የአዳማ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩንቨርስቲ እና ዕድማታው።

ማሰብ።
„ቆይቼ እግዚአብሄርን ደጅ ጠናሁት፤
እርሱም ዘንበል አለልኝ፤ጩኸቴንም ሰማኝ።“
መዝሙር ፵ ቁጥር ፩
ከሥርጉተ© ሥላሴ Seregute© Selassie
14.12.2018 ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ። 


                              ህዝባችን ኑሮው ይህ ነው።
·       መነሻዬ ይሄ ነው።

#EBC ለሁለት ሳምንታት በትምህርት ገበታቸው ላይ ያልተገኙት

 የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተገባልን

 ቃል አልተከበረም አሉ፡፡

 

እጅግ የሚገርሙ ነገሮች በዬ ዕለቱ ይደመጣሉ። የአዳማ ዩንቨርስቲ የሳይንስ

እና የቴክኖሊጂ ተማሪዎች ለሁለት ሳምንት የዘለቀ የትምህርት ማቆም አድማ መትተዋል። ጥያቄቸውን አዳመጥኩት። ግን እዬተማሩ ማቅረብ 

አይቻላቸውም ነበርን? ደግሞስ አሁን ኢትዮጵያ በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ሆና ምን አለ ከችግሯ ጎን ቢቆሙ እንደ እጩ ሊቅነት። 

 

ከቶ እነዚህ ምንዱባን ምን ይበሉ?

https://www.youtube.com/watch?v=kuGKmclKGT8&t=207s

የፍትህ ሰቆቃ - በኢትዮጵያ ሲፈጸሙ በነበሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ ተሰራ ዶክመንተሪ።



 

ለኢትዮጵውያን ልብ ቢሰራልን ኖሮ አሁን ባለው የአብይ ሌጋሲ ላይ 

ምንም ጫና ባለመፍጠር ያ የጭራቅ ዘመን እንዳይመለስ መትጋት ነበር።

 

ለነገሩ "በእጅ የያዙት ወርቅ ከመዳብ ቁጥር" ሆኖ ዓለም አይታው በማታወቅ ፍጥነት ሁሉ ነገር ፍርስርስ ሳይል በነበረው ሁኔታ በስክነት እና በተደሞ ወልጋዳውን በማረቅ፤ ጎባጣውን በማቃናት፤ ጠማማውን በማረቅ፤ 

ዝብርቅርቁን ጉዳችን በአደብ በመመርመር ዘላቂ መልክ እንዲይዝ 

መጠነ ሰፊ እና አዲስ አደረጃጃት በመፍጠር የሰማይ ገደል በሚመሰል ሁኔታ ነው አሁን ኢትዮጵያ እዬተመራች ያለችው። ጥንቃቄው፤ ስልቱ፤ ክንውኑ ስልቱ አትኩሮቱ ጥበብ ነው። ህሊና ላለው ሰው። 

 

ቢያንስ እያንዳንዱ በግሎ ከእኔ ምን ይጠበቃል ብሎ በመዳፉ ላይ ባለው አቅም እንኳን አብሮ ለመሰለፍ እንዴት ይሳናል? „ላም አረኛ ቢያኮርፍ ምሳው እራቱ“ ይሆናል እንዲሉ የትምህርት ጊዜ አላግባብ ቢባክን በቅድሚያ ተጎጂው ተማሪው እና ቤተሰቡ ነው። ሁሉም የመጣበትን ማህበረሰብ እና ደረጃ ማጤን ያስፈልግ ይመስለኛል።

                                      ይህ ተረሳ ወይ?


አሁን ማናቸውንም ዘመናይ ጥያቄዎች እሚቀርብበት ጊዜ ፈጽሞ አይደለም። ልናስብ ይገባል። ሰው ሆኖ በሰው ተፈጥሮ ላይ የዘመተ፤ በአገር ተቋም ላይ ጠላት ኢትዮጵያን ቢወራት ከቶውንም ሊሆን በማይቻል ሁኔታ በዬዕለቱ የሚደመጠው የደለበ ደባ ራስን ያዞራል። መረጃውን እራሱ ስንቱን እንያዘው።

 

መከራ በዋጣው ማህበረሰብ የተገኘው ይህ የለውጥ አዲስ ባለ ራዕይ ታሪካዊ ዘመን ከሰማይ የመጣ ስጦታ ብናከበረው ነው የሚሻለው። ባናከበረው፤ ብናቃልለው ያው ተመልሶ ያ የአራዊት ሥርዓት ተመልሶ ይመጣል። 


ተመልሶ ሲመጣ ደግሞ ሁሉም አክ እንትፍ ማለቱን ስላወቀ የአራዊቱ ሥርዓት ጉዳቱ በቀሉን ሰማይም ምድርም የማይችለው ነው የሚሆነው። ለተወሰነ ጊዜ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብለው የሚታሰቡት ጎንደር ብቻ የሚገኙት የቅማንት 

ማህበረሰብ ብቻ ናቸው። ከአራዊት አስተሳሰብ ጋር አብረው የተሰለፉ

እነሱው ብቻ ስለሆኑ። የጨለማ ጊዜ የናፈቃቸው። አራዊነት የጣማቸው፤ ሲኦል ሽው የሚላቸው፤ ፈርኦናዊ ቅጥቀጣ የናፈቃቸው። ሰው መሆን የተሳናቸው። 

 

ጠላታቸውን አጋር አድርገው ያምሳሉ፤ ሰላም እና ነፃነት ምን ስለመሆኑ ገና ፊደል ያልቆጠሩ። ለኢትዮጵያ ህዝብ መከራም ቅርብ ያልሆኑ ከድመኞች አራዊታት ጋር እኩል ተሰለፍው፤ የማያውቁት አገር እዬናፈቃቸው የሚገኙት። ለጊዜያዊ አካፋ እና ዶማነት ይፈለጉና እስከ አገለገሉ ድረስ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይቻላሉ፤ ሲበቃ ደግሞ እንደ ወልቃይት፤ ጠገዴ፤ እና ራዕያ ህዝብ የጉድጓድ ኑሮ ቤተኛ ይሆናሉ። የቅማንት ሊሂቃን ለውጡን በመቃወም ጋሬጣ ሆነዋል። የመከረኛ ነፍስ ሁሉ አዲስ የሲኦል ተስፈኛም ሆነዋል። 

 

እነሱ ጎንደርን የጎዱ መስሏቸዋል። የጎንደርን ሰላም ባወኩ ቁጥር በ100 ሚሊዮን ህዝብ ሰላም እና ተስፋ ላይ የዳግሚያ ቅብረት እንዳወጁ አላውቁትም። መስሏቸው ነው እንጂ ለውጡ የፈጣሪ ሥራ ስለሆነ እንደ ዋንጫ ወልቆ ከመቅረት ውጪ የሚያተርፍ መንገድ አልያዙም። 


ለውጡ የኢትዮጵያ ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ ስታሸንፍ እንጂ ተሸንፋ አታውቅም። እንድታሸንፍም ነው እነዚህ ቅኖች ጌጧ ያደረገላት። በከፋት ቀን ዙሪያው ጨለማ ሆኖ አፋፍ ላይ ተንጠልጥላ በነበረችበት ወቅት የደረሱላት የጥቁር አንበሳ ፍልቆች ናቸው።   

 

አይደለም ኢትዮጵያ ያለው ህዝብ አህጉራችን አፍሪካ ዓለም በሙሉ ከአብይ ሌጋሲ ጋር ነው። ይህ ሰውኛው ነው፤ አምላካዊ የሆነው ጉዳይ ደግሞ የተደሞ ባለሙያዎች ይተርጉሙት። ብፁዕ አባታችን አቡነ ዮሖንስ የስሜን ጎንደር አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዳሉት የሚታዬው ነገር ሁሉ ከትርጉም በላይም ነው።

 

የእኛ የእኛ አልመስለን እያለ ሁሉ ነው። አሁን ትናንት ዶር ለማ መገርሳ ስለ ሰላም ንግግር ሲያደርጉ የትኛው ምድር እንደተፈጠሩ ሁሉ ግራ እስኪገባኝ ድረስ ነው በተደሞ ያየኋዋቸው። አብዝቼ ሳሳሁላቸው። እግዚአብሄር የሰጠን ብዙ ነገር ነው። የንግግራቸው ለዛ እና ልስላሴ ፈውስ ነው። ስለ አገር ኢትዮጵያ ያላቸው ትልቅነት ብዕሬ ለመግለጽ አቅም ያንሳታል።


ይህን ሳይ መኖሬን መውደዴ ብቻ ሳይሆን መኖሬን ሳልፈቅደው የኖርኩትን ያህል አሁን ከሆነ መኖሬን እዬናፈቅኩት ነው። እንዲህ ዓይንት የፖለቲካ ሳይንስ ሳይንቲስት በዚህ ዕድሜ ማግኘት ህልም ነው። አስቤውም አላውቅም ነበር እኔ።

 

ብቻ አላዛሯ ኢትዮጵያ ይህ ዘመን የሰጣት እጅግ በርካታ ነገር ነው። ትህትና፤ ማስተዋል፤ ታማኝነት፤ እኛዊነት፤ ትእግስት፤ መካሪነት፤ ሩቅነት፤ አክባሪነት ይህን ሁሉ ተችራለች። በዬትኛውም ዓለም የማናፍርባቸው መሪዎች ነው ያሉን። እነሱን ይዘን የትኛውንም ፈተና መሻገር ይቻለናል። ያገኘነውን ማክበር 

ካልቻል ግን ምርቃቱ ይነሳ እና የለመደብን ትቢያ ሆነን እንደ ትቢያ ታይተን ተረግጠን ለመገዛት ተንበርክኮ በለኝ ነው።

 

ናፈቀን ወይ ያነ መከራ? ሽው አለን ያ በዬቤታችን፤ በዬምድጃችን ነፃነት ያጠንበት ድቅድቅ ጥላሸት ዘመን? ትዝ አለን በስጋት እና በሶቆቃ በዕንባ ዘልበን መኖር?


ቢያንስ ወጣቱ ባገጠጠ መከራ ውስጥ የነበረው እንዴት ለዚህ ዘመን አክብሮት አይኖረውም?

 

የአደማ ተማሪዎች ያቀረቡት ቅድመ ሁኔታ „ተመርቀን ስለምንይዘው ሥራ ቃል ይገባልን፤ ውጪ አገር ሄዶ መማር ዕድሉ ቃል ተግበቷል ይሁንልን ነው።“ ለመሆኑ ይህ ሥርዓት ካልቀጠለ በህይወት መኖር ስለመቻሉ ማነው እርግጠኛው?

 

በተፈጥሮ ሂደትም ነገ ስለመኖራችን ማነው ወሳኙ? በሌላ በኩል ትምህርት በተጓጎለ ቁጥር ለቀጣዩ ተተኪም ቦታ ለመልቀቅ ችግር ይሆናል። በድሃ አገር ወጪንም ይጨምራል። ሙሉ አካል ይዞ መማር በራሱ ዕድል እኮ ነው። 

ይህን አርበኛ ከፍያለው አግኝቶታል ወይ? አንድ ዩንቨርስቲ ለማስተርሱ ነፃ የትምህርት ዕድል እንደሰጠው አዳምጫለሁኝ። ሙሉ አካሉን ይዞ ገብቶ አሁን ሁለት እግሩን አጥቶ ነው የሚቀጥለው … ትንሽ ይታሰብ - ህሊና ከኖረን።

 

የሰው ልጅ የበላዩን ሳይሆን የበታቹን ማዬት ይገባዋል። ይህን ያለገኙ ብዙዎች እንዳሉም ማሰብ ይገባል። „ይበቃኛል“ ከቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ መማር ያስፈልጋል። ሙሉ አካልን መነጠቅ እኮ አለ። የዘር ፍሬ መንኮላሽት እኮ አለ። ይህ እኮ በእኛ ዘመን በእኛ ምድር የተፈጠረ ነው። እንደ ዜጋ ልናፍርበት ይገባል። እንደ ዜጋ ገመነኞች መሆናችን ልንቀበለው ይገባል። 

 

ወላጆችም ልጆቻቸውን ሥርዓት ሊያስዟቸው ይገባል እንዴት ናችሁ ብለው ሲደውሉላቸው። በህልም በውንም ቢታሰብ ይህን መሰል ዘመን አልታሰበም።

 

እነደዚህ ዓይነት ምራቃቸውን የዋጡ ጨዋ መሪዎችም ይኖረናል ብለን አላሰብነውም ነበር። የሆነ ሁሉ ዕጹብ ድንቅ ነገር ነው። አላዛሯን ኢትዮጵያ አምላኳ ያልተዋት መሆኑን ያዬነበት ታምር ነው።

 

ልንሳሳላቸው፤ ልንጸልይላቸው፤ ከጎናቸው ልንቆም፤ አይዟችሁ ልንላቸው ይገባል። የአብይ ካቢኔ እኮ ባዶ ካዝና ነው የተረከበው። ባዶ ካዝና መረከብ

 ብቻ ሳይሆን እዬተከፈለው የማይሰራ ደሞዘተኛ ነው የተሸከመው። 

ለአገልግሎት ያልተሰናዳ። ቢያንስ የሚከፈለውን የሚጥን ሥራ ለመስራት ህሊናውን ያላሰናደ። መንፈሱ ብኩን የሆነ ያልተደራጀ። በዛ ላይ በዬፌርማታው ዘረፋ ዋልጌነት ነው።

 

በቂም፤ በተንኮል፤ በሸር፤ በኢጎ የበከተ አስተሰሰብ ነው የተረከበው የአብይ ካቤኔ። በጫት፤ በሽሻ፤ በቁማር የደነነዘ ወጣት ነው የተረከበው የአብይ ካቢኔ። ከራሱ ውጪ ስለምንም ግድ የማይለው ወጣት ነው የተረከበው የአብይ ካቢኔ።

ነፍሱን ለማሰረፍ ጥግ ለማስጠት ዙሪያው እሾህ ሆኖ ነው የጠበቀው። የመንፈስ ጥሪት እንኳን አይዞኽ የሚለው ጠፍቶ በባዶ ተስፋ ነበር ሥልጣኑን የተረከበው።

 

በኋዋላ የተገኘው የምስጋ እና የፍቅር ቀን እርሾ መሆን ይገባ የነበረው ያን አውሬ ሥርዓት እንደዛ ለአምስት ሲታገሉት ሲፋለሙት ነበር። 


ማን አይዟችሁ አላቸው? ማን ከጎናችሁ ነን አላቸው? ማን በቀና አየላቸው ተጋድሏቸውን?

 

ማን ብቃታቸውን ዕውቅና ሰጠው? ማን ድካማቸውን ከቁጥር አስገባው? ቀንጣ ነፍስ ነበርን ልቡን የሰጠ? በምልሰት ከህዳር 2017  እሰከ ሰኔ 16 /2018 ማሰብ ይገባል። ግንቦት ወር ላይ ፓስት የተደረጉ የዛሬ ዓመት መከራ ዝክሮች ከዚህ ብሎግ ላይ ይገኛል። በተደሞ በማስተዋል ማዬት ያስፈልጋል። ስለምን እንታገላቸው እንደነበር ይነግረናል። ዛሬን ለማስቀረት ስለመሆኑ ቁሞ ይመሰክራል።

 

የሰው ልጅ ሃሳብ አለው ሲባል የሚታሰበው ነገር ፋይዳ ያለው መሆን ይኖርበታል። የሰው ልጅ ማሰብ ይችላል ሲባል ወቅት እና ጊዜን ያሰተዋለ እርምጃን መስቀደም ሲችል ብቻ ነው።

 

የሰው ልጅ „ሰው“ ነው የሚያሰኘው መልካም የሆነን ነገር እና መልካም ያልሆነን ነገር ማንዘርዘሪያ ሲኖረው ብቻ ነው። ያለፈውን 27 ዓመት ከዚህ የ7 ወር የአብይ ሌጋሲ ጉዞ ጋር ማፎካካር ቀርቶ አጠገብ ለማስቀመጥም አይቻልም። ልዩ ታሪካዊ ወቅት ላይ ነው ያለነው። 


የቀደመው የወያኔ ሃርነት ትግራይ በ አውራ ፓርቲነት ሲመራው የነበረው ዘመን ደግሞ በሰው ልጅ የሰብዕ ተፈጥሮ መርዝ ሥርዓት ነው የነበረው። የሰው ልጅ እንደ ጥንቸል የጭካኔ፤ የ አረመኔነት ሙከራ የተደረገበት። 


 ሰዎችን አትዋደዱ፤ አብራችሁ አትኑሩ፤ ለምን ትውልድ እንዲፈጠር ተጋብታችሁ ልጅ መወለድ ትቻላለችሁ፤ ከተጋባችሁም ዘር ማፍራት የለባችሁም፤ ቤተሰብ አለኝ እንዳትሉ መለመላችሁን ቅሩ ብሉ የፈረደ የግዞት ዘመን ነው የተኖረው። 

 

ዛሬ ያ የአራዊታዊ ሥርዓት እዬፈረሰ እዬተናደ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵን አፍሪካን ሊመራ የሚችል ሙሉ ሰብዕና ያለቸው ወጣቶች ናቸው ሃላፊነቱን የወሰዱት። ለሰብዕዊነት እና ለተፈጥሮ አክብሮት ያላቸው። ደግሞም ያሰኩታል። ምክንያቱም ስጦታው የፈጠሪ ስለሆነ።


ይህ ቀረ ብለን እንኳን እንዳናማርር ሁለመናቸው የተሟላ፤ የሚያኮሩ፤ የሚያስመኩ፤ ልብ የሚያስጥሉ ናቸው። አንገታችን አያስደፉንም በአህጉራዊ፤ በሉላዊ፤ በአገራዊ ጉዳይም። ክህሎቱን ለመተርጎም አቅም ሁሉም ያንሳል። ምክንያቱም ከጅማሪው አሁን እስካለንበት ጊዜ ድርስ ጥበቡ የልብ ነውና።

 

ሃሳብ ያላቸው፤ ሃሳብም የማያልቅባቸው፤ ኢትዮጵያን ውስጣቸው የእውነት ያደረጉ መሪዎች ነው አሁን ኢትዮጵያ ያላት። ይህ ማለት ግን ግድፈት ትናንትም ዛሬም የለም፤ ወደፊትም አይኖርም ማለት አይደለም። ሰው ናቸውና። ሮቦት አይደሉም። ከዚህ ባሻገር ግን ይህ የሚታዬው መከራው ታቅዶ በተደራጀ ቡድን እዬተከወነ ነው። ሳቦታጁ ታቅዶ በተደራጀ ሁኔታ እዬተከወነ ነው። 


በደሉም የነበረው በተደራጀ በሥርዓት ነው። ይህን ሁሉ መልክ ለማስያዝ ሰፊ ልቦና የተሰጣቸው በጥሩ ሁኔታ መያዛቸው ያደናበራቸው በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለሁከት አያርፉም። ይህን ነው ልብ ማለት የተሰናን። የችግሩን መነሻ እና መድረሻ ወደ ራስ አቅርቦ ጉዳዬ ነው ብሎ መመርምር ያስፈልጋል።

 

የሰው ልጅ ከእጁ የገባውን ወርቅ እንደ ብረት ካዬው ወርቁ ቀልጦ ይደፋል። ወርቅ ቀልጦ ከተደፋ ደግሞ የፈሰሰ ያልታፈስ ይሆናል።


የተደራጁ የአገር ሽፍቶች አቅደው የሚፈጥሩት ቀውስ አልበቃ ብሎ 40 ዓመት የኖረ ችግር ብን ትን ይበልልን ማለት የተገባም አይደለም። እንኳንስ ኢትዮጵያ ያደጉ አገሮች አልጨረሱትም ችግር የሚባለውን የሰው ልጅ እና የተፈጥሮ ቤተኛ።

 

ስንት ዓመቱ ነው ይህ ዩንቨርስቲ አገልግሎት መስጠት የጀመረው? እና ዛሬ የኖረ ኖሮ አገር ጭንቅ ላይ ባለችበት ወቅት ሌላ ጫና መፍጠር ያስፈልጋል ወይ? ሰላማዊም መሆኑ ብቻ ሳይሆን በመሪዎች መንፈስ ላይ ጫና ይፈጥራል፤ ተጨማሪ የቤት ሥራም ያክላል። የቤት ሥራ በመጨመር እኛን ማን ብሎን።

 

ያን ጊዜ ጠ/ሚር አብይ በተሾሙ በ2 ቀን ውስጥ የተስተናገዱት የቤት ሥራዎች ለ10 ዓመት ይበቃል፤ ብዕር የጨበጠ፤ ማይክ ያገኜ ሁሉ እያጣጣለም፤ እያዋከብም ቅደመ ሁኔታ ሲደርድር ነው የሰነበተው፤ እሱ እኮ የረባ ቢሮ አደረጅቶ አንድ ወርክሾፕ ሲሰጥ ያልታዬው ነው ሞጋች ሆኖ የቀረበው። „ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩሽ“ ሆኖ …

  

አሁን አሶሳ ዩንቨርስቲ ያን መከራ አመጣ፤ አምቦ ተከተለ፤ አሁን ደግሞ አዳማ ቀጠለ ነገ ደግሞ ሌላውም ይቀጥላል። ይታወቃል እኮ ገና ከጅምሩ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ስልጣን በያዘ ማግስት በአዲስ አባባ ዩንቨርስቲ የተፈጠረው ሰቆቃ ነፍሱን ይማረው እና የጋዜጠኛ ተፈራ አስማረ ስደት እና ህልፈት እኮ ይኸው ነው፤ በ97 ታይቷል።


ባለፈው ዓመትም የአዲግራት፤ የመቀሌ እና የአክሱም ዩንቨርስቲ ሰቆቃዎችን ማሰብ ይገባል።

 

የዚህ ዘመን ይህ ዕድል ከሾለከ የዛሬ 50 ዓመትም አናገኘውም። በፍጹም። ልብ ይገዛ ከሚሸጥበት በጅምላ ይሁን በችርቻሮ። አሁን የኢትዮጵያ ወጣት ሮል ሞዴል አለው። ሁሉ ያላቸው። ነገ እነሱም ከዛ ለመድረስ ሰብዕና ወሳኝ ነው። ሰብዕና ደግሞ እንደ ተፈጥሮ ሰው ሆኖ ማሰብ መቻል ነው።

 

አብሶ የሳይንስ እና የቴክኖሎጂ ተማሪዎች አዕምሯቸውን ለህውከት ከሳለፉት የተሰጣቸው ምርቃት ይነሳባቸዋል። ይህ ዕድል አንድ ጊዜ ብቻ ነው የሚገኘው። የመጠቀ የሳይንስ ተመራማሪነት ወቅትን ማንበብ፤ ወቅትን መተርጎም ቀዳሚ ተግባሩ ነው። ሩቅ በምናብ ተጉዙ ሰው ያለዬውን ዓለም ፈልጎ ማግኘት ተስጥዖው ነው። ያነን አጠይማለሁ ካለ ግን ቀድሞውንም ለዚህ መክሊት አልተፈጠረም ማለት ነው።

 

ከሁሉ በላይ እናት አገር ካለባት ህምም መነሳት በእጅጉ ያስፈልጋል። ብዙ ቀን አለ ገና፤ ብዙ ሳምንት አለ ገና። ብዙ ወራት አለ ገና። ብዙ ዓመታት አለ ገና … መሻማት ለበጎ ነገር እና ለተሟላ ሞራላዊ ዲስፕሊን እንጂ  ለህውከት ምክንያት መሆን ከጭብጥ ከፋክት ጋር ለተቆራኘ መንፈስ ግጥሙ አይደለም። ራሳችሁን አታሳንሱት። ብልህነት ያተርፋል። ጅልነት ደግሞ ያከስራል። ሳይንስ ጥበብ ነው። ጥበብ ደግሞ ብልህነት እና መስተዋልን አርቆ ማሰብን ይጠይቃል፤ ይህን የተቃጠለ ካርቦን ካደረገ ሳይንስ ሳይንስ መሆኑ ያከትማል። 


ሉላዊ ዓለም ከእናንተ ብዙ ነገር ይጠብቃል። ውጪ መሄድን ሳይሆን የበቃ የጠለቀ የመጠቀ ተግባር ከተሠራ የውጭዎች ሁሉ ነፍሳቸው ኢትዮጵያ ላይ ማድረግ ይችላል። ለዚህ ግን ህሊናን ለስንክሳር ግፋፎ ወቅታዊ ስሜቶች አለማሰለፍ ከተቻለ ብቻ ነው።

 

እራሱ ዘመኑ ሊከበር ይገባል። ለዚህ ዘመን እያንዳንዱ በግል ሁሉም በጋራ ከሚችለው በላይ መስዋዕትነትን ለመክፍል መዘጋጀት ይኖርበታል። ነፃነት የሰጠ ዘመን እኮ ነው። ሰው ነህ ያለ ዘመን ነው። ሰው መሆንህን ተቀብያለሁ ያለ ዘመን ነው። እና ስለምን እንዲጠቁር ይዘመትበታል? ስለምን ነው ትእግስት የሚጠፋው? ስለምን ነው አደብ የሚታጣው? ሰለምን ነው የተሰጠን እዮራዊ ምርቃት ለማክሰል ሳቢያ የሚፈለገለት?

 

የተጠበቀው እኮ አይደለም የሆነው ከተጠበቀውም ከታለመው በላይ ነው ውጤት እዬታዬ ያለው። የሃሳብ ልቅናውም እጬጌ ነው። የምንፈለገው ሥርዓት እንዲዘረጋ ነው። አይደለም ወይ?

 

ለዚህ ደግሞ አንበሶቹ ይዘውታል፤ ያውም በልግብግብ፤ በጨበራ ተዝክር፤ በቃል ሽሙንሙንነት አይደለም፤ መሰናዶው በተሟላ ድርጁ በሆነ ልዑቅ መንፈስ ነው። ረቂቅ ነው ጥበቡ። እርምጃው አደብማ ነው። ሂደቱ ልበሙሉ ነው። ዝግጅቱ ድርጁ ነው። ፍካቱ ነገን ያሰበ ነው። ናሙናነቱ ሉላዊ ነው።

 

ልብ ይሰጠን! አሜን!

የኔዎቹ ኑሩልኝ።


መሸቢያ ጊዜ።፡ 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።