የጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ጉራጅ ዘመን የአማራ እናትን ከመኖር እርስት ነቀሏታል።


እንኳን ወደ ቀንበጥ ብሎግ በሰላምመጡልኝ።

የጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ጉራጅ ዘመን
የአማራ እናትን ከመኖር እርስት ነቀሏታል።
የአማራ ወጣት ተስፋውም ባሩድ እና ካቴና ሆኗል።

„እግዚአብሔርን የዘነጉ ሰዎች ግን በቃል ጠሩት፤
ባልንጀራም አደረጉት፣ በዚህም ጠፉ።“
(መጽሐፈ ጥበብ ቁጥር 1 ቁጥር 16) 
  
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።
18.01.2020


·       መነሻ!
„ሴቶች በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ ከወንዶች የሚስተካከሉበትን
መንገድ ለመፍጠር ብልጽግና አበክሮ ይሠራል{ዶር አብይ አህመድ}። 
ስላቅ! ነው ለእኔ። ዘለግ ብሎም ይፈተሽ፤ ይሞገትም።

ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ሁልጊዜ የታይታ ስለሆነ ነገራቸው ዓለም በዚህ እሳቸው በሌሉበት ሁኔታ የተሳሰተ መንገዳቸውን ሃቅ መስሎት ዕውቅና እንዲሰጥ በእንግሊዘኛም ከሥር ይጽፋሉ። ከቶ አገር ስንት ዓይነት ሰው ይሆን ዬምታበቅለው?ከዬትኛው ዩንቨርስቲ ይሆን የተማሩት ይህን መሰል አረንዛዊ ጉዳይ?

ከዬትኛውስ ፕላኔት ይሆንስ የመጡት? ኢትዮጵያዊው ምድር አስተናግዶት የማያውቅ የአሟሟት ዓይነት በልጇቿ ላይ ይፈጸም ዘንድ የአማራ እናት በዘመነ አብይዝም ተቀጥታበታለች። ዶር አብይ አህመድ የአማራ ሴት ተቆርቋሪ እንዳልሆኑ የአማራ ሴት ጠንቅቃ ታውቀዋለች። 

አስተርጓሚም ባለቅኔም፤ ፕሮፖጋንዲስትም አትሻም፤ እንዲሁም የኦዳ ሥርዕዎ መንግሥት ካድሬም አያስፈልጋትም። ምድሪቱም፤ ጋራ ሸንተረሩም ያነባሉ - ይመስክራሉም አይደለም ተጠቂዋ የአማራ እናት // የአማራ አንስት።

ዬዬትኛው ብሄረሰብ ልጅ ነው ከዬትኛውም ዩንቨርስቲ በሴራ በደቦ - በወል እና በገፍ ነፍሳቸው ፍትህ አልባ የሆነችው? የአማራን ውስጥ በመረበሽ አማራጭ ሆነው ለመውጣት፤ በተጨማሪም አመጽ ቢነሳ የአማራን አቅም ለካቴና እና ለባሩድ ለማቀበል አቅደው ነው የሚሠሩት። ስርንቅ በግራጫማ ሰብዕና።

ይህን ዘመንም ታሪክም ይዳኛው ዘድን በአጽህኖት ለሰማዩ ዳኛ ለእዬሱስ ክርስቶስ አቤቱታ ይልካል የድምጽ አልባዋ የአማራ እናት// ሴት ዕንባ። ምን አለባት ምን አልባት ኢትዮጵያ አደብ የገዛ ትክክለኛ ሙሴ ካገኜች በቃሽም ካላት፤ በአማራ የዘር ማጥፋት ሃውልት ይቆም ይሆናል ለመንጥር አውራው።  

·       ስለዬትኛዋ ሴት ይሆን የሚነግሩት ባለ ኖቤሉ ጠቅላይ ሚኒስተር?

„ሴቶች በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ ከወንዶች የሚስተካከሉበትን
መንገድ ለመፍጠር ብልጽግና አበክሮ ይሠራል“{ዶር አብይ አህመድ} ስላቅ!
ዲስኩር ብቻ። ስለዬትኛዋ ሴት የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አቻነት ይሆን የሚነግሩን ጠቅላይ ሚኒስተሩ? አገር አልባ ስለሆነችው የአማራ ሴት ይሆን? ለመሆኑ በሳቸው ህሊናስ ሆነ በሚመሩት ህገ - መንግሥትስ የአማራ እናት/ ሴት ኢትዮጵያዊ ዜጋ ናትን ዘመን ብሎስ ያምናል የሳቸው ጉራጅ ዘመን።

ጉራጅ ያልኩት ሲሶ መንግሥት ብቻ ስላላቸው፤ እንዲሁም አገርን አሳልፈው ላልተገለጠ መንፈስ እያስረከቡ ስለመሆኑ ስለሚረዳኝ ነው። ብቻ መንግሥት አልባ ስለሆነችው የአማራ ሴት እንዲህ ቧልትን ነጋ ጠባ የሚመግቡን ጠሚሩ ሌላ ሥራ አጡ። ስንት ዓይነት ወዘተረፈ ተልዕኮም እንዳላቸው ፈጣሪ ነው የሚያውቀው
„ሴቶች በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ ከወንዶች የሚስተካከሉበትን መንገድ ለመፍጠር ብልጽግና አበክሮ ይሠራል“{ዶር አብይ አህመድ}። ስላቅ!

ባለቤት አልባ ስለሆነችው የአማራ ሴት ይሆን ይህ ምጻአታዊ ንግግር? በዬዕለቱ እሬሳ ተረከቢ ስለምትባለው የአማራ እናት ይሆን የሚነግሩን? ስለዬትኛዋ ሴት ይሆን እያዋዙ የሚጭኑት? 

ወይንስ የአማራ እናት ልጆቿን ለትምህርት ልካ በሳቸው መንግሥት እና በኦነግ ቡድን በቅንጅት ታግተው የበቀል ማወራረጃ ስለሚሆኑት የአማራ ወጣቶች ይሆን የሚደሰኩሩት? ስለዬትኛዋ የአማራ ሴት ይሆን የጨረቃ ቤታቸው ባለ ሎው ኦነጋዊው ብአዴን የተስፋ ማህደርነት የሚተርኩልን? ያደክማሉ!

የሚገርመው የአማራ ሙሁር  „የቀደመው ኢህዴግ መጥፎ ሽታ ቢኖርበትም ከቀደመው ኢህዴግ የአሁኑ {በጨካኙ የኦዴፓ መንፍስ የሚመራው ብልጽግና}“  የተሻለ ስለመሆኑ አምናለሁ“ ይልኃል - የአማራ ሊሂቅ፣ የማህበረ የሙታን መንፈስ ቅሬተ - አካል። ስንት ዓይነት ህሊና ይሆን ያለው? ይህ እኮ ሌላ ሳይሆን የሬሳ ሃሳብ ተሸካሚነት፣ የማንፌስቶ ፍቅር ከሰው ልጅ ፍቅር መብለጡን ነው የሚያሳየን።

ሰው መሆን እንዲህ ተስኖ፣ ሰውነት አይችለው የለም አንገትም ከረባት፣ አካልም ገበርዲን ይሸከማል። ትናንት ከብረት የተሰራ ቁርጥራጭ ሆነህ፣ ከህሊናህ ጋር በአኃቲነት በሙሉ አቅምህ ህዋህትን መክተህ ዛሬ ደግሞ በሽንገላ መርዝ በኦነጋዊው ኮምዳዳ ውስጠ ወይራ ልሳን የዴሞግራፊ ሰለባ ሆነህ በህሊና ነቀላ እና ተከላ ሟሙተህ ለሞትህ ፈቃድ ዓይነተኛ ፕሮፖጋንዲስት ሆነህ ትገኛለህ። እነምንም። የኦሮሙማ ሎሌ! 

ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ ከቶ ስለዬትኛው የአማራ ሴት በፖለቲካ እኩል ሆና በኢኮኖሚ የሚቀረውም እንደሚሰናዳላት ከማህበረ ደራጎን መበልጸግን ስለምታልመው ይሆን ዲዲታዊው ስብከቱ? ይሆን ይሆን ተስፋ ከጭካኔ መንፈስ ከማህበረ - ኦነጋውያን ሊጸነስ? መኖሩን በዓዋጅ የተቀማ ህዝብ እኮ ነው አማራ። አገርኛ ዜግነቱን የተነጠቀ እኮ ነው የአማራ ህዝብ።

አማራ ነኝ ማለት ሽብር ነው ተብሎ በመደበኛ ፍርድ ቤት በችሎት በዳኛ የታወጀበት ህዝብ እኮ ነው የአማራ ህዝብ። ይህን ሁሉ አቅዶ እየከወነ የሚገኘው የጠቅላይ ሚኒስተር የሸንገላ ልሳን ፍጥረተ - ነገሩ ማወቅ ምን ይሳናል። በዕብለት የታጀለ ብጭቅጫቂ።

የሚነገሩን ዶር አብይ አህመድ ለትምህርት ሄዳ በአረመኔነት በቡድን ተገዳ ስለምትደፈረው የአማራ ልጃገረድ ይሆን ዝክንትሉ ወሬያቸው? ወይንስ ተስፋን ሰንቃ ዩንቨርስቲ ገብታ መጠጊያ አጥታ በርንዳ አዳሪ ስለሆነችው የአማራ ወጣት ተስፈኛ ሴት ይሆን የሚያጫውቱን? ምን አለ ኢትዮጵያ ላይ ሆሊውድ ቢያስከፍቱ። ጥሩ አክተር ናቸው፣ የወጣላቸው። ጥሩ ይተውናሉ።

በዬደቂቃው በመሳጭ የድምጽ ቃና፤ በወዘተረፈ ቅይጥይጥና ዝክንትል የካራክተር ጭብጥ፤ ማለቂያ የለሽ በሆነው የሥንኛት ድርድር ንድፍ እዬለዋወጡ ያዛሉ፣ ያደንዝዛሉ መጨረሻ „በሬ ሆይ ሳሩን አይተህ ገደሉን ሳታይ“ ሁለመና በግባዕት ይጠናቀቃል። ሁሉም ተራውን ይጠበቅ። በአንድም በሌላም ይሰናበታል። የሳቸው ቅርበት ለሞት ነው። „አይጥ ለሞቷ የድመትን አፍንጫ ታሸታለች።“ የምዕት መርገምት።

ዶር አብይ አህመድ ለአማራ እናት እርግማን ናቸው። መጡልን ሳይሁን መጡብን ሊባሉ የሚችሉ - በድርጊታቸው። ከቶ ከዕለተ ሹማታቸው ጀምሮ አራን ይሆን መከራ ለአማራ እናት / ሴት ያዘዙላት ዶፋዊው የምተር ዘመቻ? ተግ አለ ይሆን ድንኳን መትከሉ ለአማራ ቤተሰብ?

የእራሮት ዳስ መጣሉስ አደብ አገኜ ይሆን ለአማራ ህዝብ? እረፍት ተሰጣት ይሆን የአማራን አስከሬን ተረከቢ ተብላ፤ ተቀብይ ተብላ በዬዕለቱ የምትቆፈረው ፍደኛዋ ኢትዮጵያዊቷ መሬት? የአማራ እናት ከፈጣሪዋ ምርቃቷ የተነሳ ዕለት ነበር ጥሩ የጭካኔ ተዋናይ ጠሚር በቅድስት አገር ኢትዮጵያ መጋቢት 18 ቀን 2010ዓ.ም የተሾሙት። ግራጫማ - ጨለማ!

·       ጦር በረዶ  - የወጀብ ብርንዶ።

 „ሴቶች በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ ከወንዶች የሚስተካከሉበትን
መንገድ ለመፍጠር ብልጽግና አበክሮ ይሠራል“{ዶር አብይ አህመድ}። ውስጡ የለገመ በቀል።

ህም! ብቂተ ቢስ የሆነ ነገር፤ ምናምንቴ ድርሰት እንዴት እንደሚያቅለሸልሸኝ። ቀጨርመጨሬ ዲስኩርም እንዴትም የማህጸን ውጋት እንደሚሆን ማን በነገረልኝ ለቤተ - መንግሥቱ ዓውራ ለጸረ አማራ አዝማች እና የዘመቻ መኮነን? የአማራን መንፈስ በየትኛው አደባቸው ነው ሊያስጠጉት የሚችሉት? ቁንጥንጥ። ዘመቻ ላይ ናቸው እሳቸው የአማራን ፖለቲካ ሥሩን ነቅለው ግብዕተ መሬት ለማስገባት። ተሳክቶላቸውም። በባንዳ አማራ ፊታውራሪነት።  

„አብከሮ ይሠራል“ ይሉናል። ስለማን ይሆን ኦነጋዊው ኦዴፓ ኢህዴግ አብክሮ የሚሰራው? ሰለ ኦነግን በሁለገብ ድጋፍ አብቅቶ አገር ስለማስረከብ ይሆን? ስንት ዓይነት ማላገጥ አለ? እራሱ ሥንኛቱ መከራውን የመግለጥም፤ የመሸከም አቅም የላቸውም። ስንትስ አይነት ማዳዳጥ አለ?

ስንትስ አይነት አንጀተ ቢስነት አለ? ስንት ዓይነትስ የሁለገብ የቅጥፈት ትራጄዲ - የሁለገብ የሲቃ ግራጫማ ትወና - ፌዛዊ የኮሚዲ ድንገቴ ተውኔት አለ? ግን ዶር አብይ አህመድ እንዴት ተፈጠሩ? ስለምንስ ተፈጠሩ? የጦሮ በረዶ - የወጀብ ብርንዶ!

·       እያመጥኩ ተዚህ ደረስኩኝ። 

ጫን ተደል የበቀል ውጤትን በየደቂቃው ተሸከሚ የምትባል የአማራ እናት ጭንቀት እረፍት ነሳኝ። የአማራ እናት ሸበላዋን፤ ቀንበጥዋን ይማርልኛል // ትማርልኛለች ብላ እንደ ፈጣሪዋ እንደ አላህ መንግሥትን፤ ማህበረሰቡንም አምና ልካ ሰኔል እና ቹቻ ተሸከሚ የተባለች ምንዱብ ናት። መሬት የተደፋባት።

19 ወራት በሙሉ ትኩሰ እሬሳ፤ 19 ወራት ሙሉ የማያበራ መርዶ፤ 19 ወራት ሙሉ የማያቆም ዋይታ ብቻ ተቀለበች፤ 19 ወራት ሙሉ ወቀሳ - ነቀሳ ቻይ የተባለች የአማራ እናት - ሴት። በዚህ የተፈለገው አይነት እርምጃ ይወስድባታል፤ በዚህ ደግሞ ነቀሳ። የት ትድረስላቸው በሰርክ መከራ የሚደበድባት የአማራ እናት ለጃርታዊው የአዳማ ሥርዕዎ መንግሥት ሲባል? ምንስ ትሁንላቸው ለኦዳውያኑ?

ከዛው ከበድኑ ኢህዴግ ከግንባራቸው አብረዋቸው የኖሩት ምን አልባትም ሲኒዬር ሊሆኑ የሚችሉ፤ እሳቸውን ሆነ የዞግ ድርጅታቸውን ኦህዴድን በትጋት ደግፈው የሚሠሩት እንኳን ከዚህ ማዕት ሊተርፉ አልቻሉም።

እናትም ከእንባ ስንቀኝነት አልተረፈችም። ስለምን? አማራ ናቸዋ! ለሳቸው ሥልጣን መጠንከር ላይና ታች ያሉት ሁሉ በነቂስ በተጠመደው የበቀል ፈንጂ ነደዋል - በባዕታቸው። ጠሚሩን ህዝብ ይቀበላቸው ዘንድ ሌት ተቀን የባከኑ ጓዶቻቸውን ዘመንንም ትውልድንም አዳኝ መስለዋቸው ለሰኔል እና ለቹቻ ተሸልመዋል። „ሙሴ“ ያሏቸው እኮ የአማራ መንፈስ ነበር። በጥይት ተደብድበው ተገደለው እሬሳቸው በአደባባይ የተጎተተው። ማተበ ቢስነት።

ወደፊትም ተውኔቱ አፈጻጸሙ ሊለያይ ይችላል እንጂ በአማራ ፖለቲካ ቅብረት ላይ ተጠናክሮ ቀጣይነቱን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። „አያያዙን አይተው ሸክሙን ይቀሙታል“ እንደሚሉት ጎንደሬዎች። ሁሉም ጓዳውን ሲዳስሰው የመንጥር ዘመቻውን ምህንድስና ያውቀዋል።

ይህው አሁን ደግሞ የማገት ትራጀዲይ እያዬን አይደለምን? ነገ ደግሞ ሌላ በአዲስ መልክ በቅንጅት ከአንዱ ትራጂዲ ወደ ሌላው እንዲህ ዕንባ ለአማራ እናት/ ሴት በገፍ ይቀናል። ከሰኔ 15ቱ 2011 ዓ.ም የአማራ ሊሂቃን እና ልዩ ኃይል ጆኖሳይድ ትዕይንት በኋላ እንኳን ስንት አሰቃቂ ኢሰብአዊ ክንውኖች፤ እርምጃዎችን አዬን በአማራ ላይ። መሬት መቼስ አልችል አትል የጥፋቱን መኮነን መሬት ፈርዶባት ተሸክማለች። ናዚዝም። ኦሾቲዝም

·       ማቃት።

የሆነ ሆኖ የመከረኛዋ የአማራ እናት የጭንቀት ድምፆዋ እዬመጣ ነሰተኝ። አገር የሌላት አሳራኛዋ የአማራ እናት የዓይን ተስፋዋ፤  የዓይን አበባው የዕዬለት የአፈር ሲሳይ ሲሆንባት// ስትሆንባት የምታፈሰው ዕንባም ነሰተኝ። መቻልን ማስቻል አቃተኝ። አዎን መቻልን ማስቻል አቃተኝ። በቃ! አቃተኝ። ማቃት! ማቅ።

ኡኡታ! እንዴት ይለመድ?! ለቅሶስ እንዴት ይለመድ? ሃዘንስ እንዴት ይለመድ? አዲስ ዘወትራዊ የዋይታ ማንነትስ እንዴት ይለመድ? እናት ለልጇ፤ ልጅም ለእናት ዓለም ናቸው። ሲጨልም - ልጅ እና እናትነት እዬተያዩ ሳይተያዩም ይዋጣሉ  - በጨለማ። አብይዝም እንደዚህ ነው ግራጫ። አብይዝም በሁሉ ነው ድብን ብሎ የሚቀናው። ያልተናደ፤ ያልፈረስ ሰብዕና ኢትዮጵያ ምድር የለም።

ለናሙና „ቲም ለማ“ መራራ ስንብት አድርጓል። በቀጣይም ከመኖር እርስት መነቀል ሊኖር ይችላል። በቃ አብይዝም እንዲህ ነው። እዬነቀለም፤ እዬደረመሰም፤ እዬጨፈላላቀም ወደፊት መገስገስ። ሌላውም ተሰልፎ ወረፋውን ይጠበቅ። ለቀኑ ቀን ነስቶት እንደ ተቆለፈ የመኖር ትነት - በትንታ አይቀሬ ነው።
  
·       ንድሮ።

ጤና ይስጥልኝ ቅኔዎቹ እንዴት ናችሁ? ደህና ናችሁ ወይ የአገሬ ናፍቆቶች? ዘገዬሁ አይደል ለሰላምታው? ዝም ብዬ ዘው አልኩኝ። ይቅርታ። ሰረቁን። ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ የፈለጉትን በፈለጉት ሁኔታ ፈጽመው፤ ለነገው የእልቂት ኦፕሬሽናቸው ደግሞ አለስልስ ለማለት በቁስሉ ላይ መጥተው እንዲህ ዝንጥ፤ ቅብጥ እና ቅልጥልጥ ሲሉ እግዚአብሄር በመንበሩ ያለ እንኳን አይመስላቸውም። በቃለ ምህዳናቸው ያለሙ እና ህሊናን የቀደመውን ጭካኔ አስረስተው፣ ማግለሉን አዘናግተው ቀጣዩን አዲስ ምሾዊ መከራ ያጫሉ - ይጭናሉም። ግፍ እማይፈሩ።

እኔ ቀድሜ አጣናቸው ስለነበር በ16.01.2020 ሙሉ ቀን ሌሊቱን ጨምሬ የቀደመውን ንግግራቸውን ሳዳምጥ ነበር። የራሳቸው ዩቱብ ነው ብዬ አስባለሁኝ „Hasab Meda። አሁን ቀለሙም ተለውጧል እንደ ሙሽራው ኦነጋዊው የኢህዴግ ወንበር። ውዶቼ ሌላውን ሁሉ ተውት፣ ይህን ብቻ በተደሞ አዳምጡት። እራሴን እንደ ተፈታኝ አስቀምጬ የሞገትኩበትን።

Ethiopia - Dr Abiy ከላይ ስትሆኑ በዛ መነጽር ብቻ ታች አትመልከቱ

ሙግት ከራስ ጋር። ከቶ ስህተተኛ ነበርኩኝ ያን ያህል ፊት ለፊት ወጥቼ ስሞግትላቸው ብቻ ሳይሆን ፈተናም በዓይነት የተቀበልኩላቸው ስለ እራሴን ጠይቄ - ተፈታተሽን። ሰው ይህን ያህል እራሱን ደብቆ እንዴት ሊጓዝ ቻለ? ታምር እኮ ነው። ማጅክ ነገር ነው የሚመስለው እያንዳንዱን ግጥጥምጥሞሽ ስታስተውሉት።

ስህተተኛ አልነበርኩም ያን የርህርህና፣ የተጠያቂነት እና የኃላፊነት ስሜት ሙሉዑነት አዳምጬ፤ ያን የመንፈሳዊ ሃብት ንጽህና ተመስጬበት መደገፌ። ተቀናቃኞቻቸውንም መሞገቴም። አሁን ደግሞ ድርጊቱን ለክቼ ጭካኔያቸውን አስተውዬ መቃወሜም ግድፈት አይደለም ብዬ አምናለሁኝ። መሪ እንዲሆኑ ተመኜሁ - ሆኑ። ታዩ - ተፈተሹ - ተመረመሩ። እናም ወደቁ። ክፉ የሚለው ቃል አይገልጻቸውም። አበደኑን። አዛሉን። ላጉን። ለጉንም።

ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ „ወይ ዘንድሮ“ ይላል የዘሃበሻ „ሹክሹክታ“። ሰሞኑን ይልቅ ትውር አላለም። ብቻ ወይ ዘንድሮ ነው። አያልቅ የለም ይህ ዲስኩር አሁንም በአዲስ ሞድ ህሊናን ይላሽቃሉ። የሳቸው ተውኔት በሞድ ነው። ህሊናን ጎርጉራው፣ ቆራርጠው አቋሙን ይዘርፋሉ። የህሊና ነቀላ እና ተከላ ከቶ ሙስና አይባል ይሆን? ሙስናን እጠዬፋለሁ ስለሚሉ? ግን ምናቸው ይታመናል?!

ሃሳብን ግን እንደሚዘርፉ ያውቁታልን ይሆን እራሳቸው ዶር አብይ አህመድ? ሥንኛትን ሳይቀር። „ይህቺ አገር የተዋስናት እንጂ የወረስናት አይደለችም“ እሳቸው ባዘጋጁት „ ከእርምጃ ወደ ሩጫ“ ብሄራዊና ነፍስ የነበረው ጉባኤ የቀድሞው የአቶ ዩናስ ደስታ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዳይሬክተር የተናገሩት ሃብት ነበር። እሳቸው ቀብ አደረጓታ „ብለናል“ ይሉታል።

« ይህ አገር የወረስነው ሳይሆን የተዋስነው ነው። » (አቶ ዮናስ ደስታ

ግን አቶ ዮናስ ደስታ ይህችን ምድር ሲገናኙ ስንት ጊዜ ይሆን እልል የተባለላቸው ... ?

የአቶ ዮናስ ደስታ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ስለመነፈግ።


አቶ ዮናስ ደስታ ለ8 ዓመት የሠሩበትን ኃላፊነት በአንድ ቀላጤ ነበር የተባረሩት። የንጉሦች ንጉሥ የአጤ ሚኒሊክ ቤተ - መንግሥት ዕድሳት በኦሮሙማ መንፈስ ሊለብጡት ሲወጥኑት ሰው አላማከሩም። ቢሮው እንዲያውቀው፤ የሙያው ባለቤቶች ሙያዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ አልፈቀዱም። ህጋዊ ዕውቅና ያለውን ድርጅት አላማከሩም። አጤ እንደልቡ አብይዝም። ኢትዮጵያ የግል ንብረታቸው ናት እንዳሻ እምትሸጥ እምትለወጥ፤ እምትሸነሸን እምትታገት ወይንም እምትገጣጣም ተገጣጣሚ ቤትም። 

የሆነ ሆኖ እንዴት እኛ አላወቅነውም ብለው አቶ ዮናስ ደስታ ሲጠይቁ፤ ስለምን ይህን ጠዬቅከኝ ብለው ነበር አጤ እንደልቡ ጠ/ሚር አብይ አህመድ በአንድ ቀላጤ ደብዳቤ ከሃላፊነት ቦታቸው ያባረሯቸው። „ይህቺ አገር የተዋስናት እንጂ የወረስናት አይደለችም“ ይህን ሥንኝ ግን በጉልበት የራሳቸው አድርገውታል። „ይህቺ አገር የተዋስናት እንጂ የወረስናት አይደለችም ብለናል“ በማለት።

ሙስናው እንዲህ እያለ ያዋዛል። ኮፒ ራይት የሚባል ነገርም አለ። ዶር አብይ አህመድ ግን ኮፒ ራይት ብሎ ነገር አያውቁም። ህግ፤ ደንብ፤ ሥርዓት አይገዛቸውም አያስተዳድራቸውም። የሰሞናቱ የፓርቲ ምስረታቸው አንዱንም የፓርቲ አመሰራረት መርኽ አልተከተለም። በጥሰት ነው የተከወነው። ሁሉ አውቃለሁ ቢሉም ከመርኽ አንጻር እስከ አደራጁት የምርጫ ቦርድ ሹመት ወለቁ። መርኽ ያልገዛው መንፈስ መርኽን ያሰተዳድራል ተብሎ አይታሰብም። 

ወደ ቀደመው ምልሰት ሲሆን  „ብልጽግናው በሴቶች ጉዳይ ላይ ተግቶ ይሰራል“ ይላል የጨረቃው ፓርቲ ሙሽራው ኢህዴግ በሊቀመንበሩ አማካኝነት። 50 % ሴት የካቢኔ አባል ተሆኖ ምን ፈዬደ? ምንም። ይህ  „ሴቶች በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ ከወንዶች የሚስተካከሉበትን መንገድ ለመፍጠር ብልጽግና አበክሮ ይሠራል“ {ዶር አብይ አህመድ}።

ለአማራ እናት ለድቀት! ለአማራ ሴት ለህሊና ቁርጥማት ይሆናል የሚሰራው ቁማሩ። የዳማ ጨዋታ መሰላቸው የሰው ነፍስ ርቁቅነት። ከምንም አይቆጥሩትም እንዳሻቸው ቃለ ምህዳኑን ለቀቅ ሲያደርጉት። አንድ ቀን ተጨንቀው፤ አንድ ቀን ተጠበው አያውቁም ስለ አማራ ሴት። የአማራ ልጅን ለመማገድ ጦርነትን ሳይለምኑ ይቀራሉን? ሥራ የሚፈልጉ የድሃ ልጆች አሉን ሲሉም ስለ አዳመጥን። ማን ለማገዶ እንደ ተሰናዳ ይታወቃል ያው አማራ።

የሆነ ሆኖ ካለ መሪ ዕቅድ አዲስ ፓርቲ መሰረትኩ ያለው የግልብያ መንፈስ „ሴቶች በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ ከወንዶች የሚስተካከሉበትን መንገድ ለመፍጠር ብልጽግና አበክሮ ይሠራል“{ዶር አብይ አህመድ} ይለናል። ከአማራ ውጪ ሊሆን ይችላል። እሱም የጋሞ፤ የጌዴኦ፤ የአማሮ፤ የአፋር ሴቶች ሲታሰቡ ባዶ ነው ቃለ ምህዳኑ። ወና።

ለመሆኑ የዓለሙ የሰላም አባት ዶር አብይ አህመድ ሃይማኖት አለዎትን? ክርስትናውንም ለቤተ መንግሥት ዙፋን አልመው ለፖለቲካ ማስተናበሪያ የተቀበሉት ስለሚመስለኝ ነው ይህ ጥያቄ በትህትና ያነሳሁት። አንድ ቀን ሰው ምን ይለኛል አይባልንም? ከምን ዓይነት ቤተሰብ ይሆን ያደጉት - ? መሰንጠቅ። 

እንደማያደርጉት እያወቁ ጊዜ መግዣ ልሳነ ስብከቱን ይጠቀሙበታል። ምርኮኛው እጁን ወደ ኋላ አድርጎ ይግተለተላል። የስልበት ስልባቦት።

እባክዎትን ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ በአንዱ ይጽኑ? ይለመኑን። ጭካኔን ምራኝ ብለው ይህን ያህል አረመኔነት በአማራ ህዝብ ላይ ምድር ታስተናግዳለች። በሌላ በኩል ደግሞ ጻድቅ ነኝ በቃላት ትዕይንት ይተውናሉ። በዚህ ቀመር አይሆንም። በዚህ ማምታታት ለአገር አሳቢ ነኝ አይሆንም። አገር ካለሰው ምንም ነው።

ካለ አማራም ኢትዮጵያ መቆም አትችልም። ይህ ሁሉ ብሄራዊ ዝቅጠት በሁሉም መስክ አማራ 50 ዓመት ሙሉ ከፖለቲካው እንዲገለል መደረጉ የወለደው ግዙፍና አንጋፋ ችግር ነው። ብቁ ፈላስፋ ቢያገኝ። እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መክሊት ይዞ ይወለዳል የምለውም እኔ ለዚህ ነው።

ጸጋ፤ ጥሞና፤ ልቅና፣ ልዕልና እና ጥበብ የማህበረሱ ከላይ ከአንድዬ የተሰጠው ምርቃትም መክሊትም ነው። ይዩት ከአማራ ሊሂቃን ሰማዕትነት በኋላ እንኳን ያለውን የምጣት ውሎ። አሁን የለውጡ የቡድኑ መሪ አቶ ለማ መገርሳ በህሊናዎት ውስጥ፤ እሳቸውስ እርስዎ በህሊናቸው ውስጥ ይኖሩበት ይሆን? አቅም የትም አይደፋም። አቅም ጥበብ ይፈልጋል።

አቅመወትን በገዛ እጀዎት ናዱት። በነፃ የተሰጠን ፍቅር አሁን በስብከት፤ በሽልንግ፤ በጉቦ፤ በማስፈራራት፤ በማንአለብኝነት፤ በመግደል፤ በማሰር፤ በማዳፋት ደፍጥጠው ለመግዛት ለእያንዳንዳችን ሰላይ መድበው ይደክማሉ። ምርቃተዎት ተነስቷል። አዬሩ ስመዝነው ክልፍልፍ፣ ያልሰከነ መንፈስ ነው ያለው።

ውዶቼ ቆሰልን እኮ። ዛሬ የምጽፈው ተጠያቂነትን በሚመለከት አቶ ለማ መገርሳ፤ አቶ ጃዋር መሃመድ ወይንም የቤተ መንግሥቱን ኮከብ ቆጣሪ ለእነ ዘረ ሌንጮወዲማ፤ ወይንም ለአቶ ጃልመሮ አይደሉም።

ለአማራ እናት የሃዘን ዘመንን ለማደራጀት፤ የዋይታ ዘመን ለማቀናበር፤ ሰላሟን ለመናጥ ልዩ ጥሪ ስለ አለባቸው ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ መሆናቸውን አበክሬ ላስገነዝብ እሻለሁኝ። ተጠያቂው እሳቸው ናቸው። መሪ ናቸው ለዛውም የኖቤል ተሻላሚ። የሄሰኑ የሰላምም ተሸላሚ።

ሌላው ጥሩ ማስረጃ ግን አማራ ላይ ኮሽ ባለች ቁጥር ምን ያህል ያባንናቸው እንደ ነበር በምልሰት ሂደቱ ይቃኝ። ያ ደግሞ በጥዋቱ አንቂ ደወል ነበር። ሁሉ በቅንጅት ተከትሎት ቢሆን ኖሮ ትርፍ ነበረው ያ ተጋድሎ። ግን ዘለው ሄደው አለዘዙት። የቅዱስ ላሊበላ እድሳትን ባለቤት በመሆን። የሆነ ሆኖ ያ ሁሉ የሜንጫ ሰላማዊ ስለፍ በቀያቸው ሲኬሄድ እዛው ሰፈራቸው ከሜንጫቻው ባዕት ትውር ብለው አያውቁም፤ አማራ ሰልፍ ካደረገ ግን እዛ ወጤ ይሆናሉ። ገና በመጀመሪያው የሹመታቸው ዕለት ነበር ገመናቸው የተዘረገፈው።

የአማራ ብሄርተኝነትን ለመስበር አንድ ዓመት ሙሉ በትጋት ሰርተውበታል። በዛ ላይ ተጠምደው የራሳቸው ድርጅት ተናደላቸው። የሰው ቤት አፈርሳለሁ ብለው ሲታክቱ እሳቸው ተነሳፈፉ። ይህን ለማካካስ ከአዲሱ ጉልቻቸው ከግንቦት 7 ጋር ሠርግና መልስ ላይ ናቸው። ለአማራ ፖለቲካ ድቀት የቃል ኪዳን ሰነድ ፍርርም ቢኖርም ሁሉም ተራው ሲደርስ ጠበቂው ሸኘው ዜናው ይመጣ ይሆናል።

ግርባው ብአዴንም ለሎሌነት ደረጃውን ማስጠበቅ የተፈጠረበት ነውና ያው ሞረድ አዘጋጅቶ እያሰናዳ አማራ ከምድረ ኢትዮጵያ እንዲሰረዘ ካሪያ /ቢላዋ/ አቀባይ ነው። „እንኳንም ደስ አለው ብአዴን/ ቲም ንጉሡ“ የፈለገውን በፈለገው ልክ እና መጠን የሚፈጽምለት፤ ጥቃት አውጪ መካች ጠቅላይ ሚኒስተር አግኝቷል። የአማራን እናት የጭንቅ ጃኖ እና የስጋት ደመና የሚያሸልም - በልበ ደንዳ ዘመንኛ ፈርኦን።

የኦቦ ንጉሡ ጥላሁን ትናጋ ግድነት - በኦቦነት ግንድነት

ዕንባና የማስቲካ የፕሬስ ሴክራትርያት ውሎ። /ቅኝት/

የአባ ገዳ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ሚዲያ AMMA „ፊንፊኔማለትን አህዱ አለ

·       ?

ከሰሞናቱ ስለ ሴቶች ያደመጥነው ትልም „ጽድቁስ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ“ ነው። የአማራ ሴት እኩልነቱ ቀርቶባት በጭቆና ለመኖር በተፈቀደላት። ዛሬ ዛሬ በጭቆና ለመኖር እራሱ ሱባኤ የሚያስገባ ሆኗል።

የአማራ እናት በግራ ቀኝ በበቀል ታረሰች። አላልቅ ብሎ እንጂ አማራ በአንድ ቀን ምጥጥ ቢል ይፈለጋል። ይህም ነው የአብይዝም ተልዕኮ። ይህ የላላ ሙትቻ ትልም „ሴቶች በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ ከወንዶች የሚስተካከሉበትን መንገድ ለመፍጠር ብልጽግና አበክሮ ይሠራል“{ዶር አብይ አህመድ} ለአማራ ሴት ይህ ምኗ ሊሆን? መግደያ ማጭዷ፤ መክሰሚያ ፖሊሲ ነው የሚሆነው።

„ሰው አኮ ወዶ አይስቅም“ ትል ነበር የእናቴ እናት ጽግሽ። የአማራ እናቶችን፤ የአማራ ሴቶችን፤ የአማራ ሙሁራን ሴቶችን፤ የአማራ ህፃናት ሴቶችን፤ የአማራ ተማሪ ሴቶችን፤ የአማራ የቤት እመቤት ሴቶችን፤ የአማራ ሴት ጸሐፍትን፤ የአማራ ሴት የመንግሥት እና የግል ሰራተኞችን፤ የአማራ ሴት ጋዜጠኞችን፤ የአማራ ሴት አክቲቢስቶችን፤ የአማራ ጸሐፍትን፤ የአማራ ሚስትዬዎችን እንደማይጨምር እኛም አሳምረን እናውቃዋለን። እሳቸውም በደንብ ያውቃሉ ልባም ናቸውና። ሲፈልጉ ምራቁን የዋጠ መሪ ሲፈልጉ ደግሞ ግስላ በአማራ ነፍስ ላይ።

ሦስት ጣማራ ሰይፋቸው የአማራን እናት ለመቅጣት በማንኛውም ሁኔታ፤ በማንኛውም ጊዜ በተጠንቀቅ ያለ የተሰናዳም፤ ዝግጁ የሆነ እንደለ ትንቢት ሳይሆን ኢትዮጵያዊቷ መሬት እራሷ ትናገረዋለች። አዬን እኮ። ነፃ እርምጃ በአማራ ነፍስ ሲደረግ። የሥልጣን መለማመጃው አማራን በመግደል፤ እናቱን በማሰቀቅ እና በመርገጥ፤ ተስፋዋንም በመጨፈላለቅ ነው። ፈርኦናዊነት።

ከዚህም አልፎ የአማራ ጋዜጠኞች እዬተጠሩ „ሹት“ ትደረጋላችሁም አለበት። እንደ ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው፤ እንደ ኢትዮ ታይምስ ዘገባ ደግሞ ሞጋቹ ጋዜጠኛ አቶ ያዬህሰው ሽምልስም በኦነግ የታጨቀው የደህንነት ቢሮ እዬተከታተለው ስለመሆኑ ነፍሱን አስደምጧል።

ከዚህ ማህበረ ገዳይ፤ ደም የጠማው መንፈስ የአማራ ሴት የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ እኩልነት ልትጠብቅ? „ካለ አበደ በቀር ዱባ ቅል አያበቅልም“ ይላሉ ቅኔዎች ጎንደሬዎች፤ ይህም ብቻ አይደለም „ዱባ እና ቅል አበቃቀሉ ለዬቅል“ ይሉታል የተደሞ ቤተኞች መቼም የሰጣቸው ናቸውና። 
 
ታዬኝ እኮ እኔ ሥርጉተ ሥላሴ ለአማራ ሴት ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ሲያስቡ - ሲጨነቁ - ሲባትሉ - ሲተጉ? ይሄ በዬጊዜው ምክንያት እዬተፈለገ የሚረሸነው እኮ የአማራ እናት የወለደችው ነው። 

ይሄ የጥጋቡ ልክ መጠን አልፎ ቁንጣኑም አላስችል ሲል ለካቴና ተሰጥቶ በጨለማ ቤት የሚማቅቀው የአማራ የፖለቲካ ሊሂቅ አማራ እናት አለችው አቶ ክርስትያን ታደለ፤ አቶ በለጠ ካሳ፤ አቶ አስጠረ ከበደ እናት አላቸው እኮ።

ይህ ውሃ በቀጠን በያለበት በፈጠራ ወንጀል የሚከሰሰው የአማራ አክቲቢስት ከአማራ ሴት ማህጸን ነው የወጣው፤ ይህ „እንገድልሃለን“ እዬተባለ የሚዛትበት የአማራ ጋዜጠኛ የአማራን እናትን ጡት ጠብቶ ያደገ ነው፤ ይህ በዬሰከንዱ በዬደረሰበት ወከባ ላይ የሚገኜው የአማራ ነፍስ ከአማራ እናት እንቁላል የተገኜ ነው። ሁሉም አማራ እናት አለው።

እናቱ ደግሞ በፆታዋ ሴት ናት። ነገር ግን የአማራ ሴት በማንነቷ ስቃይ እና የሃዘን ድንኳን ተበረከተላት። መንፈሷ የዋይታ ቤት እንዲሆን ታወጀበት፤ ህሊናዋ የስጋት ምሾ አውራጅ እንዲሆን መለከት ተነፋለት። የሰራ አካላቷ ስጋት እንዲንጠው በዬሰከንዱ አቤቶ ፈርኦን በዬኑበት። እግዜር ይይለዎት።

የአማራ ልጅ እኮ እናት አለው። አማራ ከእንጨት፤ ከእሳር፤ አልተፈጠረም። አማራ የእግዚአብሄር ፍጡር ነው። አማራ የአላህ ፍጡር ነው። ስለሆነም የአማራ ልጅ እህት አለው። የአማራ ልጅ አክስት አለው። የአማራ ልጅ እሚታም አለው*። የአማራ ልጅ አያት አለው። የአማራ ልጅ ሚሰት አለው።

የአማራ ልጅ እጮኛ ፍቅረኛ አለው። ከሴት ያላተፈጠረ የአማራ ህዝብ የለም። ዘጠኝ ወር አርግዛ፤ ሦስት ዓመት አዝላ አጥብታ፤ ከልጅ እግርነት እሰከ ቁም ነገር የአማራ እናት ሁሉንም መከራ ተቀብላ ዘር ታበቅላለች። ዬዘመኑ ፈርኦን እዬተቀበለ ነባሩ ሲዶዱም እንደገና በአዲስ በሰላ ማጭድ ይታጨዳል እንጂ። ዘመን ይፍረደው።

እንሆ በዘመነ ፈርኦን በጨካኞች ዘመን የአማራ ሴት ያለርህራሄ ዘሯ - ሐርጓ በአረመኔነት ይታጨዳል እንደ ጤፍ አዝመራ። ነፍሷዋ በስጋት ተወጥሮ ይንገረገባል እንደ ሽንብራ። ሩኋዋ ይሾከሾካል እንደ ጠመጅ ቆሎ* መላ አካላቷ መፍተኛ ይሆናል እንደ ጥንቸል።

እግዚአብሄር ሆይ! እግዚአብሄር ሆይ! እግዚአብሄር ሆይ! ከቶ ከመንበር አለህን? ድንግል ሆይስ! ውጽፍተወርቅ ሆይ! አለሽን ከመንበርሽ? ምነው ምነው እንዲህ የአማራ እናት በዚህ ሰቆቃ ውስጥ ሆና እንዴት እረሳችሁት? ስለምንስ ቸል አላችኋት? እባክሽን ድንግልዬ ድረሽላት? እባክሽን?!

ድንግል ሆይ! አንቺ የልጅን ስደት ታውቂዋለሽ እና እባክሽን መፍትሄውን ላኪላት ለዛች መጠጊያ፣ መተንፈሻ ላጣች የአማራ ባተሌ። እባክሽን? እኔስ ዕንባዬ ደረቀ። እኔስ ሁለመናዬም ዛለ። የት ይኬድ? ምንስ ይኮን? መከራው ተችሎ የሥንኛት ልግጫው፤ የቃላት መስቃው፤ ዥንጉርጉሩ ጡሩ ነው የገደለን። ምን አለ ጥጋቡን በልክ ቢይዙት ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ? ቢያንስ በዚህ ይተባበሩን፤ እባክዎትን?! ልጣጭ የቃላት ዳንኪራዊው ተውኔቱ አገር ፈታ።

·       „ሴቶች በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ ከወንዶች የሚስተካከሉበትን
   መንገድ ለመፍጠር ብልጽግና አበክሮ ይሠራል“{ዶር አብይ አህመድ}

እም! እውነት እርስዎ ስለ አማራ ሴቶች ግድ ሊለዎት? ህም! ዕውነት እርስዎ ስለ አማራ ሴት ወጣቶች ግድ ሊሰጠዎት? እናምጥ! እርስዎ ስለ አማራ ትውልድ አጀንዳዎት ሊሆን? ዖዬ! እርስዎ ስለ አማራ ሴት ሙሁራን ግድ ሊሰጠዎት? ዎህ! 

እርስዎ ስለ ድሃ የአማራ ሴት ከመጤፍ ሊቆጥሩት? አሃ! እርስዎ አማራ ስለጸነሰችው ልጅ አደብ ሊኖረዎት? ኦ! ምናው ወይዘሮ ደስታ አስፋ የነብይ ብ/ ጄኒራል አሳምነው ጽጌ ዕንቡጥ በበቀል መጨንገፉን እረሱት - ሳ? በደል ይረሳል ወይንስ ይለመዳል? ይህ እኮ ቆረባ የሆነ ታሪከወት ነው። በዬቦታው በዬመስኩ ማንን ለኃላፊነት እንዲሚያስቀምጡ የሚጠፍንስ ይመስለዎታልን?

አሁንም እውነቱን ብናገር የኢንጂነር ስመኜው በቀለ ሁለት ወንድ ልጆች፤ የዶር አንባቸው መኮነን አንድ ቀንጣ ወንድ ልጅ፤ የነብይ ብ/ጄኒራል አሳምነው ጽጌ ወንድ ልጅ ወላጆቻቸው እንደምንም ብለው ውጪ ካላኳቸው እና እዛም ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ካልቻሉ የፈርኦን ሰይፍ ይምራቸዋል ተብሎ አይታሰብም። በፍጹም። ወላጆቻቸው ልብ ካላቸው ልጆቻቸውን አስቀድመው ቦታ ያስይዙ። ማህበረሰቡም ይተባበር። መንፈሱ ግራጫማ ነው አገራችን የተጫነባትበቀል ብቻ እኮ ነው የጠሚር ቢሮ ወንበር ሲቀፈቅፍ ውሎ የሚያድረው።  

አማራ ሴት እናት አላት፤ አማራ ወጣትም እናት አለው። አማራ ሙሁራን እናት አላቸው። አማራ ተማርያን እናት አለቻቸው። አማራ ጽንስ እናት አለው። እና የእርስዎ ጸረ አማራ የበቀል ዘመቻ እና የአማራ መንፈስ ታርቆ የአማራን እናት እንደ ሌላው እናት እኩል ሊዩ በፖለቲካም በኢኮኖሚም? „የማይሆን ነገር ለሚስትህ አትናገር“ ይላል ጎንደሬ። ሰማይ መሬት፤ መሬት ሰማይ ይሆናል የማለት ያህል ነው።

·       „ሰይጣን ወዳጅ አያጣም።“ {ከጎንደሬዎች ቅኔ}

እስኪ ህሊናዎት አማራም ሰው ነው፤ አማራም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነው፤ አማራም ሉላዊ ዜጋ ነው ብሎ ይቀበለው። ይህን አቡጊዳም፤ መልዕክተ የሖንስም ቀርቶበት ፊደል ይቁጠር በቀልን ብቻ የሚዘክረው - መንፈሰዎት። አይችሉም። መንፈሰዎት የተሸመነው በአቶ ገብረ ጃርት አቶ ተስፋዬ ገብረ- አብ ጭራቃዊ መንፈስ ነው። „ሰይጣን ወዳጅ አያጣም“ እንዲሉ።

የብዙ ሰው ከሰውነት፤ ከተፈጥሯዊነት ያወጣው ከንቱነት መጥፊያ መንገድ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ መንገደ - ደራጎን የተስፋዬዚም መንጦላይት መንፈስ ነው። የሁለታችሁም የቤተ - መንግሥት ጋብቻ ይኽው ነው።

እንዲህ አገር በአናቷ የተዘቀዘቀችውም በዚኸው አናክሪዝም ዶክተሪን ነው። ኢትዮጵያ ከአፍጋኒስታን እና ከኢራን ተርታ ከመሆን በላይ ለቤተ - ለደራጎን ተስፋዬ ማህበርተኛ ሰናይ የለም። ፌስታ¡እንደ አቀደው አደረገው። ኢትዮጵያ ፍርሰት ላይ ናት። ይህን ዛራም መንፈስ ያዘለ ሁሉ ጸረ ሰውነትን ነው የሚወርሰው። አረመኔነት ነው የሚጋባው። ፋሽስትነት ነው የሚዋህደው። ክህደት ነው ጌጡ።

·       ም እና በቀል አመድነት ነው።   

ዶር አብይ አህመድ እኔ እምለምነዎት፤ ሰማይ እና መሬትም የሚማጸነዎትም እባከዎት ዕውነት ለመሆን ይጣሩ። በውስጠወት ያላለቀ ቂም፤ ያልተቋጨ በቀል አለበወት። በህሊናዎት ውስጥ የበቀለውን የጥላቻ ዕጢ ወይንም ሃውልት ፈቅደው እራስዎት ያፍርሱት። ይህን የምለው መጨረሻወት እንደማያማር ስለሚሰማኝ ነው። ጤዛ መስለው ይታዩኛል። 

ክብረዎት ሳይታወቀወት ሙሽሽ እንደሚልም አስባለሁኝ። አሟማተዎት እጅግ የከፋ ይሆናል ብዬም አስባለሁኝ። ልብድነትን እንደ ማዕረግ ስለሚሞሽሩት።

ስለምን? ቀን እና ሌሊት ሴራ ነው ሲያመርቱ ውለውም የሚያድሩት። ምህንድስናው ሴራ እና በቀል የሚበቀልበትን ማሳ ሲያስስ ውሎ ያድራል። የሥነ - ልቦናም ችግር ያለበዎት ይመስለኛል። ንጉሥ ዳዊት ከምን እንደ ተነሳ ይሰቡት።

ከታች የተነሳ መንፈስ ከሴራ፤ ከደባ ቢጸዳ፤ ድንግልና መንፈሱ ቢሆን አብሶ አብሶ ለምንዱባን መድህን ይሆን ነበር የእኔም ጽኑ እምነት ያ ስለነበር ነው በእርስዎ ዙሪያ ያን ያህል የደከምኩት። ሁሉ ሰው ሲወለድ እራቁቱን ነው የሚወለድ። ሲያልፍም እንዲሁ ሰኔል እና ቹቻ ብቻ ነው የሚከተለው። እኛም ሁለችንም ከንቱወች ነን። ሲለቁን ሜዳ ሙሉ ሲይዙን ጭብጥ። ይሰቡት ሞትም እንዳለ።

ኤልሻዳይ አምላክ ንጉሥ ዳዊትን „እንደ ልቤ“ ያለው ዬልቡን ስለሆነለት ነው። ለዚህ ነው እሱም „እግዚአብሄርን አንድ ነገር ለመንኩት፤ እሱም ሁልጊዜ በቤተ - መቅደሱ፤ በቤቱ እኖር ዘንድ“ አለ።

ከዚህም አልፎ „የቤትህ ቅናት በላኝ“ አለ። የቤቱ ቅናት ምንድን ነው? እኔ እንደሚሰማኝ ቃለ - ስብከትን እውን ማድረግ ነው። ለቃል መታመን። መንፈሳዊ ሃብታትን ለመሆን መቻል ነው። እግዚአብሄር ለሰጠው ጸጋ ደም ማፍሰስ በርከቱን ያስነሳል። ምርቃትን ያሰርዛል። በስብከተዎት ውስጥ እርስዎ የሉሙ። ተነዋል ወይንም ሰርገዋል።

ጥሩ አንባቢ ስለሆኑም የንጉሥ ዳዊትን ምስባህኩን አጥንተውታል ብዬ አስብለሁኝ። ብዙ የንግግር ሥንኛት በሞድ ሲቀርቡም ስለ ማስተውል። ቤት የሚለውን „ጎጆ“ ሥልጣኔ የሚለውን „መዘመን“ እያደረጉ ተክተው እንደሚሸክኑት አውቃለሁኝ „ቃል ይተክላል ቃል ይነቅላልን“ ከዬት እንደ ወሰዱት አውቃለሁኝ።

„ብልጽግና እና መንኮራኩር“ ከማን መንፈስ እንደ ተቀዳም አውቃለሁኝ። ሰው ይሁኑ። የእግዚአብሄርን ሥጦታን እባከዎትን አያራክሱት። ንጹህ ህሊና እንዲኖሮዎት ሥራ አጥተው ውሃ ሲያጠጡ ከሚውሉ የጥሞና ጊዜ ይኑሩዎት - እባክዎትን። ወንበሩንም ይቀመጡበት። ወንበሩንም ያክብሩት - ያስከብሩት። አቅለሰለሱት። እግዚአብሄር የፈቀደለዎትን ጊዜ የበቀል ሱቅ በደረቴ ከሚከፍቱበት የሰው ልጅ የፈጣሪ // የአላህ ፍጡር ነው ብለው እኩል ይዩት። ቂም እና በደል አመድነት ነው።  

ምንም እንኳን መቼውንም በሚወስዱት የበቀል እርምጃ እረክተው ከአማራ እራስ ይወርዳሉ ተብሎ ባይታሰብም ግን እንደ አገር ልጅ ከማሳሰብ መቆጠብ አይገባም። አሻም ካሉ ግን የአማራ ህዝብ ቅንነት፤ የአማራ ህዝብ ወተት ደግነት፤ የአማራ ህዝብ ወገኑን በደነገለ ልቦና ወዳድነት፤ የአማራ ህዝብ ሰው ሳይጠረጥር ቸር አማኝነት አምላኩ ስለሚያውቅ ይፈረደዎትል - ቀኑን ጠብቆ።  

የአማራን ህዝብ በድለውታል። የአማራን ህዝብን ክደውታል። የአማራን ህዝብ ተበቅለውታል። ግን ምን አደረገዎት?!

አላግባብ የፈሰሰው የሰው ደም አይለቅም። ከዛ በፊት ግን ጊዜ ስላለዎት ወደ እራስዎት፤ ወደ ቀደመው ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ በነበረው የመንፈሰዎ ቁመና ልክ ይሁኑ። ይቅርታም ይጠይቁ። ሥርዬትን ይፈልጓት። አትሸሸዎትም። በዬፌርማታው ቃለዎትን በገዛ እጅዎት እባከዎት አይረዱት። ሰው ባይችል የበቀል አምላክ እንዳለም ይሰቡት። ይህ ሁሉ ይጠፋዎታል ብዬ አይደለም። ያውቁታል።

ማስትሹ ወይንም ለጭካኔዎት ቴራፒው የትናጋ ውሎ ፋይዳ ቢስ፤ የሜዳ ሸለሸል* ስለመሆኑ ለማጠዬቅ ነው። መንፈስን ለጅል ምርኮኝነት ለመዳረግ የሚያደርጉትን የሥንኛት ማግተልተል ምንም አያበቀልም። ማህንም ነው። ስለምን? ማሳ ስሌለው። የሰው ልጅ ለእውነት ነው የተፈጠረው። ዕውነት ይሁኑ።  

·       ጉራጅ ዘመን ለውችንፍር።

የዓለም የሰላም ተሸላሚ ዶር አብይ አህመድ በቂ እኮ ነው በሹመተዎት ዕለት ያደረጉት ንግግር። ሌላ ልጣጭ፤ ቁሮ፤ ዝልግልግ ዲስኩር አያስፈልገውም። በዬዕለቱ ያን መሳጭ ንግግር ያዳምጡት ደግመው ደጋግመው።

 ሚሊዮኖችን ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ከጎነዎት ያሰለፈለዎትን ልዩ ሰማያዊ ስጦታ እንደ ባለ እራሰ-በራነት ከሚሸሹት በተግባር ቢተረጉሙት ትፍስህት ይሆን ነበር ለትውልዱም ለእርስዎም ቀሪ ጊዜ። ማለፍ አይቀርም ያልፋሉ። ነፍሳችን ቋጥረን አልያዝናትም እና።

ከመንፈሰዎ ጋር ተወያይተው እራስዎትን ቢዳኙት ጊዜ አለዎት። እርስዎ እራስዎት እኮ በራስወት ውስጥ ሟሽሸዋል። አይታወቀዎትም ከሆን እኔ ላርዳዎት። ከቃለዎት ሳይደርሱ ተነዋል። ወደ ጂቢተር ይሁን ወደ ማርስ ተጉዘዋል።

ኢትዮጵያ ያሉ አይመስልም ዲስኩሩ። አያያዙም የሥልጣኑ ልክ ቀስ አድርገው ቢይዙት ነው የሚሻለው ይህን የአንባገነንነት ጉዞ። እሱንም አላወቁበት። ተዛነፍ ነው። ዘመን ምን አለው ብለው ነው? ማንንስ ቁሞ ሲጠበቅ። ያ እንዳለፈው ሁሉ ይህም ያልፋል። እኛም እናልፋለን - ሁላችንም።    

ዕውነት ብነግረዎት ዕውነትን አይፍሩት፤ ብስጭተዎት ኩርፊያዎትም ከአፍንጫዋ ላይ ስላለችም አይበሳጩ እንጂ ዕውነቱ የእርስዎ ዘመን ለአማራ እናት // ሴት መርገምት ነው። የእርስዎ ዘመን ለአማራ እናት// ሴት የገደል ዘመን ነው። የእርስዎ ዘመን ለአማራ እናት// ሴት ዘመነ ፍዳ የዳጥ የመቃብር ዘመን ነው

የእርስዎ ዘመን ለአማራ እናት // ሴት የምጥ ዘመኗ ነው። የእርስዎ ዘመን ለአማራ እናት የምጻዓት ዘመን ነው የእርስዎ ዘመን ለአማራ ሴት የወጀብ ዘመን ነው። የእርስዎ ዘመን ለአማራ እናት የአውሎ ዘመኗ ነው። ጭንቅ በገፍ የሚመረተብት። አሳር በቦንዳ የሚታደልበት። ጉራጅ ዘመን። ጎርማዴ!

የእርስዎ ዘመን ለአማራ ወጣት የመቀጠፍ ዘመን ነው - የውችንፍር። የእርስዎ ዘመን ለአማራ ነፍስ የመቀዘፍ ዘመን ነው። 

አብይዝም ለአማራ ሊሂቃን እንደ ጤፍ ነዶ በመደዳ በግፍ የታጨዱበት ዘመን ነው፤ እና ከእርሰዎ የአማራ እናት // ሴት ትፍስህት ልትጠብቅ? የአማራ እናት // የአማራ ሴት በውነቱ በአራስ ቤቷ አላበደችም።

ሲመለሱ ቀን ግን ያው እኔ በህይወት ካለሁኝ አውጃለሁኝ ዓዋጅ! ዓዋጅ! ያልሰማህ ስማ የደራጎን ተስፋዬ የአኖሌ ባይረስ ተሸካሚው መንፈስ ወደ ቀደመው የማስተዋል ቤቱ ተመለሰ ብዬ እናገራለሁኝ።

በእውነት በውስጥነት ስክን ሲሉ። አሁን ግን ወንበረዎት ማጂካዊ እብደት ላይ ነው ያለው። እርስዎን አይደለም፤ አልወጣኝም አራት እግሩን የአራት ኪሎ አጤነት ወንበር ነው ማጂካዊ ዕብደት ተጠናውቶታል የምለው። የኦሮሙማ ፓለቲካም ጎንድ ተክለሃይማኖት ሳያሰኘው ይቅር ይመስለዎታል፤ ወይንም መምህር ግርማን?  

·       አንድ አርት የጨለመበት።

„በህብር ወደ በልጽግና“ መሪ ቃልም ለከተማ አቀፍ ሴቶች አዲስ ማማለያ አድምጠናል። ያሻችሁ ፋና ላይ ገብቶ መታደም ነው። ያው ማዕቀፉ አንድ ነው። አንድ አርት የጨለመበት የጨለማ አርት ነው።

አዎን አማርኛ ቋንቋ ይመቻል። ለቅጥፈትም - ለቃለ አባይነትም - ለመደለዝም - ለማማለልም - ለመሆንም። ቋንቋ ተመቸኝ ብለው በቃ በዬጊዜው አዳዲስ ወርቃም ቃላት እዬፈጠሩ አገር ቀይህ ነው ተብሎ በተሰጠውም እንደ እንሰሳ ማገጃ በተከለለው ሳይቀር መቀመጫ ነሱት - አማራውን እርስዎ።

ይህ በጀርመንኛ ቋንቋ የሰራሁት አጭር ትረካ ነው። አንድ ጥበብ የጨለመበት ነው። የአማራ እናት ቢዚህ ውስጥ እንዳለች ይሰማኛል። ከእውነተኛ ታሪክ ተነስቶ የተጻፈ ነው። ወደ አጭር ፊልም ለመቀዬር ፍላጎቱ ነበረኝ።

0:03 / 4:17
EINE ARTE DUNKELHEIT 19.09.2017.


አማራ አገሩ ኢትዮጵያ ናት። ነገር ግን በዘመነ አብይዝም የአማራ ህዝብ መኖሪያ አጥቶ በሙሉ የመንግሥት የሎጅስቲከስ ድጋፍ እንዲህ በግፍ ይተረትሩታል፤ ያሳድዱታል። በበዛ መከራ መኖሩን አልፈቀደለት ብሎ መንፈሱ በፋስ ይወርዱበታል፤ ተስፋውን በመዶሻ ይወግሩታል፤ መኖሩን ቁም ተሰቀል እያሉ ፍዳውን ያበሉታል። የአማራ ልጅ መኖሪያ አጥቶ ሰርክ ህይወቱ - ቀራንዮ ሆነ። 

እንደ በግ፤ እንደ በሬ እንደ ዶሮ ይታረዳል፤ ይዘለዘላል፤ ሲያስፈልግም በቀስት ተወግቶ ህይወቱ ያልፋል። የአገዳደል ዓይነት መሞከሪያ ሆነ - አማራ። እግዚኦ! ነው ለዘመነ ናዚዝሙ አብይዝም። 

ጡት የተቆረጠችው ነፍስ በአርያም ገነት እንዴት ትታዘበዎት ስለ ሴቶች በፖለቲካ እና በኤኮኖሚ እኩልነት ንድፍ ተረት ስታዳምጥ? በድንጋይ ተወግራስ ያለፈችው አንስት እህትዎትስ? በቆርቆሮ ተገዝግዛ ያለፈችው ነፍስስ? ባለቤት የሌላቸው የታገቱ ስቃይ በዬቀኑ እየበሉ፤ መገፋት እዬጠጡ ያሉ መከረኛ ወጣት የአማራ ሴቶች መንፈስስ እንዴት ይታዘበዎት? ትዳራቸውን የተነጠቁትስ? መቼም ትዝብት ጌጥ ይሆናል ብለው አይሞግቱኝም። ህም!

እርስዎ ለአማራ ለሰከንድ ሊያዝኑ? ኮከብ ጸሀይ ይሆናል። ስለምን? የአቶ ተስፋዬ ገብረአብ ሲኦል መንፈስ ጠጥተው ስለአደጉ። አምልኮኛ ነወት። እንደ ሐዋርያም ነው የሚዩት ዲያቢሎስን። በጥምቀተ ጃርተ - ተሰፋዬ ገብረእባብ ነው አገር እንዲህ እየታመሰ ያለው። አማራም እንዲህ እዬተመነጠረ የሚገኜው። የሁሉም ጦስ መነሻው ያነ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ግን አልገባውም።

ለጥበብ ሰው እኮ አሉታዊ ልበ ወለድ ታሪክ አይደለም። የፕለይ ጸሐፊ ነኝ ስለሚሉን ዶር አብይ አህመድ። አሉታዊ ልበ ወለድም የህይወት መርኽ ለዛውም ኢትዮጵያን ያህል ገናና እና ውድ አገር የሚመራበት መርኽ ሊሆን አይገባም። 

ኢትዮጵያዊው ዜጋ አላወቀውም እንጂ የአቶ የተስፋዬ ገብረአብ አማሽ መንፈስ ነው አሁን አገር እያስተዳደረ ያለው።

ገራሚው ነገር ጸረ አቶ ተስፋዬ ገብረአብ የሆነው ነፍስ ሁሉ የአብይዝም ፕሮፖጋንዲስት ነው ዛሬ፤ የአብይዝም ደጅ ጠኝም ጉልቻ አድማቂም፤ ጠጅ አሳላፊም ምንጣፍ አንጣፊም ነው ዛሬ። „ብልጽግና እንዲያሸንፍ ነው ምርጫዬ“ ይልሃል ልዩዬ፣ አብነቴ ያልከው አባወራው ጦማሪ። እም! ያው የኦነጋውያኑ ዋና እንብርት ጉዳይ የሚታይ አቅምን ማምከን ነው። ከ100% በላይም አሳክተዋል።

·       ታወቅ በጭካኔ።

በአገራቸው መኖሪያ ያጡ ወገኖችን ዜግነታቸው ይከበር ሲል የኖቤል ሸላሚው ኮሜቴ አበክሮ ገልፆል። ኢትዮጵያ ያለው አስተዳደር አሁን አሁን ጭካኔውን አለም ያውቀዋል። አማራን መግፋቱን አለም ያውቀዋል። አማራን የዘር ማጽዳት ዘመቻ ላይ እንደተሆነም አለም ያውቀዋል።

ማናቸውም በአማራ ላይ የሚፈጸመው ዘር የማጥራት እርምጃ በመንግሥት ስለመሆኑ፤ ዶር አብይ አህመድም የኦፕሬሽን መሪ ተዋናይ መሆነዎት ይታወቃል። ኃላፊነትን ቢሸሹትም ከአንዱ ግድፈት ወደ ሌላው በሚደረገው እንደ ፌንጣ ዝላይ እራሱ ድርጊቱ ገላጭ ነው።

ልብ ያልገዙ የኦሮሞ ወጣቶች በጭካኔ ውስጥ እንዲያድጉ መደረጉ አልበቃ ብሎ የእርስዎን አጥፊ ፍላጎት አስፈጻሚ እንዲሆኑ መሆንም ይረዳል ሰው ነኝ ያለ ሁሉ። የሚሹትን ጉዳይ የወጣት አጥፊ ቡድን አደራጅተው በዛ ያስፈጽማሉ።

እንዲነገርለዎት የሚፈልጉትንም እንዲሁ በአጩት መንፈስ ይከወናል። ግን ስንት ነውት? ምን ያህል ነዎት? የዚህ ትወና ቅርጽ - ይዘት - አቋቋም - ቅንጅት ሰውር ደባ ሲደመር ኢትዮጰያ ፈርሳ ኦሮምያ አህጉርን መፍጠር ነው።

በሌላ በኩል በሽምቅ የኦነግ ተዋጊ ሎጅስቲክሱን በሚገባ አሟልተው፤ ኔቱን ዘርገተው የሚፈልጉትን አማራን ማስመንጠር ሲያሰኝዎትም በዛም ያስከውናሉ። አጣዬ ማጄቴን ማዬት ነው።

ሲያሻዋት የመንፈቀ ሌሊት ሹመተወትን ዓመት ድገመኝ መሳለሚያ ለማድረግ አስፈልጎወት ፋቲክ ልብሰው የባህርዳርን የደም አላባውን እንደ መልካም ዜና ያበሥራሉ። ግን ስንት ነዎት?! በዙብኝ አለ የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ኤርምያስ ለገሰ። ቅኔ ነው የዘረፈው። ለጭካኔ መባዛት? ለሴራ መባዛት? ለሸፍጥ መብዛት? እራስዎን ዲፕሊከት እያደረጉ እያባዙ እንዲህ ከሚቸገሩ እራሰወትን አብይን ይሁኑ።

አንድ አብይ ንጽህና ካለው ይበቃናል። እኛ የጭካኔ ኪኖ አልናፈቀነም እና። የሚገርመው ከኪኖው ቀጥሎ የሚመጣው መዳጫ ነው። ለኪኖችወት ቀዳሚው የቃለ ምህዳን ክኒን ነው፤ ለቃለ ምህዳኑ ደግሞ የህልፈት ኪኖ።  
 
የአብይዝም ራዲዮ፤ የአብይዝም የቴሌቪዥን ሚዲያወቾት ቀን እና ሌሊት ደግሞ የአማራ ሥነ - ልቦና በመተርትር፤ በመሰንጠቅ፤ በመሰለቅ፤ በማበዘት፤ በማድቀቅ፤ በመፍጨት፤ በመደቆስ፤ ተጠምደው ውሎለው ያድራሉ። 

ለአማራው በራሱ ውስጥ እንደ አሸን ደመኛ ጠላት በማፍራት በሙሉ ድጋፍ በቀዬው የሚፈልጉትን የአማራ እርድ እንዲከውን ሲያስደርጉ ማህበርተኞቾወትንም ያዝናናሉ ቲያትር ቤት የቲያትር ቤቱ ሥያሜን „የመቃብር ሥፍራ ቲያትር ቤት“ ቢባልለዎትስ ይከፋዎታልን? ያስማማል አይደል? የቀደሙ የአማራ ጠላቶቹ ጋርም ለዋንጫችን በቤተ - መንግሥት መኖሩን እሚጠፋን አይምሰለዎት። 

ግን ለእርስዎ ይህ ሁሉ አይጠቅመወትም። ለሚያልፍ ቀን የማያልፍ ዕለታዊ መከራ በአንድ ህዝብ ላይ ይህን ያህል ማዕት ማውረድ - ፍርሰት ነው። እራስወት እዬተናዱ ነው።
 
እርስዎ ከኢትዮጵያ ህዝብ የተለዩ ስለሆነ ማለቴ ‚ዬሾርት ሚሞሬ‘ ጥቃት ስለማይኖርበዎት ከሌላ ፕላኔት ስለመጡ፤ የ50በ60 ያረጠ ፖለቲካም አራማጅ ስለሆኑ፤ ልቅናው ስላለ ያስታውሱ እንደሆን በ2017 የሆዴን አጫውቼዎት ነበር የነገርኩዎት።

እኔ እንዲህ ስውሩ ሲኦል ሰብዕና ያለዎት መሆነዎትን መቼ አውቄ? የጎንደር ልጅ ስለምን ለግለግ ብሎ ሊወጣ እንዳልቻለ አደብ ያለው ጹሑፍ ጽፌ ነበር። ያነቡታል ብዬም አስባለሁኝ። ያን ጊዜ የውዳሴ ፍርፋፊ የሚጽፍ ነፍስ እንብዛም ነበር እና። በድህነት ጊዜዎት ማለት ነው።

የጎንደር ልጅ ያን ሁሉ የመከራ ጊዜ አሳልፎ ከሰው ተራ የደረሰውን፤ ለእርስዎ እንዲህ መዘባነን የበኩሉን ድርሻ በቀዳሚነት የተወጡትን ለዶር አንባቸው መኮነን እንኳን አልሳሱላቸውም? ለዛ ቀንበጥ ለትንታጉ ለአቶ ምግባሩ ከበደስ? ወይንስ በርሃ ለበርሃ ሲንከራተቱ ለባጁት ለኢንጂነር ስመኘው በቀለ? እስኪ ላስታውሰዎት እነሱም እናት ነበራቸው።

የተወለዱት ከሴት ማህጸን ነው። ለነገሩ አብረው ተሸኝተዋል። እግዚአብሄር ይቅር ይበለዎት አይባል ነገር። የአቶ ተስፋዬ ጌታቸውም ቀድሞ የተከወነ ነው። መንገድ መጥሪጌያ ሴራ - ማለማመጃ። በጥዋቱ እኔ ጽፌበታለሁኝ።

ይህ ሁሉ ዬዩንቨርስቲ ተማሪ ሲፈናቀል፣ የአማራ ነገ አያለቅስም ይመስለወታልን? በረጅሙ አስበው እኮ ነው እያነደዱት ያሉት የአማራን የትውልድ ተስፋ። ባለፈው ዓመት መፈናቀል ከ40 ሺሕ በላይ ተማሪዎች የአንድ ዓመት የትምህርት ክ/ጊዜ ሲቃጠል ምን ይላሉ?

የዘንድሮን ባጀትስ አይተውታልን? አማራ ስንተኛ ደረጃ ነው? በተራድኦ የተገኜው አውቶመቢል እንዴት ተደለደለ? ስለ ሴቶች የሚጨነቁት መሪ ይንገሩን እስኪ? የበጀቱ ድልድል የአማራ እናትንም ኑሮ ይወስነዋል። የልበዎትን ይሰራሉ በዚህ ደግሞ መጥተው የህዝብ ተጨናቂ መስለው ይቀርባሉ። ልግጫ!

አማራን በሚመለከት ልበዎት አሸዋ ነው። ህሊናወትም ኮረኮንች። አንጎሎዎትም ጥምዝምዝ ጥምንም ነው። መንገደዎትም ለዛዛ ነው። እርስዎ ኢትዮጵያን ከወገብ በላይ እና በታች አድርገው ነው የሚዩይት። እንደ አማራ ህዝብ ነፍሰዎት የሚጸዬፈው አንዳችም ነገር የለም። አይወዱንም። ይጠሉናል። 

እኛ ለእርስዎ የገበረነውን ደግሞ ፈጠሪ ነው የሚያውቀው። ግርባው ብአዴን በአማራ ሥም የተጎለተ ማህበረ - አርዮስ ነው። እሱ በሰጠው ድምጽ ነው ይህን ያህል ምጽዕት በአማራ ህዝብ ላይ እዬተደመጠ ያለው።

·       ስከኛው ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ።

አማራን ይገድላሉ፤ አማራን ይሰውራሉ፤ አማራን ከትምህርት ያፈናቅላሉ፤ አማራን ያስራሉ፤ አማራን ከሥልጣን ይነቅላሉ፤ አማራን በቤተሰቡም በስውር ሴራ ይቀጣሉ እናትን ፈልገው ነው የሚቀጡት። እርስዎ ማለት እንዲህ ነዎት። የአማራ ህዝብ እናት አለው። እናቱ ሴት ናት። የአማራ ሴት በእርስዎ ዘመን የተቀጠቀጠችበት ዘመን ነው። ተልዕኮዎትም ይህው ነው። ጥሪዎትም ይህው ነው። ክፍል ሥመዎት ለእኔ ፈርኦን ነው። ለአማራ ፈርኦን ነዎት።

ከላይ ባነሳሁዋቸው ነጥቦች ዕውቀተዎትን ቢጠቀምቡት በሰውኛ በተፈጥሮኛ ዘዬ በቂ ነው። አብይዝምን መስሏቸው የሚደግፉ ብዙ የአማራ ሊሂቃን አሉ። ነገር ግን ግርዶሽ ተሰርቷል። ማክሰዎትን ለብሰው በቃላት ያንሸራሽሯቸዋል። በዚህ ስለ ፍቅር ይሰበካል መሬት ላይ ጥላቻ ነግሶ የአማራን ትውልድ ይወቃል።

የአቶ ተስፋዬ ገብረአብ አጥፊ ፍልስፍና በይፋ በአደባባይ ይከወናል። መግለጫ አውጡ የተባሉት ተፈቅዶላቸው ስለመሆኑ ይገባናል። ስለምን በእነሱ መሰላል አማራን መጋለብ ስለሚፈለግ። ነገ ተዋህደናል እናዳምጣለን ለእነ ማህበረ - አሻጋሪዎቻችን። ያው ጋብቻው ጸረ አማራነት ነው። 

„ዘረኝነትን መከፋፋልን ከሀገራችን እንጥፋ፤
የተማረና በምክንያት የሚከራከር ዜጋ እንፍጠር“
ተረብ በዓይነት የጠሚር ስብከት።

„ለማያውቅሽ ታጠኝ“ ይላል የጎንደር ሰው። አዲስ አባባ ላይ ዴሞግራፊው ለማን ነው? ለአማራ እኮ ነው። ይህ ያልገባው፤ ህሊናው የተሰረቀ ጄሌውን አማራ በመደዳ ታጠፊ አልጋ ዘርግተው ለሽ ያድርጉት።

እኔን በግል ግን አይችሉም። ስለ ሥርዓተዎት ስጽፍ „የመቃብር ሥፍራ“ እያልኩ ነው። ደግሞም ይገልጸዋታል። በቀደመው ጊዜ ያስታውሳሉ „ብሄራዊ ቀኔ“ ነበር ምስክርነቴ። ግን አሳረሩት፤ ከእሳት የገባ ፕላስቲክ አስደረጉት ጭካኔዎት ኩፍትርትር አደረገው ተስፋዬን። በራስዎት ጊዜ በራሳዎት ፈቃድ ቅምጡ ፍላጎቶዎት እንሚራዎት አጤ አደረጉት። አሪዎሳዊነት ነው አርማዬ አሉ!

እያንዳንዷ የነገረ አማራ እንቅስቃሴ መቀስ ይሰናዳለታል። እያንዳንዱ የአማራ ትንፋሽን እራስዎት ገብተው ይበጠብጡታል፤ ያውከዎታል። እያንዳንዱ የአማራ ተቋማዊ አቅም አቅለዎትን ይነስተወታል። አቅመ ቢስ ስለሆኑ። የአማራን የህሊና አቅም የሚመክት ሰብዕና የለውትማ። ያለው አይሸሸውም። ማህበረ ድውያን።

እያንዳንዱ የአማራ ልቅና መንፈስ ያቅለሸልሸዎታል። እያንዳንዱ የአማራ ብጡል ጸጋ ቃር ይሆንበዎታል። የአማራ መንፈስ ልዕልና እና አደብ በቅናት ውስጠዎትን ያነደዋል። ያጨሰዋል።

 ሰብሰበው እጅ ሲያወጣ ከግንባር የተለጠፈ ነገር ስለማይኖር ቃናውን መርምረው አማራዊ ከሆነ ቱግ ይላሉ። ይጦፋሉ፤ ትእግስት ያጣሉ። ቀን ጠበቀው ለካቴና ወይንም ለባሩድ ይሸልማሉ። ሰማዕትነት የተቀበሉት በሙሉ ለሚጠይቁት ጥያቄ ተገቢውን መልስ በድፈርት የሰጡ ስለመሆኑ እርስዎም ያውቁታል - እኔም አንቀርቅቤ አውቀዋለሁኝ። እርስዎን ቀርቦ የተረፈ ልቅና ያለው የ አማራ ሊሂቅ የለም። ቢኖርም ተራው እስኪደርስ ነው።

ገድለውም፤ አስረውም፤ በዬፌርማታው አማራ እንዲሰቃይ አውጀውም አማራን በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ እንዲወገዝ ፈለጉ እና አቶ ኸርማን ኮኽንን አሰለፈውም። አሳጥተውም አይረኩም። በእያንዳንዱ የእርስዎ የዲፕሎማሲ ዝግ ጉዞ ሆነ ለአማካሪዎቸዎት ተቋም የሚከፍቱት ስለ አማራ አሉታዊ ትርክት በማስጠናት ነው። ይህ መደበኛ ሥራዎት ነው። 

አፈጠው ሲይዙዎት እጅ መንሻ ይዘው ባልታሰብ ጉዞ ዱቅ ይላሉ። እስራኤል ያደረጉት ይህንን ነው። ኤርትራውያን ወደ አገር በመመለስ እኔ አመቻቻለሁ አይደል ያሉት። ይህ የሚጠፋን ይመስለዎታልን? የዲፕሎማሲ ጉዞው እኮ የተከረቸመ ነው።

የተመሰጠረው ስለምን ይሆን? በዚህ ያሰጡታል አማራን፤ በዚህ ደግሞ አቅም ከአማራ ይሻሉ። አርንዛነት ያውቃሉ ብዬ አስባለሁኝ። ይሰቡት። ውርዘትንም ይረዳሉ ብዬ አስባለሁኝ። ይሰቡት። አለቅት የሚባልም ነገርም ያውቃሉ ብዬ አስባለሁ። ይህንንም ይሰቡት። ቆረባ የሚባል ነገርም አለ። ይህን ይሰቡት። ደራጎን የሚባል ደግሞ አውሬ አለ። ይህንንም ይሰቡት።

የግፉ ዓይነት እና ሞድ Extravagant ነው። ለሚሰማውም፤ ለሚያውም፤ ለሚታዘበውም በመንግሥት አቅም እና ይሁንታ፤ በመንግሥት ሎጅስቲክስ እና የውስጥ ውሳኔ የአማራ እናት አልቅሳ  - አልቅሳ - አልቅሳ፤ ተሰፋ አጥታ ዘመኗ እንዲያልፍ ነው ቅጣተወት። አዋሳ ጉባኤ ላይ አይምሰላችሁ „የአቤል ዕንባ ይጮኃል“ ብለውን ነበር። አዎን ይጮሓል!

አፋር ስብሰባ ላይም ደርግ የወደቀው “ ህዝብ ስለጨፈጨፈ ነው“ ብለው እኔ „ርትህ“ በሚል በሰባት ምዕራፍ የጉዞወትን ሂደት አዎንታዊ ጹሑፍ በሞገትኩዎትም ላይ አይደለም ሌላ አምክንዮ አለ ብዬ ነበር።

አሁን እውነተዎትን ነው። እስዎም መወደቅ አለበዎት ብዬ አስባለሁኝ። ጠረነዎ ሰውኛ ሳይሆን የጨለማው ስለሆነ። ትናጋዎት የሰው ህሊናን ግራጫማ ለማድረግ ነው። ሰውኛ ጠረን ድሮ ቀረ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ላይ ሳሉ። ያን ጊዜም ድብቅ ማንነተዎት በምደባ በሥልጠና ላይ ሊኖር ይችል ይሆናል። በቃ። ለሥልጣን ሲባል መስቀልም ይረገጣል፤ መስቀለም ይጠቀጠቃል። 

ዛሬ ዛሬ ሳዬው ምስለዎትን አብዝቼ እፈራዋለሁኝ። አብሮ የተመገበ፤ አብሮ የተነጋገረ፤ አብሮ የሠራ ሁሉ ተራውን ጠባቂ ነው። በተለይ አማራ ከሆነ። የቅርብ ሰው አንድ ብቻ ቀርተዋል ከአማራ ነፍስ። እንደ ፕሮቶኮል ሹም የሚያደርገው። የማህበራዊ ኑሮ አማካሪ ነው ሲሉ የሰማሁ መስሎኛል። እሰከ መቼ መኖር እንደ ተፈቀደለት አይታወቅም። የአንድ ቀን ነው።

ውሸት ወረተኛ ስለሆነ በግቢ ላይ ነው። ዕውነት ዓይን አፋር ስለሆነ አንገተ ደፋታ ነው በጓዳ ነው። ለሌላ ለማንምስ ሳይሆን ለልጆቸዎት ሲሉ ዕውነት ይሁን። አማራ ሴት ግን ከእርስዎ የተስፋ ስንጣሪ መጠበቅ አይኖርባትም። በፍጹም። ክፉ ሰው ነዎት።

 የአማራ እናቶች እኔ አገር ቤት ባልሄድም የሄዱ ሰዎች ሲነገሩኝ ጠፉ በታባሉ ሃምሌተነሃሴ ሰሞን መሬት ተደፍቶባቸው፤ መሬት ላይ እዬተኙ ሲያልቅሱለዎት ነበር ልጅ አግኝተው ሙተው። ተገኙ ሲባሉም ደግሞ ሻማ አብርተው አምላካቸውን አመስግነዋል። እርስዎ ግን በጥርስ የያዙት ማህበረሰብ አማራን ነው። የሚናፈቀኝ የእርስዎ ዘመን ክትመትን ማዬት ነው።

ጸረ አማራ የሆነው ሁሉ በመንፈስ ማህበር ተደራጅቶ እርስዎ እንዲቀጥሉ ብልጽግና ሲል አዳምጠዋለሁ። „በሰው ቁስል እንጨት ቢሰድቡት“ ስለሆነ። ሌላው ራሱን የከዳው ደግሞ ያው የፍርፋሪ ነገር ስላለ እሱም ይመኛል የቤተ - መንግሥቱ ቅልቅል እንዳይቀር። በማን የኑሮ መርገምት? 

በአማራ እናት ዕንባ ይቀለዳል፤ ይዳነሳል፤ ይጨፈራል፤ ለዋንጫችን ይባላል።
ብልጽግና ለማበልጸግ ሲሉ ከአማራ በስተቀር ይበሉት እና ዕውነት መሆነዎትን ያስመስክሩ። ለነገሩ አሁን በውጭም በአገር ውስጥም ያለው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ጸረ - አማራ መሆነወት አውቆታል ብዬ አስባለሁኝ። የእርስዎ ጥሪ የአማራን ዘር ማጥፋት ሰለመሆኑ።  

የአማራ ህዝብን በአገኙት ሁሉ መቅጣት - መቀጥቀጥ - መቀጣጫ ማድረግ ጥሪዎት ነው። ንጹህ ዲስክርምኔሽን ነው ያለው። ንጹህም አፓርታይድ። ይህን ያህል ከአቶ እስክንድር ጋር ግብግብ የገጠሙት ሌላ እኮ አይደለም አማራ ስለሆነ ብቻ ነው። 

ከ100ሚሊዮን ህዝብ ነገር እስክንድር ዓይነዎትን ያንፈረፍረዋል። ዓይነ - ጠበብ!
ሊለቀስለዎት ይገባል። ለእኔ ሙተዋል። ሰውን ሰው ጠልቶ ከተነሳ ሙት ነው። ሙትነቱ በመንፈስም በኣካልም ነው። 

አማራ ታግሎ ባመጣው ለውጥ ይህ ሁሉ ክብር ተግኝቶ ትናንትም እስር ዛሬም እስር፤ ትናንትም እንግልት ዛሬም እንግልት፤ ትናንትም መፈናቀል ዛሬም መፈናቀል። በቀንም በሌትም ሞት።

18 ወራት ሙሉ አማራ ይሞታል። የአማራ እናት እሬሳ ትረከባላች። 18 ወራት በሙሉ መርዶ። ምን ትጸና የአማራ እናት // ምን ትበረታ የአማራ ሴት? ምን ብረት ትሆን የአማራ እናት // ምን ትችል የአማራ ሴት? ምን ትጠንክር የአማራ እናት // የአማራ ሴት የመከራው ሁለ መፈተኛ ሆነች? እግዚአብሄር ይይለዎት።

„ሴቶች በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ ከወንዶች የሚስተካከሉበትን መንገድ ለመፍጠር ብልጽግና አበክሮ ይሠራል“{ዶር አብይ አህመድ} ይህን ቅርፊት ፍልስፍና እዛው የጨረቃ ቤት ብልጽግናዎት በፍሬም አሰርተው በክብር ያስቀምጡት። ለማውጫ እንኳን አይሆንም። የእርስዎን ቃለ ምህዳን አንስቶ ለሪፈረንስ የሚጠቀም ነፍስ አያገኙም። ገለማን!

ይልቅ በማን አለብኝነት ለአማራ እናት የነጠቋትን ሰላም ይስጧት። የቀሟትን መኖር አይንፈጓት። ያወጁላትን ቅብረት ያንሱላት፤ የሚያፈሱትን የማያበራ የመቀጣጫ ጭካኔ ያስታግሱላት፤ የሚያደርጉትን ይፋዊ ጭቆና እና ግለት ይቆጡቡላት፤ ከተስፋዋ እርእስት ተነቅላለች የአማራ እናት በዘመነ ፈርኦን።

·       ጣዩ የፈርኦን ህልም።

ቀጣዩ የፈርኦን ህልም የአማራ አመጽ እንዲቀጣጠል ማስደረግ በስፋት ቀውስ በማደራጀት። በዛ አመጽ አማራን አደባባይ መረሸን። የተረፈወን ለካቴና መስጠት።  እስር ቤት ታይቶ የማይታወቅ ስቃይ አደራጅቶ መቅጣት። መቀጥቀጥ። ለዚህ ነው አሁን ብትብብር እገዳ የተካሄደው። አማራ አምፆ ተጨማሪ ግድያ መጣል ይሻል ፈርኦን። ለዚህ ነው እኔ ዘመነ የመቃብር ሥፍራ የምለው።

·       ዲስ ድምጽ ሚዲያ ይቅርታ ስለመጠዬቅ። እንደ መከወኛ።

ባልደራስ ለኢትዮጵያ እንደ አባት አደሩ ሰንበት ቅኔ ዘረፈለት በሚለው ጹሑፌ ላይ ሚዲያዎችን ስዘረዘር አባወራውን፤ የሚዲያ መሠረቱን፤ ዋርካውን፤ የውሃ ልክ ልበለው አዲስ ድምጽን መዘንጋቴን አሰተዋልኩት። ብሎጌ ላይ በፍጥነት አስተካክዬዋለሁኝ ለዘሃበሻ ቀድሜ ስለሆነ እምልከው፤ ቀንበጥ ብሎጌ ስለጥፈው ግድፈቴን አገኜሁት።
ለዘሃበሻ ከላኩ በኋላ ስለሆነ ፖስት ያደረግኩት። 

ስለሆነም በትህትና ጋዜጠኛ አቶ አበበ በለውን ይቅርታ እጠይቃለሁኝ። የእሱን ስቴዬድዬም ማዕዶት ያላደረገ የፖለቲካ ድርጅት እኔ አላውቅም። ለባልደራስም የተገባውን ክብር እንደ ሰጠ ስለ አዳመጥኩኝ፤ በቀደመው አማራጭ ሚዲያን ስዘረዝር በአንድ የወግ ገበታዬ ላይ ጽፌው በዚህኛው የወግ ገበታዬ ግን ስለዘነጋሁት በድጋሚ በድጋሚ ይቅርታ እጠይቃለሁኝ ለአድናቂዎቹም፤ ለታዳሚዎቹም በሙሉ።

ዝርዝራቸውን እምጽፈው ደግሞ እምከታተላቸውን ብቻ ስለሆነ ያልተከታተልኳቸውም ባልደራስ ለኢትዮጵያን እርድተውት ከሆነም ምስጋና ይገባቸዋል። ይህ ያንሰናል። በሚያንሰን ላይ ማተኮር ይገባ ይመስለኛል። እንኳንስ የጎላው ቅንጣቱ እገዛ እራሱ ያፋራል ዕውቅና ስንሰጠው። የሚዲያ ሥራ ከባድ ነው። ብዙ ያደክማል። ስለዚህ መመስገንም መከበርም አለባቸው መርኽን ዕውነትን የወገኑት።

·       ፍቻ። ኮከብ ምልክት አድርጌባቸዋለሁኝ።

 ሸለሸል … ሸለሸል ማለት ከብቶች እበታቸው ካልሆነ ቦታ ጥለወት ዝናብም፤ ውርጭም፤ ጸሐይም ሲቀጠቅጠው ባጅቶ ተፈጥሮው ጠፍቶ ህልፈቱን የሚያውጅ የኩበት ዓይነት ነው። ሥርዓት ያለው የከብቶች እበት ግን በወግ ተጠፍጠፎ ለማገዶ ይውላል፤ ቤት ይለቀለቅበታል፤ አውድማም ይለቀለቅበታል። ከዚህም ባለፈ እንደ ማዳበሪያም ያገለግላል። እዚህ ለማዳበሪያ በሥፋት ነው የሚጠቀሙበት።

እሚታ … በማህል አገር እሚታ አይታወቅም አያት ነው የሚሉት። በጎንደር ግን እሚታ ማለት  የአባት እና የእናት ወላጆች ማለት ነው። አያት የእናት እና የአባት ወላጆች ወላጆች ናቸው። ሦስተኛ ደረጃ ማለት ነው።

ጠመጅ  … ጠመጅ ጎንደር ብቻ የሚገኝ ይመስለኛል። በተለይ ወገራ እና ስሜን ብቻ የሚመረት ከእሳር ዘር የሚመደብ የገብስ አይነት ነው። ለቆሎ ነው አብዛኛውን ጊዜ የሚጠቅመው። ከዚህም በተጨማሪ ሰነፍ የሚባል አለ። ሲቆላ እንደ ገብስብ እንደ በልጋም፤ እንደ ጠመጅም መሾክሾክ የማያስፈልገው። ለዚህም ነው ሰነፍ የሚባለው።

ትዕግሥት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል።
„አማራነት ይከበር!“
አማራን መንቀል አማራነትን አፋፍቶ ያስነጋል!
የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ በጽናት ይቀጥላል!
የኔዎቹ ኑሩልኝ እንደ ዋርካም ስፉልኝ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።