ስለምን ኃላፊተት እና ተጠያቂነት የሚሰማው ትውልድ ማብቀል ተሳነን?

 

ስለምን ኃላፊተት እና ተጠያቂነት የሚሰማው ትውልድ ማብቀል ተሳነን?

 
"በባቢሎን ወንዞች አጠገብ በዚያ
ተቀምጠን ጽዮንን ባሰብናት ጊዜ አለቀስን።
(መዝሙር ፻፴፯ ቁ ፩)
እንዴት አደራችሁልኝ ማህበረ ክቡራን እና ክቡራት? እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ አምላኬን ተስፋ አድርጌ ደህና ነኝ። ሰሞናቱ እንደ ደመናም፤ እንደ ወጀብም፤ እንደ ዝናብም ይቃጠዋል በቅድስቷ በዕቴ በቪንተርቱር ከተማ።
ማሰብ። ማሰብ። ማሰብ። እያሰብኩ ሃሳብን አስበዋለሁኝ። ስለምን ኃላፊነት እና ተጠያቂነት የሚሰማው ትውልድ ማፍራት ተሳነን? እኛም ሆን የቀደሙት ስለምን መዝራትን ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ ከማብቀል፤ ተጠንቅቆ ከማሳደግ ጋር ምኑ አፋተን?
#በኃላፊነት እና በተጠያቂነት መሐል ጉልቻው ከፈረሰ ቆዬ። ግን ለምን?
 
#አደራ ምንድን ነው?
#ትውፊትስ ምንድን ነው?
#ትሩፋትስ ምንድን ነው?
#ቅርስ ውርስስ ምንድን ነው?
#ታሪክስ ምንድን ነው?
#ባህልስ ምንድን ነው?
#ወግ - ልማድስ ምንድን ነው?
 
ግን ምንድን ነው እራሱ #ምንድን ነው? መልስ ይሻል? እንጀራን እዬበሉ እንጀራ የተፈጠረበትን ሥልጣኔ ማብጠልጠል? አማርኛ ቋንቋን እዬተናገሩ አማርኛ ቋንቋን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት መፍጨርጨር? ሰንደቅ ዓላማው ባስገኜው የነፃነት ትንግርተ ቤተ - መንግሥት ተቀምጦ ሰንደቅ ዓላማን መፎካከር? ግን ምንድን ነው? እራሱ ምንድን ነው ምንድን ነው?
 
ኢትዮጵያ በሚለው ሙሉ አቅም ባለው ኃይለ ሚስጢር ለሥልጣን ተበቅቶ፤ ለሽልማት ተበቅቶ፤ ለክብር ለዝና ተበቅቶ አዬር ላይ ተንሳፎ በቅሎ ዙፋን የተጨበጠ ይመስል "የራሴ ጥረት ስኬት" እያሉ መጎረር በማጓራት መጯጯኽ ምንድን ነው? ግን እራሱ ምንድን ነው ምንድን ነው?
 
የተሰደደውም ኢትዮጵያ በሚል ኃይለ - ሚስጢር ስደቱን አሳክቶ ተምሮ፤ ወልዶ ከብዶ፤ ሰው ከደረሰበት ደረጃ ተደርሶ ኢትዮጵያ የምትባል አገር አላውቃት፦ አታውቅኝ ብሎ በባላንጣነት ፈርጆ፤ አንጃ ግራንጃነት ግን ምንድን ነው? ለመሆኑ እራሱ ምንድን ነው ምንድን ነው?
 
አምስተኛ የሥልጣን ኃይል ያለው ልሳነ - መንበር ይዞ "አንተ፤ አንቺ" እያለ ሲዘልፍ፤ ወይንም አንጠልጥሎ ሲጣራ ከቤቱ ቤተሰብ፤ ከጎረቤቱ፤ ከሥራ ባልደረባው፤ ወይንም በሚኖርበት አገር አክብሮት እራሱን የቻለ ትውፊት፤ ትሩፋት፤ ታሪክ ባህል እና ወግ ከዛም ባለፈ ህገ - እግዚአብሔር፤ የአላህ ድንጋጌ መሆኑ ስለመጣሱ፤ በዚህ ትልልፍ እሳቤ ውስጥ ትውልድ አረም ሆኖ ስለመብቀሉ ልብ ያለው የለም። በልጅ ምርቃት፤ በልጅ ልጅ ህይወት ውስጥ እራሱ አባ፤ እማ ወራው ያልሆነውን ልጁ፤ የልጅ ልጁ እንዴት ሰብሎ ሊበቅል ይችላል ብሎ አለማሰብ? ግን ምንድን ነው? እራሱ ምንድን ነው ምንድን ነው???? 
 
በጀርመኖች ቋንቋ በጀርመንኛ አክብሮት እራሱን የቻለ የርቢ ዘርፍ አለው። እርሷ ሴት ናት። በትንሹ ኤስ ሲፃፍ አንቺ ይሆናል። ለቤተሰብ ለቅርብ ጓደኛ፤ ለጥበብ ሰውም sie በጋዜጠኝነትም በቲያትር ጥበብ ላሉ አንቺ ይባላል ኮርስ ላይ ያዬሁት ነው። በመደበኛ ቋንቋ ኮርስ ግን እርስወ ነው አጠራሩ። ስለዚህ ሴት ከሆኑ ተማሪዋ እርስወ ነው። 
 
ይህ ማለት ኤስ በትልቁ ይፃፋል። Sie ይሆናል። እራሱ ዘርፋ ሆፍልሽካት ይባል። በጣም ፀያፍ ነው ሰውን ደርሶ አንተ አንቺ ማለት። በማቃለልም ይሁን በማግነን እርስወ ነው። የቤት ጠባቂ አንቺ ብሎ ጠራኝ ብላ ለቤቱ አከራይ ባለቤት የከሰሰች ጎረቤት ነበረችኝ።
 
በኢትዮጵያ እንኳን አንቺ እና አንተ አለቃ፤ ታላቅ ሲገባ ከመቀመጫ መነሳት፤ ኖር የሚለው ጥልቅ ባህል፤ ኧረ በእግዚአብሄር የሚለው ልዕልና ተፈጥሯዊ ነበር። መንገድ ስናቋርጥ ታላቅን፤ ሙሽራን፤ ታቦትን፤ እሬሳን ማስቀደም ያልተፃፈው ህጋችን ክፍለ አካል ነው።
 
ለረጅም ጊዜ እምለው አለ። ኢትዮጵያ በተፃፈም ባልተፃፈም ህግ ትተዳደራለች። ባልተፃፈ ህግ እንደሚተዳደሩት እንደ እንግሊዞች፤ በተፃፈ ህግ እንደሚተዳደሩ አሜሪካኖችም። የህግ ባለሙያወች ምልከታዬን ላይስማሙበት ይችላሉ። እኔ ግንከ2008 እኤአ የፀጋዬ ድህረ ገጽ እና የፀጋዬ ራዲዮን ከመሠረትኩ ጀምሮ አስፍሬዋለሁ ዕምነቴን።
 
እንደ እኔ እምነት ከተፃፈው ህጋችን ይልቅ ያልተፃፈው ህጋችን በቅጡ ካለ ሺ ሠራዊት ይከወናል። የውል መሠረቱ በመግባባት የሰከነ ስለሆነ። በእያንዳንዷ የግል እና የጋራ ህይወት ውስጥ ኢትዮጵያ ካለች ለህጓ፦ ለድንጋጌዋ መገዛት ግድ ይላል። ያ መሆን ከተሳነ ወላቃው ከአናት ብቻ ሳይሆን ከማገሩም፤ ከግድግዳውም፤ ከወጋግራውም፤ ከወለሉም ይሆናል። ኢትዮጵያ ፍርሰቷ የሚጀምረውም ከዚኽው ይሆናል። ኡኡታው እራስንም ያካታል እንደማለት። "ህግ ተላላፊወችን ጠላሁ" ይላል ልብ አምላክ ዳዊት።
 
ስፍስፍ ብሎ ኢትዮጵያን እወዳለሁ እያለ #አክብሮትን ሲጠቀጥቅ፤ ዘቅዝቆ ሲሰቅል ግን በዛ ዝልኝ ጉዞ ኢትዮጵያ አራሙቻ ማብቀሏ አይታዬውም። ወይንም አይገለጥለትም። ለምን ኃላፊነት እና ተጠያቂነት ያለው ትውልድ ማብቀል የተሳነን ከራስ የሚጀምር መታረም፤ የሞራል ልዕልና ጥሰት የመነጨ ስለመሆኑ ቢያንስ መቀበል ቀጣዩን ትውልድ እንዳናከስል በረዳ ነበር።
 
ዕውነቱን ልናገር። ማንኛውም ሰው በእግዚአብሄር በአላህ አምሳል ተፈጥሯል። አማንያን በዚህ እንስማማለን። ሰወች ክፋነታቸውን፤ ሆነ ጭካኔያቸውን ይዘውት አልተፈጠሩም። ሰውን ሲፈጥረው አምላኩ በአምሳሉ ነው። አጽድቶ አንጽቶ። ስለዚህ ክብሩ ለፈጣሪ ሊሰጥ ይገባል። እምታከብረው የፈጣሪን የአፈጣጠር በረከት ነው። ይህ ማለት እሱ የፈጠረው ፍጡርን አክብሮ መነሳት ግድ ይሆናል። ዕምነቱ ካለ። በክፋነት፤ በጥፋት ከሆነ ሁላችንም ስናጠፋ ስናለማም ኑሮናል። እራስን አርሞ መነሳት ትውልድ አረም እንዳያበቅል ይረዳል። 
 
ከሁሉ በላይ ሥራወቻችን ሁሉ ትውልድን ለማብቀል ካለው አቅም ሊመነጭ ይገባል ባይ ነው። #የሚቻለውን #የማይቻል የመርግ ክምር ያደረግነው እኛው እራሳችን ነን። #መነሻችን እና መዳረሻችን ያለማወቅ። ትውስት፦ ውራጅ ልጥፍ ስለ አጓጓን።
 
በኢትዮጵውያዊነት በኢትዮጵያኒዝም ማዕቀፍ ውስጥ ትውልድን አስተካክሎ ማብቀል የሚያስችል ሁለመና አለን። አንዱን ብጠቅስ #በራስ #የመተማመን #ክህሎት። እራስን ሆኖ እንደራስ ለመኖር እንደራሴነትን መፍቀድ ከብዙ ቀጫጫ ሰው ሰራሽ ዝለቶች፤ ፍርሻወች፤ ዝብርቆች፤ ብልቅልቆች መዳን ይቻላል። 
 
በነገራችን ላይ እዚህ በአገረ ሲዊዘርላንድ በራስ የመተማመንን አቅም የሚኮተኮቱ ኳቾች አሉ። ለሰዓት በሲዊዝ ገንዘብ 164.00 ይከፈላል ለምክር አገልግሎት። የእኛ አርበኛ አቨው እና እመው ደማቸውን አፍሰው፤ አጥንታቸውን ከስክሰው በዓለም የጥቁሮች ታሪክ ቁንጮ ያደረጉን ሚስጢረ ነፃነት።
 
 ዛሬ ስለ እነሱ መመስከረም ባዕለ ሥማቸውን ማድረግ ማዕቀብ ተጥሎበታል። የበታችነት ገዢ ሆኖ ስለወጣ።
የሚገርመው እኛነታችን የሰጠን ሚስጢረ ፍሬ ነገር ይፈራል። ይሸሻል። ይዋረዳል። ይቃለላል። ዛሬም ወደ ራስነት ጉዞውን አልጀመርነውም። ከእኛ በኋላ ከተፈጠሩ አገሮች ምጽዋተኛ ነን። ዛሬም የራስን መሰደድ ምርጫችን አድርገነዋል። የራስን መሰደድ እምለው ምንድን ነውን መመለስ ስንችል ይቆማል። 120 ሚሊዮን ህዝብ ስደት ላይ ነው? ለምን? መሪወቹም፤ መዋቅሩም፤ አይዲወሎጂያቸውም ስደት ላይ ስለሆነ። 
 
ምንድን ነው #ኦሮሙማ?
?? ኢትዮጵያዊነት #ሃይጃክ አድርጎ የበቀለ የጦሮ አራሙቻ። በዚህ ውስጥ የኢትዮጵውያዊነት ያልተፃፋ ድንጋጌወችን ጣሾችም የኦሮሙማ ፈቃድ አጋፋሪወች መሆናቸውን ማወቅ ይገባቸዋል። ለምሳሌ ካነሳሁት አንጠልጥሎ መጥራትም ኢትዮጵያዊነትን መሸራረፍ ስለመሆኑ ሊከተብ ይገባል። 
 
ዘለፋ፤ ሽብር፤ ማስደንገጥ፤ አንጠልጥሎ መጥራት፤ መዋሸት፤ የታሪክ ንጥቂያ፦ የክብር ሽሚያ እና መዋደቅ፤ ኢጎ፤ ዕብለት፤ ጭካኔ፤ የሰው እርድ፤ ቅርስ እና ውርስን ማንደድ፤ ለጥፋት ምክንያት መሆን ሁሉም የኢትዮጵንያዚም ትሩፋቶች አይደሉም። ሲቃጠል አብሮ መቃጠል፤ ሲወድም አብሮ መውደምን አለመመዘን ዕብንነት ነው።
 
ስኬት ለእኔ የተሻለ ትውልድ ፈጥሮ እራስን መቻል ነው። በጢስ እና በአመድ ፋክክር ስኬት የለምና። እርዕሰ መዲና የሌላት አገር ላይ ምን ዓይነት ኃላፊነት እና ተጠያቂነት ያለው ትውልድ ይፈራ ይሆን???
እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
መሸቢያ ውሎ አዳር ተመኜሁ በትሁት ተስፋ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
25/07/2023
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።