ጥበብ ማለት ነገን ማሰብ ነው።
ጥበብ ማለት ነገን ማሰብ ነው።
„መባህን አግባ አስበህ ስንዴህን አግባ፤ የተቻለህን ያህል
መሥዋዕትነትህን አብዝተህ አቅርብ።“
መጽሐፈ ሲራክ ምዕራፍ ፴፰ ቁጥር ፲፩
ከሥርጉተ©ሥላሴ 04.10.2018
ከጭምቷ ሲወዘርላንድ
ውዶቼ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የኢህአዴግን ጉባኤ ስከታተል። የእህት ነው የሚባሉትንም የእነሱንም እንዲሁ። የአንዳቸውንም ጉባኤ ተከታታይ አላውቅም። እንቅልፍ ክኒን ቫልዬም መግዛት አያስፍልገኝም ነበር። ለውሸትም መጋዝን ቤት አልነበረኝም። አሁን የሁሉንም ተከታትያለሁኝ።
ትግራይ ላይ አንዲት ቀና ሴት ወደ ክልሉ ምክር ቤት ተመርጠዋል። ጤነኛ መንፈስ ነው ያላቸው። ከሁሉም ትግራይ ያሳዝናል። አሁንም በገመድ ተጎተት እዬተባለ ነው። ለውጥ ናፈቀው ግን ተገደበበት።
ወደ እርእስ ጉዳዬ ስገባ ማሰብ ጥሩ ነገር ነው። ጥበብ ማለትም ነገን ማሰብ ማለት ነው። ለዛሬ መገኘት ትናንትን መርሳት ማተበ ቢስነት ነው። ዛሬን ለማግኘት የቀድሞው ጠ/ ሚር የነበሩት አቶ ሃይለማርያም ደስአለኝ ያደረጉት መልካም ነገር ሊረሳ አይገባውም።
በሌላ በኩል ም/ጠ ሚር አቶ ደመቀ መኮነን የወሰዱት እርምጃ ደግሞ ራስን መስጠት ብቻ ሳይሆን የአማራን ህዝብ ታሪክ፤ ትውፊት፤ ትሩፋት፤ ዕድል፤ የሥነ - ልቦና ልዕልና፤ ተጋድሎ፤ እና ትንሳኤ አሳለፍው ነው የሰጡት። የድርጅቱንም የቀድሞውን ብአዴን የዛሬውን አዴፓንም ዕንቁ ተስፋውን አሳልፈው ፈቀደው ነው የሰጡት። ማድረግ የሚቻለው ሥልጣን ሲኖር ነው። ክብሩ መጎሱ የተለዬ ነው። ያን አልሻም ማለት መቼም ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ድርሳን ያጽፋል።
ይህን ዕድልን አሳልፎ መስጠት ለዛውም ሲነሪቲው እዬፈቀደ፤ መርሁ እዬፈቀደ ፈጽሞ በህልም የማይታሰብ ታምራዊ ገድል ነበር። ይህም ብቻ አይደለም በሥርህ የነበረን አንድ ጓድህ ከላይህ መጥቶ ሃላፊህ ሆኖ እንዲቀጥል መፍቀድ፤ ሌት ከቀን ሌጋሲው እንዲሳካ እንቅልፍ አጥቶ በቅንነት፤ በድንግልና አብሮ መብታልም ከድንቅ በላይ ትንግርት ነበር።
የብቃት ብቻ ሳይሆን የዘመን ልዩ ስጦታ ነው። ዕውነት ለመናገር ያሳለፍናቸው ወቅታት በዘመን ታሪክ ውስጥ መልካሞቹ ሲታሰቡ ተመልሶ የመፈጠር ያህል ነው። ብዙ የሐሴት ቀናትን አሳልፈናል። እርግጥ ነው በርካታ ያላቆሙ ችግሮች ቀጥለዋል ያም ሥልጣን ያመጣው መከራ ነው።
ሌላው በጠ/ ሚር አብይ አህመድ ፍቅር ማግኘት ብዙው ሊሂቃን ውስጥ ለውስጥ እንደምስጥ ሲበላው፤ ሲያርመጠምጠው፤ ሲያሳምመው እሳቸው አቶ ደመቀ መኮነን ግን በቅንነት ከጎን ተሰልፈው ያሳዩት ሥነ - ምግባር ታሪክን የፈጠረ ታልቅ ክህሎት ነው። ይህም ብቻ አይደለም ዕውነት እንነጋገር ከተባለ ለአብይ መንፈስ ተገዢ የሆነው የአማራ ክልል ብቻ ነው። ለዚህም ነው በላይ በላይ ጫና የበዛበት። ይህ የአቶ ደመቀ መኮነን ፈቃድ እና ቀናነት ያስገኘው መሰረታዊ ጉዳይ ነው።
ይህ ባይሆን ኖሮ የት ላይ ይመሳከር ነበር መደመር? ኦሮምያ ላይ? ህም? ቢንሻንጉል? ሱማሌ? አፋር? ጋንቤላ? ሀረሬ? ያው ቀንብር ተሻከሚውም ነው እስከዚች ቀንም ያደረሰው። ቀን አድራሽ ነው አማራ። ቀን ከተደረሰ በኋዋላ ደግሞ እንደ አሮጌ አካፋ እና ዶማ መወርወር ዕጣው ነው። ግን ቅንነቱ ስላለ ቁጭ አድርጎ አማላኩ ያሰያዋል።
ወደ ቀደመው ስመለስ ባለፉት 6 ወራት ባለው አጠቃላይ ሚዛን ሲታይ ምን እና ምን እንደ ሆነ ሁሉንም እንታዘባለን። የት ላይ ትኩረት እንደ ነበር፤ የት ላይ ትኩረት እንደጓጎለ፤ የት ላይ ደግሞ ወና እንደሆነም። ያን በትዕግስት በማስተናገድ እረገድም ክልሉ የለውጡን ሂደት እዲቀጥል የጠራ፤ ቅናዊ የሆነ አቋም በማስያዝ እረገድ የላቀ የአመራር ጥበብ ምንጩ የአቶ ደመቀ መኮነን ብልህነት ያስገኛው ውጤት ነው።
ሁለቱም ዶር ገዱ አንዳርጋቸው እና አቶ ደመቀ መኮነን የነበራቸው ጥምረት የኢትዮጵያን መንግሥት ቃላ አባይ ያለደረጉ ረቂቅ ልባም ተልዕኮዎች ተከውነዋል በክልሉ። ከሁሉ በላይ ለአቶ ደመቀ መኮነን አመራር የብአዴን / አዴፓ ቀደምት አመራር የነበረው ጉልህ ተሳትፎም ልዑቅ ነበር። በፓርቲ ህይወት ውስጥ የግል እና የጋራ ሃላፊነት ካልተዋህዱ የፈለገ ብቃት ቢኖር ከህልም የሚያልፍ ነገር የለም።
ራሱ የቀድሞው ኦህዴድ የዛሬው ኦዴፓ የብአዴኢን/ አዴፓ ያህል ለአብይ ካቢኔ ቀና እና ቀጥተኛ ነበር ማለት አይቻልም። ለአብይ ካቢኔ ታዛዥ ነበር ለማለት፤ የሻሸሜነው እና የቡራዩ ምስክር ነው። ሌላም አለ ለምሳሌ በብአዴን / በአዴፓ ከ14 ያላነሱ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ብአዴን / አዴፓ ተወያይቷል።
ህብረ ብሄር ፓርቲዎች ህዝብ በአደባባይ እንዲቀበላቸው፤ ከህዝብ ጋር እንደነጋገሩ ፈቅዷል። ይህ ህብራዊነት የአንድነት ፓርቲዎችን በክልሉ የመፍቀድ መሰረታዊ ጉዳይ በሚመለከት ራሳቸው ጠ/ ሚር አብይ አህመድ በሚመሩት፤ ዶር ለማ መገራሳ በሚአስተዳድሩት ኦህዴድ / አዴፓ ግን ይህን መከወን አልተቻለም ነበር። መካን አምክንዮ ነው ሆኖ የታዬው። እጃቸውን መሰስ አድርጎ ያወጣው ያው መከረኛው የአማራ መሬት ነው። በሎቢም ይኸው 9 ወር ሙሉ ሌት እና ቀን እንባትላለን።
የኦሮሞ አክቲቢስቶች በአማራ ክልል ተገኝተዋል የውጭ አገር መንግሥታት ቢመጡ የሚደረግላቸውን አቀባባል ያህል ከብር ተደርጎላቸዋል፤ ከህዝብ ጋርም እንዲወያዩ ተፈቅዶል ይህ ኦህዴድ/ ኦዴፓ ላይ ይቻላልን? የአማራ አክቲቢስቶች ከነመፈጠራቸው ሥማቸውን እራሱ የኦዴፓ ሊሂቃኑ እንኳን አያውቋቸውም። አቶ ንጉሡ ጥላሁን አቶ ጃዋር መሃመድን አዲስ አበባ ድረስ ሄደው አቀባበል አድርገዋል። ወሸኔ ነው።
ይህም ብቻ አይደለም በኦህዴድ ጉባኤ ላይ የተፎካካሪ ፓርቲዎች የራሳቸውን ከማሳተፍ በስተቀር ለሌሎች ኦዴፓ / ኦህዴድ ላይ ዝግ ነበር። ብአዴን / አዴፓ ላይ ግን የተፎካካሪ ፓርቲ ውክል አካላት ነበሩ። ይህ ማለት የኢትዮጵያ መንግሥት የምህረት፤ የይቅርታና የፍቅር ጥሪውን ተቀብለው ለሄዱት ቃል ብቻ አለመሆኑን መሬት ላይ የተተረጎመው አማራ መሬት ላይ ብቻ ነበር።
እራሱ ኢትዮጵያዊነት የሚለውም አማራ መሬት ላይ ነው የሚታዬው። ይህ ደግሞ መንግሥት ለገባው ቃል፤ ዓለም ዓቀፍ ማህበረሰቡም አፍጥጦ ለሚከታታለው ጉዳይ መተንፈሻ የተገኘው አማራ መሬት ነው። ይህን ማስተባባል አይቻልም።
የዚህ ሁሉ የዳበረ፤ የተደራጀ የአመራር ክህሎት ባለቤት አውራው አቶ ደመቀ መኮንን ናቸው። ተዛነፍ ተባደግ የሆኑ ነገሮች ብቻ ሳይሆን ጭራሽም ከግምት ያልገቡ፤ ዕውቅና ያልተሰጣቸው በርካታ ጉዳዮች እያሉ ግን ያን አቻችሎ በመምራት ረገድ ያሳዩት ጥበብ ይህ ነው አይባልም። የሁሉም የመንፈስ ማረፊያ ነበር ላለፉት 6 ወራት አማራ መሬት።
ይህን ያደረገ አካል በፈቃዱ ራሱን ስለምን እንዲያገል ጫና የተደረገበት ምክንያት እኔ ግልጥ ቢሆንልኝም ልብ ገዝቶ ብአዴን ዕቅዱን አክሽፎ አሁን ጉባኤው ላይ በምንፈልገው ክብር እና ሞገስ ልክ አቶ ደመቀ መኮነን በጉባኤው ታደምዋል። ጉባኤውንም በጋራ እዬመሩ ነው። ቀጣዩም ያለውን ስርክራኪ ነገር እያደመጥ ነው። ይህን የነፍሳችን ያህል የምንከታተለው ጉዳይ ነው።
እርግጥ ነው ሌላ ጉዳይ እንዳለ እዬተደመጠ ነው። ቀድሞውንም የታቀደ ነገር ስለመሆኑ ባለፉት ጹሑፎቼ ጠቅሻለሁኝ። ወያኔ ሃርነት ትግራይ ብቻ ነው ብዬ እኔ አላምንም። የሆነ ሆኖ አሁን የሚደመጡ ነገሮች ነገን ይስናሉ በአሉታም በአዎንታም። የኢዴፓ የጉባኤ አባላት አማራን እንዳይሸጡት፤ እንዳይለውጡት ጥብቅ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
አማራ ጥቃትን ታጥቆ፤ ሽንፈትን አዝሎ ከሚመለስ ቢሞት ይሻለዋል። የለውጡ ሞተር አቶ ደመቀ መኮነን በሚመለከት ቁርጥ ያለ ቁልጭ ያለ አቋም መያዝ አለበት የአዴፓ የጉባኤ አባላት። አንደበቱን፤ ልሳኑን፤ ህሊናውን ማስመረጥ ግድ ይለዋል። የአማራ ይህልውና ተጋድሎን ዕውቅና ማስከበር የአዴፓ ጉባኤ አባላት ቀዳሚው ብጡል ግዴታ ይሆናል። ኦዴፓም ማተብ ከኖረው የሚታይ ይሆናል።
ቀደም ሲል ገልጨዋለሁኝ ለማሟያ ነው ጠ/ ሚር እና ም/ ጠ/ ሚር አዲስ የመምረጥ መብት የጉባኤው ነው የተባለው። ጉዳዩ የጠ/ ሚር ጉዳይ አይደለም፤ አልነበረምም። መሰረታዊ ያልተፈለገው የም/ ጠ/ ሚር ጉዳይ ነው።
የአማራ ከኢትዮጵያ የመሰረዙ ማህተሙ የሚመታው አሁን ይሆናል። ይህን ረቂቅ ሴራ ተቀብሎ ጉባኤተኛው ካጸደቀው ሌላ ቃጠሎ ይነሳል። ክፍት ነገር ስለጠፋ ነው ይህ ሁሉ ዘመቻ በአቶ ደመቀ መኮነን የመጣው። እሳቸው ለመላ ኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ባለውለታ ናቸው።
እርግጥ ነው አንድ ማስተዛዘኛ ተዘጋጅቶ ሊሆን ይችላል፤ ነባሩን ፕሬዚዳንት በክብር አውርዶ አዲስ ፕሬዚዳትነት የማድረግ። አማራ ቢሮ ጠባቂ አይሆንም!
አማራን ሚና አልቦሽ አድርጎ ኮድኩዶ ለማስቀመጥ „እንዳያማም ጥራው እንዳይበላም ግፋው“ ዓይነት ነው የሚሆነው። በምንም ታምር በዚህ ጉዳይ ድርድር የለም። ከእንግዲህ አንተኛም። በዝምታ የምንታደመው ለአብይ መንፈስ ሲባል ነው። አሁን ደግሞ የቀረ የለም ሁሉም አገር ቤት ገብቷል፤ የሚገርመው አፋር ጠንካራ አክቲቢስት አሉት ብራስልስ ነው የሚኖሩ እሳቸውም ላካንስ ገብተዋል። ለውጡ ካልቀጠለ እጅግ አሳሳቢ ነው።
ለውጡ ከተቀለበሰ ተራፊ የለም። ለውጡን አምኖ የሄደው ሁሉ የእሳት እራት ነው የሚሆነው። ተስፋው ሁሉ አመድ ነው የሚሆነው። የነበረውን የሰሞኑ ጫና ዋናው መንስኤ እኮ በሁለቱ ድርጅቶች በኦዴፓ እና በአዴፓ ጥርጥሬ እንዲኖር ለማድረግ ነበር ያ የ5 የኦሮሞ ድርጅቶች መግለጫ ካለወቅቱ የተሰጠበት ምክንያትም ይህ ታስቦ ነው። ለውጡ እንዲፍረከረክ። ግጭቶችም ለዛ ነው። ሲፈለጉማ ታዬ እሬቻ በሰላም ሲከበር። መስቀል በፋቲክ እሪቻ ከለአንድ ፋቲክ። ባልቮላው የት እንዳለ ታዬ።
የሆነ ሆኖ ያ መግለጫ ብቻ ሳይሆን የተባጀው የበላይነት መንፈስ ከልክ አልፎ ጣሪያ መንካት ምን ያህል ብአዴን / አዴፓን ብቻ ሳይሆን እጣ ነፍሳችን ስንታገልለት የነበረው የኦህዴድ/ ኦዴፓ ዕምነትን አይሆኑ እንደ አደረገው ሁላችን ደርሶብን አይተነዋል። ቆስለናል።
አብሶ ሥርጉተ ሥላሴ እጅግ እዘናባችሁ አለች። ቁስለቱ ኦህዴድ/ ኦዴፓ ውስጥ ያሉት ተባባሪ መሆናቸው ነው አንጀታችን የከረከረው። ወደፊትም ቢሆን ልብ ያስጥላል ማለት የሚቻለው ኦህዴድ/ ኦዴፓ የጠራ መስመር ሲከተል ብቻ ይሆናል።
አሁን እኔ እማዝነው ለኦሮሞ ህዝብ ነው። ፊት ለፊት ብዙ የተዳፈኑ እሳቶች አሉበት።
የዚህ መሰረቱ ደግሞ በራሱ ውስጥ ያለው የጥራት ደረጃ ስስነት ይመስለኛል። ለማን ለምን እንደሚታገሉ የቆረጡ ሊሂቃን አለመኖራቸው በብሄራዊ ደረጃ መታመንን እያሳጣው ነው ድርጅቱን። እኛ ብቻ አይደለንም፤ ምዕራብውያንም ቢሆኑ ቋፍ ላይ ናቸው። ሰው እንዴት ክብሩን ይጻረራል? ሰው እንዴት የሚሊዮንን ፍቅር እሳት ውስጥ ይጨምራል? አለመታደል።
የሆነ ሆነ በይቅርታ መንፈስ ኦዴፓ ከአዴፓ ጎን መቆም፤ አዴፓ ከኦዴፓ ጎን መቆም ግድ ይላቸዋል። „ወይ ባልዘፈንሽ ከዘፈንሽ ባላሳፈረሽ“ እንዳይሆን። ዶር አብይ አህመድ እና አቶ ደመቀ መኮነን መቀጠል አለባቸው።
ክብርት ወ/ሮ ሙፍርያት ካሜል ደግሞ ይህን ታሪካዊ የመላ ኢትዮጵያ ሴቶችን ሃላፊነት የመወጣት ግንባር ቀደም ግዴታ አለባቸው። የያዙትም የአፈጉባኤ ቦታ በቂ ነው። እሱን ከተወጡት የኢትዮጵያን ሴቶች ታሪክ በወርቅ ጻፉት ማለት ነው።
አሁን ከእኛ ከሌሊቱ 8.07 ሰ ዓት ነው። ለዛውም ለኢህአዴግ ጉባኤ ሲባል? …. እራሴ ይገርመኛል ይህ እራሱ ይደንቀኛል። … ኢህዴግ ጉዳዬ ሆኖ ከ9ወር በላይ እንቅልፍ አጣሁበት። ስለምን? የኢትዮጵያ ዕንባ ትዝታ ብቻ ሆኖ እንዲቀር በመመኘት። ነበር ብቻ እንዲባል ስለምፈልግ። በጎ መሻት።
ነገን ማሰብ ነው ጥበብ!
የኔዎቹ ኑሩልኝ።
ቸር ወሬ ያሰማን። የምትችሉ ሼር አድርጉልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ