ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ከዛሬ ጀምሮ የሦስት ቀን የሱባኤ ዓዋጅ አወጀች።
ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ከዛሬ ጀምሮ የሦስት ቀን የሱባኤ ዓዋጅ አወጀች።
"ዬሰው ልብ መንገድን ያዘጋጃል
እግዚአብሔር ግን አካሄዱን ያቃናለታል።"
(መጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ ፲፮ ቁጥር ፱)
የዚህ ግራጫማ የሲቃ ዘመን የፈተናው ሁሉ ሸክም የተጋተችው ቅድስት እናታችን በተረጋጋ፣ በሰከነ፣ በተደሞ ሆና ዛሬ ሱባኤውን ብፁዑ ቅዱሳናት አቨው አህዱ ብላለች።
ፈተና ሲጠፋ ፈተና እንበረታ፣ እንጠነክር፣ እንፀና ዘንድ ብለው ሱባኤ የሚገቡት የአቨው ይትበኃል ሕይወቷ ነውና፣ ዘመኑ ሰርክ የሚደቅንባትን ፈተና ትቋቋመው ዘንድ አምላኳን፣ ፈጣሪያዋን በአኃቲ ድምጽ ትለምናለች።
ሐዋራያዊቷ ቅድስት እናት ቤተ ክርስትያን በተደሞ ልቅና፣ በዕድምታ ልዕልና በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ይህን ጭጎጎት ዘመን ትሻገረዋለች።
ሰማዕቷ ፀጋዋ፣ ብርታቷ፣ መሰጠቷ ዬሚቀዳው ከሰማያዊ ኤዶም ነውና ዛሬም ስለ አገረ ኢትዮጵያ ሰላም፣ ስለ ሕዝቦቿ አንድነት እና ፍቅር ትሰብካላች፣ ታስተምራለች፣ ትለምናለች።
በዘመናችን ይህን መሰል ንዑድነት ያሳዬን አምላክ ይክበር ይመስገን አሜን። ሁሉን የሰጠን አምላካችን ሁለንም አድርጎልናል። ሙሴ አለን። እረኛ አለን። ጠባቂ አለን።
ስለሆነም ከትልልፍ ወጥተን አኃቲ ቤተክርስትያናችን በምትሰጠን መመሪያ መሠረት በአርምሞ፣ በጥሞና፣ በንጽህና ሦስቱን ቀን እናሳልፍ።
ምንም ዓይነት የሥጋዊ ልቅምቃሚ ሰበር ዜና ወሬ ሳያስበረግገን፣ ለዛም አቅል ሳንመግብ፣ ለእሱም ደራሽ ሁነት ሳንሰግድ ዕዝነ ልቦናችን ከእናታችን ከቅድስት ቤተ ክርስትያን ውሎ እና አዳር ዜና ብቻ ይሆን ዘንድ በትህትና አሳልፋለሁ።
ከተወረወረ ቀስት እንድን ዘንድ ፈጣሪ በሰጠን እናት መሪነት ሁሉንም ሸክም ተቋቁመን ክብራችን እናስጠብቃለን። "ከመከራ በስተጀርባ ታላቅ ክብር አለና።"
እንደ አንድ ሴት ልጅ ዬሚያሳስበኝ በትራንስፖርት፣ በምግብ ብክለት ጉዳት እንዳይደርስ ብፁዓና አቨው ጠንቃቃ ቢሆኑ እላለሁኝ። እንዲያው ድንገተኛ ህመም ቢሰማ እንኳን በፀበሉ፣ በእምነቱ በመስቀሉ ፈውስን መሻት ይገባል።
የዚህ ዘመን ዓይነቱ ብዙ ነው። የወጣ አይመለስም። ሆስፒታል ዬገባም ድኖ አይወጣም። ጥንቃቄ ያተርፋል እንጂ አያከስርም። ፈጣሪ ይርዳን። አሜን።
ወሥብሃት ለእግዚአብሄር።
ሥርጉትሻ አገልጋይ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ