ይህ አስደንጋጭ ዜና እና የአማራ ትውልድ እጣ ፈንታ #ግራጫማ ተስፋ።
ይህ አስደንጋጭ ዜና እና የአማራ ትውልድ እጣ ፈንታ #ግራጫማ ተስፋ።
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"





ይህ ቤተሰብ፤ እነኝህ የነገ #አበባወች እንደምን ይሆኑ ይሆን?
በምን ቀመር #ህፃናቱ ተረጋግተው ትምህርታቸውን ይከታተሉ ይሆን?
ህፃናቱ በምን ሁኔታ ካለ አባት #በአንድ ክንድ መኖራቸው ይቀጥል ይሆን?
ለዚህ ቤተሰብ ቀጣይ የመኖር ዕጣ ፈንታ #ዋስትና ሰጩ ማን ይሆን?
የአማራ ትውልድ እና ትምህርት በምን ሁኔታ በተስፋ #ይቀጥሉ ይሆን?
ይህቺ ሸበላ ወጣት፤ ትዳሯን በአፍላ ዕድሜዋ የተዘረፈችስ ቀጣዩን ውስብስብ ፈተና በምን አግባብ #ትወጣው ይሆን?
መርዶውን ከሰማሁበት ቅጽበት ጀምሮ ውስጤ ሙግት ላይ ነው። ሌላ ሥራ መስራት አልቻልኩም። ተስፋ እንዲህ በግፍ እዬተቀበረ ተስፋን ማሰብ ሆነ ማስቀጠል እንደምን ይቻል ይሆን? ከባድ ነው። እጅግ ከባድ።
ይህን ያህል ዘመን የደከመ፤ የለፋ ሊቀ - ሊቃውንት አስፓልት ላይ በባሩድ #ተደብድቦ ነፍሱ ሲነጠቅ የአማራ ክልል መንግሥት አለሁ ሊል ይችል ይሆን? ማነውስ ኃላፊነቱን የሚወስደው? በቀጣይ በዚህ ደረጃ የሚገኙ በዬትም ቦታ የሚኖሩ የአገር ኮከብ የሆኑ የአማራ ልዩ ጸጋ እና ችሎታ ያላቸው ሊቀ -:ሊቃውንት ቀጣይ የሆነውን የመኖራቸውን ሃዲድ እንደምን ያስቀጥሉ ይሆን???
ሆዴ - አብዝቶ ይረበሻል።
በጣም ባርባር ይለኛል።
ነገ በእጅጉ ያስፈራኛል።
ከውስጤ የምጥ ያህል ይጨንቀኛል።
አጀንዳዬ #ትውልዱ ነው። ትውልድ ከሌለ አገርም፦ አደራም የለም። የሰለጠነ፤ በዕውቀት የዳበረ፤ ተምሳሌት የሚሆን አባ ቅንዬን ሩህሩህን ዶር አንዱአለም ዳኜን ያጣ ህዝብ #ነገው ምን ይመስል ይሆን? ያስፈራል። ይጨንቃል። ወላጅ እናቱ ይኖሩ ይሆን? እሳቸውን አያርገኝ? በምንም የማይተካ፤ ድጋሜ የሌለውን የአይን አበባ ማጣት የመቃብር ያህል ይከብዳል።
ከዚህም ከዚያም ስለ ዶር አንዱአለም ዳኜ ደግነት ሊቀ - ትጉኃንነት ሲገለጽ አዳመጥኩኝ። ይህን የመሰለ አቅም ያለው ብቁ - ልቅና #በአደባባይ እናመሰግንኃለን ስለምን አልተባለም? #ጸጸቱ ይህ ነው።ለነገሩ ሙሉ 6 ዓመታት የአማራ ህዝብ ብክነት ጦርነት ላይ ነው። እርግጥ ነው ቅኖች፤ ደጎች በባለቤቱ እና በልጆቹ #መካስ ይቻል ይሆናል። ይህም እርግጠኛ አያደርግም። ምክንያቱም የደህንነት ዋስትናቸው ባለቤቱ ማን ይሆን የሚወስደው??? "#መ" መልስ የለም ስለሚሆን።
ጦርነት አስከፊ ገጽታው ይህ ነው። የምትሳሱለትን፤ የምትወዱትን፤ የምታከብሩትን፤ ለብዙኃኑ ሩህ ቀደመት አገልጋይ የሆነውን፤ ብርቅ እና ድንቃችሁን እንዲህ #በግፍ ይነጥቃል። ጦርነቱን ማን ይጀምረው፤ ማን ያስጀምረው ይህ አንኳር ጉዳዬ አይደለም - #ለእኔ። አስቀድሜ ስለተናገርኩም ፀፀት የለብኝም። ሰሚ ባላገኝም ቅሉ። የሆነ ሆኖ ጦርነት መጀመር እና ማስጀመርን አስመልክቶ በዚህ የሚወራረዱ እንዳሉ አውቃለሁኝ።
በጦርነት ወላፈን አድገን ዕውቀታችን ባክኖ ለቀረው እኔን መሰል ባተሌወች ደግሞ ቁስል እንላለን። ይህ ብቻም አይደለም ለእኔ ወሳኙ ጉዳይ ትውልዱ መኖሩን እንዳይቀጥል፤ መረጋገቱን የነጠቀው ብቻ ሳይሆን፤ የማህበረሰቡ ማገር እና ዋልታ የሆነው #ተወዳጁ፤ #ተናፋቂው የትዳር ፍርሰት እና ማግስት እንደምን ይታረቁም ነው? ብዙ ትዳር ተበተነ። ብዙ መኖር ተነቀለ። ህፃናት በስጋት ውቅያኖስ ውስጥ ነው ያሉት። ይህ ደግሞ በሥነ ልቦናቸው ላይ ሌላ መከራ ነው።
አንዳንድ ጊዜ ከውስጥ ገብቶ የሚረብሽ ሃዘን አለ። የሃዘን የክት እና የዘወትር ባይኖርም። ለህዝብ አገልግሎት ሲባትል መንገድ የቀረ #ዊዝደም ግን የውስጥ #ማህተም ነው። ሃዘኑ ከውስጥ አይወጣም። መወለድ ቋንቋ ነውና። ዛሬ ቀጠሮ ነበረኝ። መሄድ አልቻልኩም። ውስጤ አዘነ። አቅም አነሰኝ። በድምጽም ለመስራት ሞክሬ ተቆራረጠብኝ። ሃዘን ላይ አቅመ ቢስ ነኝና።
ለመሆኑ መቼ ድንገቴ አደጋ ጋር #ኢትዮጵያ ልትፋታ እንደምትችል? ናፈቀኝ። በጣም ናፈቀኝ። #ሃኪም እንዴት ተደፍሮ ይገደላል? መምምህር ላይ እንደምን #ምላጭ ይሳባል? ተመራማሪ ላይ ሰባዕዊነት ላይ እንደምን ይጨከናል??? ምን ዓይነት #መታወር ነው? መጥኔ ለአንቺ ኢትዮጵያ በስንት ዘመን መሰሉን ትተኪ ይሆን? የመዋለ ሃብትሽ - ጊዜሽ - መንፈስሽ ቃጠሎ እንዴት ይሰማሽ ይሆን??? የኢትዮጵያ በየዘመኑ ያለባት ቁልል ዕዳ እኮ ሳይከፈል ነው እንዲህ የአፈር ሲሳይ ዕውቀት የሚሆነው። አርቆ አሳቢ፤ ምራቁን የዋጠ ሰውኛ ሙሴ ኢትዮጵያ አጣች። ተስፋም በምናኔ።
አገር እንዴት #በባሩድ ይደበደባል? አገር እንደምን በቀልኃ #ሳቅ ይፈነድቃል? ይህን መሰል ግፍ የሚፈጸምባት በዕት ስለ ቀጣይ ትውልድ #የምትሰብክበት ምን አንደበት፤ ምንስ ልሳን ይኖራታል? ለአገር ወዳዶቹ፦ አገሬን ላሉ፥ በቀልኃ ተስፋቸውን መቀቀል ማንን ያተርፋል? ወንጀሉን ማን ይፈጽመው - ማን??? የከረፋ ነውረኝነት ነው። ይህ በአገር ላይ የተወሰደ ወንጀልስ መቼ ይሆን ከድራማ ውጪ መፍትሄ የሚያገኘው?
አገራዊ ምክክሩ ድርሻው ምን ይሆን? በአማራ ክልል እርዕሰ መዲና በድንቂት ባህርዳር ይህን መሰል ግፍ ሲፈፀም ድርድር? ንግግር? ውይይት፤ አጀንዳን ማማከል ፋይዳቸው ምን ይሆን??? ከአንድ የፋኖ ክንፍ ጋር ንግግሩ ከኖረስ ለምን የሊቀ ሊቃውንት ህይወት ድውለት ተፈለገ???? አገራዊ ምክክሩ እና ህልሙ ሩቅ --- ለሩቅ አመላካች ነው ለእኔ።
ውዶቼ ታስታውሱ እንደሆነ ከምርጫው በቀደሙ ዓመታት ቀደምት የቀውስ ናዳ ያስተናገደችው ኢትዮጵያ፦ ምርጫው ሲቃረብ ፀጥ #ረጭ ነበር። የቧንቧ ውሃ ሰው ፈልጉ እንደሚከፍተው እንደሚዘጋው። የጫካው የማህበረ ኦነግ ክንፍ፦ ሆነ የቤተ መንግሥቱ የቀውስ መምሪያ ፀጥ ረጭ ብሎ ነበር። አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ዘለግ አድርገው ሳያስተውሉ በሰላም መጠናቀቁ ገርሞናል ሲሉ ውሽክም ብያለሁኝ። የቀውስ ቡፌ እኮ ቀድሞ ስጋትን ሰንቆ ስለተከወነ ነበር። እና አገራዊ ምክክሩ ተጋሁ ባለበት ሰሞናት ይህን እንኳን መልክ ለማስያዝ ከሾሚው አብይዝም አካል ጋር መነጋገር እና ማስወሰን እንደምን አቃተው? ኮሚሽኑ ጦር፦ ጠበንጃ እንደሌለው አውቃለሁ። ዕውቅና እና ዕውቀት ግን እንዳለው እረዳለሁኝ።
የዚህ ብርቱ፤ ትንግርት፤ ከውስጥ በቀላሉ የማይጠፋ ትንታግ፤ #ቫወል የሆነ ንጹህ ዜጋ ነፍስ በአደባባይ ሲሰዋ ዝምታ ለምን መረጠ አገራዊ ምክክሩ? ከቀጠለ ለራሱ ለተልዕኮው ይህን መሰል የጭካኔ አዟሪት እንቅፋት ስለሆነ። ይህም ብቻ አይደለም የትኛውም ተቋም ጠረኑ ሰውኛ እና ተፈጥሮኛ ካልሆነ ሲፈጠር እንደጨነገፈ - ይሰማኛል።
የሚገርመው የብልጽግና ሹማምንቶች ወደ የኢትዮጵያ፤፦የአፍሪካ፤ የዲፕሎማቲኩ ማህበረሰብ መናህሪያ በሆነችው አዲስ አበባ ላይ በተሰዬሙበት ወቅት ነው ይህ አሰቃቂ እና ሰቅጣጭ ግፍ የተፈፀመው። "ብልጽግና ሲዳር ሲኳል" ግጥግጡን እና ቅልቅሉን ሲደልቅ የአማራ ክልል መናህሪያዋ ልዕልት ባህርዳር ግን ማቅ ለበሰች። ይህ እንደምን ታርቆ ነገ ይስተናገድ ይሆን???
አንጀት ቆራጩ ክስተት፤ አሳዛኙ ክስተት፤ መራራው ክስተት ለግርባው ብአዴን ዳጥ ላይ እንደ አለ አመላካችም ነው። ለነገሩ ሲፈጠርም ሙትቻ ሆኖ አይደል።
የገረመኝ የቀብሩ ሥርዓት ጥድፊያ እና እንደ አልባሌ ሰብዕ መከወኑ ነው። ይህ ጥቃት ነው። ይህ ደግሞ መግደልም ነው። ይህ የአማራን ትውልድ መናቅም ነው። ሲጠቃለል ግፋን እንደ ጌጡ ያዬው ግርባው ብአዴን ዘመን - ከዘመን አጃቢነቱ የሞጋሳ ልጅነቱን አጸድቆ ቀጣይነቱ ግራጫማ መሆኑን አመላካች ነው። ቀድሞ ነገር እንደዚህ ላሉ ትጉኃን የደህንነት ተቋማት ምን ይሰራሉ? የማንን ጎፈሬ ያበጥራሉ??? ያቆስላል።
ሌሎች የአማራ ልዩ ፀጋ የተሰጣችሁ ስፔሻሊስቶች መላ አፈላልጉ። መላ ለመላ ተገናኙ። የመጣው ነገር ምጥ እና ምጣት ነው። ከመቀደም መቅደም ያተርፋል። ቢያንስ ለእናታችሁ ለዛች ዕንባማ የአማራ እናት ቀጣይ ተስፋዋ መኖራችሁ ነውና መልሉ። ሌላ የሰማዕቱ ዶር አንዱአለም ዳኜ እናትም ጥንቃቄ ያድርጉ ዘንድ በትህትና አሳስባለሁኝ። ያልተገለጠው የተከደነው ስውሩ አሳቻ ዘመን ተልዕኮ ዓይነቱ ብዙ ነውና።
ፊትለፊት የወጡ የአማራ ትጉኃን እናቶች አደጋ ውስጥ ናቸው። የዶር አንባቸው፤ የአቶ ምግባሩ ወላጆች በተከታታይ ቀናት ነው በሥጋ የተለዩት። የሌሎችም እንዲሁ። ዘመኑ ከእግዚአብሄር በታች ጥንቃቄ ይጠይቃል። #አሳቻ ነውና።
የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች እስኪ ፈጣሪያችን፤ አላኃችን የሃዘን መጨረሻ ያድርግልን አሜን። ለመላ ቤተሰብ ከውስጤ መጽናናትን እመኛለሁ። የማይቻል፤ የማይገፋ መሆኑን ብረዳም።
ቢያንስ እስከ ሳልስቱ በዚህ ዙሪያ ብቻ ብንወያይ ምኞቴ ነው። የፈንታሌ ሚዲያ አዘጋጅን እጅግ አመሰግናለሁ። ውስጡን የገለጠ ንፁህ ቃል ሲናገር አዳምጫለሁኝ። ሰውነት ብቻ የሚጠይቅ ክስተትን እንዲህ በንጽህና መግለጽ የሙያ ግዴታም ቢሆንም።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። ደህና እደሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
03/01/2025
ተስፋችን አምላካችን።
ተስፋችን አላኃችን።
እንጽና ከተጎዱት ጎን እንቁም።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ