#በራስ መተማመን ሚዛኑን ሲስት እና ጠኔው።

#በራስ መተማመን ሚዛኑን ሲስት እና ጠኔው።
ዕለተ ሃሙስ ሰጋሪው
በከበቡሽ የቁራሽ እንጀራ ብራና
በቢሆነኝ የተብራራ ብራ
በሰብለ ህይወት አዝመራ
ለራህብ የሚራራ።
"ዝም ብዬ የመከራን ቀን እጠብቃለሁ።"
(ትንቢተ ዕንባቆም ምዕራፍ ፫ ቁጥር ፲፯)
በራስ መተማመን የሰብ ተክለ ሰውነት የግንባታ ሂደት ቀዳማይ ጉዳይ ነው።
በራስ መተማመን ምንጩ ነፃነት ነው ብዬ አምናለሁ። ነፃነት የአገር፣ የሙያ፣ የቤተሰብ ወዘተ ሊሆን ይችላል። ግን አያያዝም፣ አፈፃፀምም፣ አስተዳደርም ይጠይቃል።
አንድ ልጅ ከእናቱ ማህፀን ሲወጣ ራቁቱን ነው። እርግጥ ነው ለዬት ብለው የሚወለዱ ልጆች አሉ። ተክሊል ለብሰው ተወለዱ የሚባሉ። ተክሊሉ እንደ ሞራ ነገር ነው ይህ በጎንደር ይትበኃል የተለዬ አክብሮት አለው። ያ ሲቀደድ ያው ባዶ ገላ ነው።
ልጆች ሲወለዱ አካላቸውን ብቻ ይዘው ነው የሚወለዱት። የሰብዕና ግንባታው መነሻ ሆነ መድረሻው ከተዉለዱ በኋላ ነው የሚታነፀው፣ ውኃ ልኩም የሚጀመረው እንደ ማለት።
እያንዳንዱ ወላጅ ባሊህ ሊለው የሚገባ ቁምነገር ቢኖር እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ #መክሊትም #መልዕክትም ይዞ መወለዱን ነው።
……… ይህን በቅጡ ዕውቅና ሰጥተው ገርተው ያሳደጉ ወላጆች ወላጅ ሊባሉ ይገባቸዋል ብዬ አስባለሁ። ወላጅ ስል የወለደ ብቻ ሳይሆን ያሳደግም።
በኢትዮጵያ ይትበኃል ጎረቤትም የወላጅ ያህል ነው፣ የማር ልጅነት፣ የክርስትና ልጅነት አብሮ የሚሄድ ሲሆን የትዳር አጋር ልጅም እንዲሁ። "እንጀራ እናት እንጀራ አባት" የሚለውን አልወደውም። ደወሉ አሉታዊ ነውና።
ተፈቅዶም የሚሰጥ ልጅ አለ። እኔ እጅግ የምወዳቸው፣ የምሳሳላቸው ሁለት ጓደኞች ነበሩኝ ኦሮሞወች ናቸው። ሁለቱም የአንድ እናት አባት ልጆች ናቸው። አባታቸው የአደባባይ ሚስት ነበራቸው። የአደባባዮዋ ሚስት ግን መሃን ነበሩ።
ሁለቱ ባልና ሚስት ወንድ ወላጅም ነበሩ። ከዛ ልመናቸውን ሰምቶ መዳህኒዓለም ወላዷ እናት የመጀመሪያ ሴት ልጅ አገኙ። ለመሃኗ የመጀመሪያ ሴት ሲሰጣት አማኑኤል ልጇን ፈቅዳ ለመኃኗ ሰጠች። ድንቅ ነገር።
ፈጣሪ የወደደው ተግባር ስለነበር ቀጣዮዋ ሴት ሆነች እና ከወለደችው እናት ጋር አደገች። ሁለቱም ጎረቤት ሆነው ይኖሩ ነበር። ትልቋ የእኔ ጓደኛ ናት። ትንሿ ገልብጣ እኔን አሸነፈች። ግን ሁለቱም የልብ ነበሩ።
ወንድማቸውም አብሮ ይኖር ስለነበር ለውኃ አንድ ብርጭቆ ነው እምንጠቀመው። ማዳችን በጉርሻ ተጀምሮ በጉርሻ ይጠናቀቃል። ፍቅሩን ቃላቶችን ባነባብር አይገልፃቸውም። ልዩ ጊዜ ነበር።
ወደ ቀደመው ምልሰት ሲሆን … ለአውደ አመት ወደ ክ/አገር ሲሄዱ የሚገዙትን ልብስ ለእናት ለእናታቸው እኔ ብቻ ነው የማዬው። ስለሚፎካከሩ። አንዟ ለወለደቻት፣ አንዷ ላሳደገቻት።
ይህን ያመጣሁት ልጅ ከመሐፀን የወጣው ብቻ አይደለም ልላችሁ ነው። ለእኔ አይደለም ኢትዮጵያዊ የዓለም ልጆችም ልጆቼ ናቸው የእናት ማህፀን የአደራ ቤት ነው ብዬ ነው እማምነው።
ለሰከንድ ልጆችን በክፋ ዓይን አይቻቸው አላውቅም። ልጆች የውስጥ ፅላቴ ናቸው። ለዚህም ነው ቤተሰቦቼ ፖለቲካውን ተይ እና በልጆች ብቻ ሥሪ እያሉ የሚወተውቱኝ። ልጆች ታቦቴ ናቸው።
ወደ ተነሳሁበት ምልሰት ሳደርግ ልጆችን አሳዳጊ ቤተሰቦች፣ ማህረሰብ፣ በጎ አድራጎት ድርጅት፣ ት/ ቤት የልጆችን በራስ መተማመን ዓውራ ባህሪ አመጣጥኖ #በልኩ መምራት በእጅጉ ያስፈልጋል። አንዱ ቦታ የመስመር ብልሽት ካለ የልጆችን ጠቅላላ የህይወት ጎዳና ቀውሳማ ሾተላይ ያደርገዋል።
በራስ መተማመን ከልኩ በላይ ሲሄድ ነጮቹ ኦቨር ኮንፊደንስ የሚሉት ከሆነ አንባ ገነንነት፣ የተለጠጠ እብጠትን ሲያስከትል ከልኩ ሲያንስ የበታችነት ስሜት ኢንፈረሪቲኮንፕሌክስ ነጮች የሚሉትን ያመጣል። በብዙ ፖለቲከኞች ይህ ይታያል። ሁለቱም በሽታ ናቸው። ሥም የለሽ ደዌም።
ሁሉም ሆኖላቸው ነፍሳቸው አታርፍም የዚህ ደዌ ተጠቂወች። ይህ ማህበረ ኦነግ በወል የሚጋሩት ደዌ ይመስለኛል። አገር ተረክበው ገጀራ ይዘው ኮንደምንዬም ሲጠይቁ አይተናል።
አገር ግዙ አፍሪካን የመምራትም ቋሚ ርስቷ ነው ፓን አፍሪካኒስቷ ኢትዮጵያ ሲባሉ የዓለምን አራተኛ መዲና የእኛ ናት ባይም ናቸው። ማነስ፣ መድቁቅ፣ ምርቅ መሆን።
#የዓለም አቀፋ ቅቡልነት ጠኔ የተመታው በተለጠጠው በራስ መተማመን ነው።
ለውጥ መሪ ነኝ ባለው ቲም ለማ በውስጠ ታዋቂነት ቲም #አብይዝምወአባዱላ የገነገነ ኮፊንደንስ ቅቡልነቱን ጠኔ እንዲመታው አድርጎታል ውጥርጥሩ በራስ የመተማመን ሁነት። እኔ ያልኩት ይታመናል አፋፍ ላይ አንጠለጠለ።
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ የአገር ውስጥ እና የውጩ ተቀባይነት ብቻ ሳይሆን ንጉሥ ትሆናለህ እናታዊ ትንቢት ኦቨር ኮንፊደንስ ህይወታቸውን እንዲመራ ፈቅደውለታል።
በዚህ ላይ ኮከባቸውም አስተዋፆ አለው። እሳቸው ባሉበት የኮከብ ትንታኔ #መሪነትን እንጂ #ተመሪነትን ለመቀበል ጋዳ ስለሆነ። አስተዳደግ ያልተበደለ ከሆነ ማመጣጠን ይቻላል። ዶር አብይ ለዚህ አልታደሉም።
ሰኔል ላይ እዬተኙ ሞዝቦልድ ላይ እንደተኙ፣ በእግራቸው እዬኳተኑ ማርቸዲዝ እንደሚሾፍሩ ህልሙ እናታዊ የኢማጅኔሽን ያመጣው ጣጣ ነው። ልጆችን በልኩ አለማሳደግ ገደሉን ማዬት ይቻላል። ጎንደሬወች "ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳል" ይትበኃል ሊሰተዋል ሲገባ ከተሳተ ትርፋ ይህ ነው።
የሆነ ሆኖ አውሮፓውያኑ፣ ስሜን አሜሪካኑም ኃያላን የሚባሉ አገሮችን አስመልክቶ በ2011 "ዓለም መሰከረ" እኮ ብለው በድፍረት ተናግረዋል።
ከኖቬል ሽልማት ማግሥትም ባሌ ላይ "ዓለም ያውቀናል አውቆናል" ሲሉም የራሳቸው ኦቨር ኮንፊደንስ ያመጣው ጠንቅ ነበር። ኢትዮጵያን ያውቃታል ዓለም አይደለም ዕድምታው።
ከዚህ ኦቨር ኮንፊደንስ እና ጠኔው ጋር አብሮ እንዲታይ እምሻው ልባም አመክንዮ ተቃዋሚ ኃይሎችን፣ ተፅዕኖ ፈጣሪወችን ካለምንም ማንዘርዘሪያ፣ ካለምንም የመንፈስ መሰናዶ የተቀበሉበት ሁኔታም ከእጄ አያመልጡም ምላሱም፣ ቅቡልነቱም አለኝ ከሚል ከተለጠጠ፣ ካለልኩ ከተሰፋ #ቦርቃቃ በራስ የመተማመን መከራ የመነጬ ነው።
ከዚህ ጋር 90 ደቂቃ በኢንተቤ ታሪክ የተፈፀመበት የአማራ ሊቃናት፣ የጦር ኃይሎች ከፍተኛ መኮነን ህልፈትም ከተንጠራራው በራስ የመተማመን ጨጎጎታማ ዕዳ የፈለቀ ነው። ዓለምንም ለማወናበድ ሞክረዋል። ወጥ የሆነውን የኃይል አሰላለፍም ተርትረውታል።
የፌድራሉ እና የትግራይ ጦርነቱን ሲጀምሩት እና ሲተርኩት የነበረው የአገላለፅ ቃናዊ ደወልም ከዛው ከተወጣጠረው በራስ የመተማመን ቋት የተቀዳ ነው። ህወሃትንም በዚህ ውስጥ ማዬት ይቻላል።
ህዝብ አንቅሮ ተፍቶት በጦርነት ሥልጣኔን አስጠብቃለሁ ከኦቨር ኮንፊደንስ የመጣ ጠንቅ ነው። ይህ ሁሉ የሰባዕዊነት ሰቆቃ ምንጩም ይኽው ቦርቃቃ የራስ የመተማመን መከራ ነው።
አለም መሰከረልኝ ያሉት የኢትዮጵያ መሪ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ከሄሮ ወደ ዜሮ በእምርታ የተሸጋገሩበት ተደሟዊ ዕድምታዬ ከልጅነት ጀምሮ ተመጣጥኖ፣ ተቀጥቶ፣ ተጠርቦ ያልተያዘው ጣሪያ ላይ ተንጠልጥሎ ያደገው የራስ መተማመናቸው ኦቨር ኮንፊደንስ ቅጡ ከልኩ በላይ በጣም በላይ ሆን በልቅነት ስለተንቦረቀቀም ነው።
ከእንግዲህ መቀጣት አይችልም። ገርዝዟል እና። የሚቀጣው ወድቀው ትቢያ ሲለብሱ ብቻ ይሆናል።
እራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ይህን አያውቁትም። ፈፅሞ። ቢያውቁት እዬቀጡት ይሄዱ ነበር። እንዲህ ዓይነት አወዳደቅ በአጭር ጊዜም አያስተናግዱም ነበር።
#ከሳቸው የኢትዮጵያ ወላጆች የሚማሩት ቁም ነገር።
የልጆቻቸውን የሥነ -:ልቦና አገነባብ በራስ መተማመን ምጣኔ በልኩ መጥነው ሳይሞቀው፣ ሳይቀዘቅዘው በራሱ ተፈጥሮ ልክ ይዳብር ዘንድ ዕለታዊ ክትትል ሊያደርጉበት ይገባል ባይ ነኝ። ምኞት ይገኛል።
ምኞትን ማሰንበት የሚቻለው የአያያዝ ጥበብ ሲኖር ብቻ ነው። ተቀባይነትን ማበርከት የሚቻለው ያልተጣበቀ፣ ወይ ያልተለጠጠ በራስ መተማመን ሲኖር ብቻ ነው።
በድንገት ተፅዕኖ ፈጣሪ የሚሆኑ ሰወች ተሎ ኩርኩም መሆን ችግሩም ይህ ነው። ሳይጠብቁት ይፈነጠራሉ፣ ይሸለማሉ ከዛ ይለጠጣሉ።
ለያዥ ለገራዥ ያስቸግራሉ። ውይይቶች ስብሰባወች እኔን ካልመሰሉ ብለው ፈንግጡትን ያራምዳሉ። ለትዳርም ከባድ ነው። ጊዜውን ያልጠበቅ ዕውቅና ካላቸው ጋር መጎዳኜት። እድገት፣ ዕውቅና፣ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ቀስብሎ ሲመጣ፣ ቀስ ብሎ ሲያዝ ነው ሊበረክት የሚችለው።
እራሱ ዝና፣ መወድስ አስተዳዳሪ ይሻል። በልኩ የሚይዘው። በልኩም የሚንከባከበው። ልጆቻቸውን በልኩ የሚያሳድጉ ወላጆች አገራዊ ራዕይ ያላቸው የቀደሙ ናቸው። ልዩ አክብሮትም አለኝ።
ልጆቻቸውም ከአውደልዳይ ትርኪ ምርኪ ቦክስ አይገኙም፣ አቅማቸውም መኖራቸውም አይባክንም። ለትውልዱም አብነት የመሆን አቅማቸው ብጡል ነው።
የእኔ ክብሮች ቤተሰቦቼ ዘለግ ያለ ፁሑፍ ነው። ግለሰባዊ አቲካራ ሳይሆን ተቋማዊ ተጋድሎ ነው አገርም ትውልድም ሊያተርፍ ይችላል የሚል ዕምነት ያለኝ።
ኑሩልኝ። መሸቢያ ጊዜ
ቸር ወሬ ያሰማን ፈጣሪያችን። አሜን።
እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
03/06/2021
መኖርን ለማኖር እራስን ከዝበት በመቅጣት ሊሆን ይገባል።

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።