ትምህርት የመኖር ፍሬዘር #ኦክስጅን ነው፤ ፍጹማዊ #ሰላምን በአጽህኖት ይሻል።

 

ትምህርት የመኖር ፍሬዘር #ኦክስጅን ነው፤ ፍጹማዊ #ሰላምን በአጽህኖት ይሻል።
"አቤቱ ንፁህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 May be an image of 2 people, child and text
ትምህርት የራዕይ፤ የትልም፤ የሰለጠነ ግብ ማስፈጸሚያ ቁልፍ ጉዳይ ነው። ሰሞኑን በትምህርት ዙሪያ ከተለያዩ ባለሙያ ወገኖቼ አቶ ሙሼ ሰሙን ጨምሮ የፃፋትን አነበብኩኝ። ደስ ብሎኝ ነው ያነበብኩት። ምክንያቴ በማህበራዊ ዘርፍም አዋቂወች ትጋታቸው ስለአረካኝ ነው። ጉዳዬ ባዩ በርከት ሲል የሚያበረታታ ሙቀት ይሰጣል። አንዳንድ ሚዲያወችም ተነጋግረውበታል። በቂ ነው ብዬ ባላስብም።
 
ነገረ - ትምህርት በዓመት አንድ ወይንም ሁለት ቀን በመወያዬት ብቻ ስልጣኔን፤ እድገትን፤ ስኬትን ማግኜት #ጋዳ ይመስለኛል። አብሶ ሰላም ከሌለ አይደለም ተማሪው መምህሩ፤ የትምህርት ቢሮወች፤ የበታች አስተዳደሮች እንደምን የህሊና ተግባራት ሊከውኑ ይችላሉ? ሌላው ቀርቶ የኢትዮጵያ ዜናወች "#በሰበር" በድንገቴ፤ በአስጨናቂ ዜናወች የተጨናነቁ ናቸው። እንኳንስ ለልጆች ለእኔ ሙሉ ዕድሜ ላይ ለምገኘውም ይከብዳል። ለበሽታም ይዳርጋል። 
 
እራሱ ከስንት ጊዜ በኋላ አንድ ቀን የምትገኝ የይምስራች፤ የተስፋ ፍንጣቂ ወይንም ፍንካች ሁነት ሲገኝ እንኳን የሚለወሰው በስጋት፤ ወይንም በማቃለል፤ ወይ በማጣለል በዛው ሌት እና ቀን ጊዜውን አቅሙን ሁሉ በሚውጠው የፖለቲካ ጉዳይ ጋር ተዛምዶ ይቀርባል። ዓውደ ዓመታት ከትንፋሻችን ጋር የተዋህዱ ናቸው። እነሱን እንኳን ስክን ብለን፤ ቀልባችን እፎይ ብሎ እንዲያሳልፍ ፈቃድ የለም።
 
አንድ ቀን አብረን ለመሳቅ #ንፋጎች ነን - እኛው እራሳችን፤ አብረን የተሰጠንን አክብረን ከትከት ቢቀርብን #ውሽክ ለማለት እንኳን አልታደልንም ብል ይሻለኛል። ይህ ደግሞ በብዙ ሁነት የውስጥ #ጤንነታችን ይጎዳዋል። ጤና ማጣት ደንበር የለሽ ነውና። ለነገሩ የሚንቀጠቅጡ - ትንፋሽ የሚያሳጥሩ ዜናወችን አቅራቢወች #የህዝባቸው #ጤና አጀንዳቸው የሆነም አይመስለኝም። ሁሉም እናት እንዳለው የሚዘለል ይመስለኛል። መተዛዘን በዓውዳችን መንኗል።
 
የሆነ ሆኖ ሰላም አልቦሽ እንደምን ዕውቀት #ነፃነት ሊያገኝ ይችላል? የሙሉ የአየር ጊዜው መረጃ ጦርነት + ጦርነት + ጦርነት + መታገት + መሰወር + መታሰር + መደፈር + መገደል > የተስፋ ስኬት። ከአነጋገር፤ ከአካሄድ፤ ከአገላለጽ ጀምሮ ትውልድን ሊያድኑ፤ ትውልድን ሊፈውሱ፤ ትውልድን በሙሉ የራስ መተማመን ክህሎት ሊያንጹ በሚችሉ ቁም ነገሮች ላይ አትኩሮቱን ስትመዝኑት ቁልቁል ያሰኜዋል።
 
ሙሉ ፯ ዓመት ለጦርነት፤ ለውድመት የዋለውን መዋለ ገንዘብ፤ ለጥላቻ ለበቀል እና ለቂም የፈሰሰው የሃሳብ ማዕድ ስታሰሉት እኛ ኢትዮጵውያን በተፈጠርንበት ኦርጋኒክ ተፈጥሮ ልክ አለመሆናችነን መመዘን ያስችላል። ከአንደበታችን ክፋ ሃሳብን፤ ስላቅን፤ ማንአኽሎኜነትን፤ #መስቃን፤ ጥላቻን የሚያበረታቱ የንግግር ዘይቤወችን እንዳሻን ስናዠከዥከው ስንት መዋዕለ መኔፈስ - ስንት ጊዜ ፈሰሰላቸው? የተቃጠለው ጊዜያችን - በከንቱ ያባከነው ሰዓታችን ሁሉ የትውልድን መንፈስ #በላርባ #ረመጥ እያርገበገብን ስለመሆናችን ትዝ ብሎን አያውቅም።
 
በዚህ ውስጥ ሳይንቲስት፤ በዚህ ውስጥ ፈላስፋ፤ በዚህ ውስጥ ተመራማሪ፤ በዚህ ውስጥ ዓራት ዓይናማ ኢንጂነር፤ በዚህ ውስጥ የቴክኒክ ባለሙያ፤ የህክምና ጠበብት ማፍራት እንደምንችል እንሰበው። እንመዝነውም። ዕድሜ ዘመናችን በሙሉ ኋላቀሮች መባላችን አይጠዘጥዘንም። የራሳችን #ደርማሽ እራሳችን መሆናችን እንዲመረምረን - እንዲፀጽተን ብንፈቅድ በከንቱ የባተልንበት የሬሾ መጠን ግብረ መልሱ ይነግረን በነበረ። 
 
በግድፈቶች ውስጥ እኔም አለሁበትን ብንቀበል፤ #ቢጸጽተን እራሳችን ብንመረምር በአለን የመንፈስ - የተፈጥሮ - የሊቃውንት፤ የሊሂቃን አቅም እንኳንስ ኢትዮጵያን ፓን አፍሪካኒዝምን፤ የጥቁር ህዝብ ተስፋማነታችን ማስቀጠል በቻልን ነበር። ግን #ገና ነን። የግል ዝናችን፤ የተጽዕኖ ፈጣሪነት ህልማችን ይበልጥብናል።
 
ሁላችንም በየዘርፋችን #ትክክል ነን፤ #አልተሳሳትንም ብለን ስለምናምን ወደ ትክክለኛው #የዕውነት #ርዕዮት ለመምጣት አልተቻለም። ጊዜ - ይሄዳል - በተፈጠረበት ፈቃድ ልክ ይተማል። አጤ ጊዜ፤ እጬጌው ክፍለ ዘመኔ ሳይቀር አዝሎን ወይንም አሽኮኮ አድርጎን ሳይሆን በቆልማማ አፍንጫው እያሾፈብን #መጪ ይላል። ህዝባችን ለለት ጉሮር፤ ለለት ከፈን፤ ለለት መጠለያ ለመብቃት እስከ ምን ያህል ዓመት #ሊጠብቅ እንደሚችል አላውቅም።
 
ትናንት ጦርነት፤ ዛሬም ጦርነት። ነገም ጦርነት በተቃደ ቁጥር የትውልድ ሥነ - ልቦና ይጎዳል። የትውልድ የመማር ፍላጎቱ #ይጫጫል። ቀድሞ ነገር የብልጽግና መራሹ መንግሥት ካቢኔ በትምህርት ጉዳይ ላይ በዓመት በምን ያህል አጀንዳ፤ ምን ያህል ሰዓት ተወያዬ? ትምህርት ሚኒስተር፤ የሰለም ሚኒስተር፤ መከላከያ፤ የደህንነት አካላት ለመማር ማስተማር ኦክስጅኑ ሰላም በመሆኑ በዚህ ዙሪያ ምን ያህል ሰሚናር - ምን ያህል ወርክሾፕ - ምን ያህል ፓናል ዲስከሽን አካሄዱ? በትምህርት ዙሪያ በዓመት ምን ያህሉ ጊዜ የመንግሥት ሚዲያወች - ተጉ??? 
 
ወላጆች እና ትምህርት ቤቶች፤ ወላጆችእና የመንግሥት አካላት በምን ጉዳይ መከሩ? ለትምህርት ብቻ ሊውሉ የሚገባቸው ተቋማት ስለምን የሌላ ጉዳይ አስፈፃሚ እንዲሆኑ - ይታጫሉ? ትምህርት እና ጦርነት፤ ትምህርት እና ጥላቻ ለትውልድ ተስፋ ምን ያህል #አትራፎት አላቸው??? 
 
ትምህርት ወለድ ዕውቀት የህሊና ጉዳይ ነው። ህሊና ደግሞ እርቦ፤ ሲሶ ሳይሆን ሙሉ ነፃነት ይሻል። ለትምህርት ሥርዓቱ ንጹህ ነፃነት ኦሮምያ፤ አማራ፤ ትግራይ፤ አልፎ አልፎ በሱማሌ እና በአፋር ክልሎች ምቹ - እርግጠኛ የሚያደርግ ሰላም አለን? ሌላው ቀርቶ የትምህርት ሥርዓቱ በአዲስ አበባ እና በዙሪያው ባሉ ከተሞች መታመን የሚያስችል፤ ከጭንቀት የተረፈ አየር አላቸውን? አንፃራዊ በሆነ ሁኔታ ደቡብ ይሻላል። ደቡብም ቢሆን የጦርነቱ ዜና አያውከውም ብዬ አላስብም። "አንተ ደህና እንድትሆን ጎረቤትህ ደህና ይሁን" ይትበኃል ነውና።
 
የፈለገ ሥልጡን ፖሊሲ ይከተል አንድ አገር ሰላም ከሌለ ህሊና ካልተረጋጋ ጭንቀት እና ፍርሃት ከነገሠ የሚታሰበው የትውልድ ተስፋ ለስኬት አይበቃም። ሙሉዑ ሰብዕና ያለው ትውልድ ለመፍጠር በራሱ የሚተማመን፤ በብቁ ሰላም የታጋዘ የትምህርት ሂደት የግድ ነው። ጦርነት ሁሉንም ነገር ነውና የሚቀማው። ጦርነት እራስን ይቀማል። 
 
ስለ ትውልድ የሚስብ፤ ስለ ትውልድ ግድ የሚለው፤ ውስጣዊ የሆነ #ያልባለቀ መንፈስ ሰላም የህሊናው አለቃ እንዲሆን ይፈቅዳል። ለዛ ደግሞ አደግድግ ይተጋል። ኢትዮጵያ አፈሯም፤ አዬሯም ሰላም ይናፍቀዋል። ዕውቀት ላቅ ያለ የህሊና አቅም በልቅና #ለማብቀል ከሰላም ውጪ ምንም የመፍትሄ ጎዳና የለም። 
 
የብልጽግና ካቢኔ መትጋት ያለበትም፤ አቅም የመዋለ ንዋይ ሆነ የጤነኛ መንፈስ ዕውደትን መፍቀድ #የአዘቦት፤ ወይንም የአፍላ፤ ወይንም የትርፍ ጊዜ ሳይሆን መደበኛ ሥራው ሊሆን ይገባል። ብዙ የሚኒስተር መስሪያ ቤቶች ተልዕኳቸውን ቀለል ባለ አፈፃጸም ሊከውኑ ይችላሉ። ነገረ ትምህርት ግን የትምህርት ሚኒስተር ብቻ ሊሆን አይገባም። ከጓዳ እስከ አደባባይ ሁሉም በባለቤትነት፤ ሁሉም በተጠያቂነት የማህበረሰቡ፤ የሃይማኖት ተቋማት፤ የሰብዓዊ ድርጅቶች፤ የጸጥታ እና የደህንነት አካላት ሁሉ አትኩሮታቸውን በበቃ ሁኔታ ሳይሳሱ በልግስና ሊመግቡት ይገባል።
 
ሰላም #አንፃራዊ ቢሆን እንኳን የማግሥትን ተስፋ አያፋፋም። በኢትዮጵያ ፍጹም ሰላም የሚሰፍንበት ሁኔታ ላይ ቆራጥ ውሳኔ፤ ብልህ አመራር፤ የተደራጀ የተግባር ንቅናቄ ይጠይቃል። ትምህርት የእኔ፤ ትምህርት ለእኛ፤ ትምህርት ለኢትዮጵያ፤ ትምህርት ለፓን አፍሪካኒዝም፤ ትምህርት ለግሎባላይዜሽን፤ አስፈላጊነቱን መቀበሉ ከራስ መጀመርን ይጠይቃል። 
 
እንዲህ እንግልት ብላ የምታስተምር እና ነገን እንዴት ትጠብቀው? የሁላችንም አጀንዳ ሊሆን የሚገባ ይመስለኛል። አሁን ከሆነ በትምህርት ውስጥ እራሱ የመደብ መፈጠር እንደ አጨበጨበ እያዳመጥኩ ነው። በትምህርት ብቻ ጨቋኝ እና ተጨቋኝ ማህበረሰብ መፍጠር #ዕዳ ነው። ተከፍሎ የማያልቅ ዕዳ። እርግጥ ነው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዲግሪ የለለው ሰብዕና ለአባልነት፤ ለአካልነት የሚቀፋቸው እንዳሉ እርግጥ ነው። ስኬቱም ሰማይ ደጅ የሆነው ይህ የንቀት መስክ ነው።
 
 በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያን ያበዷት ሊሂቃኑ በኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዳሉ የማይቆጠሩም ናቸው። ገበሬው ግዴታ እንጂ የፖለቲካ #ውክልና የለውም። ይህ ዝበት መቀጠሉ ይመስለኛል እርካታ የራቀው ፖለቲካ ምድራችን እያስተናገደች የምትገኜው። ወደፊትስ ነው ጥያቄው? 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
19/09/2025
ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ለሁሉም!
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።