«በጠለምት በናዳ የተቀበሩ የሁለት ሰዎችን አስክሬን ለማውጣት ሲሞክሩ ከነበሩት የ7ቱ ሕይወት አለፈ" bbc
https://www.bbc.com/amharic/articles/c0mnprenz00o
«በጠለምት በናዳ የተቀበሩ የሁለት ሰዎችን አስክሬን ለማውጣት ሲሞክሩ ከነበሩት የ7ቱ ሕይወት አለፈ"
26 ነሐሴ 2024
"በአማራ ክልል፣ ሰሜን ጎንደር ዞን፣ ጠለምት ወረዳ አብና ቀበሌ በናዳ የተቀበሩ የሁለት ሰዎችን አስክሬን በመፈለግ ላይ ከነበሩት የ7ቱ ሕይወት ማለፉ ተገለጸ።
የወረዳው አስተዳዳሪ ጋሻው እንግዳው ለቢቢሲ እንደገለጹት የሰባቱ ግለሰቦች ሕይወት ያለፈው ባለፈው ዐርብ ነሐሴ 17/2016 ዓ.ም. አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ ባጋጠመ የመሬት መንሸራተት በመኖሪያ ቤታቸው ሳሉ በናዳ የተቀበሩ ሰዎችን በመፈለግ ላይ ሳሉ በድጋሚ በተከሰተ አደጋ ነው።
በአደጋው እናትና ልጅን ጨምሮ የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የጠቀሱት አቶ ጋሻው፣ ክስተቱ ባጋጠመበት ወቅት የልጁ አስክሬን ወዲያው ሲገኝ የሁለቱ የቤተሰብ አባላት አስክሬን ግን ሳይገኝ እንዳደረ ተናግረዋል።
በማግስቱ ቅዳሜ ነሐሴ 18/2016 ዓ.ም ጠዋትም የሁለቱን ሰዎች አስክሬን ለማውጣት የተሰባሰቡ ከ18 በላይ የሚሆኑ ዘመድ አዝማድና የአካባቢው ነዋሪዎች ለፍለጋ በተሰማሩበት ወቅት ድጋሜ በተከሰተ ናዳ የሰባቱ ሰዎች ሕይወት አልፏል ብለዋል አስተዳዳሪው።
በአደጋው ከሞቱት በተጨማሪም በስምንት ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።
በሁለቱም አደጋዎች ከሞቱት መካከል የአራት ሰዎች አስክሬን የተገኘ ሲሆን የቀሪዎቹ አለመገኘቱንና ፍለጋውም መቋረጡን አቶ ጋሻው ተናግረዋል።
“ መሬቱ ስላልረጋ ሌላ አደጋ ይከሰታል በሚል ስጋት አስክሬን ፍለጋው ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆም ተደርጓል። ወደ አካባቢው ሰዎች እንዳይሄዱም የፀጥታ ኃይል አሰማርተናል” ብለዋል።
በተያዘው የክረምት ወቅት በደቡብ ክልል፣ጋሞ ጎፋ የደረሰውን አስከፊ አደጋ ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች መሰል ክስተቶች አጋጥመዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጋሞ ጎፋ ዞን ሐምሌ 14/2016 ዓ.ም የደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ከ250 በላይ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉ ይታወሳል።
በአደጋው የሞቱት አብዛኛዎቹ መጀመሪያ ባጋጠመው አደጋ ናዳ የተጫናቸው አራት ሰዎችን ለማውጣት በማግስቱ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ ሰዎች መሆናቸውን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
በናዳው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተቀበሩ ቢሆንም ትክክለኛ ቁጥራቸው እስካሁን አልተገለጸም ።
በጠለምት እንዲህ አይነት አደጋ ሲያጋጥም ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የገለጹት አቶ ጋሻው፣ የአደጋው ምክንያት ከሰሞኑ እየዘነበ ያለው ከፍተኛ ዝናብ ሊሆን እንደሚችል ገምተዋል።
በአደጋው በሰው ሕይወት ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ 35 የቤት እንስሳት በናዳው ተውጠው እንደቀሩና በሰብል ላይም ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉንም አቶ ጋሻው ገልጸዋል።
የመሬት መንሸራተቱ በአጠቃላይ ከ260 በላይ ሔክታር መሬትን እንደሸፈነ የገለጹት አስተዳዳሪው፣ ሌላ አደጋም ሊከሰት ይችላል በሚል ስጋት ከ2 ሺህ 400 በላይ ነዋሪዎች ከአካባቢው እንዲነሱ መደረጋቸውን ተናግረዋል።
“ ከሚኖሩበት 5 ጎጦች የተፈናቀሉት ነዋሪዎች በቀበሌው ውስጥ በሚገኙ ተቋማት ውስጥ እንዲጠለሉ ተደርገዋል።ጊዜያዊ መጠለያ ለማዘጋጀትም እየሰራን ነው” ብለዋል።
በቅርቡ በሰሜን ጎንደር ዞን በሚገኙ ሌሎች ወረዳዎችም ተመሳሳይ አደጋ ማጋጠሙን የአካባቢው ኃልፊዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የዞኑ የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ ፈንታ ተረፈ እንደተናገሩት በጃናሞራ፣ አዲርቃይ እና በየዳ ወረዳዎች በተከሰተ የመሬት መንሸራተት የ13 ሰዎች ሕይወት አልፏል።»
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ