የዜግነት እርቦ እና ሲሶ የለውም። የደቡብ ልጆችም ወገኖቻችን ናቸው።

የዜግነት እርቦ እና ሲሶ የለውም። የደቡብ ልጆችም ወገኖቻችን ናቸው።
 
 

 
እራስነት ይጠዬቅ። እኔነት ይፈተሽ። እኔ ሰው ነኝ። ሰውነት የተለያዩ መለኪያወች ይኖሩታል። መጀመሪያ ግን ቅቡል ሊሆን የሚገባው ጉዳይ እኔ በፈጣሪ በአላህ አምሳል የተፈጠርኩ ሰው ነኝ ብሎ ማመን እና ዕውቅና መስጠት ይገባል። ከዚህ ቀጥሎ ያለው ሰውነት የመኖሩ ጊዜ የተገደበ ሁሉም ከመኖር ጋር እንደተገናኜ ሁሉ ከመሞት ጋርም ሊገናኝ እንደሚችል መቀበል ይገባል። ይህ የመኖር እና የማለፍ ጊዜ በሁሉም ለሁሉም የሚደርስ ነው። ከሞት የሚያመልጥ የለም።
ለሁሉም እኩል የተሰጠው ነው። ጊዜውም አይታወቅም። ለዚህ የኩንትራት ጊዜ የክፋ ነገር ጫካነት ግን ስለምን ለምን ያስፈልጋል? ሲወለድ እልል ተብሎ የተቀበልነው የሰው ልጅ በታቀደ ሞት ስለምን መኖሩ ይቀማል? ስለምንስ በድህነት ለመኖር ሰላሙ ይታወካል። መኖሩ ስለምን ይስተጓጎላል? ለሥልጣንም፤ ለወንበርም ምንም የማያሰጉ ሠርቶ አዳሪ ባተሌወች ባዕላት በመጡ ቁጥር ስለምን መኖርን እንዲፈሩት፤ መኖርን እንዲሰጉት ይደረጋሉ? ድህነታቸው ላይበቃ፤ በጉስቁልና መኖራቸውላይበቃ እዬተደበደቡ ለምን ወደ እስር ይጋዛሉ? እኮ ለምን? ትናንት በአዲስ አበባ የሆነው አሰቃቂ ድርጊት ነገ በሁሉም ከተሞች ይህ ጨካኝ ሥርዓት እስከ ቀጠለ ድረስ መከራው ቀጣይ ይሆናል። የዜግነት ሲሶ እና እርቦ የለውም። የደቡብ ልጆችም ሠርቶ አደሮች ወገኖቻችን ናቸው። ዝም አንልም።
እጅግየሚገርመኝ የጠቅላይሚር አብይ አህመድን ሌግዠሪ ጉዞ፤ ሽርሽር ዓመት ይዞ እስከ ዓመት የጫጉላ ሽርሽር ዘጋቢወች ይህን መሰሉን በገፍ ድኃ አንይ ተብሎ የሚካሄደውን የእግዚአብሄር ፋጡር ድብደባ፤ ረገጣ፤ ባይታወርነት ሲያወግዙ አይደመጡም። በአቤ ቱኩቻው በጣም ነው እኔ እማዝንበት።
ቅንጡ ነገሮችን አድምቆ፤ አጉልቶ ሲናገር ይህን መራር ግፍ እና በደል እንዳላዬ ያልፈዋል። ሌላው የቂራ ጩኽት ስለሆነ አላዳምጠውም። ከበሮውን ይደልቅ። አቤ ግን የእኛ ስለእኛ የምንለው ወንድማችን እንዲህ ሆኖ ሳዬው በጣም ይገርመኛል። በጣምም አዝናለሁኝ። አገር እያለ እሱ ጽፎት ያላነበብኩት አሽሙር መጣጥፍ አልነበረም። እያዋዛ ይሞግት ነበር። አሁን ግን ቅባው የት ገባ???
ደሃ ጠል ሥርዓት፤ ፀረ ሰው እና ፀረ ተፈጥሮ አንድ ቀን ከሰው ደም ፍሰት ሰበር ዜና ወጥቶ የማያውቅ ኢትዮጵያ ችግር የቸገራት ይመስል ችግርን ሲቀፍቅፍ ውሎ የሚያድር የቀውስ ማምረቻ ተቋም ምኑ ጣዕሜ ነው ሊባል እንደሚችል አላውቅም። አይገባኝም። እንዲገባኝም አልፈቅድም።
ቀደም ብዬ ለስልጣን የማያሰጉ ሰወች ለምን ተጠቂ ይሆናሉ ስል የሚያሰጉት ይገባል ተጠቂ መሆናቸው ማለቴ አይደለም። ዕውነቱን ብናገር ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ደጋግመው እንደሚገልፁት ከ10 አመት በታች ያሉ ልጆች አብይ ነፍሳቸው ነው ሲሉ ከዛ በላይ ያለ ማንኛውም የሰው ዘር እንደማያስፈልጋቸው ነው እኔ እማስበው። ኮረና ሲገባ እንደ እሳቸው የፈነጠዘ አልነበረም።
ስለዚህ በበሽታ፤ በራህብ፤ በጦርነት፤ ብቻ ሰውን በሚመነጥር፤ ተፈጥሮን በሚያራቁት ሁነት ሁሉ ያለው ደኃ ህዝብ ምጥጥ ቢል ጉዳያቸው አይደለም። ገና በጥዋቱ ግብጽ ትውረረን ሥራ ያጡ ወጣቶች አሉን ነበር ያሉት። ሰው አልባ ሥልጣን? ሰው አልባ ክብር? ሰው አልባ ድሎት ሥምዬለሽ ድዌ ነው።
በአማራ ሆነ በትግራይ እንዲሁም በአፋር በመከላከያውም ያለቀው፤ ታቅዶ የሚገደለው አማራ እና ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማንያን፤ ታቅዶ የማናውቃቸው የሚሰወሩ ቤት አልባወች፤ በወረርሽኝ እንዲያልቁ የተፈረደባቸው፤ በአማራ ክልል የተከፈተው ጦርነት፤ ነገ እጮኛ የሆነው የወደብ ማስመለስ ቅዠት ሁሉ ለኢትዮጵውያን የሰው መተራ የተሰናዳ ፕሮጀክት ነው።
ሌላው የቀደሙ የተደራጁ፤ የተሠሩ ተግባራት ሁሉ ይወድማሉ። ህዝቡን የማድህዬትም ፕሮጀክት አለ። ምርታማ አካባቢወች በራህብ እንዲያልቁ ማዳበሪያ ምርጥ ዘር መከልከል፤ በእርሻ ወቅት፤ በአዝመራ ወቅት ጦርነት መክፈት፤ ማሳደድ፤ ማፈናቀል ቁልጭ ያለ የሰይጣን ተግባር ነው። ዲያቢሎስን ደግፎ መቆም ቅጣቱ የላይኛው ይሆናል።
የሰውን ዕንባ ለማዬት መጓጓት። በሽብር በጭንቀት ማመስ። ስጋት መቸርቸር የፀላዬሰናይ ተግባር ነው። ማህፀን አብራክ ማት ነው የወረደባቸው። ሳቅ መዳር መኳል መርገምትን ነው የተጋበዙት። መሠረቱ የአስተዳደግ መበደል እና የማንነት ቀውስ ያመጣው መከራ ነው።
ለዚህ ነው እኔ ጠሚር አብይ አህመድን አሳቻው መሪ የምላቸው። በተጨማሪም ቤርሙዳ ትርያንግልም እላቸዋለሁ። አስሩን አብይ አዬሁኝ። አስረአንደኛው ደግሞ ይቀጥላል።
ውዶቼ ቀጣዩ ምዕራፍ አስራ አንድ ይሆናል። ነገ ምዕራፍ አስርን ለማጠቃለል ሁለት ጉዳዮች ይኖሩኛል። ከዛ ጽጌ ፆም ዋዜማ ላይ ነን ከጥቂት ቀናት ጥሞና በኋላ እመለሳለሁኝ። ነገ ግን እንገናኛለን በጤና እና በድርቅ ጉዳይ።
ክብሮቼ ደህና እደሩልኝ። አሜን
ሰው ሁነን ለሰው አዘኔታ ይኖረን ዘንድ ፈጣሪ ይርዳን አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
05/10/2023

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።