ለበደል ፕሮፖጋንዲስት አያስፈልገውም። ለበደልም የፖለቲካ ተንታኝ አያስፈልገው። በደሉን የሚመክት እራሱን በዲስፕሊን ያረቀ ተቋም እንጂ።

ለበደል ፕሮፖጋንዲስት አያስፈልገውም።
ለበደልም የፖለቲካ ተንታኝ አያስፈልገው።
በደሉን የሚመክት እራሱን በዲስፕሊን ያረቀ ተቋም እንጂ።

 
የአማራን ሕዝብ በነፍስ ወከፍ በሩ ድረስ ሄዶ ቤቱን መቃብር ሲሆን፣ ጓሮው የራሱ አካል ሙት መንፈስ እና ሽታ ሲጎፈንነው፣ ቤተ እምነቶቹ ሲደፋሩ፣ ልጆቹ በፊቱ በማገጡ ሰብዕናወች እዬተሰደቡ ሲደፈሩ ………፣
ማሳው ሲነድ፣ የጤና ተቋሙ አመድ ሲሆን፣ የትምህርት ዓውዱ ሲወድም፣ አገልግሎት መስጫ ተቋማቱ በግፍ ወደ አመድነት ሲቀዬሩ፣ ተሰልፎ ሲረሸን፣ በአንድ ጉድጓድ በግሪደር በተቆፈረ ጉድጓድ ካለ ሃግ ባይ ሲያሸልብ፣
አትወልድም፣ አትከብድም ተብሎ ጽንስ ወጥቶ መላገጫ ሲሆን፣ ሰግቶ የሸሸውም አስፓልት አቆሸሽክ ተብሎ ሲንገላታ፣ ስብሰባ ተጠርቶ ሲረሸን፣ ሲታረድ፣ ጭካኔው፣ አረማዊነት አገር ምድሩን ሲያካልለው ዬፖለቲካ ሳይንቲስት፣ የማይክ ኤክስፐርት አያስፈልገውም። ችግሩ እራሱ ካሪክለም፣ ችግሩ እራሱ መፀሐፋ ነው። ምፅዓት የፊደል ገበታው የሆነ ህዝብ ቢኖር አማራ ብቻ ነው።
ቀለጤው ፖለቲከኛ ዬአማራ ሕዝብ አልተበደለም ይላል። እንደ ሽንብራ ቂጣ እዬተገላበጠ ዬእሱ ወገን ካልተሰቃዬ ለእሱ የድሎት ዕለቱ ነውና።
ዬሆኖ ሆኖ ግፍ በቃ ብለው ብቅ ዬሚሉትም በመደዳ ሲረሸኑ፣ ሲታገቱ፣ ሲታሰሩ፣ ሲሰወሩ፣ ሲፈረጁ ያያል፣ ይሰማል፣ ይኖርበታል ጭምቱ፣ ቅኑ ደጉ አማራ።
ይህን ሁሉ ግፍ ችሎ ደግሞ የሁሉም ጎደሎ ማሟያ አቅሙ፣ ፖለቲካው፣ ሥነ - ልቦናው፣ ትውፊት ትሩፋቱ ይሆናል።
ዬሰጠው፣ የቻለ ህዝብ የማይቻለውን ችሎ፣ የጭካኔ ሪሰርች እዬተሰራበት፣ እንደ ጥንቸል ቤተ ሙከራ ሆኖ ይወገዛል፣ ይረገማል።
አንድም ቀን ስለ እሱ ደፍረው ለመመስከር፣ በስቃዩ በመከራው ሁሉ ያልኖሩ፣ ያልነበሩ ደግሞ ማት ያወርዱበታል። ዬሚገርመው እዬተጫኑት መንበርህ ልሁንም አለበት።
ግን ፈጣሪ ለታምር የፈጠረው ሆኖ በእሱ ትክሻ ዬተንጠለጠለው ሁሉ በስውር እና በግልጥ በማህበረ መንጥር እንሆ አቅሙን በሽሚያ፣ መንፈሱን ለቀረመት ቅርጫ ዘርግተው ፖለቲከኞች ሲፎካከሩ፣ ከስጋቱ፣ ከሞቱ፣ ከመፈናቀሉ፣ ከአፈናው ግን ያዳነው አኃቲ ነፍስ ለነፍሱ ጥግ፣ ለተስፋው ጃንጥላ መሆን አልተቻለም።
ዬሚያሳዝነው የአማራ ሕዝብ መከራ፣ ሰቆቃ ያጣ፣ ዬቸገረው ይመስል ባባዕቱ ተገኝተው እንደ እርጎ ዝንብ በሚፈጥሩት ልክል ምንም ዬማያውቁ ንፁኃን ጦርነት ተከፍቶባቸው፣ ሲሳደዱ፣ ሲረሸኑ፣ የተሰበሰው ተበትኖ ለካቴና መሪወቹ ሲዳረጉ ያም እንደ ድል፣ እንደ ሽልማት ይቆጠራል።
ከሰኔ 15/2011 ጀምሮ እስከ ያዝነው ዘመን እና ወር ድረስ ድንኳን ሰበር ፖለቲከኞች የፈጠሩት የራዕይ ዝርፊያ እና ብተና ነው። እነሱን ተጠልለው ዬሚመጡ የጡንቸኞች መከራ በባዕቱ እንኳን ተስፋውን ዬሚመሩት ሰላማቸው ይነጠቃል።
አሁን የ12 ሺህ በላይ ዬአማራ ልጆች ብስጭት እና እሱን ተከትሎ የቀናው ጨካኝ የትምህርት ሚር ዬአስተዳደር የወሰነው ውሳኔ ሳቢያው ሳይሆን ምክንያቱ የድንኳን ሰበር ፖለቲከኞች ጦስ ነው።
ለሰላው በቀሉል አልጋ አንጣፊ መሠረቱ ዬመነሻ ምክንያት አለው። ላይ ላዩን እንደ ኮረፌ ለማንኩረፈረፍ ፖለቲከኞች።
ግዴታ ከአፍ እስከ ገደፋ ዬሚደረደርለት ዬአማራ ህዝብ በመብት፣ በሰውነት ጥሰት፣ በእንግልቱ እና በመከራው መፍትሄም ስኬትም ቀርቶ ወጥ አቋም መያዝ አልተቻለም።
ደጋፊውም፣ ተዋህጂውም፣ ቅልጠመኛውም፣ ያን የተፀዬፈውም ዘለግ ብሎ በስልት፣ በረቀቀ የሳለ ፕሮግራም ዘሩ ከምድር ለማጥፋት፣ በተነፈሰ ቁጥር ውሳኔ፣ ዓዋጅ፣ መግለጫ የሚዥጎደጉድበት ገር ህዝብ እንዲህ አውላላ ሜዳ ላይ ሆኖ አዋቂውም አላዋቂውም ቧ ብሎ በተከፈተው ቅንነቱ እዬተወራኜ ፋይዳ ቢስ እውኃ ቅዳ ውሃ መልስ።
አሁን ዬአማራ ሕዝብ ከጀመረበት መስመር ላይ እንኳን ዬለም። ዜሮ ላይ መገኜት አለመቻል። ዜሮ መነሻ ነውና። ለቀናው 1/2/3/4/……… እያለ ይቀጥላል፣ ላልቀናው -1/-2/-/-4………
እና፣ እናማ ያን ዳይናሚክ ሁለገብ አጓጊ እጅግ ማራኪ፣ ሳቢ፣ ተፈሪ የማንነት እና ዬህልውና ተጋድሎውን እንኳንስ እዬተመነገደ ሊሄድ ባለበት ለማስቀጠልም አልተቻለም። "በጥባጭ ሳለ ማን ጥሩ ይጠጣል?"
ይህን ዬሚያመቻቹት የራሱ የአማራ የፖለቲከኞች መሆናቸው ሲታሰብ ያስምጣል። ከእነ ጓዛቸው ዘውታው መዘዙ ለአማራ እናት ማህፀን ነውና። እርማት ዬለም። እራስን መቅጣት ዬለም። ሁልጊዜ ሙትልኝ። ሁልጊዜ ተጨነቅልኝ። አንድ ቢክ እስክርቢቶ ገዝቶ ዬማያውቀው ሁሉ።
ማህበራዊ መሠረቱን ያጣው ሁሉ እንደ ጉድ ሰርክ ይጎርፋል ወደ አማራ ፖለቲካ፣ እና የአማራ ሕዝብ ለመጣ ለሄደው ሲያደገድግ፣ ሲያጅብ፣ ሽልንጉን ሲበትን፣ ጊዜውን ሲገብር መገበር።
ከሁሉ በላይ በቅይጥ እና ቅምጥ ፍላጎት በሚዳክሩ መንፈሶች መንፈሱን ያባክናል፣ ጥቂት ጥቂት ቋጠሮ እንደ ድመት አራስ ይሰበሰባል፣ በዬቦታው ይመደመዳል፣ በዛ ፖለቲካው ሲፈተግ ሲታሽ፣ በደጋፊ እና በተቃራኒ ጎራ ሲፋለም መሽቶ ይነጋል፣ ነግቶ ይመሻል። ሰብስቦ ማፍሰስ፣ አፍስሶ መሰብሰብ። ነዳላ ፖለቲካ።
ያን ጥሶ የሚወጣ ቡቃያ ሲኖርም አሰፍስፎ ሁሉም ይደፋበታል። ለካቴና ሲበቃ፣ ወይንም በምናኔ ሲሰወር የሚዲያው ተርኒግ ፖይንት ኩምሽሽ ብሎ ይፋድሳል። ይረሳል። ድልቂያው ተግ ይላል። አሁን የፋኖ አጀንዳ ዬለም። የአፍ መፍቻ ቋንቋ ሆኖ ባጅቷል።
ስውር እጆች ለግልጡ ፍጅት ደላድለው አስመቱት። ጥበብ፣ ስልት፣ አርቆ ማሰብ ቀርቶ ተው ሲባል መስማትም የአባት ነበር። ዬለም። እንዲህ ተያይዞ ለሽታ ሲመጣ ከዋናው ደራጎን ሽፍኑ ደራጎን ወህ ይላል።
ዬአማራ ሕዝብ ማህበራዊ ንቃቱ ከመሪወቹ በላይ ስለመሆኑ ከስድስት ዓመት በላይ አዬን። ግን ያ አቅሙ የግለሰቦች ሰብዕና ማነጫ፣ ማጫ ማማቻ ከመሆን ያለፈ ትርፋ ቀደም ብዬ እንደ አነሳሁት ከተጋድሎው ግብ ቀርቶ ከተነሳበት መስመር ላይ ለመጽናት አቅም አልቦሽ ሆነ። ያለው በደሉን ዬሚተነትን መንፈስ ብቻ ነው።
እሱንም ዬሚደፍሩ የታደሉት ናቸው። ግን ለራሳቸው የሰብዕና ግንባታ ለጎፈንድ ሚ ፕሮጀክት ነው። ለጥወራ። ይህ ሁሉ በህወሃታውያን፣ በኦነጋውያን ቤት አይሞከርም። በአማራ ብቻ እንጂ። ዬአማራ ፖለቲከኞች አፈለሱት፣ አፈሰሱት ዬአማራ ሕዝብን።
#ግርም ዬሚለኝ።
የህወሃት ቤተኞች የኦነግን ብቻ ያወግዛሉ፣ የኦነግ ቤተኞች የህወሃትን ብቻ ያወግዛሉ፣ የህወሃት እና የኦነግ ሠርገኞች ደግሞ አማራን እና ልጆቹን ያወግዛሉ፣ ይረግማሉ። ውግዝ ከአርዮስ ይላሉ።
ኢትዮጵያ ከአማራ ውጪ ሌላ አጀንዳ ዬለም። አውሮፓም፣ ምዕራባውያኑም አሁን አውስትራልያ ተጨምሯል ነገ አንታርቲካ እና ዩንቨርስም ይጠቃለሉ ይሆናል አጀንዳቸው ሁሎቹም አማራ ነው።
ስንት ተግባር እያለ የአማራ ልጅ በሩን ዘግቶ በዝምታ ለተልዕኮው መትጋት ሲገባ ዬአማራ ፖለቲካ ውራጅ ዬፖለቲካዊ መናፍስትን ህዋስ ተቀብሎ፣ ዬራሱን የነጠረ ፍላጎት ጥሎ እንሆ ኤሉሄ ላይ ይገኛል።
የማንነት ግጭት ያለባቸውን በማስጠጋት ብቻ ሳይሆን በአማካሪነት፣ በበላይነት፣ በመሪነት ሁለመናውን ከፍቶ ሰጠ ተጎርጉሮ፣ ተቦርቡሮ እንሆ አሁን በምንም ላይ ይገኛል።
#ዬማንነት ቀውስ ፀላዬ ሰናይ ነው።
ከዜግነት ወደ ዞግነት፣ ከዞግነት ወደ ዜግነት ሲመጣ ዬአዲሱን ማንነት ለመሸከም ነባሩ ጋር ፍጭት ይሆናል። ፍትጌያ ይሆናል። ግጭት ይፈጠራል። ሌላው ቀርቶ በአንዱ የዞግ ድርጅት ቆይቶ በሌላው የዞግ ድርጅትም እንዲሁ።
አቶ ዛዲግ አብርኃም ከህወሃት ወደ ግርባው ብአዴን? ሁለቱም ዞገኞች ናቸው። ግን እንወክላለን የሚሉት አንዱ ተጋሩን፣ ሁለተኛው አማራን ነው። መንፈሳቸው ሌላም ሊያጭ ይችላል። ራያ ነኝ ስለሚሉ።
ራዩማም ሌላ የተከደነ ወቅት ዬሚጠብቅ ጉዳይ ነው። በዚህ ላይ ዬሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የሙያ፣ የአስተዳደግ አካባቢያዊ ማንነት ሲታከልበት መጠነ ሰፊ ውጥረት ያመጣል። ያ ውጥረት ተረጋግቶ ህዝብን ለመምራች፣ ለችግሮች መፍትሄ ማፍለቅን ይጫናል።
በዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ የሚማስነው ዬአማራ ፖለቲካ ማጥቃቱ ቀርቶ እራሱን ለመከላከል ከማይችልበት ደረጃ ደርሷል። ይህን ለምሳሌ አነሳሁ እንጂ ከተመሳሳይ የዜግነት ፖለቲካም ወደ ሌላም ሲሸጋገሩ ብዙ ግጭቶች ይገጥማሉ።
ይህ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚታመስበት አሹቅ ባህሉ ነው። ለዚህ ነው በዬጊዜው በሚፈነዱ የማንነት ግሽበቶች እዬንገረገበ ዬሚገኜው ፖለቲካው። አረከሰት። በውነት ምርቃቱን አስነሱት። መደወሪያው ዬአማራ ፖለቲካ መሆኑ ይጠዘጥዛል። ምክንያት መኖሩን የተዘረፈ ሕዝብ ስለሆነ። ብቻውን የቆመ ሕዝብ ስለሆነ።
ዬተበተነን መሰብሰብ ቢሞከር ዬውጩ ደራጎን ገብቶ አነኩሮ አይሆኑ ያደርገዋል። ዬሚሻለው ዬአማራ ህዝብ ዬሚከፍለውን አላስፈላጊ መስዋዕትነት፣ መገበሩን ተግ አድርጎ በመጠነ ሰፊ ለማድመጥ፣ ለተደሞ ጊዜ መስጠቱ ዬሚገባ ይመስለኛል።
የአማራን ዬማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ከግልፁ የህወሃት፣ እና ህወሃት አፈራሽ ድርጅቶች ይልቅ ዬጎዳው ስውሩ ፈንጅ ነው። ያን ነቅሎ መጣል ካልተቻለ ሌላ ቡቃያ ቢበቅልም ይነቀላል፣ በአረም ይዋጣል፣ ተመቻችቶ ለኦነግ መራሹ ማጭድ ይዳረጋል። ምሪቱም መከራ አምራች ይሆን እና መጨረሻውም ስንብት ይሆናል። ያዬሁትም ይህን ነው።
አዲስ መንፈስ ለመፍጠር ያለው ዳጥ እና ዳገት ይህ ነው። ዬአማራን ፖለቲካ ከጥገኝነት የሚወጣ፣ በራሱ የሚተማመን ግብረ ኃይል መሬት ላይ መፍጠር ያስፈልገዋል።
ግን ጋራንቲ ዬለም። ለአራት ኪሎ ሽፋን በሚሰጡ የውጭ ደራጎኖች ሴራ እግር ከወርች ታሥሮ ምርኮኛ ይሆናል። ለአጥቂውም በር ይከፈትለታል።
"በሬ ሆይ" የጠቅላይ ሚኒስተሩ ብቻ ሳይሆን የተለዋጩ ደራጎን የፍፃሜ ማስደምደሚያ ይሆናል። ይህን እያሳካ ያለው ጃርታዊ መንፈስ በጤናው ይፏልላል። እሱን የተጠለሉ ባተሌወች ደግሞ?????
በደሉ ይተነተናል፣ ግን ለበደሉ መፍቻ ሳይሆን ለበደሉ ማደለቢያ ጃርታዊው ፖለቲካ ተግቶ ይሠራል። ለጠላት አመቻችቶ ያስረክባል። ጎልተው የወጡት፣ ደምቀው የወጡት ዬአማራ ሊቃናት በክብር እና በማዕረጋቸው ልክ ቀጥለው የማናያቸውም መቅደም ስለተሳናቸው፣ እራሳቸውን ችለው በአላቸው አቅም ጣሪያ እና ግድግዳ ቆርጠውና ደፍረው ለመታገል ስላልወሰኑ ነው።
ከሴራ ቸረቸራ አጋዥነት እና ጃን ጥላ የራስ የክህሎት ማነስ ለክፋ ቀን ይሆናል። ይጠበቅላም። ብልህነት ቢሸመት። ግን አላያቸውም በዚህ ልኬታ።
ሰፊውን ንቁውን የአማራ ሕዝብ መንፈስ ይዞ #ምጥዋት ልመና እንዲህም እንዲያም ያደርጋል። ብድር የሚያስኬደን ምንም ነገር አልነበረም። ዬአማራ ሕዝብን ቀጥ አድርጎ በተፈጥሮው ልክ ለመምራት ከህወሃት ቡቃያ ልመና የሚያባዝን ምንም ኩነት አልነበረም። ግን ጉድጓድን ለፈቀደ ምሱ ጉድጓድ ሆነ እና የአማራ ሕዝብ መሐል ሜዳ ቀረ።
ተገባሪው ሺህ ነው። በአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ በአንድ ሰሞን ብቻ 20 ሺህ ወጣቶች በዘመነ ህወሃት ታሰሩ። ወጣቶቹ የጎጃም እና ዬጎንደር ነበሩ። የተሰውት ሰማዕታት፣ አዲስ አበባ የታሠሩት፣ ታፍነው በህወሃት 15 ገኃነሞች ከታሠሩት ከተረሸኑት ውጪ። ዛሬስ?
እንዴት አረፈዳችሁ ውዶቼ። መልካም ሰንበትን ልመኝ እና ልሰናበት። ቸር ሁኑልኝ። አሜን።
እግዚአብሔር ይስጥልኝ።

 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
15/10/2022
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።