ኢትዮጵያ #በልዕልና ቀደምትነት የተሰራች አገር ናት። ኢትዮጵያ በፋንታዚ ክምር አዲስ #እምትሰራ አገር አይደለችም።

 

ኢትዮጵያ #በልዕልና ቀደምትነት የተሰራች አገር ናት። ኢትዮጵያ በፋንታዚ ክምር አዲስ #እምትሰራ አገር አይደለችም።
 
"የቤትህ ቅናት በልኝ።"
 
 May be an image of 1 person
 
1) "ኢትዮጵያ #እንደገና እየተሠራች ያለች አገር ናት።" ኢንጂነር አይሻ መሃመድ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሚኒስተር። #ጸያፍ አገላለጽ።
ኢኒጂነር አይሻ መሃመድን ሞግቻቸው አላውቅም። እንዲያውም ከመከላከያ ሚር ሲነሱ ዲሞሽን ነው ብየ ለሳቸው ወግኜ የአብይዝምን ውሳኔ ሞግቻለሁኝ። ምክንያቴ ኢንጂነር አይሻ የወቅቱ የመከላከያ ሚር በነበሩ ጊዜ በኢትዮጵያዊነት ላይ ያላቸው ውስጥነት በንግግራቸው ትልልፍ ስላልነበረበት ነው የተለየ አክብሮት የነበረኝም። ዩንቨርሷል ኢትዮጵያን ሲያነሱ ገፃቸው ፈክቶ እመለከት ስለነበር ከማክበር ውጪ ሙግት በእኔ ብዕር ነክቷቸው አያውቅም ነበር። 
 
በሌላ በኩል ሠራዊት ነክ ጉዳዮችን እራሱን የቻለ ሙያ፤ ተመክሮ ስለሚጠይቅ ተዳፍሬው የማለውቅ ዘርፍ መከላከያ እና የኢኮኖሚ ጉዳዮችን ነው። የሆነ ሆኖ ከፋና ቴሌቪዥን ጋር የመከላከያ ሚኒስተሯ ኢንጂነር አይሻ ያደረጉትን ቃለምልልስ አዳመጥኩኝ። ቢቢሲ የአማርኛው ዘርፍ በእሳቸው ዙሪያ ያወጣውን ተከታታይ ዘገባም አንብቤያለሁኝ።
 
ስለሆነም ለስሜቴ ቅርብ የሆነውን ሃሳብ ብቻ ላነሳ ፈቅጃለሁኝ። #በልቅና #በጥሞና ተስርታ ባደረች አገር ተፈጥሮ፤ አድጎ፤ ለቁም ነገር ተበቅቶ " ኢትዮጵያእንደ #ገና #እየተሠራች ያለች አገር" ብሎ መናገር የዘመናት የኢትዮጵያ ታሪክን #መዳፈርም ነው። በአንድ ወቅት ቤተ - ኢሳት በአክቲቢስት ታማኝ በየነ የተመራ ቡድን ሲዊዝ ስብሰባ በመጣ ጊዜ ይህን መሰል አገላለጽ አድምጬ ነበር። 
 
ከቡድኑ ውስጥ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ቀጸላ ዛሬ ኢንጂነር አይሻ መሃመድ ያሉትን ስንኝ ቃል የሚመሳሰል ቃል ተናግራዋለች። ዘግባውን ሠርቼ የምልከው ደጉ ዘሃበሻ እና ደጉ ሳተናው ነበሩና በዘገባየ ላይ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ቀጸላ "ኢትዮጵያ ገና ያልተሠራች አገር" ብላ ማስተማሯን ገልጬ ጽፌ ነበር። 
 
እኔ የሥላሴ ባሪያ ማንንም ስለማልፈራ ያየሁትን፤ የሰማሁትን እንቅጩን ለመናገርም ነው በራሴ ወጪ፤ በራሴ ጊዜ ረጅም መንገድ ተጉዤ የምታደመው። በወቅቱ ቂም ጠንስሶ ብዙ ፈተና ታልፎበታል። ማንም ይሁን ማን ከኢትዮጵያ ተፈጥሮ በታች እንጂ በላይ አይደለም እና ለዕውነት ጋራጅ ስለማያስፈልገው እንቅጩን መግለጽ ይገባል።
 
በየጊዜው የሚፈበረኩ ቅንጥብጣቢ ዕሳቢወች ናቸው ኢትዮጵያን ዘመኗን ሁሉ ለቀራንዮ የዳረገው። የሚዳርገውም። ኢትዮጵያ ረቂቅ ሚስጥር ናት፦ ኢትዮጵያ ሳይንቲስት ናት፤ ኢትዮጵያ ፈላስፋ ናት፤ ኢትዮጵያ ህግ ናት፤ ኢትዮጵያ ዩንቨርስም ናት፤ ኢትዮጵያ አናባቢም ተነባቢም ናት ብየ፦ ኢትዮጵያኒዝም ካሪክለም ተነድፎለት ልንማረው የሚገባ የዕውቀት ዘርፍ ነው በማለት መፃፍ የጀመርኩትም በ2014 እአ ነበር። 
 
#በጸጋየ ድህረ ገጽ እና ራዲዮም ከ2008 እአአ ጀምሮ በትጋት ሠርቸበታለሁኝ። በዩቲውቤም እንዲሁ። ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ነውም የትግሌ ካፒቴንም ነው። ይህን ፓልቶክ ላይ የነበረ ሁሉ የሚያውቀው ዕውነት ነው። አባባሌ ትክክልም ነው። የሰሞኑን ውጥረት እና ወጀብ እሰቡት እና የሞዴሊስት ሐሤት ደረጄ ውጤት እንደምን የሚወራጨውን አየር #ረብ እንዳደረገው ከልባችሁ መርምሩት። በቅንነት። ኦኦ! ለካንስ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አጤ ቅንነት ስለመፈጠሩም አይውቅም። 
 
ወደ ቀደመው ምልሰት ሲሆን ኢትዮጵያ ፈጥራ፤ ለወግ ለማዕረግ አብቅታ "ገና ያላለቅሽ ፕሮጀክት ነሽ???" #ሰቅጣጭ ግንዛቤ ነው። በምን አቅሙ ይሆን በዊዝደም የተገነባችን አገር " እንደ ገና እዬተሠራች አገር" ማድረግ የሚችለው የአብይዝም ካቢኔ????? "ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳል" ይላሉ ባለቅኔወቹ ጎንደሮች። 
 
የነፃነት የድል ንግሥት፤ የፓን አፍሪካኒዝም ልዕልት፤ የአፍሪካ አንድነት መሥራች፤ የተመድ ቀደምት ቤተኛ፤ የእኔ የምትለው የመኖር የአኗኗሪ #ስልጡን ዘይቤ በቋሚነት ያላት ብቁ፤ ልዑቅ፤ ልዕለ አገር እንደ አንድ የጭቃ ቤት ምርጊት ተደርጋ የምትታይበት ጉዳይ አይገባኝም። እንዲገባኝም አልፈቅድም። 
 
የመከላከያ ሚር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ አፋቸውን ሞልተው የተናገሩት ሥንኝ #የተፈለሰ ስለሆነ ሊስተካከል ይገባል። የሴት ሊቃናት ወደፊት እንዲመጡ ጉልበታም ተጋድሎ አድርጌበታለሁኝ። ይህ ዕድል ከሰማይ የወረደ መና አይደለም። የኢትዮጵያ እናቶች ዕንባ መሠረቱ የኢትዮጵያ ሴት ሊቃናት ወደ መሪነት እንዳይመጡ የገበርዲን እና የከረባት ትልም ስለሆነ ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባል፤ ከዕንባችን ጎን ቁሙ በሚል በትህትና በቀረበ አቤቱታ የተገኜ ዕድል ነው። ተገብረንበታል።
 
ምክንያቱ ተሠርታ ባደረች አገር የተፈጠርን ልጆቿ የየዘመኑን ፖለቲካ ባህሪ በመመርመር የትግል አቅጣጫችን በብቁ ምህንድስና ስለተመራ ነበር 50% የኢትዮጵያ ካቢኔ በሴት ሊቃናት እንዲሆን የተደረገው። የለውጡ አመክንዮ መነሻው ይህ ጭብጥ ስለሆነ። ስለሆነም የተገኜው ዕድል ተሠርታ በኖረች አገር የተገኜ ነውና ሊከበር ይገባል።
 
2) ኢንጂነር አይሻ መሃመድ የኦነግን የጫካ ታጋይ "ሸኔ" ሲሉ ፋኖን "ጽንፈኛው ፋኖ" የሚል ቃል ሁለት ጊዜ ተጠቅመዋል። በሁለተኛው ንግግራቸው "#የጽንፈኛው ወይንም የሸኔ" ወይንም "#ጽንፈኛው" ያሉት ፋኖን ነው። ውስጣቸውን አይቸበታለሁኝ። #ጽንፈኛ" ካሉ አንዱን #መፍራት የለባቸውም። ከፋን ያሉትን ሁሉ "#ጽንፈኛ" ማለት ይችላሉ ካመኑበት። በሥማቸው መጥራት ከሆነም ቅጥል ሳያስፈልጋቸው "ሸኔ፦ ፋኖ" ማለት ይችላሉ። እኔ አንድም ቀን "ሸኔ" የሚለውን ቃል ተጠቅሜ አላውቅም። 
 
እንደማስበው ጊዜ አጥቼ አልፃፍኩበትም ግን ምንግዜም የወልቃይት ጉዳይ ቀጣይ ስለሆነ ቆይቼም ቢሆን እጽፍበታለሁኝ የአቶ ጌታቸው እረዳ እና የአንባሳደር ሬድዋን ቃለምልልስ፥ ይሁን የመከላከያ ሚኒስተሯ ኢንጂነር አይሻ ቃለምልልስን ውስጡን ሳጠናው ብልጽግና ወጥ ፓርቲ ነኝ የሚለውን አመክንዮ የሳሙና አረፋ ሆኖ ያገኜሁበት አጋጣሚም ነው። ብሄራዊ ጉባኤን ምስክር አድርገው ብልጽግና ወጥ ነው እያሉ የሚሞግቱለትም አሉ። 
 
የሆነ ሆኖ የህወሃት የዶክትሪን መሠረት የአማራ ጥላቻ ነው። በዚህ ላይ ምንም ስላልተሰራ የአብይዝም ሊቃናት አሁንም እዛው ላይ ስለመሆናቸው ማረጋገጥ ችያለሁኝ። ይህ ሳይስተካከል በፍጹም ማግሥት በተስፋው ልክ ይቆማል ብሎ ማሰብ በዱቡሽት ላይ ቤት ለመገንባት እንደማሰብ እቆጥረዋለሁኝ። አልተሠራበትም። የህወሃት አስተሳሰብ ሊሸነፍ የሚችለው በኢትዮጵያዊነት ፍልስፍና ብቻ ነው። ዜጋ እኩል ነው የትም ይኑር የት፤ የትኛውንም ሃይማኖት ይከተል፤ የትኛውንም የፖለቲካ መስመር ይምረጥ፤ ከየትኛውም ዞግ ይፈጠር ከሚል አገርንም ትውልድንም በሚያድን የፖለቲካ ካስማ ሲሠራበት ይሆናል።
 
የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች ከዘመነ ህወሃት በአስተሳሰብ ደረጃ የአብይዝም ሊቃናት አንዲት ስንዝር ፈቅ አላሉም። ኢትዮጵያዊነት በውነቱ አንጀት የሚበላ ማንነት ነው። በኢትዮጵያ ሁለመና ላይ ቁብ ብሎ ኢትዮጵያዊነትን በሚያከስለው የጥላቻ እና የአድሎ ቀመር ውስጥ መዳከር ያስገምታል።
 
የመከላከያ ሚኒስተሯ ጫካ ላይ በሚገኙ የኢትዮጵያ ልጆች ጉዳይ ቁልጭ ያለ አድሎ ነው ያየሁባቸው። መጀመሪያ ሳዳምጥ ግድፈት ይሆናል ብየ አሰብኩኝ፥ ሲደግሙት ግን #የተመረዘ አስተሳሰብ እንዳለ ተረዳሁኝ። አቤቱ ብልጽግና ሆይ ሥራህን ገና #ታቱ በማለት እንኳን አልጀመርከውም። ቁንጮው በዚህ በተቃጠለ ካርቦን ዕሳቤ ከተጓዘ ነገ #ይደክመዋል
 
3) "ኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላምያላት አገር ናት።" (የመከላከያ ሚኒስተሯ ኢንጂነር አይሻ መሃመድ።)
 
ክብርት ሆይ! እንደ አፈወ ያድርግላት ለሳይንቲስቷ ኢትዮጵያ። ትግራይ መሄድ ትችላላችሁን? አማራ ክልል ትልማችሁን እኩል ተደራሽ እያደረጋችሁ ነውን? ኦሮምያስ ደልቶታልን??? ከአዲስ አበባ ስንት ኪሎ ሜትር በሰላም ወጥቶ መመለስ ይቻል ይሆን? እንደ ደላው አገር ህዝብ እኮ ነዋሪው የአውሮፕላን ዋጋውን ካልቻለ ከቤተሰቡ ጋር ተቆራርጧል እኮ።
 
ለመሆኑ የኢትዮጵያ የአገር አቋራጭ ሹፌሮች፤ የአገር ውስጥ ሹፌሮች መኖር አላቸውን? ሹፌርነት እኮ የሞት መንገድ ሆኗል በኢትዮጵያ ህይወት። ከቤተሰቡ ጋር የተቆራረጠው ቤት ይቁጠረው። ሰው በገንዘብ በድርድር እንደ ሸቀጥ እየተሸጠ እኮ ነው። ስንቱ ታፈነ? ስንቱ እንደ ወጣ ቀረ? ስንቱ አድራሻው ጠፋ? ስንቱ ቤቱ ተበተነ?
 
ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ መፈናቀል ደረጃዋ እኮ ቁጥር አንድ ነው። ይህ ክብር ነውን? ይህ ግርማ ሞገስ ነውን? አዲስ አበባ እራሱ አንድም ብሄራዊ በዓል ካለማስጠንቀቂያ ዓዋጅ ተከብሮ ያውቃልን ሙሉ 7 ዓመት?
 
የአማራ ክልል ያልተሻረ ስውር #የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ እንዳለ አያውቁንም? ሠራዊቱ ሠፈር ወይንስ ደንበር ማስጠበቅ ይሆን መደበኛ ተልዕኮው???? ክብርት ሆይ! እውነት ሊደፈር ይገባል። ይልቅ መፍትሄ አመንጭቶ በመሸነፍም ውስጥ ቢሆን ኢትዮጵያን የሰላም ቀጠና የማድረግ ትጋት ተሻግሮ የሚወረወር አለሎ ሳይሆን አንጋፋው ተቋመወ መከላከያ ድርጊት ላይ ሊያውለው የሚገባ ጉዳይ ይመስለኛል።
በራስ ህዝብ ላይ #ድሮን እያዘነቡ ሰርክ "ኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም አላት" ማለት ትጥቅ አስፈቺ ግንዛቤ ነው። ኢትዮጵያ ለእኔ #ኢመርጀንሲ ሩም ያለች እናት አገር ናት። 
 
አብዝተው ክብርቷ ስለ ሪፎርሙ ትጋት እና ስኬት አስተያዬት ሰጥተዋል። አይደለም ሌላው የብልጽግና ሊቁ እኮ ከኖረበት ዕይታ ፈቅ አላለም። መሪው ከተመሪው ህዝብ ተሽሎ ከጥላቻ፤ ከግለት ነፃ ሊሆን አልቻለም። ህወሃት አካሉ እንጂ ገዢ መንፈሱ ፋፍቶ እና ጎልብቶ ነው እኔ በግራ ቀኙ ቃለምልልስ የተረዳሁት። መጀመሪያ ሚኒስተሮች ይዳኑ። ዕውነትን ይቀበሉ። ሰው እኩል ነው ብለው ይመኑ። ይህን አላየሁም። አንዱ ሲቃለል ሌላው ተከብሮ ሲሞገት ነው የማዳምጠው። እማታውቁት ነገር ሳይለንት ማጆሪቲው ያለውን #የዝምታ አቅም እና አቋም ነው። ለዚህ ነው ትልልፋ #አና ያለው። ቂም እና በቀልን፤ ጥላቻ እና ማግለልን ያላሸነፈ መሪነት ስኬቱ ተኩረፍርፎ ይቀራል።
 
"ሀገራዊ አስተሳሰብ የተላበሰ የመከላከያ ሰራዊት"
 
ማህበረ ቅንነት ደህና እደሩልኝ። አሜን።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
03/06/2025
ትዕግሥት ሲያልቅ፤ ፍቅር ይሰደዳል።
ፍቅርም ሲያልቅ፤ ትዕግሥት ይሰደዳል።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?