መወላለቃችን አሁንም አልታዬንም።

 

 

 
መወላለቃችን አሁንም አልታዬንም።
"የሰው ልብ መንገድ ያዘጋጃል
እግዚአብሔር ግን አካሄዱን ያቃናለታል።"
(ምሳሌ ፲፮ ቁጥር ፱)
ገና ከመነሻው ፍላጎታችን #ባለቤት አልነበረውም። እንወጣዋለን ለእኛ ተውት ያሉትም መተንፈሻ ሲያገኙ ካለአቅማቸው ነበር እና ኃላፊነቱ አላቀቀን ብለው የአራጅ አባሪ ገባሪ ሆነው አረፈቱ።
ለመሆኑ #አይዋ ትግል የአሁነኛው ሥምህ ማን ይባል ይሆን? ለፍትህ? ለነፃነት? ለርትህ? ለዴሞክራሲ እንዳትለኝ እና ቁጥቧን ሳቄን እንዳታፈነዳት።
እራሱ አሁናዊ ትግሉስ ቀለሙ፣ ጣዕሙ፣ ቁመናው ማን ይሰኛል? ለመሆኑስ ብሄራዊ ታጋዩስ አለን? ማነው ባለቤቱስ? ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ እንደ ፍጥርጥርህ ተብሎ የተሰጠው አደራ ነፍሱ አለን? ትንፋሹ ብን ትር ትላለች #የአሻግሬ ማሸጋገር?
ምን የተያዘ? ምን የተጨበጠ ነገር ኖረን? ከአንድ እርቦ #የሚርነት ማዕረግ በስተቀር። ለዛስ #ሥልጣኑ ወይንስ #ደሞዙ ይሆን ያለው? እንጠይቃለን። ጥያቄውም አያልቅ እኛም አይደክመን?
ለመሆኑ አሁን እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የቀረን፣ የተረፈን ኢትዮጵያዊ ተቋም? ክብር? ልዕልና? አለን። ደፍረን እንናገራለን? ተስፋ ደረጃው የት ላይ ይሆን? አፈላልጋችሁት ታውቁ ይሆን አባ ወራ የአገር መሪነት እጮኛ የነበራችሁት።
ከዘመን እስከ ዘመን የተሰው ሰማዕታት ተነስተው ቢጠይቁን መልስ አለን? በተለይ ሁሉንም ጨፈላልቃችሁ #አውራ ነን፣ እኛ ህይወት እና መንገድ ነን ላላችሁ ሰብዕናወች ተኝታችሁ ማደራችሁ ይገርመኛል።
እንቅልፍ ይወስዳችሁ ይሆን? ስንት ቡቃያ አዝላችሁ፣ ነቅላችሁ እንዲህ አገር #አረም ሲበቅልባት። ሙሉ ትውልድ ከተስፋው ሲነቀል፣ ከተስፋው ሲቆራረጥ፣ በተበተነ ሃሳብ ሲታጨድ፣ ጎዳና ላይ ሲወድቅ።
#የተረፈን ነገር አለን? #አለን የምለው ነገር አለን? ኢትዮጵያን ካለ #ርዕሰ መዲና፣ አፍሪካን ካለ #መናህሪያ በስምምነት ሸኝታችሁ በግብረ ሰላም አታሞ፣ በቡና ሻይ ሴሪሞኒ? ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ ስንት ኪሎሜትር ገብታ ግንባታ እዬገነባች? ሉዓላዊነታችን በጠራራ ጠሐይ ተደፍሮ።
ትግራይን ኦሮምያን ተሸኝተው፣ ደቡብን ብትንትኑ ወጥቶ፣ አማራ እና አፋር አፈር፣ ትቢያ ታቅፈው። የሰጣችሁት አቅም እና ጉልበት የሰራችሁት ፍኖተ ካርታ አማካሪነታችሁ ለዚህን ነበርን?
አቅም፣ በገፍ የለገሳችሁት ድጋፍ #አጥንት ሆኖ ይወጋል ወይንስ ሞዝቦልድ ሆኖ የከረባት እና የገበርዲን ሲሳይ ሆኗል? ልጅስ ያወጣልን?
ዝም ብላችሁ እሰቡት ምን እንዳለን። ባልተከፈለ ዕዳ የተሠሩ ፕሮጀክቶች አመድ ሆነዋል። ዕዳው ግን አለ። ተከፋፍሎ፣ ተከፋፍሎ ቢና ጢናው ካልወጣ የቀጣዩ ትውልድ ያልበላው ዕዳ ተሸካሚ ነው።
ይህ ደላችሁ ይሆን? ያሻግሩናል ብላችሁ ከፍ ዝቅ ስትሉ የቆያችሁ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ አንጋፋ የፖለቲካ መሪወች፣ ሚዲያወች፣ በግል ልዩ እገዛ ምክር የሰጣችሁ ኤክስፐርቶች ሁሉ በእጃችሁ አለን የምትሉትን እስኪ ንገሩን።
አራቱ ዓመት በደም ጽዋ ተጠናቆ አምስተኛውም እዬነጎደ ነው። አተረፋችሁ ወይንስ ከሰራችሁ?
ጥያቄዬ ለድል አጥቢያ አርበኞች ወይንም በቅርቡ የፖለቲካ ድርጅት ለፈጠሩት ፖለቲከኞች አይደለም። ለገዘፋት የኢትዮጵያን በትረ ሥልጣን ይመኙ ለነበሩት፣ ለዛም ለታተሩት፣ ስለ እነሱ ሲባልም ስለ ሰማዕታቱ ነፍስ ነው እምጠይቀው።
መቼ ነው #እምትፀፀቱት?
መቼ ነው #ንስኃ እምትገቡት?
መቼ ነው #ይቅርታ ጠይቃችሁ ሻጋታ ትርኪ ምርኪያችሁን ይዛችሁ እግሬን አውጫኝ የምትሉት?
ይህ በኢህአዴግ ውስጥ ላሉ፣ ለነበሩ፣ በኢትዮጵያኒዝም ውስጥ እናታግላለን እንመራለን ብለው ለኦነጋዊው ጃራይዝም ተስፋችን አሳልፈው የሰጡትን ነው የምጠይቀው።
የራሳችሁን ዕድል በራሳችሁ ለመወሰን የሚያስችል ዕሳቤ አመንጩ። አዲስ ሰውኛ ሃሳብ። እና ይህን ድሪቶ፣ የዛገ፣ የወዬበ ዘመን ታግላችሁ ለቀጣዩም ትውልድ፣ ለራሳችሁም ነፃነትን ዕውጁ። የእኛ ብክነት ይበቃል። የእኛ የድካም ብትልና ይበቃል። ለዕድላችሁ ሁነኛ ሁኑለት።
በአረጀ፣ በመከነ፣ ባረጠ ፍልስፍና መዳን የለም። የፈጠሩት እንኳን በዛ ውስጥ የሉም።
እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
02/05/2022
ወጣቶች ሆይ! ዕድሜያችሁን አታዘርፋ!

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።