#አዲስ #አበቤወች።
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ወደ ሥልጣን እንደመጡ ንቅል ብሎ የደገፈው አዲስ አበቤ እንጂ ኦሮምያ አልነበረም። ጉራጌ እንጂ አዲስ አበቤ አልነበረም። ደቡብ አዋሳ ላይ እንጂ ኦሮምያ አልነበረም። ድፍን አማራ ክልል እንጂ ኦሮምያ አልነበር። ለአመል አንቦ ላይ ጥቂት ነገር አይተናል። አካሉን የገበረ ግን አዲስ አበቤ ነበር። ዙሪያ ገባ የሚቀቀለውም #አማራ።
ጳጉሜ መግቢያ ግንቦት 7 አገር ሲገባም፤ ሌሎችም ተጽዕኖ ፈጣሪወች ሲገቡ አዲስ አበቤ ለጋስ፤ ቅን እና ህብራዊ ስለሆነ #ፏ ብሎ ብሄራዊ ሰንደቁን ተጎናጽፎ ኢትዮጵያ በውስጡ መስጥሮ ሳይሆን ቀን ወጣልሽ ሳቂልኝ ብሎም እንግዶቹን አክብሮ አልቆ ተስፋ ሰንቆ ተቀበለ። እናቱን እምዬን ውስጡ አድርጎ።
ከዛ በተበታተነ ሁኔታ የነበረው ማህበረ ኦነግ በመስከረም አምስት 2011 ዓም ኢትዮጵያ ገባ። ኢትዮጵያን ድል አድርጎ የገባ ይመስል ነበር። ምድሪቱ በኦነግ የፖለቲካ ድርጅት ዓርማ #ተጥለቀለች። መሬትን ለመርገጥ የተጠዬፋ የተንሳፈፋ ቄንጠኛ ፖለቲከኞችንም አስተውያለሁ። ዛሬ ስደት ላይ ናቸው አቶ በቀለ ገርባ። በውነቱ ከሩቅ ቦታም የመጡ ስለነበሩ አዲስ አበቤ በተለያዬ ሁኔታ #ቢዋከብም አክብሮ በፍቅር ተቀበለ።
አቀባበሉ በቡራዩ ንፁኃን የደም አላባ ነበር። በድምጽ የተመረጠ በድምጽ ሥልጣን የተሰጠው ኦህዴድ #ቡራዩ ላይ፤ ሻሸመኔ ላይ በኢትዮጵያ ታይቶ የማይታወቅ ይፋዊ ጭካኔ ፈፀመ። በተከታታይም ለገጣፎ ለገዳዲ፤ ሰንበታ የሚኖሩ ነዋሪወች አራስ ቤቷ በላዮዋ እዬፈረሰ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቀሉ። በርካታ ወገን ተፈናቀለ።
ያን ጊዜ አንድ የለገጣፎ ትንሽዬ ተማሪ ትምህርት ቤት አልሄድም ብሎ ሲጠዬቅ ስመለስ ወላጆቼን ከቤቴ ላጣ እችላለሁ ብሎ ነበር። ጠቅላይ ሚር አብይ ሲጠዬቁም እኔ የከተማ የሠፈር አስተዳዳሪ አይደለሁም የሚል ዕድምታ ያለው ንግግር አደረጉ። አልሰማሁም ብለው ካዱ። አዲስ አበባ እኮ ሲያሰኛቸው አስኮባ ይዘው ይጠርጉ ነበር ያን ጊዜ። ዘይትም ያከፋፍሉ ነበር።
#የሆነ ሆኖ።
ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉት ቅኑ፤ ገሩ፤ የዋሁ፤ በግሎባል የሚያስበው፤ #ሥልጡኑ የአዲስ አበባ ህዝብ ለወገኖቹ ደረሰ። ለእርዳታ ተጣደፈ። ባተለ። ተጋ። ወዲያው #ንፁህ 5 ወገኖቻችን መሐል አዲስ አበባ ላይ በግፍ ተጨፈጨፋ። ጋዜጠኛ ካሳሁን ይልማ እዬተከታተለ ይዘግብ ስለነበር ሙሉ መረጃው ይኖረዋል።
የእነኛ አምስት ንፁኃን ቤተሰቦች የት እንደደረሱ የሚታወቅ ነገር የለም። ጠቅላይ ሚር አብይ በወቅቱ ሲጠየቁ ታቅዶ በመንግሥታቸው ለተፈፀመው ጭፍጨፋ #ለለውጡ #እንደ #ተከፈለ #መስዋዕትነት ቁጠሩት ሲሉ ተሳለቁ። ተሳለቁ እምለው ሙሉ አምስት ዓመት ለእነኝህ ንፁኃን የሆነ መታሰቢያ ተሰርቶ ስላላዬሁ ነው። ቤተሰባቸው፤ የሟቾቹ ሥም ዝርዝር እንኳን አይታወቅም። ሞታቸው እንኳን ክብርም ዕውቅናም አላገኜም። ለማህበረ ኦነግ የልብ አድርስ አቀባበል በበቀል ቁርሾ ለዛውም ንፁኃንን።
አይጠይቃቸውም። ጭራሹንም ዕውቅና አልተሰጣቸውም። በኋላ ላይ ባልደራስ ሲነሳ፤ ሲተጋም #አላስታወሳቸውም። 5ቱ ሟቾችም ደመ ከልብ፤ ታሳሪወችም ጠያቂ አልባ ሁነው ካቴና በልቷቸው ቀረ። አስታዋሽ የላቸውም። ጠያቂም የላቸውም። ባሊህ ባይ የላቸውም። ከሚጮኽላቸው እስረኞች ዝርዝር የሉም። አንድም ቀን ከቁጥር ገብተው አይጮህላቸውም ውጭ አገርም።
ባልደራ እራሱ ትዝ ብለውት አያውቅም። እነኝህ ሩሁሩኃን አሁን አሁን ሳስበው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እና አማራ ግን ኢትዮጵያን ከልባቸው የሚወዱ ስለሆነ ይመስለኛል እንዲህ ስደት ላይ እንዳሉ ኢትዮጵያዊ እስረኞች ተረስተው የቀሩት። አንድም ሚዲያ፤ አንድም ሰብ፤ አንድም የፖለቲካ ድርጅት አስቧቸው አያውቅም።
#ወጣቶች ሆይ!
እባካችሁ ለዕድሚያችሁ፤ ለቀጣይ ተስፋችሁ እያሰባችሁ ተራመዱ። አዲስ አበባ ለምን ብሄራዊ ሰንደቋን ለብሳ እንግዶችን እንኳን ደህና መጣችሁ አለችን በቀል የተቀበሉ ግፋዓን ጠያቂ፤ ዕውቅና አልባ በዚህ ሁኔታ ይገኛሉ። ይህን በጥልቀት ስታዩት ኢትዮጵያኒዝም ባለቤት አልባ እንደሆን፤ አዲስ አበባም ተቆርቋሪ የፖለቲካ ድርጅት እንደለላት ትገነዘባላችሁ።
እነኝህ ወጣቶች በግንቦት 7 ሰበብ ቢታሰሩም የአዲስ አበባ ነኝ ያለው ባልደራስ የግንቦት 7 አመራር አካላትን ሲረከብ ዲያስፖራ ላይም ትርታው በዛው ሲገነባ ስለምን እነኝህን ግፋዓን ሊያስታውስ እንዳልቻለ እንቆቅልሽ ነው።
አያችሁ ወጣቶች በፖለቲካ ድርጅቶች ፋክክር ውስጥ ባለ ዝብሪትም መስዋዕትነታችሁ እንዲህ ባክኖ እንደሚቀር እሰቡት። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ወቅት ይመሠርታቸዋል አብዛኞቹ ምርጫ ሲደርስ፤ ወይንም የተጋጋለ ነገር ሲፈጠር በስሜት ቲፍ ብለው ይመሠረታሉ። ወቅት ያሰናብታቸዋል። ሲያሰናብታቸው ተከፋፍለውም ነው። ጭድ የሚሆነው ግን #ትውልዱ ነው። ዕድሜው እንዲህ የሚዘረፈውም።
የአድዋ ድል በአዲስ አበባ፤ የካራማራ ድል በአዲስ አበባ ሲከበር የሚሳተፋ አዲስ አበቤወች እዬታፈኑ፤ እዬተደበደቡ፤ እዬተሠወሩ ብዙ መከራ እንዳዩ ይሰማኛል።
ምክንያቱም አዲስ አበባ ውስጥ በግል መኖሪያ አፓርትመንት እስር ቤቶች እንዳሉ፤ ወለላቸው ደም ብቻ እንደሆነ፤ ቦታውን ተለይቶ እንደማይታወቅ ከዚህ ቀደም ታሥረው የተፈቱ ጋዜጠኞች እና ፀሐፍት ገልፀዋል። እኛ የምንጮኽው ሁለት ፍሬ በሥም ለሚታወቁት ብቻ ነው እንጂ በሥም የማይታወቁ በርካታ ወገኖቻችን ኢትዮጵያን ብለው ተገብረዋል።
የሚገርመው ለሚቀጥል፤ ለትውልድ ለሚሆን የፖለቲካ ድርጅት ቢሆን ምንም አይደለም። አንድ ኢትዮጵያኒዝምን ይዞ #አንጃ ሳይፈጠር፤ ሳይከፋፈል የዘለቀ የፖለቲካ ድርጅት የለም። ትውልዱ ግን ሙሉ 50 ዓመት ምራቅ ለሆነ የድርጅት ፍላጎት እራሱ ሳይፀና #አረግርጎ ለሚረግብ የፖለቲካ ድርጅት ተገበረ።
ወጣቶች ሆይ! በማስተዋል ሆናችሁ፤ ስሜታችሁን አረጋግታችሁ፤ ለመኖር መፈጠራችሁን አስልታችሁ ሊሆን ይገባል የፖለቲካው ተሳትፏችሁ። ሺ ብሬን ደስአለኝን ዛሬ ማን ለቤተሰቧ ይደርሳል? ወጣትነት የነፃነት ፈላጊነት ተስፈኛ መሆኑን ባውቅም መስዋዕትነታችሁ ከንቱ ሆኖ እንዲህ ሲቀር ግን ያሳዝነኛል።
እሰቡበት። እንደ ሃይማኖታችሁ ፀልዩበት። አንድ የፖለቲካ ድርጅትን ስትደግፋ - ስትሰውም። ማን አለኝ ለእኔ? ማንስ አለው ለቤተሰቤ ብላችሁ? የምትከፍሉት መስዋዕትነት እና ለእናንተ የሚሰጠው ዕውቅና ምንም ነውና።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
24/06/024
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ