በማምሻ ከብት ግባት ጀንበር ስታዘቀዝቅ ምዕራፍ ፲ን አህዱ አልኩ። - ምን አጉደልን? ቀጣዩ ጭብጤ ይህ ነው። (ምዕራፍ ፲)
በማምሻ ከብት ግባት ጀንበር ስታዘቀዝቅ ምዕራፍ ፲ን አህዱ አልኩ።
- ምን አጉደልን? ቀጣዩ ጭብጤ ይህ ነው። (ምዕራፍ ፲)
በሲቃ ነው እምጥፈው። እምነግራችሁ ተረብ እንዳይመስላችሁ። ዕንባ - ይተናነቀኛል። ሳግ - ይፈትነኛል። ሆዴን ባር ባር ይለዋል። ልቤ #ይሻቅላል። ትርታዬ - ይጨምራል። ትርታዬ - ቁርጥ ቁርጥ ይላል=
መቼ እና መቼ? ዜና ላደምጥ ቴሌቪዢኔን ስከፍት። የምነግራችሁ ዕውነት ነው። በጣም ደንጋጣ ሁኛለሁኝ። የሚፃፋ፤ የሚዘገቡ፤ የሚደመጡት ሁሉ ያስፈራሉ። እኔ በእኛ ዘመን ያበቃል ያልኩት የጦርነት ሲቃ ዛሬም??? ህልማችን ተስፋችን የዕውቀት ጥማታችን በሰላም እጦት ጨንግፎ ቀረ እንደ አቀረቀረ ስለ እኛ እኛን ስለአጣ። ዛሬም??? ያማል።
የሚያጽናና የሚያረጋጋ አይዟችሁ የሚል መንፈስ ክው ብሎ ደርቋል። የዜናወች ዕርዕስ ቀለም፤ የቃላት ምርጫ ሁሉ ያስደነግጣሉ። የሚፃፋበት ቀለም እራሱ አለርም። ህም።
እናም ቁጭ ብዬ እራሴን ስሞግት ሰነበትኩኝ። አልፎ አልፎ ብቅ እላለሁ። ግን ውስጤን የሚጨነቅበትን ነገር ለመፃፍ አቅም አጣለሁ። በፍጥነት ግጥምጥሞሹ ይደመጣል፤ ፍጥምጥሙ ሳይከወን ፋክክሩ አና ይላል። በዚህ ማህል ትውልድ ይባክናል። ምጥ።
በወል ውርጅብኙ በረዱን ይለቀዋል፤ አውሎውን ይልከዋል፤ አቤቶ ስክነት አቤት ያንት ያለህ የእኛ ጌታ የህዝብህ እንባ ሆነ ከርታታ እያለ ወደ እዮር ሲጮህ ይሰማኛል። ፍጥነቱ፤ እሩጫው፤ ጥድፊያው ከዬት ተነስቶ የት እንደሚከነዳ ይፈትናል። ፈተና ለፈተና ግብዣ ሠርግ እና መልስ፤ ግጥግጥ እና ቅልቅል። #እህ።
ልርገመው _ እላለሁ።
ልውቀሰው _ እላለሁ።
ልቆጣው _ እላለሁ።
ለዚህም አቅም አጣለሁ። ልርገመው፤ ልቆጣው፤ ልገስፀው የምለው ባላወቅኩት፦ ከእሳት ከእውኃ በምልበት ዘመን #ፖለቲካ የጠለፈኝን ቀን እና ሰከንድ ነው። ቤተሰቦቼን አባክኜ፤ አሳዝኜ በመራራ ሃዘን በስንብት ተወራረደ። ያን ቀን ባገኜው ምንኛ በወደድኩ። ፖለቲከኞች የጠለፋኝ ቀን። ተጠልፌ እኮ ነው ከጥዋት ከማታ ሳይታሰብ።
ግን ምን አጉድለን - ተረገምን?
ምን ተላልፈን ቅጣታችን መቋጫ አጣ?
በቃ ምዕራፍ ፲ ይህው ይሆናል አጀንዳዬ።
ነገ እንገናኝ። እሺ። ኑሩልኝ። ልቤ ሲባትል የሰነበተበትን ነገ አህዱ እላለሁኝ።ለአንዱ መፎከሪያ፤ ለሌላው መቆዘሚያ፤ ለሌላውም መሳለቂያ ግን የእኛው የራሳችን የእርግማን ገብያ።
ቸር ሁኑልኝ። አሜን።
ቸር እደሩልኝ። አሜን።
ቸር ያሰማን። አሜን።
በማምሻ ጀንበር ስታዘቀዝቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ምዕራፍ ፲ ተጀመረ። ለወትሮው ወይ ጎህ ሲቀድ ወይ ረፋድ ላይ ነበር።
ግን ግን ምን ሁኜ ይሆን? አደራ እንዳትጠይቁኝ። እኔም አላውቀውም። ለነገሩ እኔ ሰው መጠዬቅ /// መጠዬቅም ባህሌ አይደለም። ብዙ ጥያቄም አያሰኜኝም #አሻም ባልልም። ምጥን አስተናግዳለሁ እንደማለት። በፈለገ ልክ ባቀርበው አልጠይቅም። የሚነገረኝን ማድመጥ ብቻ። ቤተ ሰቦቼም ቢሆኑ አልጠይቅም። የት? እንዴት? መቼ? ለማን? ለምን? ምን? ከእኔ ጋር ለትኛውም ዓይነት ግንኙነቶች ስለመፈጠራቸው ተግባር ላይ የማይውሉ አውጫጭኝ ዕድምታወች ናቸው። መታደል ይሁን አለመታደል ባለውቀውም። አለማወቄንም እንዳትጠይቁት አደራ።
ሰው ለእኔ የፈቀደውን ብቻ ሲነግረኝ ለማድመጥ የወሰነ ማንነት። ይገርመኛል ለራሴም።
ምን ያህል እንደተጓዝኩ አላውቀውም።
ምን ያህል እንደሚቀረኝም አላውቀውም።
አለማወቄንስጠይቀው፤ አለማወቁንገለፀልኝ።
ተስፋን እጠብቃለሁ።
"የሰው ልብ መንገድን ያዘጋጃል፤
እግዚአብሔር ግን አካሄዱን ያቃናለታል።"
(ምሳሌ ፲፮ ቁጥር )
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
02/07/2023
እስኪ አንተ ታውቃለህ የሠራዊት ጌታ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ