ክፍል አምስት - ርትህ።

ርትህ።
ክፍል አምስት።
ከሥርጉተ ሥላሴ02.07.2018
(ከገዳማዊቷ ሲዊዘርላንድ)
„ዪሚያስታርቁ ብፁዕና ናቸው የእግዚአብሄር ልጆች ይባላሉና።“
(ማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፭ ቁጥር ፱)



  • ·         መነሻ።

„ጠ/ / አብይ አህመድ ከአፋር ህዝብ ጋር ያደረጉት ሙሉ ውይይት PM Dr Abiy Ahmed discusses with the people of Afar“

በዚህ ውስጥ የሠማራውን ጉባኤ መዳሰስ የምፈልገው ከ20.38 ባለው ደቂቃ ብቻ ያደመጥኩትን ነው። ቀሪው ክ/ጊዜ ደግሞ ይቀጥላል ማለት ነው። ይህን እማደርግበት ዋናው ምክንያት ዛሬ ያለው የለውጥ ተስፋ እና እኛ ያለን መጣጠም መቀራረብ እንዲኖረው ለማድረግ ነው። ክፍተት ከኖረም መገጠም ስለሚያስፈልገው ነው።
  • ·       ተጠቃሚና ጥቅሙ ትልልፍ።

በዚህ በአፋሩ ስብሰባ የአፋሩ ጉባኤ አልተጠቀምነም የሚል ዕድምታ ቢደመጥም አፋር የተጠቀመበትን ጠ/ ሚር አብይ አህመድ ለማመሳከሪያነት አንስተዋል። አውሮፕላን ማረፊያው እና የተሰበሰቡበትን አዳራሽ እንደ ምስክር አቅረበዋል። ይሄ ከሆነ ስለምን ትግራይ አልተጠቀመም የሚለውን አገላለጻቸውን በዚህ መነጸር ሊያመዛዝኑት እንደማይፍለጉ ብዙም ግልጽ አይደለም ለእኔ።

ብሶትን ለማቀጣጠል ክብሪት መሆኑን መድፈር ባይችሉም ወያኔ ሃርነት ትግራይ ከመጣ በዋላ የተወለዱት ልጆች ሳይቀሩ ደግሜ የተወለድኩ ያህል ይሰማኛል ያሉበት ምክንያት ጥናት ሊደረግበት ይገባል። ከዚህ በላይ በራብ ውስጥ፤ በሞት ውስጥ፤ በመፈናቀል ውስጥ ያለ ህዝብ ከዚህው ሥርዓት ጋር እዬሠሩ ተስፋዬ ብሎ ሊደግፋቸው፤ አይዞህ ሊላቸው የሚፈልግበትን መሠረታዊ ምክንያቱም ከሥረ መሰረቱ ቢመርምሩት መልካም ይመስለኛል። አይደለም እኛ ኢትዮጵውያን ዓለም የሚውቀውን ዕውነት አለዬሁም አልሰማሁም ቢሉ "የቂጣም እንደሆን ይጠፋል የልጅም እንደሆን ይገፋል" መሆኑ አይቀሬ ነው።

እኔም በዚህ ጉዳይ በርካታ ማስረጃዎችን ጽፌ ነበር። የኔውን ልተዎው እና እኔ መሃይም ስለሆነኩኝ ሊቀህቃኑ የሚሉትን ማድመጡ ይሻል ይመስለኛል። ለማገናዘቢያ። በዚህ ጉዳይ ላይ በአንድ ወቅት ዶር ደረሰ ጌታቸው ከኢሳት ከጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ጋር በነበራቸው ቆይታ በተጨባጭ ያቀረቡት ጭብጥ ጣዖት ሳይሆን ፋክት ነው። እኔም የልቤ ያልኩት ሙግት ነበር። መቼም በዚህ ሙግት ላይ ዶር ደረስ ጌታቸው እና ዶር አብይ አህመድ ቢቀመጡ ዶር ደረስ ጌታቸው ያሸንፋሉ። ስለምን ዶር ደረስ መሪ ስላልሆኑ ማቻችል የማይገባውን ጉዳይ ቻል ብለው ስለማያስጨንቁት። የ ኦሮሞ ንቅናቄስ የ አማራ የህልውና ተጋድሎስ ስለምን ፈንቅሎ መድፍ እዬረገጠ ፈነዳ? ስለምንስ የ አመራር ለውጥ አስፈጋ? እኩል የሃብት ክፍፍል፤ ሚዛናዊ አስተዳር እና አያያዝ ቢኖር። ከሁሉ በላይ የሥነ ልቦና እኩልነት በዜግነት ላይ ቢመሠረት። ብቻ ገመናው ብዙ ነው ... 

ESAT Bezih Samint Sisay with Dr Semahegn Gashu and Dr Derese Getachew Fri 25 May 2018


ምንም ካላገኜ ስለምን ይሆን አሁን ከመሪው ድርጅት ጋር ያሉ ነፍሶች ይህን ያህል አዲስ የሞት ዓዋጅ አውጀው የኢትዮጵያ እናቶች የማህጸን ድርቀት የተፈረደበት? ህዝብ እኮ ገና ሚዛናዊ አስተዳደር አለዬም አሁን እኮ ተስፋ ብቻ ነው ያለው። ለተስፋው ይህን ያህል ዕምነት እና ዕወቅና የሰጠው የወያኔ ሃርነት ትግራይ ለተፈጠረበት ማህበረስብ የተለዬ እንክብካቤ አላደረግም በሚል ዕድምታ አይደለም።

ያ ፋሽታዊ ሥርዓት የመወገጃው ጥርጊያ መንገድ ላይ ስላለም ጭምር ከመሆኑም በላይ ራዕዩን ያሳክልኛል የአብይ ካቢኔ በማለት ነው እንጂ በሦስት ወር ውስጥ ይህን ያህል ዕምነት፤ ይህን ያህል ዕውቅና፤ ይህን ያህል ምስጋና ባረበበ ነበር … ከመራራ የኑሮ መከራ አውጥቶ ሙሴዬ ያሻግረኛል የሚል የጸና ተስፋ ነው … እንዲህ ያደረገው። አሁን እኮ በኢትዮጵያውያን ስሜት ወስጥ የትኞቹ ፊደል ነገሱ ለሚለው „አ“ „ብ“ „ይ“ ሦስት ፊደሎች ገነዋል። ጸሎትም ሆነዋል። እኔ በክቡርነታቸው ላይ ሥራ ስጀምር ታህሳስ ላይ ይመስለኛል ፎቶ ፍለጋ ስጎግል በውል 1ሺህ ያልነበረው ቁጥር ዛሬ ከሦስት ሚሊዮን በላይ በዬሰከንዱ የሚወጣበት ጊዜ አለው። ነፍስ መንፈሱን ፈለጋት። ውስጡን ስላገኘበት።
  • ·       የፓርቲ መርህ ውስጣዊነት።

ዶር አብይ አህመድ ቀላል ሰው አይደሉም። በፓርቲ ጽንሰ ሃሳብ ውስጥ ያላቸው ግንዛቤ ያከብረኩላቸው አቅማቸው ነው። እኔ ተዚህ በቋንቋ የማልግባበት ጉዳይ ይሄው ነው። ህዝብ በሙሉ አባል ይሁን የሚል ዕሳቤ የፓርቲ አመሰራረትን ፍልስፍና ጽንሰ ሃሳብ ጋር ባእድነትን ያመለክታል። አያውቁትም የፓርቲ አባል የሆኑበትን መርህ። አንዷን ቃል "አባልነት" በፈቀደኝነት የምትለውን። መቼም በታሪክ 1000.00 ዬዬሐገሩ ገንዘብ በሁለት ጊዜ ክፍያ የአባልነት ምዝጋባ ስታካሂድ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ናት ለግንቦት 7 አባልነት። መርዶ ነው ይሄ ለፓርቲ አደረጃጀት እና አመራር መርህ። ሆኖ አያውቅም። 

ገንዘብ የከፈለ ነው የዜግነት የምስክር ወረቀት የሚሰጠው። ይህ እንግዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ መሬት ያዬዘ ተግባር ድርጅቱ እጀምራለሁ ካለ እንደገና አቅምን የመጠነ መረህን የተከተለ የተግባር ፊደል ገበታ መግዛት ሊኖርበት ነው። ገንዘብ የከፈለ አይደለም አባል መሆን የሚያስችል፤ መስዋዕትነት የፈቀደ ራሱን ለፓርቲው ህግ ደንብ እና ፕሮግራም እንዲሁም የውስጥ መመሪያ ለማስገዛት የፈቀደ ነው። ክፍያ በደንብ ውስጥ አንዲት ትንሽዬ ዘርፍ ናት። ሰብዕና ነው ዋናው ቁም ነገር። ጽናትም የሚመጣው ከ አገነባቡ ነው። 

ህይወቱ መምህር የሆነ ሰውን እንደ መርገመት ሳይሆን እንደ ፍጡር የሚይ ለዛም የሚጨነቅ የሚጠበብ ... የሰው አያያዝ አደረጃጃት እና አመራር ማለት ነው የፓርቲ መወቃራዊ ሃላፊነት ግዴታ። ሰውን በቁስ ለክተህ ነፃነት የለም። ነፃነት የህሊና የስሜት ጉዳይ እንጂ የሃብት ደረጃ መሊከያ አይደለም። በዬትኛውም ሁኔታ ፓርቲው ኖረም ሞተም ፈረሰም የነበረበትን ፓርቲ የማያስወቅስ የማይስነቅስ በሙሉ ዲስፕሊን የሚያንጽ አልፋ ኦሜጋ መርህ ያለው ነው ፓርቲ ማለት። ሰው ማብቀል፤ ማብቃት። 

በመርህ ደረጃ ግን ቀደምቶቹ አንጋፋዎቹ የማሌ ርዕዮት ቅኝቶች በዚህ መስመር መቼም አይታሙም ነበር። የንደፈ ሃሳብ ብቃታቸው አለ ግን ተለዋዋጭ ሆኖ። አሁን ከሆነ በግንባሩ በኢህአዴግ ውስጥ ያሉ ኩነቶችን ሳዳምጥ በድርቅ የተመታ እንደ ነበር ነው የምገነዘብው። በተፎካካሪ መሪዎችም፤ ተወካዮችም ሆነ አስተባባሪዎችም ለቅንጣት ለናሙና ቃሏን ሰምቼ አላውቅም። ለዚህም ነበር የጸጋዬ ድህረ ገጽ አክቲብ በነበረበት ወቅት በፓርቲ አደረጃጃት እና አማራር ላይ  በትጋት እስራበት የነበረው። የደጋፊ እና የአባል ልዩነቱ እንኳን በወል አይታወቅም ተዚህም ተሰለጠነው አገር። ለዚህ ነው የጅምላ ግዳጅ እና የጅምላ ጉዞ ውሃ የበላው ቅል የሚሆነው። ውዶቼ ለመግቢዬ ይህን ካነሳሁ ወደ በሠመራው ጉባኤ መጪ እንበል ...
  • ·       ዕቅዳዊ ጸጋ መዋደድ።

አንድ ጊዜ ዶር አብይ መሃንዲስ ናቸው ብዬ ጽፌ ነበር። የኦህዴድ የጽ/ቤት ሃላፊ በነበሩበት ወቅት። መቼም ዕቅድ ከመንፈስም፤ ከጸጋም ከስልጠናም የሚገኝ ክህሎት ነው። ዕቅድ ትልም ነው፤ ንድፍ ደግሞ በምልከታዊ ምናቦች የሚሰራ ነው። ሁለቱም ተወራራሽ እና የጥበብም ቤተኞች ነቸው፤ ሥነ ጥበብ። ንድፍ ኑሮም ነፍስም ህይወትም ንድፍ ናቸው የፈጣሪው። ተፈጣሪውም የተፈጠረበትን ንድፍ በኑሮው አሳምሮ መቀጠል እንዲያስችለው አስቅድሞ በህሊናው ሰሌዳ ያሰበውን ንድፍ በወረቀት ላይ ይሰራዋል።  

ዕቅድ የረጅም የአጭር ጊዜ ሲሆን ሁለቱንም የሚያገናቸው ሊንክ ደግሞ የመካከለኛው ጊዜ ትልም ነው። ከዚህ አንጻር ለምሳሌ የረጅም ጊዜ የሦስት ዓመት ቢሆን የአጭሩ ጊዜ የዓመት ቢሆን የመካካለኛው ጊዜ  የመንፈቅ ሊሆን ይችላል። ሁለቱ መንፈቆች የዓመቱን ማለትም የአጭር ጊዜውን፤ ስድስቱ መንፈቆች ደግሞ የረጅሙን ትልም ስኬት ያመጣሉ ማለት ነው።

በዚህ የሠመራ ጉባኤ ላይ እኔ እንደተገነዘብኩት ከሆነ ከንድፍ በፊት ጥናትን በኮሜቴ ማስጠናት አንደቀደመ እና በጥናቱ የውሳኔ ሃሳብ መሰረት ንድፍ እንደሚዘጋጅ ነው የተገነዝብኩት። ኮሜቴ እነማን የሚለውም ትልም ነው። ለነገሩ ጥናትን እራሱ የንድፍም የትልምም የሥርዓተ አካል ነው። አጥኚው የሚያጠነው ነገር በምን ጭብጥ ላይ ስለመሆኑ የሚጀመርበት እና የሚጠናቀቅበት ጊዜ የሚያስፈልገው፤ መዋለ ንዋይ፤ መዋለ መንፈስ፤ የሚሠራበት የመስኩ ወለል፤ የቀጥተኛ እና የተባባሪ ተሳታፊዎች ቅንብር ራሱ ንድፍ ያስፈልገዋል። የት? እንዴት? መቼ? በምን? ስለምን? 

ይህ መቼም መልካም መረጃ ነው። ስለምን በግብታዊነት አቅዶ በግብታዊነት ከመወደቅ የሚያድን ነው። በውድቅቱ ውስጥ የሚባክነው ጊዜ - ማዋዕለ ንዋይ - የሰው ጉልበት - የዕምሮ ውጤት ሁሉ ስለሚያጠቃለል አላዛሯ ኢትዮጵያ ለማዳን ሥር ነቀል መንገድ መጀመሯን አሳይቶኛል። እጅግም ረክቻለሁኝ።

ከዚህም በተጨማሪነት ከጅማላ ርምጃ ወደ ጥናታዊ መስክ ማዘንበሉ ስክነትን ስለሚያሰገኝ ነገሮችን ለዘለቄታ ከሚያስገኟቸው አምክንዮ ውጤቶች ጋር ለማያያዝ የተሸላ የተስፋ መንፈስ አለው ብዬ አስባለሁኝ። ከዚህ ጋር ማቀድ መተግበር ብቻ ሳይሆን በዬትልሙ የዘመን ፍሰቶችም ግምገማው ቁጥጥሩ አትራፊ እና አክሳሪው መንገድ ሁሉ ቀድሞ ስለሚተነበይም ጥሩ እርምጃ ነው።

ከዚህው በተጨማሪም በማፈረስ እና በመግንባት፤ በመገንባት እና በማፍረስ መካከል የነበሩ ሳንኮችን ለማሰወገድ ጅምሩ አበረታች ነው። ጉዳዮችን ከመሠረታቸው አጥንቶ ዘላቂ ጥቅማቸውን ለማምጣት ህሊናዊ ሥራዎች በርጋታ መጀመራቸው በዬሥርዓቱ ሹም ሽር በማፍረስ ለምንባዝነው ለእኛ የተለዬ አቅጣጫ ነው። ለትውልድም ሌላ የታሪክ አዲስዘመን ነው። በሌላ በኩልም ግንባታን ከቁጥር ብዛት አጋርነት ብቻ ተሰክቶ የነበረው የፖለቲካ ሸቀጣዊነት ወይንም መናጆነት ተወጥቶ ጥራት ባለው ሁኔታ ከእንግዲህ ላሉ ዘመኖች መሠረት ለመጣል ያለው ጅምር እንደ ዜጋ ለእኔ ደስ ብሎኛል።
  • የበጀት ዝውውር

የበጀት ዝውውርን በሚመከትም እንዲሁ አዲስ መረጃ በዚህ ስብሰባ ተደምጧል። ለቤንሻጉል፤ ለአፋር፤ ለጋንቤላ ክልሎች የተሻለ መንግሥታዊ ድጋፍ ለመስጠት ውሳኔን የሚጠበቅ የ400 ሚሊዮን የባጀት ድለድል እንዳለም አዳማጫለሁኝ። ይህ ማለት ሁሉም ዜጋ እኩል ነው። መጠቀምም ካለበት የሃብት ስርጭቱ በእኩልነት ሊመራ፤ ሊደለደል ይገባዋል። አቅም ለሚያንሳቸው ክልሎችም እገዛ በማድረግ የሥነ ልቦና አቅማቸውን ማስተከካል ስለሚቻልበት ሁኔታ ጅምሩ ይበል የሚያሰኝ ነው።
  • የእቅድ ዝውውር።

የእንድስትሪ ፓርክ በሚመለከት ከሌላ ክልል ወደ አፋር ዕቅድ ሽፍት እንደ ተደረገም አዳምጫለሁኝ። ይህ እንግዲህ የተዛበውን የሃብት ሥርጭት እና ድልድልም መልክ ለማስያዝ እዬተወሰደ ያለ እርማጃ መሆኑ ነው። ከዚህ በተጨማሪ እኔ የገበሬ ነገር አይሆንልኝም እና  ኢትዮጵያ ደጋዊ ቦታዎችን ብቻ ተጥልላ ከመኖር ቆላዎችንም በመስኖ ለማልማት ቀደም ባሉት ጊዜ ባደመጥም ይሄኛው ደግሞ ከበጀት ዘውውሩ እና ከትኩረት ተመስጦው አንጻር ወሸኔ ነው። ይህ እንግዲህ ሰፊውን የኢኮኖሚውን ድርሻ ለያዘው የግብርና ኢኮኖሚ ቅድምያ እንደተሰጠው አመላካች ነው። ወሸኔ!
  • ሽማግሌዎች

 ሌላ እጅግ የመሰጠኝ አመክንዮ ከሽማግሌዎች ጋር ያላቸው የማድመጥ አቅም አንቱ መሆኑን ነው። የሚገርመው የ አዲስ አባባው የምክክር ወቅት እንደ ትውውቅ ነበር እኔ የወሰድኩት የነበረው። አሁን ሳዳምጥ የልብ ለልብ ግንኙትን እንደነበረው ተረድቻለሁኝ። ያን ጊዜ ከ አፋር ሽማግሌዎች ጋር ሲነጋገሩ የገቧቸውን ቃል መሠረት ለመጣል ከሁሉም ክልሎች በተሻለ ለ አፋር የተለዬ አያያዝ እንዳለ አዳምጫለሁኝ። ይህ ለእኔ ታምር ነው። አፋር የዓለም መዲና ነው። በዛ ላይ ማድመጥን መፍቀድ ብቻ ሳይሆን በዚህ ሁሉ ውጥረት እና ጫና ቃላቸውን ለመፈጸም የሚገድባቸው አንድም የአቅም ስስነት እንደ ሌለባቸው መታመንን በትልቁ በልቤ ውስጥ እንድመዘግበው አድርጎኛል። ማለፊያ! 
  • ቃል እና ነፍሱ።

በዚህ ጉባኤ የመሰጠኝ ጉዳይ ቃል እና ነፍሱ ነው። „ቃል ብቻ በቂ አይደለም“ በማለት ከክብርት ወ/ሮ አና ጉምዝ ጀምሮ ገኖ የተደመጠ ጉዳይ ነበር። ቃል አይደለም ቁስን ሰውን የፈጠረ ስለመሆኑ ተዘሎ ማለት ነው። ቃል የማህበረሰብ መሠረት የሆነውን ሦስት ጉልቻ ፈጣሪ ስለመሆኑ ተዘሎ ማለት ነው። በዚህም ጉዳይ ቀደም ብዬ ሠርቸበታለሁኝ።

 ጠ/ ሚር አብይ አህመድ በምርጫ ተወከሉበት ዞን የገቡትን ቃል ፈጽዋል ከመንገድ በስተቀር የሚል አንድ ሪፖርት ላይ በዛ ሰሞን አንብቤያለሁኝ። እስከ አሁን በተናገሯቸው ውስጥ በአመዛኙ የመፈጸም ሂደቶች ይታያሉ። ስለዚህ በቀደመው ተጠያቂ ሊሆኑ እንደማይፈቅዱ እሳቸው ወደ ሥልጣን ከመጡ በዋላ ስለተከናወኑ ተግባርት እና ስለሚቀሩ ጉዳዮች፤ የሚጠፉም የሚተጓጎሉ ጉዳዮች ከኖሩ ተጠያቂ ነኝ በማለት ቃላቸውን የመጠበቅ ቃል ገብታዋል። እኔ ደግሞ የተፈተኑ ስለሆነ ዛሬ ሳይሆን ቀደም ባለው ጊዜም ቢሆን መታመንን አበረክትላቸዋለሁኝ። እኔን የሚከተልም እንዲሁ …

ይሄ እንግዲህ በአቅም ልክ፤ በጥናት በተመሰረተ ዕቅድ፤ በተስተካከለ የእኩልነት ሚዛናዊነት የሚገቡ ቃሎች ወደ ተግባር ሽግግራቸው ከፈጣሪ ጋር ወደ እርግጥ የሚያራምዱ ሃሳቦችን አግኝቼበታለሁኝ። በተዝረከረው የድንጋይ ማስቀመጥ፤ የጀምሮ መቋራጥ፤ የተሰራውም ለብቄት ሳይበቃ የመፍረስ ድብልቅል እና ቅልቅል ያለ እረኛ አልባ ለነበረው ዝርክርክ ጉዳ ጉድ መልክ ለማስያዝ ከሥር የጀመረ ሁለገብ ተግባር እንደ ተጀመረ ለማወቅ ችያለሁኝ። አብሶ የምርጫ ሰሞን ቃል እና ከምርጫ በዋላ አሞራው በረረ ቅሉ ተሰበረ ቲያትር ከዚህ ላይ እንደ አበቃ ደንግገዋል። እንደ ዋዛ ነው የሚናገሩት ግን ነገ የሚተጉበትንም መረጃ ነው የሚሰጡት። ቃል እና አሳቸው በገህዳዊ ዓለም ሳይሆን የመንፈሳዊ ቁርኝት አላቸው ብዬም አስባለሁኝ።
  • ·       ክልላዊነትን ፈቅዶ መሻገር።

ቀደም ባለው ጊዜም ክልላዊነትን የተሻገሩ፤ ከወረቀት አምልኮ ወጥተው ሁሉንም ሠራተኛ በአቅሙ እና በብልህነቱ፤ በጥበብ መምራት እና ማስተዳደር ለክቡርነታቸው ልዩ የነፍስ ጉዳይ ነውና ለዚያም የሚተጉበትን ዛሬ ላይም የሚታዬው ይሄው ነው። እስከ አሁን የተፈጠሩባትን ክልል እንዲያው ለናሙና እንኳን አላነሱም ስለዚህ እኔ ሳስበው ከፓን አፍሪካኒስትነት በላይ ሉላዊነት ነፍስ እንዳላቸው ተገንዝቤያለሁኝ።
  • አጋርነት ወይስ አባልነት

አጋርነት እና አባልነት በተቀራረበ ትርጉማቸው ነው ለማብራርት የሞከሩት ጠ/ ሚር አብይ አህመድ። የክብሩነታቸው መርህ ልዩነቶችን እያጠበቡ መምጣት ስለሆነ። እንደ መሪ ትክክል ናቸው። እኔ ግን እንደ አንድ ተርታ ዜጋ እንዲያውም ትቢያ ላይ እንዳለች ሴት ነው የምገልጸው። እኔ የምላው አጋርነት ማሟያነት ነው። የወያኔ ሃርነት ትግራይ ራሱን ከፍ አድርጎ ለማውጣት የተጠቀመበት መሰሪ ስልት ነው ብዬ ነው እማስበው። 

አባልነት ባለሙሉ መብትነት ነው። በሌላ የማህበራዊ ኑሮ ይሄ ሊሠራ ይችላል። በፖለቲካ ህይወት ግን ዜጋ ዜጋ ነው። አጋር በመብቱ ጉዳይ ላይ ባይታዋር ሊሆን አይገባም። ኢትዮጵያ አደጋ ላይ ስትወድቅ ደሙን እኩል የማፍሰስ ግዴታ እንዳለበት ሁሉ ኢትዮጵያዊው ዜጋው መብቱም እኩል መጠበቅ አለበት። ሲሶ ዜግነት፤ እርቦ ዜግነት ስሌለ።

ስለዚህ የኢህአዴግ ግንባር አባል መሆን እና አጋር መሆን የሁለት አገር እንጂ ለአንድ አገር ልጅነት የማይመጥነው የተፋለሰ ፖለቲካዊ መርህ ነው። ሌሎች አገሮች ይህን ቢሰሙ ራሳቸውን ይዘው እሪ ነው የሚሉት። ተፈኮካሪ ፓርቲዎች ቀርቶ። ለዚህ ጠ/ ሚር አብይ አህመድ በቀጥታ ተጠያቂም ባይሆን ግን የግንባሩ አፈጣጠር የሄሮድስ መለስ ዜናው የናጠጠ ህግ አልቦሽ የጭቆና ተግባር ነው። አንዱን ሎሌ፤ ሌላውን ጌታ እድርጎ ነው የተፈጠረው ወያኔ ሃርነት ትግራይ። በዚህ ውስጥ አማራ ማህብረሰብ ውክል አካል እንዳልነበረው ይታወቃል። የተሰረዘ ነው። በተጨማሪ አፋር፤ ጋንቤላ፤ ቤንሻጉልም ዳሽ ናቸው።

በመንግሥት ፓርላማ የመቀመጫ ወንበር ማግኘት እና በፓርቲው ውስጥ ወሳኝ አመራር ሰጪ ሆኖ መወሰን መቻል የሰማይ እና የምድር ያህል ልዩነት አለው። ሚረው እኮ ፓርቲው ነው። መንግሥት ፈጻሚ ነው። ፓርቲው ከፖለቲካ መሪነት ተገለህ አስፈጻሚ መሆን ብቻ ከሆነ የአንዱ ዜጋ የበላይ የሌላው ዜጋ የበታች ነው ለእኔ የሚሰጠኝ ምላሽ ቁልጭ ያለ discrmnation ነው። ግዴታ አለብህ ግን መብት የለህም። ረቂቅ የሆነ የማግለል እና የመጨቆን ሰውር በደል። እንግዲህ አፋር 2 ሚሊዮን ያልሞላው ነው ተገለልን የሚለው፤ አማራስ ምን ሊል ይሆን? ስለዚህ ድምጽ አልባ ሆኖ መቀመጥ የፎቶ ፍሬም ማለት ነው ለእኔ ወይንም ግማሽ 1/ 2 ሰውነት ማለት ነው። 

27 ዓመት የተቃጠለ የዜግነት ዓመት ነው። በዚህ ላይ 4% ደግሞ 9 ድምጽ አለው። የመወሰንም አቅሙ ከ9% በላይ ነው። ስለምን ብአዴን እራሱ 9% ወያኔ ሃርነት ትግራይ ሳልባጅ ስለነበር። የቀልድ ይባል፤ የፌዝ ይባል፤ የብልጠት ይባል የጮሌነት ይባል ብቻ መላቅጡ የጠፋው የፖለቲካ ሥርዓት ሲከተል እንደነበር ነው እኔ እማስበው ኢህአዴግ።

ምክንያቱም እኔ በፖለቲካ አደራጅነት ነው የሰለጠንኩትም የሠራሁትም። መሪው ድርጅት ከሚመራቸው የሲቢክስ ድርጅቶች በታች የወረደ የፓርቲ ዲስፕሊን ነው ሲያራምድ የኖረው። ኢትዮ ሱማሌ ከትግራይም በላይ ነው። ግን ድምጽ አልባ ነው። ይሄ የተዛባ ሥርዓት በአግባቡ መልክ ሊይዝ ይገባዋል። ወያኔ ሃርነት ትግራይ በልኩ ቁጥር ሊኖረው ይገባል። ሌሎችም ¼ ዜጎች ሳይሆኑ ሙሉዑ ዜጎች ናቸው በመከራዋ ሁሉ የነበሩ ያሉም።  ለመቀመጥ፤ ቀንበር ለማሞቅ ሳይሆን መሪያቸውን ለምረጥ ሆነ ላለመምረጥ መብት ሊኖራቸው ግድ ይላል። ከዚህ ጋር አባል ያልሆኑትን ምርኩዞች፤ ጥላ ያዦችን በሚመለከትም ቁልጭ ያለ የመርህ ተግባር ሊፈጸም ይገባዋል ለወደፊት። መቼም የጠ/ ሚሩ የሥራ ጫና ሳስበው እኔ እራሴ ማሰቡ እራሱ ራሴን ሊያፈነዳው ይቀረባል።

ቀድሞ ነገር እሱ ያለወሰነበትን የሱማሌ የቤንሻንጉል እና የአፋር የኢህዴግ ጽ/ ቤት እንዴት በራሱ ላይ ተፈጻሚ እንዲሚያደርግ፤ እንደምንስ ተጠያቂ ሊሆን ችሎ 27 ዓመት እንደኖረ ይገርመኛል። የእስተ ዛሬው ሆኗል መሪ ኢትዮጵያ ስላልነበራት ከእንግዲህ ይህ በመርህ ደረጃ ወኪልም የመወሰን ሙሉ መብትም ለእነዚህ ክልሎች በልመና ሳይሆነ በመርህ ደረጃ መብታቸው ስለሆነ እንደ አቅማቸው ውክልናቸው በሙሉ ነፃነት ርትሃዊ ውሳኔን ይሻል። ለድርድርም ሊቀርብ አይገባውም። አማራ ላይም አማራን የሚወክሉ ድምፆች የግድ መወከል አላባቸው የብድር ዱቄት ቤት ስለማይመራ።
  • ·       ፓርላማ እና ውክልና።

ሌላው በመንግሥት ተዋካዮች ምክር ቤት፤ ፓርላማ የግድ ነው በህዝብ ብዛት ውክልና መምጣት። አፋሮች ይህን ሊገነዘቡ ይገባል። የንድፈ ሃሳብ ግንዛቤ እጥረት እንዳለባቸው ተገንዝቤያለሁኝ። በዚህ የውክልና ሂደት ዝበት ያለ አልመሰለኝም። ውሳኔ ላይ ግን የወያኔ ሃርነት ትግራይ የየአንበሳውን ድርሻ ይዞ ስለመኖሩ የአደባበይ ሃቅ ነው። በቁጥር እኩል ቢሆንም የፍላጎት ተፈጻሚነት ቅኝት ግን የጨቋኙ ፓርቲ የወያኔ ሃርነት ትግራይ መንፈስ ነበር አሸናፊው።

አፋርን፤ ቤንሻንጉልን፤ ጉምዝን በሚመለከት ያው ማሟያ ናቸው የነበሩት ውክልናውም ቢኖር። እርግጥ ነው ወኪሎቻቸው እነሱኑ በደም በዘር በሐረግ የሚወክሉ ናቸው እንደ አማራ በባይታወርነት አልተገረፉም ቢያንስ። ችግሩ ያለው አሁን አማራ ላይ ነው። እነማን ናቸው ወኪሎቹ? እናማን ናቸው ተጠሪዎቹ? አሱን ቀጥቅጠው የሚገዙት ወይንስ ስለ እሱ የሚሞግቱት? ልሙጥ ነው። አቅም ያላቸው አማራ ማን አድርሷቸው ለዚህ እኮ ነው አሁን መሃን መሬት የሆነው። እንኳንስ ተተኪ በተተኪ እንደ ኦህዴድ ሊሆን ቀርቶ ራሱን ችሎ ለመቆምም ጋዳ ነው። 

ይህ ሲባል አማራ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ብቃት፤ ሰብዕና፤ ሞራላዊ አቅም ለመወከለ አካል የሚያስመካ የተግባር ሰውነት የግድ ይላል። ችሎታ ተመክሮ ልምድ ፈቃደኝነት። አገልግሎት መስጠት ችሮታ ሳይሆን እንደ መባረክ የሚቆጠር ባህልን ማዳበር መልካም ነው። 

እኔ እንደ ዕድል ሆኖ ሥራ ከጀመርኩበት ጀምሮ አቴንዳስ ፈርሜ አለውቅም። ቀድሜ እገባለሁኝ ዘግይቼ አውጣለሁኝ። ሰንበትም ቀን የሥራ ቀኔ ነው። አገሬ እያለሁኝ አንድም ቀን የዓመት እረፍት ወስጄ አላውቅም። 

እንዲያውም እምሠራውን ስብስቤም ቀሪውን ቤት ውስጥም እሰራለሁኝ። ውጪ አገርም ፊርማ ገጥሞኝ አያውቅም። ስለምን እኔም አይገባኝም። አንዲት አለቃ ነበረችኝ የሰራ ሰዓት ከማለቁ በፊት ማጽጃ ዕቃዎችን ማስቀመጫ ቤቱን የምትቆልፍብኝ። 50 ሠራተኛ በሚሠራበት ሁልጊዜ በዬዕለቱ እኔ ተሻምቼ ስለማጸዳ። መሥራት ጥሩ ነገር ነው። አንድ ሰው ሲሆን ሲሆን ከሚከፈለው በላይ በስተቀር ግን የሚከፈለውን የሚመጥን ሥራ መስራት የህሊና ጸጋ ነው። ይሄ መርሄ ነው ከልጅነት እስከ ዕወቅት። ዜጋ የሚሠራው ለራሱ የህሊና ብርኩነት ነው። 
  • የኔዎቹ ይቀጥላል

ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!
ማለፊያ ጊዜ ኑሩልኝ።


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።