#ቡርሽ ውል አለኝ ሽውም። ውስጣችን ጎድፏል። ውስጣችን #ጎልድፏልም። እንተባተባለን። አለን ግን በሽሽት። እንኖራለን ግን በሽግሽጎሽ። እና? እናማ መኖር ብለነዋል ድብቅብቆሹን።
#ቡርሽ ውል አለኝ ሽውም።
አብረን እንማስን እስቲ። ቡርሽ ፍለጋ አብረን - አብረን እላለሁኝ። ቡርሽ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያስፈልገናል። ውስጣችን ጎድፏል። ውስጣችን #ጎልድፏልም። እንተባተባለን። አለን ግን በሽሽት። እንኖራለን ግን በሽግሽጎሽ። እና? እናማ መኖር ብለነዋል ድብቅብቆሹን።
አገር ከአለትውልድ አይታሰብም። ትውልድም ካለ አገር አይሞክርም። እንደ ኩርድሾች ካልገጠመን። ለነገሩ ኩርድሾችን ለመሆን እዬቧጠጥን ነው። ማህከነ። አዬ አንሻዬ የአንቺን ህይወት ምነው ሁሉ ቢያይልኝ። አይሻ የኩርድሽ የራዲዮ ጋዜጠኛ ናት። ዬማውቃት ለ15 ዓመታት ነው በራዲዮ ጋዜጠኝነት ነው።
ቅድመ መሰናዶ ከእኔ ቀጥላ እሷ ናት። ስትዲዮ እምትረከብ ከኮረና በፊት፦ እና እህት አንሻዬ ቁጭ ብላ ምግብ ስትመገብ አላዬትም። ቁጥር ሁለት ስትዲዮ ስለቅላት #ኬባቧን ይዛ ትገባለች። ኬባብ በሥጋ በሰላጥ የሚዘጋጅ ፋስት ፋድ ዘርፍ ውስጥ ነው። ምነው አንሻ ለምግብ ጊዜ ቢኖርሽ ስላት "#ስሞት ይሆናል" ትለኛለች። መንገድ ላይም ሳገኛት ምግቧ መንገድ ላይ ነው። መጠጧም እንዲሁ። ሁልጊዜ እንደባከነች ነው። አርበኛ ሴት የኩርድሽ ጓዶቿ ታጋዮች ጉዳይ ውስጧ ነው። ኩርድሽ ሴቶች አቻ እና ወደር የላቸውም። የወጣላቸው አርበኛ፤ የወጣላቸው ጀግናም ናቸው። አላቃዬ እራሱ እግሯን ያጣችው በትግል ሜዳ ነበር።
ይበልጥ ብልሽቱን ደግሞ እንደሚሆን አድርገህ አድርገው ተብለው በሳቸው ጎራ የተኮለኮሉት ማለፊያ ብለው ይለፍ ሰጥተዋቸዋል። አሁንም ይሞግቱላቸዋል። እኔ የማይገባኝ ምቹነት ካለው ለምን ስደት ላይ ይቀመጣሉ የአብይዝም ማህበርተኞች። አገር ሄደው ምንጣፍም ጉዝጓዙንም ቢያሰናዱ ባይ ነኝ።
ውስጣችን ቆሽሿል። ውስጣችን ቂም ያረገዘ ነው። ውስጣችን በቀልን የጨለጠ ነው። ውስጣችን ሴራን የጠመቀ ነው። ውስጣችን ሽብርን ያጨ ነው። ውስጣችን ምቀኝነትን ያረገዘ ነው። ውስጣችን ፋክክርን አቤት ወዴት ያለ ነው። ውስጣችን ጭካኔን አንቱ ያለ ነው። ውስጣችን በክፍልፋይ፤ በክት እና በዘወትር፤ በቤት እና በእዳሪ አቀራረብ የታጀለ ነው።
ከፍተናል። ተሸንሽነናል። ተፍረክርከናል። እያለቅን መሆናችን ዕውቅና መስጠት ተስኖናል።
? አጤ ጥያቄ ይጠይቀናል???
#የት ላይ ተሳሳትን?
#ስህተቱ ምንድን ነው?
#ግድፈታችን ለማረም ምን አቅም አለን?
#መፍትሄው እንደምን እናምጠው?
#በምን ሁነት ውስጣችን ያለውን ቆሻሻ ማፅዳ እንችላለን?
ፈጣሪያችን፦ አላኃችን ያዘንብን ነገር ምን ይሆን?
እርግማኑ እንዴት መጣ?
#ማግሥት ቀርቶ ዛሬን እንደምን የእኛ እንዲሆን እንሞርደው?
ህልውና? ህላዊነት አድራሻቸው የት ይሆን????
ሁላችንም አቅል ነስቶናል። ሁላችንም ቀልብ አጥተናል። ሁላችንም አደብ አጥተናል። ሁሉም ሰው ከታዳጊ ወጣቶች በታች ሆኗል። ኮበሌ ኮበሌ፤ ኮረዳ ኮረዳ ያሰኜናል። ከወጣቶች ያነሰ ሙሉ ዕድሜ ላይ ያለ ግን ብላሽነት አልቦሽነት ከትሟል። ማስተባበል ብቻ። ዕብለት ብቻ። እራሱን ፃዕዳለማድረግ መንደፋደፍ ብቻ። እኔ ጥፋተኛ ነኝ ብሎ እራሱን አጋልጦ ለትውልዱ መዳን አብነት የሚሆን ሰብዕና ማፊ። ጉዲሰዲ ነው።
ቢያንስ ጆሮ ሥራውን እንዲሠራ። በቅጡ እንዲያዳምጥ። ጉሮሮ የተላመጠለትን ብቻ እንዲውጥ። ልቦና አጣርቶ እንዲነሳ በፍረጃው ሁሉ እዬተዘፋፈቀ ትውልድን ዝልቦ እንዳያደርግ ማንዘርዘሪያ ማሰናዳት። ህሊና መጨመትን ተመግቦቱ እንዲያደርግ መፍቀድ እንዴት ይሳናል? ለምን ተሳነን? ስለምንስ አቃተን???
ግን ሁሉም በአንድ ማንቆርቆርያ እንዶልዶል ነው። ግን ስለ ዲሞክራሲ ደግሞ ዓዋጅ ይደመጣል ከሁሉም አቅጣጫ። ዴሞክራሲ የማይፈለገውንም፤ የማይወዱትንም አደብ ገዝቶ የማድመጥ፤ አድምጦ በጭብጥ በፋክት ያልተመቸን ሃሳብ መሞገት መቻል ያስፈልግ ነበር። መፍትሄ አመንጭቶ በጨመተ መስመር በተለይ ሳይለንት ማጆሪቲውን ከጎኑ ማድረግ መቻል ነበር። ዕድሎ ቢገኝ እንኳን አዚሙን አላውቅም ይበተናል። በዘመናችን ያዬነው ይኽውን ነው።
ብቻ የማዬውም፤ የማደምጠውም ጠቅልሎ መጥላት፤ ጠቅልሎ ማውገዝ፤ ወይ ተጠቃሎ መደገፍ ነው። የሚገርመው በዚህ ውስጥ ያለው የግድፈት ሸክማ ሸክም ነው። ፀድቶ ነው ማፅዳት የሚቻለው። ነጥቶ ነው ማንጣት የሚቻለው። ቆሽሾ ከሆነ ቆሽሾ ማቆሸሽ ነው የሚሆነው ካልኩሌሽኑ። በሚተቸው፤ በሚወገዘው፤ በሚወቀሰው ውስጥ ሁሉም እራሱ ፃዕዳ ስለመሆኑ ጠያቂም ተጠያቂም የለበትም። ተዓብ ነው።
ትውልድን ለማዳን ቡርሹ ከራስ ይጀምር። በሚወገዘው ውስጥ እራስ ተዘፍቆ ማዳን /// ማዳን ከቶም ሊታደገው ፈጽሞ አይቻልም። "የዝብሪት ቤት" የግል ጎጆን ይሁን ከጣለ። በዛች ታላቅ ግርማ ሞገሷ በፀጋ ለከበረ አገር የማን ደም ፈሰሰ ዝብሪት ግን ቋት አይገፋም። መደፋት። መፍሰስ ብቻ። ትርፍ ነው ከተባለ።
ግልቢያ ……… ብቻ። ጥድፊያ ………? ብቻ። ሩጫ …??? ብቻ። መዘላለፍ ………… ብቻ። መወቃቀስ ……… ብቻ። መካሰስ ……… ብቻ "ሲሮጡ የታጠቁት ………" እንዲሉ። በሁሉም ውስጥ ንጽህና ቢኖር እንዲህም ባልተዋረድን ነበር። እንዲህም መላ ቢስ ባልሆን ነበር። የተፍረከረከ እንጂ የተሰበሰበ ነገር የለም። ንደት መሸራረፍ ነው ያለው። መቀነስ መቀናነስ ነው ያለው። ለዕውነት መቼስ ጋራጅ አያስፈልገውም።
አቅም አለኝ ለማለት ብዙ ደፋር አለ። ውድቀቱነው በስኬት፤ በምስጋና፤ በሞገስ ይንቆጥቆጥልኝ የሚባለው። ስኬት ቢኖር እንዲህ ሁለመናው ውሎ ጉዞ ባልጠፋበት ነበር። ተዛነፍ ጥሩ አይደለም። መዛነፍ ቢናፈቅም በእኛ የፖለቲካ አያያዝ አይገኝም። መሻል ነው ስኬት። አቅምን አውቆ መወጠን ነው የስኬት ባቡር። ሁሉንም አጥቶ ሁሉንም ገብሮ በሰርክ ዕንባ መታደም። ህም።
ለመሆኑ???
ነገስ ማን ፦፦፦፦፦ ይሰብለት?
ማግስትስ፦፦፦፦ ማን ይሁንለት?
ከነገ ወዲያስ ማን፦፦፦፦፦፦፦ አለው?
በዛሬ ውስጥ - ትናንት፤ ከትናንት - በስቲያ ከዛም - በስቲያ አለ። በዛሬ ውስጥ ነገ --- ማግስት እንዴት እርሾ ይኑረው? በዚህ መንደፋደፍ? በዚህ --- ጥድፊያ? በዚህ ባልተያያዘ የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግብግብ እና ፍርክርክ የሴራ እና የአድማ ውድድር?
ቢያንስ የቆሸሸው ልቦና፤ የጎደፈው ህሊና ቡርሽ ቢገዛለት በፀሎት አምላካችን፤ አላኃችን በድዋ ይታደገን ዘንድ እራስን ማፅዳት ይቅደም ነው የጭብጡ ሃሳበ ምህዋር። ጎድለናል። ፈሰናል። ሰው ሆነን ግን ክደነዋል።
እግዚአብሔር ይስጥልኝ። የእኔ አዱኛወች ደህና አምሹልኝ። ሰላም የረበበት ሌሊትም ይሁንላችሁ፤ ይሁንልን አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
26/07/2023
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ጋራጅ አያስፈልገውም።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ