ሰማዕት የእኔ ሰው ገብሬ።

የመሆን የእኛ ሰው በመሆን!

ከሥርጉተ -  ሥላሴ 12.04.2018 (ከጭምቷ - ሲዊዘርላንድ - ዙሪክ።)

     
 
                           „ነፍሴ በኋዋላህ ተከታተለች፤ እኔንም ቀኝህ ተቀበለችኝ።" 
                                      (መዝሙር ፷፪ ቁጥር ፰)

  • እንደ መቅድም።

ይሄ ጹሑፍ እንደምታዩት በ12.04.2108 የተፃፈ ነው። ይህ ሰማዕት በውስጤ ያለ ነው። ስለ ጀግናው ረ/ አውሮፕላን አብራሪ በጻፍኩበት ወቅት አብሬ የኔ ሰው ግብሬ እና የሰማዕት የሽብሬን ደስአለኝን ሠራሁት። በዛን ሳምንት ደግሞ ቅኑ ሳተናው ድህረ ገጽ አብዝቼበት ነበር። ከ እኔ ጋር መሥራት ከባዱ ነገር እኔም አይደክመኝ ሰውንም ይደክመዋል ብዬ አላስብም። ስለሆነም በተከታታይ ቀናት ላይ የእኔ ከ4 በላይ ጹሑፍ ብራናው ላይ ሲለጠፍ ለህሊና ዳኝነትም ከባድ ነው። ይገባልም። ተግ በይ በማለት ልጓም ማበጀት። ለእኔም ለጤናዬ የተገባ ነው። ተቆጣጣሪ ከሌለኝ በጣም ነው ሥራ እማበዛው።   

በዛ ላይ የእኔን ጹሑፍ ማተምም በፈተና ውስጥ ያለ ቀራኖዮ ነው። ጽናቱ እራሱ ይገርመኛል የሳተናው። የሆነ ሆኖ ጹሁፍ አብዝቼ በላኩበት ወቅት ተልኮ ዕጣ ያልወጣለት ስለነበር ዛሬ በእኔው ብሎግ ላይ መለጠፍ አሰብኩኝ። የሰማዕቷ ሺ ብሬም ይቀጥላል። ቢያንስ ለዛሬ ቀን ያደረሱ የትናንት ጀግኖችን፤ ሰማዕታት፤ ቅዱሳንን ማሰብ የተገባ ስለሆነ። 

መንፈሳቸው ይወቅሰናል። ውስጣችነንም በእሳት ነበልባልም ይገርፈዋል። ይቀጣዋል። ቀን እዬወጣ ስለሆነ በዚህ ቀን መውጫ ላይ ሰማዕታቱን ማሰብ የህሊና ጉዳይ ነው። ያን ጊዜ እንደ ዛሬው ሃላፊነት የሚሰማው መንግሥት ስላልነበረን ደመ ከልብ ሆኖ የቀረ ሰማዕት ነው፤ ለዛሬ ቀን ራሱን እንዲህ በእሳት አቃጥሎ የነደደ የጀግኖች ቁንጮ ነው።

                        የመሆን የእኛ ሰው በመሆን!

ስለምን እንርሳህ ስለኛ ነደህ?
ስለምን እንዘንጋህ ስለኛ ሞትህን መርጠኽ?
ከቶም አንረሳውም የማማጥ - ህማማት፤ ግብርህን።

ስለምን እንተውኽ መስቀላችን ስትሆን?
አንተ የንብ ዓውራ የመሆን መሆን።

አንተ የእኛ ጌታ የፍቅር የኔታ፤
አንተ የእኛ ልዑል የሰማዕት ገበታ፤
አንተ የእኛ ተቋም የአብሮነት መርጌታ!

አንተ የእኛ ጸሎት የነፃነት ፍትኃት
አንተ የእኛ ቤዛ የአደራ ጉልላት!
!ስለምን እንርሳህ?! ስለምን እንተውህ?
!ስለምን እንሸሸው ቁርጡን ልቦናህን!
… የፍቅርህን ጣዝማ፤ የክህሎት ጧፍህን።

አስታውሰህ አለሁ እንባዬን ገብሬ፣
ሁሌ አሰብሃለሁ ጌጤ ብዬ ክብሬ፣
የዓድዋ፣ የማይጨው የግርማ ዝማሬ!
የመታማ ሲሳይ የጎዴ ፉካሬ፤
የባድም መቅደላ የቃል ካርታ ግብሬ፤
የአንባላጌ ወልወል የባድመ ዝካሬ።

አንተነትህን ሰጥህ፤ ሰውነት ስትሆነኝ
ራስህን አቃጠልህ አለሁሽ ስትለኝ፤
እንዴት ይረሳኛል የርቀትህ ጥሪኝ?
!እንዴትስ ይተዋል የሰማዕት ሥንኝ?!

ያን መራራ ሰዓት ቀራንዮ ሆነህ፤
ያን ጎምዛዛ ዕለት ጎለጎታ ሆነህ፤
ራስህ ሰጠኃት ላምጠች እናትህ።

ከወዴት ይገኛል እንዳንት ያለ ብዛት?
ከዬትስ ይመጣል እንዳንት ያለ ጽናት?
የውርስ ነህ - ትውፊት የዘመን ሽልማት!

ሱስም ሆልኃል ማንነት አጉልቶ፤
ኢትዮጵያም ተፈታች ካቴናዋ ወልቆ!

በአብይ ዝማሬ በቄሮ ታገድሎ፤
በአማራ አብዮት በሰንደቁ ውሎ።

ኪዳኑ ደረሰ በአማኑኤል ሰምሮ!
ገዱ ተዋዋለ ኪዳን ተምሮ፤
ዕንባችን ተግ አለ ቀኑነን መርምሮ።

ነገም ተስፋ አለ የለማ የሚሉት …
ነገም ብርሃን አለ አንባዬ የሚሉት …
ነገም ራዕይ አለ ፍቅርነህ የሚሉት …
የዘመናት ገድል የማግሥት ለት።

ለዛሬው ዛሬ ነው ለነገም እሱ አለው፤
ያለለት ይሆናል እሱባለው ጊዜው።

አልሞትክም የኔሰው የኛነት በኩራት
ዕሴቱ ምስጢራቱ የመኖር አሥራት፤
የነፃነት ቀንዲል መድህን አብነት!

  • ·      መታሰቢያነቱ --- ራሱን ሳይሳለት ለነፃነት፤ ለፍትህ፤ ከቃል እልፍ ለሚል ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ሲል በቤንዚን፤ በቁሙ ነዶ፤ ተቃጥሎ፤ ከስሎ፤ ልክ እንደ በግ ሥጋ ተጥብሶ፤ ውስጡ በባይታዋርነት ተክኖ፤ ጭሶ፤ አሮ፤ አመድ ለሆነው፤ የእናቱን ፍዳ እና መከራ ለንዑዱ ለመምህር የእኛ ሰው የመሆን መሆን ይሁንልኝ።

  • ·      ኑሮውን በይበቃኛል ሰማዕትነት ጠልፎ የጽድቅን ጉዞ ፈቅዶ ለተመኘው፤ ኤልሻዳይም ለምልክትነት ለመረጠው ለሰማዕቱ መምህር የእኔ ሰው ገብሬ ይሁንልኝ። የቻላችሁ በሥሙ ሻማ ብታበሩለት አከብራችሁዋለሁኝ - ኑሩልኝንም እሸልማች-ሁአለሁኝ። ትናንትም በዝምብሎ አልተገኘም በአባቶቻችን እና እናቶቻችን እንዲሁም በብሄራዊ ሰንደቃችን በልሙጡ በአረንጓዴ ቢጫ እና ቀይ መሪነት የተገኘ ነው፤

  • ·      አዬር ላይ ተነሳፎ የተፈጠረ፤ ሐገር፤ ህዝብ፤ ታሪክ፤ ትውፊት እና ዛሬ የለም። በንፋስ ተንሳፎ የተፈጠረ ሰው ሰራሽ ክንፍ የተገጠመለት ማንነትም መኖርም የለም።

  • ·      ያለው ኢትዮጵያዊ ማንነት መሬት የያዛ፤ በከበረ የፈጣሪ ጥበብ ተመርቆ የተሰጠ ሰማያዊ ጸጋ ነው። ኢትዮጵያም ከዓለም ደምቃ ከመፈጠሪያው ባልተለዬ ሁኔታ ተቀብታ በፈጣሪይዋ በአንደበቱ ልሳንወርቅ የሆነች፤ ህዝብ ክርስቲን/ ዓለም በሙሉ ሥሟን በቅድስና በወንጌል ቃለ ምህዳን የተቀበላት ፍጽምት የበቀለች ሐገር ናት። ወንጌልም እኮ ነው ኢትዮጵያን ያነገሳት፤ እጬጌ ያደረጋት። ኢትዮጵያ ሰው ሠራሽ የዳንቴል ሥራ አይደለችም። ቅዱሳን ነብያት ያመኗት፤ በጸሎቷ የታመነች።

         (ዕለት - 12.04.2018፤ ሰዓት 13. 32
          ሲዊዘርላንድ ቪንተርቱር ቤተ መጸሐፍት ቤት ተጣፈ።)
  • ·      መጠገኛ እንደ አጥሚት።

  • ·       ተጨማሪ መረጃ።

የታህሳስ 10 የ1948 ዓለምዓቀፍ የሰብዕው መብት ህግ በ ኢትዮጵያ በወያኔ ሃርነት ትግራይ ሥርዕዎ መንግሥት በዜሮ የተባዛ መሆኑን ቅኑ ዘሃበሻ ድህረ ገጽ በታህሳስ 10፣ 2014 ጹሑፌን ለጥፎልኝ ነበር ፎቶው የ የኔሰው ገብሬ ነበር። ለነገሩ ዛሬ ቀን እዬወጣለት ስለሆነ አከታትዬ እለጥፈዋለሁኝ ሙሉውን።  

ዜሮን በሞራ፤ በሁሉም የወደቀ ዱለኛ። (ሥርጉተ ሥላሴ)

  • ·      ክውና።

የኔዎቹ ሰሟናቱን በነፃነት አርበኞቻችን ዙሪያ ቀልባችን መሰብሰብ ይገባናል። ዛሬ ከመሬት ላይ ዱብ ያለ አይደለም። ለትናት መኖር የትናንት ተጋድሎ። ለዛሬም መኖር የትናንት የሰው ግብር ነው መስመሩ። በተረፈ ቅንነታችሁን ለሰጠችሁኝ ቸሮቼ ሙንሙን ያለ ምስጋና ከኑሩልኝ ጋራ በትሁት መንፈስ ተረከቡ።

ኢትዮጵያዊነት ዓራት ዓይናማው መንገዳችን ነው።
ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ነው።
ሰማዕትነት በዕውነትነት ብቻ የሚገኝ ሰማያዊ ረድኤት ነው!

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

መሸቢያ ጊዜ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።