እግዚአብሄርን መዳፈር ይቁም። ስትትበሰበሱ፤ ስትዝረከረኩ አቅምን በአቅም ማስተዳደር ተስኗችሁ ከኋላዋ ዬተፈጠሩ አገሮችን እርዳታ ዬምትለምን አገር ተይዞ ፈጣሪን አሻቅቦ መናገር ልክን አለማወቅ ነው።
እግዚአብሄርን መዳፈር ይቁም። ስትትበሰበሱ፤ ስትዝረከረኩ አቅምን በአቅም ማስተዳደር ተስኗችሁ ከኋላዋ
ዬተፈጠሩ አገሮችን እርዳታ ዬምትለምን አገር ተይዞ ፈጣሪን አሻቅቦ መናገር ልክን አለማወቅ ነው።
እያንዳንዱ አመክንዮ፤ እያንዳንዱ ሰብዕና ለተፈጠረበት ሰማያዊ ሚስጢር ህግም፦ ድንጋጌም አለው።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ አቅም የለውም። ኢትዮጵያን ለመምራትም ቅባዓ የለውም። ምክንያቱም ፈጣሪውን ተዳፍሮ ስለሚነሳ። ጥሞና ስለለው። ስለተደረገለት ጥሞና ሦስት ቀን ማድረግ የተሳነው ከአመት በላይ በካቴና ሲያባጀው ያለው ጨካኙ ፖለቲካዊ አመራር አያገናዝበውም። ሚስጢር ተላልፎ ይህ ስለመፈፀሙ። ከእስር ሲለቀቅም ጥሞና የለም። በእስር ወቅት የተፈጠሩ የኃይል አስላለፎች እና ተደሞወች የአረፍተ ነገር ድርድር ይመስለዋል። እዬተንደረደረ ሄዶ ዘው ነው። ይሉኝታ ስለመፈጠሩም ማስተዋል ዬለም።
ዛሬ ሞልቶ በቅጽበት ለሚፈስ፤ ዛሬ ሰክኖ በድንገት ለሚታወክ፤ ዛሬ ተደራጅቶ ለታሪክ ሳይበቃ #በአንጃ ለሚዥጎረጎር፤ ዛሬ ዲል ባለ ድግሥ እና ድጋፍ ጉባኤ ተደምጦ በማግስቱ ሰብሳቢ አልባ ሲበተን ውሎ ለሚያድር የኢትዮጵያ የፖለቲካ አልፎ ተርፎ በፈጣሪ ሥራ፤ በፈጣሪ ጥበብ፤ በፈጣሪ ታምር ገብቶ ማነኮር ጎንደሮች ባለ ቅኔ ናቸው እና "ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳል" ይባላል። ልክ የለሽ ዝልኝጉዞ ነው። ፍሬፈርስኪ።
የሰማይ እና የምድር ንጉሥ፤ የሰማይ እና የምድር ልዑል፤ የሰማይ እና የምድር ጌታ አጋይሥተዓለሙ ሥላሴ በአንድም በሦስትም ሰውን በመልኩ ለፈጠረ አማላክ አልፎ ተርፎ ሥልጣነ ክህሎቱን ሲዳፈር የኢትዮጵያ ፖለቲካ ማት አውርድ ብሎ መሬት ከመደብደብ የሚተናነስ አይሆንም። ፈጽሞ። ከሁሉ በላይ እናት የወለደች አምጣ፤ ተቸግራ ሁሉን ችላ ያሳደገች እናትም አለች። እሷ ባልሰራችው የፈጣሪ ጥበብ ቁሚ ተቀመጪ እንደምን ትባል? ከእነ ሙሉ አካሉ ለተፈጠረውም፤ ለታምር ለገድል ለተፈጠረው የአካል ጉድለትም እናት እናት ናት። እኔም ከሙሉ አካል ካላቸው ይልቅ እማርበት ዘንድ የተራራው ስብከት ተፈጥሯዊ ሲሆን እና ሲቃለል ውስጤን ያቆስለዋል። ጠበቃውም ነኝ። የፖለቲካው አመክንዮ ሲያቅት አሻቅቦ ሚስጢረ ሰማያትን መዳፈር አጉል መቃናጣት ነው። አጓጉል የጓጎለ ጉዞ።
ስታሙረቀርቁት፤ ስታዝለገልጉት፤ ስታዝረከርኩት፤ ስታነኩሩት፤ ስትፈርሱ - ስትሰሩ፤ ጨካኝ ስትከበክቡ #ስትወደሱ፤ ስትሾሙ ስትሸለሙ፤ ዬበዛ እንክብካቤ ሲደረግላችሁ #ትክክል ነን ባዮች፤ ዛሬ ደግሞ የጨመተችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አቅም፤ ልቅና እና ክህሎት ከሁሉም ፈርኃ እግዚብሄር አመራሯ እና ዊዝደሟ ስላስጎመጀ በየአቅጣጫው መጣን መጣን የተለመደ ነው። መጉረፍ። መጎፈርም። አይተናል እኮ መስከረም ሳይጠባ በወረፋ ስትጓጓዙ። የነፃነት ትግሉ የማያውቃቸውም አጥቢያ ነን ብለው አራጊ ፈጣሪ ሆነው ባለ ካባ፤ ባለ ተክሊል ሲኮን።
ይህም ሆኖ የሰው ልጅ በድንገተኛ አደጋ፤ በጦርነት፤ በበሽት፤ በእድሜ መግፋት፦ ፈጣሪ ለገድሉ መገለጫ ለእኛም መፈተኛ ከአካሉ አንዱ ሊጓደል ይችላል። ይህን ለፖለቲካ አቅም ማዋል ህሊና ከቋንጃ ወይንስ ከጀርባ? ወይንስ ከአከርካሪ ያሰኛል?
ምድራዊውን ዕድል፤ ሥልጣኔ የሰጠውን ሥጦታ መጠቀም አቅቶት ሲትበሰበስ፤ ሲለዋወስ፤ #ሲግለበለብ መሽቶ የሚነጋለት የኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ፖለቲከኛ ከፈጣሪ ሥራ እና ዬሰው ልጅ ባላቀደው ሁኔታ በሚፈጠር ዬአካል ጉድለት መሳለቂያ፤ ዬፖለቲካ አቅም መመጣጠኛ ማድረግ የመፈጠራችን ሚስጢር ሳይገባን በዝልኝ መኖራችን ያናብባል። የለለ ሰውነት ሰው ተብሎ የመኖር ያህል ነው ለእኔ የሚሰጠኝ ግብረ ምላሽ። አካል ጉዳተኞች የግሎባል ዜጎች ናቸው። አካል ጉዳተኞ የእኛ እንጂ የሌላ አይደሉም። ለእኛ ሰብእና መመዘኛ፤ መመተሪያ የተሰጡን ሽልማቶቻችን ናቸው።
ትውልድ ህግ ሆኖ እንዲፈጠር "በህግ አምላክ" ከሚለው ይተባኃል መነሳት ይኖርበታል። እያንዳንዱ አመክንዮ ለተፈጠረበት ጥሪ መልዕክት ይሁን ስምሪት ህግ አለው። ደንብ አለው። ድንጋጌ አለው። አንደበት ለመናገር የተፈጠረ ነው። ግን ድንግሉ፤ ሐዋርያው፤ ሊቀ ሊቃውንቱ ፃድቁ አባታችን ቅዱስ ጳውሎስ "ሁሉ ተፈቅዶልኛል፤ ሁሉ ግን አይጠቅምም ይላል።" ለመናገር የተፈጠረው አንደበት በህግ እንዲተዳደር ቅዱስ ቃሉ ለአማንያን ይገልጣል።
ጆሮም አለ። ለማድመጥ። እጅም አለ መኖርን ለማስጠበብ። #ከድርሻቸው #ሲወጡ፤ #ጥሪያቸውን #ሲተላለፋ #መፈጠራቸው #አለመፈጠር #ይሆናል። እኔ ክፋ ነገር ማድመጥን ለማስቆም ስምንት ዓመት ሆነኝ ስልክ መደወልም፤ መቀበልም ካቆምኩኝ። ጓደኞቼ የራሳቸውን የእጅ ስልክ የሰጡኝ ጊዜ ነበር። ገዝተው የሰጡኝ ቁጥሩን ሳላውቀው ቨርዥኑ ተቀይሯል። እናም ከስልክ ጋር የነበረኝን ማናቸውም ግንኙነት ወሰንኩ ተገላገልኩኝ። አሁንም ይህ ገኖ በሚደመጥባቸው ቤተ - ንግግሮች አልታደመም። ጆሮዬ ለክፋ ነገር ካንፓኒ ስቶርነት፤ ወይንም ማቋቸነት አልተፈጠረም።
ቀድሞ ነገር በብስጭት ለሚወራከቡ ወይንም ለሚወራጩ ሰብዕናወች የሰከንድ ዕድል አልሰጥም። ፕሮፖጋንዳ እራሱ የምትማሩት የሚመራበት ህግ አለው። ያው የፖለቲካ አንዱ ቱል ስለሆነ። እሱ እንኳን ከግልምጫ እና ከእርግጫ ጋር ሲወራከብ ነው የሚታዬው። ለነገሩ እንኳንስ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ለሻብያም ፖለቲካ እኔ ፕሮፖጋንዲስት ስለማልሻ ስኩን ፕሮፖጋንዲስቱን አላዳምጥም እንኳንስ እንጡሩብ የሚዘለውን። ጋላቢውን።
የኢትዮጵያ ዕንባ፤ የግፋዓን ጥግ ማጣት፤ የትውልድ ዕድሜ መዘረፍ እኔንም ይጨምራል ይህ ስለሚመለከተኝ ተገድጄ እማዳምጣቸው ሁነቶች ገዢ ነኝ ካለው ከማህበረ ኦነግወኦዳ ከሌንጮወዲማ፤ ከዳውድወቀጀላ፤ ከአብይወሽመልስ ጨለማ ዶክተሪን በስተቀር ሌሎች ቅጥልጥሎችን አላዳምጥም። እነሱንም በፋክት፤ በመርህ፤ በተፈጥሯዊነት በኢትዮጵያዊነት ዝልቅ ልዕልና እና ልቅና አንፃር መዝኜ መሞገት ስለሚገባኝ። ፎቶም ስለጥፍ ውስጡ የተነበበ፤ ውስጡ በስክነት የተስተዋለ ነው።
በዚህ መሃል ስሳሳት ፀጋ ነው። የሰው መሆኔ ትርጉም መገለጫ። እርማት ሲመጣም ዲቃላ ፍላጎት ካላንጠለጠለ በአክብሮት ተቀብዬ አርማለሁኝ። ካልሆነም በትህትና ሞግቼ አሳምናለሁ። ዘመናዮች አሉ ፊደል ሲለቅሙ ውለው የሚያድሩ፤ ወይንም በራሳቸው ብራና መድፈር ያቃታቸውን እኔ እንድጽፍላቸው የሚሹ። እኔ ለቀለጤ ፖለቲከኛ ባዕት የለኝም። አፌን ሞልቶ የሚያናግር የደከምኩበት ህይወት ስለሆነ በልበ ሙሉነት እሰራለሁኝ።
ሌላው ቀርቶ ህወሃት በትረ ሥልጣኑን ከለቀቀባት ከመጋቢት 24/2010 ጀምሮ አንድም ቀን በህወሃት ፖለቲካ ላይ #የቸከ እና #የመነቸካ #እኚኚ ጋር ብዕሬም ብራናዬም #ልፋ #በል ሲል አልተገኘም። ብዕሬ ያ ሁሉ የፖለቲካ ድርጅት እና ተቋም እያለ ህወሃትን መቅኖ ያሳጣበት ሰላማዊ ሙግት በቂ ነው። የተገኘውን የሰማዬ ሰማያት ዱብ ዕዳ ዕድል መምራት የተሳነው #የደመቀወገዱ መና፤ አልቦሽ፤ እሬሳ መንፈስ ለደፋው እድል ህወሃት ተጠያቂ ሊሆን አይገባም። ሥልጣን ፈቅዶ ድምጽ ሰጥቶ ከማስረከብ በላይ ህወሃት ምን ያድርግላችሁ???
ለዚህ ነው እኔ ጦርነት አያስፈልግም ከማለት ጀምሮ የግራ ቀኝ ጉዳቱን ከመዘገብ ውጪ በምንም መልኩ አቅም እማላዋጣው። የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ የድካም መንፈስ ሙት መሬት ላይ ሆኖ ፍርፋሪ ለማኝ ያስደረገው ሁሉም ነው። ለኦነግወኦዳ ሥርዕወ የምርጫ ዕውቅና ማን ያልተሳተፈ? ማን ያልተጋ ሚዲያ ነበር? ሚኒሊክ ቴሌቪዥን እራሱ የተፈጠረው ለዛ ነበር። ማን ሌት ተቀን ያልባተለ አለ? ይነገረን? ሁሉም #ጭካኔን ያፀደቀ ነው። ወቀሳውን ወደ እራስ መውሰድ ይገባል።
እኔ እማውቀው ሚዲያ ሽፋን ያልሰጠ ርዕዮት ሚዲያ ብቻ ነበር። የኦነግ ምርጫ አጀንዳው ፈጽሞ አልነበረም። የእኔም ግራ ቀኙ ሚዲያዬ የፀጋ ራዲዮን ጨምሮ ዬከበቡሽ ልሳንወርቅ ሚዲያም፦ ፌስቡኬም ከእቁብ አልቆጠርነውም። ኦነግ ህጋዊ ዕውቅና ያግኝልኝ ብዬ መታከት እናቴ በአራስ ቤቷ አላበደችም። መላ ኢትዮጵያ ነዳ በጭካኔ ውጥረት ነው ምርጫው ዬተሳካው። በሞቴ ንገሥልኝ በእኔ ቤት አይታሰብም????? አማካሪው ሊቃናት ሁሉ በአቶ ኤርምያስ ለገሰ አዝማችነት ተሰልፎ ነበር። ጠብ ያለ አልተገኘም። ከቅኔው ጎጃም በስተቀር።
"ከንቱ የከንቱ ከንቱ፤ ሁሉም ነገር ከንቱ።"
ምርጫ እርግጫ።
ምርጫ ልግጫ።
ምርጫ #የሽብር ማምረቻ ማሽን ስለነበር አዕምሯችን ያላባከን ሰወች አለን። አቅም ቆራጣ ያላቀመስን አለን። ያላረገረግን፥ ያላሸበሸብን ሰወች አለን። እና በራስ አርቆ አለማሰብ ለመጣው ድቀት ፈጣሪ እንደምን ተወቃሽ ይሆናል???? ጥያቄው ይህ ነው።
ይህም ሆኖ ባለቤት ያጡ አመክንዮወች እንግልታቸው ሲያሳስብ ደግሞ፤ #ከእርኪርኪው፤ ከውቂ ደብልቂው፤ ከከንቱ ውዳሴ ሰርግ እና መልስ በኋላ "ቁርጥ ያጠግባል" እንዲሉ ድቅቅ ሲል ሁለመናው። ሙሉ ሁለት ዓመት ዲስክርምኔሽኑ ሲቀጠቅጥ፤ መላ አልባው ተቋም ፋይዳው ሲደበዝዝ፦ ፈጣሪ ታምር ይሰራ ዘንድ ተጠዬቀ። ፈፀመው። ዬተፈፀመው ፈፃሚው ፈጣሪ መመስገን ሲገባው አሁንም በኮፒ ራይት ሲተራመሱ፤ ሲትበሰበሱ፤ እያስተዋል ዝምታ እና ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው ብለን እናስተውላለን። ፈጣሪ ለሚሰጠን ቀንም ፈጣሪ ምስጋናው ሲቀማ፤ ሲዘረፍ፤ ፈጣሪ ለታምራቱ ዬሰራቸው ፍጥረታት ደግሞ ለፖለቲካ ውቅር መዋለ ንዋይ ሆኖ አካለ ጎደሎ ሲባሉ፦ በጥበቡ መዘባበቻ ሲሆን ትውልድ ከዚህ ምን ይማራል ነው???
ቅዱስ ሚኬኤል ከአንዲት የታደለች ብላቴና አድባር ተገኜ አንድ አባት የነገሩኝን ነው እማጫውታችሁ። "መሽቶብኛል፤ መንገድ ጠፍቶኛል ልጅሽ ይሸኜኝ ይላታል።" እሷም ሳትሰስት ልጇን ፈቀደች። መላዕኩ ቅዱስ ሚኬኤል መሆኑን ሳታውቅ። ከዛ ልጁን በገደል ይለቀው እና ይመለሳል። ሲመለስ "መንገድ የሚያሳዬኝ አጥቼ ተመለስኩ" ይላታል። "ልጄን ሰጥቸህ?" ትለዋለች። እሱስ "የት ሄደ ብላ" ትጠይቀዋለች። የሆነውን ይነግራታል። ታዝናለች። የእናት ነገር። ቢኖር አሁን ከምታዝኝው በላይ የጥፋት ሁሉ መሰረት ሆኖ አንቺን ያስጠፋሻል።" ለዚህ ነው አላት።
ፖለቲከኛ ጎርፍ አይደለም። ፖለቲከኛ የሳሙና አረፋ አይደለም። ፖለቲከኛ እንደ ሊጥ ኩፍ ብሎ፤ እንደ ድፍድፍ ደንፋፍቶ #እረብ የሚል አይደለም። ወንዝ እንኳን መነሻም መደረሻም አለው። በዘውታ እዬተንጨባረቁ በህዝብ ግብር ሞቅ ካለው ሁሉ እዬተዶሎ መከራ እያንዶለዶሉ አሁንም ላላባራ ጭንቀት ትውልድን መማገድ ክብርም - ልዕልናም - ልቅናም - አይደለም።
ትውልድ እንደ ሽንብራ ቂጣ ከሚገለባበጠው የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚማራው መርህ እና ዲስፕሊን፤ ሞራል እና ኤቲክስ የለም። ቢኖርማ እንዲህ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በህግ ጥሰት ባልተሰመጠ ነበር።
"ለአንደበቴ ጠባቂ አኑርልኝ።"
ኢትዮጵያ እና ተፈጥሮዋ፤ ኢትዮጵያ እና ፀጋዋ፤ ኢትዮጵያ እና መክሊቷ፥ ኢትዮጵያ እና በረከቷ፦ ኢትዮጵያ እና ኃያል መንፈሷን የሚሸከም የፖለቲካ ተቋም ወይንም ሰብዕና ወይንም #ዕድል ወይንም ሥጦታ አላዬሁም። የሚገርመው ሁሉም የራሱን ሥርአትአልበኝነትን ሸጉጦ ወቃሽ እና ተራጋጭነቱ ነው።
የጠራ ~~~ የሰመረ ~~~~ የሰከነ ነገን የሚያዘልቅ፤ የትውልድ የሆነ የኖህ መርከብ አይደለም ተቋም አስተሳሰቡም አልተፈጠረም። በትውስት አይዲኦሎጂ፤ በውራጅ ርዕዮት 50 ዓመት ነደደ። የዶግ አመድ ሆነ። ቃጠሎው ገና 100 ዓመት ቀጣይ ትውልድን ዕዳ ያስከፍላል።
የወደመው፤ የጠፋው የከሰረው ሁሉ ዛሬ አይታይም። ቆይቶ ነው እሮው የሚከሰተው። እዳው ሳይከፈል ፕሮጀክቱ አመድ ሆኗል። ቢያንስ እንዴት ለዛ ፕሮጀክት የፈሰሰው መዋለ መንፈስ አይታዘንለትም። ለነገሩ ሰማዕቱ ኢንጂነር ስመኜው በቀለ በግፍ ሲገደሉ ነበር ሁሉም ሂደት መጠናቀቁን፦ ለትውልድ የማይሆን ሥርዓት ላይ ስለመሆኑ መገንዘብ ይገባ ዬነበረው። የጎርፍ ነገር ከጎረፈው ጋር፤ ዬዝላይ ነገር ከዘለው ጋር መዛለል። ሙሉ 50 ዓመት። አጤ ሂደት አንደበት ቢኖርህስ???
ስንት በፍርስራሽ ላይ እምትፈጥሩት ህግ ተላላፊ፦ ያልጠና፦ ላንቁሶ፦ በጥገኝነት ላይ የተንጠለጠለ በራስ መተማመኑን ለእርዳታ የሚያስገዛ ድርጅት እንጠብቅ???? ቁጥር ………
የራስን ድርሻ መወጣት ሲሳን ፈጣሪ ወስኖ በሚፈጥራቸው ፍጡራን አካላዊ ጉዳት ትርፍ ንግግሩ ይቁም!!! ትውልድን - ያመከናል። ህግ ተላላፊነትን ያፋፋል። ለምድራዊ ህግ መገዛት የተሳነው ሰማያዊ ህግን አሻቅቦ መራገጥ ከዚህ በላይ መሬትን እዬደበደቡ መከራ ጨምር፤ የዕንባውን ውቅያኖስ አስፋልን ይሆናል።
የተሸከምነው የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ የቤርሙዳ ትርያንግል ዘመን ምጣት በቂ ነው። ይህም የሆነው የእርግማናችን ውጤት ነው። ፍቅር ነስቶን፤ "ላም እረኛ ምን አለን?" ማድመጥ ተስኖን፤ ጥሞና መውሰድ አቅቶን የመጣ ሰማያዊ ቅጣት።
እኔ የተስፋ አቀንቃኝ ስለሆንኩኝ የተሰበሩ ቀናት ቀና የሚቃኑበት ዘመን፤ አጽናኝ መሪ፤ አዛኝ ቲም ኢትዮጵያ ታገኛለች ብዬ አስባለሁ። እዬሰራሁ ያለሁትም ያንኑ ነው። እምደክመው በዚህ አቅጣጫ ብቻ ነው። ከሳይለንት ማጆሪቲው የሚወጣ አቅም በኢትዮጵያ ተፈጥሮ ልክ የሚመጥናት ልዩ ሥጦታ። በአምላኬ ተስፈኛ ነኝ እና በአንድ ምሽት ብትን፤ ብትክትክ፤ ፍርክርክ ያለውን የአብሮነት ተፈጥሮ በአህቲ ወላዊነት የሚሰበስብ ሙሴ ፈጣሪ ይሰጠናል ብዬ አምናለሁ። "ፈረሰኛው ይመጣል።" ትንቢቱም ይፈፀማል።
መልካም ሰንበት።
መሸቢያ ቀን።
ማለፊያ ሌሊት ይሁንልን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
27/05/2023
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ