"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን። "#ግጭት" ወይንስ "#ጦርነት"
ኢትዮጵያ ከዝምተኛው ማህበረሰብ #የህግ ባለሙያወችን፤ የሰብዓዊ መብት ዕውነተኛ #ቅን ሞጋቾችን፤ #በፖለቲካ ሳይንስ የተማሩ የተመራመሩትን ሊቃናትን አክላ፤ ተገለው ያሉትን #ሊሂቃንንም ጨምራ፤ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ከብልጽግና አገዛዝ አሻፈረኝ ካሉት ከኦላም ጋር ይሁን ከፋኖ ጋር፤ በቤንሻንጉል ጉምዝ፤ በጋንቤላም ካሉ ትናንሽ ቲሞችም ጋር ቢሆን የሚደረገውን የአፈሙዝ ግጥሚያ ይህን በኽረ ጉዳይ አጥንተው በአጭር ጊዜ #ሊዳኙት የሚገባ ይመስለኛል። ጦርነት ነው ወይንስ ግጭት? መፍትሄው በልኩ ሊታሰብለት ሲገባ። እራሴን ከበረደኝ ኮፍያ ብቻ አደርጋለሁኝ። ሙሉ ሰውነቴን ከበረደኝ ግን ጃኬቱ፤ ጓንቱ፤ ድርብ ካሊሲው፤ ሻሉ፤ ካፖርቱ፤ ሱሪ እና ሹራቡ ሁሉም ይጠራሉ። ችግርን በልኩ ማድመጥ ይገባል። መፍትሄውን በልኩ ለማደራጀት።
ከዚህ ላይ ህወሃት የቀደመው ኢትዮጵያን የመረከብ የመሻት ናፍቆት በነጩ ቤተ- መንግስት አይሆኑ ሆኋል። ለዚህ ነው በአዲስ ቅርጽ አይድኔው ህወሃት እያነኳኮረ ያለው። በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የነበረው ተቀባይነትም ሟሽሿል። በዚህ አመክንዮ ዙሪያ በህወሃት መጠለያነት ስሌት ይገኛል ተብሎ ታስቦ ከሆነ ይህ ዕይታየ መርዶ ሊሆን እንደሚችል አስባለሁኝ። በሌላ በኩል ዕውቅናን ከፍ የሚያደርገው የራስ ጉልበታም ጥረት እና ስኬት ነው። በራስ ላይ መታመን ይበልጣል እንደማለት።
የኤርትራ መንግሥትን በሚመለከት ዓለም ዓቀፋ ማህበረሰብ ያለው አቋም ይታወቃል። በራሱ ሪሶርስ የቆመ አገር ሲሆን ከዛ እርዳታ ለማግኜት ከታሰበ ብቻ የሚገኝ ይኖራል። አለቅነቱን ማስተር ማይንድነቱን መቀበል ከተፈቀደ።
#ወደ ቀደመው ………
ከሁሉም በላይ በአማራ ክልል እና በኦሮሞ ክልል እየተካሄደ ያለው ግብግብ፤ የመሳሪያ ፍትጊያ፤ የድሮን ውጊያ የጭካኔ ጦርነት ወይንስ ግጭት? ይህ በጥናት የተደገፈ ወጥ ፖለቲካዊ አቋም ይጠይቃል። ስለ አሳነሰክው ማነስን የማይቀበል አመክንዮ ይገጥማል። ስለ አከበድከውም ሊከብድ የማይችል ዕውነት ይኖራል። ለምሳሌ የአባይ ግድብ መጠናቀቅ ከግል የትዳር ጉልቻ መሳካት እና አለመሳካት ጋር አድርገው የሚያባጭሉ ድምጾች አሉ።
ትዳርን መምራት ያቃተው፤ ወይንም በየዘመኑ የፖለቲካ ድርጅት መስርቶም፤ በተመሠረተው ውስጥ ዘው ብሎ ገብቶም ያልቀጠለ፤ ወይንም አንጃም ፈጥሮ ያልተሳካለት ነፍስ ያን የመሰለ የትጋት ስኬት፤ ነገ ሌላ ቻሌንጅ አጤ የአባይ ግድብ ቢኖርበትም፤ የመጀመሪያ የምስራች ምዕራፍን ሲያናንቅ፤ ሲያንኳስስ እራሱን ያስገምታል እንጂ ማን ይውጥለታል?
ምክንያቱም ሃቅ እና ዕውነት እራሳቸውን ገልጸው በህሊና አደባባይ ስለሚሞግቱ። ዕውነት ይደፈር፤ ለዕውነት መሽኮርመም አያስፈልግም ብየ የፃፍኩት እኔም ለዚህ ነበር። ልክ እንደዚህ ሁሉ ፊት ለፊትም፤ በሽምቅም፤ በሰማይም በምድርም ተከታታይ ፍልሚያ እየተደረገ በገፍ ሰላማዊ ነዋሪ መኖሩ ተናግቶ፤ ተፈናቅሎ፤ ሚሊዮኖች ከትምህርት ተስተጓጉለው፤ የታጠቀውም በምርኮ እና በዕቀባ፤ በእገታ እና በመቁሰል ትራጄዲ እየዋኜ #ዕውነትን መግፋት ለመፍትሄ መዳረሻ ሊሆን ፈጽሞ አይችልም።
የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ቀን ሁላችሁንም በቃኝ ልቀቁኝ፦ ሌላ ተመድ የሚመድበው ቡድን ይምራኝ፤ ለደህንነቴ ዋስትናም የተመድ ሰላም አስከባሪ ይረከበኝ ሊል ይችላል። እስከ መጨረሻው ማሰብ አርቆ ማየት ያስፈልጋል። ጨዋው ጭምቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ግራ ቀኛችሁን ስንቅም ትጥቅም ታክሲም ሆኖ ችሏችኋል። ለግራ ቀኛችሁ የመከበር ዕድልም ሰጥቷችኋል። ግን አቅም አጣችሁ የማድመጥ። የኢትዮጵያ ህዝብ ዝምታ አስፈሪ ነው። እኔ ከአየር ኃይል፤ ከሮኬት ይልቅ የህዝብ #ዝምታ በእጅጉ ያስፈራኛል።
አሁን እኔ ለግል ለመኖሬ፤ ለቤተሰቤ ሳይሆን ለማያዳምጠው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ስደክም ኖሬያለሁኝ። አሁን ጭራሹን ደክሞኛል። እኔ አቶ አንድአርጋቸው ጽጌ ከእስር እንዲፈቱ በጣም ተጋሁኝ። ከተፈቱባት ዕለት ጀምሮ ግን አዳምጫቸው አላውቅም። ስለወደፊቱ መናገር ባልችልም።
የዛሬ 15/17/20 ዓመት የነበረው ሁነት ተመልሶ ፋይዳ ሳያመጣ ሌላ አቅም በዛው #ልሳን ይጠይቃል። አይደለም ሌላ አቅም ላዋጣ ለማድመጥ እራሱ አቅም የለኝም። ስልችት ብሎኛል። የተሻለ ሃሳብ፤ የተሻለ ተቋም እኮ የለም በሰላማዊው የትግል ዘርፍ። ታውቃላችሁ በ7ኛ ቀኑ በተፈጠረ ያለፈ የትጥቅ ትግል ተቋም እንደ አለ።
ዓርማውን አስቀምጨዋለሁኝ። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ አቀማመጥ ቅደም ተከተል የተዛባ ስለነበር። ምስሉን ያገኜሁት ከመረጃ ቲቢ ነበር። ያ ተቋም ለሦስት ቀን ሚዲያ ላይ ተረተረ ……… አሁን ወደ አይጥ ጉድጓዱ ገባ። ለዛውም የገናና ባለታሪክ ሥም ይዞ ከሰመ። እኔ እህታችሁን ጠይቀውኝ ነበር። እንደማይቻል ገለጽኩኝ። ወደፊትም የየትኛውም ተቋም አባልም፤ አካልም አልሆንም። ፈጽሞ። የብላቴ ሎሬት ጸጋዬ መንፈስ ተቋሜ ነው። አይደበልበትም። የሆነ ሆኖ የዛ ጤዛ የሳምንት ግርግር ሁነት በዛ ሥም ግን ስንት ወጣት ዋጋ ከፈለ???? የሚገርመኝ #ጸጸት የለም ያን ተቋም በፈጠሩት። አይደለም የሰው ልጅ የበቀለ ዕጽዋት ሲቀነጠስ ያሳዝነኛል።
#ርጋ ይባል።
የሆነ ሆኖ ግራ ቀኛችሁ #ተፈታትሻችኋል። ተፈታትናችኋል። እልሁ፥ መሽኮርመሙ ይብቃና ሰላምን ለኢትዮጵያ መመገብ አጀንዳ ይሁን። የፈለገ ሜጋ/ "ጌጋ" ፕሮጀክት ይፈጠር ሰላም ከሌለ የተመረቁትም፤ የመሠረት ድንጋይ የተጣለላቸውም ዋስትናው ዘላቂ አይሆንም። ጠባቂ አረጋጊ ዘላቂ ሰላም ብቻ ነው። ፌክኛ ያልሆነ ፈቃደኝነት ከግራቀኙ ይጠበቃል።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
08/10/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ