"#ፕሮፌሰር ዶር ብርሃኑ ነጋ "ጉራጌ ስለሆኑ ወጀብ በዛባቸው ያልከው" በፍጹም #አይመስለኝም - ለአቶ ኤርምያስ ለገሰ።

 

"#ፕሮፌሰር ዶር ብርሃኑ ነጋ "ጉራጌ ስለሆኑ ወጀብ በዛባቸው ያልከው" በፍጹም #አይመስለኝም - ለአቶ ኤርምያስ ለገሰ። 
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን!
 
 
ጤና ይስጥልኝ አቶ ኤርምያስ ለገሰ እንደምን ሰነበትክ? ሁለቱንም በፕሮፌሰር ዶር ብርሃኑ ነጋ በግልህም ለሁለትም ሆናችሁ ያደረጋችሁትን ውይይት አዳመጥኩት። ስለምን በፕሮፌሰር ብርኃኑ ነጋ ላይ ወጀብ በዛ በሚለው አመክንዮ የሰጠኽው አስተያዬት " ፕሮፌሰር ዶር ብርሃኑ ነጋ ጉራጌ ስለሆኑ ነው " ብለህ ያቀረብከው አመክንዮ በፍጹም አይመስለኝም የሚል ሃሳብ አቀርባለሁኝ። 
 
አንተም እንደምታውቀው "ከኢትዮጵያ ሱሴ ነው" ንቅናቄ በፊት በዓለም ዓቀፍ አሉ የሚባሉ አብዛኞቹ ሙሁራን፤ ውጭም አገር፤ አገር ውስጥም ያለው ኢትዮጵያዊ ተስፋውን ያሳካልኛል ብሎ የሚጠብቀው በፕሮፌሰር ዶር ብርሃኑ ነጋ ስኬት ልክ ነበር። ሚሊዮኖች ከውስጣቸው ያከብሯቸው፤ ከህሊናቸው ይፈቅዷቸው እንደ ነበረ አንተው እራስህ ያዬኽው የሃቅ እንክብል ነበር። አብሶ በአውሮፓ ህብረት የነበራቸው ዕውቅና እና ተቀባይነት ልዩ ነበር። 
 
ሙግታችን ኢትዮጵያን ለመረከብ ጎደለ የምንለውን ንቅናቄያቸው እንዲያስተካክል ነበር። እርግጥ አገር ቤት ከገቡ በኋላ ብዙ ደጋፊያቸውን ለከቅላይ ሚር አብይ አህመድ እንዳስረከቡ ይረዳኛል። የሳቸው ማህበራዊ መሠረት ምንጩ ዜግነት ነበር። አብዛኛው ተስፋ የጣለባቸውም አማራ ነበር። 
 
ደጋፊያቸው፤ አክባሪያቸው አማራ ነበር። ነገር ግን ከአማራ #መደራጀት ጋር በሚነሱ ሃሳቦች ዙሪያ ተስፋ እና ተስፈኛው እንደተፋጠጡ አስተውያለሁኝ። አማራው የራሱን ድርጅት ሲፈጥር በእሳቸው ድርጅት፤ የሳቸው ራዕይ ችግር እንደሚገጥመው ያውቁ ስለነበር በአማራ ህዝብ መደራጀት ላይ ደስተኛ አልነበሩም። 
 
ስደት ላይ ያቋቋሙት ግንቦታቸው መጠነ ሰፊ ደጋፊ በመላ ዓለም ነበረው። ሚዲያቸው ኢሰትም ተወዳጅ፤ ተደማጭ ነበር። ያን ጊዜ እኔ በግሌ እሞግት የነበረው የበታች አካሎቻቸው በግል ህይወት ሳይቀር ገብተው ሰላማችን ይነሱ ስለነበር፤ ይህ እንዲስተካከል በአጽህኖት እኔ በግሌ እጠይቅ ነበር። የሚገርመው ግንቦት ፯ ፈርሶ እንኳን ሊተውን አልቻሉም። ይህንን አሁንም ለወዳጆቻቸው ቢነግሩልኝ እፈልጋለሁኝ።
የሆነ ሆኖ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜግ የግድ የአንድ ንቅናቄ ይሁን ህብረት ይሁን የፖለቲካ ድርጅት አባልም ሆነ ደጋፊም የመሆን ግዴታ የለበትም። አባልነት በፈቃደኝነት ነው። የንቅናቄው ግዴታ የሚኖርበት አምኖ ፈቅዶ ንቅናቄውን #የተጠለለው ብቻ ነው።
 
 ገና ለሥልጣን ባልበቃ ንቅናቄ የማይደግፍም ቢሆን በኢትዮጵያ ዜግነቱ ሊከበር፤ ሊታቀፍ ይገባል እንጂ ሊሳደድ፤ ሊገለል፤ ሊታደምበት አይገባም። አንድ እጩ የአገሪ መሪ ሁሉንም ዜጋ ደጋፊውን፤ የማይደግፈውን፤ የሚቃወመውንም ሳይቀር በእኩል ዓይን የማዬት፤ የማቅረብ ተፈጥሯዊ ግዴታም አለበት። ለዴሞክራሲ ለሚተጋ መንፈስ ይህ ቀላሉ መስመር ይመስለኛል። ብዙ ተሰቃይቻለሁኝ በንቅናቄው ወኪሎቻቸው። የድርጅትን ጽንሰ ሃሳብ፤ የአደረጃጀት መርሁንም ስለማያውቁ ይመስለኛል። 
 
ከዚህ አንፃር የሚነሱ ሙግቶች ካልሆኑ በስተቀር በአመዛኙ ለውጥ ፈላጊ ማህበረሰብ ክብር በገፍ የሚለገሳቸው ነበሩ ፕሮፌሰር ዶር ብርሃኑ ነጋ። በቅንጅት ጊዜም ልዩ የሆነ የህዝብ ፍቅር እንደነበራቸው ይታወቃል። አንድ የታሪክ አጋጣሚ ላይ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ንግግር ሲያደርጉ አንድ ጨዋ፤ የተማረ እሳቸው ተናግረው እስኪያጠናቅቁድረስ ቁሞ ሲያዳምጣቸው በአይኔ አይቻለሁኝ። ያ ልዑቅ ወጣት የቅኔው ጎጃም ልጅ ነው። ፕሮፌሰሩ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ታሥረው በነበረበት ጊዜም ከሊቅ እስከ ደቂቅ በአህቲ ድምጽ ታግሎላቸዋል። በፍጹም በፌጹም የመጡበት ማህበረሰብ ትዝ ብሎን አያውቅም።
 
ተመን አልወጣለትም እንጂ ለእሳቸው የተሰጠው ፍቅር በዲያስፖራ ታሪክ #የክስተት ያህል ነበር። የአብዛኛው የየአገሩ የንቅናቄው ትጉኽ አስኳል አማራወች ነበሩ። እኔ ይህንን በአካል ከቦታው ተገኝቼ ያረጋገጥኩት ሃቅ ነበር። እሳቸው የተገኙበትን የፍራንክፈርት አማይን ስብሰባም በአካል ተገኝቼ አይቻለሁኝ። አዳራሹ መፈናፈኛ ቦታ አልነበረው። የተሳታፊው አክብሮ የማድመጥ ሥርዓትም ሙሉ ነበር።
 
ይህን የመሰለ ሙሉ አትኩሮት፤ ተፈጥሯዊ ፍቅር የሰጠ ህዝብ ከዘር ሐረጋቸው ጋር የተነካካ ምንም ጎደሎ፤ ስንኩል የሆነ ዕይታ አልነበረውም። ሊመሰገን ነው የሚገባው እንጂ በጥርጣሬ ሊታይ አይገባም። ሃሳቡ በዛ መልክ መቅረብ ነበረበት ብዬም አላምንም። ተግባራችን ሆነ የአኗኗራችን ዘይቤ በፖለቲካ አቋም ምክንያት ማዶ --- ለማዶ ተፋጦ ያለውን የፍላጎት መስክ ማቀራረቡ ነው የሚበጀው።
በፍጹም ሁኔታ በአብዛኛው ህሊና ውስጥ የሌለውን ሃሳብ ነው አቶ ኤርምያስ ለገሰ ያቀረብከው የሚል ዕምነት አለኝ። ብዙ ጊዜ እንዲህ መሰል ሃሳቦችን ታቀርባልህ። ባይሆን ነው የምመርጠው። ጥርጣሬን ይዞ ሚዲያ ላይ ማቅረብ እኛ ላለንበት ውጣ ውረዳዊ የፖለቲካ ሁነት አይጠቅመንም። 
 
በመረጃ፤ በዳታ፤ በጥናት ያልተገፋ ክብሪት እሳቢወችን ማንሳት ለቀጣይ ትውልድ አብሮነት ሳንክ ይፈጥራል። ያለው ተራርቆ ጉዞ እኮ ከበቂ በላይ ነው። ዕውነትን ለመድፈር ማጥ እና ድጥ ላይ እኮ ነን። ይህን መሰል መራራቅ የሚቀልብ አልሚ ምግብ ማደራጀት በፍጹም አያስፈልግም። ቢሆን እንኳን እንዳላየን ማለፍ የሚገባን ጉዳይ ሊኖር ይገባል። 
 
ሰፊ ተደማጭነት ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ፓርቲ ቋሚ ሠራተኝነት ዕድሉን ያገኜ መንፈስ ብርቱ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል። ጫፍ እና ጫፍ፤ አፋፍ እና አፋፍ እኮነው ያለነው። ለማድመጥ እንኳን ትዕግስቱ በግራ ቀኙ ወገን የለም። ሥልቹ አየር ውስጥ ነው እየቀዘፍን የምንገኜው። ይህም ሆኖ ቢያንስ በዚህ መሰል ጉዳይ ጠንቃቃ ልንሆን ይገባል - ሁላችንም። እኔ #ቢበቃን ባይ ነኝ። 
 
የጉራጌ ህዝም ምኑ ይጠላል? ሊቃናቱ እኮ የወጡት ከጉራጌ ህዝብ ነው። ሁሉም እናት አለው። ጉራጌ ከቀደምት ማህበረሰቦች አንዱ ነው። ኢትዮጵያን በማበጀትም ከውስጡ በመውደድም የሚታማ ህዝብ አይደለም። ትጉህ፤ ታታሪ ህዝብ ነው ጉራጌ። አምጡ ድገሙ ቢባል እንደ ጉራጌ ህዝብ ጸጥተኛ፤ የጨመተ፤ ትጉህ ህዝብ ማን አለ። ጭምት ህዝብ አለን።
 
ከሥራ ዲስፕሊን አንፃርም የጉራጌ ህዝብ ኢትዮጵያዊው #ኢኮኖሚስት ነው። በዘመነ ኢህአፓም መሪወቹ ጉራጌወች ነበሩ። አንጃ ኢህአፓ ውስጥ ሲፈጠርም ያው የጉራጌ ሊቃናት ነበር በበላይነት የያዙት። በኢህአፓ የነበረው ተጋድሎ ምን ያህል ወጣት እንደተሰለፈበት፤ እንደተሰዋበትም ይታወቃል። አብዛኛው የኢህአፓ አንጋች ደግሞ ማን እንደሆን ይታወቃል። ኢህአፓ ዱርቤቴ ሲልም አንጥፎ ጎዝጉዞ፤ ስንቅ ትጥቅ ሆኖ፤ አንጋች መሪ ሆኖ ያገለገለው የአማራ ህዝብ ነው። 
 
ቆይታው አጭር ቢሆንም በዘመነ ቀስተዳመና፤ በዘመነ ቅንጅት፤ በዘመነ ግንቦት ፯፤ የጉራጌ ሊቅ #መረኝ ብሎ የአመጸም፤ የአማረረም፤ የተከዘም የለም። ፖሊሲያቸውን የሚሞግት መፈጠሩ ደግሞ የተገባ ነው። ፕሮፌሰሩ የአገር መሪነት እርካብ ላይ ይወጡ ዘንድ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ምኞት ነበር። ያ ምኞትን በማሳካት እረገድ እግዚአብሄር የፈቀደው ተከወነ። 
 
እርግጥ ነው ፕሮፌሰር ዶር ብርኃኑ ነጋ በሚያነሷቸው ሃሳቦች፤ ባላቸው የፖለቲካ አቋም የሚከፋ ሊኖሩ ይችላሉ። #ማር አይደሉም ለሁሉም የሚጣፍጡ። በተረፈ ዛሬ የሚሞግቷቸው ባልደረቦቻቸው ፕሮፋይላቸው እኮ የፕሮፌሰሩ ምስል ነበር። እሳቸውን ሳይነካ ገና ይሆናል ተብሎ የስንት ሰው መኖር፤ አቅም አፈር ድሜ ግጧል።
 
አቶ ኤርምያስ ለገሰ እኔ የማምንበትን ልንገርህ። ስለምን በእሳቸው ላይ ወጀቡ እንደሚይል? 
 
1) ስለምን ከብልጽግና ጋር አብሮ ሠራ? ብልጽግናን ከውስጡ ስለምን ተቀበለ? በብልጽግና ላይ ስለምን ሙሉ ዕምነት ኖረው?
2) ስለምንስ ብልጽግና #እንዲደረጅ በገፍ አቅም ያዋጣል?
3) ስለምንስ ህዝብ በሚከፋባቸው ጉዳዮች ላይ #ዝምታን መረጠ?
4) ስለምንስ የትምህርት ሚኒስተርነቱን #ሹመቱን ተቀበለ? ወዘተ ……… ነው።
5) ቅናትም መጎምጀትም የሳቸውን ሰብዕና የፊት ረድፍ ተፈላጊ የማድረግ ምኞትም ያለ ይመስለኛል።
 
#አሁን ደግሞ።
 
አዲስ የተቃዋሚ ንቅናቄ በዲያስፖራው አለ ከፋኖ ንቅናቄ መጎልበት ጋር ክሱት የሆነ፤ አዲስ የአየር ላይ ስብስብ እያዬን ነው። የብልጽግናን መንግሥት #አሻም የሚል የሊቃናት ንግግር፤ ውይይትም አየር ላይ አለ። እኔ እንደማስበው ይህን መሻት #የሚመራው መንፈስ ይፈለጋል። ለዚህ ደግሞ ቢያነሱ ቢጥሉት እንደ ቀደመው ዓይነት የግንቦት ፯ ያህል ተቀባይነት ለመፍጠር የከበደ ይመስለኛል። 
 
ለዚህም ነው ስብሰባው ከአዳራሽ ይልቅ ኔት ላይ በትጋት የሚሠራው። በሌላ በኩል ለአንድ አገር መሪነት በሥርዓተ መንግሥት ውስጥ ማገልገል ወሳኝ ጉዳይ ነው። ማት እየወረደባቸው በብልህነት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ይህን ፈጽመዋል። ይህ አቅም ተፈላጊ ነው። ለሽግግር ይሁን ለድልድል።
 
በሌላ በኩል ለውጥ በሚሻው የብልጽግና ተቃዋሚ ወገን ውስጥ በግሎባሉ ዓለም ደረጃ ዕውቅና ያለው #ተቀባይ መሪ ማግኜት #ጋዳ የሆነ መሰለኝ። ፕሮፌሰር ዶር ብርኃኑ ነጋ እንደ ባንኩ ገዢ ፈቅደው ሥልጣን ቢለቁ፤ ለትግሉ አሰባሳቢ አቅም ያገኛል ብለው የሚያምኑ ይመስለኛል። በወል እኮ ከኢዜማ አመራር፤ ደጋፊነት በገፍ ስንብቱን ሳስተውል የሚጠበቅ #ቁልፍ ሰውን የማሰብ መንፈስ ይፈጥራል። ያ እስከ አሁን አልተሳካም።
 
መመዘን አይቻልም፥ እንጂ ፕሮፌሰር ዶር. ብርሃኑ ነጋ ወደ ለውጥ ፈላጊው ማለት ወደ የብልጽግና ተቃዋሚ ቲም ቢቀላቀሉ ሁሉም ሊቀበላቸው ይቻል አይቻል ሌላው ፈታኝ ጉዳይ ነው። መገመት - አይቻልም። ምንአልባትም ከአሁኑ የበለጠ ወጀብ ሊፈጠር ይችላል። ምርጫው የእሳቸው ቢሆንም። ፕሮፌሰሩ #ጫናውን ለምደውታል። #ወጀቡም የኖሩበት ነው።
 
 ለእሳቸው አዲስ ነገር የለም። ጫካውን በተደጋጋሚ አይተውታል፤ እስሩንም እንዲሁ፤ ስደቱንም የኖሩበት ነው። አሁን የብልጽግና ተቃዋሚወች የሚያነሷቸው አመክንዮች የሚታወቁ ብቻ ሳይሆን የተኖረባቸውም ናቸው። ለፕሮፌሰር ዶር ብርሃኑ ነጋ ቀርቶ ለእኛ ለባተሌወቹ ለምናውቀው አቅም፤ ለምናውቀው የሙገት ዘይቤ አቅማችን ቆጥበን ነው እያስተዳደርን እምንገኜው። ጊዜ አላባክንም እኔ እራሴ። 
 
በሌላ በኩል በተሟላ የፖለቲካ ፓርቲ መርህ እና አሰራር ነው #ኢዜማ የተደራጀው። በሚገባ ተከታትየዋለሁኝ። የኢዜማ አደረጃጀት እና የብልጽግና ግጥምጥሞሽ ጥራቱም፤ ደረጃውም ፈጽሞ አይገናኝም። ሁለት ነገር አጣምሮ ነው ኢዜማ የተመሠረተው። ይህ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ አደረጃጀት አዲስ መንገድም ነበር። መንግሥት እና ፓርቲ ሆኖ ነው ኢዜማ የተደራጀው።
 
በሌላ በኩል #ፖሊሲ ቀመስ ጉዳዮችንም በበሰለ፤ በሰከነ ክህሎት የማቅረብ አቅም ኢዜማ አለው። ከዚህ መሠረታዊ ማዕከላዊ ከሆነ የተቃዋሚወች ፍላጎት አንፃር ይህን አቅም ሙሉለሙሉ ለመመገብ መስራቹን ማግኜት አንድ የድል እርካብ ነው ለብልጽግና ተቃዋሚወች። ……… ግን #ይቻላል ወይ? ...ግን #ተቻለ ወይ? ጊዜ የሚፈታው ነው።
 
በነገራችን ላይ የኢዜማ ደጋፊ #ዲያስፖራ ላይ አለን? የሆነ ሆኖ የፖለቲካ ድርጅት የሚደራጀው ለመንግሥተ ሰማያት አይደለም። ለገሃዳዊው ዓለም ለፖለቲካ ሥልጣን ነው። በምርጫ ተወዳድሮ የተሸነፈው ኢዜማ የቀረበለትን ቁልፍ ዕድል አሻም ሳይል መቀበሉ ዊዝደም ነው። ሊከበር እንጂ ሊብጠለጠል አይገባም። በተወሰነ ደረጃም የራሱን ዝንባሌ የማስፈጸም አቅም ይኖረዋል። ይህን ደግሞ ኢዜማ ያሳካ ስለመሆኑ የቀደሙ ራዕዮችን ከልብ ለተከታተልን ሰወች ቃናውን አያለሁኝ። 
 
ሌላው ኢዜማ ተፈላጊ የሚያደርገው ጉዳይ ኢዜማ #አገር #ውስጥ ያለ የፖለቲካ ድርጅት ነው። የዲያስፖራው ተቃዋሚ ኢዜማ የአንድነት የፖለቲካ ፓርቲን ግዴታ የሚመስል ተልዕኮ እንዲኖረው ይፈልጋል። ሁለት ነፍስ ያላቸው የተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው አገር ውስጥ ያሉት። ኢህአፓ እና እናት። በብልጽግና ጉዞ የተመሰጡት ደግሞ አብን እና ኢዜማ ናቸው። ግን አብን አለን???
 
 ከሁሉም በጣም ተፈላጊው ግን ኢዜማ ነው። ኢዜማ ሁሉም አለው። በአንድ የፖለቲካ ድርጅት የሚፈለግ የአቅም፤ የክህሎት፤ የተመክሮ ደሃ አይደለም ኢዜማ። በሌላ በኩል ለዴሞክራሲ ለሚታገል አንድ ሰብዕና ወይንም ተቋም የድጋፍ አቋም ለገዢው የመስጠት ወይንም የመንሳት ሙሉ ያልተሸራረፈ መብት ነው። የትኛውም አካል ቆርሶ፤ ቆርጦ የሚያስተዳድረው ከሆነ ብቻ መብት ጥገኛ ይሆናል። 
 
ሌላው ባለፈው ጊዜ ፕሮፌሰር ዶር. ብርሃኑ ነጋ ኢዜማንም እንደሚለቁ #ወስነዋል። ይህን ስሰማ እኔ ኢዜማ የትውልድ የመሆን አቅሙ #መራራ ስንብት እንደሚያደርግ ነው ያሰብኩት። ከፕሮፌሰሩ ጋር ያለው የአቅም፤ የቅብዕ መንፈስ ረቂቅ ነው። ይህን ሲያጣ ኢዜማ ቀጣይ ተስፋው ጥንዙል ሊሆን ይችላል። ይህ የእኔ ዕምነት ነው። አንዳንድ ጊዜ እያለ የማታውቁት፤ እያለ የማትገምቱት አካል፤ ግለሰብም ሊሆን ይችላል ስታጡት ግን ብዙ በጣም በብዙ ያጎላል። ይህን እናታቸውን ያጡ ልጆች ያውቁታል። 
 
እንደ ፕሮፌሰር ዶር ብርኃኑ ነጋ በብልጽግና መንግሥት ሹመት የተሰጣቸው የፖለቲካ ድርጅት መሪወች አሉ። ነበሩም። ግን ምንም ዓይነት ወጨፎ ገጥሟቸው አያውቅም። ሰሞኑን የህዳሴ ግድቡ በኽረ አጀንዳ ነበር። ዶር አረጋዊ በርሄን ያነሳ፤ ፎቷቸውን የለጠፈ፤ ተስትፏቸውን ያደነቀ ወይንም የሞገተ አላየሁም። 
 
ፕሮፌሰር ዶር ብርሃኑ ነጋ በፓርላማም፤ በብልጽግና የትምህርት ፖሊሲ አፈፃጸም፤ ስለ ትምህርት ጥራት እና ተስፋው በመጠነ ሰፊ ይሞገታሉ። ይልቀቁ የሚሉ ሃሳብ ሁሉ ተነስቷል። በነገራችን ላይ ይህን የትምህርት ሚኒስተር ቦታ አቶ በቀለ ገርባ ይመኙት ነበር።
ነገር ግን ብልጽግና ለኢዜማ ሰጠው። 
 
የሆነ ሆኖ ፕሮፌሰር ዶር ብርሃኑ ነጋ ጉራጌ ስለሆኑ አይደለም የሚሞገቱት። ከብልጽግና የተሻለ፤ በአደረጃጀትም መርህን የተከተለ፤ በማኒፌስቶም ደረጃውን የጠበቀ ዓላማ እና ግብ ያለውን የፖለቲካ ድርጅት መሥርተው እየመሩ ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ይወቀሳሉ፤ ይሞገታሉ፤ እላፊም የሄደ ቀደም ባለው ጊዜ በአድናቂያቸው የተፃፈ መጣጥፍ በንባብ አዳምጫለሁኝ። እላፊ የሄደ ንግግርም እንዲሁ አዳምጫለሁኝ። ቻይ ናቸው። #ሰፊም
 
ፕሮፌሰር ዶር ብርሃኑ ነጋ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሉም። ይህ ደግሞ በእጅጉ የምደነቅበት አመክንዮ ነው። ውዳሴም፤ ተከታይም የሚሹ አይመስሉም። የሰከነ ጉዞ ላይ እንደ አሉ ይሰማኛል። በተለይ ዕድላቸውን ሳያፈሱ፤ ተጨማሪ ጊዜም ሳያባክኑ የተሰጣቸውን የኃላፊነት ቦታ በብልህነት ተቀብለው የህዝብ አገልጋይነትን ማጣጣማቸው እራሱ አዲስ ክስተት ነው።
 
ከህዝብ ጋር መሥራት፤ በመንግሥት የአሰራር እና አስተዳደር፤ በመዋቅር የአደረጃጀት ዲስፕሊን ውስጥ ማለፍ የማይገዛ፤ ዩንቨርስቲ ውስጥ የማይገኝ ልዩ ዕድል ነው። ይህን ዕድል ፕሮፌሰሩ ተጠቅመውበታል። በህይወት ዘመናቸው ካገኙት ተመክሮ በላይ ጠቃሚ ልምድ እና ተመክሮ እንዳአገኙበትም ምንም ጥርጥር የለኝም። ነገ የሚወስኑትን ባላውቅም እስከዛሬ በአስተዋልኩት ግን ዕድሉን መጠቀማቸው የክህሎት ብክነትን አስቁመውታል ብየ አስባለሁኝ።
 
እራሱ የሥራ ሰዓት መግብያ እና መውጫው፤ የሠራተኛ ቅጥር እና ቁጥጥሩ፤ የፋይናስ ፍሰቱ እና ስኬቱ፤ ከላይ አለቃ ኑሮ በሥሩ ለመተዳደር መፍቀዱ፤ ከሥርም እሳቸው ከላይ ሆነው የሚመሩት ሠራተኛ መኖር ስሜቱ፤ ጣዕሙ፤ ማዕዛው፤ ጠረኑ ዓውዱ እንደ ጀምላ እና ችርቻሮ ቦንዳ ገብያ ላይ የሚገኝ አይደለም። ረቂቅ ነው። ይህን አሳክተዋል ፕሮፌሰር ዶር ብርኃኑ ነጋ። ታዛዥነት እና አዛዥነትን ማዕከሉ እሳቸው ሆነው ህይወቱን ኖረውበታል። በመጠነ ሰፊ ትዕግሥት እና የመቻል አቅም ውሳኔያቸውን አክብረው እዬኖሩበት ነው።
 
በአንድ አጋጣሚ ሲገልጹ የሰማኋቸው ከብልጽግና ምንም ጫና እንደሌለባቸው ነው። ስለሆነም በሚያምኑበት የህይወት መሥመር እየኖሩበት እንዳሉ ይሰማኛል። ይህ ሙሉ መብታቸው ነው። የማንንም ይለፍፈቃድ አያስፈልጋቸውም። በንግግራቸው እንደ ታዘብኩት ውስጣቸውን ያገኙ ይመስለኛል። ይህን ዕድል ባይቀበሉ ኖሮ ምን ይጠብቃቸው ነበር ስንል፤ የኖሩበት ስደተኝነት እና መምህርነት ብቻ ይሆናል። ሞናትነስ የሆነ ገጠመኝ። አገር ውስጥ መኖር ፈልገዋል። 
 
ሲኖሩም በፈቀዱት ቦታ እና ኃላፊነት መሆኑ ተመችቷቸዋል። በፕሮፌሰር ዶር ብርሃኑ ዘመን ትምህርት ሚኒስተር እንዲህ እና እንዲያ ነበር የሚያስብል አሻራ ተክለዋል። በራሳቸው ምርጫ ውስጥ መሆናቸውን ደጋግመው ሲገልጹ ሰምቻለሁኝ። ጫና እንደሌለባቸው። 
 
በጣም የገረመኝ ግንቦት ፯ ወደፊት ሊገጥም ይችላል ብሎ ያሰላቸው ሃሳቦች እና ዕውነታው ነው። የፕሮፌሰር ዶር ብርሃኑ ነጋ ብልጽግናን አምነው አብረው እየሰሩ መኖር የፈቃድ ምንጩም በትንቢታቸው ውስጥ እራሳቸውን ማግኜታቸው ይመስለኛል። የሚያስፈጽሙት የብልጽግናን የትምህርት ፖሊሲ ነው። በከፋውም በፈካው ሁነት ኃላፊነት እና ተጠያቂነቱን ወደውት ቀጥለውበታል። መብታቸው ነው።
ትምህርት እና የትውልድ ተስፋን በሚመለከት ለባለሙያወች መተው ምርጫየ ነው። ነገረ የገበሬው ልጅ ጉዳይ የተገባ አትኩሮት ይሰጠው ዘንድ በትህትና አሳስባለሁኝ።
 
የአቶ ኤርምያስ ተከታታይ ዝግጅት ፕሮፌሰር ዶር ብርሃኑ ነጋን በመደገፍ፤ ለውሳኔያቸው ክብር በመስጠት ነው ዝግጅቱ። የእኔ ሙግት ወጀቡ የበዛው ጉራጌ ስለሆነ አይደለም። ለሚመኟቸው ዕድሉን ስለነፈጉ ነው የእኔ ሃሳብ። ስለምከታተላቸው፤ ስለማደምጣቸውም።
የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች ደህና አምሹልኝ። ደህና እደሩልኝ።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
19/09/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።