"ስዊትዘርላንድ ስደተኞችን ለመቀበል ፈቃደኛ ላልሆነችው ኤርትራ የምትሰጠውን እርዳታ ለማቆም ወሰነች" BBC

 

 

"ስዊትዘርላንድ ስደተኞችን ለመቀበል ፈቃደኛ ላልሆነችው ኤርትራ የምትሰጠውን እርዳታ ለማቆም ወሰነች"

 https://www.bbc.com/amharic/articles/cm23120denvo

 

የስዊዝ ባንዲራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

 

"ስዊትዘርላንድ፤ የኤርትራ መንግሥት ተመላሽ ስደተኞችን ለመቀበል ባለመስማማቱ ምክንያት ለሀገሪቱ ስታደርግ የነበረውን እርዳታ ለማቋረጥ ወሰነች።

የስዊትዘርላንድ መንግሥት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ኤርትራ ስደተኛ የሆኑ ዜጎቿን እንድትቀበል ለማበረታታት ሲሰጥ የነበረው እርዳታ የታለመለትን ግብ ለማሳካት እንዳልቻለ በሀገሪቱ መንግሥት የተደረገ ግምገማ ካረጋገጠ በኋላ ነው።

የስዊዝ ራዲዮ እና ቴሌቪዥን ዘገባ እንደሚያመለክተው ስዊትዘርላንድ ውስጥ ሰባት ሺህ ገደማ ጊዜያዊ ተቀባይነት ያገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ይገኛሉ። ከሁለት መቶ በላይ በሀገሪቱ የሚገኙ ኤርትራውያንም ሀገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ይጠበቃል።

የስዊትዘርላንድ መንግሥት ኤርትራ ተመላሽ ስደተኞችን እንድትቀበል ለማበረታታት የቀረጸውን "የልማት እርዳታ ፕሮግራም" መተግበር የጀመረው እ.አ.አ በ2017 ነበር።

ፕሮግራሙ ኤርትራ ውስጥ ለወጣቶች የሚሰጠውን የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና በማሻሻል የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እና የሥራ እድል ለማሳደግ ያለመ ነበር።

ይህ ፕሮግራም በሀገሪቱ ያለውን የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ለማጠናከር እንደቻለ የስዊትዘርላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማይክል ስታይነር ለስዊዝ ራዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

ይሁንና ኤርትራ ውስጥ ያሉት የግል ኩባንያዎች እና የሥራ አማራጮች ውስን በመሆናቸው በሀገሪቱ የሥራ እድል የተፈጠረው ተፅእኖ የተገደበ መሆኑን ቃል አቀባዩ ገልፀዋል።

የእርዳታ ፕሮግራሙን ውጤታማነት በተመለከተ በሀገሪቱ መንግሥት የተደረገ ግምገማ ኤርትራ ተመላሽ ስደተኞችን ለመቀበል አሁን ፈቃደኛ ባለመሆኗ ፕሮግራሙ የታለመለትን ግብ እንዳላሳካ አሳይቷል።

ኤርትራ እየተቀበለች ያለችው በፈቃዳቸው የተመለሱ ስደተኞችን ብቻ እንደሆነ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።

የስዊዝ መንግሥት ባደረገው ግምገማም የኤርትራ መንግስት ስደተኞችን በተመለከት ንግግር ለማድረግ ፍላጎት እንደሌለው ገልጿል።

የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማይክል ስታይነር ከኤርትራ ጋር ያለው ግንኙት መሻሻሉን ገልጸው፤ "ይሁንና በስደተኞች ጉዳይ ላይ ምንም አይነት መሻሻል አልታየም" ብለዋል።

በዚህ ምክንያት ፕሮግራሙ ከመጪው ግንቦት ወር ጀምሮ እንዲቋረጥ የስዊትዘርላንድ መንግስት መወሰኑን ቃል አቀባዩ ለስዊዝ ራዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

ከአሁን በኋላም ስዊትዘርላንድ ኤርትራ ውስጥ ለሚካሄዱ ተጨማሪ ፕሮግራሞች ድጋፍ አታደርግም ተብሏል።

ይሁንና የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወደፊት ሊኖሩ የሚችሉ አነስተኛ እና ውስን ዓላማ ያላቸው ድጋፎችን በዚህ ውሳኔ ውስጥ እንዳላካተተ ዘገባው ጠቅሷል።

የስዊትዘርላንድ መንግሥት በዚህ የእርዳታ ፕሮግራም ሊያሳካ አቅዶ የነበረውን የኤርትራውያን ስደተኞች ነገር አሁንም ቢሆን በሀገሪቱ ውስጥ ፖለቲካዊ ግፊት የፈጠረ ጉዳይ መሆኑ ቀጥሏል።

ባለፈው ዓመት የሀገሪቱ ፓርላማ ተቀባይነት ያላገኙ ኤርትራውያን ስደተኞችን ወደ ሶስተኛ ሀገር እንዲላኩ ውሳኔ አሳልፎ ነበር። ይሁንና ምክር ቤቱ፤ ስደተኞቹን ለመቀበል ፈቃደኛ የሚሆን ሀገር እስካሁን ድረስ አላገኘም።"


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?