እዮባዊቷ ቅድስታችን።

እዮባዊቷ ቅድስታችን።
በማዕከላዊ መንግሥት ሁነኛ ልጅ የሌላት እናታችን።
አባቶቻችን ቅድስና አላነሳቸውም።
አቨው ልቅና አልጎደለባቸውም።
ብፁዓን መንፈሳዊ ፀጋ አልሳሳባቸውም።
ደናግላን ገሃዳዊ የቀለም ትምህርትም አልነጠፈባቸውም። ሁሉም አላቸው።
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"

 
አንዳንድ ነገር አዳመጥኩኝ። ቀረ፣ ጎደለ ስለሚባለው አመክንዮ። ግፍ ነው። በጣም። እርግማን እንዳይሆንም ፈጣሪ ይርዳን። አሜን።
ብፁዑ አቡነ ኤርምያስ የሠሩት ገድል በቂ ነው፣ የማስተዳደር፣ የመምራት፣ የማደራጀት፣ የርህራሄ ክህሎታቸውን አይተንበታል።
ይህ ሁሉ ሰርክ በግብረ ሰላም ዬሚሽሞነሞነው ዘመነኛ ባለስልጣን ሁሉ የሳቸውን ሲሶ ያክል አቅም ቢኖር የሚሊዮን ደም እና ዕንባ በቅድስት አገር ኢትዮጵያ ምድር ባላጎረፈ ነበር። በብዙ እኮ ተዋርደናል። አንገታችንም ተደፍቷል።
ዬእኛ አባቶች ተረጋግተው ጥሪያቸውን እንዳይከውኑ ዘጠኝ አብያተ ቤተ ክርስትያናት በጅጅጋ በማቃጠል፣ በማንደድ ነበር የአብይዝም ዘመን አህዱ ያለው።
ብፁዑዓኑ አበው አንድም ወር፣ አንድም ወቅት፣ አንድም ሳምንት፣ አንድም ዓመት፣ አንድም ጊዜ ከወከባ እርፍ ብለው ተረጋግተው የአደባባይ በዓላትን ያከበሩበት ጊዜ አልነበረም። አስተዳደራቸውን ሰክነው ለመምራት አልታደሉም። እነሱን የሚዋጋ የሰለጠነ ሾተላይ ዘመን ላይ ነውና የባጁት።
በርካታ ቤተ መቅደሶች ሹግ ሆነዋል።
ማህበረ ምዕመኑ፣ ማህበረ ካህናት እስከ ቤተሰቦቻቸው ሰማዕትነት በተለያዬ ጊዜ ተቀብለዋል። ሰብሳቢም የላቸውም።
አጥቢያ አድባራት ዬፈረሱት ፈርሰው፣ የቀሩት ተዘግተዋል። ማህበረ ምዕመኑ ሚሊዮኖች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። በሃዘን፣ በዕንባ፣ በዋይታ ዬከተመ ዘመነ ምፅዓት።
እንደዚህ ዘመንም በርከት ባለ ሁኔታ ብፁዑ ቅዱሳን ጳጳሳት በሥጋ ዬተለዩን ዘመን የለም። አልነበረምም። ይህም ሌላው ያጎደለው አምክንዮ ነው። አንድ ሊቀ ሊቃውንት መጉደል ገድለ ድርሳናትን ማጣት ነው። ላወቀበት። ብፁዓንጳጳሳት መፀሐፍት ናቸው። ለዛውም ንዑድ።
ጦርነቱ እራሱን የቻለ ዬገዘፈ መከራ ነበረው። ግጭቶች ሌላው ትራጀዲ ነበር።
በአዲስ አበባ ታቦት እስከ መታሠር ተደርሷል። ዘማርያን በዓውደ ምህረት ተጨፍጭፈዋል በወይብላ ማርያም። ስለ መስቀሉ ለመሮጥ እንኳን ፈቃድ ዬለም በርዕሰ መዲናዋ በአዲስ አበባ።
ለጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ከመኪና ማቆምያ ፓርክ፣ ከወዳጅነት ፓርክ ያህል የሚመጣጠን ነፃነት ቅድስታችን የላትም። ታፍናለች።
የአደባባይ በዓላት ያለነበራቸውን የሃይማኖት ተቋማት በፋክክር አሰልፈው ተጋድሎውን በድርቡ ገምደውታል።
በመንበረ ቅዱስ ሲኖዶስ በፆታም፣ በእምነትም የማይፈቀድላቸው ቲም ወ/ሮ ሙፍርያት፣ ቲም ወ/ሮ አዳናች በድፍረት ተገኝተዋል። እላፊም ተናግረዋል።
ቲም ለማም ሆኑ ቲም ደመቀ ከዕምነት አኳያ ለዛ አደባባይ ዬማይፈቀድላቸው ነበሩ።
በብፁዑ ወቅዱስ አባታችን ፓትርያርክ አቡነ ማትዬስማ በመንበረ ፀባዖት ሳይቀር እንዲደፈሩ ሙከራ በ2012 ነበር።ጽህፈት ቤታቸው ድረስ ተኪዶ።
ዘግይቶም እንደዛ ታመው በአውሮፕላን ማረፊያ ግፍ ተፈጽሞባቸዋል። ርግማኑን ከቻሉት። የጽናታቸው በትረ አቅም መከተው እንጂ ብፁዑ ወቅዱስ አባታችን ያላዩት የመከራ ሰንበር የለም። የሰጣቸው ናቸው እዮባዊነት። በዚህ ፈታኝ ዘመን እሳቸውን የመሰለ ጽኑ አባት ስለሰጠኝ ፈጣሪዬን አመሰግነዋለሁኝ።
ቤተ ክርስትያናችን ትናድ ዘንድ፣ ትቸገር ዘንድ፣ ሰላሟን ታጣ ዘንድ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ሌት - ተቀን ባትለዋል። መደበኛ ተግባራቸውም ይኽው ነበር።
በዚህ ሂደት ቅድስት ቤተክርስትያናችን ቀኖ እና ዶግማዋን ጠብቃ መቆሟ በራሱ የነጠረ ድል ነው። ፀጋዋ ሰማያዊ በመሆኑ ወጀቡን ሁሉ ተቋቁማ ከዚህ ደርሳለች።
ጎደለ፣ ተሸረፈ፣ አነሰ፣ሳሳ ተብላ ልትወቀስ፣ ልትነቀስ አይገባትም። ፈፅሞ። ኢትዮጵያን ጠላት ቢይዛት እንኳን ይህን ያህል ሁለገብ ጦሮ አይመጣባትም።
ቅባት ምንትሶ ቅብጥርሶ ተብሎም አዲስ ዘዬ ተዘይዶ ነበር እኮ። በውስጥም በውጪም እሾ በጋመ ረመጥ ተሰናድቶ ተንገላታለች። ተንገርግባለች። ብጽዕናዋ እዬመከተው እዚህ ደርሳለች።
ዘመናይነት ይመስለኛል ይህን፣ ያን ብታስተካክል መባሉ። መጀመሪያ ክብሯ፣ ልዕልናዋ፣ ልቅናዋ፣ ታሪክ ትውፊቷ ዕውቅናውን ይዞ መገኜቱ በራሱ ትንግርት ነው። ዋነኛ በጠላት ተፈርጃ ያለች እኮ ናት።
በብዙ ሁኔታ አምስት ዓመት ሙሉ በድፍረት ድፍጠጣ እና የጭፍለቃ ዲስክርምኔሽን ተፈጽሞባታል። ሰላም አጥታ ብን ትል ዘንድ በመንግሥት ፖሊሲ፣ "በብልጽግና" ሰነድ ተሰናድቶ ሁሉንም የመከራ ዓይነት ተቀብላለች። በሰማዕትነት።
እንዲያውም ይህን በጠቅላይ ሚር ቢሮ የሚመራ ፈተና ተሻግራ አለች መባሉ የሰማዬ ሰማያት ታምራት ነው። ትንግርትም ነው። በመንበረ መዲናዋ እኮ በትውስትነት እንዳለች ገዢወችም እኛም አሳምረን እናውቀዋለን።
ዝም የምንለው የአባቶቻችን ዊዝደም ድል እንደሚያደርግ፣ የፈጠራት፣ የቀደሳት አምላኳ እንደማይተዋት ስለምናውቅ ብቻ ነው። ቤተክርስቲያናችን ብሄራዊ ብቻ ሳትሆን ዓለም ዓቀፋዊትም ናት። ድርብ አጋርም አላት። አቤት ብትል ትደመጣለች። ምዕመኔን ላነቃንቅ ብትልም ዲታ ናት። ግን የአርምሞ ልዕልት፣ የተደሞ ቅድስት ናት።
ቅዱሳኑ መሳሪያቸው ፀሎት ነው። ትምክህታቸው ስግደት ነው። ጋሻቸው ምህላ ነው። ጥላ ከለላቸው ሱባኤ ነው። መተማመኛቸው የምርቃታቸው አባት እዬሱስ ክርስቶስ ነው። ረዳታቸው ቅድስት እናታቸው ድንግል ማርያም ናት።
እስካሁንም አልዛሉም። ነገም አይዝሉም። የአባቶቻችን አምላክ ኃይል እና ጥንካሬ፣ ብርታት እና ጋሻቸው ነው።
በሥራ ተገላይ፣ በጭካኔ ተገዳይ፣ በአረመኔነት ታጋች እና ታሰሪ የማን ልጆች ናቸው። ስለ እሷ ትውፊት፣ ታሪክ፣ ሥልጣኔ ምስክርነት ሰጪ ተቀጣሪ ልጆቿ አይደሉም።
ከፖለቲካ ሥልጣን በፍፁም ሁኔታ የተገለለች ናች ዬኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ። ግፋ ሞልቶ እዬፈሰሰ ነው። ይህ ሁሉ ተችሎ ስሜን ኢትዮጵያ የሁለመና መሠረት ተገሎ አዲስ ህገ ጣሽ ተቋም ተፈጠረ።
"የሚመካ ቢኖር በእግዚአብሔር ይመካ።"
"ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ"

 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
24/01/2023
አቤቱ አምላካችን ሆይ ጽናትን አስታጥቀን። አሜን።

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።