አጋጣሚሰጥ ስሜት ምንድን ነው?

አጋጣሚሰጥ ስሜት።

„ከቸር ሰው ጋር ቸር ሁነህ ትገኛለህ፤
ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፤
ከንጹህ ጋር ንጹህ ሆነህ ትገኛለህ፤
ከጠማማ ጋር ጠማማ ሁነህ ትገኛለህ።“
(መዝሙር  ምዕራፍ ፲፯ ከቁጥር ፳፭ እስከ ቁጥር ፳፮)
ከሥርጉተ©ሥላሴ 09.07.2018 
(ከገዳማዋቷ ሲዊዝሻ።)



ስሜት የሰውነት ቋንቋ ነው። ስሜት የመንፈስ መርከብ ነው። ስሜት የነፍስ ተልዕኮ ነው። ስሜት ረቂቅ ነው። ስሜትን የሚተረጉሙ ሁነቶች የመኖራቸውን ያህል የስሜትን ትክክለኛ ገጸ ባህሪ ሊገልጹ የማይችሉ ሁነቶችም ይገጥማሉ። ሥም የለሽ ስሜቶች እንደ ማለት።

ይህን እኔ ያወቅኩት የኤርትራ ልዑክ አዲስ አባባ ሲገባ የተሰማኝን አዎንታዊ ስሜት መልኩ፤ ቁመናው፤ ይዘቱ፤ አፈጣጠሩ፤ ሂደቱ፤ አቅጣጫው በፍጹም ሁኔታ ስሜቴን ማወቅ ከቻልኩበት ዘመን ጀምሮ አዲስ እና የተለዬ ነበር።

ለዚህን ያህል ዘመን ይህን መሰል ሥም የለሽ ስሜት እንዳለኝ አለማወቄ ብቻ ሳይሆን ሌላም አጋጣሚ ቢፈጠር እንዲሁ በተቀማጭንት ያሉ ሌሎች የስሜት ዓይነቶችም ሊኖሩ እንደሚችሉ አሁን አዲስ ምናባዊ መስመር ያበጀሁላቸው ይመስለኛል።

የታወቁ ስሜቶች በስዕል፤ በምልክት፤ በጹሁፍ፤ በትይንት፤ በምልክት፤ በደወል፤ በንግግር ሲገለጡ ኖረዋል። እኔ ወደዛ መግባት ብዙም አልፈልግም።  ለእኔ ሳብ ያደረገኝ ይህ የማላውቀው ስሜትን የመግለጫ ቋንቋ ማጣቴ ብቻ ሳይሆን ተደብቆ የመቆዬቱ ሚስጢርም ነው። ሚሰጢሩን ፍልፍዬ ማግኘትን በቀጣይነት እሻለሁኝ።

የኤርትራን ሰው በማዬቴ እንዳልል ሲዊዝ ራስ እግሩ ኤርትራዊ ነው። በዛ ላይ ከኢትዮጵያዊው ሰው የሚለይበት ምንም ነገር የለም። የልሳናችን የድምጽ አወጣጥ ቅላፄያችን ብቻ ነው ልዩነት ለሚለው ተቀራራቢ ነገር የማይበት፤ የአዲስ አበባው አውሮፕላን ማረፊያም ቢሆን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሚዲያ ላይ የማዬው ያው የተለመደው ቦሌ አዬር ማረፊያ ነው።

ሥርዓቱ ነው እንዳልል ያው የተለመድ የእንግዳ አቀባባል የዘወትር ተግባር ነው። ታዲያ ምን ይሆን ያን የተለዬ ስሜት ሊያመጣ የሚችለው?

እኔ እንደ ተረዳሁት የሰው ልጅ አጋጣሚን የሚጠብቁ ግን ሳያውቃቸው ከእርሱ / ከእርሷ ጋር የሚኖሩ ረቂቃን ስሜቶች ጋር አብሮ እንደሚኖር ነው የተረዳሁት።
እነዚህ በተቀማጭነት ያሉ የተመሰጠሩ ግን ገሃድ ያልወጡ ስሜቶች አጋጣሚ ካልረዳቸው ከተፈጠረው ሰው ጋር ምድራዊው ኩንትራት ሲያልቅ ያው አብረው ይቀበራሉ። ስለዚህ ገና ምርምር ያልተሠራበት አዲስ የሃብት ቀመር እንዳለ ይሰማኛል።

በተለምዶ ሳቅ እና ዕንባ ከሆነ ሲቃ ይባላል። ድብልቅ ያለ። ባለፈው ጊዜም በዬትኛው እርእሰ ጉዳይ እንደሆን በማላስታውሰው ጹሑፌ ላይ የሰዎችን አፈጣጠር ስገልጽ ከዚህ ቀደም በተውኔት ዓለም ዓቀፍ እውቅና ያገኙ ሁለት ታላላቅ አውራ ሁነቶችን „አስቂኝ // አሳዛኝ Tragedy and Comedy“ በሚል ይከፍላቸዋል።

እኔ ደግሞ በ2008 እ.አ.አ በጀመርኩት ጸጋዬ ድህረ ገጽ ላይ ከሁሉቱ ማህል ያለ ሌላ ሦስተኛ ሁነትም አለ በሚል ጽፌ ነበር። ያን ጊዜም „ሲቃ“ የሚለውን እንዳ ናሙና ውስጄ ነበር። የቀደምቶቹ ሁለቱም „ሳቅ እና ሃዘን Tragedy and Comedy“ ስሜት ናቸው። ሁለቱ የተቀላቀልበትም „ሲቃም“ ስሜት ነው። ማዕከላዊ ዝንቅ ግን ውህድ የሆነ ስሜት። ወጥነት ያለው የውስጥ ሙቅ ስሜት።  

ስሜት ይሰጠነጠቃል፤ ስሜት ይንጠለጠላል፤ ስሜት ይሻቅላል፤ ስሜት ይነዳል፤ ስሜት ይሾፈራል፤ ስሜት ይቀረጻል፤ ስሜት ይነደፋል፤ ስሜት ይጣመራል፤ ስሜት ይዋህዳል፤ ስሜት ይሰበራል፤ ስሜት ይሄዳል፤ ስሜት ይደብዝዛል፤ ስሜት ይመጣል፤ ስሜት ይቀዘቅዛል፤ ስሜት ያቆጠቁጣል፤ ስሜት ለብ ይላል፤ ስሜት ይፈላል፤ ሰሜት የነጥራል፤ ስሜት ይበቅላል፤ ስሜት ያጠራል፤ ስሜት አቋም ይፈጥራል፤ ስሜት አቋም ያሰናብታል፤ ስሜት ያስወስናንል። ስሜት ቋሚነትን ስሜት ዘለቄታነትን ለማግኘት እጅግ የረቀቁ የመሆን ንጥረ ነገሮች አሉበት። ይሄ እንግዲህ በሚታወቁ ስሜቶች ሰንሰለታም ተፈጥሮ ሲኬድ ነው።

ለነገሩ እኔ አምስት የስሜት ህዋሳት የሚለውን አልስማመበትም። እኔ ስድሰተኛም አለ ብዬ አምናለሁኝ። ያም የነቃው የህሊና ክፍል ነው። ከዬትኛው መጸሐፌ ላይ እንዳለ አላስታውሰውም ይሄኑኑ ሰርቸዋለሁኝ። እንዲያውም የስሜት ጄኔሬተር የምለው የነቃው የህሊና ክፍል ነው። 

የነቃው የቋሚዎቹ የአምስቱ የስሜት ህዋሳት የበላይ አዛዥና ሞደሬተር ብቻ ሳይሆን የትዛዙን ምላሽ ስበሳቢም ነው። በሌላ በኩል እሱ ራሱን ችሎም ቤተኛ ነው። ይህም ማለት ከማዛዝ እና ምላሽ ከመሰብበሰብ ጋር ራሱም ስድስተኛ የስሜት ህዋስ አንድ አካል ነው ባይ ነኝ። ይህ የስሜት ህዋስ እንደ ሌሎችም በአንጎል ይመራል ምላሹንም ይሰበሰባል። ስለዚህ እንደ አባልም እንደ መሪም ሆኖ ያገለግላል ማለት ነው የነቃው የህሊና ክፍል የስሜት ሚና።

ይህ እንግዲህ በሚታወቁ የስሜት ጠገጎች ውስጥ የሚያልፍ ሲሆን አዲሱ ግን የማላውቀው ስሜቴ መጤ ማለት አልችልም። ባለርስት ነው። ግን አላውቀውም። ለምሳሌ ሳዝን አለቅሳለሁኝ። ደስ ሲለኝ እስቃለሁኝ። ሳኮርፍ ከንፈሬ ዳሽንን ያክላል። ይሄኛው ግን እንዴት እና እንደምን ብዬ ልገልጸው አልችልም። 

ምክንያቱም የአፈጣጠሩ ቅጽበት እና ሁኔታ እኔን እንጂ ሌላውን ሊገለጽ አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን፤ አብሮኝ ያለ ሰውም በዛች ቅጽበት ቢኖር ሊያውቀው አይችልም። እጅግ ጥልቅ እና ስውር ግን ውስጤን በውስጤ የገለጸ ነው።

ማን ልበለው? ምንስ ልበለው? ለረጅም ጊዜ እከታተለው የነበረ ትራውማ ቴራፒ የሚባል ነበር። በዛ ቴራፒ ረቂቅ ነገር አትርፌበታለሁኝ። የድሉ ዕለት ቀጥ ብዬ ሄጄ ኬክ እና ሻማ ገዝቼ ቤት መጥቼ ዕለቱን አስብኩት። በቃልም በጹሁፍም ልገልጸው የማልችለው ስለነበረ እንደ መንፈሴ ለማቀረባቸው ለሁለት ጓደኞቼ ነገርኳቸው። አሁን ከመሼ ደግሞ በተለዬ ሁኔታ ለሌሎች ለሁለት ሰዎች አብራራሁላቸው። በድምሩ ለአራት ሰው ማለት ነው።

በዛ ስሜት ውስጥ የነበረው መኖር ፈተናው ከባድ የነበረ ቢሆንም፤ ግን ፈተናውን ለማለፍ የተጠቀምኩባቸው ሂደቶች እጅግ ድንቅ ነበሩ። በዛ ፈተና ውስጥ ራሴን ውስጤን መኖሬን ነፍሴን ሁሉንም ፈትሼ ከአገር ሆድ ይሰፋል ሳይሆን ከአገር ስሜት ይሰፋል የሚለውን ተምሬበታለሁኝ።

ስለዚህ በስሜት ውስጥ ያልተጠቀምንባቸው፤ የ እና መሆናቸውን የማናውቀው ግን አጋጣሚን የሚጠብቁ ስምም ያልወጣላቸው የስሜት ዓይነቶች እንዳሉ አውቄያለሁኝ። እርግጥ ነው እኔ ሳይንቲስት አይደለሁም። ግን ሁኔታዎችን በአስተውሎት የማዬት ዝንባሌው ግን አለኝ። አሁን ፎቶ እኔ እንዳገኘሁት አላዬውም። ፎቶ ሳገኝ አሰቀምጠዋለሁኝ። ያን ፎቶ ጊዜ ሲኖረኝ በተለያዩ ቀናት እያወጣሁኝ እመለከተዋለሁኝ። 

ያን ፎቶ ቁጭ አድርጌ አነጋግረዋለሁኝ። ያን ፎቶ አወያዬዋለሁኝ። ያን ፎቶ በዛች ቅጽበት ካሜራ ውስጥ ሲገባ የነበረውን ሁነት እመረምረዋለሁኝ። ቪዲዮም ቢሆን እንዲሁ ነው። ሁለመናውን በዓይን ቀዶ ጥገና ይደረገትለት እና ክፍትፍት ብሎ ይጎበኛል። ዝርዘር ብሎ ይተነተናል። ስለምን ጉዳዬ ውስጥ ስለሆነ።

በአንድ ወቅት እኔ ፕ/ ኢሳያስ አፈወርቂን ሳቃቸውን አይቼ አላውቅም አልኩኝ። የሳቁበት ፎቶ አግኝቻለሁኝ። ያ ውስጣቸውን ገላጭ አልነበረም። ሌሎች ፎቶዎችንም አትሜ ተመለከትኳቸው፤ ውስጣቸው በሃዘን ኩምትር እንዳለ ተረዳሁኝ። በዛ ህይወታቸው ውስጥ ያጡት ነገር የተከደነው ምንድን ነው ብዬ አሰብኩኝ።

ኤርትራን አገር ማድረግ ተሳክተላቸዋል። ኤርትራ ሉዑላዊት አገር ናት። አንድ ሉዑላዊት አገር ያላት መብትም አላት አገራቸው። ነገር ግን ይህም ሆኖ መሪዋ ደሰታቸውን ተቀምተዋል። ይህን የሚነገረኝ የፎቷቸው ውስጥ ነበር። 

አሁን ትናንት ስጽፍ ፕ/ ኢሳያስ አፈወርቂ ሳቁ ብዬ ጻፍኩኝ። የመከፋታቸው ማብቂያ መባቻ ቀን ስለሆነ። ከሳቸው የተፈጠረውም ሳቅ ቀን የወጣለት ከትናት ጀምሮ ነው። ያጡትን ግን ሳይገልጹልን የቆዩትን የታመቀ የስሜት ንጥረ ነገርን አግኝተዋል።

ስለዚህ በዚህ ውስጠት ውስጥ ቂምም፤ በቀልም፤ ቁርሾም፤ ብልጠትም፤ ጥላቻን እኔ ማሰብ አልችልም። በፍጹም። በጣም ንጹህ የሆነ ተስፋ ነው የታዬኝ። ዛሬን ሳስበው ባለቅኔው ጠ/ ሚር አብይ አህመድ በተንቀሳቀሱ ቁጥር ልቤ እንደ ቅል ልክ እንደወለድኩት ልጅ ነበር በስጋት እምወጠረው። ከኢትዮጵያ በተሻለ ምቾት ተሰምቶኛል። ምንም የጥርጣሬ የስጋት እና የፍርሃት ስሜት በውስጤ አልመጣም። ስለምን? ያ የማላውቀው ስሜት የፈጠረብኝ ተጽዕኖ ይመስለኛል።

ያገዘኝ ያ የማለውቀው አዲስ ስሜት ነጥሮ የወጣ ማህተም ስለነበር ጥርጣሬዬን ሁሉ ከባህር ከገደል ጣልልኝ። የኤርትራ ልዑክ ቦሌ ላይ ሳያቸው ነው ያ ስሜት የተፈጠረብኝ። ውስጤ የነበረ ግን የማላውቀው ስሜቴ ጋር ተገናኘን። ያ በፍጹም ሁኔታ ማመንን ፈጠረልኝ። ተመስገን!

 ስለሆነም እኔ ሳስበው የእኔ መሰል ስሜት በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ ብዙ ሰዎች ሊገጥማቸው ይችላል ብዬ አስባለሁኝ ፕ/ ኢሳያስ አፈወርቂን ጨምሮ። ስለምን? አጋጣሚዎችን ካለገኙ እንደዛ ዓይነት የማይታወቁ ስሜቶች አይከሰቱም፤ ከተከሰቱ ግን የጸዱ የጸደቁም ናቸው። መታመንን የሚያፈልቁ - የሚያበለጽጉም። መታመንንም የሚለግሱ፤ እርግጠኝነትን የሚያቆምሱ። እንደ ስለት ልጅ የሚታዩ ይሆናሉ።

የኔዎቹ ስለ ሥም የለሹ አጋጠሚሰጥ ስሜት ለዛሬው በዚህ ይከወን፤

ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!

ቅኖቹ ኑሩልኝ ማለፊያ ጊዜ።


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።