ባለ #ንቃቃቱ ቀንበር። መሪነት ትራጀዲ ወይንም ኮመዲ ወይንም ሲቃ፤ ወይንም የኳስ ሜዳ አይደለም።
ባለ #ንቃቃቱ ቀንበር። መሪነት ትራጀዲ ወይንም ኮመዲ ወይንም ሲቃ፤ ወይንም የኳስ ሜዳ አይደለም።
ቀንበር የሆነ ሥርዓት ቀንበሩን እንደ ድሎት ብቻ ሳይሆን እንደ ክብር ቆጥሮ ሲንከላወስ፦ ቀንበሩ የጫነው በራሱ ላይ ስለመሆኑም ያመላክታል። ቀንበር ጫኞች ቀንበሩ እነሱንም እንደሚያካት አለማወቃቸው የቆባ እኩይነት ነው።
#ግን። ማስተባባያው ተምን ይመደብ።?።
ይህ ክብር ሆኖ አንገትን ቀና አስደርጎ ጉዟችን ትርፋማ ነበር የሚያስብል ነበርን?
በሂደቱ እና በክስረቱስ ፌስታ የሚያስቀምጥ ነበርን?
ወይንም ውርዴቱ እንደመዳሊያ ሊያስቆጥር ይገባ ነበርን?
ሁሉንም - አዳመጥኩኝ።
ሁሉንም - መዘንኩት።
ሁሉም ለሁሉም እራስን ማድመጥ ያቃተው ስለመሆኑ ገባኝ።
#ግንን ልድገመው። አዎን ግን ሁለት ጊዜም ከፈረንሳይ ጉዞ መልስ ቀውስ ማስከተል ………
የዛሬ ሦስት ወር ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በደም አላባ በጽልመተ በኦነጋዊው የሲኖዶስ ግልበጣ የመንንግሥት ውንብድና እዬተዋከበች ሦስተኛ የነነዌ ፆም ላይ ዕለተ ሮብ ላይ ነበርን። ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ አሊ ፈረንሳይ ፓሪስ መግባታቸው የተደመጠው። ጉዞው ሽሽት ነበር። ጣሊያን ደርሰው ወደ ፈረንሳይ አቀኑ።
ከፈረንሳይ ሲመለሱ ፈረንሳይ የሁለት ዓመት የጡሮታ ጊዜ ተራዘመ ብሎ በሰላማዊ ሰልፍ ተናጠ። እግረ ደረቅ። አሁን የዛሬ ሳምንት ደግሞ ፈረንሳይ የዓለምን ኢኮኖሚ ያማከለ ግሎባል ጉባኤ አካሄደ። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ እዛው ነበሩ። ሲመለሱ ያ ህውከት በፈረንሳይ ቀጠለ። ዕውነት ምንድን ነው ጉዱ አሰኝቶኛል። ምንድን ይሆን የተሸከሙት መንፈስ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ አሊ አሰኜኝ። ፈረንሳዮችስ ይህን አጢነውት ይሆን? እግረ ደረቅ ይባላል በአገራችን ………
የማንኛውም አገር መሪ ወደ ሌላ አገር ሲሄድ የሚጠቀመው በራሱ አገራዊ ቋንቋ ነው። የጀርመን መሪ አሜሪካ ቢሄዱ በጀርመንኛ ነው የሚናገሩት። የፈረንሳዩም እንዲሁ። ቋንቋ ያለው ስለምን ይቸገራል? የውስጥን አቅም ለመጠቀም፤ ለተጠዬቁት ጥያቄም ትክክለኛውን መልስ ለመስጠትም በራስ በሚያውቁት ቋንቋ መናገር ቢያስከብር እንጂ የሚያዋርድ አልነበረም። በራሱ መተማመን ላለው ብቁ እና ምጡቅ የመሪነት ቅባዓ እራስን ሆኖ መቅረብ ነው። ሳይለበዱ ሆነ ሳይወረጁም። የሆነ ሆኖ በራስ መተማመኑ ራድ ላይ ለሆነ ሰብዕና እራስን አለማድመጥ ምልክቱ እንዲህም ይገለጣል።
አሁንም በአክብሮት እና በትህትና ለጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ የማሳስባቸው ዕድላቸው ቅስሙ መሰበሩን ነው። ይህን ተቀብሎ በአቅም ልክ እንደ አቅም ቀጣይ ህይወትን መምራት ጅልነት ሳይሆን ብልህነት ነው። የማይካደው ለሳቸው ሆነ ለቲማቸው ኢትዮጵያ ከብዳቸዋለች።ዕውነት ሲናገር እንቅጭ እንቅጩን ነው።
ያን በመሰለ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ዬወከሉት አገርን፤ የወከሉት አህጉሩን፤ የወከሉን ግሎባሉን ዓለም ሆኖ ሳለ ብድግ እያሉ ማይክ ይዞ አስታኮ ያሹትን ዘራፍ እዬተባለ እንደሚቀለድበት የኢትዮጵያ ምድር አልነበረም - ዕድምታው። #እከክ ነበር። ለዛውም #ቹፌ። ቹፌ እከክ ቀን ቀን አይታይም። መሸት ሲል ብቅ ይላል። ከዛ እያሳከከ ደም ያዘንባል።
ቀን ያ ሁሉ ማት ያረፈበት አይመስልም የቹፌ እከክ ሰላማዊ ይመስላል። በጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ የፈረንሳይ ቀራቢ አጥቶ መንከራተት፤ ዓይናቸው ይታዬኛል፤ የእጃቸው እና የእርምጃቸው አከናዳድ ይመጣብኛል፤ የውስጥ ረመጥ ፍም ያዘለ የቹፌ እከክ ነው። ለሳቸው ብቻ ሳይሆን በመታበይ ሠረገላ ሆኖ አና ላለው ለሚመሩት ለእነ ዶር ዓለሙ ሥሜ ሆነ ለጠቅላላ ለአገር ውስጡም ሆነ ለውጩም የኦነግ ታንቡር መተንፈሻ ቀዳዳ ነው። #ነፍሶበታልና።
አድማጩ አህጉራዊው አንገቱ በሃፍረት አውሎው ጠኗል፥ ግሎባሉም የኖቤል ሽልማት፤ የሄሰን፤ የዩኒስኮ ክብር ሁሉ አንገቱን የደፋበት አጋጣሚ ነበር። ለፓን አፍሪካም፤ ለግሎባላይዜሽኑም የዓለሙ የሰላም አባት ሎሬት ጠ/ሚ አብይ አህመድ አሊ የከወኑት ማናቸው ዝልኝ አቀራረብ፤ ወጣገባ ንግግር፤ እራስን ያላረመ ዝንጥላ #ውርጭ ነበር።
የንግግር ጥበብ የእጅ፤ የአካል፤ የገጽ ንቅናቄው ሁሉ የተናጋሪውን አቅም ያሳያልና። ተናጋሪው የሚናገርበትን ጭብጥ ማስተር ማድረግን ይጠይቃል። ያዬሁት #ደመመን የተጫነው #ንቃቃት ነው። ሳቁ እራሱ የሃዘን ልብስ #ማቅ ነበር። ለካ ሳቅ ሆነ ውሽክታ ካለቦታው እንደዛ ቀፋፊ ነው። አንገቴን ደፍቻለሁኝ። እኔ እኔ ነኝ እና በራሴ ላይ ለመሳለቅ አልደፈርኩም። አገሬ እምሳሳላት አገሬን የወከለ ምልክት እንደዛ ሲወዛወዝ ጤና አይሰጠኝም።
አንድ ተናጋሪ ለዬትኛውም ፕረዘንቴሽን የሚያውቀውን ጭብጥ እንኳን በስርዓት ደግሞ፤ ሰልሶ መለማመድ ይኖርበታል። ሪህርስ ማድረግ ይኖርበታል። ሲሆን ሲሆን ሙያዊ ጉዳይ ኤክስፐርቶች ስላሉት አጭር እና ግልጽ ስምምነት ላይ የተደረሰበት የፁሁፍ መሰናዶ ሊደረግ ይገባ ነበር። የኦዲዬንሱን ስብጥር ልኩን ገምቶ መነሳት ጥበብ ነበር። መሪነቱ ቢታወቅበት። ሌላው ታዳሚው የተመክሮው እና የዕውቀቱ ልክ መዳፈር አናርኪዝም ነው። የቆሎ ጓደኛ የለም እና።
አንድ በዚህ መሰል ጉባኤ የሚገኝ ሰብዕና ዓለም ዓቀፍ ሁነቶችን፤ አህጉራዊ ተፈጥሮወችንም አጥንቶ በሚገባ ተለማምዶ ብቻ ሳይሆን አዋህዶ መቅረብ ገበርዲን እናከረባት አሟልቶ እንደ መቅረብ ቀላል አይደለም። ወይንምአሸባሪ አደራጅቶ በጀምላ እንደማዋረድ፤ በጀምላ አቃሎ እንደማፈናቀል፤ ወይንም በጅምላ ገድሎ ለሬሳው ጥላ የችግኝ መትከልን ተዝናኑበት እንደማለት ቀላል አልነበረም። አስገምቷል። አስመዝኗል። ተስፋን አራቁቷል።
ለነገሩ ይህንንም ሳይችሉ ኢትዮጵያን የሚመኙም እንዳሉ አውቃለሁኝ። ማለቴ ልብሳቸውን አስተካክለው፤ ቢሯቸውን አደራጅተው ሳይገኙ እነ ፕሮፌሰር ዶር መራራ ጉዲና፤ እነ አቶ ዳውድ ኢብሳም። የኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ ዶር. ለገሰ ቱሉም በጠማማ ከረባት ዘራፍ ሲሉ አስተውያለሁኝ። ቀን እና ቀና ባልተገናኙበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንቶ ፎንቶ እንዲህ ይዳክርበታል። እንዲህም። እንዲያም። ችግሩ ይህ መንዘላዘል ወንዝ ሲሸጋርም ከእነ ገመናው መሆኑ ነው።
የሆነ ሆኖ በኦነጋዊው አገዛዝ #ማስተባበያ ከመስጠት መቆጠብ ብልህነት ነበር። ዝምታው ትውልድን ለማዳን ነበር። እንጂ የታዬው፤ የተደመጠው ስብርብር ሳያደርገኝ ቀርቶ አይደለም እኔ በግሌ። እንደ ዜጋ ማህፀንን እንደ ዱባ ይቀረድዳል። ገመናው እንደ ቄጤማ በዓለም ይፋዊ አደባባይ የዋለበት ክስተት ነበር እና። ለዛውም ማመቅ በማይቻልበት በሚዲያ ዘመን። መጽናናት #ጥረት ባለው #ጥራት እንጂ በዝልግልግ እና ዝርክርክ አቅርቦት ሊሆን እንዲህ አይገባም ነበር። የሚሻል በለለበት በሻገተ ውይበት ሌላ ልጥፍ ማስተባበያ ማከል እንዲህ በዝምታ ዝም ያልነውን የውርዴት አዟሪት እንድንመለስበት ግድ ሆነ።
መከበር ከሄሮ ወደ ዜሮ ያሽቆለቆለበት ሁነት ቁጭ ብሎ ሊጠና ሲገባ "የፈረንሳዩ የጠቅላይ ሚኒስተራችን ጉዞው አትራፊ፤ ስኬታማ ነበር" ብሎ ማቅራራት የናስ ጩኽት ይሆናል። ወይንም የገደል ማሚቶ። ጉድለቱ እራስን ማድመጥ መሳን ነው። መነሻን መሳት ጉዳይ ነው። በዓለም መድረክ ሲገኙ አንዲት በመንፈሳዊ ሃብቷ እና በአመሰራረት ተፈጥሯዋ አንቱ የተባለች ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ወክሎ ስለመሆኑ ከውስጥ ተቀብሎ ሊሆን ይገባል። በዛ ውስጥ ስንት ረቂቅ ፍልስፍናዋች እና ዕሴታዊ ጠረኖች፤ ህብራዊ ጥልቅ ቀለማት እንዳሉም ማስተዋልን መመገብ ያስፈልጋል።
አሁን አደባባይ ልታይ ልታይ ሳይሆን ደብቁኝን ውጦ ጥሞና ላይ ሊገኙ ይገባቸው ነበር የዓለሙ ሎሬት። ለቀውስ እና ለማምታት በሰላም ሚ/ር የሚል ፋንታዚ፦ በፒኮክ ሠረገላ ፋንታዚን መጪ እያሉ የሚገኙት ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ። ቢችሉ መቻልን ማስቻል ቢያቅታቸው በዝምታቸው ትንሽ ፋታ ሊሰጡን በተገባ ነበር። ባአለቀ እና ኤክስፓዬርድ ባደረገ ካርቦን ሌላ ጡሁፍ ላይ #ባይለቃለቁ።
ፈረንሳይ፤ አልፎም በቅርበት በጎረቤት አገር ለምንኖር ኢትዮጵዊ ስደተኛ ልጆቿም ሊታሰብ ይገባል። ከቁስለታችን ገና አላገገምንም። #ኢትዮጵያዊነት ገብያ ተሂዶ የሚሸመት ሸቀጣ ሸቀጥ አይደለም። እራሳችን ቀጥተን፤ ገርተን፤ ሁሉ እያለ፤ ሁሉ በሚቻልበት ሁኔታ "ይበቃኛልን" ተቀብለን የምንኖረው አገረ ኢትዮጵያ እራሷ ተፈጥሯዋ ህገ - መንግሥት ስለሆነ ነው።
ቀድሞ ነገር በኦነግ ፖለቲካ ፕሮቶኮል የሚባል የሙያ ዘርፍ የለም። ጠቅለይ ሚኒስተሩም ለዚህ የማይመቹ #በሲሄዱ #ማደር ባለሟል ናቸው። ጎንደሮች ባለ ቅኔ ናቸው እና "ያለአባቱ ዶሮ ባጓቱ" ይሉታል ይህን መሰል የታዛ ተዛነፍ ምስቅልቅል ሲገጥማቸው። ጠቅላይ ሚኒስተሩን ምናቸውን መቆጣጠር እና ማረቅ ይቻላል? ቅጽበታዊ ናቸውና። ሲቃ ናቸው እና። ለዛውም ግራጫማ ሲቃ እና #ሳግ። ማህበረ ኦነግ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ልቅነት፤ የንግግር ለዛን ጥሰት፤ ይሉኝታዊውን ኢትዮጵያዊ ቀለም የጣሰ ዘይቤ ነው ያላቸው።
አውሮፓ ውስጥ ወግ አጥባቂም ዘመናዊም ፖለቲካ ይራመዳል። በዓለም ዙሪያም እንዲሁ። የኦነግ ፍላጎት ግን ከሁሉም የለለ በቀውስ እና በደም መነከር፤ በአመድ እና በጢስ ውበትን የተቀበለ ነው። ጥንታዊነትን ተጣሮ፤ ዘመናዊነትን ሰዋዊነትን #አክ ያለ። ይህ ተጥፎ ሳይሆን ዕድሉን ባገኙት አጋጣሚ በመሳጥ በደርግ እና በህወሃት፤ በመያዝ እና በመጠቅለል በያዙት ዘመን አዬን። ምፃዓትነት። በደርግ ጊዜ እነ ዶር ዲነግኦ፤ በዘመነ ህወሃትም ዶር ዲማ ነግኦ፤ በራሳቸው ዘመንም ዶር ዲማ ነግኦ 50 በእነሱ ታመሰን፤ ተቀቀልን።
ንግግር ልጓም ያስፈልገዋል። ንግግር ጥበብ ነው ህግ አለው። ሙያም ነው የሚማሩት። ፀጋም ነው ከሥጦታ ጋር ቤተኛ የሆነ። አካሄዱም ቅጥ አለው። አያያዙም ይዘት አለው። በቅርጽ ፎርሙላ ወይንም በምናብ ፋንታዚ ያልተቁላሉ እና የማይተዳደሩ ይህን መሰል አብሮነታዊ ግሎባል ጉባኤ ላይ የታረሙ፤ የተቀጡ፤ ዲስፕሊን የገዛቸው አንደበቶችን አጥብቀው በአጽህኖት ይጠይቃሉ። ዘው እያሉ እንደ ድንኳን ሰባሪ በዬመድረኩ ማይክ ላይ ቁብ ብለው የመኪና ፓርክ እንደማስመርቅ ቁብ ቁብ የለም በዓለም ዓቀፍ መድረክ። አገራት በህግ እና በሥርዓት ያለፋ በዚያ ውስጥም መኖርን ያስጠበቡት በአናርኪያዊ እርምጃ አይደለም እና።
ኢትዮጵያ ሁሉ እያላት ያላጠኗት እዬዋሿት እዬተዶሉ ሲንዶለዶሉ ማዬት እና በዚህ ውስጥ አዲሱ ትውልድ አገሩን እንደምን በውስጡ ፕራውድ ሊያደርግ ይችላል ነው የእኔ ጭንቀቴ? ኢትዮጵያ እንደ ፓን አፍሪካኒስት መሥራች እና መሪ አገርነቷ ለአፍሪካውያን መኩሪያ መሆን ሲገባት፤ ለጥቁሮች ምልክት መሆን ስትችል በኦነጋዊው አይዲኦሎጂ እንዲህም መሸማቀቂያ፤ መኮመታተሪያ ስትሆንስ አፍሪካዊው ትውልድ እንደምን ፕራውድ ሊያደርጋት ይቻል? መቀጣት ያለበት ጉዞ ማን ሃግ ይበለው ሲባል እንዲህ ዓይነት ጉባኤው ያሳዬው ግብረ ምላሽ ይሆናል። ግብረ ምላሹ መንጠራራቱን በልክ አትመጥንም ነው ዕድምታው። ገራሚው ነገር ይህ ክብር እና ስኬት ሆኖ ደንቅሩ መባሉ ነው።
#እኮ እስቲ ናልኝ። እንደ መከወኛ።
ያልተመጣጠነ፤ ያልተመዛዘነው ተዛነፍ ዘመን እና ትውልዱ እንደምን ይገናኙ? የጎደለን እራስን አድምጥ አለመነሳት ነውና እራስን አድምጦ እራስን ሆኖ መነሳት ይቅደም ነው ፍሬ ነገሩ። እራስነት አይሸሽ፤ አይፈራም። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ሽሽታቸው ለሚወጥኑት የቀውስ አንበላቸውም ጭምር ነው መልዕክቱ። ሽሽት ላይ ናቸው። ሸሽተው ሸሽተው የት እንደሚደርሱ ያያቸው ሰው።
ትልቅነት እራስነትን ንቆ ወይንም ጠቅጥቆ ሳይሆንእራስን አክብሮ ሊሆን ይገባል። ኢትዮጵያዊነት ተሸሽቶ ስኬት የለም። በውስጡ ኑረውበት አያውቁም ኦነጋውያኑ። ለብጠው እና ተለብጠው ቀረቡ። እሱንም ሸሽተው ልብጣቸውን አፋፍ - ለአፋፍ እንዲህ ይወራጫል።
የጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ አሊ በኖቤል ሽልማት የለት ለለት አልነበረም። እሳቸው ግን ከፋንታዚያቸው ጋር አዳብለው ስላሳኩት ከዛው ከፋንታዚያቸው ውስጥ እንሆ በዕብለት አጅለው፤ በማስመሰል ኮስሞቲክስ ያዳክሩታል። ትልቅነት መነሻን መቀበል። መነሻን ማወቅ። መነሻን ማጽደቅ። እና በመነሻ ህይወት ውስጥ መኖር ነው። ይህን አልቻሉም።
ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ለቦታው የሚመጥን የመሆን አቅም ከፕሮቶኮል፤ ከንግግር፤ ከቁጥብነት አቅም ጋር አልተገናኙም። በዝልኝ ተገኜ ክብሩ። በዝልኝ #መጭ ላይ #እጭ ሆኖ ቀጠለ።
የፈረንሳይ የተቃጠለ ካርቦንነት ያቺ ቀን አትመለሰም። በለቃለች። ተጋግጣለች። በእኔ ህሊና እራሱ ትዕይንቱ ታትሟል። ያ ገጠመኝ በምንም ተለብዶ አዲስ በርዥን አህዱ ሊልባት አይችልም። ህፍረቱ፤ ዝቅታው፤ ስላቁ፤ ዱላው ደግሞ ለሁላችን ደርሶናል። ስለዚህ በራስ ላይ የተዘመተው የኦነግ ወረራ ሊታረም ብቻ ሳይሆን ሊቆም ይገባል። አዝኜ ነው የተከታተልኩት። ያ ሃዘኔ ላይበቃ #ማስተባበያው ደግሞ ያቆስላል። ያን ውድቀት እና ድቀት ለመገሸር ይሁን ለመለበድ የሚደረገው ቀጣይ ሙከራም ክሽፈት ነው።
#እንደ መደወኛ።
ለምን? መነሻውን ያላወቀ መድረሻው አሳቻ ነውና።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
03/07/2023
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ