እሳት እና ውኃ የአቨው የእመው አውራ ጥበብ።

 

ሳት እና ውኃ የአቨው የእመው አውራ ጥበብ።

"የሰው ልብ መንገድን ያዘጋጃል

እግዚአብሔር ግን አካሄዱን ያዘጋጃል።"

(ምሳሌ ፲፮ቁጥር )

 

#ዕፍታ ለሰላምታ።

እንዴት አደራችሁልኝ ክብረቶቼ? ኑሩልኝ። አሜን።

እንዴት አደርሽልኝ ክብሬ እናት አገሬ ኢትዮጵያ?

ኑሪልኝ። አሜን።

#ጠብታ

ነዷል። እንደዚህ ሁነት የቅኔው ዕንቡጥ ዶር ቴወድሮስ ካሳሁን ጥቁሩ ሰውን አሳትሞ በዓለም ኦሎንፒክ እንዲገኝ ከዓለም ዓቀፍ ድርጅት ጋር ንግግር በጀመረ ጊዜ ጃዋሪዝም እንዳቆጠቆጠ፣ ጃራይዝም አገርሽቶበት በኦነጊዝም ሲያጎራ በዬፓልቶኩ በነበረበት ወቅት እንደነበረው ነው ምድሪቱ ቋያ የሆነችው። ሰርክ መንገብገብ፣ ሰርክ መለብለብ፣ ሰርክ መገረፍ፣ ሰርክ መታመስ።

ቅድስት አገር፣ የተመረቀች አገር፣ ብሩክ አገር፣ ሁሉን የሰጣት አገር መፈጠሯ የሚጎረብጣቸው፣ መኖሯ የሚቆረቁራቸው ኃይሎች ጊዜ እዬጠበቁ፣ ወቅት እዬጠበቁ ሰላሟን፣ ቅድስናዋን፣ ታሪኳን እንዲህ ይዘቀዝቁታል። እንዲህ ያብጠለጥሉታል።

ሞትን አጭተው ሞትን ይድሩበታል። ግጥግጡ፣ ቅልቅሉ ሞት እና ውርዴት ነው። የበቀለ ሲነቀል፣ የለማ ሲወድም። የሞላ ሲፈስ ዘመን ተዘመን በአላደገም ሲዳካር በሰው ግብር ብቻ መንዘላዘል። ክብር ሆኖ። ማዕረግ ሆኖ።

#አታሞው ከድንጋይ #በላንቃ

ዛሬ ሁሉም ትቢያ መልበስ አለበት። ሁሉም #በሻሻ መሆን አለበት። ሁሉም ሻሸመኔ፣ አጣዬ፣ ዝዋይ መሆን አለበት። ሁሉም አመድ ዱቄት መሆን አለበት ተብሎ ዘመቻው መውደም ነው። ዘመቻው መክሰል ነው።

ፋክክሩ መጥፋት ነው። እራሱን በራሱ የሚያጠፋ ትውልድ የተፈጠረባት ምድር - ኢትዮጵያ። ሁሉ እሳት ነው። ሁሉ ነዲድ ነው። ሁሉ ሹግ ነው። ሁሉ ነበልባል #ላንቃ ይተፋል። ተው የሚል የለም። ሃግ የሚል የለም። የሃይማኖት አቨው፣ ሊቃውንት፣ ሊሂቃን፣ የአገር መሪ ሁሉም ባለ #ክብሪት ባለ #ነዳጅ

ውኃ የያዘ #ወላ ኃንቲ። ምንም። ውኃ ቀዝቃዛ የያዘ የለም። ተግ የሚል የለም። ሁሉም ማጋጋም - ማጋጋል - ማፋፋም ማባባስ፣ የባሰበትን ቦታ ሄዶ መቆፋፈር ነው። በለው -- ቀርድደው -- ቀጥል --- አቀጣጥል --- ጨርስ --- ድፋው ከንብለው --- የአንተ --- ጀግንነት --- ይበልጣል --- በቃ ይህ ነው የተያዘ --- የተረዘዘው ከበሮ ድልቂያ።

ይህ ደግሞ አከረረው፣ ጨመረው፣ አባሰው እንጂ የቀነሰው ነገር የለም።

#ለምን?

ቀዝቃዛ ውኃ ይዞ የሚረጭ የለም? ቁራኑም፣ ወንጌሉም መዳኜት አልቻሉም። ህገ - መንግሥቱም ያው ተጋጩ፣ ተለያዩ ውህድ አይደላችሁም ባይ ነው። የዬፓርቲወች ፕሮግራሞችም የአሻቦ መጠቅለያ መጋዚን ያህል አቅም አላገኙም።

እንሆ ……

በምድሪቱ አናርኪዝም ነገሰ። እናም ውስጤ በጣም ፈራ።

ለተፀነሱት ህፃናት ፈራሁ።

አልጋ ላይ ላሉ ህሙማን ውስጤ ፈራ።

ለነፍሰጡር እናቶች ውስጤ ፈራ።

መንገድን ተማምነው ጎዳና ላይ ለወደቁ ወገኖቼ ፈራሁ።

ለአቅመ ደካማ ረዳት ላጡ የዕድሜ ባለፀጋ ወገኖቼ ሰጋሁኝ።

ነገን ለሚጠብቁ ታዳጊ ወጣቶች በእጅጉ ፈራሁኝ።

ለኢትዮጵያ #ህይወት ፈራሁኝ።

ለብሄራዊ ሰንደቄ ፈራሁኝ።

ለአሳረኛው የአማራ ህዝብ ፈራሁኝ ኮሽ ባለ ቁጥር ጦሩ ለእሱ ነውና።

በቁጥራቸው አናሳ ለሆኑ የማህበረሰብ ወገኖቼም ሰጋሁኝ።

የተለያዬ ዕምነት ለሚከተሉ ቁጥራቸው ጥቂት ለሆኑትም ፈራሁኝ።

አዬሩን ፈራሁት።

እሳር ቅጠሉን ፈራሁት።

ወንዙን ጋራ ሸንተረሩን የአገሬን ሳማትር ፍርኃት ፍርኃት አለኝ።

መኖሬን ፈራሁት።

#የቀደምቱ ድንቅ ጥበብ ዊዝደም።

የቀደሙት አቨው እናትን ያቆዮዋት ሁሉም በእኩል ደቂቃ፣ በእኩል ሰከንድ #እሳት ሆነው አይደለም። አንዱ እሳት ሲሆን ሌላው ውኃ፣ ከውኃም አልፈው #በረዶ በመሆን ነው።

ይህ አሳቻ ዘመን ግን እንደዛ አይደለም።

መጠጊያ የለም ሁሉም ሳማ ነው።

ሁሉም አበርባራ ነው።

ሁሉም ይለባለባል።

ሁሉም ይጋረፋል።

ሁሉም ያቃጥላል።

ሁሉም ያንገረግባል።

የመጠጊያ ያለህ ያሰኛል።

የት እንግባ የትን እንድረስ ያሰኛል።

ሁሉሙ ጡፏል።

ሁሉም ተቀጣጥሏል።

#ኤሌትሪክ ነው በዬቦታው የተያያዘው። ይህ ትውልድ አያተርፍም። ፈፅሞ! ቢያከስል እንጂ።

#ጥፋት እና ጉዞው

እዩት ለዩክሬዬን የበለፀጉት አገሮች በሥነ - ልቦና በመሳሪያ ያስታጥቃሉ። ግን የዩክሬናውያንን ነፍስ የታደገ የለም። 5 ሚሊዮን በላይ ተሰደዋል። የሞቱትን፣ አካል ጉዳቶኞችን ሳይጨምር። ሥልጣኔያቸውን ሳይጨምር። ደጋፊወቻቸው የደረሰባቸው የለም።

ይህ ለዩክሬናውያን የሚገባቸው 30 ዓመት በኋላ ይሆናል። ይህ የሆነው ፕሬዚዳንታቸው አንድ ቃል ማውጣት ተስኗቸው ነው። የጦር ቃል ኪዳን አገር አባል ባይሆኑስ?

አያችሁ ማስተዋል ሳት ሲል ያለውን ጥፋት። እኛም ማስተዋላችን በጠራራ ጠሐይ እንዳወጣ ለፖለቲካ ነጋዴወች ሽጠን ለውጠን አለቅን። ለአንድ ለዶር አብይ አህመድ ሥልጣን ሲባል ኢትዮጵያ ልትጠፋ ነው።

#የሰይጣን ጆሮ ይደፈን እና።

ኢትዮጵያ እሷ ከጠፋች ሃይማኖት ይኖራል?

መስጊድ ቤተ እግዚአብሔር ይኖራልን?

መቀበሪያ ብትን አፈር ይኖራልን?

አዲስ አበባ ላይ 7 ዓመት በኋላ አፅማችን ማረፊያ የለውም። ወጥቶ ተቃጥሎ ወይ ደቆ ማዳበሪያ ይሆናል? በዚህ ውስጥ የሃይማኖቶቻችን ቀጣይነት ይታያችኋል የእስልምና ይሁን የክርስትና?

#ቁርጡ

መጠጊያ የለም። በውጭ የምንገኝ እራሱ ዜግነት ስንጠዬቅ መልስ አይኖረንም። ምንም። እናስተውል። ዝልዝሉን እናቁም። መናሻችን እንወቅ።

ለመድረሻ መነሻን ማወቅ ይገባል። በሁሉም ነገር ቅደም ተከተል አለ። በሁሉም ነገር ሲነሪቲ አለ። #የቀደመን አክብሮ ደረጃን አውቆ መኖር ከተከታይ ይጠበቃል። ይህ የማስተዋል ጥበብ ነው። ይህ ብልህነት ነው።

ለአንድ ሰው ሥልጣን ተብሎ አገር የመሠረቱ ህዝቦች፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ ሊደረመስ አይገባም። አገር የሚመሠረተው በቀደመ ህዝብ፣ በቀደመ ቋንቋ፣ በቀደመ ሃይማኖት ነው።

ይህም ሆኖ ለአዲስ ሥልጣኔ እንኳን ደህና መጣህ ብሎ ለተቀበለ ህዝብ እና አገር፣ ለኢንተግሬሽን የምሥራችን ያጋራ ህዝብ እና ሃይማኖት ሊሸለም፣ ክብር ሊሰጠው ሲገባ እሳት፣ ወቀሳ፣ ነቀሳ፣ ማሳጣት አይገባም። ብልህነት ይጎድለዋል።

ዳኝነት ይጎድለዋል። ፍትህ ያንሰዋል። ፈጣሪም አላህም ያዝናል። በቸገረ ወቅት፣ ግራ በገባ ጊዜ፣ ያዘነ ቤት ለእንግዳ ያለ፣ በሩን አድርጎ ብሎ ለተቀበለ፣ ለግልጽ እና ቀጥተኛ ቅን ህዝብ፣ ዕውቀትን በቅንነት፣ በልግሥና ለመገበ፣ ለፈወሰ አይገባም። ዘመቻው ትክክል አይደለም። ከሁሉ ከሁሉ ፈጣሪ ይከፋዋል።

እንደ ቀደምቶች ልዑቅ አቨው እንሁን ውኃ የያዙ ሰልፎች ይበራከቱ። እሳቶች ዞር በሉ። እባካችሁን ክሉልን። አታቀጣጥሉ። አትወኩ።

ሰላም ለኢትዮጵያ!

እግዚአብሔር ይስጥልኝ።

ሰናይ ውሎ። ለሁላችን። አሜን።

ሥርጉተ©ሥላሴ

Sergute©Selassie

29/04/2022

29/04/2022

ውሃማ ጊዜ ያሰኜኛል!

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።