። በዛ ዙሪያው ጨለማ በሆነበት ዘመን መጽናኛም ተስፋም ነው። ታሪክም አይረሳው ትወፊትም ነው።

ዳባት፤ ጎንደር ከተማ፤ ባህርዳር ሲገቡ የተደረገላቸውን አቀባበል አይቻለሁኝ። እግረ መንገዴንም ዳባትን በማዬቴ ደስ ብሎኛል። ያም መልካም ነገር ነው። እናመሰግናለን መባሉ የተገባ ነው። ጎንደር ከተማ ላይ በነበረው አቀባባል የራያ ተወካይም ነበሩ። ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ነው የተቀበላቸው። 

ይህ ሁሉ እንኳን ለአገራችሁ መሬት በሰላም አገባችሁ እንደ አርበኛ ጎቤ እንኳንም አላጠናችሁ፤ እናመሰግናችሁ አለን ስለሆነ የተገባ እና መሆን የሚገባው ሆኖ ሳለ ሩምታ ተኩሱ ግን አስፈልጊ አልነበረም። ትውፊት መሆኑን ረስው አይደለም። ግን ወቅት መታዬት ይኖርበታል። በዛ ላይ ጎንደር ከተማ ነው፤ እንደገናም አሁን የገና ፆም የሱባኤ ወቅትም ነው። የሆነ ሆኖ ያስተዋሉ ወገኖች ወዲያውኑ አስቁመውታል። ይባረኩም።

·       ተጋድሎን ስኬት መጠበቅ እንደ ነፍስ ሊሆን ይገባል፤

ያ የተጋድሎ ፍሬ እግዚአብሄርም ረድቶ ለውጤት ለፍሬ ሲበቃ ፉከራ ሳይሆን፤ ቀረርቶ ሳይሆን፤ የጥይት ሩምታ ሳይሆን መሆን የሚገባው ሱባኤ ነበር። አሁን እኮ የሱባኤ ወቅትም ነው። አሁን የጾም ወቅት ነው። እምሰማው ንግግር ሁሉ ሰውነቴን ያንቀጠቅጠዋል። እማዳምጠው ንግግር ሁሉ መንፈሴን ያውከዋል። በግራ በቀኙ በኩል።
  
የፈለገ አካል፤ ድርጅት ጦርነት ይወጅ ሌላ ቦታ ላይ ሆኖ። አዲስ አባባም ተሁኖ፤ መቀሌም ተሁኖ። ከጫካ ወደ ከተማ የገቡት ግን ይህን ማርብ ይኖርባቸዋል። እውነት ብናገር ጎንደርም ትግራይም ወሎም በቃው።

ከጦርነት ሦስቱ ቦታዎች የቱ ተጠቀመ ቢባል ትግራይ ነው። ልብ ያላቸው ልጆች ስላሉት። እንጂ ሦስቱም ቦታ ልጆቹን ገብሯል። ኑሮውን ገብሯል። እርግጥ ነው 27ዓመት መሉ አንድ የተጋሩ ትውልድ በተገኘው ዕድል ሁሉ ልዩ ጥንቃቄ እንክብካቤ ተደርጎለታል። ለከፍተኛ ትምህርት የተላኩት፤ ተምረው ምርጥ ቦታ ያያዙት በሚገርም የተደራጀ እና የተቀናጀ ባስተዋለ ተግባር ነው። ለሥነ ልቦናው የተደረገው ጥንቃቄ በራሱ ረቂቅ ነው በምንም ሊመነዘር የማይችል። ራሷ ትግራይ ከተማ ሌላ አገር ነው የምትመሰለው። ይህም የራስ ወገን ስለሆነ በተዛብም፤ ባልተመጣጠነ ኢኮኖሚም ቢሆን በቅንነት ማዬት ይገባል። ቢራቡ ቢጠሙ ማዘናችን አይቀርም አያት ቅድመ አያቶቻችን ያዝኑ እንደነበረው። 

ጦርነት ቢመጣ ደግሞ ተጠቀመ የሚባለውም የትግራይ አስፓልት እና ህንፃ ይወድማል። ሰው እኮ የሃብት ሃብት ነው። ስንት ዘመን ነው የትግራይ፤ የወሎ፤ የጎንደር እናት ልጇን ማግዳ የምትኖረው። አያብቃም ወይ? አትማሩም ወይ የሦስቱ ክ/ አገራት እናቶች። በዛ ሰሞናት አንዲት የትግራይ ሊሂቅ ልባም መልክት አሰተላልፈው ነበር። እሳቸው የትግራይ መስተዳድር ፕሬዚዳንት ቢሆኑ እንደ እኔ ትግራይ ወደ ህሊናዋ ትመለስ ነበር። ባልተገባ ወኔ ጉሮሮን ለማድረቅ ፉከራውም ተግ ይል ነበር። ወኔ እኮ ውጭ ለመጣ ጠላት እንጂ ለክፉ ቀን በሆነ ወገን መሆን አይገባውም ነበር።  

ጠ/ሚር አብይ አህመድ ብልህነት ደግሞ የጠቀመው ከሁሉም በላይ በዛ ሥርዓት የበለጠ ቀዳሚ ተጠቃሚ ለነበረው ለተጋሩ የማንፌስቶ አባልተኞች ነው። ይህ ባይሆን ዕዳው ከባድ ነበር ለማወራረድ። ስለሆነም አብይ መላዕካችን ሊባል በተገባ ነበር። ግን ከዛ መንደር ይሉኝታ ማተብም የለም። ቢሆንማ ጎንደር ያን ያህል ባልተቀጠቀጠ ነበር። ለካንስ ወልቃይት ለጉምዝም ተሸልሞ ነበር? አዬ የጥላቻው የበታችነቱ ዓይነት ልክ እኮ የለውም።  

በ27 ዓመቱ የዘመናይነት ዘመን ከባድመ ጦርነት ውጪ ትግራይ ሰላም ናት። አሁን እንኳን መቼም የማይታመስ አካባቢ የለም ሊሂቃኑ መቀሌ ላይ ሆነው በሚያዘምቱት የቀዝቃዛ ጦርነት ሴራ። 2ሚሊዮን ህዝብ አይሆኑ ሆኖ ሜዳ ላይ ፈሷል። ለትግራይ 1/3ኛው ህዝብ የሚያክለው ማለት ነው። ትግራይ ልማት ላይ ናት። ትግራይ ብርሃን ላይ ናት ሙሉ 27 ዓመት። ጎንደር እና ወሎ ደግሞ አሳርን መከራ በዬዘመኑ ልክ ሲቀበሉ ኑረዋል 50 ዓመት ሙሉ።

አሁን ጎንደር እና ወሎ ያ ዘመን ያሸከማቸውን መከራቸውን እንደ ተሸከሙ፤ በጦርነት ድቅቅ እንዳሉ ድህነታቸውን ጉስቁልናቸው እንዳዘሉ ዘመኑ ግን ተለውጧል። ዛሬ ሁሉም እኩል ነው በመብትም በግዴታም። በመብትም በግዴታም እኩል ተጠቃሚ ለመሆን ደግሞ ሰላም ወሳኙ ነገር ነው።

በዚህ ዘመን አንዱ የክት ህዝብ ልዩ ጥበቃ የሚደረግለት፤ ሌላው የዘወትር ሳንጃ የሚመዘዝበት ወይንም ዘር ፍሬውን የሚንኮላሽበት፤ ወይንም ዘሩ የሚመክንበት ወቅት አይደለም። አሁን ሃላፊነት የሚሰማው መንግሥት አለን።

ለእኔ ሁሉም እናት አለው። እናቶች በዬዘመኑ ማልቀስ የለባውም። ስለዚህም ነው የሰላም ሚ/ር ከዓለም በተለዬ ሁኔታ የተቋቋመው በዘመነ ዶር አብይ። ለዚህ ሰላም መቀጠል ከሁሉ በላይ የጎንደር፤ የወሎ፤ የትግራይ እናቶች ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም ቀጥተኛ ተጎጂዎች እነሱ ስለሆኑ። ያ የተፈጥሮ አቀማመጣቸው እጅግ ጎድቷቸዋል። ምሽግነት ቀብሯቸዋል። እርግጥ ነው ትግራይ እና ወሎ በላፉት 27 ዓመታት ምሽግ አልነበሩም። ስሜን ጎንደር ግን መከራውን በ አንድ ክብዱ ተሸክሞ ለዚህ ዘመን አድርሷል። አመስጋኝም ባያገኝም። 

ትግራይ እንኳን ተክሳለች። አካካሱ ሌላ አሳሳቢ ቀጣይ ዕዳ ቢኖርበትም። ዕዳውን ለማወራረድ ባይቻልም እንኳን ይህን ረገብ ለማድረግ የአብይ መንግሥት ያለው ትህትና ሊደመጥ ሲገባ እንደ ጠላት መቆጠሩ ግን ያላዩትን መናፈቅ ይመስለኛል። እንደ ህውሃት ያለ ኢ - ሰብአዊ ድርጅት እኮ ዓለም በዓዋጅ ነው ማፍረስ የነበረበት። ጀርመኖች ያደረጉት ይኽንኑ ነው። ያን ለማካካስ ያወጡት መዋለ መንፈስ እና ንዋይም እጅግ ብዙ ነው -ጀርመኖች።

መቀሌ ላይ የሆነውን ሁሉ አይቻለሁኝ። የዛን እልህ ደግሞ ያህል ደግሞ ጎንደር፤ ወሎና ጎጃም መድገም የለበትም። በእልህ ትውልድ አይበቅልም። እልህ ቁጭት ብስጨት ትውልድን በአዎንታዊ ትውፊት አያሰብልም። ዛሬም በዛ የዲርቶ ኑሮ ዳስ ውስጥ ስለሚማራው ልጅ ማሰብ ይገባል። 



ዛሬም ውሃም ኤሌትሪክም የማዬገኘው ህዝብ ሊጸጸትን ይገባል። ዛሬም በሰላም እጦት ትምህርት ቤቶች ሲቋረጡ ሊያንገበግብን ይገባል። እና ይህ ይሆን የሚናፍቀን? ከሦስት መቶ በላይ ት/ቤቶች በድንኳን በአማራ ክልል ልጆች እንደሚማሩ መረጃ በዛ ሰሞን ሰምቻለሁኝ።

·       ትዮጵያዊነትን  እንክብል ኪኒን ለክብርቷ።  

… እርግጥ ነው ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም ኢትዮጵያዊነት ክኒን በእንክብል መልክ ያስፍልጋቸዋል። እያጋገለው ያለው የእሳቸው ያልተገባ ዲስኩር ነው። ቦታውም ሃላፊነቱም ፈጽሞ አልገባቸውም። መቀሌ ላይ ያሉ ይመስላቸዋል።



ሌብነት ማዕረግ አይደለም። ወረራም ግርማ ሞገስ አይደለም። ሌብነት ይሁን ወረራ የሚታፈርበት ገመና ነው። ገመናው ደግሞ የሁሉም ነው እኛም እንፍርበታለን እንደ ትውልዱ አባልነታችን። እንደሳቸው ወ/ሮ ሙፍርያት ካሚል አሉ ትልቅ ቦታ ያላቸው። ክብርቷ ኢትዮጵያዊነታቸው ላይ ነው እዬተጉ ያሉት፤ በመጸህፍት ህይወት ንግግር ጠ/ሚር አብይ አህመድ ጠ/ሚር ሳይሆኑ ያደረጉትን መሰል ንግግር ሰሞኑን እንዳደረጉ ሳዳምጥ መልሼ የተፈጠርኩ ያህል ነው የተሰማኝ።

ሌላም ላንሳ ወ/ሮ አዳነች አቤቤንም ማንሳት እሻለሁኝ። እንደ እኔ በሚኒ/ር ደረጃ ኮከብ የሴት ሚኒስተር የመሆን ዕድላቸው ሰፊ ነው። የኦነግ ድርጅቶች ክንፎችም ባላባቶች ባለሟሎች እንዲሁም ኦፌኮንም ልከል በ50 ዓመት ውስጥ ይህችን የመሰለች ፍሬ ዘር አንስት አልፈጠሩም፤ አላበረከቱም። ኦዴፓ ግን ትምክህት ሳይሆን እጅግ የሚመስጡ ይጨርስላቸው እንጂ ተመስጦ የሆኑ በዚህ ዘመን የኢትዮጵያን በቁሟ ማለቋ ላይ ተግታው እዬሰሩ ያሉ ድንቂት ኢትዮጵያዊት ሊሂቅን እያዬን ነው። 

በካቢኔ ሚ/ር ሹመት ጊዜ እኔ የተደስትኩበት ብዬ በወቅቱ ጽፌበት ነበር። እንደ ዓይኔ ብሌን ስለማያቸው የቡራዩ የሻሸመኔ ጊዜም እንዴት እርሰዎ እያሉ ይህ ኢ - ሰብዐዊነት ድርጊት ተፈጸመ ብዬ ጽፌ ነበር። ስለምን? እምነት ስላለኝ። የፈለገ ይከፋኝ ለወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም ግን ምንም ዓይነት አቤቱታ አላቀርብም። ከሳቸው መንፈስ እምጠበቀው የሚዛን ፍትህ ስለሌ። ያ ቢሮ መቼም ሰው ወጥቶ አያውቅበትም አሁን እሬሳ ሃሳብ ተሸከም ተብሎ ተፈርዶበታል። ትንሽ ለአንደበት መግቻ ቢበጅለት እንኳን መልካም በሆነ ነበር።

„የወልቃይትን ለወልቃይት ህዝብ ተወት“ ይላሉ። የሌላውንስ ስለምን እንደዛ ብለው አይተውቱም። ወልቃይት ማለት እኮ እኔንም ይደምራል። በስደት እንዴት አድርገው ቁስል እንደሚያደርጉኝ ማን በነገረልኝ ለዛውም ደግሞ ያን የተከበረ የእስልምና ልብስ ለብሰው ነው እንደዛ እንዳሻቸው እሚፈነድቁት። እኔ አንስት የእስልምና እህት ይህን የከበረ ልብስ የለበሰች እንዲህ ሌብነትን፤ ወረራን ስተጸዬፍ እንጂ ስታበረታታ አይቼ አላውቅም። ለስጋቸው እንዲህ የሚያድሩ ያ የክብርን ልብስ ምን አለ ክብሩን ሳያዳፈሩት ቢቀር?

 ሁላችንም እኮ ወገኖች አሉን የእስልምና ዕምነት ተካታይ የሆኑ ሃጂዎችም ሼኽዎችም።  
ክብርቷ ከቀደሙት የህውሃት የጫካ መናፍስት ውጪ የተለዬው አልባሳታቸው ብቻ ነው። ስለኢትዮጵያዊነት ለመስራት ዝግጁ አይደሉም። ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ግን የቀደሙ የድንቆችን የጀግኖች ጀግኖች የእነ ኮ/ አብዲሳ አጋን አደራ ተረከበው ያን ፈለግ በመከተል አድባራቸው፤ ታቦታቸው ህሊናቸው ኢትዮጵያ ሆና ነው እማዬው። በንግግርም ቁጥብ ናቸው። እላፊ አይሄዱም። አያቆስሉንም። እንዲያውም ይፈውሱናል። 
  
ኢንጂነር ወ/ሮ አይሻ መሃመድን እንወሰድ የታምር በሚመሰል ሁኔታ ልዩ ክህሎታቸው እንዲያውም ኢትዮጵያ ማንን ትመስላለች ቢባል እኔ ወ/ሮ አይሻን ነው እምለው። መዳን ያልቻሉት ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም ናቸው። እሳቸውን ዞር ማድረግ አንድ ብልሃት ነው ለአብይ ካቢኔ። አሁን ላለው የፉከራ ማህበርተኛ ቁጥር መበራከት ዋንኛዋ ተጠያቂ እሳቸው ናቸው። ልክ አቶ ታዬ ደንዳአ ፌድራል ላይ ተቀምጠው የፌስ ቡክ ላይ እንደ ከፈቱት ትርምስ ማለት ነው። 

እኔ እራሱ እሳቸው ሲናገሩ ውስጤ ይጎዳል። ስለምን እትብት አይሸጥም አይለወጥም። ቢያውቁት በወገራ በር በገፍ ይገቡ የነበሩ ተጋሩ ደንቢያ ላይ የእርሻ ሥራ ለማገዝ ነበር። ወደ ሰቲት የሚሄዱትም ለጥጥ ለቀማ እና ለማሽላ ቆረጣ ነው። ያልሞቱ ያልታመሙ ቤተሰቦች እኮ አሉ ውጭ  አገር የዛን ጊዜ አራሽ የነበሩ። ያን ጊዜ የጉልበት ሠራተኛ ሸቃላይ ነበር ይባል የነበረው።

ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም እሳቸው የዛሬ 50 ዓመት ላይ ሆነው የወያኔ ሃርነት ማንፌሰቶ የታላቋን ትግራይ ህልም አሳካለሁ ብለው በተነሱ ቁጥር አገር እዬተናደ እንደሆን አላወቁትም፤ ጦርነት የሚያሳውጁት እሳቸው ናቸው። የፌድራል ሃላፊነት ተረከበው የታላቋን ትግራይ ህልም ስልጣን ወደ መንበሩ ለማምጠት የመንፈስ ብተና ተግባር ያሟላሉ፤ አማራነት እንዲከር የሚያደርጉት እሳቸው ናቸው። እመ ቆስቋሽ ናቸው። ተልዕኮም የተሰጣቸው ይመስለኛል። 

መንፈስ እዬተረተሩ፤ መንፈስ እየበተኑ ነው ያሉት። ስለምን? አማራ ለአብይ መንፈስ ልዩ ፍቅር እና አክብሮት ስላለው። ሆን ብለው አቅደው ነው እዬሠሩ የሚገኙት። ያን የተደራጀ የፍቅር መንፈስ ለመናድ። 

አንድ ነገር ቢፈጠር ጦሱ ከሳቸው እራስ አይወርድም። የታረመ ንግግር አያደርጉም። የዘር ጥፋት እኮ ከባሰ፤ ከባሰ እኮ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንዲያው ይደረጋል። ቀልድ አይደለም ወልቃይት ጠገዴ ላይ 43 ዓመት ሙሉ የተደረገው።

ለነገሩ የገበሬን ጀንዴ ለሚሰርቅ ሌባ ጥብቅና ከመቆም በላይ ምን የሚያሳፍር ነገር አለና? ቀድሞ ነገር አንድ ተብዕት 12 በላይ ሴቶች ጋር የፆታ ጥቃት ከመፈጸም በላይ ምን አንገት የሚያስደፋ ነገር አለን? ለዚህ ናዚያዊ ተግባር ሊሸማቀቁ፤ ሊኮማሸሹ ሲገባ ወንበሩ ተገኜ ብለው እልፊ እዬሄዱ ነገሩን ያካሩታል ወ/ሮ ኬሪያ።

አላወቁትም ሲከር መበጠሱን፤ ሲሞላም መፍሰሱን። አማራ መሬት ላይ ሁሉም ቦታ የአብይ ፎቶ እንዳለ ነው ከዛ ደርሰው የሚመጡ የሚነግሩን፤ ያን ነው እሬት እዬቀቡት ያሉት በስውር ቡርሽ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም። የ ጠ/ሚር አብይ ካቢኔ ደግሞ ይህ የውስጥ ጥቃት አፈጻጻም ያሰተዋለው አይመስለኝም።

አሁን የእነ አርበኛ መስፍን ተስፉም ንግግር ያን መሰረት ያደረገ ነው። ሴት ሆኖ እንዴት ጦርነት ይናፍቀዋል? ምን አለ በ50 ሺህ የአሮሞ እና የአማራ ወጣት ፍዳ እሳቸው የፌድሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው ከጠ/ሚር አብይ አህመድ ጋር እኩል ወሳኝ ሆነው ተቀምጠዋል።

እሳቸውንም ሆነ አዲሱንም ካቢኔ ወደ ስልጣን ያመጣው ያ ገናና የጎንደር የአማራ የህልውና  የበቃኝ አብዬት ነው። 20 ሺህ ወጣት ታስሮበታል። መቶዎች አልፈውበታል። አካላቸውን አጉድለውበታል። ትዳር ተፈቶበታል፤ ኑሮ ተበትኖበታል። ያፈራቀቁትን የ ኦሮሞ እና የአማራ መንፈስ አህዳዊ አድርጎበታል።

 መልሱ ቱማታ ይመለስ አይደለም። አንደበትን መከርክም ግን ያስፈልጋል። በቆሰለ ሥነ ልቦና ላይ ባልተወለደ አንጀታቸው ዲዲቲ መበተን አይገባቸውም። አንድ የነደደው አርበኛ ብዙ ግድፈት ሊፈጽም ይችላል። ዛሬ ሰው ሳቢያ ነው የሚፈለገው። የጎንደር ቅዳሜ ገብያ የጎንደር ከተማ የመሰረተ ታሪክ ነው። ቤተሰቦቻቸው ቤንዚን እና ክብሪት አስይዘው አቃጥለውታል። ይህን ታግሶ የተቀመጠን ታጋሽ ህዝብ ባይቆሰሱሱት ይሻላል። በኋዋላ የፈሰሰ ያልታፈስ እንዳይሆን …  አንደበታቸው ቁጥብ ሊሆን አልቻለም። በጣም ይተላለፋሉ።

ለነገሩ የህግ ተርጓሚነት ቦታ ህግ ላልተማሩ መስጠቱም የተጋባ አልነበረም። አሁን የባለሙያዎችን ጥናት በምን የህሊና አቅማቸው ይሆን ሊፈትሹት የሚችሉት?  እኔ እሳቸውን ብሆን ስልጣኑን በፈቃደኝነት ነበር የምለቀው። ህዝብ ጠላ እግዚአብሄር / አላህ ጠላ ነውና። ዛሬ ያለው ትውልድ ደግሞ ከባድ ነው። እሳቸውም ገና ወጣት ናቸው ስለምን ከግራ ፍልስፍና ጋር መጣበቅ እንደፈለጉ አላውቅም።

እስቲ እህቶቻቸውን ይዩ ምን እዬሠሩ እንዳሉ ሳይሆን በውስጣቸው ለኢትዮጵያዊነታቸው የሰጡትን ፋይዳ እና ክብር። እነሱ የሚሠሩት ማለቴ ክብርት ኢንጀነር ወ/ሮ አሻ መሃመድ፤ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፤ ክብርት ወ/ሮ ሙፍርያት ካሚል ስለኢትዮጵያዊነት ነው እዬተጉ ያሉት፤ እሳቸው ደግሞ የሚሠሩት ለትግራዊነት ነው ላታላቋ። ለነገሩ አቅል የደም ጉዳይ ነው። 

ስለዚህ በዬቦታው የፉከራ ማህበርተኛ ተበራከት። እሳቸው ሚዛን መሆን ይገባቸው ነበር። ግን አልሆነም። እሳቸው ቤንዚን ሆኑ፤ ጭዱን መቀሌ ያቀበልላል ሌለ ፉከራ ደግሞ አማራ መሬት ላይ አለ። 

·       ሰላም ትውልድ ነው! 

እኔ ከሽምቅ ውጊያ ለተመለሱት የጎበዝ አለቃ አርበኞች እምናገረው ሰላምን መርጦ የመጣ ወገን የመሳሪያ ጨዋታውን ማቆም አለበት። ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም አንድ ነፍስ ናቸው። አስቀረው ድርጅታቸው የማንነት እና የወሰን ኮሚሽን ዓዋጅ ከማጸድቅ? አላስቀረውም። ያ የዕውነት ቀበኛ ሥርዓት በጥበብ ስለተወገደ አሁን ዕውነትን የሚደፍሩ ጀግኖች ተበርከተዋል። 

·       ክነት በእኛ ይብቃ!

በሌላ በኩል ግን ጦርነት በቃን! የጎንደር የጦርነት አውድማነት የጠቀምን የለም። ዕድሜያችን በልቶ አባክኖ ነው ያስቀረን። ብክነት በእኛ ይብቃ!  ከእኛ ተከታዩም በአማራኑቱ በጎንደሬነቱ ባክኖ ቀርቷል። ተሰደን እንኳን መቀመጫ አጥተን ነው የምንኖረው። ጎንደሬም መሆን አማራም መሆን ግማድ መሸከም ነው። በህይወት መቆዬታችን ከፈጣሪ በታች እራሳችን ዘግተን አስረን በመቀመጣችን ነው።

የሆነ ሆኖ እንግዲህ ጎንደርን የጦርነት አውድማ ማድረግ ህሊና ቢስነት ነው። አብይ እኮ የጎንደር ጌጥ ነው! አብይን የሚተካ ጎንደሬ ጎንደር ፈጽሞ አልፈጠረችም! አብይ የዛሬ ሰው አይደለም። ኪጋሊ / ራውንዳ ሲዘመት በዓለም ሰላም አስከባሪነት ጎንደርን አብይ በውስጡ ሰንቆ ነው።

ሲመለስ ከ22 ዓመት በኋዋላ ጎንደር ትቢያ ተጎናጽፋ ሲያት ከማንም በላይ ውስጡ የተጎዳ የጎንደር አንድያ ልጇ የአብይ ነበር። አብይ እኮ ለጎንደር የሰማይ ስጦታ ነው። ይህን የምለው ዛሬ ዶር አብይ ጠ/ሚር ስለሆኑ አይደለም። ብዙም በፖለቲካው መድረክ ሥማቸው ጎልቶ ሳይወጣ ይሄን የዛሬ ዓመት ነው የጻፍኩት።

የተጻፈበት ዕለት 18.12.2017 ዙሪክ ሲዊዘርላንድ
የተጻፈበት ዕለት 24.12.2017

ጎንደር ተወልዶ አድጎ ስለጎንደር የጨነቀው ሊሂቅ በሉት አክቲቢስት በሉት አላውቅም። ጎንደሬ ለሌላ ሠፈር ምንጣፍ እና ጉዝጓዝ ሆኖ ሲያረግድ ነው የማውቀው። ዛሬም ይኸው ነው የሚደመጠው። በጎንደር መከራ ውስጥ ጎንደሬው ታዋቂ ተብዬው ሁሉ አልነበረበትም። 

የአብይ መንፈስ ግን ዕውነት ትጥቁ ስለሆነ ጎንደር ህሊናው ስለነበር ግርም ብሎኝ የዛሬ ዓምት በዚኸው ወር ነበር ይህን የጽፍኩት። በዓይኔ የመጣ ሰው ስለነበር። በዓይኔ የመጣ ከቶውንም የማይደፈር ሚዲያ ስለነበር። ልብ ይኑራችሁ - ጎንደሬዎች። የአብይን ካቢኔ አትወኩት - ጎንደሬዎች አርበኞች ሆናችሁ ነዋሪዎች።

አሁን እምሰማው ነገር አለ እነ ዶር አብይ አህመድ በህውሃት ሥርዓት ውስጥ የሠሩ ናቸው የሚል አዲስ ቋንቋ ደግሞ መጥቷል። ለሄሮድስ መለሰ ማን ከጎንህ አይደለንም ብሎ ነውና ቀድሞ ነገር? ያን ጊዜ አብሮ ለመስራት ማን ያልተጣደፈም ኑሮ ነውና ቀድሞ ነገር? ሁሉም ልኩን ሲያውቅ ነው ልቡ የሸፈተው።

ሌለው ግን በአንድ ሥርዓት ውስጥ መስራት ግድ ይላል። 90/ሚሊዮን ህዝብ ልሰደድ ቢል አይችልም፤ ጫካ ልግባ ቢልም አይቻለውም። መከራን ተጋፍጠው ራሳቸውን ቀቅለው ውስጥ ሆነው ታግለው ዛሬን ያበሩ ጀግኖች ናቸው እነዚህ ፈርጦች። ከቶውንም ከሌሎች ነገሮች ጋር እያለካለክን መንፈስ ባንበትን መልካም ነው። እነሱ ባይኖሩ እንደ ግብጽ አብዮት አንድ ጉልበተኛ ነበር የሚፈንጭበት።

የትኛውም የፖለቲካ ድርጀት ተፎካካሪ/ ተቃዋሚ/ ተቀናቃኝ የሚባለው ተጠቃሎ አንድ ቢሆን የእነሱን ያህል ብልህነት እና ጥበብ የለውም። ሃሳብ እራሱ የደረቀባቸው ናቸው። የመፍትሄ መንገድም አልነበረም። አፍርቶ ዘልቆ የታዬ የመስዋዕትነት ዘርፍ ቢኖር የአማራ ታገድሎ እና የኦሮሞ ንቅናቄ ብቻ ነው፡፤ ለዚህ ትልቅ ጆሮ የጸደቀ ብልህ ህሊና ያላቸው ሊሂቃን ስላገኜ። ለመሪነት ብቁ የሆኑ ፈርጦች ስለተገኙለት።

ቁጣ በመጣ ቁጥር የሚናደው ይሆን እንደ ጀብዱ የሚቆጠረው? ወይንስ ህዝብ ለሰጠው ፍቅር ዘረጋግግፎ መበርገግ ይሆን ጀግንነተቱ? ሌላው አገር ቤት ያሉት የማያውቁት ነገር አለ። እዚህ እኛም ታስረን መኖራችን።  እዚህ ያለነው ቃሊቲ፤ ቂልንጦ ቢኖር ድራሻችን አይገኝም ነበር።

ምን ለማለት ነው ጎንደሬዎችም የፖለቲካ ሊሂቃን አስበውለት አያውቁም ስለጎንደር ከዶር አብይ አህመድ በስተቀር ጎንደር ማንን የለውም አልነበረውም። ለጎንደሬዎች ጎንደር አጀንዳቸው አይደለም። አጀንዳ የሚፈለገው አሻጋሪ ድልድይ እንዲሆን ብቻ አንጠፊ እና ጋሻ ጃግሬ እንዲሆን ብቻ ነው። ዛሬም መለከቱ ይኸው ነው። 

ለጎንደር ህዝብ ግን ከአብይ መንፈስ በላይ ተስፋ እና ጌጥ የለውም። አብይ ኬኛ የማይታጠፍ ቃል ኪዳኔ ነው! እርግጥ ነው እንደ ህዝብ ጎጃም ዋርካው አለለት ለጎንደር። ተመስገን! ሁሉ አጀባኒቱ ትናንትን ዛሬም ለየትኛው አካል እንደሆነ ይታወቃል። አብይ ኬኛ ዘመን የማይሽረው የህሊና ታቦቴ ነው። ጎጃምም ሃይማኖቴ ነው! ጎንደርም ልብ ይኑረው።

 ለአብይ ካቢኔ ደጀኑ፤ ወታደሩ፤ የመንፈስ ጠባቂው፤ የፍቅር አልፍኙ ሊሆን ይገባል - ጎንደር ሆነ ጎጃም - አማራ። የአብይ መንፈስ ብቻ አይደለም ለደጉ ለለማ መንፈስም እንዲሁ። እንዲያውም ጎንደር ለቅኔው ለዶር ለማ መገርሳ እና ለጎጃም ህዝብ የምስጋና ቀን ሊያዘጋጅ ይገባዋል። እርጋ ያለው የለማ መንፈስ ነው። የለማ መንፈስ የዕድምታ ባለሙያዎችን ይጣራል ለትርጉም። ለማ ዘመን ነውና!

·       ዛሬ ባለቤት አለው።

ኢትዮጵያ መንግሥት አላት። የመንግሥትን ተግባር ለመንግሥት መተው ነው። እንደልቡ መሆን አይገባም። ከእላፊ ንግግርም በጣም መታቀብ ያስፈልጋል። ያን ሁሉ መከራ ያሳለፈ ህዝብ አሁን ደግሞ ለሌላ ማገዶነት ወጣቱን ማንሳሳት ፈጽሞ የተጋባ አይደለም። ሰላሙን አታውኩት! ጀግንነት ማለት ብልህነትም ማለት ነው። ጀግንነት ማለት ማስተዋልም ማለት ነው። 

2 ሚሊዮን ወገን የተፈናቀለው እኮ የራስ ወገን ነው። እና የምን ሩምታ ተኩስ ነው? የምን ጥጋብ ነው? ጎንደር ከተማ መሰቀል አደባባይ ላይ ተኩስ? አይበቃም ወይ? አይሰለቻችሁም ሞት እና እልቂት? አያንገሸግሻችሁም ያ የጨለማ ዘመን? መር የለም? ሽማግሌ የለም? የምን ተኩስ ነው?

ሃሳብ ነው ያለው። የሃሳብን ክፋት በጥሞና በበሰለ ሃሳብ ነው የሚረታው። ጠበንጃ አመደ ትርፉ ነው። ከጠበንጃ አትርፎ የሚያውቅ የዓለም ዜጋ የለም። ከጠበንጃ አትርፎ የሚያውቀው ቂም በቀል ብቻ ነው። ቂም እና በቀል ደግሞ ትውልድ አያበቅልም። ምን አለ ብትታገሱ። 27 የጨለማ ዓመት እኮ ተኑሯል።

ልማት ቀረ፤ መብራት የለም፤ ውሃ የለም። ት/ቤት የለም፤ መንገድ አልተሰራም። ዛሬ ሰላም ከሌለ ትውር የሚልባችሁ የለም። አሁን በዛ ሰሞን አትሌት ሃይሌ ገ/ሥላሴ አንድ የሆቴል ፕሮጀክት እንዳለው አዳምጫለሁኝ። ሰላም ከሌለ ጥሎት ይሄዳል።

መጪው አስተሮዬ ነው። የጎንደር ጥምቀት በዩኒስኮ ለማስመዝገብ ጥረት እንዳለ አዳምጫለሁኝ። እና ከታወከ እንዴት ይኮናል? አይጸጽታችሁም ዘመን ይዞ ከዘመን አማፂ መጣ በተባለ ቁጥር ምንጣፍ ድልዳል መሆን። ጦርነት ይናፍቃችሁ አሁን ደግሞ? ስለ እናንተ እኔ እንዴት እንደማፍር ማን በነገራችሁ?

አሁን የአብይን ካቢኔ ለማወክ ሌላ የጦርነት ጡርንባ መናፋት አለበትን? አይበቃችሁም? አይሰለቻችሁም? ምደሪቱ ምን አደረገቻችሁ? ምድሪቷን አሳርፏት።

ሰላም ያላቸው አገሮች ናቸው የሥልጣኔ ተጠቀሚ የሆኑት። ለእነሱ ሆነው ለእኛም መጠጊያ የሆኑት። ዛሬ ሲዊዲን፤ ዴንማርክ፤ ኖርወዬ፤ ሲዊዘርላንድ በተለዬ ሁኔታ የሰዎች መንፈስ ማደሪያ የሆኑት ለሰላም በሰጡት አክብሮት ነው።

አሁን እኔ ሲዊዝን ውድድ ከማደርገበት አንዱ እና ዋንኛው የጥይት ጮኽት አንድም ቀን አዳምጬ ስለማላውቅ ነው። ሰምቼ አላውቅም። ፈጣሪን ስለምነው የጥይት ጩኽት ከማልሰማበት አገር አድርሰኝ ብዬ ነበር። አሁን ለነፍሴም ለስጋዬም እርጋታ የሰጠኝ የባሩድ ሽታ ስለማልሰማ ነው። 

ጦርነት ክፉ ነው። ብዙ ነገር ነው የሚያሳጣው። ምን እንሁኑን ብላችሁ ነው አሁን እምትንደት? ምን አውር ብላችሁ? የወልቃይት፤ የጠገዴ ጉዳይ ህግ ይዞታል። ወ/ሮ ኬርያ እብራሂም እንዳሉት የወልቃይትን ጉዳይ ለወልቃይት ጉዳይ የሚተው ሳይሆን ጉዳዩን ዓለም አቅፉም ድርጅት ይዞታል።

በሌላ በኩልም ጉዳዩን አጥንቶ የሚያቀርብ ኮሚሽን በዓዋጅ አገር ቤት ተቋቁሟል። ምንድን ነው የምትፈልጉት ጎንደሬዎች አርበኞች? ህውሃት ያን ለማደናቀፍ ሳቢያ ይፈልጋል፤ እናንተ ደግሞ ለሳቢያው ብርድ ልብስ ሆናችሁ በዬስብሰባው ትፎከራላችሁ። ስታሳዝኑ? 

ብልህነት የሚባል አታውቁንም? በኛ ዘመን ያለው ወጣት በዘመነ ኢህአፓ መናህሪያ ሆኖ ታጨደ፤ በኢዲዩ፤ በከፋኝ፤ በኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር፤ በግንቦት 7 ፍዳ ተከፈለ። ይህን ያዬ በቃችሁ ሲለን ፈጣሪ አንድ የተቀባ ሰው ፈጠረ ኮ/ ደመቀ ዘውዱን ምክንያት ሆነ በቃችሁ ሲል የአማራ የህልውና አብዮት ፈነዳ የሆነው ሆነው። እዮር አዳመጠ ዘመኑን በአጭር ጊዜ ውስጥ ባልተሳበ ሁኔታ ቀዬረ።

አሁን ትግሉ ወደ ነበርንበት እንመለስ ነው ወይ የአሁን የጥይት ሩምታ? ያልገባኝ እንዲገባኝም እማልፈልገው ይኸው ነው። አንድ የጎበዝ አለቃ አርበኛ በገባ ቁጥር የረጋ ነገር እዬተገፋ ሌላ ትርምስ መፈጠር አለበት ወይ? ለትውልድ ይታዘን። የእኔ ትወልድ ባክኖ ቀረ። ከእኔ የቀጠለውም እንዲሁ ባክኖ ቀረ። አሁን ደግሞ ለሦስተኛ ትወልድ በሰላም አገር ጦርነት ይታወጅለታል? አንዲት የፖለቲካ ሊሂቅ፤ አንድ የፖለቲካ ሊሂቅ ማፍራት አልተቻለም። አይከነክናችሁም ይህ?

እስኪ ከዛ ሰፈር፤ ከዛ ባዕት አንድ ቀና ብሎ የወጣ፤ በቴሌቪዥን ወጥቶ አቅም ያለው የሚደመጥ ፖቲከኛ አንስት ይሁን ተባዕት ወጣበትን? ይህ አያንገበግባችሁም ወይ? ይህ አያቃጥላችሁም ወይ? ሰው መክኖበታል ጎንደር? አዋቂ የለውም ጎንደር? አሁን ታዳጊ ከሚባሉት ክልሎች ስንት ሰዎች አሉ የሚታዩ የሚጨበጡ የሚዳሰሱ ጎንደር ግን ፍልሰት ነው እኔ እማዬው?

በሦስት ትወልድ አንድ ነፍስ ያለው ህሊናው የፋፋ ሞግቶ የሚረታ በሃሳብ በሳል አሰተዋይ ጎርፍ ያልሆነ - ጤዛ ያልሆነ - የሳሙና አረፋ ያልሆነ - ብልህ ልብ ያለው ማውጣት አልተቻለም።

ያ የባከነው ትውልድ አልበቃ ብሎ አሁን ደግሞ በዚህ ዕድል ተጠቅሞ ተምሮ እንዲያው ለዛሬ 20/30 ዓመት አንድ እንደ ወልዴ ቢወጣ ብትወጣ ህልም ቢሳካ እንኳን ዛሬ ከታወከ አይቻልም? እንደተለመደው መክኖ ወና ሆኖ መቀረት ነው።

 ጎንደር አንድ ሚ/ር አለው ወይ? አንድ የካቢኔ አባል አለውን? በደርግ ጊዜም አልነበረውም፤ በህውሃት ጊዜም አልነበረውም፤ በአብይ ጊዜም የለውም ለምን? ወኔ ብቻ? ለዬዘመኑ የጦርነት ነጋሪ ብርንዶ አቅራቢ ስለሆነ ጎንደር። የመጣው መንግሥት ሁሉ በጥርጣሬ ይመከተዋል። የአሁኑ የአርበኞቻችን ጥሪም ይኸው ነው። እነሱም ይረፉ ትውልዱንም አሳረፉት እባካችሁ። ልጆች ስለትምህርታቸው ይሰቡ። ወላጆችም ሰለ ልጆቻቸው።

·       ምርቃት ካለወቁበት ይነሳል።

ዓላማ ግቡን ከመታ ምን ያስፈልጋል? ህውሃትን ከሙሉ አራጊ ፈጣሪነት ማወረድ ነበር ተጋድሎው ያ ሁኗል። በሰው ጥበብ አይደለም በፈጣሪ እርዳታ ዓላማው ግቡን መቷል። ምርቃት ካለወቁበት ይነሳል። እንደዚህ ዘመን ጎንደር የምርቃት ዘመን ገጥሞት አያውቅም። ፈጽሞ።

የፈለገው ዓይነት ጥያቄም ቢሆን ዘመን ጊዜ ይፈታዋል። ስለምንድን ነው ጎንደር ጠ/ሚር አብይ አህመድን ካቢኔ የማያምነው። ለምድን ነው ለአብይ ካቢኔ ታማኝ እማትሆኑት? አንድ የአገር ጠ/ሚር በ7 ወራት ውስጥ ስንት ጊዜ ነው ጎንደር የመጣው? አይገባችሁም? ህሊናችሁን ማን ቀማችሁ? በአንድ ወር ውስጥ እኮ ምክትል ጠ/ሚር አቶ ደመቀ መኮነን ሁለት ጊዜ ነው የመጡት።  እግዚአብሄርን አታማሰገኑም። ማን ይህን ያህል ክብር ሰጥቷችሁ ያውቃል በድፍን 27 ዓመት ሙሉ። ማን ይነገርልኝ ይሆን ከቶ ይህን ዕውነት?!

·       ነፃነትን ማወቅ።

ሌላው አማራነት ነው። አማራነት ብርቅ ሆኖባችኋዋል። ይገባል። ስለምን አብረነው ስላልኖርን። አቅብጠነው አቅልጠነው ስላማነውቅ። ነገር ግን ፍቅር በልክ ሲሆን ነው የሚያምረው። ማርም በልክ ሲሆን ነው የሚጣፍጠው። ከልኩ ሲያልፍ ይመራል። ያ አማራነትን የጨቆነው ሥርዓት ፈርሷል። ተደግሞ ያ ጥቃት አገግሞ እንዳይመለስ ስክነትን የጠዬቀ ተግባር መከወን የአባት።

ለዚህም በዓይነት ድርጅት አለ። ራሱ ኮ/ደመቀ ዘውዱ ድርጅት ነው መንፈሳቸው። ኮሜቴ አለ። በቃ ድርጅት ካለ ለዛ ማንነት፤ ክብር፤ ትውፊት ይተጋል - በበሰለ የፖለቲካ አቅም። ከዚህ አልፎ ተርፎ ግን ጣሪያ ማስነካት በፍጹም የተገባ አይደለም። ልክ ያስፈልገዋል።

ነፃነትን በወጉ  በአግባቡ መያዝ ያስፈልጋል። ነፃነት ለማግኘት ስንት ተከፍሎበታል። ድሉ የራሱ የአማራው ነው። ስለዚህ አማራው ድሉን ካወከው ድሉን ቢያጣ እንጂ ድሉን ሊያስጠብቀው አይችልም። „ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳል“ ይሉ የለንም ጎንደሬዎች።
ይህ ድል ቢጨናጎል እንደለመደብህ ትታደናለህ/ ትታደኛለሽ። ወዮ! ነው የዛን ዕለት።

 ትግራይ ላይ የመሸገው ህውሃት ሽንፈት ስለገጠመው ነው። ቢፎክርም ይገባዋል። ሳቢያ የ አብይን ካቢኔ ጦርነት ለመክተት ቢፈልግም ይገባዋል። የጎንደር አርበኛ፤ የአማራ አርበኛ ግን ምን ቀረብኝ ብሎ ይሆን የሚፎክራው? "ሙያ በልብ" ሲሉ ጎንደሮች ለላንቲካ መሰላችሁን?

አንድም ሊሂቅ ዛሬ ካለጠባቂ አይሄድም የህውሃት ባለስልጣን የነበረ። እናንተ ግን እንዳሻችሁ ትንፈራሰሳላችሁ። ይህ ታዲያ ድል አይደለንም? ሰለሆነ ነው የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ በሙት መሬት ላይ ሆኖ በተልዕኮ ጦርነት ክሎችን ሁሉ ሲያተራምስ የባጀው። አሁን የቀረው ሀረሪ ብቻ ነው። አማራ መሬት ሳቢያ ፈልጎ ጦርነት መለኮስ እና የ አብይን መንግሥት ማሳጣት፤ ድሬድዋ ላይ እዛ የቀበረው ፈንጅ ጊዜ ጠብቆ ይፈናዳል ወይም የአብይ ፈንጅ አጥማጅ መንፈስ ቀድሞ ያመክነዋል።

ዛሬ ፈጣሪ የሰጠው ጸጋ አላመሰገን ብሎ አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል ሆኖ ነው እንጂ … ገዢ መሬት ላይ ያለው ነፃነት ነው። ስለዚህ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ የትም ላይ ሆኖ ቢያቅራራ ለዛውም ሙት መሬት ላይ ሆኖ ቢፎክር አልፎ ተርፎ ሌላ ቦታ ጦርነት ቢያቀጣጥል ያጠውን ለማስመለስ ነው። ከሚሊዮን በላይ ህዝብ በጅጅጋ፤ በሙያሌ ተፈናቅሎ አትኩሮታቸው ዶር ለማ መገርሳ የህውሃትን ሥርዓትን ከመንቀል ላይ ነበር። ይህ ረቂቅ ነው ለማንም አይታዬውም።

ስለሆነም አማራ ድሉን ለማስጠበቅ ሰላሙን ለማስጠበቅ ነው መትጋት ያለበት። መሰከን አለባችሁ። ስክንት ጎድሎባችሁዋል። ሁሉንም በልክ መያዝ። ደስታንም ቢሆን በልክ። የተንጠራራ ነገር አልወድም እኔ። መታበይም አባቶቻችን / እናቶቻችን አላስተማሩንም። ከሁሉ በላይ የእዮር ምርቃት እንዳይነሳ ስጋት አለብኝ። እፈራለሁኝ።

እሰቡ እንጂ 20/ 30 ሺሕ የትግራይ ልጆች እኮ ጎንደር አሉ። ወገኖቻችሁ ናቸው። ለምን ታሸብሯችሁ አላችሁ። ጫና አትፍጠሩባቸው! ይሰጋሉ። ተረጋግተው ይኑረ። ለምን ይሰጋሉ? የእነሱን ሰላም የመጠበቅ ግዴታ አላባችሁ - ጎንደሬዎች። ውሻ ነው በቤቱ የሚኮራው። ጎንደር በሥነ - መንግሥት ፍልስፍና ነው የኖረችው። መዲና ናት ጎንደር ለሁሉም ዜጋ። ትውፊት ይጠበቅ! ፈርሃ እግዚአብሄርም ሊኖር ይገባል፤ ቂም አስፈላጊ አይደለም። በቂም አገር አይገነባም።

·       ክወና።  

ከሁሉ በላይ በላይ ኢትዮጵያዊነት መከፋት የለበትም። በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ሲኮን ማስተዋል የሚያሰብለው። ይህን ሊያሳጡን የሚታገሉ ስሜቶችን ሁሉ ታግሎ ማሸነፍ ያስፈልጋል። 27 ዓመት ሙሉ ተሰዶ የኖረው መንፈስ ወደ ባዕቱ ለመመለስ እያንዳንዱ በግል ሁሉም በጋራ ራስን ለማሸነፍ መትጋት ይኖርበታል። ይህን ማድረግ ከተሳናችሁ መስጊድም ቤተ እግዚአብሄርም አትሂዱ። 

„አቤቱ ከንፈሮቼን ክፈት፤ አፌም ምስጋናህን ያወራል።“
   (መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፶ ቁጥር ፲፭)
 

ሰላም ህዝብ ህሊና እና መንፈስ!
ሰላም ለአብይ ካቢኔ!

የኔዎቹ ኑሩልኝ። መልካም የአዲስ ዓመት ዋዜማ!



አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።