መከራው የዕለት ደራሽ አይደለም። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ= ዘ ቬርሙዳ ትርያንግል።
መከራው የዕለት ደራሽ አይደለም።
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ= ዘ ቬርሙዳ ትርያንግል።
ዬግራጫማው ዬሲቃ ዘመን ፍልሚያው ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያዊነት ጋር ነው።
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"
በቅንነት፤ አማራጭ የለም በማለት፤ የፈለገው ይሁን በማለት፤ ሃይማኖት ነክ ነው በማለት፤ ወይንም ፖለቲካ ቀመስ ነው በማለት፤ ወይንም በገዘፈው የህወሃት ችግር ምክንያት እሱ ከሚመለስ በሚል፤ በከበደ መልኩ የሶሻሊስት ርዕዮት መጤ ሃሳብ ተፈጥሯዊ ከሆነው ከኢትዮጵያ አመሰራረት ጋር ባለመመጣጠን ብዙ አቅም የዴሞክራሲ ፍላጎቱን ጥረት አሰልቺ አድርጎታል።
ከዚህም ዬተነሳ አቅምን መጥኖ፤ አቅምን አዋህዶ፤ አቅምን አዋዶ ቢያንስ እንደ ኩርድሽ ብትን አፈር ለማኝ እንዳንሆን በሚያደርጉን መሠረታዊ ብሄራዊ አመክንዮ ስክነት ነሳን።
የእኛ የምንላቸው አቅሞች ዛሬ የሌላ ናቸው። ተሳስተውም ይሁን ተዘናግተው፤ ተዘናግተውም ይሁን አማራጭ የለም ከሚል ድፍን እሳቤ በቅንጥብጣቢ ጉዳዮች ብቻ ሲደመሙ የገዘፈው መሠረት ንደት ቁብ ሳይሰጡት አያለሁኝ። ይህም ብቻ ሳይሆን መለያ ክብራችን ንፁሁ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅን ጥንት የህወሃት አመጣሽ ብለው የተጠዬፋትን ዛሬ ህጋዊ ሲሉ አዳምጫለሁኝ። ጋዜጠኛ አቶ ሲሳይ አጌና በብዙ ሁነት በአብነት ትምህርት ቤት ስንጠቅሰው ኑረናል። አብሶ እኔ። የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አድናቆት ቃሉ እራሱ ምንጩ ዬእኛ ምስክርነት ነበር። ለረጅም ጊዜ እዬሰማሁ፤ እንዳልሰማሁ፤ እያዬሁ እንዳላዬሁ ተጨማሪም ተቃውሞም ሳልሰጥ ቆዬሁኝ። ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ብዕሬ አነሳችው። ሌሊቱን ሁሉ ሳስበው አደርኩኝ። እኔ ዬማላውቀው እሱ ዬሚያውቀው አገራዊ ችግር ምንድን ይሆን ብዬ።
ከውድቀቱ አካሄድ ጋር እራሱን አስማምቶ ይህን አትዩት፤ ይህን አትስሙት፤ አዋጪው መንገድ ይህ ነው እያለ የሚሠራው ድንጋጌ አልፎ ተርፎ ከህግ ውጪ የወጣን ነገር በህግ ብቻ መፍታት አይቻልም ሲል። አናርኪዝም ይምራችሁ፤ አናርኪዝም ያስተዳድራችሁ፤ አናርኪዝም ይዳኛችሁ ከማለት በላይ መተርተርም፤ መቀደድም፤ መነደልም ዬለም።
ሃዘን አልተሰማኝም። ለምን? መብት ስለሆነ። ግዴታዬ ኢትዮጵያን ያህል አገር በህግ ተፈጥራ በህግ አምላክን ዬኖረችበት ሉዓላዊት አገር ህገ ወጥነትን ተቀበሉ ድንጋጌን አሻም በለው፤ አይ በለው፤ አይሆንም በለው፤ እንብኝ በለው ብዬ መሞገት ግን ይኖርብኛል። አስተምህሮቱ የተሠራች በዊዝደም፤ ዬተበጀች በልቅን፤ ዬተዋቀረች በተመሰጠረ ልዕልና እራስ እግሯ ፍሬዘር ለሆነች አገር ይህን መሰል የደፈረ፤ ዬተጫነ ስላቅ አይሉት ድንጋጌን መቀበል ለእኔ አሰርነት ነው።
መከራው 50 ዓመት የቆዬ። ጊዜ ገዝቶ አድብቶ ዬጠበቀ ነው። በአገርኛው ስሌት። በውጩ ሁነት የኢትዮጵያ ጆግራፊያዊ አቀማመጥም፤ አፈጣጠርም፤ ለአፍሪካ ካስማነትም ቱርኮች፤ ፖርቹጊዞች፤ ጣሊያኖች፤ እንግሊዞች፤ ግብፆች ያለሙትን ለማሳካት ዘመን የሰጣቸው ኃያላን አጋራት ያለሙት ጉዳይ ነው። ለምሳሌ የሦስተኛው ዬዓለም ጦርነት መዳረሻ ዩክሬን እና የራሽያ ሁነት እንመልከተው። የኢትዮጵያ እና የህወሃት ጦርነትን እናመጣጥነው። ሚዛኑን መዝኑት። ለሰላም ግፊቱ የትላይ እንደ አለ። ዩክሬን እና ራሽያ ሰላም ቢሆኑ የሚል ድምጽ ዬለም። ጭራሹን። በእኛ ጉዳይ ግን ዬነበረው ጫና ያያችሁት ነው።
ለምን? ወደፊትስ እንዴት? ምን እዬተሠራ ነው? ማንን ስለአገኙ? እኛስ አድራሻችን የት ላይ ነው። በጥምቀት ዕለት በፋና እና በአሚኮ አረብኛ ቋንቋ ነበር። ቋንቋ ጥበብ ነው። ግን የባቢሎን አግናባቱ ስለምን? አረብ አገር ጠቅላዩ ነበሩ። ዛሬም ሱዳን ናቸው። በዝንጥል፤ በጭፍጫፊ አንመልከተው። ባለፈው ሃጂ ዶር ሙፍቲ ሲገፋ ብሄራዊ አድርጎ የማዬት አቅሙ ስስ ነበር።
ነቀላው እና ተከላው። ለዚህ ፕሮጀክት የተሰለፋ ኃይሎች። የህዝብ የጅምላ እልቂት እና የሰርክ የማቋቋም ተግባር እና ታጥቦ ጭቃነት፤ እንደ ዘመኑ ታዳሚነት ነጣጥለን ወይንስ አዋህደን፤ ገጣጥመን ወይንስ ሰነጣጥረን፤ በታትነን ወይንስ ሰብስበን ማዬት ይኖርብን ይሆን? እኛን ዘመኑ ከወቄቱ አስቀምጦ እዬሠፈረን ነው።
ወደ መሰባሰብ፤ ወደ መማከል፤ ወደ መዋህድ ስንመጣ ድንጋጤው በሰበር ዜና ሱማኔ መጥለቅለቁ እኮ የጀርባ ሳይሆን የፊት ለፊት ዕውነት ነው። የሚጨበጥ የሚዳሰስ። በፍርሰት ውስጥ ፍሰሃ፤ በመናድ ውስጥ አቃቂር፤ በመውደም ውስጥ ቅልጣን፤ በማለቅ ውስጥ ሠርግና መልስ፤ ቅብጥ እና ፍንሽንሽ፤ በመቅለጥ፤ በመፍሰስ ውስጥ አርቲፊሻል ውዳሴ ይህን ነው እምናዬው።
የማንም ዳኛ እሱ እራሱ ነው። ፀፀትን አምጦ ወልዶ ብትን አፈር ላጣ ወገን ድርና ማግ መሆን ሲገባ ይበልጥ አብሮ የኦርኬስተር አባል ስለመሆን ሊያሳስብ ይገባል። አርቲፊሻል ኩሬ፤ አርቲፊሻል የውሃ ዳንስ፤ አርቲፊሻል ባለ ቀለም መብራት፤ አርቲፊሻል የመኪና ማቆሚያ ለማዬት የውጭ ዜጋ ኢትዮጵያ አይመጣም። አለው። በዬሠፈራችን ፓርክ አለ።
ዛሬም፤ ትናንትም፤ ተነገ ወዲያም ኢትዮጵያን ጥንታዊ ያደረጋትን ዊዝደም ፍለጋ ነው ቱሪስትም፤ ግሎባል ፖለቲካውም ተፈላጊ ያደረጋት። ጀርመን ብራና ዘርግታ ልጆቿን በዩንቨርስቲ ደረጃ ግዕዝ የምታስተምረው አንዱ መፀሐፈ ፈውስ የሰጣትን ልዕልና ታውቀዋለች። እንኳንስ ሁለመናዋ ዕንቁ የሆነችበትን።
የባህል ሚር ኢትዮጵያን ታሪኳን፤ ትውፊቷን፤ አካል አምሳሏን ለሚጠዬፍ ሰው ሰራሽ ድርጅት ለኦነግ ሲሰጥ የኢትዮጵያ ፍርሰት ታውጇል። በአንድም ቁልፍ ወሳኝ ቦታ የመሠረት ድንጋይ የሆነችው ቅድስት ተዋህዶ ልጅ የለም፤ ዬለችም። ይህ ፍርሰት አይደለም፤ ይህ መቀርደድ አይደለም። ይህ መሰወወር አይደለም ለአፈ አብይዝም የመቃብር ሥፍራ።
ይህም ብቻ አይደለም በይፋ በአደባባይ አሉታዊ ዴሞግራፊ በርዕሰ መዲናው ሲፈጽም ኢትዮጵያ እዬታረሰች ወይንስ እዬፈረሰች? ይህ እጅግ የገዘፈ አመክንዮ የኔቶ እና የዋርሶ እስከ አሁን ያላባራው ጦርነት ስለመሆኑ ጊዜ ወስዶ ማጥናት ቀርቶ መሆኑን የገብያ ውሎ ያህል ያዬው፤ ያስተዋለው ጭራሽ ዬለም። የሚሆነው ዬንደት ኩነት ሁሉ ምንጩ ይሄው ነው። ፍኖተ ካርታ፤ ራዕይ አልተነገረም ሲሉ እሰማለሁ ትላልቅ ፖለቲከኞች፤ አልፈው ተርፈውም ጠቅላይ ሚሩ ባላቸው የሥልጣን አፍቅሮት ምክንያት ሲሉ ያለውን ብሄራዊ ናዳ የሚተነትኑም አሉ።
ኧረ በህግ። ፎኖተ ካርታ አለ። ዴሞግራፊ። ለዛውም አሉታዊ ዴሞግራፊ። ዬሚገርመው አንዲት የነበረችው ብሄራዊ መግባቢያ ቋንቋም ባቢሎን ግንብ ሲሰራለት ቁጭ ብለን እያዬን ነው። መስቀልም በዞግ ሲደራጅ። ፈጣሪ ማስተዋልን ሲፈጥር እንድናጌጥበት አልነበረም። እራሳችን እንመራበት ዘንድ ነው።
እዬነጣጠሉ ጥቃት ሲያደርሱ የወል የቁም ሞት መሆኑ አናስተውለውም። ሙሉ አምስት ዓመት ያፈስነው ሬሳ፤ አመድ፤ ጥላቻ እና አመድ ነው። ይህን ለማስቀጠል ነው ህገ ወጥነትን ተቀበሉ የሚሉን የራሳችን እንደራሴወች።
አሳቻ መሪ፤ ሰላይ መሪ። ድንገቴ መሬ። ሰበር መሪ። ደራሽ መሪ። ቅጽበታዊ። ፈረሰኛ ውሃ ሙላት መሪ ያላት አገር መሳሪያዋ ፆም፤ ፀሎት፤ አርምሞ፤ ጥሞና፤ ዕምነት ሲሆን ይኽውን ደርምሶ እገሰግሳለሁ ሲል ሃግ ማለት የሊቀ ሊቃውንታት፤ የሊሂቃን፤ የጋዜጠኞች፤ የዕድሜ ባለፀጎች፤ ዬፖለቲከኞች ድርሻ ነው። አገር ሲኖር ብቻ ነው የራስ ህሊና ጌታ የሚኮነው። ያ እዬተቀፈቀፈ፤ ያ እዬተመነጠረ፤ ምሶሶው እዬተነቃቀለ አገር ዬለም። ወረራው ዘርፈ ብዙ፤ ጥቃቱ መጠነ ሰፊ፤ ፍጥነቱ ከብርኃን የቀደመ መከራ ለመቋቋም ሁሉንም የእኔ፤ በሚል የያገባኛል ስሜት ቆቅ ሆኖ መከታተል ይገባል።
በግልቢያ 5 ዓመታት ሙሉ ስንቅ እና ትጥቅ ሆኖ ማሸብሸቡ ውርዴት እና ውርዴ እንጅ ክብር እና ኩራትን አላሳፈሰንም። ኢትዮጵያ በውጭ ጠላት እጅ ብትያዝ በዚህን ያህል ፍጥነት ከሥራችን አይነቅለንም። የንጉሦች ንጉሥ ዬአፄ ሚኒሊክ ቤተ መንግሥት ዬፒኮክ መደለቂያ ከመሆን በላይ ንደት፤ መነቀል፤ መበወዝ የለም። ቤተ መንግሥቱ ጥንተ ሥሙ ተሰርዟል። ሥሙ እራሱ ባለ ዘውድ፤ ባለ ተክሊል ቅርስ እና ውርስ ነው።
እጅግ ሥልጡኑ፤ እጅግ ዘመናዊው፤ ቅኔው ቋንቋ አማርኛ ግሎባል ደረጃው በተፈጠረበት አገር ተጥሶ ፈተና ላይ ነው። ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማው የማበሻ ጨርቅ ያህል ክብር የለውም። ነፃነትን የሰራ አፍሪካን ያበጄ የጠይሞች የቃልኪዳን ውል በመዲናዋ በአዲስ አበባ ልዕልናው ወልቆ ሲረጋገጥ ከዚህ በላይ መቃብርነት በምን ይሰላል?
ይህን ዘለግ አድርጌ እምጽፈው የሚያዳድጡ መሲሃን ስላሉ ነው። በውስጣቸው ያለውን መርማሪ ፈጣሪ ነው ዬሚያውቀው ትናንት ምን ዛሬ ምን እንደ ሆኑ። በዜግነት ህብረት ግን የውራጅ ማንነትን መሻት የህሊና ብሎንጎደሎነት ይመስለኛል።
ሌላው በመሪነት ውስጥ ዕብለት ከነገሠ ጉዞው ክህደት ነው። የተቋማት ውቅረትም ይህንኑ ያጠይቃል። አምስት ዓመት ሙሉ እኔ ያዬሁት በከቅላይ ሚር፤ በፕሬዚዳንት፤ በጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ፤ በዓለሙ ሎሬት ዬሰላም አባት አብይ አህመድ አሊ የሚደገም አንድም አመክንዮ የለም። ለምን? ውሸት ስለሚረሳ። ክህደቱ በዬዕለቱ ነው። ለለት የአፍ ማሟሻ ቃል ለቅጽበት ብቻ።
ሰው ይሰለቸኛልም ዬለም። ሲሰልሏት ዬኖሯትን አገር መንፈሷን በጣጠቁት። አቅላችን ሰወሩት። በድንገቴ ሱናሜ አጥለቀለቁን። እኔስ እላለሁኝ፤ ለአፍሪካም ለኢትዮጵያም ቤርሙዳው ትርያንግል ናቸው።
ብዙ ጊዜ ዬሚነሳ ነገር አለ ባለፈው ጊዜም ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና አንስቶታል። ዙሪያው ጨለማ ነው። አማራጭ የለንም ሲል። በዘመነ ህወሃትም የእኞቹ እስኪጠነክሩ ህወሃት ሥልጣኑን ይዞ ይቆይ ሲል ነበር። የእሱ የምልከታ አንቴና የእኔ ስላልሆነ መብቱ ነው። በዬዘመኑ በያላችሁበት ዳክሩ የሚል የቅንድብ ፀጉር ፡ዕይታውን የሚያጋራው።
ዓለም ስትፈጠርም፤ ስትኖርም በልውጥ ህግጋት ውስጥ ናት። አማራጭ እንድናጣ ያደረጉት አሳቻው ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ናቸው። እሳቸውን እንደ ፀሐይ፤ እንደ ጨረቃ ይቆጥራሉ። የፋንታዚ ልዑል ናቸው። ያ ሁሉ ዕምቅ አቅም አሻግራለሁ ሲሉት ተላሌ ሰልችቶት ነበር እና ሸብረክ ብሎ ገብቶ ለወራት ስንቅ ተመድቦለት ሆቴል ባጀ። ዛሬም ሁሉ ነገር ተከፍሎላቸው የሚዘባነኑ ዘመናዮች አሉ። ተቋማትን ሁሉ አዋርደው፤ አላሽቀው ቢና ጢናው አወጡት። ተጽዕኖ ፈጣሪውን ሁሉ አንበርክከው ነዱት። ለመሆኑ ወዳጄ አቶ ኦባንግ ሜቶ፤ኮነሬል ጎሹ ወልዴ ዬት ገቡ? ሌሎች ሥም አይጠሬ ትንታጎችስ????
ምርጫ አሸነፋ። በምናብ በተሰራ ማህበር። በአናርኪዝም ጉዞ ዕውቅና ተሰጥቶት። ጫን ተደል መከራ ተጭኖ፤ ስጋት ተደግሶ። የቡራዩ፤ ዬለገዳዲ ለገጣፎ፤ የሻሸመኔ ዝዋይ፤ ዬአጣዬ ሽዋ ሮቢት ነዲድ፤ የባህርዳር የጭፍጨፋ ውሎ፤ ዬሰኔ 16/2010 መከራ ሁሉም ታቅዶ ዬተከወነ ነው። ወሊሶ ሲኖዶስ ሲፈጥሩ አጣዬን የዶግ አመድ እያደረጉ ነው።
አማራጭ እንዲታጣ ታቅዶ እዬተሠራበት ነው። ነገ ደግሞ አንድ ትልቅ ነገር ያወድማሉ፤ ወይ ይገድላሉ በዛ ጫና ያሹትን ይፈፅማሉ። አቅም፤ ክህሎት፤ እርጋታ የጋዳ ሥርዓት ተፈጥሯዊ ባህሪ ይሁን አይሁን አላውቅም።
እነሱ ወረራ፤ መስፋፋት፤ አስምሌሽን እና ዲስክርምኔሽኑን ጨፈላልቀው እያስኬዱት ነው። እኛስ አብረን መጋለብ ወይንስ ተግ ብለን ሂደቱን በፈርጅ በፈርጅ ለይተን ለመዳን እንተጋለን ወይ? ጥያቄው ይህ ነው።
"ተረኝነት" እጭ ፖለቲካ ነው። የሥልጣን ሱስ ቀለም የሚለውም ግርዶሽ ነው። ደፍሮ ለመሞገት አቅሙ ያጋደለ ሁሉንም ላለማስከፋት የታለመ ብልጥ የፖለቲካ ዕሳቤ። ለፖለቲካ ስኬት ብልጠት ሳይሆን ብልህነት ነው ፈውሱ። ብልጠት የዝናብ ጃኬት ነው። ለድልም አያበቃም ወልቆ መቅረት ነው።
ዬዘመኑን የፖለቲካ ባህሬ ከስሜት ወጥቶ፤ ከራስን መሸንገል ተሻግሮ አገርን፤ ትውልድን ለማዳን ሊውል ይገባል። ውዳሴ ከንቱም ሬሳ ከመቁጠር ሰኔል ከማምረት አላወጣንም። ለእርቃንነታችን ከፈን ያስፈልገዋል። ሁሉም በራሱ ውስጥ ጥሞና ያድርግ። የጥሞና ጊዜ ይውሰድ። ይህ ትዕዛዝ አይደለም። ኧረ ምን በወጣኝ።
ፖለቲከኛው፤ ጋዜጠኛው፤ ሚዲያወች፥ ተንታኞች ቢጠሞኑ ያተርፋሉ። ምላስም እረፍት ይሻል። ማይኩም እንዲሁ። በዝግታ ውስጥን ከውስ ለማድመጥ መፍቀድ።
እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
እንዴት አደራችሁ እንደምን ዋላችሁልኝ? መሸቢያ ጊዜ። ደህና ዋሉልኝ፤ ደህና አምሹልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
26/01/2023
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ