የእኛ መከራ ማለቂያ የለውም። ሞት ስንቃችን ሆኑ። "በጉጂ ዞን ወርቅ በማውጣት ላይ የነበሩ 8 ሰዎች መሬት ተንዶባቸው ሕይወታቸው አለፈ" BBC
"በጉጂ ዞን ወርቅ በማውጣት ላይ የነበሩ 8 ሰዎች መሬት ተንዶባቸው ሕይወታቸው አለፈ"
https://www.bbc.com/amharic/articles/c70kn2y5pn8o
"በጉጂ ዞን ሰባ ቦሩ በተባለ አካባቢ ወርቅ በማውጣት ላይ የነበሩ ሰዎች መሬት ተደርምሶባቸው መሞታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።
በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ውስጥ አደጋው በደረሰበት አካባቢው ነዋሪ የሆኑት ኢዮብ ጂሎ እንዳሉት ለአደጋ መንስዔ የሆነው በማሽን የተቆፈረ መሬት ነው።
"መሬቱ በሁለቱ ቦታ በማሽን ተቆፍሮ ነበር። ሰዎች በተቆፈረው መሬቶች መካከል ገብተው ነበር ወርቅ ሲፈልጉ የነበረው። በዚህም ምክንያት መሬቱ ተደርምሶ ሕይወታቸው ሊያልፍ ችሏል" ሲሉ ተናግረዋል።
አደጋው ሰኞ ጥር 26/2017 ዓ.ም. ጠዋት 3 ሰዓት አካባቢ መድረሱን የዓይን እማኙ ተናግረው ሁሉም ሟቾች ወንዶች መሆናቸውን አስረድተዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች በማሽን እና በባሕላዊ መሣሪያ ታግዘው በአደጋው ከመሬት በታች የተቀበሩትን ሰዎች ለማዳን ለአምስት ሰዓታት ያህል ቁፈሮ ካደረጉ በኋላ ግለሰቦቹ ሕይወታቸው አልፎ አስከሬናቸውን ማውጣታቸውን ተናግረዋል።
ከአደጋው የተረፉ ሰዎች እንደሌሉ እና መሬቱ ተንዶባቸው ተቀብረው የነበሩት የሁሉም ሰዎች አስከሬኖች መውጣታቸውን አክለው አስረድተዋል።
የጉጂ ዞን የኮሚዩኔክሽን ኃላፊ አሸናፊ ዳንቁ በአካባቢው በባሕላዊ መንገድ ማዕድን የሚቆፍሩ ሰዎች ላይ መሰል አደጋዎች እንደሚከሰቱ ገልፀዋል።
"በባሕላዊ መንገድ ማዕድን የሚያወጡ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው። አንድ ጉድጓድ ውስጥ በርከት ብለው ነው የሚቆፍሩት። ይህ ደግሞ አደገኛ ነው" ብለዋል።
አክለውም በባሕላዊ መልኩ ወርቅ የሚያወጡ ሰዎች ተደራጅተው በዘመናዊ መላ ማዕድን ማውጣት እንዲጀምሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ኃላፊው በማኅበራዊ ሚድያ የሟቾች ቁጥር 11 ነው ብሎ የተነዛው ወሬ ሐሰት መሆኑን ገልፀው ትክክለኛ የሟቾች ቁጥር 8 መሆኑን እንዲሁም የሁሉም አስከሬን መገኘቱን አስታውቀዋል።
ሟቾች ወርቅ እና ታንታለም የተባሉ ማዕድኖችን ለማውጣት ሲሞክሩ ነው በመሬት መንሸራተቱ የሞቱት።
በጉጂ አካባቢ እንደ ወርቅ፣ ታንታለም፣ ኤሜራልድ እና ሌሎች ማዕድኖች ይገኛሉ። የአካባቢዎች ነዋሪዎችም በባሕላዊ መንገድ ማዕድናቱን በማውጣት ይተዳደራሉ።
በኢትዮጵያ በባሕላዊ መንገድ ማዕድን ለማውጣት በሚሞክሩ ሰዎች ላይ በሚከሰት የመሬን መንሸራተት ምክንያት ሰዎች ሲሞቱ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
ባለፈው ዓመት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ውስጥ በተመሳሳይ ኦፓል የተባለውን ማዕድን ለመገለግ ከመሬት በታች ባለ ጉድጓድ ውስጥ በነበሩ ሰዎች ላይ መሬቱ ተደርምሶ በርካቶች መሞታቸው ይታወሳል።"
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ