ዬአቅም ምንጩ ትውልዱ እና ዕጣው። #ከሳይለንት #ማጆሪቲው የተውጣጣ አጽናኝ፤ ሰባዕዊ ግብረ ኃይል ወይንም ቲም ቢመራት ምርጫዬ ነው። ትውልዱም ቢያርፍ። ማገዶነቱ ቢያከትም
ዬአቅም ምንጩ ትውልዱ እና ዕጣው።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ አቅም አጀንዳ ሆኖ አያውቅም። አቅም ጊዜ፤ የሰው ልጅ ጉልበት፤ መንፈስ፤ መዋለ ንዋይ ነው። በአንድ የፖለቲካ ማዕቀፍ ውስጥ እነኝህ ሁሉ ያስፈልጋሉ።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ፋይናንስ ብቻ ነው እንደ አቅም የሚታዬው። ከዛ ውጪ ያለው ጥልቅ የሆነ እያንዳንዱ በግል ሁሉም በጋራ የሚያፈሰው የጊዜ እና የመዋዕለ መንፈስ እርዳታ ከመጤፍ አይቆጠርም። ለምን? በነፃ ስለሚታደል።
አንድም ፖለቲከኛ ስለሚሰጠው የነፍስ ወከፍ ሙሉ ድጋፍ ከቁብ ቆጥሮት አያውቅም። እሱ በተገለባበጠ ቁጥር እዬደፋፋ አዲስ አቅም ሲመኝ ይሉኝታ እሚባል አልፈጠረለትም። ድጋፋ፤ እገዛው፤ ማበረታቱ ቀርቶ ማለት ነው።
ከሁሉ የሚከፋው አንድ ኮቢ ሳይገዛ፤ አንዲት እራፊ ሳይሸምት ወላጅ ያሰናዳውን ትንፋሽ ቄራ ላይ መዋሉ ነው። ዘመን ከዘመን የኢትዮጵያ ትውልድ ይታጨዳል። አንዱን ደግፎ ሲወጣ፤ ሌላውን አሻም ሲል በግብግቡ ዬትውልድ መተራ።
የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ግብታዊ ናቸው። ግብታዊነታቸው ሳያቅዱ ተነስተው ስለሚፈጠረው የትውልድ ብክነት አንድ ቀን አጀንዳቸው ሆኖ አያውቅም። በዛው በተደረተው አስተሳሰብ በአዲስ ሸበላ ድምፅ የፖለቲካ ድርጅት ባመረቱ ቁጥር ያልደከሙበትን ትውልድ እዬዘረፋ ለካቴና፤ ለስደት፤ ለመሰወር እና ለዕልፈት ይዳርጋሉ።
እነሱ አክተር ናቸው። ተተኪ ማብቀል ሃራማቸው ነው። ተተኪ ብቻ ሳይሆን የተሻለ ዕሳቤ ካለም ገብተው አነኩረው በአንጃ አንቆጥቁጠው ይበትኑታል። ይከተክቱታል። ከበተኑት በኋላ እስከ ግል ህይወት በደረሰ ደመኝነት፤ #አጋ ለይተው በጎራ አንዱ ሌላውን በፍረጃ ድራሹን ያጠፋዋል። በዚህም አያበቃም። ማህበራዊ ኑሯችን፤ ሰላማዊ ህይወታችን፤ ጥረታችን እና ተደራሽነታችን ይታወካል። ሰላሙ ይዘረፋል።
ወላጅ ፍዳውን ከፍሎ ያስተማረን ቀንበጥ እና ሸበላን በአዲስ ቅላፄ በማማለል ለማገዶነት ይሰናዳል በሞገዳዊ ፕሮፖጋንዳ። ቀድሞ የተማገደው አስተዋሽ የለውም። ፈጽሞ። ሊማገድ የተሰናደው ከተቆሰቆ በኋላም የግንባር ሥጋ ከሆነ ትዝ የሚለው የለም። መከራው፤ ፍዳው፤ አሳሩ፤ መከፋቱ ያው ለወለደ ማህፀን እና አብራክ ይሆናል። ለቅርብ ቤተሰብ ጥቁር ልብሱም ስንቅ አቀባይነቱም ይተርፋል።።
የሚገርመኝ ደጋፊ እና አባል ሲጠዬቅ ዘርተው፤ ኮትኩተው አሳድገው፤ አብቅለው ያሰበሉ ይመስላሉ። የኢትዮጵያ ልጆች ልክ እንደ ወንዝ ዳር አሽዋ ይታፈሳሉ። በባከነው #ወፌፌ ፖለቲካ ተቆስቁሰው በነው ይቀራሉ። ፖለቲካው ካለ ቦታው ገብቶ ሲገሸር ለዕለት እንጂ ነገ፤ ከነገ፦ በስቲያ ትርፍ እና ኪሳራው፤ ዘላቂ ግቡ እና መዳረሻው አይሰላም። ይህም ሆኖ ያ ስንት የተደከመለትን የትሜና በትነው አዲስ ደግሞ በአዲስ ሥያሜ ይመደምዳሉ። አያረግዙ፤ አይወልዱ ምን ቸገራቸው አምራቿ የኢትዮጵያ እናት አለች። የእነሱ ልጅ፤ የልጅ ልጅ መኖሩን ሞሽሮ ይቀማጠላል። ለሰርክ ልኳንዳ ቤት ቁርጥ አቀባይ የኢትዮጵያ ማህፀን እና አብራክ።
አቅም ማስተዳደር ስለማስፈለጉ ሰጩም ተቀባዩም አጀንዳቸው አይደለም። ስለዚህም ትርፍ አልባ ዘመን ተዘመን የትውልድ ብክነት፤ የአገር ድቀት #አና አለ። በዚህ ውስጥ ፀፀት የለም። በዚህ ውስጥ ይቅርታ የለም። ብላሽላሽ።
በተለያዩ ሁኔታወች የኢትዮጵያን ቀደምት ከተሞች አያለሁኝ። አርጅተው፤ አፍጅተው ሻግተዋል። አንድም ተሻለ የምለው በገጠር ከተማ አላዬሁም። እኔ ኢትዮጵያ እያለሁ የተተከሉ የስልክ እና የኤሌትሪክ እንጨቶች እራሱ ዘመንን እዬረገሙ አሉ እንዳሉ።
ለምኑ ይሆን ይህ ሁሉ ግብርነታችን?
ለማን ተብሎ?
ምን ለማግኘት የኢትዮጵያ እናቶች እዬወለዱ ለይሉኝታ ቢሱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ፖለቲከኞች የማይጠግን ህልም ይገብራሉ? ተግ ብሎ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው።
ትውልድም አቅሙን ቆጥቦ ሁነኛውን ቲም፤ ሁነኛውን የቲም ሙሴ እስኪያገኝ ድረስ አንድ ቀን እናመሰግንኃለን፤ ዕንባህ ዕንባችን ነው፤ ሃዘንህ ሃዘናችን ነው ያልተባለው የነፃ የህይወት ዬአቅም ምንጭ በአደብ ሆኖ፤ ጊዜን መርምሮ አቅሙን በቅጡ ቢያስተዳደር የአክተሮችን ገባወጣ፤ ጠራጠሮ ጨዋታውን ትውልዱ በድል ሊቋጨው ይችላል።
ለዚህም አደብን፤ ስክነትን፤ መጨመትን፤ ህሊናን ሆነ ዕዝነ ልቦናን ከቂም፤፦ከምቀኝነት፤ ከበቀል፤ ከጥላቻ አፅድቶ እራስን ማሰናዳት ይገባ ይመስለኛል። መርገብገብ ሆነ መጣደፍ ትርፍ የለውም። እራስን፦ ውስጥን፦ አካባቢን፦ መስተጋብራዊ ግንኙነትን በእርጋታ ማስከን ያስፈልጋል።
ውዶቼ ቸር ዋልሉኝ። አሜን።
ቸር እነሰብ። አሜን።
ቸር ያሰማን። አሜን።
እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
28/07/2023
ትዕግሥት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል።
ፍቅርም ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ