"ጠሚር አብይ አህመድ እና አቶ ጃዋር መሃመድ ሁለቱ ብቻ ለምርጫ ቢቀርቡ ምርጫዬ አቶ #ጃዋር #መሃመድ ነው። (ዶር ዮናስ ብሩ በአንድ አፍታ እና አንከር ሚዲያ። ) ኢትዮጵያን እንዴት ብትለካ? እንደምን ብትገመት? እኔ ሥርጉተ ሥላሴ ተወዳዳሪ አቶ ጃዋር መሃመድ (ሃጂ) #ብቻ ቢሆን #ምርጫዬ አይሆንም። በፍፁም።
(ዶር ዮናስ ብሩ በአንድ አፍታ እና አንከር ሚዲያ። )
ዶር ዮናስ ብሩን በመደበኛ የምከታተላቸው ሙሁር ናቸው። ቃለ ምልልሳቸውን አብዛኛውን ጊዜ አዳምጣለሁኝ። ደፋር እና ቀጥተኛ አስተያዬት ያቀርባሉ። ቀድመው የሚዮቸው አመክንዮችም አሉ። የሆነ ሆኖ የአቶ ጃዋር መሃመድን (ሃጂ) ወደ ፖለቲካው መድረክ በሙሉ አቅም መመለስ በቀናነት ካዩት ሙሁራን ዶር ዮናስ ብሩ አንዱ ናቸው።
የገለጡልንም፤ ያልገለጡልንም፤ እሳቸውን በመደበኛ ለምንከታተል ሰወችም የተገለጠልን አመክንዮ ይኖራል። ያ አመክንዮ የሳቸው ብቻ ሳይሆን፦ ሃሳቡን የሚጋሩ ሌሎችም ፖለቲከኞች እንዳሉ ይረዳኛል። የአማራ ትግል መሟሟቅ የሚያስፈራቸው ጉዳይ #የአማራ #ሊቃናት #ለአገር #መሪነት ከሆነ የማይመች አመክንዮ ይሆናል።
እኔ አቅም ያለው፤ የተሟላ ሰብዕና ያለው፤ ውስጡ ኢትዮጵያን እና ህዝቧን የማያገል ከሆነ ከየትኛውም ወገን ኢትዮጵያን ቢመራ ችግር የለብኝም። እንዲያውም የእኔ ዕይታ ከፖለቲከኞች ውጪ ሳይለንት ማጆሪቲ ውስጥ የሚገኙ ሰብአዊነት፤ ተፈጥሯዊነት፤ አዛኝነት እና አጽናኝነትን መርሃቸው ያደረጉ #በቲም ኢትዮጵያን ቢመሩ የሚል ዕይታ ነው ያለኝ።
የሆነ ሆኖ ኢትዮጵያን እንዴት ብትለካ? እንደምን ብትገመት? እንደምን ብትታሳብ እንዲህ ያለ ውሳኔ ላይ ሊያደርስ እንደቻለ አላውቅም። ዶር ዮናስ ብሩ ብቁ ሃያሲ ናቸው። ይህ አቅማቸው እና አቋማቸው የት ሄዶ አቶ ጃዋር መሃመድ (ሃጂ)ምርጫቸው እንደሆነ አልገባኝም። ኢትዮጵያ፦ ህዝቧ ሁልጊዜ እንደ ጥንቸል መሞከሪያ ጣቢያ መሆኑ ለምን ይሆን?
አቶ ጃዋር መሃመድ (ሃጂ) ሙያው ፖለቲካል ሳይንስ ነው። ፕ/ መራራ ጉዲና እኮ ሙያቸው ብቻ ሳይሆን መምህርም ናቸው እኮ። የፖለቲካ ሳይንስ ሙሁርነት ብቻውን አገርን ለመሪነት ያበቃልን? አንድ ቀበሌ በመሪነት ያልመራ በቀጥታ የአገር መሪነት እጮኛነት በምን ቀመር ይሆን??? አክቲቢስነት የአገር መሪነት ደረጃ ካልተሰጠው በስተቀር??
ዶር ዮናስ ብሩን ያህል ትልቅ ዓለም ዓቀፍ የሊቆች ሊቅ ኢኮኖሚስት፤ በአገራቸው ፖለቲካ በትጋት የሚሳተፉ ይህ የመሰለ ዕውቅና ሲሰጡ በጣም ያስደነግጣል። የኢትዮጵያ መሪነት አህጉሩንም ያካታል እኮ። ለአፍሪካም ይታሰብ እንደማለት። በአቶ ጃዋር መሃመድ (ሃጂ) ጀርባ ያለው ሃይልም የተከደነ ነው። #ማንም #ምንም የሚያውቀው ነገር የለም።
ለአቶ ጃዋር መሃመድ (ሃጂ) ኢትዮጵያ ከነታሪኳ፦ ትውፊቷ፦ እምነቷ፦ ወግ ልማዷ፦ መንፈሷ፦ ነፍሷ ልትሰጥ? ወጣት እኮ ነው። ቅጽበታዊም ነው። የጥሞና ጊዜው የወደድኩለት ቢሆንም መሰረታዊው የጃዋሪዝም ሰብዕና ግን እያዬሁ ነው። እና እኔ ሥርጉተ ሥላሴ ተወዳዳሪ አቶ ጃዋር መሃመድ (ሃጂ) #ብቻ ቢሆን #ምርጫዬ አይሆንም። በፍፁም።
ለሌላ ደረጃ ላለው ቦታም ቢሆን ከህዝብ ጋር ተገናኝቶ መሬት ላይ #ተፈትኖ ነጥሮ መውጣት ግድ ይሆናል። የኮንፒተር ትግል እና በአገር መንግሥት ህግ እና ሥርአት ኃላፊነት እና ተጠያቂነት ባለው ቦታ መስራት ከፍ ያለ ልዩነት አለው።
አቶ ጃዋር ገና መድከም አለበት። ምኑ ተነካ እና። እሱ የተቀላቀለው ኦፌኮ እሱን ስለአገኜ ምን #እድገት አሳዬ? ምን ስልጣኔ አተረፈ? የአመራር ፈተናውን ገና አልጀመረውም፤ እንኳንስ ሊመዘን፦ አለፈ አላለፈ ሊባል ቀርቶ። ሁለን ነገር በጥንቃቄ እና በማስተዋል ቢሆን መልካም ነው።
የሆነ ሆኖ የዶር ዮናስ ብሩ ሪኮመንዴሽን በቀላል ሊታይ አይገባም። ትጉህ ጸሐፊ ናቸው። ቻይም ናቸው። በኢትዮጵያ ፖለቲካ መሳተፍ እኮ ቋያ ነው። እኔ ይህን ስጽፍ ያለውን ሁኔታ ስለምከታተል እዬተሳቀቅሁ ነው። የሆነ ሆኖ ዶር ዮናስ ከዲፕሎማቱ ማህበረሰብ ጋርም ግንኙነት አላቸው። ምክር ይጠዬቃሉ። አስተያዬት ይጠዬቃሉ።
ጥናትም ያቀርባሉ። ይህን አቋማቸውን እንደ ያዙ ከሆነ በጣም ለኢትዮጵያ የገዘፈ ፈተና ይሆናል። ምንም እንኳን ፈፃሚው እና አስፈፃሚው የእግዚአብሄር #ፈቃድ ቢሆንም። መሪነት ቅባዕም ነውና። በሌላ በኩል የሰውን ልጅ ለመምራት የፀና አቋም እና ተለዋዋጭ ያልሆነ ሰብዕናን ይጠይቃል። ለነገሩ ኢትዮጵያ የከበደችን ለሁላችንም ነው።
ግን……… እንዲያው ግን ከ120 ሚሊዮን ህዝብ ማህል አንድ ዕጣ ነፍስ ለመሪነት የሚታጭ #አቅመኛ ጠፋን? አንደበቱ የታረመ፤ ህይወቱ መምህር የሆነ??? ይህን ያህል ኢትዮጵያ #የእጩ #መሪ ድርቀት አለባትን? አንገተ ደፋታው፤ ጭምቱ ሳይለንት ማጆሪቲውስ???
ሌላው የሚያሳዝነኝ ነገር ብቻ ያለው አብይዝም ይልቀቅ እንጂ የመጣው ይምጣ የሚባለው ነገር ነው። ስንት ጊዜ ኢትዮጵያ እስከ ህዝቧ #ትቀጣ? በሌላ በኩል ከነፃ አውጪ ግንባር የኢትዮጵያ ትንሳኤን ማሰብ ብልህነት - ጎደል ይመስለኛል። ውስጣቸው ከውስጧ የራቀ ነው። አገር #ትሞክረው አይባልም። ጠፈፍ ያለ ተግባር በቅንነት ከውኖ፦ አገርን ማስቀጠል ብልህነት ይመስለኛል። ሁልጊዜ ሽግግርም፤ እስኪ እንየውም ደንበር ሊሰራለት ይገባል።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ደህና እደሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
16/01/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ