የባድመ ምስጢር


የባድመ ምስጢር
ክፍል አንድ እና ክፍል ሁለት 
(ወንድወሰን ተክሉ)
June 9, 2018
ክፍል አንድ

**መነሻ ጭብጥ-
በእለተ ቅዳሜ ግንቦት 13ቀን 2002 ላይ በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ምኒስትር የሆኑት አቶ ስዩም መስፍን All disputed areas have been given to Ethiopia በማለት ለኢትዮጵያዊያን እና ለመላው ዓለም የባድመ ለኢትዮጵያ መፈረድን አሳወቁ፡፡
ሰውዬው ዘሄግ የሚገኘው ዓለም አቀፉ አስታራቂ ተቋም International Tribunal Commission ባድመ፣ዛለአንበሳ፣ኢሮብ፣አሊተና፣ባዳ እና አጠቃላይ አዋዛጋቢ ሆነው በሻእቢይ ይገባኛል ጥያቄ የቀረበባቸው ስፍራዎች በሙሉ ለኢትዮጵያ ተወስኗል በማለት ኢትዮጵያዊያንን አስጨፈሩ፡፡
አያይዞም ስለ አጠቃላይ የኮሚሽኑን ውሳኔ በተመለከተ Ethiopia is satisfied with the decision. We hope that the decision will once and for all seal any attempt by the military adventurers to change boundaries by forceful means በማለት ውሳኔውን የሻእቢያን ተስፋፊነትን ውሳኔው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማስቆም ሚንውን ይጫወታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ይህ መግለጫ በአዲስ አበባ በተደመጠ ሶስት ቀናት በኋላ ማለትም ግንቦት 16ቀን 2002 ከአስመራ የተደመጠው የፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ንግግር የአቶ ስዩም መስፍንን አባባል ግልብጥብጡን የሚያወጣና ለኢትዮጵያዊያኑ የተነገረውም የውሸት መሆኑን የሚያጋልጥ ሆኖ ተገኘ፡፡
አይተ ኢሳይያስ ለህዝባቸው ባድመንና አወዛጋቢዎቹን ስፍራዎች በማሸነፋቸው የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት ሲያስተላልፉ Gift to present and future generations of Eritreans who will live within secure and recognized borders ” በማለት ከአወዛጋቢው የባድመ ግዛት ሌላ በአጠቃላይ የኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስኗት ድንበር በአጠቃላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ባለው መንገድ መወሰን በመቻሉ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡
ስለ አጠቃላይ የኮሚሽኑ ውሳኔ ፕሬዚዳንቱ ሲገልጹ Truth ,which had been severely battered over the past four years, has triumphed ” በማለት ፍትሃዊ ውሳኔ እንዳገኙበት ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያን ህዝብ በሀሰት ዜና ያስጨፈረውም ህወሃት መራሹ ስራዓት አይኑን በጨው አጥቦ ብቅ በማለት «የኮሚሽኑን ውሳኔ በመርህ አንጻር ተቀብለናል፡፡ ሆኖም ለተፈጻሚነቱ መነጋገር/መደራደር እንፈልጋለን» ብሎ የገለጸ ሲሆን ለዚህ አቋሙም ከኤርትራ በኩል የተደመጠው ፈጣን መልስ «የኮሚሽኑን ውሳኔ ከመተግበር ውጪ አንዳችም መደራደርም ሆነ መነጋገር አያስፈልገንም» የሚል አቋም ሆኖ ተገኝ፡፡
ይህ አቋም በሁለቱም ዘንድ ዛሬ 16ዓመታት ቆይታ በኋላም ቢሆን የተለወጠ አይደለም፡፡ አዲስ አበባ ያለው ስርዓት ደጋግሞ ሲገልጽ እንደተሰማው የኮሚሽኑን ውሳኔ በመርህ አኳያ እንደተቀበለ ይገልጽና ለዝርዝር አፈጻጸሙ ግን ከአስመራው ገዢ ኋይል ጋር መደራደር እንደሚፈልግ ደጋግሞ (ዛሬም ጭምር) ቢገልጽም በሻእቢያ በኩል ግን «ምንም የሚያደራድረን ነገር የለም፡ የኮሚሽኑን ውሳኔ ብቻ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተግብሩና ከዚያ በኋላ እንነጋገራለን» የሚል የጸና አቋም በመያዙ በሁለቱ ሀገራት መካከል No peace,No war ሰላምም ሆነ ጦርነት የሌለው ጉርብትና ተብሎ እርሰበርስ እየተቆራቆሱ ዘንድሮ ላይ ደርሰዋል፡፡
በተለይ ሰሞኑን (ከሁለት ሳምንት በፊት) / አቢይ አህመድ ለጉብኝት ወደ ሳኡዲ ዓረቢያ በተጓዙበት ወቅት የሳኡዲው ልኡል አልጋ ወራሽ ሰልማን /ምኒስትሩን ከኤርትራው አቻቸው አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር በስልክ ለማነጋገር ያደረጉት ሙከራ በአቶ ኢሳይያስ ከሪያድ የተደወለላቸውን ስልክ ለማንሳት ባለመፈለግ የከሸፈ ሲሆን በአቶ ኋይለማሪያም ጊዜ የአዲስ አበባው ስርዓት 53ጊዚያቶች ያህል ከአስመራው መንግስት ጋር ለመነጋገር ሞክሮ እንዳልተሳካለት ይታወቃል፡፡
ሆኖም በቅርቡ ስልጣን የያዙት እኚሁ / / አቢይ አህመድ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ጤናማ Normalization ለማድረግ ትኩረት ሰጥተውበት እንደሚንቀሳቀሱ ከማስታወቃቸውም በላይ አስመራ ላለው መንግስት «እንነጋገር/እንደራደር» ጥሪ ያስተላለፉ ሲሆን ኋያላኑ ሀገራትም እንደነ አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት እና ሳኡዲ ዓረቢያ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ፖለቲካዊ ውጥረት ለማርገብ -በተለይም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለውን ሁኔታ በእርቅ ለመፍታት ያላቸውን ፍላጎት እያሳዩት ካለው እንቅስቃሴ አንጻር መረዳት ይቻላል፡፡
የዶ/ አቢይ መራሹ መንግስት አስመራ ካለው የሻእቢያ መራሹ ስርዓት ጋር ተቀራርቦ ለመነጋገርና ያሉበትን No peace,No war ደረጃን በሰላማዊ መንገድ ለመለወጥ እንዳሰበ ያለውን ፍላጎትና ዓላማን ቢያስውቅም በባድመ ጉዳይ ላይ ምን ዓይነት አቋም ይዞ እንደተነሳና ብሎም የኮሚሽኑ ውሳኔ ሳይተገበር መደራደር የለም ያለውን የአስመራውን ገዢ በምን አይነት አዲስ አቀራረብ ለመቅረብ የነደፈውን እቅድ ይፋ ባያደርግም የባድመን ግዛት አሳልፎ ከመስጠት ውጪ ሌላ አማራጭ የለውም የሚሉ ወገኖች እንዳሉ ሁሉ አዲሱ /ምኒስትር በማቹ /ምኒስትር አቶ መለስና አቶ ኢሳይያስ መካከል የተፈረመውን እና የአልጀርሱ ስምምነት ተብሎ የሚታወቀውን ፊርማ እውቅና ያለመስጠት ህጋዊ መሰረት አላቸው በማለት አዲስ የመደራደሪያና የመነጋገሪያ አጀንዳ መቅረጽና ማዘጋጀት ይችላሉ ሲሉ ይናገራሉ፡፡
ለመሆኑ የባድመን መሬት ኮሚሽኑ እንዴት አድርጎ ነው ለኤርትራ ሊፈርድ የቻለው?
**መለስ ባድመን ለኤርትራ ያሰጠበት መሰሪ ሴራና የፈጸመው ሀገራዊ ክህደት
ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ አቶ ስዬ አብርሃ በመቀሌ ለህወሃት ካድሬዎች የአቶ መለስን ሀገራዊ ክህደት በመጥቀስና ሰውዬው በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን በትግራይ ህዝብ ላይም ከፍተኛ ክህደት የፈጸመ በመሆኑ መወገዝ አለበት የሚል ሀሳብ በማቅረባቸው በካድሬዎቹ ዘንድ ከፍተኛ መከፋፈልና ፍጭት መፈጠሩን ሰምተናል፡፡
ለክፍፍሉ መፈጠር ብገረምም-ብሎም ዛሬም ጭምር የአቶ መለስን ከፍተኛ ሀገራዊ ክህደት የሚረዳ የህወሃት ካድሬ ቁጥር አብላጫ ያለመሆን ቢያስገርመኝም በአቶ ስዬ በኩል የቀረበው ሀሳብ ትክክለኛነትን የሚያጠናክሩ እጅግ በርካታ መዛግብትና ማስረጃዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህም ሀገራዊ ክህደቶችና ሸፍጦች መካከል የባድመ ጉዳይ አንደኛው ክፍል ብቻ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡
ሆኖም ይህንን የእነ አቶ ስዬ አብርሃን የአቶ መለስ ክደውናል አቋምና አመለካከት የኢትዮ ሚዲያ ኤዲተሩ አቶ አብርሃ በላይ «መለስ ምንም አይነት ክህደት አልፈጸመም» ሲል ይሞግቷል፡፡
እንደ አቶ አብርሃ በላይ ሙግት አቶ መለስ ዜናዊ ገና በዊንጌት /ቤት ሳለ ኤርትራዊነቱን በይፋ በማወጅ፣የሻእቢያና ጀብሃን የመገንጠል ጥያቄን ፍትሃዊ ጥያቄ አድርጎ በጸረ ኢትዮጵያዊነቱ አቋም የተነሳ ግለሰብ በህወሃት አመራር ላይ ተፈናጦ እና አቋሙን በይፋ ገልጾ የተነሳለትን ለኤርትራ የመስራቱ ጉዳይ የክህደት ጉዳይ ተብሎ የሚገለጽ ሳይሆን ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ቢመረንም የተነሳለትን ዓላማ ያስፈጸመ ኤርትራዊ ነው ሲል ይናገራል፡፡
በክህደት የሚከሰስ ሰው ቀደም ብሎ በኢትዮጵያዊነቱ ያመነና የታወቀ ኢትዮጵያዊ ታጋይ ድንገት አቋሙን ለውጦ ለኤርትራ ቢሰራ ክህደት ፈጸመ ይባላል የሚለው አብርሃ የአቶ መለስ ጉዳይ ግን ገና ከመነሻው በግልጽና በይፋ የታወቀ ሆኖ ሳለ አጠቃላይ እውነተኞቹ ኢትዮጵያዊያኑ የትግራይ ተወላጆች ኤርትራዊነታቸውን በይፋ አውጀው ለኤርትራ መገንጠል በተነሱ ስብሃት ነጋ፣መለስ ዜናዊ፣ቴውድሮስ ሀጎስ፣ሳሞራ የኑስ፣ዓባይ ጸሃዬና መሰል አመራር ስር መመራታቸውና መታገላቸው ነው ትልቁ ክህደትና ጥፋት ሲል ይሞግታል፡፡
ክፍል ሁለት (ወንድወሰን ተክሉ)
ሆኖም አቶ መለስ በባድመ ጉዳይ የፈጸማቸው ሸፈጥና ሴራዎችን የምንገልጸው ሰውዬው በኢትዮጵያዊነት ስም እስከ መሪነት የደረሰ በመሆኑ ድርጊቱን ሀገራዊ ክህደት ብለን ከመግለጽ የተሻለ አማራጭ ቃል ባለማግኘቴ የመለስ ክህደት በሚል ድርጊቶቹን ለመግለጽ እገደዳለሁ፡፡
የአስመራውን የባድመን አሸናፊነት መግለጫ ከተሰማ በኋላ በአቶ መለስና ስዩም በኩል የዓለም አቀፉን ድንበር አስታራቂ ኮሚሽን ዳኞችን የሚያወግዝና አድሎአዊ ስራ እንደሰሩ የሚገልጽ መግለጫዎች መዥጎድጎድ ጀመሩ፡፡ ሆኖም ሄግ የተቀመጠው Permanent Court of Arbitration ዳኞች ዋና ሰብሳቢ ናይጄሪያዊው ሰር ኤሊያሁ Sir Elijahu እጅግ አስደንጋጭ የሆነ ምላሽ ሲሰጡ ተደመጠ፡፡
እንደ አቶ አመለስና አፈቀላጤው አቶ ስዩም መስፍን አገላለጽ ሄግ ያሉት ዳኞች በምስጢር ባድመን ለኤርትራ በመስጠት ሴራ እንደፈጸሙ በመግለጽ ዳኞቹን ያወገዘ ሲሆን (ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ማለት ነው) የሰር ኤሊያሁ መልስ ግን «የኢትዮጵያ መንግስት በባድመ ይገባኛል ጥያቄ ላይ ያለውን የባለቤትነት ማሳያ ማስረጃ በላከልን መሰረት ለኤርትራ ትገባለች ብለን ፈርደናል» ካሉ በኋላ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ስለቀረበው ማስረጃም ሲያብራሩ «የኢትዮጵያ ተወካዮች ባቀረቡልን ካርታ መሰረት ባድመ የኤርትራ መሆናን በማያሻማ ሁኔታ የሚያሳይ ማስረጃ በመሆኑ ለኤርትራ እንዲሰጥ በማለት ልንወስን ችለናል» ሲሉ አብራርተዋል፡፡
እዚህጋ በጣም ልብ ማለት የሚገባን ፍርድ ቤቱ «የኤርትራ መንግስት ባቀረበው ማስረጃ መሰረት »ሳይሆን ያለው «የኢትዮጵያ መንግስት ባቀረበው ማስረጃ መሰረት የባድመ መሬት የኤርትራ ግዛት ውስጥ መሆኑን ያረጋገጠ በመሆኑ..» በማለት ነው የባድመን መሬት ለኤትራ ለመስጠት የቻለበትን ሂደትና ማስረጃ ለመጥቀስ የቻለውና ለመሆኑ ይህ በእኛው መንግስት በኩል የቀረበው ማስረጃ ምንድነው?ከየትስ ተገኘ ብለን ልንጠይቅ እንገደዳለን፡፡
በአቶ መለስና አቶ ስዩም የፕሮፖጋንዳ ጩህት የተገረሙ የሆኑት ዳኛ በዚህ ብቻ አላበቁም፡፡ ቀጥለውም ሲናገሩ «የኢትዮጵያ መንግስት በተወካዮቹ በኩል ባቀረበው ማስረጃ መሰረት የባድመን መሬት ወደ ኤርትራ የጾረናን አጠቃላይ ግዛት ወደ ኢትዮጵያ ይገባል ብሎ ችሎቱ ውሳኔ በሰጠበት ወቅት የኢትዮጵያ ተወካዮች የጾረና ግዛት በኢትዮጵያ ግዛት ስር ተዳድሮ አያውቅም ብለው አምርረው በመቃወም ውሳኔው እንዲሻር ከማድረጋቸውም በላይ የኤርትራ ተወካዮች ይዘውት ያልመጡትንና ባድመን የኤርትራ መሆናን የሚያሳይ ማስረጃን የኢትዮጵያ ተወካዮች ይዘው ያቀረቡ ሆኖ ሳለ ፍርድ ቤቱ አድሎዓዊ ውሳኔ ወስኗል ማለታቸው አግባብ አይደለም» በማለት የመለስን ሀገራዊ ክህደትና ሴራን በይፋ አስታውቀዋል፡፡
በአቶ መለስ ኢትዮጵያን እንዲወክሉ የተመለመሉት ኤርትራዊያኖቹ የማነ ጀማይካና / ፋሲል ናሆም ሲሆኑ በወቅቱ ኢትዮጵያ በአግባቡ እንድትወከል ነጻ የህግ አገልግሎት ለማበርከት ጥያቄ አቅርበው የነበሩ እንደነ / ያእቆብ አይነቱን ዓለም አቀፍ የህግ ባለሙያን አቶ መለስ ዝር እንዳይሉ በማገድ ከለይ የተጠቀሱትን ኤርትራዊያንን እንዲወክሉን በማድረግ ታላቅ ሸፍጥና ክህደት እንደፈጸመ እናያለን፡፡
አቶ መለስ እነዚህን ኤርትራዊያንን ተወካይ አድርጎ ወደ ሄግ ከመላኩ በፊት የባድመን ኢትዮጵያዊያንትን የሚያስረዱ ማስረጃዎችን በሙሉ ማለትም
1-በልኡል መንገሻ ስዩም አስተዳደር ወቅት የወረዳውን ግብር የገበረበትን ደረሰኞች
2-የባድመን ከትግራይ ክፍለ አንድ አውራጃ ውስጥ ያለች ግዛት መሆናን የሚያስረዱ የአስተዳደር ካርታዎችና መዋቅሮችን ገላጭ ማስረጃዎች
3-የባድመን ህዝብ በባህል፣በቋንቋና፣በሀይማኖትና በታሪክ የትግራይ ክፍለ ሀገር አካልነትን በተጨባጭ የሚያስረዱ ዘርፈ ብዙ ማስረጃዎች ከመቀሌ ተሰብስቦ እንዲላክለት በጠየቀው መሰረት እነዚህ ሁሉ ታሪካዊ ማስረጃዎች ተለቃቅመው ለአቶ መለስ እንደተላኩለት ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ሆኖም እነዚህን ወሳኝ ማስረጃዎች በእጁ ያስገባው አቶ መለስ መቅረብና መከራከር በማይገባው ሄግ አስታራቂ ፍርድ ቤት ላይ ለሚወከሉት ኢትዮጵያዊያን ተከራካሪዎችን መድቦ ከመስጠትና ከመሸኘት ይልቅ እሱ ግን ያደረገው
1-እነዚህን ወሳኝ ማስረጃዎችን ሙሉ በሙሉ ማውደም
2-በፍርድ ቤቱ የሚወከሉትን ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ኤርትራዊያንን ማድረግና
3-በኢጣሊያ ዘመን የባድመን መሬት ከኤርትራ ግዛት ስር ያካለለን ካርታ ብቻ አስይዞ ወደ ፍርድ ቤቱ የመላክን ስራ ስለፈጸመ አስታራቂውም ፍርድቤት በራሳ በኢትዮጵያ በኩል በቀረበለት ካርታ ላይ ተመርኩዞ ፍርዱን ሊሰጥ እንደቻለ ነው በግልጽ መረዳት የቻልነው፡፡
በሚገርም ሁኔታና ከባድመም ውሳኔ በላይ እጅግ የሚያስደንቀው ጉዳይ የድርድ ቤቱ የባድመን ጉዳይ ለኤርትራ እንደፈረደ የጾረናን ግዛት አጠቃላይ ለኢትዮጵያ ብሎ በሚፈርድበት ወቅት ትልቁ ተቃዋሚና ተከላካይ ሆነው የተገኙት የኤርትራ ተወካዮች ሳይሆን በስም የኢትዮጵያ ተወካይ የተባሉት የማነ ጀማይካና / ፋሲል ናሆም መሆናቸውን ስናውቅ መለስ ምን ያህል በኢትዮጵያና በትግራይ ህዝብ ላይ ታላቅ ክህደት እየፈጸመ እንዳለ በግልጽ ያሳየናል፡፡
የማነ ጀማይካና / ፋሲል ናሆም ከአዲስ አበባው መለስ ዜናዊ በተሰጣቸው ግልጽ መመሪያ መሰረት በሰር ኤሊያሁ የሚመራው ዓለም አቀፉ አስታራቂ ኮሚሽን ዳኞች «ጾረና እና አከባቢው በፍጹም የኢትዮጵያ ግዛት ሆነው የማያውቁ ግዛቶች በመሆናቸው ኢትዮጵያ የራሷ ያልሆነና የኤርትራ የሆነ ግዛት ወደ ግዛቷ እንዲካለል አትፈልግም» በሚል ቅዋሜ ችሎቱን አስገርመው ያስሻሩት ውሳኔ እንደሆነ ከተለቀቀው አጠቃላይ የችሎቱ ዝርዘር ሂደት መረዳት ተችላል፡፡
*ለምንድነው መለስ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ኤርትራዊያንን ለኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ውዝግብ ወክለው እንዲከራከሩ የላከው?
* ለምንድነው መለስ በእነ ልኡል መንገሻ ስዩም ጊዜ ጀምሮ የባድመን ኢትዮጵያዊያነት የሚያሳይ ማስረጃዎችን አውድሞ(ደብቆ) በጣሊያን የተሰራና ግዛቷን በኤርትራ ስር መሆናን የሚገልጽ ካርታን አሳቅፎና ሆን ብሎ ወደ -ሄግ ሊልክ የቻለው?
*ለምንድነው መለስ በውሳኔው እለት በአፈቀላጤው ባድመ ለኢትዮጵያ ተፈረደ ብሎ ህዝብን በሀሰት ያስጨፈረውና በኋላም ቁርጡ ሲወጣ ጥፋቱን በዳኞች ላይ ሊያላክክ የቻለው?
*ለምንድነው መለስ የአልጀርሱን ስምምነት ለመፈርምና ብሎም ይግባኝ የሌለው ፍርድ ይሰጠን ብሎ እራሱ ጠይቆ ሊፈርም የቻለው?
የዚህ ሰውዬ (የአቶ መለስ ማለቴ ነው) ሀገራዊ ክህደትና ሴራ በዚህ በባድመ ብቻ ተገልጾ የሚያበቃ አይደለም፡፡ በጾረና ግንባር በዚሁ በባድመ ጦስ በተካሄደ ውጊያ ሰራዊታችን እጅግ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ እንዲጨፈጨፍ ተደርጓል፡፡
መለስ የጾረናን እልቂት ከማስፈጸሙ በፊት እንደነ / በርሄ ሻእቢያ የመሳሰሉ ጀግና እና ሀገር ወዳድ ተወጊዎችንና አዋጊዎችን ለምንድነው ነጥሎ ከእነባለቤቱ ሊገድላቸው የቻለው?
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን በአፍሪካን ጉዳይ ኋላፊ በነበረችው ሱዛን ራይስ አማካኝነት ለመለስ መደራደሪያ ይሆንህ ዘንድ ጦርነቱን ከማቆምህ በፊት አሰብን እንድትቆጣጠር ሶስት ቀን ሰጥቼሃለሁ »በማለት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አሰብን ይቆጣጠር ዘንድ ትእዛዝ መስጠቱን ከዲፕሎማቲክ ምንጮች የተረጋገጠ ሀቅ ነው፡፡
ይህንን ትእዛዝ የተቀበለው አቶ መለስ ግን አይደለም አሰብን ሊቆጣጠር ቀርቶ በባድመ በተገኘው ታላቅ መስዋእትነትን ባስከፈለን ድል ሞራሉ የተነካውን የሻእቢያን ሰራዊት ሞራል ጥገና እና ግንባታ ባደረገው ከፍተኛ የሆነ አሻጥርና ደባ ሰራዊታችንን ጾረና ላይ ክፉኛ በማስቀጥቀጥ ኢትዮጵያ የባድመን «ዘመቻ ጸሃይ ግባትን» ያሸነፈችና ግና በአጠቃላይ ከሻእቢያ ጋር እየተካሄደ በነበረው ጦርነት ግን የተሸነፈች ሀገር አድርጎ ለተሸናፊው ሻእቢያ ገጸ በረከት ያዋለበት ግንባር ሊሆን በቅቷል፡፡
ገና ከመነሻው መከላከያችን በቂ የጦር መሳሪያም እንዳይታጠቅ ከፍተኛ ሳቦታጅ እያደረገ ሲከላከል የነበረው መለስ በእነ ስዬ አስገዳጅነትና በራሱ በስዬ ከሚያዘው የኤፈርት ካዝና አቶ ስዬ 3ቢሊዮን ብር ለኢትዮጵያ «አበድሮ» መሳሪያ እንዲገዛ ከተደረገና በተለይም እሱ አንዳችም አስተዋጾኦ ባላደረገበት የባድመ ዘመቻ በድል ከተደመደመ በኋላ ባሉት ወታደራዊ ዘመቻዎች ውስጥ ጣልቃ በመግባት የኢትዮጵያ መሪ ሆኖ ግን እንደ የሻእቢያ መሪ ሰራዊታችንን በጾረና ግንባር፣በተሰነይና ባሬንቱና በአሰብ ቡሬ ግንባር እጅግ በሚያስቀቅ ሁኔታ እንዳስጨፈጨፈ የሚገልጹ ማስረጃዎች ከበቂ በላይ በሆነ ሁኔታ በገፍ ተከማችቶ ያለ ሀቅ ነው፡፡
የባእድ ሀገር መሪ የሆነው ቢል ክሊንተን «ለመደራደሪያነት ያግዝሃል አሰብን ተቆጣጠር» እስከማለት በደረሰበት ዳተኝነቱ መለስ ያደረገው አሰብን መቆጣጠር ሳይሆን ወደ አሰብ እየገሰገሰ የነበረውን ሰራዊታችንን በአየር ኋይልና በመድፍ በማስደብደብ እንዲመለስና እንዲያፈግፍግ ማድረግ ነበር፡፡
በሚደንቅ ሁኔታ በአሰብ በኩል ያለውን ድንበር በተመለከተ በዘ-ሄግ ያለው አስታራቂ ፍርድ ቤት ድንበራችሁን ከዓለም አቀፍ ውሃ ድንበር በመነሳት ስድሳ ኪሎ ሜትር ይወሰን
ሲል መለስ አይሆንም ከዓለም አቀፉ ውሃ ድንበር ሳይሆን ከምድር ተነስቶ ስድስ ኪሎሜትር መሆን አለበት ያለ አስገራሚ ሰው ነው፡፡
አሰብ በቀይ ባህር ላይ 12 ይጋዛና 48ደግሞ በየብስ በመረዝም የኢትዮጵያና የኤርትራ ድንበር ተብሎ ሊካለል የነበረውን የዳኞቹን ፕሮፖዛል በመለስ የተወከሉት የማነ ጀማይካና / ፋሲል ናሆም በአለቃቸው ትእዛዝ መሰረት «የለም ድንበሩ ከባህር ውስጥ በሚጀምር ቆጠራ ሳይሆን ከየብስ በሚጀምር ቆጠራ ስድሳ ኪሎ ሜትር ይወሰን »በማለታቸው በአሰብ ድንበር በኩል ሻእቢያ 12ኪሎ ሜትር ተጨማሪ መሬትን ከኢትዮጵያ እንዲሰጠው አድርገዋል፡፡
እነዚህ የአይተ መለስ ውስጣዊ ሴራዎችና ተግባራት በሙሉ ይህችን ሀገር በመሪነት እመራለሁ ብሎ ግን የፈጸማቸውን ክህደትና አሻጥር ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ሲሆን እውነተኛ የህገር መሪ ቢኖር በወቅቱም ሆነ አሁንም ሆነ ወደ ፊት መለስ በሀገር ክህደት Treason ተከሶ ለፍርድ መቅረብ ሲገባው ዛሬም ጭምር በትግራይ መቀሌ ለምውት ክቡሩ የሚሞግቱለትን ካድሬዎችና ብሎም አስከሬኑን 7/24 ሰዓት በወታደር ሲጠበቅ የምናይበት ዋና ምክንያት ሀገራችን ገና ትክክለኛ ሀገር ወዳድ መሪ ስላለገኘች ወይም አሁን ስልጣን ላይ ያሉት / አቢይ ገና ስላልተጠናከሩ ብቻ ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያን 21ዓመታት የገዛት መለስ ዜናዊ አንዲትም ቀን ኢትዮጵያዊ ሳይሆንና እንዲሁ ከጫካ ጀምሮ «የኤርትራ ትግል ከየት ወደየት» እያለ ስለ ኤርትራ ሲቃትት እንደነበረ በስልጣን ዘመኑም ለኤርትራ በመስራት ኢትዮጵያን የካደ ከሀዲ በመሆኑ ዛሬ እነ አቶ ስዬ አብርሃን የመሳስሉ እጅግ ቢዘገዩም መለስ ከሀዲ ነው ብለው መነሳታቸው የሚያስገርም አይደለም፡፡
ለመሆኑ በአንድ ሀገሩን በከዳ መሪ የተፈረመ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ጅጎች በተከታዩ ወራሽ አዲስ መንግስት የመጠበቅ ግዴታ ምን ያህል ነው?
በከሀዲው መለስ የተፈረሙ ፊርማዎችን የዛሬው መንግስት የማክበርና ያለማክበር ሞራላዊና ዓለም አቀፋዊ ህግጋቶች ምን ይላሉ?

የዚህ Permanent Court of Arbitration ተቋም አስገዳጅነት ስልጣንና መሰል ዓለም አቀፍ ህግጋቶች በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸውን አቋምና አመለካከት የምቃኝበትን ክፍል በመጣጥፌ ሶስተኛው ክፍል የምቃኝበትን እስካቀርብ በቸር እንሰንብት፡፡
  • ምንጭ። http://www.satenaw.com/amharic/archives/58101

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።