ኢትዮጵያን ቁም ነገር የማድረግ ዓላማ መሪነትን ይመትራል።
ኢትዮጵያን ቁም ነገር የማድረግ ዓላማ መሪነትን ይመትራል።
መሪ ለመሆን የፀና ተጋድሎ ይጠይቃል። በአንድ ምሽት መሪነት አይወለድም ይፀነሳል እንጂ። መሪነት በአጃቢ ብዛት ሳይሆን በሃሳብ ጥራት ፍሬ ነገር ይለካል።
መሪነት ኢትዮጵያን ቁም ነገር ለማድረግ ከመቁረጥ ይነሳል። ከኢትዮጵያ ቁጥር አንድ ጠላት ጋር ፀበለ ፃዲቅ ጀምረህ ኢትዮጵያን ቁም ነገር ለማድረግ እራሱ ሃሳቡን ማሰብ አይቻልም።
አገር ለውለታ አይሸጥም አይለወጥም። በአገር ጉዳይ ላይ መሪም ቢኮን እንደ እኔ እንደ ተርታዋ ዜጋ አንድ ድምፅ ብቻ ነው ያለው። ኢትዮጵያ አገራችን አይደለችም የሚሉ የመብትም የግዴታም ታዳሚ አይደሉም።
አሁን ያለው የኦሮሙማ ሥርዕዎ መንግሥት ትንፋሹን ማስተካከል ያልቻለ ስለሆነ በአገር ውስጥም፣ በውጭም ባሉ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች መታቀብ አለበት። ኢትዮጵያን ለኤርትራ ጥገኛ ማድረጉን ጨምሮ።
ኤርትራ የወትሮ አካላችን የዛሬ ጎረቤታችን ናት። ኢትዮጵውያን ቁርሾኛ አለመሆናችን ዓለም መስክሮታል። አገር መሆን ፈልገው አድርገውታል። ተከባብሮ መኖር ያባት ነው። ነገር ግን ሆድ ዕቃ እንዲሆኑ ማድረግ እና ማስደረግ ግን ውርዴት ነው።
የሚታዩ ነገሮች ቸር ወሬ አይደሉም። አገር በራሷ ብቁ ልጆች እንጂ በሞፈር ዘመት ጉርድነት ልትመራ አይገባም። ይህ ሊስተካከል ይገባል።
ዩፖለቲካ ድርጅትህ ስለሚፈልገው ብቻ ውስጥን አውልቆ መስጠት ለልዑላዊነት የተከፈለውን መስዋዕትነት አጥንት ከመቃብር አውጥቶ አንድዶ መሞቅ ነው።
ይህ እኛን አይገልፅም። ይህ እኛን አያብራራም። ይህ እኛን አይተነትንም። ይህ እኛን አይተረጉምም። ይህ እኛን አያመሳጥርም ወደ እራሳችን እንመለስ። ቅኝ ተገዢነት አይናፍቀን። ለሉዕላዊነታችን ለተሰውት ጥቃት አውጪ እንሁን። መንፈሳቸው ይረግመናል።
በእኛ ውስጥ እኛ እንኑር። በእኛ ውስጥ እኛን እንሁን። በዚህ ውስጥ ለኩት መሪዬ የምትሉትን? በእኛነት ውስጥ አለ የለም? መሪነት የቅልሞሽ ጨወታ አይደለም። እንድርቺ እንድርቺም አይደለም። ላሜ ወለደችም አይደለም።
መሪነት በስኬት ልክ ነው ሊሠፈር የሚችለው። በሂደት ውስጥ የትውልድ የሆነ የዘለቀ ቁምነገራዊ ተቋም መሪነትን ይገልፀዋል። በመፍረስ እና በማፍረስ ውስጥ መሪነት አይኖርም።
መሪነት ቀውስ ጠራኝም አይደለም። መሪነት እዩኝም አይደለም። መሪነት አወድሱኝም አይደለም። መሪነት ጉግሥ ግጠሙልኝም አይደለም።
መሪነት ትውልድን በሰከነ መክሊቱ ልክ ለማስቀጠል የሚያስችል ረቂቅ የመሆን እና የማድረግ ጥበብ ነው።
መሪነት ከራስ በላይ አገርን ማክበር ነው። መሪነት ከወገብ በላይና በታች የሽብሽቦ ቅርጫ አይደለም። መሪነት ሰውን መውደድ በሰው ልጅም መወደድ ነው።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
የትውል የሆነ መሪ ይናፍቀኛል። ያፈራን የማያደርቅ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ