ፖለቲካ ሰው ነው።
ፖለቲካ ሰው ነው።
ኦ! ይህ አባባሌ ፈላስፎችን እንዳያስቆጣ ሰጋሁ። ስጋት በልኩ ጥሩ ነው። ህግ ተላላፊነትን መመከት ስለሚችል። ማስማማትም ይቻላል።
እንዲህ … ፖለቲካ ለሰው የተሠራ የአስተዳደር፣ የአመራር፣ የአደረጃጀት ሥርዓታዊ ሰበነክ ፍልስፍና ነው።
እርግጥ ነው ሰው እና ተፈጥሮ በሚያገናኛቸው ጉዳዮችም አስተናባሪ ጥሩ ሊጋባ ነው ፖለቲካ። የሆነ ሆኖ ማዕከሉ ሰው ነው። ፖለቲካውን ሳይረዱ ዘው የሚሉ ነፍሶች ግን ያሳዝኑኛል። የቀጠሮ ስለሆኑ።
ለምን ብትሉ ማህል ቤት ተቋርጠው ስለሚቀሩ። ሲገቡ ሜዳው አይበቃቸውም ያዙኝ ልቀቁኝ ነው። ሲወጡ ደግሞ ድብዛቸው አይገኝም። እግር ጣላቸው እግር ሸኛቸው።
የሚገርመው ከባህር የወጣ አሳ ስለሚሆን ብቅ ጥልቅ እያሉ ማተራመስም ይኖራል። እንደ ወራጅ ወንዝ አይቶ መተው ነው። ፖለቲካ በቃህኝ የምትለው አይደለም።
በእያንዳንዱ የህይወት መሥመር እንደ ሃሳብ አብሮ ይኖራል። ልዩነቱ በነቃ ህሊናዊ ወይንም ባልነቃ ህሊናዊ ክፍል መወራኜቱ ብቻ ነው።
ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ ስለ ዘዌዎች ችግሩ ያለው በሚቆዩበት ወቅት የሚያተራምሱት፣ የሚያምሱት፣ ባልወለደ አንጀታቸው ሰቅስቀው የሚደፋት ሃቅ እና ለዛ መስሎት የሚማገደው፣ ኑሮው የሚታወከው፣ ሰላሙን የሚያጣው፣ አምኖ የሚቀቀለው ነፍስ ዕልፍነቱን እሰቡ እና እግር የጣለው ታጋይ ባሰኜው ሰዓት ሲሾልክ ባክኖ የሚቀረውን የትውልድ ዕጣ ፈንታ እሰቡት። ኪሳራው ታያችሁ? የሚደቀው የሰው ልጅ የመኖር ዕጣ ፈንታ ነው።
ራዕይ ብለህ አቆላምጠው፣ ዓላማ ብለህ አሽበልብለው፣ ግብም ብለህ ቀሽረው ልማታዊም በለው፣ ማህበራዊ ፍትህ ማዕከሉ ሰው ነው።
በሰው ውስጥ መኖር አለ። ፖለቲካ ሰውን ለማኖር አኗኗሪ ጥበብ ነው። ሰው ከሌለ ድርጅት የለም። መንግሥት ህንፃ አይደለም። የሰዎች የተማከለ የአመራር ሥርዓት ነው መንግሥት።
ስለሆነም በጠናና፣ በወልጋዳ፣ በኮረኮንች፣ በቡላማ መንግሥታዊ ሥርዓት ውስጥ የሰው ልጅ ሰቆቃ ይቀናለታል፣ በተስተካከለ መንግሥታዊ ሥርዓት ደግሞ ሰውን፣ ተፈጥሮን ማዕከል ያደረገ ስለሆነ ሰው በመከበር ውስጥ ይኖራል። መስዋዕትነትም ግጭትም ቢኖርም የቀነሰ ነው፣ ፍፁማዊ ምድራዊ ዓለም የለምና።
እንደ ፕሬዚዳንት ዶናል ትራንፕ አያያዝ አሜሪካ አትኖርም ነበር ሥርዓቱ በማይናወፅ ተቋማት ባይገነባ። ለዚህም የዜጎች ጥበቃ በሙሉዑነት አለ።
ስለዚህም የሰው ልጅ ፅናታዊ ትግል እራሱን ካለስጋት ለማኖር የሚችል ዋስትና ሰጪ ሥርዓት በቋሚነት ታግሎ ከሚያታግል አቅም ጋር በስክነት መጓዝ ይጠይቃል። መሰናዷዊ ውሳኔ የራስ ነው። ለዛ እንጂ ለግለሰብ የአርኬብ የዝና ክምችት መትጋት በቃህ ሊባል ይገባዋል ነው የፁሁፌ ጭንቅላት።
ካጎፈረውም፣ ካጎረፈውም ጋር ሳይጋልቡ በራስ ዕውነት ውስጥ መዝለቅ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
20.06.24
ሰውነት ሥርዓታዊ አመክንዮ ክፍሉ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ