“ወልቃይት፣ ጠገዴ እና ቀብቲያ ሁመራ፣ የበጌ ምድር ግዛት እንጂ የትግራይ አካል ኾነው አያውቁም" አቶ ገ/መድህን አርአያ፣ የቀድሞ የህወሓት ታጋይና የሥራ አመራር የነበሩ

ከአቶ አስፋው ሞገስ የተገኜ ነው። እንዴት ናችሁ ውዶች?
ምንጩ ከዕውነት አርበኛው ከአቶ ገብረመድህን አርያ የተገኜ ነው። አሟቸው ነበር። ተሻላቸው ይሆን?
“ወልቃይት፣ ጠገዴ እና ቀብቲያ ሁመራ፣ የበጌ ምድር ግዛት እንጂ የትግራይ አካል ኾነው አያውቁም" አቶ ገ/መድህን አርአያ፣ የቀድሞ የህወሓት ታጋይና የሥራ አመራር የነበሩ
 

 
አዲስ አበባ: ሐምሌ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) "ከዛሬ 45 ዓመታት በፊት፣ ኢትዮጵያውያን የግራ ዘመም ፖለቲከኞች አውራ የኾነው ትህነግ (ወያኔ) በተከለው አሜኬላና በቀበረው የሴራ ፖለቲካ ፈንጅ እርስ በርስ ተባልተው ዛሬ ላለንበት የፖለቲካ መድረክ ከመብቃታችን እና ሀገሪቱ በዘር በሽታ ከመታመሟ በፊት፣ ትህነግም ወልቃይት ጠገዴን የቅዠቱ አካል አድርጎ ካርታ ላይ ሳይስል፣ በወያኔ ከፍተኛ አመራር አባላት አማካይነት ለወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ አንድ ኹነኛ ጥያቄ ቀርቦ ነበር" ይላሉ የቀድሞ ታጋይ ገ/መድህን አርአያ።
በወቅቱ ይላሉ፣ እኒኽ ጉምቱ ፖለቲከኛ፣ "ወልቃይት ጠገዴ የማን ግዛት አካል ነው...?" ተብለው ሲጠየቁ፣ በወቅቱ የነበሩ ሰዎች ያለምንም ፍርሓትና ማመንታት “ወልቃይት ጠገዴማ፣ የበጌ ምድር ክፋይ፣ የአማራ ሕዝብ ርስቱ ነው" ብለው መለሱላቸው ይሉናል።
አቶ ገብረመድህን አርአያ በትህነግ ቤት ከከፍተኛ አመራር አባልነታቸው ባሻገር፣ የፋይናንስ ክፍል ኃላፊ ኾነው ሰርተዋል። ስለኾነም የትህነግን የተንሸዋረረ እይታና የተወላገደ አሥተዳደግ ጠንቅቀው የተረዱና ለዘመናት በተለያዩ የትግል ሥልቶች ሲታገሉ የመጡ ጨዋ ኢትዮጵያዊ ናቸው..።
የቀድሞ የህወሓት ከፍተኛ አመራርና የፋይናንስ ኃላፊ አቶ ገብረመድህን አርአያ በሚያዝያ ወር 2006 ዓ.ም በኢትዮ ሚዲያ ጎልጉል ድረ-ገጽ ላይ "በወልቃይት ጠገዴ የዘር ማጥፋት ወንጀል" በሚል ፅሑፋቸው ወልቃይት መሰረታችን የበጌ ምድር ነው፤ ይህ መሬት ከጥንት ጀምሮ የጎንደር በጌ ምድር ግዛት ተብሎ ይጠራ ነበር ዋና ከተማውም ጎንደር ነው ይህም ከጥንት ጀምሮ የመሩት የኢትዮጵያ ነገሥታት እስካሁን ድረስ ያሉ መንግሥታት እውቅና ሠጥቷቸዋል በማለት ይናገራሉ።
በተጨማሪም ተከዜ ወንዝ አማራንና ትግራይን የሚለይ ድንበርም ነው ሲሉ ገ/መድህን አርአያ ይገልፃሉ።
በወያኔ በኩል "ወልቃይት የማን ነው...?" ለሚለው ተደጋጋሚ ጥያቄ የታሪክ መዛግብት እንደሚያሳዩት የአማራ ተወላጆች ለእነዚህ ጥያቄዎች ግልጽና ቀጥተኛ መልስ በመስጠታቸው ተደብድበዋል፣ ተፈናቅለዋል፣ ተረሽነዋል ሲሉ አቶ ገ/መድህን አርአያ ያስረዳሉ።
የቀድሞ የህውሓት ታጋይ ገ/መድህን አርአያ ከሌሎች ሚዲያ ጋርም ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ወልቃይት ጠገዴ የትግራይ ግዛት ኾኖ አያውቅም፤ ተከዜ አማራንና ትግራይን የሚለያቸው ድንበር ነው ታሪካዊ እውነታው ይህ ነው ሲሉ መስክረዋል።
ወያኔ ከኢትዮጵያ የመገንጠል እና የራሱን ታላቋን ትግራይ የመመስረት የጥላቻ ህልም ነበረው የሚሉት አቶ ገ/መድህን አርአያ እውነታውንም በግልጽ አስረድተዋል።
ሕወሐት ከመጀመሪያው ጀምሮ ከኢትዮጵያ በመገንጠል የራሱን ህልም የሆነች "ታላቋ ትግራይ" ለመመስረትና የወልቃይት መሬት ለም በመሆኑና በእርሻ ከሁሉም የተሻለ ስለሆነ ወደ ራሱ የመሠልቀጥ በሽታ ተጠናውቶት ነበር።
ወያኔ የወልቃይት መስመር የኢኮኖሚ ኮሪደር ከመሆኑ ባሻገር ወደ ሱዳን ለመግባትና ለመውጣት ካላቸው ከፍተኛ ፍላጎት ወልቃይትን በጉልበት ወደ ራሳቸው ግዛት ጠቅልለውት እንደነበር ተናግረዋል።
ወልቃይት፣ ጠገዴ እና ቀብቲያ ሁመራ የአማራ ሕዝብ ግዛት አካል ብቻ ሳይኾን የበጌ ምድርም መፈጠሪያ ነው ሲሉም አስረግጠዋል።
በሳሙኤል ኪሮስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።