"ኬንያ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ላይ ያነጣጠረ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሯን አስታወቀች" BBC
ኬንያ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ላይ ያነጣጠረ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሯን አስታወቀች
https://www.bbc.com/amharic/articles/c5yvrn3jrero
የኬንያ ፖሊስ ምክትል ዋና አዛዥ ጊልበርት ማንጊሲ ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር
"ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰንበት የድንበር ግዛቶቿ ላይ ባሉ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ላይ ያነጣጠረ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሯን አስታወቀች።
የኬንያ መንግሥት የጦሩ አባላት ተደብቀውባቸዋል ባላቸው የማርሳቤት እና ኢሲዮሎ ግዛቶች ላይ "ወንጀለኞችን ማስወገድ" የተሰኘ ከፍተኛ የፀጥታ ዘመቻ ባለፈው ወር፣ታህሳስ 25/2017 ዓ.ም. መጀመሩን ገልጿል።
እነዚህ የሰሜን ኬንያ ግዛቶችን ታጣቂ ቡድኑ "ድንበር ዘለል የወንጀል ድርጊቶችን ለማሳለጥ የሚጠቀምባቸው ናቸው" ሲል የኬንያ መንግሥት ብሔራዊ የፖሊስ አገልግሎት ሰኞ፣ ጥር 26/2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ወንጅሎታል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በሽብር ቡድንነት የፈረጀው እና "ሸኔ" እያለ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በኬንያ ግዛቶች ውስጥም ሕገወጥ የማዕድን ማውጣትን ጨምሮ ሌሎች ሕገወጥ ድርጊቶችን እየፈጸመ ነው ስትል ኬንያ ወንጅላለች።
የኬንያ ብሔራዊ ፖሊስ ቡድኑን "በተለያዩ ሕገወጥ የጦር መሳሪያ፣ አደንዛዥ ዕጾች ዝውውር፣ ሕገወጥ የማዕድን ማውጣት፣ የሰዎች ዝውውር ንግድ ተሰማርቶ ይገኛል" ብሎታል በመግለጫው።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት "ለገንዘብ ሲል እገታዎችን በመፈጸም እንዲሁም ድንበር ዘለል ወረራዎችን በማካሄድ እና በጎሳዎች መካከል ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ በማድረግ ለኬንያ የብሔራዊ ደኅንነት ከፍተኛ ስጋት" ሆኗል ሲል ፖሊስ ጠቅሷል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በበኩሉ ቡድኑን መወንጀል አዲስ ነገር እንዳልሆነ ጠቅሶ በዘረፋዎችም ሆነ በሕገወጥ ተግባራት እንዳልተሳተፈ እንዲሁም "ለፍትህ" የሚታገል ድርጅት መሆኑን ለቢቢሲ ገልጿል።
"እንዲህ ዓይነት ጥሰቶችን የሚፈጽሙ አካላትን ከኬንያ መንግሥት ጋር በመተባባር እንደሚዋጉ" የጦሩ ዋና አዛዥ አማካሪ ጂሬኛ ጉዴታ በሰጡት ምላሽ ተናግረዋል።
ኬንያ በታጣቂዎቹ ላይ ዘመቻ የጀመረችው ባለፈው ወር የኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ወደ ኬንያ ተጉዘው ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ነው።
በውይይቱ ላይ የኬንያው የብሔራዊ መረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል ኑረዲን ሐጂ ተገኝተው ነበር።
ታጣቂው ቡድን "በኬንያ ቦረና እና በኢትዮጵያ ኦሮሞ ማኅበረሰቦች መካከል ያለውን የባህል ትስስር እንዲሁም ቅርብ ዝምድና በመጠቀም በማርሳቤት እንዲሁም ኢሶዮሎ ግዛቶች ውስጥ ባሉ ሕዝቦች መካከል ሰርጎ በመግባት በድንበር አካባቢ በሚኖሩ ማኅበረሰቦች ላይ ጥሰቶችን" እየፈጸመ ይገኛል ብሎታል የኬንያ ፖሊስ መግለጫ።
መግለጫው አክሎም "ቡድኑ በሴቶች እና በታዳጊዎች ላይ ወሲባዊ ጥቃቶችን ጨምሮ ማስፈራራት፣ በኃይል ንብረትን በመውሰድ በአካባቢው በመፈጸሙ ጥቃቶች ማኅበረሰቡን ለሰቆቃ ዳርጎታል" ብሏል።
ሕይወትን፣ ንብረትን እንዲሁም ሰላምን ለማስጠበቅ በግዛቲቱ ተደብቀው የሚገኙ "የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ወንጀለኞችን ለማስወገድ" የኬንያ ብሔራዊ የፖሊስ አገልግሎት የመጀመሪያ ምዕራፍ የወታደራዊ ዘመቻ በይፋ መጀመሩን የአገሪቱ ፖሊስ ምክትል ዋና አዛዥ ጊልበርት ማንጊሲ እንዲሁም የወንጀል ምርመራ አገልግሎት ዳይሬክተር መሐመድ አሚን ትናንት ሰኞ ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, @National Police Service of Kenya በፖሊስ ኃላፊው ዳግላስ ካንጃ ኪሮቼ መሪነት የተጀመረው ዘመቻ ለአገሪቱ ብሔራዊ ደኅንነት አሳሳቢ በሆኑ በተለያዩ ወንጀሎች ላይ በተሰማሩ ሕገወጥ አካላት ላይ ያነጣጠረ ነው ተብሏል።
በኬንያ መንግሥት የተከፈተበትን ወታደራዊ ዘመቻ አስመልክቶ ከቢቢሲ ለተጠየቀው ጥያቄ ምላሽ የሰጠው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከኬንያ ጋር ምንም ጸብ እንደሌለው እና ከኬንያ ጋር ለመዋጋት ምንም ዓይነት አላማ እንደሌለው ገልጿል።
የኬንያ መንግሥት በድንበሮቹ ውስጥ ወታደራዊ ዘመቻ የማካሄድ መብት እንዳለው የገለጹት የቡድኑ አዛዥ አማካሪው፣ ጦራቸው ለመፋለም ምንም ዕቅድ እንደሌለው ተናግረዋል።
"በኬንያ መንግሥት ላይ አንተኩስም። ከኢትዮጵያ በኩል ከመጣ ግን መፋለማችን የማይቀር ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
አክለውም "እኛ ትግላችን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ነው። የኬንያ መንግሥት እንዲህ ዓይነት ምላሽ እንዲሰጥ ያደረጉት ከኢትዮጵያ በኩል በተደረገበት ግፊት ነው" ብለዋል አማካሪው ጂሬኛ።
በኬንያ መንግሥት በኩል ስህተት እንደተፈጸመ የጠቀሱት አማካሪው "ወንጀለኛውን ቡድን ከመለየት ላይ ይልቅ ሁሉንም የተፈጸሙ ጥሰቶች በሙሉ በሠራዊቱ ላይ ተሳብቧል" ብለዋል።
ጦራቸው በእንደነዚህ ዓይነት ሕገወጥ ተግባራት እንደማይሳተፍ አጽንኦት ሰጥተው "ይህንን የሚፈጽሙ የመንግሥት እጅ ያለበት ቡድኖችም ሊኖሩ ይችላሉ" ብለዋል።
የኢትዮጵያ እና የኬንያ መንግሥታት በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ላይ የጋራ ዘመቻ ለማካሄድ ወታደራዊ ስምምነት ሊፈራረሙ መሆናቸውን በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ባጫ ደበሌ ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
አምባሳደሩ በዚህ ዓመት መስከረም ወር ላይ ከቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ጋር ባደረጉት ቆይታ "ለሰላሳ አንድ ዓመታት ታጣቂዎች ሰላማዊ ዜጎችን እየገደሉ ይገኛሉ። ወደ ኬንያ ተሻግረው ሰውን እየገደሉ፣ ከብቶቻቸውን እየዘረፉ ይወስዳሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት ድንበር አቋርጦ ሰዎችን አይገድልም" ብለዋል አምባሳደሩ።
የሁለቱ አገራት መከላከያ ሠራዊቶች ቀደም ሲል ከተፈረመ የመግባቢያ ሰነድ በተለየ መልኩ ወታደራዊ ዘመቻ ለማካሄድ የጋራ ስምምነት ሊፈራረሙ እንደሆነም ጠቁመው ነበር።
አምሳደር ባጫ "ይህ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ጉዳዩ እልባት ያገኛል" ብለዋል።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ ኬንያ ውስጥ በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ የተወሰዱት ሁለት ኮሪያውያን፤ መንግሥት "ሸኔ" እያለ በሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት "ታግተው ለአልሸባብ ተላልፈው መሰጠታቸውን" የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት መግለጹ ይታወሳል።
ታጣቂ ቡድኑ፤ በሶማሊያ ከሚንቀሳቀሰው አልሸባብ ጋር "ቀጥታ ግንኙነት አለው" ሲልም መንግሥት ከስሷል።
ቡድኑ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ስለቀረበበት ክስ ከቢቢሲ ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ ክሱን አስተባብሎ፣ ከሶማሊያው ታጣቂ ቡድን ጋርም ግንኙነት እንደሌለው ገልጾ ነበር።
ከዚያ ቀደም ብሎ ነሐሴ አጋማሽ ላይ የኬንያው የብሔራዊ መረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል ኑረዲን ሐጂ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ጋር አዲስ አበባ ላይ ተገናኝተው ተወያይተዋል።
በኢትዮጵያ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት መግለጫ መሠረት የሁለቱ አካላት የውይይት ዋነኛ አጀንዳ "በሁለቱ አገራት ድንበር እና በኬንያ ውስጥ" በሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጉዳይ ነበር።
ታጣቂ ቡድኑ በድንበር አካባቢ እና ኬንያ ውስጥ "ገባ ወጣ እያለ የተለያዩ እኩይ ተግባራት" እንደሚፈጽም የጠቀሰው ይህ መግለጫ፤ ቡድኑ በአካባቢው እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ "ለመግታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ" ምክክር መደረጉን ገልጿል።
ተቋሙ፤ "ቡድኑ በተለይም ሲፈጽማቸው የነበሩ ዜጎችን የማገት፣ ንብረት የመዝረፍ እና የማውደም እንዲሁም የሰዎችን እንቅስቃሴ የማስተጓጎል ተግባር የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የኬንያ ዜጎችንም ጭምር ችግር ላይ መጣሉ ተነስቷል" ተብሎ ነበር።
የሁለቱ ተቋማት ኃላፊዎች፤ "ድንበር አካባቢ እና በኬንያ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድን አመራሮች እና ታጣቂዎች ላይ የጀመሩትን ኦፕሬሽን አጠናክረው ለመቀጠል" ተስማምተዋል ተብሏል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በበኩሉ በወቅቱ ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ እና በኬንያ ድንበር ላይ በምትገኘው ሞያሌ ከተማ ለተፈጸመ "ተኩሶች፣ የማቃጠል ተግባር እና እገታ የመጀመሪያ ተጠርጣሪ" የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሆነ ገልጾ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት ዓመታት በቀጣናው ላይ "አለመረጋጋትን ሲያመጣ" ቆይቷል በማለት የከሰሰው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፤ "ምርመራዎች በሂደት ላይ ቢሆኑም ቀዳሚው ተጠርጣሪ ሆኖ ይታያል" ሲል ወንጅሏል።
በነሐሴ ወር ከኢትዮጵያ የመጡ ታጣቂዎች ከናይሮቢ ወደ ሞያሌ ሲጓዙ የነበሩ ሰላማዊ ዜጎች መግደላቸውን የማርሳቤት ግዛት አስተዳዳሪ መሐመድ ኩቲ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ሁለቱ አገራት በሚያዋሰኗቸው ድንበር እንዲህ ዓይነት ጥቃቶች የሚያጋጥም ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ሲወነጅል ታጣቂው ቡድኑም በበኩሉ ጥቃቶቹ የሚፈጸሙት በኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ነው ሲል ይከሳል።"
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ