መመረቅ የሚታፈሰው #ለሰላም በሚሰጠው ክብር እና #ልዕልና ልክ ነው። #ሰላም ያስከብራል።
ኤርትራን እና ኢትዮጵያ ሁለት ሊለያዩ የማይገባቸው ግን ተለያይተው ያሉ ሁለት ሉዓላዊ አገራት ናቸው። የኢትዮጵያ ህዝብ እና የኤርትራ ህዝብ የደም ዝርያቸው ቢመረመር #ወጥ የሚሆን ይመስለኛል። ባህል፤ ወግ እና ልማድ ባለፈም ሃይማኖትን በሚመለከት ተመሳሳዮች ናቸው። ይህ ዕድል የማይገኝ ነው።
አንድ ተብዕት እናቱን ወይንም እህቱን የምትመስል:ከገጠመው የቅድሚያ ምርጫው ልትሆን ትችላለች። አንዲት ሴትም አባቷን ወይንም ወንድሟን የሚመስል ከገጣማት ፈቃዷን ለመስጠት #አታቅማም። ውስጥ ሲገኝ ውስጥን መፍቀድ አይከብድምና።
ሌላው ሁሉም ሰው ከምል አብዛኛው የሰው ልጅ የራሱን ገጽ ወይንም ምስል ይወዳል። እኔ ወጣት እያለሁ መስታውት እወድ ነበር። ምክንያቴን አሁን ሙሉ ዕድሜ ላይ ሆኜ ስገመግም ለካንስ የመልኬን ነገር ስለምወደው ኑሯል። የትኛውንም ፎቶግራፍ በጣም እወዳለሁ።
የማየውም ከውስጤ ነው። የፎቶግራፍ ፍቅሬም ምንጩ የራሴ ምስልን መውደድ ይመስለኛል። የኤርትራ ህዝብ እና የኢትዮጵያ ህዝብም አምሳዮች ነን። ሁልጊዜ የሁለቱን አገር ህዝቦች አቅርቤ እያዬሁ አሁን ምኑ ይሆን፤ አንዳችን ከአንዳችን የሚለየን እላለሁኝ። ሌላው ቀርቶ በሌሎች አፍሪካ፤ ወይንም እስያ አገሮች ያሉትን የእኛን መሰል ገጽ ያላቸውን ከውስጣችን እናቀርባቸዋለን። ምክንያቱም እራሳችን #በውስጡ ስለምናገኝ ነው።
እና ውስጣችን ለውስጣችን፤ ለውስጣችን ውስጣችን ሰላምን ለመፍቀድ እንደምን ተሳነው? ከራስ ጋር መጣላት፤ ከራስ ጋር ጦርነት መግጠም በተፈጥሮ ላይ #ማመጽ ይመስለኛል። የበረንቱ፤ የባድመ ጦርነት ሊያስተምረን ሲገባ፦ አሁንም የጦርነት አየር አገር ምድሩን ሲያካልለው ይገርመኛል። ግን ለምን በኃይል፤ በስቃይ፤ በውድመት ምኞትን ለማሳካት መመኜት ተፈቀደለት???
1) ኢትዮጵያ የባህር በር ያስፈልጋታልን? በርግጥም ያስፈልጋታል።
2) ኢትዮጵያ ቤተ - ቀይ ባህርነቷን ለመመለስ መናፈቋ ተገቢ ነውን? አወን ተገቢ ነው።
3) ኢትዮጵያ ወደብ ያስፈልጋታልን? አወን ያስፈልጋታል።
ይህን ሦስት ጥያቄ ስመልሰው ጥያቄው ትክክል እንደ ሆን አምኜበት ነው። በሻብያ፤ በህወሃት በደርግ መሃል የነበረው ጦርነትም በእኔ ዘመን የነበረ ነው። ኤርትራ ስትገነጠል፤ ህወሃት ፬ኪሎን ሲታደል አይቻለሁኝ። አጀንዳውን፤ ሂደቱን፤ ፍልሚያውን፤ የዘመኑን የፖለቲካ ባህሬም አሳምሬ አውቀዋለሁኝ።
#የባህር በር የወደብ ጉዳይ ባለፈም የራስን ጠረን አሰብን የማስመለስ ምኞት።
ግን እንዴት? በጦርነት? ሊሆን አይገባም። በተከታታይ በሚሠራ ዲፕሎማሲ።
*****
አሰብ በወሎ ሥር ነበር። እራስ ገዝነትም አሰብ፤ ኤርትራ ትግራይ ወዘተ ሲሰጥም ነበርኩኝ። እንደማስበው አሁን ላይ ያን ጊዜ ፕሮ - ህወሃት እና ፕሮ - ሻብያ የነበሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በደርግ መንግሥት ውስጥ ሆነው የሠሩት #ድልዳል ይመስለኛል። ክፍላተ አገራትም የተሸነሸኑት ከዚህ አንፃር ይመስለኛል። የሆነ ሆኖ አሁን ምን ላይ ነን? የትስ ላይ ነን ነው ጉዳዬ። #ፍጥጫ ለይ።
ፍጥጫው መፈጥፈጥም ሊያመጣም ይችላል። የትኛውንም ክስተት አግንኖም፤ አንኳሶም ማየት አይገባም። ጊዜ፤ ቀን ሰዓት የሚሰጥም፤ የሚነሳም ገጠመኝ ሊኖር ይችላል። ተግ ብሎ ማድመጥ ይገባል። ኢትዮጵያም ትሁን ኤርትራ በውስጥ ፖለቲካቸው ውስብስብ ችግሮች አለባቸው። ግራቀኙም በዲፕሎማሲዊ ዘርፍ ይሁን ከጎረቤት አገራት ጋርም ጤናማ የሆኑ፤ ጤናማ ያልሆኑ ችግሮች አሉባቸው። ይህ ሁነት እያለ ሌላ ወላፈን መሻት የተገባ አይመስለኝም።
ለተመድ አቤቱታው ግራ ቀኙ እያቀረቡ ነው። ከተመድ ይልቅ ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ይቀራረባሉ። ሌላ ሳይሰማ መፈታት የሚችል ችግር ነው እየጋመ ያለ። አቤት አንዳንድ ሚዲያወችማ በቅጽበት ጦርነቱ ቢጀመር የሚሹ ናቸው። እግዚኦ ነው። በዚህን ያህል ርቀት ሰባዕዊነት ሲሰላ።
ኢትዮጵያ በትጋት የባህር በር ጥያቄን፤ የወደብ ጥያቄን፤ የቤተ - አፍሪካ ቀንድ ባለድርሻነት ጥያቄ፤ የቤተ - ቀይ ባህር ቤተኝነት ጥያቄ ፊት ለፊት አምጥታለች። ሙከራወችንም በሱማሌላንድ አድርጋው ነበር። አሁን ፈጦ ጥያቄው በተመደ ስብሰባ ላይም ቀርቧል። ግራ ቀኙም አቤቱታቸውን እያሰሙ ነው።
ቅንነት ቢኖር ኖሮ በቀላል ሁኔታ መፍትሄ ማግኜት ይቻል ነበር። አሁንም ቢሆን አንዷ #ጥይት ሳትተኮስ ለእልባቱ የኤርትራ የፖለቲካ ሊቃናት፤ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊቃናት፤ የኤርትራ የተፈጥሮ ሊሂቃን፤ የኤርትራ የተፈጥሮ ሊሂቃን፤ በሁለቱ አገሮች የሚገኙ የሃይማኖት መሪወች፤ ተጽዕኖ ፈጣሪወች፤ የጥበብ ቤተኞች፤ ጋዜጠኞች፤ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በፍጥነት እና በትጋት ሁለቱ አገሮች ችግሮቻቸውን #በሰላም ለመፍታት እንዲችሉ ጫና ሊፈጥሩባቸው ይገባል ባይ ነኝ።
ጦርነቱ የሚካሄደው ኢትዮጵያ መሬት ነው። ኢትዮጵያ #ደክሟታል። የኢትዮጵያም የኤርትራም እናቶች የልጅ ሰርክ #መርዶ ይበቃቸዋል። ኢኮኖሚውም ዝሏል። ሥልጣኔውም #ፈዟል። ይህ ሊናፍቅ አይገባም።
ጦርነት በቃን! የወል ቋንቋችን ሊሆን ይገባል ባይ ነኝ። ማን ያሸንፋል? የማን ደም ፈሰሰ የሚያባብሉ ሰብዕናወች ተፈጥሯዊነት የከሰለባቸው ናቸው። ውድመት፤ ቃጠሎ፤ ኪሳራ መናፈቅ ጤነኝነት አይደለም።
ኢትዮጵያ ሆነች ኤርትራ ከፕሬዚዳንት ዘለንስኪ መማር ይገባቸዋል ባይ ነኝ። ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በፖለቲካ የገጠማቸው ውስብስብ ሁነት በርጋታ አስበውበት ቢሆን ኖሮ ይህ ሁሉ አሰቃቂ ትራጄዲ ዩክሬን ላይ ባልመጣ ነበር። እጅግ ከሚከብደው ጉዳይ፤ ቀለል ያለውን ክብደት መምረጥ የማስተዋል ጸጋ ይመስለኛል። ጦርነት የሠርግ ግጥግጥ፤ የጫጉላ ሽርሽር አይደለም። የጦርነት #ማገዶው፤ #ጥሬ #ዕቃው የሰው ልጅ #አካልና መኖር ነው። ትርፋ በቀል እና አመድ። ጥላቻ እና ቂም ብቻ እና ብቻ።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
08/10/2025
በቃ ጦርነት!
ጦርነት በቃ!
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ