በዚህ የጭንቅ ጊዜ እንዴት ሰው ጥል ያምረዋል?

የሚገርመኝ።
በዚህ የጭንቅ ጊዜ እንዴት ሰው ጥል ያምረዋል?
በዚህ የጭንቅ ጊዜ እንዴት ሰው ምቀኝነት ትዝ ይለዋል? በዚህ አስደንጋጭ ጊዜ እንዴት ዝና ሰው ትዝ ይለዋል?
በዚህ የጭንቅ ጊዜ ፕሮፖጋንዲስትነት እንደምን ያምራል? በዚህ ጨለማ ጊዜ የሰው ልጅ ከበቀል ጋር እንደምን ጋብቻ ይፈፅማል?
በዚህ ግራጫማ ዘመን ስለምን ሰውን ለማስከፋት ይጣራል?
በዚህ ቀኑም ቀን፣ ፀሐይም ፀሐይ በማትመስልበት የሞት ዘመን ወገኑን ወገኑ እንደምን ያሳደዋል? እንደምንስ ያስረዋል? ስለምንስ ይገድለዋል ያስገድለዋል?
የሰው ልጅ ጠላቱን ኮሮናን ወይንስ አምሳያውን የሰውን ፋጡር ይዋጋ? ሚዛኑን ሳስተውል የዕውነት ይጨልምብኛል።
እማያስፈራ ነገር እኮ ዛሬ የለም። የኖራችሁበት ቤት ያስፈራችኋል። የኖራችሁበት ግቢ ያስፈራችኋል። የኖራችሁበት እቃ እራሱ ያስፈራል። መንገዱ ያስፈራል። መስኮት ከፍታችሁ ስታዩ አዬሩ ያስፈራል።
የምታነሱት፣ የምትጥሉት ነገር ያስፈራል። ፖስታ ለመክፈት ትፈራላችሁ። ደብዳቤውን መክፈት አትደፍሩትም። እንዳታጥቡት ወረቀት ነው። እንዳትተውት ትሰጋላችሁ። ስለዚህም የፀጉር ማሞቂያችሁን ከፈት አድርጋችሁ በሙቀት አገላብጣችሁ ትገርፋታላችሁ።
ፖስታው ሳይከፈት እኮ ነው ይህ ሁሉ ጉድ፣ ከተከፈተ በኋላ ደግሞ ደብዳቤውንም እያገላበጣችሁ በወከባ በወላፈን ታላጉታላችሁ። የምጥ ጊዜ ፈተና።
እና በዚህ ወቅት ቂም፣ በቀል፣ ሸፍጥ፣ ሴራ፣ ትርምስምስ ሲል ስታዩት ይገርማችኋል። አጠገባችሁ ሞት እያጫወታችሁ፣ እዬኮለኮላችሁ እኮ ነው ይህ ሁሉ ክፋ መንፈስ ተሰንቆ ደግሞ ጉግስ የሚገጠመው። የሚገርመው ሰባራ ገል ይዘው እሳት የሚያጫጭሩት ናቸው።
ብቻ ይገርመኛል። ሞት እና ሰው፣ ሞት እና ተፈጥሮ ተፋጠው የሸፍጥ አደንጓሬ ሲኮን እግዚኦ ነው ተሳህለነ።
ልብ ይስጠን ስንደግፍም ዕውነትን ከማዳን፣ መርኽን ከመከተል ቢሆን ጥሩ ነው። ማነካካት የማይገባውን አናነካካ፣ እራሱን አስችሎ ፕሮፖጋንዳውን ማስነካት ግን ከልካይ የለበትም። ስንቃወምም ከቂም እና ከበደል ፀድተን መሆን ይኖርበታል።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
እውነት እንሁን።

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።