ባልደራስ ለኢትዮጵያ።


እንኳን ወደ ቀንበጥ ብሎግ በሰላም መጡልኝ።

ባልደራስ ለኢትዮጵያ እንደ
አባት አደሩ ሰንበት ቅኔ ዘረፈለት።

„አሁንም ልጆቼ ሆይ ስሙኝ ካፌ ቃል አትራቁ።“
 (መጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ 5 ቁጥር 7)

ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
15.01.2020
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።


·        እፍታ።

እንዲህ በአጭር ጊዜ ባልደራስ ለኢትዮጵያ ጉዳይ እመለሳለሁ ብዬ አላስብኩም ነበር። ዘለግ ያለ ሃሳቤን ስለገለጽኩኝ። ብቻ አዎን ብቻ በኽረ አጀንዳችን ይሆን ዘንድ አቅሙን በበለጠ፤ በመሰመረ ሁኔታ ገንቡለት ተባልን፤ ጥበብ ያነሳቸው ፍጥረቶች እነ ማህበረ - ኦነጋውያን። ስለሆነም ደግመህ ናብኝ ማንጠግቦህ ተበላ! እና ብራና እና ቀለም ተመሳጠሩ። 

የህልውና ተጋድሎ እንዲህም መራራ ነው። እንዲህም በዬፌርማታው ቀጠሮ የሚሰጥበት አይደለም። ተግ! እስኪ በል ማለት አይቻልም። ቆራጥ ውሳኔ የሚሰጠው እረኛ ያስፈልገዋል። አዲስ አበቤ ሆይ! እንደ ተመኘሁልህ ቀንቶኃ። አይዞህ ባይ ማግኘትህ ዕሴትህ አድርገው።

·        በር።  

እንዴት ናችሁ ቅኔዎቹ ተዋጥን እኮ በኦነጋውያን የድንገቴ ዝብርቅ ተውኔት። ድብልቅልቅ ያደርጉታል ሁለመናውን። የሰከነውን አዬር እራሱ ይቀኑበታል። ቀናተኛ ናቸው። የረጋውን አውደ ምህረት ቀይጠው ቀወጡት። ሱናሜ ነው የኦነጋውያን ቅይጡ ቅንጡ ንጠት። ከቶ ተግባባን ይሆን? እኔ ለረጅም ጊዜ ስጽፍበት የባጀሁትን በቅርቡ ለዘሃበሻ ልኬለት አውጥቶት ነበር። ሊንኩን ከሥር እለጥፋለሁኝ። ጉዳዩ የፈረቃም፤ የተረኝነትም አይደለም ከዛ ያለፈ ነው ብዬ ነበር። አምቀው፤ አሽገው አጥረው ይዛዋታል ልዕልት ኢትዮጵያን በቃላት ጅዶ ከሽነው።

የችግሩን የውሃ ልኩን ሳታውቅ ትግል ግብ አይመታም። ቁልፉ አጀንዳ ሊሆን የሚገባው ይህ የፖለቲካ ጭብጥ ነበር። ነገር ግን ሰሚ አሁንም አላገኜም። ይደገም እስኪ … ጥገናዊ ለውጥ ተብዬው ተጥልፏል። ፈረቃም ተረኝነትም አይደለም በኦሮሙማ ማንፌስቶ የሚመራ አገር፤ በኦሮሙማ የሚመራ አህጉር የመፍጠር ምኞት ብቻ ሳይሆን ተግባር ላይ እየተተጋበት ያለ ሞጋች ጉዳይ ነው። አውስትራልያ አገርም አህጉርም ነው። ህልሙ ይሄው ነው። ኦሮምያ አገርም አህጉርም እንድትሆነው ትጋቱ።

ህሊናቸውን ተነቅሎ ልብ እንዲገጥምላቸው ለማይፈቅዱ ቆራጦች ሃቁ ይህ መሆኑን ይረዱት። ኦነጋውያን መቼውንም የማጠረቃ አጋሰስ ፍላጎት ነው ያላቸው እንደ ግብጽ መንግሥት። ከፍላጎታቸው ጀርባም ይህ አመክንዮ ተጋብቶ መኖሩም ይታሰብበት። „ልብ ያለው ሸብ“
 
የሆነ ሆኖ ለማህበረ ኦነጋውያን አሳፋሪም፤ አዋራጅም የሚባል ነገር የለም። ፈቀድከው // አልፈቀደክው፤ ወደድክም // አልወደድክም ገዳነትን አፍንጫኽን ሰንገን ትወጣታለህ ነው ፍጥጫው እና እርግጫው። ዴሞግራፊ እና ምጽአቱ።

አሁን የማሽላ አጨዳ ላይ የባጀው መንፈስ ጥር 3 ቀን 2012 በሚሊዬነም አዳራሹ ጉባኤ የልቡን ገልጧል። „ከ6 ወር በኋላ መንግሥት እንሆናለን“ ይልኃል ዘንጋዳው ሃሳብ። „ፌድራሉ ካለከተማው ነው የተቀመጠውም“ ይልኃል።

 ሌላው ዝንጥ ያለው መታበይ ይመጣልህ እና ከአዳማ ደግሞ „የፖለቲካ ሥልጣንን እንጥፍጣፊ ሳናስቀር ከስሜን ፖለቲካ ወደ ደቡብ እንወስደዋለን“ ይልኃል። በዚህ ቃሬዛ ላይ ያለው ብአዴን በኮዳ ውሃውን ይዞ ጅም ይሠራል። ለጉዳይ አስፈጻሚነት። በወረፋ በመታበይ፣ ሰረገላ የኦነጋውያን መንፈስ ለሚያደርጉት ደባ የቆሽት ማርጠቢያ። በመዋረድ ላይ ጥማት ታከለበት።

ይህ ዓዋጅ ለተደማሪው፤ ለምርኮኛውም፤ ለድንኳን ሰባሪው ለሁሉም የሚመች፣ የሚስማማ ነጋሪት ይመስላል። ሚዜነቱም ያምርበታል - ለዋንጫችን። ዘመነ አሮሙማ መልቲ ቢታሚን ይለግስና ከቀፈት ደጎስ ያደርጋል። ከህሊና ደግሞ ቀነስ። በተለይ በተለይ „ለአክ ወሬ“ ጠሐፊ ለሊቀ ሊቃውነቱ ለፕ/ አለማርያም ልዩ የዘመን ስጦታ ነው። ሽልማትዬ። ለዚህ ነው እኔ የጸጸቱ ቋያ ከተቻለ እምለው ለመርኽ ሳቹ ሁሉ።

·        ብታ።

በ12.01.2020 የባልደራሱ ስብሰባ እገታ ላይ የተስፋ የምሥራች ጠበቂው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ብስጭትን፤ ቁጭትን፤ እልህን አስተናግዷል። ያለቀሱም ነበሩ፣ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ እኔ እንደ ታዘብኩት። በውነቱ መደናገጥ አያስፈልግም። መደናገጥ ትግልን ያለዛል። 

መበሳጨት አያስፈልግም። አቅምን ይበላል። ኢትዮጵያ በዘመኗ ከ135 አገሮች የመጡ የዓለም ዜጎች በአውሮፕላን አደጋ ህይወታቸው ያለፈው ባልደራስ ለባለ አደራው በተመሰረተበት ዕለት በመጋቢት አንድ ቀን በ2011 ዓ.ም ነበር። ይህን ልብ ብሎ ያዳመጠው የለም። እዮር ሊነግረን የፈለገ ዕውነት ግን ነበረው።

በዚህ ዕለት ቀድሞ ያልታቀደበት ድንገቴ የፉክክር ስብሰባም ቤተ - መንግሥት አሰናድቶ ነበር። ጠሚሩ እንደሚገኙ ተነግሮ፣ ግን በደረሰው አደጋ እሳቸው አልተገኙም ነበር። የሚገርመው የአውሮፕላኑ አደጋ እና ህዝብ የተሰበሰበት ሰዓትም ተቀራራቢ ነበር። 

በባልደራስ አዳራሽ አንድ ህዝባዊ ስብሰባ ነበር ፕሮቶኮል ያልነበረበት - ድንግል፤ በቤተ - መንግሥት ደግሞ ሌላ በፕሮቶከል የተኳለ በኦዳ ሥርዕዎ መንግሥት የተጠራ የሚዲያ እና የፖለቲካ ሊሂቃን ያሰባሰበ ጉባኤ ነበር - ውስጡ የባለቀ። ግርጫማ ሲቃ ሰብዕና ምን እንደሚመሰል ገለጣ የሚካሄድበት። አንድ ደፋር ጋዜጠኛ የግራጫማ ሲቃማ ሰብዕና ባለቤቱን አቶ ጃዋር መሃመድን „አንተ ገላጭ መሆንህን ባውቅ አልመጣም ነበር“ ብሎ ነበር።

ሌላው ልባም ነገር ማህበራዊ ሚዲያው አዲስ የኃይል አሰላለፍ አምጥቷል። ባልደራስ በባለ አደራው ሳለ ደጋፊ የነበሩ አሁን ወደ ፓርቲነት መሸጋገሩን ውጭ አገር ሳለ ደግፈው፤ ነገር ግን ይታገዳል ብለው አስበው የነበር ይመስላል አቅም ሲያጠረቃቅሙ ባጅተው፣ አሁን የጉሮሮ አጥንት ሆኖባቸውል። ሌላ ማስታገሻ ፍልጋ ላይ ናቸው። አሁን በማይረባ አጀንዳ ተጥምደው አያቸዋለሁኝ። ይህም ሌላ ምዕራፍ ነው። ሁሉም የአቅሙን ያህል ሠርቶ በአቅሙ ልክ ተፎካካሮ ይምጣ። 

ወይ ጉድድድድ። ምን አልባት ምርጫው መጨረሻ ላይ ካልተራዘመ። በቀውስ ኢትዮጵያን ንጦ ምርጫ ይራዘምም ከዚህ ሁሉ ጉግስ በኋላ ከች ሊልም ይችላል። አንድ የልብ ስክንት ከሚጠይቅ ደረጃ ላይ ሲደረስ። ለእነ ድንብልብል የሚሳን የለም። ኦነጋውያኑን ለማስደስት ይሆናል የአሁኑ መሰናዶ አልቋል ጨዋታ። ብቻ ብቻ ለሁሉም መሰናዳት ነው። 

ምርጫው ተካሄደም አልተካሄደም በሁለቱም ዘርፍ ህሊና አሰናድቶ መጠበቅ ይገባል። ቁልፉ ጉዳይ ትጥቅ አለመፍታት። ትጥቅ ስል የመንፈስ ትጥቅ ማለቴ ነው። የሞቀውን አለማብረድ፤ ትትርና ወይንም ትጋትን እረፍት አለመስጠት። እምነትን በአቅም እና ለህዝብ ታማኝነት ብቻ ማድረግ። ጸሎትን አለማቋረጥ። 

·        ቤተ - መንግሥቱ ዓይነ ጠባብነት። 

የንጉሦች ንጉሥ የአጤ ሚኒሊክን ቤተ - መንግሥቱን የሚመሩት ነፍሶች ዓይነ ጠባቦች ናቸው። ስስታሞችም። ሁሉ እያላቸው አገር ምድሩ አይባቃን ያሉ የጉድ ቁልቁለቶች። ይሉኝታም ብሎ ያልፈጠረላቸው። ያ የመጋቢት 1/2011ዓ.ም  የቤተ - መንግሥት ስብሰባ የህዝብን መንፈስ አቅል ለመስረቅ ነበር። ግን ባክኖ ቀረ። ቀጥሎ „ጦርነት እንገባለን“ ከጠቅላይ ሚኒስተር ዓዋጅ የሰማነው በዚህው በባልደራስ ጉዳይ ነበር። ብስጫታቸው አይጣል ነበር። ሌላ ሰው ሆነው ያዬንበት አጋጣሚ ነበር። 

እኔ አይኔ ነውን እስክል ድረስ። መሰረቱ ግን አንድ ነው። አቶ እስክንድር ነጋ አማራ ነኝ ስላለ ነውአለን የሚባል ስለ አዲስ አበባ የሚቆረቆር የሲቢክስ ድርጅት ለጥ ባለ አደራሽ ካለምንም እንከን ሲያከሂድ ተከታትዬዋለሁኝ። „የጦርነት አዋጅ“ አልታወጀበትም። ለምን?

የሆነ ሆኖ ጠሚር አብይ አህመድ የአማራን ሥነ - ልቦናዊ አቅም፤ ጠረን ይህን መታገስ አይችሉም። ትእግስታቸው ሙጥጥ የሚለው ስውሩ ቃልኪዳን የሚያፈርስባቸው የአማራ አቅም ተደማጭ ሆኖ ሲመጣ ነው። አሁን ተሰሞኑ ለፕሬዚዳንት ትራንፕ የመለሱትን እሰቡት። ምራቁን የዋጣ፣ የሰከነ መልስ ነበር። ለሚፈሩት እንዲህ ናቸው። ለሚንቁት ደግሞ እንዲያ።

እኔ ያነን የማስተዋል የአገላለጽ ዘዬ ሳደምጥ ይህን አቅማቸውን ጸረ አማራ ተልዕኳቸውን ቀብረው እንደ አገር ልጅነት ቢሰንቁት ምን አለ አልኩኝ። ያላቸው ነገር አለ። ግን እንዳይሰራ የሚያደርጉበት ጊዜ አለ። ይቆልፉታል። „አማራነትን“ አይወዱትም። በኢትዮጵያ ውስጥም እንዲያዩት አይፈልጉትም። ይህ የተደማሪዎቻቸው የመደመር የጋብቻ አኃታዊ ፍልስፍና ነው። የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጠቀራማ የቃል ኪዳን ሰነድ በቤተ-መንግሥት ሙሽት።

በሰጨኝ ለጠቅላይ / ፈጽሞ አያምርም።


ይህም ብቻ አይደለም ቤተ - መንግሥት መጥታችሁ ከተሰበሰባችሁ ትችላላችሁ ሌላ ቦታ ከሆነ ዋስትና አንሰጥምም ነበር። አንድ አገር የሚመራ መንግሥት እርዕሰ መዲናው ላይ ለሚሰበሰብ ህዝባዊ የስብሰባ ዋስትና መስጠት ካልቻለ አገር የለችም ማለትም ነበር። ይህ ሁሉ ራድ ለአንድ ቀንጣ ነፍስ ነው። ብዕር ብቻ ለያዘ። ተፈሪነቱ ግን ከምን ንጥረ ነገር ይሆን ምንጬ? በኽረ ጥያቄ ነው። እጬጌው ዘመን ይመስጥረው እንደ ፈረደበት።

የርዕሰ መዲናን ደህንነት ከአቅሙ በላይ ከሆነ የፌድራሉ መንግሥት ጠቅልሎ ገዳም ግባ።


ጠበንጃ የያዙት፤ ባለ ሜጫዎች፤ ባለ ሳንጃዎች፤ በዬጊዜው „በ24 ሰዓት መንግሥቱን መጣል እንችላለን“ እያሉ የሚፏልሉት ግን ዝንባቸውን እሺ የሚል የለም። እንዲያውም መኮነኑ ከዘንጋዳ አጨደ ወጥተው አዲስ ጦር እያሰለጠኑ እንዳሉ እዬተደመጠ ነው። „ሌለውም አሁንስ ለመገንጠል“ ምን ሲገደን ብሎ ቡራዩ ላይ የደም ትዕይነት ሲያሳይስ? ይህ አይስክሬም ነው ለቤተ- መንግሥቱ። ጡር ቢፈሩ ምን አለ?

 የሰው ልጅ በእግዚአብሄር እጅ እንጂ በሰው እጂ አይደለም። ፈጣሪ ምን ሊያደርግ እንደሚችል አይታወቅም። ማዕት ሊያወርድ ይችላል። ቁጣው ከመጣ ብትንትን ማድረግ ይሳነዋል ተብሎን ይሆን ፈጣሪ? ምን አለ በልክ ቢይዙት መታበያቸውን? ለዛ መከረኛ ለቁቤ ትውልድስ ቢታሰብ ምን አለ።  
የባልደራሱ ባለ አደራ ተጠያቂ በሌለበት ብዙ ስብሰባዎቹ፤ ብዙ ጋዜጣዊ መግለጫዎቹ፤ ሰላማዊ ሰልፉ ተስተጓጉሏል። 

እስርም ነበረበት። ስብሰባውን፤ ጋዜጣዊ መግለጫውን የሚያስተጓጉሉት ቀደም ባለው ጊዜ የቄሮ አባላት ነበሩ። የእነሱ ጉዳይ በተገባው ልክ ለዓለም ሪፖርት ስለተደረገ መንግሥት አሁን እራሱ ገባበት። ለወንጀለኝነቱ ምስክርነት ላለመስጠት። በጥበብ ኮሽ ሳይል። ስለዚህ በፊት የነበረው ህውከት፤ ቀውስ፤ ትርምስ፤ ተስፋ ማሰቆረጥ ታቅዶበት በመንግሥት ደረጃ ይከወን ነበር ማለት ነው። ማህተም! ቀውስ ጠማኝ መንግሥት። ህውከት አመጣ ብሎ መሬት መደብደብ። የሰው ስቃይ እንዴት ወንበር ያጸናል? እም!

ባልደራስ በባህርዳር ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ሊያደርግ የነበረውም ስብሰባ እክል ነበረበት። ያው የሰኔው ግርግር አሁን በባልደራስ ላይ ታቅዶ ከሚከወነው ጋር በአርምሞ ሲፈተሽ መልሱን ማግኜት ይቻላል። ግፍ እንደ ነበር። ሌላው ቀርቶ ወደ አዲስ አበባ የመመለሻ የአውሮፕላን ትኬት ተቆርጦ በአውሮፕላን መመለስ እንዳይችል ታግዷል ባልደራሱ። ይህ ለተደማሪዎች ጌጥ ነው። እንዲያውም የበቀል ማወራራጃም ነው።

የባልደራስ ባልደረባዎች በዬብስ በትራንስፖርት ጉዞ ላይም በፈጣሪ ጥበብ ህይወታቸው ተርፏል። አንድ መላዕክ ሹፌር አንድዬ በጥበቡ ሰጥቷቸው። እግዚአብሄር የሚመሰገነው አውሮፕላኑ ላይ እንዳሉ አንድ ነገር ቢኮን ምንስ ይባል ነበር? ኢታማጆሯን አጥታ ኢትዮጵያ ምን አለች? ምንም።

·        ሲመሰጠር። 

የሰሞናቱ የአማራ ሊሂቃን የመንፈቅ የሙታኑ የህሊና የጸሎት ሥርዓት ነበር። ግርም እያለኝ ታደምኩበት። ምን አለ ባትገባኝ እያልኩኝ። ከጥቂት ቀናት በኋላ የሟቾቹ የዶር አንባቸው መኮነን እናት፤ የአቶ ምግባሩ ከበደ መነኮሳት ወላጆቹ አባታቸውም እናታቸውም በተከተታይ ቀናት አልፈዋል። ነፍስ ይማር። አሜን። በዚህ አጋጣሚ ኢትዮ 360 የሰጠው ውስጣዊ አክብሮት ያስመሰግነዋል። ለቤተሰብ መጽናናትን ተመኝቷል በ13.01.2020 „በዛሬ ምን አለ?“ ማጠቃለያው ላይ። ህዝባዊነት እንዲህ ህሊናዊ ሲሆን የትውልድ መንፈስን ያበራክታል። ግን ይጨርስላቸው።

 ወደ ቀደመው ምልሰት ሲሆን የሟቾቹ ሊሂቃን ወላጆች በተከታታይ ህልፈትን አስመልክቶ ሂደቱን ማጥናት ግን ይጠይቃል። ወለም ዘለም ለሚሉ ነፍሶችም እጬጌው ሂደት ሐዋርያ ሆኖ እያስተማራቸው ነው። በልዝ አቋምም ጽናትን ለሚፈታተኑት የፖለቲካ ተንታኞችም ሆነ ጸሐፍት ልብ ይስጣቸው። የትግሉ ዓይነት፤ የትግሉ ተፈጥሮ፤ የትግሉ ባህሪን በስሱ ሳይሆን በጥሞና መመርመር ያስፈልጋል። ቀጣዩ የማን ንቁ ታታሪ ነፍስ፤ የማንስ ትጉህ ቤተሰብ ላይ ጥቃት ሊኖር እንደሚችል። 

ተከድነው ያለፉም መከራዎች ስላሉ። ትግሉ የትውልድን ጥጋዊ የተስፋ መንፈስ መንቀል ነው። ማፍለስ ነው። አቅምንም ቅስምንም መስበር ነው። ሥነ - ልቦናን እርስት አልባ፤ እርሾ አልቦሽ ማድረግ ነው። ይህን ሰውኛ ሳይሆኑ በመንፈሳዊ ዕሳቤውን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጨካኝ መንፈስ ማነው? ምንድንስ ነው? በምን ሁኔታ መቋቋም ይቻላል ብሎ በማስተዋል ማሰብ፤ ደጋግሞ ማሰብ፤ ተኝቶም ማሰብ ይገባል። መፍትሄው ሳናጃዊ ጦርነት አይደለም። በቃን ጦርነት። ጸሎት አቅም ይፈጥራል። መጸለይ። መጸለይ። መጸለይ። ለክፉ መንፈስ መዳህኒቱ ጸሎት ነው።

በዚህ ውስጥ ባልደራስ ለኢትዮጵያ ሲታሰብ ምን ያህል የገዘፈ ፈተና ላይ እንዳለ፤ ትውልዱ በምን ያህል ውጥረት ውስጥ እንዳለ፤ ኢትዮጵያም ህልውናዋ በምንኛው አስጨናቂ የቀለም ዓይነት ውስጥ እንዳለች ማስተዋል ይቻላል። በተለይ ያልተደመሩ የፖለቲካ ሊሂቃንም በቀጣይነት ያለባቸው ስውር እና ግልጽ የፈተና ዓይነት ማስተዋል ይቻላል። 

ጠንቃቃነትን መጠጣት ያስፈልጋል። መቾኮል አያስፈልግም። በእርጋታ ውስጥ ሆኖ ዘመኑን መፈተሽ ግን በሚገባ ያስፈልጋል። ዛሬ እምናያቸው የዕውነት አርበኞች ነገስ እናያቸው ይሆን? የቤተሰቦቻቸው ደህንነትስ ዋስትናው ከምን ይገኝ ይሆን? በፈጣሪ ስለሚሆነው ሳይሆን ክፉነት ስለ አደመበት የመንጥር ዘመቻ። ምዕራፍ ሦስት ኦፕሬሽንስ ምን ያስከትል ይሆን?!

·        ሪክን በጥንቃቄ ስለመያዝ።  

ባልደራስ ለታሪኩ ቀናይ ሊሆን ይገባል። ከዚህ ጋር አያይዘን የምናዬው ለባልደራስ ለኢትዮጵያ ህዝብ የከፈለው መስዋዕትነት በጥሞና ሊታይ እንደሚገባው ላሳስብ እሻለሁኝ - በአክብሮታዊ ትህትና። ጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም ባልደራስ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ሲጠራ ከዬትኛውም ክልል የባላደራሱን መንፈስ የሚደግፉ መንፈሶች ይመጡ ይሆናል በማለት መንገድ ተዘጋ። ቅጣቱን ተጓዡ ለተከታታይ ቀናት ተቀበለ። በቀል። ካለ መጠለያ፤ ካለ ምግብ። ህጻናት የያዙ፤ ነፍሰጡር ሴቶች፤ አቅመ ደካሞች ሁሉ ተጉላሉ። ይህ ድል ነው ለነውረኛው ኦነጋዊ መንፈስ። 
  
ኗሪውም ደግሞ በሌላ ቤቱ በዚህ ሊሰሙት በሚከብድ የኑሮ ውድነት እዬተገረፈ ግን ወገኖቹን እረዳ፣ ያለውን አካፈለ፤ ነፍስ አውሎ አሳደረ። ኢትዮጵያዊነት ትርጉሙ ጥልቅ ነው። የሚገርመው፤ የሚያሳዝነው ነገር በአማራ ክልል እርዳታ ያደረጉ አስተባባሪ ወጣቶች እንደ በደለኛ ተቆጥረው ሲዋከቡ ነበር። የርህራሄ ስደት።

 የተንገላቱትን፤ መጠጊያ ያጡትንም መርዳት ያስቀጣል በሲዖላዊው የአዳማ ሥርዕዎ መንግሥት። ኢትዮጵያዊነት በምን ያህል ኪሎ ፈተና ላይ እንዳለም እንመርምረው። ይህ ሁሉ በባልደራስ ለኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አብሮ የሚካተት መሰረታዊ አመክንዮ ነው። ታሪክ ዕንቁ ነው።

አቅሙ ጠፍቶ ነው እንጂ በዬፌርማታው የተጉላሉት ወገኖቻችን ሥም ዝርዝር መያዝ ይገባ ነበር። እርግጥ ፎቷቸው በከፊል አለን። ባልደራስ ለኢትዮጵያም የእኔ ታሪክ ብሎ ሊይዘው ይገባል። ቢያንስ እነዛ የተጉላሉ ወገኖች የጠነዘለው ምስላቸውን፤ የድንጋይ ጦርነቱን ውሎ፤ የአውቶብሶችን የእንቅልፍ ሰዓት የለሽታ ዲካ፤ የብትሩን ትዕቢታዊ ትርኢትም ወዘተ …

·        ዲስ አበባ አገር ናት። ደማም! ደመግቡም።

አዲስ አባባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ናት። አዲስ አበባ ደግሞ የአፍሪካ ህብረት ዋና ከተማ ናት። በአዲስ አበባ ብዙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ይገኛሉ። አዲስ አበባ ለዓለም በዲፕሎማሲ ዘረፍ ከኒወርክ፤ ከጄኔባ፤ ከቬይና ቀጥላ የምትገኝ ሉላዊ የውስጥነት ከተማ ናት። አዲስ አበባ የደም ሥር ናት ለዓለም የግንኙነት መስመር። 

አዲስ አበባ ሥልጡን ከተማ ናት። አዲስ አባባ በኢትዮጵያ የሚገኙ ከ80 በላይ የሚሆኑ ብሄረሰቦች በአንድነት የሚኖሩባት አንች ትብሽ አንተ ትብስ ተባብለው፣ ተዋውጠው የሚኖሩበት ብሄር አልቦሽ ከተማ ናት። አዲስ አበባ የአብሮነት ከተማነቷ በመሆን የከበረ ብልጹግ ነው። በተጨማሪም ከዬትኛውም አህጉር የመጡ የዓለም ዜጎችም ወደዋት የሚኖሩባት ከተማ ናት።

አዲስ አበባ የፍቅር ከተማ ናት። አዲስ አበባ ሁሉም አላት። ህብርነቷ ዘመን የሰጣት ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮም የለገሳት አጓጊ እና ሁሉን ቻይ ከተማ ናት። አዲስ አበባ የሁሉም የመኖር ደረጃ ያላቸው የሰው ልጆች እንደ አቅማቸው የሚኖሩባት ከተማ ናት። መንገዷም ዋሻ፣ መጠጊያ ሆኖ ቀን ለተደፋባቸው እናት ሆዱ ነው። ፌርማታዋም የድሆች መንፈስ ማረፊያ ነው። ሁሉን ተቀባይ፤ ሁሉን ታጋሽ አዲስዬ።

አዲስ አበባ ተናፋቂ ከተማም ናት። አዲስ አበባ ሳቢም ከተማ ናት። አዲስ አበባ ሳቂተኛም ከተማ ናት። አዲስ አበባ በእቅፏ ውስጥ ንጥረ ነገር አለባት። ኢትዮጵያዊነት። አዲስ አበባን ሊተረጎም የሚችለው አቅም ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው። አዲስ አበባ ለኢትዮጵያዊነት ባለውለታ ከተማ ናት። መከራዋ የበዛ ነገር ግን በመቻሏ ውስጥ ደግሞ ጥበቡን አትረፍርፎ የሰጣት የእናታዊነት ጸጋ የተሰጣት ከተማ ናት። ርህርህት!

አዲስ አበባ አድዮም ናት። አድዮ አገናኝ ድልድይ ማለት ነው። የብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማችን ቀለማት ቀደምት ሊቀ - ሊቃውንታት እንደ መገናኛ የተጠቀሙበት አድዮ ነው ብዬ እኔ አምናለሁኝ። ለልጆች በፃፍኩት „እንካ ሥላንትያ“ መጽሐፍም የፊት ለፊቱ ሽፋን አድዮ አበባ ነው። በመጸህፌ ውስጥም ላይ እርእስ ሰጥቼ ይህን እምነቴን በአጽህኖት ገልጫለሁኝ። 

አረንጓዴ እና ቀዩ ቀለም የተገናኜበት ቢጫ ቀለም አባቶቻችን ከብሄራዊ አበባ ከአድዮ ሚስጢር ቀድተው ነው ብዬ በጽኑ አምናለሁኝ። አዲስዬም አድዮ ናት ለእኔ። አዲስ አበባ ቢጫውን ቀለም ትወክላለች። ላሂዋ ያመረ መገናኛ! አዲስ አበባ ደማም ደም ግቡም ናት። ዳማ!

በአዲስ አበቤ በማንነቱም ውስጥ ያሉት ንጥረ ነገሮች ልዩ ቅመም አለበት። የተመሰጠረ። አዲስ አበባ ላይ እንግድነት የለም። እኔ ጎንደር ከተማ ተወልጄ ስላደግኩኝ እዛም እንግድነት ስሌለ አዲስ አበባ መኖር ስጀምር ጎንደር ያለሁ እስኪመስለኝ ህሊናዬ፤ መንፈሴ ምችት ብሎት ነው የኖርኩት። አላማጅም ናት አዲስዬ። አዲስ አበባ እሸትነቷ የሰውነት ተፈጥሯዊነት ውህድነት የሰከነባት ስለሆነም ነው።

·        ነፃነት በአዲስ አበባ።

ነገር ግን አዲስ አበባ ነፃነት የላትም። የአዲስ አበባ ህዝብ በተለይ አሁን በከፋ ሁኔታ የመሰብሰብ ነፃነት የለውም። የአዲስ አበባ ህዝብ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት የለውም። የአዲስ አበባ ህዝብ የመናገር ነፃነት የለውም። የአዲስ አበባ ህዝብ የራሱን መሪ ለመምረጥ መብቱን 27 ዓምት ሙሉ ተነፍጓል። ድሬድዋም መሰል ችግር እንዳለበት የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ኤርምያስ ለገሰ በቀደመው ጊዜ በበዛ መመሰጥ ሲናገር እሰማዋለሁኝ። በሁለቱ ከተሞች የነፃነት አያያዝ የተለዬ ተቆርቋሪነት፤ ፍጽምና ያለው የባለቤትነት ውስጥነት አለው።

የሆነ ሆኖ ያልታወቀው፤ ሰው ደፍሮ ማመን ያቀተውም የአዲስ አበባ ህዝብ በኦነግ መታገቱን ነው። ኦነጋውያን የሚያስቡት ኦነግ ኢትዮጵያን ድል አድርጎ እንደ ገባ ነው። ለዚህ ደግሞ ህሊናዊ ሁኔታ በማመቻቸት አቶ ለማ መገርሳ ወሳኙን ሚና ተጫውተዋል። አቅም በማጉረስም ዶር አብይ አህመድ አንጎል ሆነው አገልግለዋል። ስንቅ እና ትጥቅ በመሆን ደመቀወገዱ። ታሪክ እንዲህ ይዛግጣል። ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ሥር። የውርዴት ዝናብ።

ወደ ቀደመው ምልስት ሳደርግ የአዲስ አበባ ህዝብ በችግሩ ለመነጋገር እንደ ኢትዮጵያ አቋጣጠር ለመጀመሪያ ጊዜ መጋቢት 01.2011 በባልደራስ አዳራሽ ተሰበሰበ። ወደ 10000 የሚገመት ህዝብ ለስብሰባው ወጣ። አዳራሹ አልበቃ ብሎ ስብሰባውን ህዝቡ የተከታተለው በውጭ ሆኖ ነበር። ስብሰባው ድንቅ ነበር። የህዝቡ የፈካ ገጽ ተስፋን ያጨ ነበር። ወጣቶች ሲደሰቱ ከማዬት በላይ ምን ሰናይ አለና?

ያን ዕለት ደስ ብሏቸው ነበር ወጣቶች ቀኑን በሰናይ ያሳለፉት። ከኢንጂነር ስመኜው ህልፈት፤ ከአምስቱ ከቡራዩ ጭፍጫፋ፤ ከ5 የአዲስ አበባ ወጣቶች የጅምላ ጭፍጨፋ በኋላ ወጣቶቹ ደመመን ተጭኗቸው ነበር። ይገባልም። ባለቤት አጡ። አይዞህ ባይ አጡ። ደግፈውም መጨፍጨፍ ሆነ። መገለል ሆነ። ኦ! ኢትዮጵያ የተስፋ ቀንሽ ይናፍቀኛል።

የሆነ ሆኖ በገድለኛው በመጋቢት 1/ቀን 2011 ዓ.ም በዚህ ቀን የአዲስ አበባ ህዝብ አንድ ምክር ቤት አቋቋመ። „የባለ አደራ ምክር ቤትም“ መሰረተ። ይህ ምክር ቤት ከተመሰረተ ጀምሮ ብዙ ፈተናን አስተናግዷል። ከላይ መግቢዬ ላይ እንዳነሳሁት ኮሜቴው መሰብሰብ እንዳይችል ታግቷል። ኮሜቴው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳይሰጥ ታግቷል። አመራር አካላትም ታሰረው ነበር። አሁን ተፈተዋል። ቢሆንም እኔ እንደማስበው የቁም እስር ላይ እንደሆኑ ነው አሁንም።

እንደ ገናም ህይወታቸውም ሰፊ ክትትል እንደሚደረግበትም ነው እኔ እማስበው። ይህም በመሆኑ ኢትዮጵያ ላይ ያለመቻል ችግር ተስተውሎ በዲያስፓራ ኮሚቴውን ፈጠረ ባለ አደራው። ብልህነት! መንፈሱን አስፍቶ ልቅናውን አሳዬ። 

የሰብሳቢ ምርጫው የተገባውን ሰው ለተገባው ቦታ ነበር። ውስጥነት ነበረው። የአመራር አቅም መሰጠትም /ጸጋ/ አቅም አያለሁኝ። ይህን ያስተዋልኩት የባልደራስ ባለ አደራው በሆላንድ ባደረገው ጉባኤ ነበር። ላይፍ ላይ ነበር የተከታተልኩት። ከሥርም የተሳብኩበትን ነገር ጽፌያለሁኝ። ባልደራስን ስናነሳ የአቶ ኤርምያስ ለገሰን ቁልፍ ድርሻ መዝለል የተገባ አይሆንም። የታሪካችን ክፈለ አካል ነው።

እራሳችን መጣል፤ አቃለን ማዬት አይገባንም። አቅምን ዕውቅና ስትሰጠው ሌላ ቢቀር ህሊናህ ያመሰግንኃል። በትልቁ ሲታይ ግን ትውልዱ አብነት ማግኘቱ ነው። ዕውቀት ዲካ የለሽ ነው። ብዙም ዘርፍ አለው። ግን ካለቦታው ከሆነ ባትሪ የለሽ ወይንም ቻርጅ አልቦሽ ይሆናል በባትሪ ለሚሰሩ ማናቸውም ኤሌትሮኒክ መሳሪያዎች። በዛ ላይ ጸጋም ሊኖር ይገባል። 

አሁን እኔ ተመክሮዬ ማደራጀት ነው። ፍሬ ያለው ተግባር መሥራት እምችለው በዚኽው ሙያ ነው። ሙያ ብቻ ሳይሆን ጸጋዬም ነው። ይህ ሙያ ለዬትኛውም የኑሮ አይነት ፈተናን አሸንፎ አቅምን በአቅም መጥኖ ስክን ያለ ህይወት ለመኖር ብሌን ነው።
  
·        የችግሩ ከመጠን ማለፍ እንደ አባት አደሩ ሰንበት ቅኔ ዘረፈ።

ቀደም ባለው ጊዜ የአባቶቻችን የስብሰባ ባህል ታወሰኝ። እንደገናም የገበሬ ማህበር አደራጅ በነበርኩበት ጊዜ ሜዳ ላይ ተሰብስበን ስንት ብልህ ተግባር እንከውን እንደ ነበር ትዝ አለኝ። ምልስቱ ከናፍቆቴ ጋር አገናኝን። እንደ አባት አደሩ። እንደ አባት አደሩ ብንሆን ዕድልም ምርቃትም አይሾልክም ነበር። ስንሰበስብ ስናፈስ፤ ያፈሰስነውን ስንለቅም፤ መልሰን ስናፈስ ይኽው አለን እንዳለን።

ወደ ተነሳሁበት ስመለስ፣ የባልደራሱ ባለ አደራ ምክር ቤት በኢትዮጵያ የአዲስ አበባን ህዝብ መሰብሰብ አልተቻለውም። የባልዳራሱ ባለ አደራ ችግሩ ጠና። ይህም በመሆኑ ኮሜቴው በጥቅምት እና በታህሳስ ወር ደጋፊወቹን በሰሜን አሜሪካ እና በአውሮፓ ሰበሰበ። ስብሰባው እጅግ የሚደንቅ በርካታ ኢትዮጵውያንን ያሳተፈ ነበር። እንዲያውም አዲስ ተስፋ ተወለደ ብለው ይሻለኛል። 

በረዶ ውስጥ ነበርን ሁላችንም። ተስብሳቢው ህዝብ ባልደራስ ወደ ፖለቲካ ድርጅት ተለወጦ በቀጣዩ ምርጫ እንዲሳተፍ ወሰነ። ይህ የእኔ ሙሉ እምነት ነበር። አቅም መቋጠሪያ ሊኖረው ይገባል። በስተቀር እንደ ዳንቴል ይተረተራል።

ነገረ ባልደራስ ይመስጠኛል አፈጣጠሩ እና ፈተና አፈታቱ። መስናክሉ እና መፍቻ መንገዱ። ጽናቱ እና ውስጥነቱ። በተለይ አላስፈላጊ መስዋዕትነት ህዝብ እንዳይከፍል ብርቱ ጥንቃቄ ያደርጋል። ኃላፊነት እና ተጠያቂነት ሚዛናቸውን ይጠብቃል። ይህ መቼም መመረቅ ነው። ባልደራስ ለኢትዮጵያ ከሁሉ በላይ ለህልውና ትግል ዘመን ኃላፊነት የሰጠው የአዲስ ምዕራፍ ባለውለታ መሆኑ ነው።

በአውሮፓ እና በስሜን አሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵውያን በወሰኑት መሰረት፤ ቃሉን ጠብቆ የባልደራስ ምክር ቤት በጥር 3 ቀን 2012  {01.12.2020} ስብሰባ በአዲስ አበባ ቅድመ የጉባኤ መሰናዶ ጠራ። ለስብሰባ አዳራሽም ለኢንተር ኮንትኔንታል ሆቴል 90000.00 /ዘጠና ሺህ/ የኢትዮጵያ ብር አስቀድሞ እንደ ከፈለ ሰማን። እራሱ ክፍያው በጣም ውድ ነው።

የባልደራስ ኮሜቴ በጥዋት ሲሄድ ግን የአዳራሹ መግቢያ በሩ ታሽጓል። አዳራሹ ሳይሆን ተስፋ ነው የታሸገው። ራዕይ ነው የታሸገው። ትውልድ ነው የታሸገው። ህልውና ነው የታሸገው። የሆነ ሆኖ ሆቴል አስተዳዳሪዎችን ሲጠይቅ መልሱ ረብ የለሽ ነበር። በኋላ ዘመን ሰጥ ሚዲያ ደግሞ ሌላ ልሳነ ነገር አመጣ። የኦሮሞ ፖለቲካ እንዲህ ነው።

ልባሙ ባልደራስ ተስፋ ሳይቆርጥ መንገድ ላይ ህዝቡን ሰበሰበ። በቁም ሱባኤ አካሄደ። ባልደራስ ለኢትዮጵያ የገኃዱን የደረጀ ሴራ፤ የወፈረ ሸፍጥ እና ዲርቶ በቀል በጥበቡ ጥልቀት አሸነፋቸው። ያፓርቲውን ሥያሜ በህዝብ ድምጽ አስወሰነ። „ባልደራስ ለዕውነተኛ ዴሞክራሲ" አዲሱ ሥሙ ነው። እኔ ግን ከፈቀዱልኝ ውስጤ የሚለኝ ባልደራስ ለኢትዮጵያ ነው። የቁልምጫ ሥም ሳይሆን የናፍቆት ሥም ነው ለእኔ። የብዕር ሥምም አይደለም ለእኔ// ለእኔ ኢትዮጵያዊነት ፈተናን ድል አድርጎ ስለመቀጠሉ የብሥራት ዓዋጅ ነጋሪ ሥም ነው ባልደራስ ለኢትዮጵያ። 

ወደ ቀደመው እንደ አቨው … በመቀጠልም ባልደራስ እዛው መንገድ ላይ ሆኖ በቁሙ ሱባኤ ላይ ሆኖ የፓርቲውን መሪ መረጠ። የአዲሱ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ መሪ ጋዜጠኛ፤ የሰብዕዊ መብት ተሟጋች፤ የዴሞክራሲ ታጋይ አቶ እስክንድር ነጋን መሪው አድርጎ በሙሉ ድምጽ መርጧል። ባዬነው ልክ የድምጽ ልዩነት አልነበረም። አሁን የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ሊቀመንበር አቶ እስክንድር ነጋ ነው። /እርስዎ/ ለማለት ከበደኝ። አንተ በማለቴ ቅር እንዳትሰኙ።

በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ዋና ከተማ በአዲስ አባባ ከተማ መንገድ ላይ ነፃነቱን በማን አለብኝነት የተነጠቀ ህዝብ ተሰብስቦ ፓርቲ መሰረተ።  የዓለም ሰላም አባት በኖቤል ተሸላሚው ጠሚር አብይ አህመድ በሚመሩት አገር። ኖቤል ደህና ሰንብትችሎቱንም ይስጥህ። ለነገሩ ተቀናቃኙም ጠንቶበታል። ኮፒራይቱ ፈንዳድቷል። በዚህ ማህል ሉዕላዊነት?!

የባልደራስ ለኢትዮጵያ ስበሰባው ሲካሄድ አንዲትም መቀመጫ ወንበር የለም። ጠረጴዛም የለም፤ ስብሰባው በሱባኤ በቁም ይሆን ዘንድ ፈጣሪ አላህ ፈቀደ። የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ይህን ይመስላል። ዓለማችን አዲስ ምዕራፍን አስተናገደች።

ለባልደራስ ለኢትዮጵያ ግን እንደ ቀደመው እንደ አባት አደሩ ሜዳ ላይ ጉባኤውም ማድረጉ ምን አልባት /// ምን አልባት ያን የቀደመ ጥበብ አምጠህ ውለደው ልቅናህን፤ ልዕልናህን ከፈለግክ ይመስላል የእዮር መልዕክት ለባልደራስ ለኢትዮጵያ የላከለት። ያው ጥሞና፤ የሱባኤ ጊዜ ያስፈልገዋል ይህን መሰል ስጦታዊ አጋጣሚ። ለዚህ ነው እኔ በቀደመው ጹሑፌ የጥሞና ጊዜ ያስፈልጋችኋልን አበክሬ የገለጽኩት። ምልክቱ ይህን እንደል ስለሚጫነኝ። 
  
·        ሚስጢር።

ብዙ ሰው በሰውኛ አዳራሽ መከልከሉን ነው ያዬነው። ሁልጊዜ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ፈቃደ እግዚአብሄር ይረሳል። እኔ እማስበው ግን ፈቃደ እግዚአብሄር የራሱን ታምር እና ገድል መስራቱን ነው። እኔ እንደ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓአ.ም ታማራታዊ ቀን አድርጌ አዬዋለሁኝ ጥር 3 ቀን 2012 ዓ.ም። ስብሰባ ተከለከለ። ስብሰባው እንደ አባት አደሩ በምልሰት እንዲሆን ሰንበት እራሱ በወግ በማዕረጉ፤ በልኩ ቅኔውን ዘረፈለት። መታደል ነው! 

እኔ በአውንታዊ እና በቅንነት ነው ያዬሁት። ቅንጣት ብስጭት አልመጣብኝም። ባልደራስ ለኢትዮጵያ አትርፎበታል። ሪፖርቱ እራሱ ፈጥኖ ነው የደረሰን እያዬን፤ አዳራሹ ተሳክቶ ቢሆን ስናምጥ እንውል ነበር። ሊፈጠር የሚችለውንም አናውቅም። አዳራሹ ውስጥ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማን ያውቃል? ፈጣሪ ሊያንድንህ ሲፈልግ ምክንያት ይፈጥራል። 

አንድ የኢትዮጵያ ጦር ኢታማጆር ሹም የአገር ሃብት በቤታቸው ውስጥ ነው ህልፈታቸውን የሰማነው። የት ላይ እንዳለን እንወቅ - እባካችሁን? ? የእውነት መታደል ነው በሰላም መመስረቱ። ብትፈቅደው የማታገኜው ብጡል አጋጣሚ። ልዩ ህብራዊ አቅም ፈጠረ። ልዩ ማህሌታዊ ቀለም አደራጀ። ልዩ ቅናዊ መንፈስ አመረተ፤ ልዩ ቃና ያለው ጣዕማዊ ምስረታን አበሰረ። ዕንቁ ለዛ ያለው ታሪክ አስመዘገበ ባልደራስ ለኢትዮጵያ። የትውልድ የመሆን አቅም እንዲኖረው ነው ምኞቴ። ምኞቴ ይሳካ ይሆን? ፈቃዱ ከሆነ ለምን አይሳካም።

በ21ኛው ምዕተ ዓመት በኢትዮጵያ ዋና ከተማ፤ በአፍሪካ ህብረት ዋና ከተማ፤ በሉላዊቷ የዲፕሎማሲ ከተማ፤ በሉሲ እርእስ መዲና አዲስ አበባ ላይ መሰብሰቢያ አዳራሽ ታግዶ መንገድ ላይ ባልደራስ ለኢትዮጵያ „ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክርሲ ፓርቲ“ ተወለደ።  

በዚህ ውስጥ ፈተናውን እዩት። ፈተናው የሚሰጠወን ኃይል ደግሞ አስተውሉት። በማስተዋል ውስጥ ያለው ጽናት ደግሞ ሐዋርያነቱን ለትውልድ ስንቅና ትጥቅ ስለማቀበሉ መርምሩት። ድንቅ ቀን። ውብ ቀን። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከሸፍጥ፤ ከሴራ የዳነ ዕውነት የተጠራበት ቀን፤ ጽናት ልቅና ያገኜበት ዕለት፤ ለህዝብ መታመን ብቃቱ የአደባባይ የሁሉም ሃብት ሆኖ እኛዊነትን አበክሮ ከበረ - ሰበለ በጥበቡ - ለቅኖች።

በዛ ቅጽፈት ውስኔውን በጥልቀት ታደሙበት፤ የሚልክላችሁ የምሥራች አለ። መሬት አስተናግዳው እማታውቅ ዜና። ማን አቀበለው ይህን ውሳኔ? ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ስለመሆኑ ነው ፍሬ ነገሩ። ዕንቁነት - እኛዊነት - ቅኔያዊነት - ከራስነገር ጋር አብረው ተዋህዱ። እንደራሴነት በውስጥነት አብረው ተፈጠሩ።

እንዴት ኃሳቡ ፈለቀ ብትሉ እራሱ አቶ እስክንድር ነጋም አያውቀውም። ሁላችንም ይከለክሉታል ብለን አላሳብነውም ነበር። እኔ በግሌ በፍጹም አላሰብኩም። ቢከለከልም እንዲህ መንገድ ላይ አዲሱ ፓርቲ ይፈጠራል ብዬም አላስብም። እግዚአብሄር እንዲህ ነው ሥራውን የሚሠራው። ለዚህ ነው እኔ የፈጣሪ ፈቃድ አለበት የምለው። እኔ ስላልኩ ሳይሆን እራሱ ሂደቱ የሚጽፍልን ይኸው ነው። ማንበብ ከቻልን። ግን ንባብ የመጸሐፍ ብቻ ሳይሆን ሂደትን የማንበብ አቅምን ይጠይቃል። እንስከን!

የውሳኔው ጻዲቅነት ባልደራስ ለኢትዮጵያ እንድለው አስችሎኛል። ሌላ ቢሆን ያው አለቃቅሶ፤ ድንኳን ጥሎ የውግዘት ናዳ እዬለቀቀ ሰራዊቱን አሰልፎ ወጀብን እያዘዘ ህወከትን ያውጃል። በቀል ቋጥሮም አድብቶ አጋጣሚ ሲቀናው ባህርዳር ላይ እንዳዬነው ጥቃት ይፈጽማል - ያስፈጽማል። ኢትዮጵያን ጽላቱ ያደረገ መንፈስ ግን በጥበቡ ልክ፣ በዓላማው ህሊና ውስጥ ብልህነት በቅሎ እንሆ ሆነ። በቀጥታ በማግሥቱ ሥራውን ቀጠል። አስተሮዮን አሳመረ። ሥያሜው ተሰዬመ። ንቅናቄ ሳይሆን ፓርቲ ሆነ። ይህ በራሱ ትልቅ ውሳኔ ነው። ፈል እና ችግኝ አንድ አይደለምናያለቀለት ሥራ ቀጠሮን አሻም ያለ ውሳኔ። ብርቱ ሲበራታ ያበረታ - ለአብረንታት።

የሚገርመው መላው የባላደራስ መንፈስን ያሰጠጋው ሁሉ በአደባባይ ላይ ካለቀጠሮ በክፍት ስብሰባ ታደመበት እንደ አባት አደሩ። ደስ አይልም?! የውነት ልዩ ምዕራፍ ነው። ሊወደደ፤ ሊናፈቅ፤ እንክብካቤ ሊደረግለት የሚገባ የልቅና ልዕልና ክስተት። 

ባለፈው ጹሑፌ „የባልደራሱ ባለ አደራ የፖለቲካ ፓርቲ ምስረታ ጥንቃቄ ስለማስፈለጉ“ በሚለው ጹሑፌ የባልደራሱ ባለ አደራ ክስተት ነው ብዬ ነበር። በሌላም በኩል ኢትዮጵያ ከቀስት ትድን ዘንድ ሽልማት ነው ብዬም ነበር፤ እንደ ኢትዮጵያዊነት ተፈጥሯዊነትን አይበታለሁም ብዬ ነበር። የሆነውም እንዲሁ ነው። 

መንገድ ላይ ጉባኤ፤ መንገድ ላይ የፓርቲ ሥያሜ፤ መንገድ ላይ የመሪ ምርጫ። መንገድ ላይ የፓርቲ ምስረታ። የእስራኤላውያን ታሪክ መታደሙ አይከፋም። ልዑል እግዚአብሄር በጉዞዋቸው ሁሉ እዬተከተለ እንዴት ይመራቸው እንደ ነበር፤ ፈተና እና ጽናት እርስ በእርሳቸው እንድምንስ ይፈራረቁ እንደነበር በአስተውሎት ይመርመር። ለጠሚር አብይ አህመድም ፈጣሪ ጊዜ እዬሰጣቸው ይመስለኛል እንዲማሩበት። በመማር መዳንም ማዳንም አለና። እንደ ፈርኦን ልበ ደንዳነነት መልካም አይመስለኝም። ከከፍታ ዝቅታ፤ ከማን አለብኝነት ትህትናን ማስቀደሙ ይበጃል። ይመስለኛል።  ለእኔ ባልደራስ አናባቢም ተነባቢ ነው። ልክ እንደ ኢትዮጵያዊነት። ኢትዮጵያዊነት አናባቢም ተነባቢም ነው። 

·        በማሸነፍ ውስጥ ያለ ጥሪት።

እስከ አሁን ባዬነው የባልደራስ ለኢትዮጵያ ማንኛውም እቅድ ተስተጓጉሎ ግጭትን ይመኙለታል። በባልደራስ የትህትና ልስላሴ መጠን ይመከተዋል። ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዶ በህይወት ተጠያቂ ለማድረግ ይወሰናል። በባልደራሱ ልዩ የታጋሽነት አቅም መክኖ ይቀራል።

የስብሰባው ተልዕኮ ጠንዝሎ፤ ጠውልጎ እንዲቀር ያቅዱለታል፤ ነገር ግን በበራ ህሊና ስብሰባውን ባልተጠበቀ ሁኔታ መንገድ ላይ አካሄዱ መርሃ ግብሩን ይፈጽማል። አስከ ስሜን አሜሪካ ድረስ አቅም ለመከፋፈል፤ መንፈስን ለመስረቅ የተለያዬ ቡድን ተሰማርቷል። ነገር ግን „የሰው ልብ መንገድን ያዘጋጃል፤ እግዚአብሄር ግን አካሄዱን ያቃናለታል“ የሚለው ቃል ይፈጸምለት ዘንድ በወጀብ ውስጥ ሁሉ ስኬትን ይመገባል። ጥንካሬን ይቀለባል። አሁን በታዬው የመወሰን ጉልበታም አቅሙ፤ ከጥበብ ጋር ያዋህደበት መንገዱ የልቅና ልዕልና ክስተት ይባዘበት ይሆን?!

በአንጻሩ ባዬናቸው ሰከን ያሉ ጉዞዎች ተቃናቃኙ መንፈስ እና በመጋረጃው ያሉ እነ ባለ ፍሪንባ ተደማሪያን ጨምሮ ሽንፈትን ሳይወዱ በግድ ይጎነጫሉ። ውርዴትንም እስኪበቃቸው ያወራርዳሉ። ጽናት ለሚጎለንም ቁጭ አድርጎ ተቋም ከፍቶ ያስተምረናል። ብልጽግና ማለት ኢህዴግ በቤሎ ማለት ነው። ለዛውም ኦነጋዊ መንፈስ የሰፈነበት።

·        ኢትዮጵያዊው ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ።

„የፊት የፊቱን“ ይላል ጓያ ነቃይ። ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ለመመዝግብ ከበቂ በላይ ነው ብሎለታል። የባልደራስ ለኢትዮጵያን ቅዱስ መንፈሱን ተቀብሎታል - መዝግቦታል። ለዚህ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሳያጉላላው ምዝገባውን ስለተቀበለው ማመስገን ይገባል። ነገ ለራሱ ይጨነቅ። ዛሬ ባለው ሁኔታ ግን ባልደራስ ክፉ ተቀናቃኝ መንፈሶችን ሁሉ ምርኮኛ አድርጓቸዋል። ድንጋጤ ኮማ ውስጥ ያሉም ይመስለኛል።

ወደፊትም በትህትናው ልክ፤ በመቻል አድማሱ ስፋት ልክ፤ በታማኝነቱ ድንግልና ልክ፤ በአመራር ብቃቱ እና ጥራቱ ልክ ከሁሉም በላይ በፈጣሪ በአላህ እርዳታ እና እገዛ ጥንካሬውን ይቀጥላል ብዬ አስባለሁኝ። እንዲህ የምንመሰጥበት ነፍሶች የታሪኩ አንባቢ መሆን ያስችልን ብቃቱ ነው። ሚሰጢር የመተርጎን አቅሙ ነው። 

የውሳኔ አሰጣጡ ቀርጠኝነት ክህሎት ነው። አበክሬ ልገልጽ የምሻው ትልቅ ጆሮ እንዲኖረው ነው። አድማጭነት አትራፊ መንገድ ነው። አድማጭ ይሁን። ይከፋል ተብሎ የሚነገረውን ከማንም ከዬትኛውም ወገን ይሆን ይታደምበት፤ ይመርምረው። አቅምን የወል ያድርገው። 

·        ንባብ።

በዚህ የባልደራስ ለኢትዮጵያ የመፈጠር፤ የማደግ፤ የመጎልመስ ጉዞ ውስጥ ፈጣሪ እንዳለበት እኔ በጽኑ አምናለሁ። ከተለመደው ውጪ ስለሆነ እኔ በግሌ ፓርቲ ተመሰረተ ሲባል ብዙም አይገጠግጠኝም። እንኳን ነጋ ጠባ ልጽፍበት ቀርቶ አድንቄ ከሌላ ጹሑፍ ጋር አዳብዬ እንኳን አላቀርብም። በአዲስ ፓርቲ እና በሚጣማሩት ላይ በጣም ቁጥብ ነኝ። ጋብቻው ሰሞነኛ ስለሚሆን አቅም ማፍሰስ አልሻም። ብክነት አይናፍቀኝም። ቅንነትን በልክ አድርጎ ማስተዳደር ይገባል።

አሁን ደግሞ ተቀጥተንበታል። አንዲት የጎንደር እናት አንድ ሊሂቅ ለማውጣት ህልም ነው። ተፈጥሮ የሰጠው የትውልድ ማጭድ አቀማመጡ ሁላችን ተገብረንበት ባክነን ነው የቀረነው። ሁሉም እዛ ሄዶ ይመሽጋል። አንድ ቀን በሰላም ሳንማር የትምህርት ክ/ ጊዜው ያበቃል። 

በስንት ጣር ወጡ የተባሉትም በመደዳ ነው የታጨዱት። እነሱ ብቻ ሳይሆን በቤተሰቦቻችን የሚደርሰው መከራስ?! በሌሉበት፤ ባልነበሩት? እናት ስለምን የበቀል ማወራረጃ ትሆናለች?! ለምን?! ሻማ አብርተው ስለጸለዩ ለአብይዝም? ስለዚህ አደብ ያስፈልጋል። አቅምህን ሊባለ ላሰፈሰፈ ዋጮ ነበር አቅም የተሆነው። ቅንነት አሳረደን። ቅንነት ቅጣት ነው የሆነው። ከትናንት መማር ይገባል። 

ወደ ቀደመው ባልደራስ ለኢትዮጵያ ስመጣ ክንውኑ፤ ትትርናው፤ ሰውኛ መንፈሱ ንባብ ነው። የሚነበብ። ከጨረሰለት። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጠላፊው ብዙ ነው። የሆነ ሆኖ የባልደራስ ለኢትዮጵያ የበለጠ እዬሳበኝ የመጣው መሰናክል ሩጫው እና ዋንጫው ነው። ስንት ለስንት እዬመራ ይመስላችኋል? 
6 ላባዶ። ወይንም 6 ለምንም!

በዚህ ውስጥ በውጭ አገር ያሉት ሚዲያ አዲስ ድምጽ፣ አስራት፤ ኢትዮ 360፤ በመደበኛ ርዕዮት ሚዲያ ሰፊ ድርሻውቸውን ተወጥተዋል። እውነት ለመናገር ሰንበት ላይ በተፈጠረው ክስተት ልትበሳጩም ልታዝኑም አይገባችሁም። ይህን እናይ ዘንድ ፈጣሪ ፈቀደ። ይህም አለ ለካ ማለት ይገባል። ይህም ለመልካም ነው ብሎ በልበ ንጽህና መቀበል ይገባል። 

ሁልጊዜ ነገሮችን አምርሮ፤ አክሮ አሳክሮ መመልከት አይገባም። ለዘብ፤ ለስለስ አድርጎ ማዬት ጥሩ ነው። ለጤናም ጥሩ ነው። ለትውልዱም አንድ የምርምር መስክ ይሆናል። ታላላቆቻቸው እንዴት ችግርን እንደሚፈቱ ይማሩበታል። በዚህ ሂደት ወጣቶች ብዙ ትምህርት እንዳገኙበት አስባለሁኝ። ከተለመደው ውጪ የተገኜ ስኬት ነውና። አዳራሽ ሲዘጋ ሜዳ ላይ ዕቅዱን ሙሉ ለሙሉ ማሳካት። ትንግርት! አልነጠፈም ጥበብ ከባዕቱ አለ። አንገተ ደፋታ ሆኖ ደንግሎም።

በሌላ በኩል የትናጋ ውሎም ምን ያህል እንደ ወረደ ማሰብ ይገባል። ዋጋ አልባ ነው የሆነው። መናገር ባባዶ ቤት ማን አድማጭ አለው? እሰከ አሁን ለ18 ወራት የተሰማው የወግ ገባታ ውሎ በልቦና ሳያድር ትነት - ብንት - ምነና ገጠመው። የሽንፈት ዓይነት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያዊነት ዓይነትም ገኃድ ሆነ። ይህ የታበዬውን መንፈስ እዬናደ ዕውነት ወደ አለበት የሚሰባሰበው ያልባለቀ መንፈስ በራሱ ጊዜ ፕሮፖጋንዲስት አያስፈልገውም። ዕውነት እራሱ ይጠራዋል። መርኽ እራሱ ይሰበሰበዋል ድንግል መንፈሱን።

ከሁሉም የመንግሥስት ሚዲያ እና ሥርዓተ ቀብሩን ደግሞ አዬን። ይህስ ደስ አይልም? ኢትዮጵያ በኃብቷ የሚተዳደር የእኔ የምትለው ልሳን መቼ ሊኖራት እንደሚችልም በዛው ልክ ልብ ላላቸው የቤት ሥራ ተሰጥቷቸዋል። ለነገሩ የመንግሥትን ጋዜጠኞች „ቅልብ ጋዜጠኞች“ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ በአንድ ወቅት በአደባባይ ዘልፈዋቸዋል። መቼም አፋቸው ሞገድ አልሰራለትም።

የሚገርመው ከሰሞናቱ ከኢትዮ 360 የ11.01.2020 በዘመነ ኢህዴግ በሚዲያ አስተዳደር ጉዳይ ሲወያዩ እንደ አዳመጥኩት ደግሞ ጋዜጠኛ አቶ በቃሉ አላምረው የሚባል „የአውሎ ሚዲያ“ ዋና አዘጋጅ ወደ ጠሚር ፕሬስ ሰክሬታርያት ቢሮ ተጠርቶ „እንገድላለን“ መባሉን ሰምቻለሁኝ። ያውም በገዳ ንጉሡ ጥላሁን አንደበት ነው። ኦ አምላኬ! የባህርዳር የደም አላባ ቀጣይነት ያስፈራል። ይህም አለ … ሦስትኛ ጋዜጠኛ መሆኑ ነው አቶ በቃሉ አላምረው። ጋዜጠኛ ተመስገን ደስአለኝ፤ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ነበሩ ተዚህ ቀደም።

አሁን ሦስተኛ ሰኔል እና ቹቻ የታጨለት ደግሞ ነፍስ ታክሏል በይሙት በቃ ፍርደኝነት። እንግዲህ በዚህ ስሌት የአማራ ሊሂቃን መሰዋትንም በማስተዋል መመርምር ነው። ሞት እንዴት እንደ ረከሰ። የሰው ልጅ ዋጋው እንዴት እንደ ቀነሰ። 

እግዚኦ! ነው ደም ከአላዬ የማይነጋለት ሲኦል የኦሮሙማ መንፈስ። አቤቱ አባታችን አምላካችን ሆይ! እንደ ቸርነትህ ብዛት እባክህን አስታግስልን ይሁን ጸሎታችን። እስከ ዛሬ ያዬነው፤ የሰማነው ይበቃል። እባክህን አማኑኤል የሃዘን ዳርቻም አድርግልን። ተለመነን ጌታ ሆይ! እባክህን? ያስፈራል። ይጨንቃልም። ዘመኑ ከጨለማ በላይ ይጨልማል።

·        ማከ

ለባልደራስ ለኢትዮጵያ ሊቀ - ትጉኃን ሆነ ለደጋፊዎቹ የማሳስበው አሁን የፊርማ የማሰባሰብ ምዝገባ ላይ ናቸው ያሉት። ሰንበት ጨምረው ቢሰሩ መልካም ነው። ግን ምንግዜም ማስተዋል ያለባቸው ማምሸት እንደ ሌለባቸው ነው። አምሽተው መሥራት ካለባቸው ሳያውጁ ከአንዳቸው ቤት ሆነው ይሥሩ። ቁጥብነት። ነገር ግን ከሥራ በኋላ፤ ሲመሽ ወደ ቤት እንሄዳለን አይበሉ። እዛው አብረው ይደሩ። እርስ በእርሳቸው ይጠባበቁ።


ይህን ሃሳብ ፌስ ቡክ ሳነሳ „መፈራት የለባቸውም፤ በአፍሪካ ህብረት ከተማ ምንም አይሆኑም“ የሚል አሰተያዬት ይሰጡኛል። ጀብደኝነት ለሰማይም ለምድርም አይበጅም። „ልክን ማወቅ ከልክ“ ያደርሳል የሚሉት ጎንደሮችም ለዚህ ነው። ምን ግብግብ ያሰገጥማል። ለመሆኑ የአንድ አገር ብሄራዊ ኢታማጆር ሹም እንደዛ የውሻ ሞት የሞተው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ሳትሆን ቀርታ ይሆን? ለመሆኑ ኢትዮጵያ የደህንነት ቢሮ አለኝስ ብላ ደፍራ ልትናገረው ይሆን? የኢንባሲ ጠበቂዎችም ሞቱ ሰምተናል እኮ።  

ወይንስ የውኃ ፖለቲካ ጭንቅላት መስቀል አደባባይ ላይ ሞቶ የተገኜውስ ነፍስ ከቶ ምን ሊባል ይሆን?  5 የአዲስ አባባ ወጣቶች አደባባይ ላይ የተረሸኑትስ ኢትዮጵያ የአፍሪካ እርእሰ መዲና ተሰርዞ ይሆን? አንድ ቤተሰቡን የሚረዳ ታዳጊ ወጣት፤ አንዲት ሙሽራ፤ አንድ ከካናዳ የሄደ ኢትዮጵያዊ ነፍስ አዲስ አበባ ላይ አይደለምን ህይወታቸው በጠራራ ጸሐይ የተቀዘፈው? በዚህን ጊዜ አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫነቷ ወደ ኪጋሌ ወይንስ ወደ ዳካር ተዛውሮ ነበርን? ሌላስ ቤተ መንግሥቱ የባልደራሱን ባለ አደራ እኛ ለደህንነታችሁ ዋስትና እንድንሰጣችሁ ከፈለጋችሁ ቤተ - መንግሥት መጥታችሁ ተሰብሰቡ እኮ ነበር። ይህ የክተት ዓዋጅ ነው። ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው ተጥርቶ እኮ "እንገድላችሁ" አለን መባሉንም እያዳምጥን ነው።

ጊዜው ሌላ ነው፤ አዬሩም ሌላ ነው። ሲኦል። ስለዚህ እራስን መጠበቅ ብሄራዊ ግዴታ ነወ። ሁሉም ለራሱ ዘብ ይቁም። ይህ የሚሆነው ደግሞ በልክ መኖር ሲቻል ነው። ጀብደኝነትን መጠዬፍ ሲቻል ብቻ ነው። በጊዜ ወጥቶ በጊዜ መግባት ሲቻል። እራሱ የኃይል አሰላለፉ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሯል። በግንኙነት ዘርፍ ሁሉ መጥኖ መጓዝ፤ መጥኖ ግብዣን መቀበል ያስፈልጋል። „ሁሉ ተፈቅዶልኛል ሁሉ ግን አይጠቅምም“ ቃለ ህይወት ነው።

·        ርገት።

ሰነበት ላይ የገጠመውን ክስተት ከሌላ ባለ ጊዜ መንፈስ ጋርም ማፎካከር አይገባም። ሰንበት ሚሊዬንም አዳራሽ ኦነግ ስብሰባ አካሂዷል። ዛሬም በሙሽራው ኢህዴግ አንድ የሴቶች ስብሰባ እንዳለ እያዬን ነው በዛው በሚሊዬነም አዳራሽ። እኔ እንኳን የካቲት 29 ይጠበቃል ብዬ ነበር። የሆነ ሆኖ የክፋት መንገድ ሰፊ ነው። የቅንነት መንገድ ደግሞ ጠባብ ነው። የጻድቃን መንገድ ጠባብ ነው፤ የኃጥዕ መንገድ ደግሞ ሰፊ ነው። ስለዚህ ጠባቡን መንገድ የመረጡት ስክነትን ምራን ማለት ይገባቸዋል።

በመኖር ውስጥ ሁሉን አጸያፊ ዝባዝንኬ የሚረከቡ ነፍሶች ይሳካላቸዋል፤ ቁጥቦች ደግሞ ከስኬት በታች ሊሆኑ ይችላሉ። ግን ሰብዕናን ሳይሸጡና ሳይለውጡ ከመኖር በላይ ሰውን ሰው የሚያሰኜው አመክንዮ የለም - ለእኔ ለሥርጉተ ሥላሴ።  የህሊና ነቀላ እና ተከላ ተቀብሎ ከሚገኝ ክብር በራስ ውስጥ ሰክኖ የሚገኝ የህሊና ነፃነት ውድ ነው።


የአዲስ አበባ ህዝብ ውስጡን ስለ አገኜ በቦታው እዬተገኜ በመመዝገብ መኖሩን ለማኖር የሚያስችለው በመዳፉ ያለ የገነት መንገድ ብቻ ነው። የባጀበትን ትትን የታቀለደልትን መሞገት የሚችለው በእጁ ባለ አቅሙ ብቻ ነው።

 ለራሱ ነፍስ ፕሮፖጋንዲስት አያስፈልገውም - አዲስ አበቤ። ለራሱ መኖርም ካድሬ አያስፈልገውም - አዲስ አበቤ። ስለዚህ በእጁ ባለው መፍቅድ ዕድሉን ሊጠቀምበት ይገባል። መኖር እንደ ከብት በአሻቦ መላሾ ሳይሆን መኖርን ማኖር በሚችል መርኽዊ ጉዞ ብቻ ነው መኖርን ማገኜት የሚቻለው።

·        ያያዣ።

ተያያዥ ሊንኮች ናቸው። ከፈቀዳችሁላቸው እነሱ ሊፈተሹ ትጥቃቸውን አሳምረው ክብሮቻቸውን ይጠባበቃሉ።

ዛሬ ያለው ነገርፈረቃም፤ ተረኝነትምአይደለም።

አዲስ አበባዬ የልዕልት ሉሲዬ ዬድንቅነሽም ናት!

ውሃም የሜንጫ ቤተኛ ….

https://www.youtube.com/watch?v=cfDOG1eSSrI


ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ነው።
የኔዎቹ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።