ይሄ ከደስታ በላይ ሐሤት ነው።
ይሄ ከደስታ በላይ ሐሤት ነው።
እኔ አቶ እስክንድር ነጋን ይሁን ባለቤቱን ወሮ ሰርካለም ፋሲልን አላውቃቸውም። በጋዜጠኝነት ሕይወት ያላቸውን ሰብዕና ፈጽሞ አላውቀም። እነሱም ከነመፈጠሬ አያውቁኝም። ጽሁፋቸውንም አግኝቼ አንብቤ አላውቅም። በፖለቲካ ሕይወት የተሳትፎ ደረጃቸውንም ምንም አላውቅም ነበረ። ተጽዕኖ ፈጣሪን ለማግኜት ቅንጣት ፍላጎትም የለኝም። ስለሆነም አያውቁኝም።
ያን ጊዜ የህፃናት ጋዜጠኛ እና የመጋዚን ዝግጅት መምህራችን ጉዳዩን ሳስረዳት እሷም ትግሉን ተቀላቀለችው። ከዛን ጊዜ ጀምሮ አቶ እስክድር ነጋ ፋኖን እስኪቀላቀል ድረስ ብዙ፤ እጅግ በጣም ብዙ የደከምኩለት ቤተሰብ ነበር።
ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል በስደት አገር በጥንቃቄ፤ እራሷን ጠብቃ እና ቀጥታም ያደረገችው ክንውን ለትውልዱ አብነት ነው። ወጣትነቷን አታውቀውም። የትዳርን ትፍስህትን አታውቀውም። መንፈሷ ተረጋግቶ መኖርን #የመራችበት ጊዜ ይኖራል ብየም አላስብም። መቋጫ በሌለው ጭንቀት እሷም፤ እሷን የፈጠረው ማህጸንም ተቀጡ።
የኢትዮጵያ እናቶችን ዕንባ ለማስቀረት ነበር እኔ በትጋት በትግሉ ውስጥ በጉልህ የተሳተፍኩት። ድምጽ የሌላቸው የኢትዮጵያ እናቶች የእኔን የበሞቴ ልዕልቴን እናቴን እቭየ ሆዴን እሙኃይን ጨምሮ ተንገብግበዋል፥ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊሂቃን ፈርጀ ብዙ የትግል ዓይነት። በዚህች ሰከንድ ልጆቻቸው ጭንቅ ላይ ናቸው። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊሂቃን አንድ እስክርቢቶ ገዝተው ያስተማሩ ይመስል ያላመረቱትን ሰብል ሰርክ ለማገዶነት ማቀድ #ሊቆም ይገባል።
ወጣት #ናፍቆት እስክንድር ቢሆን በስደት አገር በተገኘው ዕድል ነፍሱ ተርፋ የመማር ዕድል ማግኙቱ መልካም ነገር ነው። ግን #ከጽንሰቱ እስከ ዛሬዋ ዕለት ሕይወቱ በቀራንዮ ነው የኖረው። ተሰዶም በሰላም #መተንፈስ ያልቻለ ወጣት ነው። በየጊዜው ያሉ የቤተሰብ ፈታኝ ገጠመኞች ሁሉ ይህን የእግዚአብሄር ስጦታ የሆነ ልጅ ሰላሙ እንዲቀማ አድርጎታል። በምን የመቻል አቅም ከዚህ እንደደረሰ እራሱ #ታምር ነው። ሥነ - ልቦናው የተጎዳ ልጅ ነው። ጉስቁልና የሰረጸው የወላጅ አባቱ ፎቶ ሲለቀቅ ስለእሱ የህሊና ጭንቀት እና ሊያመጣ የሚችለው ጦስ ታስቦበት የሚያውቅ አይመስለኝም።
#ተዚህ ላይ አንድ ነገር ትዝ አለኝ።
አንድ ጊዜ አንዲት የአረና ታጋይ እስር ቤት ገቡ። ሦስት ልጆቻቸው #ጎደና ላይ ወጡ ተባለ። እና የእኔ ጓደኛ የሆነች የህክምና ዶር. ኢትዮጵያ ካለ አንድ አሳዳጊ ድርጅት ጋር የቀረበ ግንኙነት ስለነበራት፤ ለሦስቱ ልጆች ድርጅቱ ጥበቃ ያደርግ ዘንድ ጠይቅኳት። የሰጠችኝ መልስ "ለእናቱ የቱ #ይበልጥባታል? #ትግሉ ወይንስ #ልጆቿ" አልችኝ። በውነቱ እኔ የምወስነው ጥያቄ አልነበረም። እኔ እነኛ ልጆች ህይወታቸው በጎዳና ከቀጠለ የትውልድ ተስፋ መቁሰሉ ነበር የጨነቀኝ። እሷ መለሰችልኝ። " እስረኛዋ #ፖለቲካውን #ትተው እና ልጇን ታሳድግ፤ ልጅ ያለው ሰው ልጆቹን በጥንቃቄ የማሳደግ #ግዴታ አለበት" አለችኝ።
ፖለቲከኞች የእኛን ድካም፦ ልፋት በትግሉ ውስጥ እየደከምን እንኳን ያለብን ትብትብ ፈተና ዕውቅና መስጠት ይሆን ማክበርን ይርሱት እና ለቤተሰባቸው፤ ለትዳራቸው እና ለትዳር አጋራቸው የወጣትነት ዘመን ትልልፍ ሊያስቡ ይገባል። ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል በፈጣሪ እርዳታ ለዚህ ስኬት በቅታለች። እሷም እኮ ታስራለች፤ ተሰዳለች፤ በአንድ ክንድ ትዳሩን ለማስቀጠል ደክማለች። የእሷን መጎዳት ዋጥ አድርጋ እንደ ሻማ ቀልጣለች። ልትመሰገን ይገባታል።
"አድርገህልኛል እና አመሰግንኃለሁኝ።" ለጋዜጠኛ ሰርኬ የተጋድሎ ሂደት የሚመጥን ነው። መጨረሻውን ያሳምርላት ፈጣሪ አምላክ። አሜን። የኢትዮጵያ እናቶችም ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲልን ይመስላሉ። በጥልቀት ሊመረመር የሚገባው ክስተት የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች መሻት እና የኢትዮጵያ እናቶች የልጆቻቸው ሐሤት የመሰቃየት ጉዳይ ሊሆን ይገባል። አንዱ ልጅ ጭንቀት ተቀልቦ ይኖራል። ሌላው ደግሞ ይማገዳል። በሁለቱም በኩል የሚሰቃዩት የኢትዮጵያ እናቶች ናቸው።
ነገር ግን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ድምጽ አልባወቹ የኢትዮጵያ እናቶች ማህጸናቸው #ቄራ እንዲሆን የሚታሰብበት መንገድ እና ሂደት ጥናት ተደርጎበት አያውቅም። ትውልድ ሲድን ነው የኢትዮጵያ እናቶች ሊድኑ የሚችሉት። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሊቃውንት ፍላጎታቸው መጨረሻ የለውም። ማገዶው ደግሞ የየዘመኑ ትውልድ ነው። ጸ ጸት እንኳን የለባቸውም።
የሰው ልጅ ሰኞ ተረግዞ፤ ማክሰኞ ተወልዶ፥ እሮብ መዋለ ህፃናት ወይንም ቄስ ትምህርት ቤት ሄዶ፤ ሃሙስ ትምህርት ቤት በመደበኛ ገብቶ፤ አርብ ትምህርቱን ጨርሶ፤ ቅዳሜ ምርቃቱ እንደሚሆን የሚያስቡ ይመስለኛል። አይሰቀጥጣቸውም በየጊዜው ትውልድ መንጣሪ ፕሮጀክት በአዳዲስ ሥያሜ ሲነድፋ። መጥኒ ለዛች መከረኛ ፈላስፊት ኢትዮጵያ።
የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የራሳቸውም ልጅ ሆነ፤ የማህበረሰቡ ልጅ እንደ ልጃቸው የማየት አቅም ሊፈጥሩ ይገባል። በእርምጃቸው ሁሉ ሰው ማትረፍን ሊያስቡበት ይገባል። ትውልዱ በስጋት ትምህርቱን ቢማር እንኳን ጠንካራ ዜጋ የመሆን ዕድሉ ስስ ነው። ይህ ዘለግ ተደርጎ ሊታሰብበት የሚገባ ቁምነገር ነው።
ኢትዮጵያን ቁምነገር የማድረግ ዓላማ የትውልዱ የመኖር ፈቃድ ያለ ስጋት መሪ ሃሳብ ሊሆን ይገባል። አዲስ ትግል ሲወጠን ማገዶው ከስቶር ሳይሆን የመሐጸን ፍሬ ስለመሆኑ በጥልቀት ሊታሰብበት ይገባል። በሌላ በኩል ልጆች ወላጆቻቸው በጋራ ሲያሳድጓቸው እና በተናጠል ሲያሳድጓቸው መጠነ ሰፊ ልዩነት አለው። በቀጣይ የሕይወታቸው ዘርፍም ተጽዕኖ አለው። ስለሆነም የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ከራሳቸው ጋር በጥሞና ሊመክሩ ይገባል። የየዘመኑ ፖለቲከኞች ትውልድን ከማናቸውም ስጋት እና ሰቀቀን ማትረፍ ህሊናዊ መርሃቸው ሊሆንም ይገባል። መራር ሃሳብ ነው ፥ ገቢር ላይ መዋል አለበት።የአንዲት እናት ደስታዋ ልጇ ነውና።
ብርቱዋ እናት ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል ከናፍቆትሽ ጋር ለስኬት ስለበቃሽ እንኳን ደስ አለሽ።
የእኔ ክብሮች እንዴት ሰነበታችሁልኝ? እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ ደህና ነኝ።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
#Sergute©ሥላሴ
03/06/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ