#በቁሙ #ቀብር #ላይ #የዋለ #ብትክትክ እንኮሸሽሌ #ዕሳቤ።
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"

Anchor Media ''ጦርነቱ ቢጀመር ደስ ይለኝ ነበር። ...ከዚያን በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ እፎይታን ያገኛል'' ፕ/ር መሀመድ ሀሰን»
ይህቺ አገር ኢትዮጵያ ስንቱን ዝክንትል ዕሳቤ፤ ስንቱን ድሪቶ ምልከታ፤ ስንቱን ስቃይ #ጠሪ ዕሳቤ እንደ ተሸከመች አመላካች ነው። እርእሱን በቁሙ ያለ ተርጓሚ ስታነቡት። ጥገኝነትን ተጠይፋችሁ አመሳጥሩት። የጦርነት ናፍቆት ለእኔ ጭካኔ ነው። በዚህ ጭካኔ ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን እስቲ አፈላልጉ? ግን ማህበረ ቅንነት እንዴት ናችሁ? ከሠራተኛ መሪነት፤ ከሊቃውንትም፤ ከዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሥመጥሩነት፤ ከቀደምት የነፃነት ታጋይነት፤ ከመሪነትም ጎራ የሚመደቡት ባለሁለገብ የልምድ ባለቤቱ ፕሮፌሰር መሐመድ ሃሰን በጦርነት "#እፎይታ" ይገኛል ይሉናል። ማን በሚመራው ጦርነት ብላችሁ ጠይቁልኝ በትህትናም። ሎቱ ስብኃት።
ለእኔ ዝርግ ዕሳቤ ነው። ለእኔ ይህ አንካሳ ዕሳቤ ነው። ፍላጎቱ በግራ ቀኝ ቢኖር እንኳን ይህን ኩፍኝ መንገድ ማበረታት፤ ከጃርታዊው ጦርነትም ተስፋን መጠበቅ እርቃኑን የቆመ ምኞት ነው። እርግጥ ነው አጃቢ ይኖረዋል። ለእሳት ማገዶ እንደሚቀርበው። ግን ለትውልድ ፀር የሆነ አጥፊ ዕሳቤ ነው።
ፕሮፌሰር አንድ ጊዜ አንከር ሚዲያ ላይ "ኢትዮጵያ የሚለው ሥያሜ #ባይስማማን ልንቀይረው ተነጋግረን እንችላለን" ሲሉ #እግዚኦ ብዬ ነበር። ጋዜጠኛ አቶ መሳይ መኮነንም እናቱ ማንነቷን ሊገፍ የሚችል እጮኛ ግን ድውይ ሃሳብ ሲፈልቅ አልሞገተም። ዝም ብሎ አሳለፋቸው። እስከ አሁንም ይገርመኛል። ያንዘፈዝፋል ሲቃም ያስይዛል። ድፍረቱ እኮ ልክም የለው።
ሌላ ጊዜ የመለያችን ዓርማ የሆነውን የፋኖ ትግል የኤርትራ መንግሥት አንጡራ ሃብት እንደ ሆነ በዘውዱ ሸው ሲናገሩ ፕሮፌሽናል ጋዜጠኛው ጭጭ ብሎ፦ ቁልጭ ቁልጭ እያለ አሳለፋቸው። ምነው የዘመናችን ዓራት ዓይናማ ሰማዕቱ አርበኛው፦ #ሐዋርያውም ጎቤ ቀና ብሎ ባዳመጠህ እያልኩ ነበር - በውስጤ። የፕሮፌሰሩ ድፍረት ምንጊዜም ይሰቀጥጣል።
ዛሬ ደግሞ "የኢትዮጵያ እፎይታ #ጦርነት ነው" ሲሉ አዳመጥናቸው። በጦርነት ትርፍ አለ ከተባለ #አመድ እና #በቀል ብቻ ናቸው አትራፊወች። በጦርነት የሚገነባ ሥርዓትም ዕድሜው አጭር ብቻ ሳይሆን ቀውስ አምራች፤ የሴራ ማህበርተኛም ነው። ለኤርትራም ለኢትዮጵያም የወል ችግር መፍቻቸው ጦርነት ሳይሆን ቁጭ ብሎ በንፁህ ልብ #በቅንነት መነጋገር ብቻ ነው መፍትሄው።
የሚገርመኝ ፕሮፌሰር የልጆች አባት ሆነው፤ በትውልድ ላይ ጦርነት መናፈቅ #ጨካኝነት ነው። ወልዶ ያላዬ ቢል፦ ወይንም በአንባገነን ሥርዓት ውስጥ መኖሩን ከመሰረተ ስደተኛ ከሆነ ከማን ያዬውን፦ የሰላም ሥልጣኔ ትሩፋት ሊባል ይቻላል። በተቀማጠለ አገር የተቀማጠለ ኑሮን እዬመሩ ክርቢትነትን መመኜት አለመታደል ነው። መካከለኛው ምስራቅ፤ አፍሪካ፤ አውሮፓ በጦርነት ያተረፋት ቅንጣት ነገር የለም። ጦርነት ሥልጣኔን #ሥልጣኔ ያጠፋው ዘንድ የተፈቀደለት ሲኦላዊ መንገድ ነው።
ውጭ አገር ተቀምጦ። ልጆቹን፦ የልጅ ልጆቹን በስስት ውለው እስኪገቡ እያዬ፤ እዬጠበቀ ያ መከረኛ #ስሜነኛ ግን ይማገድ ማለት #የሲኦል ጥሪ ነው - ለእኔ። ፕሮፌሰር ቀደምት ታጋይ ናቸው። የወጣላቸው ፖለቲከኛም ናቸው። ግን በማይመቹኝ ሃሳቦች እንደ ሌሎች ወገኖቼ እኔ ሞግቻቸው አላውቅም። ምክንያት - ነበረኝ። ከዛ በዕት ተገኝተው አዋን በፖለቲካው በትጋት ተሳትፈው፦ ስለምን ቲካ ቲካ በሚል ይሞገቱ በሚል አርቄ አገናዝቤ፦ አስቤ፥ በውነቱ አክብሬያቸው ኖርኩኝ። ቢያንስ እሳቸውን የመቻል #አቅል ሊኖረን ይገባል የሚል የግል ውሳኔ ነበረኝ። አሁን ግን በዛ - ገለማም።
እሳቸው ከኢትዮጵያ ከእራሷ ከልዕልቴ፤ ከኢትዮጵያ በፍጹም ህሊናዬ ከምሳሳለት አዲስ ትውልድ፤ ደግመው ከማናገኛቸው ከኢትዮጵያ ቀደምት የአንጡራ ኃብታት ቅርስ እና ውርስ አይበልጡም። ጦርነት ህግ የለውም። ያ ሁሉ በአንድ ምሽት ትቢያ ሊሆን ይችላል። የዞግ ፖለቲካ ለተጠያቂነት እና ለኃላፊነት በጣም እሩቅ ነውና።
አለመጀመሩ እንጂ ከተጀመረ በጦርነት ውስጥ ዲስፕሊንን የሚጥሱ #አናርኪያዊ ክስተቶች መኖራቸው አይቀሬ ነው። በጦርነት ከታቀደው ጥፋት ይልቅ፦ የማይታቀደው የወል የመንፈስ ድቀት እና #ክስለት ይበልጣል። ግምትም - ስሌትም ሆነ ሬሽውንም ማውጣት የማይቻለው ለረቂቁ መንፈሳዊ የመሰዋዕትነት ክፍለ ጊዜ ነው። ዘመን የማይጠግነው መከራ ነው የጦርነት ሂደቱ።
#ቅንነት የማይፈውሰው፦ ርህርህና ወጌሻው ሊሆነው የማይችል ወዘተረፈ የችግር ክምሮች አሉ በጦርነት ጦስ። ብዙ ሰው የሥነ - ልቦና ተጠቂ ይሆናል። ይህ ተጠቂነት ደግሞ በራስ የመተማመን መቅኖ ስለሚፈታተን የበታችነት ስሜት - ያገረሻል። ይህ ማለት #ፈሪ ትውልድ፤ ጭንቀታም ትውልድ በራስ ይፈበረካል። ይህን ሙሉ 6 ዓመታት ተኑሮበታል፤ በዚህ ላይ ይጨመር ነው የፕሮፌሰሩ ናፍቆት። ሆዳቸው በደረሰው ድቀት ይሁን ውድመት ገና አልሞላም። "በሰው ቁስል ነውና።" ሁሉም የአብራኩን፦ የማህፀኑን ፍሬ ሲያጣ ግን ያውቃታል። ግን የአክተሮችም፤ የአክተር ቤተሰቦችም መኖር በዋስትና ውስጥ ነው።
ፕሮፌሰር ከፈቀዱ የመረጡትን አገር ዜግነት መውሰድ ይችላሉ። ኢትዮጵያን ግን ለጦርነት ማጨት ጭካኔ ነው። በዚህ መሰል ውይይት እማዬው ሁልጊዜ ለሌላ አገር #አድሎነት መዝኖ፦ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ #ተገሎ ወይንም #ድብ ብሎ ነው። ይህ አሳቻ ዘመን ለእኛ ራዲዮሎጂያችን ሆኗል። ማን ምን እንደ ሆነ ግልጥ ሆኗል። ገብያ የሚሰጠውን የእናት ልጅ አይሰጥም ይባላል።
ለዚህም ነው ረጅሙን ጊዜ በጥሞና ብዕራችን የምታሳልፈው። ሰው እርቃኑን ሁኖ እናዬው ዘንድ ዘመኑ ፈቀደ እና ጊዜያችን በአግባቡ ማሰተዳደር ቻልን። አሁን ከሆነ የአቅም ብክነት የለም። የትናንቱ ለማን - ዝምንምን? የነገውስ ለማን ቅብጥ እና ቅልጥ እንደሆን አናውቀውም። አንዱንም የሥልጣን ምኞተኛ፤ አንዱንም ተጽዕኖ ፈጣሪ፤ አንዱንም የሚዲያ ትጉህ አናውቅም። #አንተዋወቅም። ዘመናችን የሰውን ሰብዕና በመገንባት ነው ያቃጠልነው። ኪሳራ! እናምኪሳራ በቃን ካልን ሰነባበትን እኔ እና እትጌ ብዕሬ።
ታምቆ ቢቆይም፦ አሁን ከሆነ በጎረቤታማ አገሮች ሊቃናት፤ በግራ ቀኙ ባሉ ደጋፊ ሚዲያወች ፍጥጫውን አያለሁኝ። አይጠቅምም። ለድኃ አገራት፤ ለኋላ ቀር አገራት ጦርነት ሳይሆን አትራፊያቸው የሰላም ጎዳና ነው። በሰላም ውስጥ ስቆ ጥሬ ቆርጥሞ ማደር ይቻላል። በጦርነት ግን ፍርሰትን እያጣጣሙ መቀለብ ነው። በሰላም ውስጥ መተማመንና ፍቅር አለ። በጦርነት መጠራጠር እና ጥላቻ ነው የሚገኜው።
በሰላም ውስጥ ተስፋ እና ብርኃን አለ። በጦርነት ግን ዋይታ እና እሬሳ ብቻ ነው የሚገኙት። በሰላም ውስጥ ተረጋግቶ ማሰብ፤ መመራመር - መፈላሰም - መሰልጠን ይቻላል፤ በጦርነት ግን ያልተረጋጋ ማህበረሰብን ማዋለድ ነው። ጦርነት ፈቅዶ ዋይታን፤ ፈቅዶ ድህነትን፤ ፈቅዶ መራራ ስንብትን መፍቀድ ነው። ይህን ስል ተገደው ጦርነት የሚገቡትን ማለቴ አይደለም። ጥቃትን መከላከል ተፈጥሯዊ ነውና። የሆነ ሆኖ ፕሮፌሰር ያሉበት አገር ለራሳቸው በቅተው ለእኛ የተረፋን ሰላማዊ ህይወትን በቅጡ ማኔጅ ማድረግ ስለቻሉ ነው። እስከ ቤተሰቦቻችን የሰላምን ትፍስህት የሚቀልቡን ትውልዳዊ ድርሻቸውን በቅንነት እና በትጋት ስለከወኑ፤ ዕድላቸውን በተገቢ ጊዜ እና ሁኔታ ስለተጠቀሙ እራሳቸውን ጠቅመው ለእኛም ተረፋን። ይባረኩ።አሜን።ትልቅሐዋርያነት ብቻ ሳይሆን ነብይነትም ነው።
ስሜን ኢትዮጵያ ከተፈጠረበት ዘመን ጀምሮ የስልጣኔ መሰረትነቱን ሲፈትነው የኖረው ጦርነት ነው። ጦርነት የሚናፈቅ አይደለም። ዲያቢሎስ ሊናፍቀው ይችላል። የሰው ልጅ በፈጣሪ ፈቃድ ሲፈጠር፥ ለሰላም፦ ስለሰላም እንጂ በሰላም ጠርነት አይደለም። በክርስትና ዕምነት ፈጣሪያችን የውስጡን ሰላሙን ትቶልን እንደሄደ እናምናለን። ስለዚህ ለሰላም ስስታም - ነን። ቀናዕይ - ነን። ናፍቆተኛ - ነን። እንዲህ መሆናችን ደግሞ ኃላፊነት እና ተጠያቂነትን አዋህዶ መምራት ይመስለኛል። ጥልቁን የቅዱስ ቁራንን ዶግማ ባላውቅም በየቤተሰባችን ያሉ የእስልምና እምነት የሚከተሉ ወገኖቻችን "እስላም ማለት ሰላም ማለት ነው" አስተምህሮው እያሉ አሳድገውናል። ይህ አስተምህሮ ደግሞ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም።
ኢትዮጵያዊነትን - የሚያወይቡ፤ ኢትዮጵያዊነትን - የሚገፋ፤ ኢትዮጵያዊነትን - የሚዳፈሩ፤ ኢትዮጵያዊነትን - የሚያገሉ ንግግሮች ጥንቃቄ ቢደረግባቸው መልካም ነው። ምክንያቱም ትውልድን ሊገነቡ፤ ሊተኩ ስለማይችሉ። አክሰሱ ላላቸው ታዳጊወችም መንፈሳቸውን ማወክም ነው። እኔ ብጠዬቅ ከየትኛውም አገር ጋር በሚደረግ ጦርነት የሚገኝ ትርፍ እንኳን ቢኖር በአፍንጫዬ ይውጣ። አያስፈልገኝም። እምዬ ሲዊዝ ኦኮ ወደብ የላትም። እምዬ ሲዊዝ የአውሮፓም የኔቶም አባል አይደለችም። ግን ፈጣሪ በዊዝደም ልጆቿ ብቃት ከሁሉም አገር እኩል ሆና በፀጥታ፤ በእርጋት፤ በቀስታ ትኖራለች። ለነገሩ ዓለማችን ዛሬ ሌላ ምዕራፍ ላይ ስለምትገኝ ምኞቱ ተኖ ሊቀር ይችላል። በኖ ሊቀር ይችላል። ፈጣሪ ያድርገው። አሜን።
#ትራንፒዝም ምቹ ጊዜ ለጦርነት ናፋቂወች የሚያድል አይመስለኝም። ለጦርነት የሚውለው መዋለ ንዋይ፦ ስንት ለለት ጉሮሮ ያልበቁ የዓለም ዜጎች ስላሉ ለእነሱ እርዳታ ሊሆን ይገባል። ንፁህ የመጠጥ ውሃ፤ ኤሌትሪክ፤ ቀርቶ ለአልባሳትም ያልበቁ ወገኖች አሉን። አገሮች ለዜጎች መኖር ብቃት ቢኖራቸው እኮ መሰደድ ያበቃ ነበር።
ለጦርነት የሚደረግ ማናቸውም መዋለ መንፈስ ይሁን ጊዜ፦ ገንዘብ በትህትና፤ በቅንነት፤ በቸርነት፤ በሰባዕዊነት፤ በተፈጥሯዊነት ትውልድን ሙሉሰው አድርገው ሊቀርጹ በሚችሉ መልካም ተልዕኮች ላይ ሊውል ይገባል። ይህን የዛሬ 15 ዓመት ተመድንም፤ አውሮፓ ህብረትንም፤ የአሜሪካ መንግሥትንም የጠዬኩበት በኽረ ጎዳናዬ ነው። አይደለም እኛ ላደጉት አገሮችም ጦርነት የትውልድ መቆራረጫ ነው። ሥልጣኔን ሥልጣኔ እንዲያጠፋው ስለምን እንደሚፈቀድ ፈጽሞ አይገባኝም።
እራሱ በጦርነት ዘመናይነቱ የቦንቡ፤ የሮኬቱ ስልጣኔ ለእኔ ምጥ ነው። የፍቅር ተፈጥሮ ት/ቤት፦ ኮሌጅ፦ ዩንቨርስቲ ለምን አይከፈትም። ከዚህም የሚሻገር ምልከታ ነው ያለኝ። የሰውን ልጅ በፀርነት የሚያጠፋ ማናቸውም ነገር ሁሉ ዕቀባ ሊደረግበት ይገባል ባይ ነኝ። ለድንኳን ኑሮ ይህን ያህል የጥላቻ ማምረቻ ፋብሪካ አያስፈልግም።
የሆነ ሆኖ ኢትዮጵያስ፤ ልጆቿስ ምን አደረጉ በየዘመኑ ለማገዶነት የሚታጩት??? ባልተከፈለ ዕዳ የተሰሩ መሠረተ ልማቶችስ ስለምን ይንደዱ????? ለዛውም የኢትዮጵያ ትንሳኤ በጎረቤት አገር ሲታለም??? መጀመሪያ ራሳቸውን ችለው ለህዝባቸው ተስፋ ቀልበው እራሳቸውን ያድኑ። የዬአገራቸውን ትውልድ አስደስተው ይደሩ።
ኢትዮጵያን የሚያድናት ተግማሽ፤ በሩብ ልብ ሳይሆን በሙሉ ልብ ቅንነት እንዲመራ ቢደረግ የብዙ ችግሮቻችን መፍትሄ በመዳፋችን ነው። ህወሃት ፈቅዶ መንበሩን እንዲለቅ ሲደረግ እኮ የፕሮፌሰሩ ሳህል በረኃ መንከራተት አልነበረም ለዛ ድል ያበቃው። ከታናናሾቹ ጎራ ያሉ፦፦ ዝምተኞች በእመ እና አቨው ዊዝደም በሰሩት ትጋት #በተባ ተግባር ነበር። ለዚህም ነው ፍሬዘሩ እንደ ቄጤማ በዬአስፓልቱ ተዝረክርኮ የማይገኘው። "ሙያ በልብ" ስለሆነ።
ለወደፊትም ቢሆን መስመሩ መስዋዕትነትን ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር፦ በሳል ብቃት እና ጥንቃቄ ያለው ተግባር ብቻ ነው። ዘባጣውን አርቆ የሚገራው፤ ሸካራውን - የሚልገው። ባሩድ ትውልድ አይሠራም። መደማመጥ፤ በልክ መጥኖ በአቅም ርጉ ተግባር መከወን ሐዋርያነቱም ሆነ ሰብሉ ለምዕት ይሆናል። ብልጥነትም ለፖለቲካ ህይወት ቁልቁለት ነው። ብልህነት ግን ምሰሶ ነው ለምኞት፤ ለፍላጎት ለራዕይም።
ለመሆኑ ማህበረ - ፕሮፌሰሮች ለኢትዮጵያ ያጩላት "እፎይታ" አጎናፃፊ የፖለቲካ ድርጅት እና ሙሴው ማን ይባሉ --- ይሆን??? መቼም አያልቅ ሥም ይነገረን --- እንደ ማለት። ለዛውም ጦርነቱን መርቶ ለድል የሚያበቃ እሸት ታጋይ እና ሸበላ አታጋይ ሳይኖር በሞገድ ትናንትም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለድል አላበቃም --- ለነገም አያበቃም። ያው የኢትዮጵያ ፖለቲካ የገበርዲን እና የከረባት ስለሆነ ነው። በተባዕት እምጽፈው። እንያችሁ እንደማለት።
ደጎስ ብሎ፤ ደርጀት ብሎ ሳይጠበቅ ከች የሚል እንደ ፋኖ ያለ ልበሙሉ ተጋድሎ ብቅ የሚል ሲገኝም ሙሉ አካላት ያለ ደንበር ዘው ይልና መሪው እና ተመሪው በዝንቅንቅ የሰውን ልጅ ያህል የተሰዋበት ገድል ባክኖ ይቀራል። በኮፒ ራይት ፍልሚያ አቅሙ ይፈተናል። ይህም ብቻ ሳይሆን ገድሉ እና ድሉ ተላልፎ እንደ ሸቀጣ ሸቀጥ በችርቻሮ እና በጅምላ ለሌላ አገር ይሸላለማል። ማህከነ! ትውፊታችን ብቻ ሳይሆን ውስጣችን ፕሮፌሰሩ ለኤርትራ መንግስ ሲሸልሙ ቅጭጭ አላላቸውም።
የጎላ ብቃት ሲበቃቅል፤ ከነበረው ያልነበረው/// ካለልምዱ ገብቶ ቤተኛ ሲሆን ለፍቶ አዳሪው ማገዶው አይሆኑ ሆኖ ይቀራል። የኢትዮጵያ የተስፋ አንባ ሲነሳ ደምቆ፤ መጨረሻው ደግሞ --- ????
የአብይዝም አሳቻ ሥርአት ልሞግተው በብዕሬ እችላለሁኝ። ኢትዮጵያን ግን በምንም - በማንም ሁኔታ ልፈትናት እኔ፦ ለሌላም ለጨረታ አላቀርባትም። ፈጽሞ አይታሰብም። ከዬትኛውም ጎረቤት አገር ኢትዮጵያዊነት እና ኢትዮጵያ ይበልጡብኛል። እናት ለጨረታ አትቀርብም እና። እናት ለመደለያ አትቀርብ እና። ምንም ይክፋት፤ ትጠቋቁር፤ ትክሳም፤ ከዚህም በባሰ አልጋ ላይም ትዋል፦ ኢመርጀንሲ ሩምም ላይ ትሁን፦ እናት ትድክም፤ ቅያሬ የላትም እና። ኢ ትዮጵያ የዓለም ቅኔዊ ዝማሬ ናት። መንፈሷ ጥልቅ እና በሚስጢር ህብራዊነት የዘለቀ ነው። ንግሥቴ ከማንም ከምንም ትበልጥብኝ አለች። ለእሷ ስለእሷ ክብር እና ሞገስ ነው የተጋሁት። የምኖረውም። ከእሷ ዝንፍ የሚለው ሁሉ ዋልሎ ነው የሚቀረው። ሚስጢር ሲፈስ ወናነት ይዋኛል።
ጎንደሬወች ባለ ቅኔ ናቸው እና "ሸማ በየዘርፋ ይለበሳል" ይላሉ። የአብይዝም ሥርዓትን መታገል እና ክብሬን እና ሞገሴን እናቴን መጠበቅ በጣም የተለያዩ አመክንዮወች ናቸው። የመንፈስ እርዳታ እገዛ እንኳን ቢያስፈልግ ኢትዮጵያን የማይቀናቀኑ፤ በእሷ የማይቀኑ እሩቅ ያሉ አገሮች አሉ። እነሱን እንዲረዱ መትጋት ይቻላል።
ለዛውም እጅግ ዲስፕሊንድ የሆነ ቅንነት፤ በእጅ ያለ አቅም በኢትዮጵያ ተፈጥሮ ልክ የሆነ፦ ልብ ሞልቶ የሚያናግር፦ ተደማጭ የሆነ ክህሎት፦ ብቃት ያለው ነፍስ ድርጅት ያስፈልጋል። አገር የተልባ ስፍር አይደለችም። እንኳን ዛሬ ድሮም - አልነበረንም በተፈጥሯዋ ልክ የሆነ የእኩልነት አቅም። የሚሊዮኖች ህልም ግንቦት 7 በነበረበት ጊዜ። ያ ባይሆን ለማህበረ ኢህአዴግ ዕድሉን ሰጥቶ ኤሉሄ ኤሉሄ ባልተባለ ነበር - ዛሬ። በእነሱ ቅንጥብጣቢ እና ቅርጥፍጣፊ ፈቃደኝነት የተጠለለ የለውጥ ፍላጎት እንደ ነበር ነው ዛሬ ላይ እያስተዋልኩ ያለሁት። እራስን ሆኖ፦ እራስን ችሎ መቆም ነው ልብ ሞልቶ የሚያሳቅድ፤ የሚያናግርም። ከግብም - የሚያደርስ።
አይደለም የቡድን በግል ደረጃ እንኳን የሚታይ አቅም እንደ ዘመነ ግንቦት 7 ዛሬ የለም። አገር በጦርነት ወይንም በመፈንቅለ መንግሥት አንድ ነገር ቢደርስባት የወለሌ ገበታ ነው የሚኮነው። በጥልቀት፦ ከኢጎ ጋር ተፋቶ ደጋግሞ በብልህነት ማሰብ ይጠይቃል። ጥንቃቄ ያተርፋል እንጂ አያከስርም። ህወሃት ከደረሰበት አሉታዊ ሆነ አውንታዊ ማናቸውም ክስተት መማር ብልህነት ይመስለኛል። እራሱ ትምህርት ቤት ነው የህወሃት አነሳስ እና የህይወት ሂደቱ።
እራሱን የቻለ፤ በራሱ ሙሉ አቅም የቆመ ምኞት፤ ፍላጎት የመንፈስ እና የፋይናንስ አቅም በመዳፍ ውስጥ ሊኖር ግድ ይላል ለባለ ህልመኛው። ከሁሉ በላይ ታማኝነት። ተማላ ታማኝነት አይደለም። ፍፁም የሆነ የፖለቲካ ታማኝነት ያስፈልጋል ተስፋን ከዳር ለማድረስ። በስተቀር "ወትሮ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ፤ አሁን ምን ያደርጋል ወጪት ………" ይሆናል።
በዬዘመኑ በማይረካ የሊሂቃን የፍልሚያ ሜዳ ምንም የማይደርሰው ትውልድ ነው የሚታጨደው። ቄራው ደግሞ የድምጽ አልባዋ የኢትዮጵያ እናት ማህጸን። በአመዛኙም የአማራ እናት ማህጸን። ለዛውም ለአንጋችነት ብቻ ነው የአማራ ልጅ የሚፈለገው። ለሥልጣኑማ ትውር እንዳይል አስቀድሞ ይታለማል።
ለጨዋታ ማሟያ ሲነሳም የኢትዮጵያን ሊቃናት ሲያንገሸግሻቸው ነው የማስተውለው። በዚህ ዝበቱ ልክ በሌለው ዕሳቤም ምኞትን ማሳካት አይቻልም። ከላይ እስከታች ወይንም ላዕላዩ ይሁን ታህታዩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በጊዜያዊ ሞቅታ የሚረካ፤ ለዘላቂ መሠረት የማይተጋ የእነ ተሎ ተሎ ቤት ነው። በሆነ አጋጣሚ ይፈጠራል፤ በትንሽ የገዥወች ካልቾም ይበረግግ እና ይበተናል። ከሩቁ ጥገኝነት የውስጥን ሰባራ እና ሰንጣራ አጥርቶ መጀመር ይገባል።
ለትውልድ የሆነ ምን ተቋም አለ በፖለቲካ ዘርፍ? በአንጃ ሲንቆጠቆጥ ነው የኖረው። በሥም ብዛት ሲያሸብርቅ ነው የምናውቀው። በውጥኑ ሲጨነግፍ እና ሲከፈል ነው የምናውቀው። የትኛው አስመኪ ተመክሮ ኑሮ ይሆን እንዲህ እና እንዲያ የሚደመጠው። ሁልጊዜ "ጊዜ የለም ነው።" ጥድፊያ እና ሩጫ ……… ቅንጣት መሰዋት ባልተደረገበት የትግል መስመር።
መከወኛዬ አንድ ሐረግ ነው የጨመተ፤ ምራቁን የዋጠ፤ ልቅና በልዕልና ያዋህደ የአማራ ልጅ ኢትዮጵያን ለመምራት ቢወጣ ምን ይሰማችኋል? ውስጣችሁ ምንምን ይለው ይሆን?????? እስቴ ከውስጥ የስሜት ቋንቋችሁ ጋራ ተፈታተሹ። እያንዳንዷ ጉዳይ በግድፈት ተነቅሳ ያለ ምህረት የሚቀጠጠጠው የአማራ የፖለቲካ ልጅ ሲሆን ነው። የሌላው ተነጥፎ፤ ተጎዝጉዞ ጎሽ እንኳንም መጣህልን ነው፦ አይደል??? የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድኽትም ምንጩ ይህ ነው። ዊዝደም ማስተዋልን ይጠይቃል። ይህ ደግሞ ሾልኳል።
ማህበረ ቅንነት ዘለግ ያለ ጊዜ አብረን ቆዬን። ኑሩልኝ። ሸበላ አዳር።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
20/02/2021
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ