"የጭካኔ ግድያዎችን ለማስቆም ሰብዓዊነት ብቻ ይበቃል!" ሪፖርተር።

 

"የጭካኔ ግድያዎችን ለማስቆም ሰብዓዊነት ብቻ ይበቃል!"
 
 የጭካኔ ግድያዎችን ለማስቆም ሰብዓዊነት ብቻ ይበቃል! - ሪፖርተር - Ethiopian Reporter - #1 Best And Reliable News Source In Ethiopia
 
February 9, 2025
 
 https://www.ethiopianreporter.com/138164/
 
"ኢትዮጵያ ውስጥ በየትም ሥፍራ የሚፈጸሙ የጭካኔ ግድያዎችን፣ ማሰቃየቶችንና ነውረኛ ድርጊቶችን በጋራ ማውገዝና ማስቆም የሁሉም ዜጎች ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡ መንግሥት ሕግ የማክበርና የማስከበር ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ በንፁኃን ላይ የጭካኔ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ፣ በተገዳዳሪነት የቆሙ ኃይሎችም የዘፈቀደ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ ሰላማዊ ዜጎችን እንዳያጠቁ በአፅንኦት ማሳሰብ ተገቢ ነው፡፡ በመላ አገሪቱ አስተማማኝ ሰላም ሰፍኖ መረጋጋት እስኪፈጠር ድረስ፣ በተቻለ መጠን ንፁኃን የፖለቲካ ሒሳብ ማወራረጃ እንዳይሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ከሚለቀቁ ተንቀሳቃሽ ምሥሎችም ሆነ ከዓይን ምስክሮች መገንዘብ እንደሚቻለው፣ ጭካኔዎች ከመብዛታቸው የተነሳ እጅግ አስደንጋጭ ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ በተፃራሪ ጎራ የተሠለፉ ኃይሎች ሕፃናት ከአዛውንት ሳይመርጡ የጭካኔ ግድያዎች ሲፈጽሙ፣ ችግሩን በአገርና በሕዝብ ላይ ሊደርስ ከሚችል አደጋ አኳያ ማገናዘብ ተገቢ ነው፡፡ ሰብዓዊነት የጎደላቸው የጭካኔ ድርጊቶች አገር እንደሚያፈርሱ መገንዘብ የግድ ይላል፡፡
 
በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጸሙ ነውረኛና የጭካኔ ግድያዎችን ተባብሮ ማስቆም አለመቻል የሚያስከትለው መዘዝ ከባድ እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡ የዕለት እንጀራቸውን ለማግኘት ከሚማስኑ ባተሌዎች ጀምሮ፣ አገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ አስተምራ ለወግ ማዕረግ ያበቃቻቸው ባለሙያዎች ድረስ በጭካኔ ሲገደሉ ማየት ያሳቅቃል፡፡ የአዋቂዎቹ አልበቃ ብሎ ለአቅመ አዳምና ሔዋን ያልደረሱ ታዳጊዎችና ሕፃናት ጭምር የጭካኔ ግድያዎች ሰለባ እየሆኑ ነው፡፡ በከፍተኛ ደረጃ የተለያዩ የእምነት አስተምህሮዎች በሚሰበኩባት አገር ውስጥ ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ አዛውንቶች፣ ነፍሰ ጡርና አጥቢ እናቶች፣ አቅመ ደካሞች፣ ሐኪሞች፣ መምህራን፣ ነጋዴዎችና በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ዜጎች ጭካኔ የተሞላባቸው የዘፈቀደ ግድያዎች ሲፈጸሙባቸው ተባብሮ አለማስቆም መወገዝ አለበት፡፡ በመላ አገሪቱ የብሔርና የእምነት ማንነቶች ሳይገድቡ በሰብዓዊነት በጋራ መቆም የግድ ሊሆን ይገባል፡፡ ሰብዓዊነት እርስ በርስ ለመደጋገፍና አገርን ከአደገኛ ውድቀት ለመታደግ የሚጠቅም የጋራ እሴት መሆን አለበት፡፡
 
ዜጎች በሰላም ወጥተው ለመግባት፣ ሥራቸውን በሕጋዊ መንገድ ለማከናወንና ነፃነታቸው ተጥብቆ እንዲኖሩ የሕግ የበላይነት መኖር አለበት፡፡ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በተለያዩ አንቀጾች ውስጥ የሠፈሩት የዜጎች የሕይወት፣ የአካል ደኅንነትና የነፃነት መብቶችም ይህንን ያረጋግጣሉ፡፡ ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነትና የነፃነት መብት አለው፡፡ ማንኛውም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት አለው፡፡ በሕግ ከተደነገገው ውጪ ወንድም ሆነ ሴት ነፃነታቸውን አያጡም፡፡ ማንኛውም ሰው በሕግ ከተደነገገው ውጪ ሊያዝ፣ ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰርም ሆነ ሊሰቃይ አይገባም፡፡ ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው፡፡ እነዚህ ሁሉ ወርቃማ ቃላት የሠፈሩት ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ነው፡፡
 
በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በዜጎች ላይ ይፈጸማሉ የሚባሉ የመብት ጥሰቶች ተጣርተው አጥፊዎች መቀጣት አለባቸው፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርቶች ሲቀርቡ ከማንም በላይ በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ ያለበት መንግሥት ነው፡፡ መንግሥት ለሁሉም ዜጎቹ ባለበት ኃላፊነት መሠረት ለሚነሱ ቅሬታዎችና አቤቱታዎች ምላሽ መስጠት አለበት፡፡ ዜጎች ሥቃይ ደረሰብን፣ ያላግባብ ታሰርን፣ ንብረታችንን ተቀማን፣ በግፍ ተፈናቀልን፣ በታጣቂዎች ጥቃት ደረሰብን፣ ወዘተ ብለው አቤቱታ ሲያሰሙ የመደመጥ መብት አላቸው፡፡ የሕግ የበላይነት አለ በሚባልበት አገር ውስጥ ሕገወጦች መፈንጨት የለባቸውም፡፡ ሕግ የሚከበረው የእያንዳንዱ ዜጋ ነፃነትና መብት ሲከበር ነው፡፡ ይህ መብት በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠ ስለሆነ ይከበር፡፡ ዜጎች መብታቸውንና ግዴታቸውን አውቀው በሰላማዊ መንገድ የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን ሲያከናውኑ የሕግ ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ጉልበተኞች ሕጉን እየደረመሱ ሰብዓዊ መብት መጣሳቸውን የሚቀጥሉ ከሆነ ግን ለአገር አደጋ ነው፡፡ ሰላምና መረጋጋት የሚኖረው ዜጎች በነፃነት መኖር ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ 
 
ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ ክብሩና መልካም ስሙ ተጠብቆ በአገሩ በነፃነት እንዲኖር የማድረግ ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል እስከሆኑ ድረስ በመካከላቸው ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በሕግ እኩል ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ በመሆኑም በብሔር፣ በእምነት፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ አመጣጥ፣ በሀብት፣ ወይም በሌላ ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት እንዳላቸው በሕገ መንግሥቱ ላይ ሠፍሯል፡፡ እነዚህን መብቶች ተባብሮ ማስከበር ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም በዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጽሙ ኃይሎችን መከላከል ወይም ከለላ መስጠት አይገባም፡፡ በዚህም መሠረት ሰብዓዊ መብት የሚጥሱ ለሕግ እንዲቀርቡ መረባረብ ይገባል፡፡ እነዚህ ወገኖች የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ጥሰው በሕግ የማይጠየቁ ከሆነ ግን የሕግ የበላይነት አለ ለማለት ያዳግታል፡፡ 
 
የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ኅብረተሰብ ውስጥ ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል ነው፡፡ ይህ በተግባር ሲረጋገጥ ደግሞ ምሁርም ሆነ ነጋዴ፣ አርሶ አደርም ሆነ ወዛደር፣ ከተሜም ሆነ ገጠሬ፣ ወጣትም ሆነ አዛውንት፣ ወዘተ በአገራቸው ጉዳይ እኩል ይሆናሉ፡፡ ዜግነትን ማንም ለማንም እንደማይሰጥና እንደማይነሳ ሁሉ፣ መብትንም እንዲሁ ማንም ሰጪና ተቀባይ አይሆንም፡፡ በሞራል ልዕልና ላይ የተገነባ ማኅበረሰብ እንዲኖር የሚፈለግ ከሆነ፣ ሁሉም ዜጎች በነፃነት በአገራቸው ውስጥ የመኖር፣ ከጥቃት ከለላ የማግኘት፣ እንዲሁም በአገራቸው ዙሪያ ገብ ጉዳዮች ተሳትፎአቸው የበለጠ እንዲያድግ ጥረት መደረግ አለበት፡፡ ሕዝብ በሚገባ ፍላጎቱ እየተደመጠ መሆኑን የሚያምነው፣ ደኅንነቱ አስተማማኝ ሆኖ በዚህ መንገድ ሲስተናገድ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የሚከናወኑ የጭካኔ ድርጊቶች አደገኛ በመሆናቸው ውጤታቸው ለአገር ጠንቅ ነው፣ ለሕዝቡም ሥጋት ፈጣሪ ነው፡፡ የጭካኔ ድርጊቶች በትብብር እንዲቆሙ ማድረግ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ይሁን፡፡ የጭካኔ ግድያዎችን ለማስቆም ሰብዓዊነት ብቻውን በቂ ነውና!"


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?