ሴቶች #ተገደው #ሲደፈሩ #በዓዋጅ ነውን???

 

 
"የቤትህ ቅናት በላኝ።" 
 
 
ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በሕፃን ሔቨን ጉዳይ ጠንከር ያሉ ውይይቶች እዬተካሄደ ነው። በተለይም "የሴታ ሴት ፓወር" የሚባለው አዲስ ሃሳብ የያዙ ወጣት ሴቶች ሙግቱን በቲክቶክ ፎርማት ተጠቅመው ጠንክረው ይዘውታል። ሰብሳቢዋ ወ/ሮ ቤተልሄም አካለወርቅ ወጣት ትንታግ ናቸው። ከሀሌታ ሚዲያ ጋር የነበራቸውን ቆይታ ክፍል አንድን እና ሁለትን አዳምጫለሁኝ። በሚዲያው እና እሳቸው በሚመሩት ሃሳብ ዙሪያ የነበረውን ክፍተት ግራ ቀኙ ያስተካከሉት ይመስለኛል። የቅሬታቸውንም መሠረት አስቀድሜ አዳምጨው ስለነበር ውይይቱ ግልጽ ነበር ለእኔ። 
 
"የሴታ ሴት ፓወር" ሰብሳቢ ወ/ሮ ቤተልሄም አካለወርቅ በህፃን ሔቨን ጉዳይም ከእዮሃ እና ከአርተስ ጋር የነበራቸውን ቆይታ አዳምጫለሁ። የእኔን የወጣትነት ጊዜ አስታውሶኛል። በዚህ ሃሳቤ እኔን በወጣትነት የሚያውቁኝ ወገኖቼ ይስማማሉ። በውነቱ እራሴን ነው ያዬሁባቸው። ማለፊያ ነው። የህግ ባለሙያወችም ቁጥብ በሆነ መልኩ ጉዳዩን የእኔ ብለው እዬተነጋገሩበት ይገኛል። ይህም ወሸኔ ነው። በሌላ በኩል ሚዲያ ላይ ያሉ ወገኖችም እንዲሁ ጠንከር ባለ ሁኔታ እዬተወያዩበት ነው። ይህም ይበል የሚያሰኝ ነው። 
 
በጠቅላላ ግሎባል ንቅናቄውና ግብረ መልሱ አበረታች ጅምር ነው። በሴቶች ጉዳይ ብዙ መጣጥፎችን ጽፌያለሁኝ። መዋለ ዕድሜያችን በፈተና ዘልቦ ስለሚጠናቀቅ። አደራጅም ስለነበርኩኝ ብዙ በጣም ብዙ አመክንዮወች የውስጤ ናቸው። 
 
ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ ይህ ክስተት #አስፈሪም #ነውርም ስለሆነ መቆም ስላለበት በተከታታይነት ሊሠራበት እንደሚገባ ይሰማኛል። ሲጨልም መንቀሳቀስ አለመቻሉን ያዩ ቀደም ሳይንቲስቶች መብራትን ፈለሰሙ ችግሩ ነው መፍትሄ ያመነጨው። ከእያንዳንዱ አዲስ ግኝት ጀርባ #አጤ ችግር አንቱ ነው። አስተዋዮች፦ ተመራማሪወች፦ አትኩሮተኞች ችግሩን ከውስጣቸው ሆነው ያጠኑታል። በቀጣይ ለችግሩ መፍቻ መንገድ ያሰላሉ፤ ይመራመራሉ ይፈለስማሉ። 
 
የህፃን ሔበን ጉዳይም በተደጋጋሚ የሚታዩ ፍፁም #ነውር የሆነውን ብሄራዊ ችግር መፍቻ መንገድ መቀዬሻ አዲስ የአዲስ ጎዳና ምህንድስናን የሚጠይቅ አመክንዮ ነው። ብልህ ሰው ችግር ለምን ተከሰተ ሳይሆን ከችግሩ እኔ ምን እማራለሁ? ተምሬስ ለችግሩ እንደምን መፍትሄ አመነጫለሁ ብሎ ያስባል። እንኳንስ የአንድ አገር ብሄራዊ መንግሥት። ስለሆነም በትናንቱ መጣጥፌ እንደገለጽኩት ለችግሩ የተሰጠውን ግሎባል ዕውቅና ተጠቅሞ ችግሩን በዘለቄታ ሊፈታ የሚችል የመፍትሄ አማራጭ መተለም ይገባል።
 
ይህ በዚህ እንዳለ የተከሳሽ ቤተሰቦች ባለቤት /// ወንድማቸውን ጨምሮ ሚዲያወች እያነጋገሩ ነው። ሌላ ጉዳይ ቢሆን የበዳይም የተበዳይ ቤተሰብን አነጋግሮ ዕውነትን ማፈላለግ ይገባል። ይህ ግን #ተመስጥሮ የሚከወን፤ በዓዋጅ #ዕወቁልኝ ተብሎ መለከት የማይነፋበት በመሆኑ የበዳይን ቤተሰብ ጋብዞ አውጫጭኝ መስራት በፍፁም የተገባ ነው ብዬ አላምንም። ተጨማሪ ነውርም ነው። በህጋዊ ጋብቻ እንኳን ተፈቅዶለት ግን በተባው የባህላችን፤ የሃይማኖታችን ሥርዓት በወግ እና በማዕረግ ተመስጥሮ የሚከወን ነው። እንኳንስ ይህን መሰል የጭካኔ ጥቃት። 
 
መብት እኮ ሥርዓት አለው። ድንጋጌም አለው። ግዴታም እንዲሁ። የደፋሪ ባለቤት ባለቤታቸው ህፃን ሔቨንን ልደፍር ልሄድ ነውና #መርቀሽ ላኪኝ ሊሏቸው ነውን? በሌላ በኩል የደፋሪ ወንድምን ደፋሪው ወንድማቸውን ልደፍር ልሄድ ነው እና #ቡራኬውን አስቀድምልኝ ሊሉ ነውን??? ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ከፋክት ጋር ውጊያ የሚገጥም ጎዳና ነው ሚዲያወች የተጠቀሙት። ነውርም ነው። ድርብ በደልም ነው። እደግመዋለሁ ነውርም ነው። 
 
ይህን ምክንያት አድርጎ የኢትዮጵያ መንግሥት ሊሠራው ያሰበው ጉዳይ ካለም #ጫና መፍጠርም ነው። መሰናክል መሆንም ነው። ብዙ ሳይነገሩ ተዳፍነው የተቀመጡ ስንት ዕውነቶች አሉ??? በሌላ በኩል የሚሊዮንን የህፃናት ሴቶች ተስፋም #ማጨለምም ነው። ግፍም ነው። እደግመዋለሁ ግፍም ነው።
 
እንኳንስ ይህን መሰል ጭራቃዊ ድርጊት ቀርቶ በኖርማል ህይወት በዐዋቂወች ዘንድ ከትዳር በላይ ሌላ ሴት ጋር ሲኬድ በዓዋጅ አይደለም። ፈፅሞ። እጅግ ተመስጥሮ፤ አዩኝ አላዩኝ ተብሎ ተሸሽጎ ነው። ምክንያቱም ቁልጭ ያለ ህግን #የሚደፈጥጥ ወንጀልም // ሃጢያትም// ፀያፍም ስለሆነ። 
 
በዚህ ልምድ ያካበቱ ጩሌለወች ከትዳር በላይ ህግ ተላልፈው ልጅም የሚወልዱ አሉ። ያ ልጅ በማህበረሰቡ፤ በቤተሰቡ ላይ የሚፈጥረው ጫና ከባድ ነው። ትዳሩ ሊፈርስ ይችላል። በሌላ በኩል ልጁ በማያውቀው ጉዳይ "ዲቃላ" እዬተባለ ሙሉ ዕድሜውን በማንነት ቀውስ ውስጥ ሲሰቃይ ይኖራል። 
 
ለአቅመ አዳም ሲደርስም ትዳር መሥርቶ ለመኖር በጣም ነው የሚያቅተው። ደፍሮ ለመጠዬቅም #ፈሪ ነው የሚሆነው። የሥነ - ልቦና ተጠቂ ስለሚሆን።
እንኳንስ እጅግ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ የሚደፈሩ ህፃናት የሞት ጽዋ መቀበል ቀርቶ። የገረመኝ ጉዳዩን ለአደባባይ ያበቃው ሚዲያ የተከሳሽ ቤተሰብን ጠይቆ ከተበዳዮዋ ወ/ ሮ አበቄለሽ በላይ ተመልካች አግኝቷል። 
 
የሠራውንም ታላቅ ምዕራፍ አደብዝዞታል ብዬ አስባለሁኝ። ቁጥሩን ነው ያዬሁት። ለማዳመጥ ፈቃደኛ ስላልሆንኩኝ። ሌላም እማከብረው ሳብስክራይብ ያደረኩት ሌላ ሚዲያም የበዳይን ወንድም ቃለምልልስ እንዳደረገ እሱንም እርዕሱን ነው ያዬሁት። ለማዳመጥ ጊዜ ማባከን አልፈለኩም። ምክንያቱም የአመክንዮ አንባጓሮ መፍጠር ጥሪዬ አይደለም እና። 
 
እያንዳንዱ ሰው እህት/ አክስት/ ሴት ልጅ ባይኖረው #እናት አለው። እናት በምድር ውስጥ አቻ የማይገኝላት ፍጡር ናት። በእሷ የሰቀቀን፤ የሲቃ ዕንባ ውስጥ ሙሉ #ውስጥን ማስቀመጥ አለመቻል መበደል ነው - ለእኔ። ፍ/ ቤቱ እኮ ወንጀሉን አምኖበት ቅጣት በይኗል። ይህ ማለት በዳዩ ወንጀለኛ ነው ማለት ነው። 
 
ይግባኝ መጠዬቅ መብት ስለሆነ መብት ተጠይቆበታል። ይህ የህግ አግባብ ቢኖረውም ተመስጥሮ ለሚከወን ነውር አብረው የወሰኑ// ያስፈፀሙ ይመስል ቤተሰቦች #አልፈፀመም ብሎ ሙግት የሚገርም ኮሳሳ ገጠመኝ ነው። ሃፍረትም ነው። ይህ ድርጊት እጅግ ፀያፍ፤ እጅግ ነውር፤ እጅግም ሃራም ሆኖ ቤተሰቡ ደግሞ ይህን ጉዳይ አቃሎ እና አሳንሶ የወንድሜ// የባለቤቴ ስሜትን መሪ እኔ ነኝ ማለት የተገባ አይደለም። ስሜቱ ሊጠና ይገባል። ገፊ ምክንያቱም። 
 
ምክንያቱም #በከፍተኛ #ጥንቃቄ #ተመስጥሮ የሚከወን #ነውረኝነት እና የወንጀሎች ሁሉ #ቁንጮ ስለሆነ። ሁሉም ሰው #እናቱን ሊያስብ ይገባል። ሁሉም ሰው ነገ እናት፤ እህት፤ አክስት ልትሆን የምትችልን #ሴት ልጅን ከውስጡ ሊያስብበት ይገባል። እስኪ ወንዶች ብቻ የሚሠሩትን ፊልም እዩት። ቃና ማና የለውም። ክው ብሎ የደረቀ #በድን ነው። ካለ ሴቶች ዓለማችን ድቅድቅ ጨለማ ነው። 
 
የህፃን ሔቨን ጉዳይ የሚሊዮኖች ድምጽ ስለሆነ ዕድሉን በአግባቡ ማኔጅ ሊደረግ ይገባል። ለመፍትሄ የሚቀርቡ አገራዊ እርምጃወችንም ይሻል። ሕፃን ሔቨን በሰማዕትነት ብታልፍም ሰማዕትነቷ ግን እንደ ቀደሙት ቅዱሳን ሊታይ የሚገባው ባይ ነኝ። መስዋዕትነቱ ቅብዓ እንዳለው እረዳለሁኝ። ለእኔ የተለዬ ትርጉም የሰጠኝ የዘመናችን #ክስተት ነው ባይ ነኝ። ታምቆ የቆዬ ፍላሎት ነው ቀን የሰጠው። የህሊና ዳኝነቱ ከተከፋ ጎን መቆም ነው እንጂ በዳይን ማባበል፤ ማቆላመጥ የሚገባ አይመስለኝም።
 
ምን ፍርድ ቢሰጥ ትረኪያለሽ? ብትሉኝ ይህ የእኔ ሳይሆን የተከበሩ ዳኞች ተግባር ነው ብዬ እመልሳለሁ። ህግ ዕውነት ከገዛው። ህግ መርኽ ካስተዳደረው። የዳኞችን ፍትሃዊ ብቻ ሳይሆን ርትኃዊ ብያኔ እጠብቃለሁ። ለእኔ በፍትህ እና በርትህ መሃል ልዩነት አለው። ርትህ መንፈፃዊ የጽድቅ ጎዳና ነው ብዬ አምናለሁ። ፍትህ ግን ለገኃዱ ዓለም የእርካታ አንባር ነው ብዬ አምናለሁኝ። 
 
ተመስጥሮ ለሚከወን በደል በሌግዠሪ ቃለ ምልልስ ፍትህ ሊዛባ አይገባም ባይ ነኝ። ሌላ ወንጀል ቢሆን ግን የከሳሽም // የተከሳሽም ቤተሰብ ስሜት መጠዬቁ እና ሚዛን ለማስጠበቅ መሞከሩ ብዙም አይከፋም። የነውር መጨረሻ በሆነ ግፍ ላይ ግን የአዬር ጊዜ ማባከን በራሱ #የክፋ #ሃሳብ ተባባሪነት ነው ብዬ አምናለሁኝ። ቢያንስ ወላጅ እናቷ ለምን ጫና በዛባቸው ብሎ ማሰብ እንደምን ያቅታል??? ለምን መኖሪያ ቀያቸውን ትተው ተሰደዱ???? ይህ በራሱ እኮ በቂ ምስክር ነው።
 
ህፃን ሔቨን የመፍትሄ ንቅናቄ #ውክል #ዓርማ ናት። መደፈር፤ ጥቃት፤ ፍትህ፤ ጥበቃ፤ Vergewaltigen, Angriff, Gerechtigkeit, Schutz. 
 
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ኑሩልኝ።
መልካም ምሽት። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
27/08/2024
#ነፃነት ለኢትዮጵያ #ህፃናት!
#ህፃናትን አስገድዶ መድፈር በህግ ይታገድ!

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።