አዲሱን የአማራ ፓርቲ ማን ወለደው?

አዲሱን የአማራ ፓርቲ ማን ወለደው?
    ከጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው

June 9, 2018 | Filed under: የዕለቱ ዜናዎች | Posted by: -ሐበሻ

ዛሬ ሰኔ 2/2010 ዓም በባህርዳር አዲስ የአማራ ፓርቲ ምስረታ ጉባኤ ተጀምሯል። በምስረታው ላይ ሁለት አይነትየሕዝብስሜት ይብፀባረቃል። አንደኛው ደስታ ነው። ሁለተኛው በጥቅሉ ትችት ይመስላል። በዘር ተደራጁ የሚል። ደስታው ሕዝብ ወኪል ከማጣቱ የመጣ ነው። የሕዝብን ብሶት የሚያሰማ አካል በመጥፋቱ አማራጭ ተገኘ ከሚል ነው።
የትችቱ ስሜት የሚመጣው አማራ እነ መለስ በተለሙት የዘር ቀመር መደራጀት የለበትም ከሚል የቅንነት የሚመስል ሙግት፣ የአማራው ሕዝብ በማንነቱ ከተደራጀ ቦታ አናገኝም ከሚሉ ቡድኖች ስጋት ይመስለኛል።
በዚህ ወቅት የአማራ ሕዝብ አይደራጅ ለማለት ይህን ህዝብ የሚታደግ ሌላ አማራጭ ያስፈልጋል። ሁለት አማራጮች አሉ ሊባል ይችል ይሆናል።
·         አንደኛው
የትህነግ/ህወሓት ተላላኪ ሆኖ የአማራን ሕዝብ ሲያስገዛ፣ ሲያስገድል፣ ሲያስዘርፍ የኖረው ብአዴን የሚሉት ቡድን ነው። ይህ ቡድን የትህነግ/ህወሓት ወኪል ሆኖ የአማራን ሕዝብ ላይ በደል ሲፈፅም የኖረ እንጅ ለህዝብ የሚሰራ አይደለም።
·         ሁለተኛው
አማራጭ አንድነት ሀይሉ ነው። ብአዴን የአማራውን ስም እየጠራ አማራን ሲበደል ኖሯል። የአንድነት ሀይሉ በበኩሉ አማራ አይደራጅ ከማለት አልፎ ስለ አማራ መናገርን ነውር አድርጎታል። ገዥዎቹ ከመነሻቸው ስለ አማራን በጠላትነት ፈርጀው፣ በዚህ ወቅት አማራውን በስም እየጠሩ በቀየው ሲያፈናቅሉ፣ ሲያኮላሹ በበደሉ መጠን የሚናገር የአንድነት ሀይል ጠፍቷል። ወልቃይትና አርማጭሆ፣ ወልደያና ቆቦ፣ ቤንሻንጉልና ኢሉአባቦራ የሚፈፀመውን ጭካኔ ለማውገዝ ድፍረት ያጣ የአንድነት ሀይል ነው ያለው። ይህ ሀይል አማራ አይደራጅ ለማለት መጀመርያ እሱ ስለ አማራ በደል መጮህ ይገባው ነበር። ለአማራው መድረስ ይገባ ነበር። የአማራውም ትልቅ ቁስል አድበስብሶ ሌላ መለስተኛ በደል ፈልጎ ለመጮህ የሚጥር አካል ስለ አማራ መደራጀት የመናገር ሞራል ሊኖረው አይችልም።
በአማራው ላይ ባሰ እንጅ የአንድነት ሀይሉ ከስም ያለፈ የሚገባውን እየሰራ አይደለም። የገዥዎቹን አጀንዳ ተከትሎ ከሚያደርገው መፈራገጥ ያለፈ በዚህ ጠባብ ምህዳርም ቢሆን ሊያበረክተው የሚችለውን አድተዋፅኦ ዘንግቷል። በዚህም ምክንያት እምነት ታጥቶበታል። አዲሱ የአማራ ፓርቲም የተወለደው በእነዚህ ምክንያቶች ነው። አብዛኛዎቹ መስራቾች ስለ አማራነት ማውራት ነውር ይመስላቸው የነበሩ ናቸው፣ አብዛኛዎቹ በአንድነት ሀይሉ ውስጥ ያለፉ ናቸው፣ ምን አልባትም ሁሉም ስለ ኢትዮጵያዊነት መልካም አመለካከት ያላቸው ናቸው። የህዝብ በደል ሲበዛ፣ ለዚህ በደል መጮህ የነበረበት ድምፁን ሲያጠፋ፣ የአንድነት ሀይሉ ሲፈዝ ከመበደል፣ ከመዘንጋት በብሶት የተወለደ እንጅ ከምንም የመጣ አይደለም።



ይህ ፓርቲ ለአማራ ሕዝብ ጉልህ ሚና ተጫወተም አልተጫወተም በአንድነት ሀይሉ ድካም፣ ደንታ ቢስነትና ግብዝነት የመጣ እንጅ ከምንም የተወለደ አይደለም። ብአዴን የገዥዎች ወኪል ነውና እሱን ተጠያቂ ማድረግ የዋህነት ይመስላል። ተቃዋሚ ነኝ የሚለው አካል ግን አማራ ተደራጀ ብሎ ትችት ከማቅረቡ በፊት ለአማራ ሕዝብ የሰራውን ተመልሶ መገምገም ይገባዋል። የአማራው መደራጀት ስህተት ነው ከተባለም ከራሱ ከአንድነት ሀይሉ ውድቀት የመጣ አድርጎ ሊወስድ ይገባል።
·         የተቃዋሚ ወገን ትችት።
ከተቃዋሚው ወገን የሚቀርበው ሌላኛው ትችትእንዴት አማራው በእነ መለስ የማንነት ቀመር ውስጥ ይጠለፋል?” የሚል ነው። ይህን ትችት ለማቅረብም ሌላ የሞራል ተጠተቅ ይከተላል። የአንድነት ሀይሉ የአማራውለኢትዮጵያ ቀጣይ ዕጣበሚል ሰበብ ወይንም ቀናነትየአማራውን በደል ሲያድበስስ በሌላ ሕዝብ ስም የተደራጁ የብሔር ድርጅቶችን ሲያባብል ኖሯል። እንዲያውም እነዚህን አካላት ለማስደሰት ሲባል አማራውን ቀጠናዬ ነው የሚለው የአንድነት ሀይል አማራውን የረገመበት ጊዜ ብዙ ነው። በእነ መለስ ቀመር የተደራጁ ሌሎች ሀይሎች ጋርእፍ ክንፍሲል የኖረ አካል፣ አሁን አማራው በራሱ በአንድነት ሀይሉ ተስፋ ሲቆርጥወደ ጎጥ ወረደ፣ ጠበበ… ” ለማለት ከማን ጋር ሲዳራ እንደኖረ ማስታወስ አለበት። በየትኛውም መንገድ አማራው የተደራጀው አንድነት ሀይሉ አማራውን የሚፈልገውን ያህል፣ አማራው ከአንድነት ሀይሉ የሚፈልገውን አላገኘሁም ብሎ ተስፋ በመቁረጡ ነው። ከዚህም ሲያልፍ አንድነት ሀይሉ የአማራውን ቁስል በሚያመረቅዝ መልኩ የሰራባቸው አጋጣሚዎች የተበራከቱ መሆናቸው ነው። የአማራውን መደራጀት እንደ ውድቀት የሚመለከት ካለ፣ ይህ ክስተት በራሱ በአንድነት ሀይሉ ድክመትና ስህተት የመጣ መሆኑን መገንዘብ ይኖርበታል!
·         ደስታ።
በሌላ በኩል ግን በአማራው መደራጀት ደስታውን የሚገልፀው አካልም ከፍተኛ ፈተና እንደሚጠብቀው ባይዘነጋ መልካም ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በአማራነት የመደራጀትን ያህል ፈተና ያለ አይመስለኝም። ገና ከመሰረቱ ፕሮግራሙንአማራ ጠላት ነውብሎ የተነሳው ትህነግ/ህወሓት አለ። አማራን ጠላት ብሎ ለተነሳው ትህነግ ጉዳይ አስፈፃሚ የሆነው ብአዴን ባህርዳር ላይ ከትሟል። አማራውን ዋነኛ ቀጠናዬ ነው የሚለው አንድነት ሀይሉ ጋር መጠላለፍና ከዛ ያለፈ ፈተና ይጠብቃል። የአማራ ሕዝብ በደል የፈፀመበት በአገዛዝ ሂደት አይደለም። በፖሊሲ የተነደፈ ነው። በእነዚህ ምክንያቶች የአማራው ችግር እጅግ ውስብስብ ነው። የአማራ ሕዝብ ከበደሉ ብዛትና በደሉን የሚናገር በማጣቱየአማራ ድርጅት መጣሲባል የሚጠብቀው በተሸከመው በደል መጠን ነው። ከዚህ ባሻገር ይህ ድርጅት በመመስረቱ ድርጅቱም ሕዝብም ላይ የሚቃጣ ሌላ በትር ይኖራል። ይህ ድርጅት ሲመሰረት ይህን ሁሉ ሸክሞች እንዳሉበት ሊሰመርበት ይገባል። ከደስታው ባሻገር የቤት ስራው የከበደ መሆኑ መታወቅ አለበት። የሕዝብን ክብርና ጥቅም የሚያስጠብቅ፣ ከቀደሙት ፓርቲዎች ስህተት ተምሮ የሚጠበቅበትን የሚያበረክት፣ የአማራ ሕዝብ በድርጅት ላይ ያለውን ተስፋ ዳግመኛ እንዳይጨልም የሚያስችል የሰከነ ስራ መስራት ያስፈልጋል!
  • ምንጭ ዘሃበሻ ድህረ ገጽ።


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።