ጌታ ሆይ! ተስፋችን ስለጠበቅክልን እናመስግንሃለን!

ጌታ ሆይ! ተስፋችን ስለ ሰጠህን ስለ ጠበቅክልንም እናመሰግንህ አለን።
ከሥርጉተ ሥላሴ 04.07.2018 (ከገዳማዊቷ ሲዊዘርላንድ)
„ለምኑ ይሰጣችሆዋልም፤ ፈልጉ ታገኙምአላችሁ፤
            አንኳኩ ይከፍትላችሁማል።“
(የማቴወስ ወንጌል ምዕራፍ  ፯ ቁጥር ፯)




ጌታ ሆይ! አምላኬ ሆይ! ፈጣሪዬ ሆይ! አንተ ሁሉ የሚቻልህ የሰማይ እና የምድር ጌታ፤ የሰማይ እና የምድር ልዑል፤ የሰማይ እና የምድር ንጉሥ ውስጣችን ስለ ሰጠህን እጅግ አድርጌ አመሰግንሃለሁኝ። ዕንባችን ስላዳምጥክም አመሰግንሃለሁኝ። ጥያቄያችን ስለመለስክም አመስግንሃለሁኝ።

ልዑሌ ሆይ! ህልማችን መዳፋችን ውስጥ ስለ አገባህልንም ተመስገን። አዎን አባታችን ሆይ! ዕንባ ጠራጊ ሙሴ ሰጠህን፤ መከፋታችን ዝቅ ብሎ የሚያዳምጥ ሰጠህን፤ ስለ እኛ ሞቱን የፈቀደ ሙሴ ሰጠህን ተመስገን ጌታ ሆይ!
ንጉሴ ክርስቶስ ሆይ! እንደ እኛ ሳይሆን ስለቀደምቱ ደጋጎቹ፤ በዱር በገደል ክልትምትም ስለሚሉት፤ ስለሚሰደዱት ቅዱሳን ሁሉ ብለህ የይቅርታ በትረ አሮን ሸለምከን።

አምላካችን ሆይ! ላንተ ምን ይሳንሃል? ከሞትም አተረፍክልን። ከመበተንም ታደግከን! እባክህን አምላካችን፤ እባክህን ጌታችን ሆይ! ክፉዎችን አስተምራቸው፤ ማስተዋሉን ስጣቸው። ወደ ልባቸው መልሳቸው። ያ የባከነ ትውልድ ቀጥሎ እናዳይባክን አንተ ሁነኛ ሁንለት ለአሜኑ ለተስፋችን።
ፈጣሪያችን ሆይ! ለዋቢያችን፤ ለዋስ ጠበቃችን፤ ለተስፋችን፤ አንተ አለህለት እንል ዘንድ ያደረግከው ምልክትን በሱባኤ ተቀብለነዋል። ፈጣሪ ሆይ! ስላደረክልን መልካም ነገር ሁሉ አመሰግንሃለሁኝ። ቸርነትን ሰጠህን! ርህርህናን ሰጠህን! ተመስገንን ሸለምከን!

ልዑል ሆይ! ዓይናችን ጠብቅልን! አደራህን! ፈጣሪ ሆይ! ያን ቅን፤ ያን ደግ፤ ያን ንጹህ፤ ያን ባተሌ፤ ያን ሳተና፤ ያን የፍቅር ቅኔ፤ ያን የምህረት ጣዝማ፤ ያን የይቅርታ ተደሞ፤ ያን የመሆን እጬጌ፤ ያን ባከና፤ ያን ታታሪ፤ ያን ምስጉን፤ ያን ትጉህ ጠብቅልን። አደራ!



ፈጣሪ አምላክ ክፉዎችን ወደ ልቦናቸው ይመልስ። አሜን!

ቅኖቹ ጸልዩ ቅንነትን ለማሰንበት እሺ!


የኔዎቹ መሸቢያ ጊዜ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።